የህወሓት ጁንታ ተግባርና አንደበት ፈጽሞ የተለያዩ ናቸው። ይህ ቡድን በተለይ በትግራይ ህዝብ ላይ ላለፉት 47 ዓመታት ከሠራው በጎ ነገር ይልቅ በማይጨበጥ የውሸት ፕሮፓጋንዳ የተሞላው የማይጨበጥ ትርክት እንደሚበልጥ ቡድኑን በቅርበት የሚያውቁና በጥልቀት የመረመሩ ሁሉ የሚናገሩት እውነታ ነው።
ለአብነትም ገና በበረሃ ውስጥ እያለ ጀምሮ በሚያራምደው የፖለቲካ ርዕዮተዓለም ጭምር የራሱን የትግል ጓዶች እና ህዝቡን ጭምር ሲያታልል ነበር። የቀድሞ የህወሓት አባል የነበሩት አቶ ገብሩ አስራት በመጽሐፋቸው ላይ እንደጠቆሙት። ቡድኑ ገና በበረሃ እያለ እንኳ የሚከተለውን ርዕዮተዓለም በግልጽ ከመናገር ይልቅ ከራሱ ጥቅም አንጻር በሚያመች መልኩ ለተለያዩ አገራት የተለያየ መልክ ነበረው።
የሃውዜንም ታሪክ የማይረሳው የጁንታው የጭካኔ ማሳያ ነው። በወቅቱ የጁንታው አባላት ደርግ በትግራይ ህዝብ ላይ በአውሮፕላን ጭፍጨፋ እንዲያካሄድ በማድረግ በህዝብ ደምና አጥረት የራሱን የፖለቲካ ቁማር የተጫወተ ቡድን ስለመሆኑ እማኞች የሚናገሩት ሀቅ ነው። ይህም ቡድኑ ለሱ ፖለቲካ እስከተመቸው ድረስ የትግራይ ህዝብ ቢጨፈጨፍም ሆነ ቢጠፋ ደንታው አለመሆኑን ያሳያል። እዚህ ላይ ታዲያ የደርግን አምባገነናዊነትና ደካማ ጎን በመጠቀም የሠራው የተንኮል ሥራ መሆኑን ጭምር መገንዘብ ይቻላል።
በቅርቡም ጁንታው በሃገር መከላከያ ሠራዊት የደረሰበትን ጥቃት መቋቋም ሲያቅተው ድሮ እንደለመደው አንዴ በህዝቡ ውስጥ፤ ሌላ ጊዜ ደግሞ በእምነት ተቋማት ውስጥ ራሱን በመሸሸግ መከላከያ ሠራዊቱ ህዝቡ ላይ ጥቃት እንዲያደርስ ያልፈነቀለው ድንጋይ አልነበረም። ይሁን እንጂ የሃገር መከላከያ ሠራዊቱ ህዝባዊ መሰረቱና የህዝብ ወገንተኝነቱ ጠንካራ በመሆኑ ጥንቃቄ በተሞላበት ሁኔታ አንድም ሲቪል ዜጋ ሳይጎዳ ጁንታውን የማጽዳት ዘመቻውን በብቃት ተወጥቷል።
ጁንታው በሁሉም መስክ ከራሱ ውጪ ለህዝቡ ምንም ዓይነት ዓይንና ጆሮ እንደሌለው የሚያሳዩ ሌሎች በርካታ ማሳያዎችንም ማንሳት ይቻላል። ከእነዚህም ውስጥ ሰሞኑን በህዝብ የውሃ ጥያቄ ስም ሲያደርግ የነበረው ሴራና ተንኮል ሲታይ ደግሞ ወደፊት በቡደኑ የተፈፀሙ በርካታ ድብቅ የክፋት ተግባራትን እንደምናይ ከወዲሁ ማስረጃ ሊሆን ይችላል።
እንደሚታቀው መቀሌ ከተማ በአገራችን የመጠጥ ውሃ እጥረት ካለባቸው የአገራችን ከተሞች አንዷ ናት። በከተማዋ ነዋሪ ለዘመናት ሲቀርብ የነበረው የንጹሕ መጠጥ ውሃ ፍላጎት በዚሁ የጁንታ ሴራና ተንኮል ሳይሳካ ቆይቷል። እኔ ብቸኛ የህዝቡ ተወካይ ነኝ እያለ በአደባባይ ቢምልም የህዝቡ አንድም ጥያቄ ሊመልስ አልቻለም። ይልቁንም የፌዴራል መንግሥትም ለህዝቡ ጥያቄ ምላሽ እንዳይሰጥ እንቅፋት ሲሆን ቆይቷል።
