በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)fenote1971@gmail.com
ከሀዲው የትህነግ ቡድን ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በሰሜን ዕዝ ላይ የፈጸመውን ክህደት። ጭፍጨፋና የጦር መሰሪያ ዘረፋ ያለሀፍረት በቴሌቪዥን ቀርቦ” መብረቃዊ “ ያለውን ታሪክና ትውልድ ይቅር የማይለውን አሳፋሪ ክህደት በመፈጸሙ መንግስት ተገዶ ሕግን የማስከበርና የሕልውና ዘመቻ ውስጥ መግባቱን ስሰማ እውነቱን ለመናገር ይህ ከሃዲ ቡድን ለዚህ ጦርነት ለዓመታት ዝግጅት ማድረጉን፤ ለዚህ እንዲረዳው እንደ መከላከያና ብሔራዊ ደህንነት ያሉ ተቋማትን ማሻጠሩን ፤ በኋላ ላይ ደግሞ ከሀገሪቱ ከግማሽ በላይ የሆነውን የሰሜን ዕዝ መጨፍጨፉን ስሰመና ሀገሪቱ አሉኝ የምትላቸውን ዘመናዊና ከባድ የጦር መሳሪያዎችን በእጁ እንዳስገባ ስረዳ ዘመቻው ብዙ ዋጋ ሊያስከፈለን እና የተራዘመ ሊሆን ይችላል የሚል ብርቱ ስጋትና ፍርሀት ነበረኝ ።
ክቡር ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ይህ ቀን እንዳይመጣ ፤ ጦርነት እንዳይቀሰቀስ እሳቸውም ሆኑ ፓርቲያቸው ውደ ዋጋ የከፈሉበት ልፋትና ትዕግስት መና መቅረቱ በእጅጉ ሰላሳዘነኝ ምነው መንግስት ቀድሞ የሕግ ማስከበር ስራውን በሰራ ኖሮ የሚል ቁጭት ሁሉ ፈጥሮብኝ ነበር። የአብዛኛው ኢትዮጵያዊ ስሜትም ከዚህ የተለየ አልነበረም።
በነገራችን ላይ ይህን አሳዛኝ ዜና የሰማሁት በኮቪድ 19 ተጠቅቼ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ተኝቼ እያለ ስለነበር የማልተረጉመውና የማልረደው ጭንቀትና ትኩረት ማጣት ገጥሞኝ ነበር ።
እንደምንም ብዬ ወደ ራሴ ስመለስ ዘመቻው የመረጃ ጦርነትም ስለሆነ የዜግነት ድርሻዬን ለመወጣት በመደበኛውም በማህበራዊ ሚዲያው ዘመቻውን ተቀላቀልሁ ። ህክምና ላይ በነበርሁባቸው 38 ቀናት አንድም ቀን ሳላስተጓጉል የትህነግ ቡድንን ጭፍራ የፈጠራ ወሬ ለማርከስ አቅሜ የፈቀደውን በማድረጌ በሰሜን ዕዝና በማይካድራ የተፈጸመው ጭፍጨፋ ከፈጠረብኝ ሀዘን ተፅናንቻለሁ ።
ይሁንና መንግስትና የኢትዮጵያ ሕዝብ ተገደው የገቡበትን ጦርነት በክቡር ጠቅላይ ሚንስትር በሳልና አስደማሚ አመራር ፤ በየደረጃው ባሉ ወታደራዊና ሲቭላዊ አመራሮች ፤ በሰራዊቱ ጀግንነት ። ብቃትና ዲሲፕሊን እና በመላው ኢትዮጵያውያን አኩሪ ደጀንነት የሕግ ማስከበርና የህልውና ዘመቻው በሁለት ሳምንት ለዛውም ሰላማዊ ሰው ሳይጎዳ ። መሰረተ ልማቶች ሳይወድሙ እና ከተሞች እንደ እነ አሌፓ። ሲርት ። ሞቃዲሽ ። ትሪፓሊ ። ሰንዓ።
