ጌታቸው በለጠ – ዳግላስ ጴጥሮስ gechoseni@gmail.com
“ሰው የሚማረው አንድም በፊደል፣
አንድም በመከራ ነው፡፡
አንድ ቃል ከፊደል መዝገብ፣
አንድ ቃል ከመከራ መዝገብ፤
አንድም በሣር “ሀ” ብሎ፣
አንድም በአሳር “ዋ”ብሎ፡፡” (ሎሬት ጸጋዬ ገ/ መድኅን)
“ቦ ጊዜ ለኩሉ!”፤
ጊዜው ነው የሚሮጠው ወይንስ እድሜያችን? ቀድሞ የሚሮጠውስ ማነው? እድሜያችን ወይንስ ጊዜ? ጎን ለጎን እየሮጡ ከሆነ መልካም፤ የአሸናፊነት ጥብጣቡን አብረው ስለሚበጥሱ ቀዳሚና ተከታይ ላይኖር ይችላል።
አንዳቸው ፈጥነው ከሮጡ ግን ቆም ብሎ ማሰብና ማሰላሰሉ አይከፋም፡፡ የቅዱስ መጽሐፉ የመኃልየ መኃልይ መጽሐፍ ደራሲ ጠቢቡ ሰለሞን “ለሁሉም ጊዜ አለው!” በማለት እቅጩን የነገረን ያለጊዜው ጊዜን ለመቅደም እየተንፈራገጥን እንዳንላላጥ ወይንም ሌላውን አላግባብ እንዳንልጥና የጊዜ ጀንበር ዳምኖብን እንዳንወድቅ ሊመክረን አስቦ ይመስለኛል፡፡
የጠቢቡን ስምና ሥራ ካስታወስን አይቀር ጥቂት ሃሳቦችን እንጥቀስ፤ “ለሁሉ ዘመን አለው፤ ከሰማይ በታችም ለሆነ ነገር ሁሉ ጊዜ አለው፡፡ ለማፍረስ ጊዜ አለው፤ ለመሥራትም ጊዜ አለው፤ ለማልቀስ ጊዜ አለው፤ ለመሳቅም ጊዜ አለው፤ ለመቅደድ ጊዜ አለው፤ ለመስፋትም ጊዜ አለው፡፡ ዝም ለማለት ጊዜ አለው፤ ለመናገርም ጊዜ አለው፤ ለሰላም ጊዜ አለው፤ ለጦርነትም ጊዜ አለው፤… ለሥራ ሁሉ ጊዜ አለው፡፡ ፈጣሪ ነገርን በጊዜው ውብ አድርጎ ሠራው፡፡” (መጽሐፈ መክብብ ምዕ. 3)
“ለጊዜ ጊዜ እንስጠው” – የተከበሩ አበው አባባል፤
በወጣትነት እድሜዬ ካጋጠሙኝ አይተኬ እድሎች መካከል አንዱ በእድሜም ሆነ በልምድ፣ በእውቀትም ሆነ በጥበብ ተንጠራርቼ ከማልደርስባቸው የተከበሩ አባቶች ጋር የአንድ ሀገራዊ ታላቅ ተቋም ብሔራዊ ቦርድ አባል ሆኜ ያገለግለኩባቸው ስምንት ዓመታት ተወዳዳሪ አይገኝላቸውም፡፡
ከእነዚህ አባቶች እግር ሥር ቁጭ ብዬ የተማርኩትን ትምህርት ካለፍኩባቸው የትኞቹም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለማግኘት አልቻልኩም፡፡ ጊዜና ዕድል አገጣጥሞኝ ከእነዚህ አባቶች የቀሰምኩትን ማስተዋል በተመለከተ ለአንባቢያን ትልቅ ትምህርት ስለሚሰጥ በአጭሩ አስታውሼ ወደ ዋና ጉዳዬ አዘግማለሁ፡፡
ከቦርድ አባላቱ መካከል በግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመን ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር እንድትዋሃድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረከቱትና በተለያዩ ከፍተኛ የመንግሥት ሹመቶች ዘመናቸውን ያገባደዱት ክቡር ቢተወደድ አስፍሃ ወ/ሚካኤል፣ በአምባሳደርነትና በሚኒስትርነት ለሀገራቸው የደከሙት ክቡር አቶ አማኑኤል አብርሃም፣ በተለያዩ መንግሥታዊ ታላላቅ ተቋማት እስከ ሚኒስትር ዴኤታ ማዕረግ በመድረስ በትጋታቸው የሚታወቁት ክቡር አቶ ነዋይ ገ/ጻድቅ፣ የአየር ኃይላችን ቆፍጣና ወታደር የነበሩት ክቡር ኮሎኔል ታደሰ ሁንዴ፣ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ካህን (አሁን ጳጳስ) የተከበሩ አባ ፀጋዬ ቀነኒ፣ ክቡር ዶ/ር አማኑኤል ገ/ስላሴ የኢምፔሪያል ሆቴል ባለቤት የነበሩት ክቡር አቶ አስፋው ተፈራ ከሺህ ውበት (ሽበት) ባለፀጋዎቹ መካከል ጥቂቶቹ ነበሩ፡፡