የፌዴራል መንግሥት ለአካባቢው የውሃ ችግር ምላሽ ለመስጠት በጀት መድቦ ሥራውን ለመሥራት ሙከራ ሲደርግ በጀቱ በእጃችን ካልተሰጠን በስተቀር አይሠራም በሚል ሰበብ ህብረተሰቡ ለዘመናት ሲያቀርብ የነበረው ጥያቄም እውን እንዳይሆን አድርጓል።
ሰሞኑን ታዲያ ጁንታው በመቀሌ አዲዳእሮ አካባቢ ቆፍሮ ያከማቻቸው 22 የነዳጅ ማከማቻ ዴፖዎችን መከላከያ ሠራዊት ከህዝቡ በደረሰው ጥቆማ መሰረት አግኝቷል። ጁንታው ይህንን ነዳጅ ያከማቸው ደግሞ የህዝቡ የነዳጅ ፍላጎት ለማሟላት ሳይሆን ለጦርነት ነው።
አስገራሚው ነገር ደግሞ ጁንታው ይህንን ሲያደርግ የነበረው የህዝቡ የልብ ትርታ የሆነውን የውሃ ፍላጎት ለማሟላት እንደሆነ በማስመሰል ነበር። ጁንታው ዴፖውን ሲያዘጋጅ ለአካባቢው ማህበረሰብም ሆነ ዴፖውን ለሚጠብቁት የጥበቃ አባላት ጭምር የውሃ ታንከር በመሆኑ በአግባቡ እንዲጠብቁ አሳምኗቸው ነበር። በዚህ የተነሳ ጠባቂዎቹ እስከመጨረሻዋ ሰዓት ድረስ የሚያውቁት የከተማዋን የውሃ ታንከር እንደሚጠብቁ እንጂ የጁንታውን ለጦርነት ያዘጋጀውን ነዳጅ ስለመሆኑ አንዳችም መረጃ አልነበራቸውም።
ይህ ብቻ አይደለም። ጁንታው በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ የሚሊሻዎችና የልዩ ኃይል አባላት ሲያሰለጥንና ለጦርነት ሲያዘጋጅ ከመከላከያ ሠራዊት ጋር እንደሚዋጉ አንዳችም መረጃ አልሰጣቸውም። ከዚህ ይልቅ ከጠላት ጋር እንደሚዋጉ አልያም የክልላቸውን ሰላም እንደሚጠብቁ ነበር ሲሰብካቸው የነበረው።
እንግዲህ እነዚህና መሰል የጁንታው ሴራዎች ይህ ቡድን ምን ያህል ከህዝብ ፍላጎት ይልቅ ለራሱ ጥቅምና የራሱን ሆድ ብቻ ለመሙላት የኖረ ድብቅ ኃይል እንደነበር ያሳያል። ቡድኑ ለበርካታ ዓመታት የኖረውም በውሸትና በሴራ ብቻ ነው። እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስም በሞት አፋፍ ላይ ሆኖ ሲዋሽ ነበር። እናም የዚህ ሴረኛ ቡድን አጀንዳ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንዲዘጋና የክልሉ ህዝብ ለዘመናት የታገለለት የእኩልነት፤ የነፃነትና የብልጽግና ፍላጎት እንዲሳካ አሁንም የጁንታውን አባላት በማጋለጥ እና ከአዲሱ አስተዳደር ጋር በመሆን ህዝቡ ፊቱን ወደልማት ሊመልስ ይገባል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 11/2013