ወዘተረፈ ወደ ፍርስራሸነት ሳይቀየሩ መጠናቀቁ ዛሬ ድረስ በአግራሞትና በአድናቆት እጅን በአፍ እንዳስጫነ ነው። ከግማሽ በላይ የሚሆነው ሰራዊት ተጠቅቶበት። የሰራዊቱ ሞራል በክህደት በተጎዳበት ለ20 ዓመታት በቀበሮ ጉድጓድ ሆኖ ትግራይን ሲጠብቅ የነበረ ጓዱ በትህነግ ከሀዲዎች በግፍ መስዋዕት ሆኖ ፤ ተጨፍጭፎ እና የጦር መሳሪያው ተዘርፎ በአጭር ጊዜ ውስጥ ራሱን መልሶ በማደራጀትና በኢትዮጵያዊ ወኔና ጀግንነት በእግሩ ከ700 ኪሎ ሜትር በላይ ተራራ ቧጦ ቁልቁለት ወርዶ በየደረሰበት ከደርዘን በላይ ከባባድ ጦርነቶችን አካሂዶ አንድ ሰላማዊ ሰው ሳይጎዳ መቐሌን መቆጣጠሩ የአንድ ረጅም ልቦለድ ወይም ፊልም አጭር ታረክ ( ሲኖፕሲስ ) ወይም ፊልም ቅምሻ (ትሪለር ) እንጂ በገሀዱ ዓለም ለዛውም በኢትዮጵያ ተፈጽሟል ብሎ ለመቀበል ይከብድ ይሆናል። ቢከብድም ይህ እውነት በምስራቅ አፍሪካዋ
የአናብስት ሀገር እውን ሆኗል። ከሀገር በተዘረፈ ሀብት እስካፍንጫው ከታጠቀ ፤ ለበርካታ ዓመታት ሲዘጋጅ ከኖረና ከልዩ ኃይሉ ውጭ ከ200ሺህ በላይ ዘመናዊ ስልጠና ወስዶ የታጠቀን ሰራዊት ብትንትኑን ማውጣት ለዛውም ያለምንም ኮላተራል ዳሜጅ ። ታዲያ የሆሊውድ ፊልም አጭር ታሪክ እንጂ በገሀዱ ዓለም የተፈጸመ ነው ብሎ ሰው ለማመን ቢቸገር ይፈረድበታል ።
በዓለማችን በስኬታማነታቸው በምሳሌነት ከሚጠቀሱ ወታደራዊ ዘመቻዎች ሳይቀር የበለጠ ውጤታማ ነው ቢባል ማጋነን አይሆነም ። አንባብያን ራሳችሁ ፍርድ ትሰጡ ዘንድ እነዚህን በዓለም ደረጃ በስኬታማነት ብዙ የተጻፈላቸውንና የተነገረላቸውን ወታደራዊ ዘመቻዎችን በአጭሩ እንመልከት ።
በዘመኑም ሆነ ዛሬ ድረስ በጦር ስትራቴጂስትነቱና ጀግንነቱ ትውልድ በአድናቆት ስሙን የሚቀባበለው የፈረንሳይ አብዮት ሰሞነኛው የናፓሊዎን ቦናፓርት የየና ድል ፤ የእስራኤልና የአረቦች የስድስት ቀን ጦርነት ። የሶቪየት ሕብረትና የጃፓን የነሐሴው ማዕበል። የኢሊያድ ጦርነት ። የአሜሪካን መሩ የኢራቅ ጦርነት (የበርሀው ማዕበል) ። በ2ኛው የዓለም ጦርነት እነ ሒትለር ፈረንሳይን ለመውረር የሰነዘሩት ጥቃት ( ዲ ደይ )በዓለማችን የተሳኩ ወታደራዊ ዘመቻዎች ተደርገው በታሪክ ተመዝግበው ይገኛሉ ።
እነዚህ ድሎች የተሳካላቸው የተባሉት ወታደራዊ ስህተት ስላልታየባቸው መሆኑን ብሌክ ስቲልዌል ማይቲ ሒስትሪ ላይ የለጠፈው መጣጥፍ ያትታል። ምዕራባውያን ዓለማቀፍ ሚዲያውን። የጥናትና የምርምር ተቋማት ። ተፅዕኖ ፈጣሪ ልሒቃንን ። ተረኩን ። ወዘተረፈ ስለተቆጣጠሩት የነኩት ሁሉ ይወደሳል ይሞገሳል እንጂ እነዚህ ወታደራዊ ዘመቻዎች ከስህተት የጸዱ እንኳ ቢሆን በሰላማዊ ሰዎችና በመሠረተ ልማቶች ላይ ተጓዳኝ ጉዳት( ኮላተራል ዳሜጅ ) ማድረሳቸው አይካድም። እዚህ ላይ ሒትለር በዲ ደይ ዘመቻው በፈረንሳይ ፤ ጆርጅ ቡሽ በኢራቅ ላይ ያደረሱት ዘርፈ ብዙ ተጓዳኝ ጥፋቶችን ያስታውሷል ።
ዘመን ተሻጋሪ ከሆኑ ስራዎች ቀዳሚው የታዋቂው የጦርነት ስትራቴጂስት ሰን ሱን ፤ “ The art of war “ / የጦርነት ጥበብ / ነው ። ይህ ጥንታዊ መጽሐፍ ከ1500 ዓመታት በኋላ ዛሬም እንደ አዲስ የሚጠና የሚተነተን ድንቅ ስራ ነው ። ይህ ታላቅ መጽሐፍ 13 ምዕራፎች ያሉት ሲሆኑ እያንዳንዱ ምዕራፍ እንደየ አውደ ውጊያው የሚለያይ ስትራቴጂና ታክቲክ ነው። የሶንግ ንጉስ አጼ ሼንዙግ በጎርጎረሳውያን አቆጣጠር በ1080 ዓ.ም “ ሰባቱ ወታደራዊ ዘመን ተሻጋሪዎች “ በሚል ርዕስ አሻሽሎ አሰናድቶታል ።
በዓለማችን ያለ ርዕዮት ዓለም ። የእድገት ደረጃ ። ቀለም ። ሀይማኖት ። ዘር ። ልዩነት ፤ ከምዕራብ እስከ ምስራቅ ። ከሰሜን እስከ ደቡብ ፤ በሁሉም አህጉራት የተዋቀረ የመከላከያ ሰራዊት የሱን ወታደራዊ ሳይንስና የጦርነት ስትራቴጂን እንደየ ተጨባጭ ሁኔታው አዋህዶ ያልተጠቀመበት የለም ማለት ይቻላል። ዓለማቀፍ የወታደራዊ ሳይንስ ትምህርቶች ከዚህ ቻይናዊ አበርክቶ ብዙ ቀስመዋል ።
ይህ ድንቅ መጽሐፍ ከወታደራዊ ሳይንስ ባሻገር ለስራ አመራር ። ለኢኮኖሚክስ ። ለስነ ልቦና ። ለንግድ ። ለገበያ ሽያጭ ወዘተረፈ ትምህርቶች ሳይቀር በግብዓትነት ማገልገሉ በየዘርፉ ልሒቃን ይወሳል ። የዚህ መጣጥፍ አላማ አስገራሚውንና ለማመን የሚከብደውን የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት አንጸባራቂና አኩሪ ድል ከአለቃ ሱን የጦርነት ጥበብ አንጻር በወፍ በረር መቃኘት ነውና ወደዚያው እንለፍ ።
ኃያሉ የሱን የጦርነት ጥበብ ፤
“ ያለ ጦርነት ጠላትን ማንበርከክ “ የሚለው ነው ። ክቡር ጠቅላይ ሚንስትር ወደ ኃላፊነት እንደመጡ ከኤርትራ ጋር የሰላም ስምምነት መፈራረማቸው ከሀዲውን ትህነግ አንድ ጥይት ሳይተኮስ እንዲረታ አድርገውታል ። በውል ባልተረዳሁት ምክንያት ከሀዲው ትህነግ እንደ ወዲ አፎም ወይም ሻአቢያ እንደ ጦር የሚፈራው ኃይል የለም ።
ከዚህ በላይ በኤርትራውያንና ሻአቢያ ፊት በትንሽነት አባዜ የሚሰቃይበት ምክንያት ዛሬም ወደፊትም አይገባኝም። በዚህ የፍርሀትና የትንሽነት ድባብ ውስጥ እየተሰቃየ እያለ ፕሬዝዳንት ኢሳያስ ሸገር ሲመጡ ወይም ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አስመራ ሲገቡ በፍርሀት ይንቀጠቀጣል ። ይርዳል ። ይሄን
ፍርሀቱን ለመደበቅ ፤ የሸሸውን በራስ መተማመን ለማለባበስ የልዩ ኃይል የሰልፍ ትርዒት ያሳያል ። የጦርነት ነጋሪት ይጎሰማል ። እንግዲህ ክቡር ጠቅላይ ሚንስትር ያለውጊያ ከሀዲውን ትህነግ ያንበረከኩት በዚህ የሱን ኃያል የጦርነት ቀመር ነው ።
ክቡር ጠቅላይ ሚንስትር በእነዚህ 34 ወራት ሰላምን አጥብቀው በመሻታቸው ከሀዲው ትህነግ እንደ ፍርሀት ቆጥሮት እንደ ፈርኦን በግብዝነት አንገቱን አደንድኗል። ልቡን ደፍኗል። ይህ ለተሳሳተ መደምደሚያና ውሳኔ ገፍቶት ውርደትን እንዲከናነብ አድርጎታል። እዚህ ላይ ክቡር ጠቅላይ ሚንስትር “ ጠንካራ ሆነህ እያለ እንደ ደካማ ፤ ደካማ ሆነህ እያለ ጠንካራ ታይ ።
“ የሚለውን የሱን ወታደራዊ ታክቲክ ተግብረዋል። ጦርነት እንደማይፈልጉ በተደጋጋሚ መግለጻቸው ከሀዲው የልብ ልብ እንዲሰማውና ደካማነት ሆኖ ስለተረዳው እንዲዘናጋ ስላደረገው መንግስት በመከላከያ ሰራዊት ላይ የሚያካሂደውን ማሻሻያ ለመጨረስ ጊዜ መግዛት አስችሎታል ።
አያዎ ( ፓራዶክስ ) ቢመስልም ጠቅላይ ሚንስትሩ ያሳዩት የነበረው በራስ መተማመን ለጁንታው ድንፋታና ፉከራ ጆሮ ነፍገው መቆየታቸው በሌላ በኩል በተወሰነ ደረጃ ጠንካራ ሆነው እንዲታዩ አድርጓቸዋል። እፉኝቱ ትህነግ ከእብሪቱና ከማንአህለኝነተ ባሻገር በዚህ መወዛገብ ሆኖ ወደ ጦርነት ለመግባት ተገዷል።
ይህ ጦርነት በሙሉ የሰን ሱን የጦርነት ጥበብ ሳይዛነፍ የተገለጠበት ነው ማለት ይቻላል። ይሁንና በዚህ አጭር መጣጥፍ እያንዳንዱን የሱን ቀመር ወይም ታክቲክ እያመሳከርን መዝለቅ ስለማንችል የተወሰኑትን ብቻ እንመለከታልን። “ እራስህንና ጠላትህን ጠንቅቀህ ካወቅህ 100 ጦርነት እንኳ ቢመጣ አትፍራ ።
“ ክቡር ጠቅላይ ሚንስትር የኢፌዴሪን የመከላከያ ሰራዊት ብቃትና የትህነግ ሚሊሽያንና ልዩ ኃይል አቅም ልቅም አርገው ስለሚያውቁት ፤ ከሀዲው ትህነግ የሰሜን ዕዝን እንዳጠቃ የሕግ የበላይነት የማስከበር ዘመቻውን በልበ ሙሉነት አዝዘዋል ። ሆኖም የጠላት አቅምና ዝግጁነት ባይታወቅ አልያም የወገንም የጠላት አቅም ሳይታወቅ ወደጦርነት ቢገባ የከፋ ጉዳት ከፍ ሲልም ሽንፈት ሊከተል እንደሚችል የሱን ታክቲክ ያመላክታል።
አንድ ወሳኝ ታክቲክ ልጨምርና ላብቃ ። “ እቅድህ ሚስጥራዊና የማይደረስበት ፤ አይን ቢወጋ እንደማይታይ ድቅድቅ ጨለማ መሆን አለበት። “ ከሀዲው ትህነግ የኢፌዴሪ የመከላከያ ሰራዊት ያከናወናቸውን የማሻሻያ ተግባራት ፤ ሰው አልባ የጦር አውሮፕላን ( ድሮን ) ጨምሮ የታጠቃቸውን ዘመናዊ የጦር መሳሪያዎች እና የውጊያ ስትራቴጂውን ቀድሞ አለማወቁና በጥብቅ ዲሲፕሊን በሚስጥር መያዛቸው ፤ ትህነግ ሱር በቆፈረው ምሽግ ይዞ ሲጠባበቅ ጦርነቱ በአየር ኃይል ፋና ወጊነት ፤ በድሮን ድንገቴ ጥቃት እና በኮማንዶው መብረቃዊ ጥቃት በስምንት ቀናት በአንጸባራቂ ድል ተደመደመ።
መንግስት ሁለት ጊዜ የሰጠውን የሶስት የሶስት ቀናት ገደብ ስድስት ቀናትን ቀንሼ ነው በስምንት ቀናት ያልሁት። ለዚህ ነው የሰን ሱን የውጊያ ጥበብ የተገለጠበት ዘመቻ ያልሁት። ከሁሉም በላይ ክቡር ጠቅላይ ሚንስትር እንዳሉት ዘመቻው በሰላማዊ ሰዎች ። በመሠረተ ልማትና በከተሞች ምንም ጉዳት ሳይደርስ የተጠናቀቀ ዘመቻ ስለሆነ ልዩ ያደርገዋል ።
ሀገራችን ኢትዮጵያ በጀግኖችና ሀቀኛ ልጆቿ ተከብራ ለዘላለም ትኑር ! ! !
አሜን ።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 11/2013