ቦርዱ በሥራ ላይ በነበረበት አንድ ወቅት ከሀገር ውስጥና ከውጭ ሀገራት ታላላቅ እንግዶች የተጋበዙበት አንድ ታላቅ ኩነት በአዲስ አበባ ከተማ ተከናውኖ ነበር። ይህንኑ መርሃ ግብር ለመዘገብ ከመጡ የውጭ ሀገራት የሚዲያ ተቋማት መካከል የታወቀ የመጽሔት ዝግጅት ክፍልም ባለሙያዎቹን ልኮ ፕሮግራሙ እንዲዘገብ አድርጓል፡፡ በወቅቱ የነበሩት ቅዱስ ፓትርያርክ፣ በርካታ ብጹዓን ሊቃነ ጳጳሳትና ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት የተከናወነው ያ መርሃ ግብር የተጠናቀቀው እንደታቀደው በውጤት ነበር፡፡
ከፕሮግራሙ መጠናቀቅ ጥቂት ሳምንታት በኋላ ግን በዕለቱ ተቀዳሚ የክብር እንግዳና መልዕክት ካስተላለፉት አንዱ የነበሩት ቅዱስ ፓትርያርኩ የቦርድ አባላቱን ማነጋገር እንደሚፈልጉ አንድ የጽሑፍ ማስታወሻ ይልካሉ፡፡ የማስታወሻው ይዘት ትንሽ መረር ያለ ቁጣ የተቀላቀለበት ዓይነት ስለነበር የቦርድ አባላቱ መደናገጣቸው አልቀረም፡፡
በቀጠሮው መሠረት ክቡር ቢተወደድ አስፍሃ ወ/ሚካኤልን ጨምሮ የተወሰኑ የቦርድ አባላት ቅዱስነታቸውን እንዲያናግሩ ሃሳብ ይቀርባል፡፡ በዚህ ጊዜ ቢተወደድ አስፍሃ ጥበብና ለዛ በተላበሰው ንግግራቸው “ሁኔታው አላማረኝም፡፡
ቅዱስነታቸው ያዘኑበት አንድ ክስተት ተፈጽሞ ሊሆን ስለሚችል ሁኔታውን ጊዜው ካልገለጠው በስተቀር ያለጊዜው ሄጄ ነገር አላበላሽም። የተቀራችሁት ሄዳችሁ ብታነጋግሯቸው ይሻላል። በማለት አቋማቸውን አሳወቁ፡፡ እንደተባለውም በእርሳቸው ቦታ ሌላ ሰው ተተክቶ ቅዱስነታቸውን ለማነጋገር የልዑካን ቡድኑ በጽሕፈት ቤታቸው ተገኘ፡፡
ለካስ ቅዱስነታቸውን ያሳዘናቸው ጉዳይ እርሳቸው በበዓሉ ላይ ያደረጉትን ሙሉ ንግግር ያ የውጭ ሀገር መጽሔት እንዳለ አትሞ ሲያበቃ የተጠቀመው ፎቶግራፍና በፎቶግራፉ ላይ የተገለጸው ስም ግን በእለቱ ንግግር ያደረጉ ሌላ ሊቀ ጳጳስን ነበር፡፡ በእውነትም ስህተቱ ግዙፍ የሚባልና ከቦርዱ እውቅና ውጭ የተፈጸመ ነበር። ሁኔታው በወቅቱ ከነበረው የቤተ ክርሲቲያኒቱ ችግር ጋር ተገጣጥሞ ቅዱስነታቸውን በእጅጉ ቢያሳዝናቸው የሚገርም አልነበረም፡፡
ሁኔታው ከእነርሱ ቁጥጥር ውጭ የተፈጸመ መሆኑን የቦርዱ አባላት ደጋግሞው ቢያስረዱም ቅዱስነታቸው ልባቸው መለስ ሊል አልቻለም፡፡ በተከታታይነትም በደብዳቤም ሆነ ተወካዮች ተልከው ይቅርታ ለመጠየቅ ቢሞከርም ሁኔታው ሊረግብ አልቻለም፡፡ ይህንን ችግር የተረዱት ጠቢቡ ቢተወደድ አስፍሃ ለቦርድ አባላቱ እንዲህ የሚል ምክር ለገሱ፡፡
“ወንድሞቼና ልጆቼ ቅዱስነታቸው አምርረው ቢቆጡ እውነት አላቸው፡፡ ደጋግማችሁ በመሄድም ስሜታቸው ባይጎዳ መልካም ነው፡፡ ይህን ችግር የሚፈታው ጊዜ ስለሆነ ለጊዜ ጊዜ እንስጠው፡፡ ያለጊዜው የምንፈጽማቸው ተግባሮች ለብዙ ችግሮች ሰበብና ምክንያት ሊሆኑ ይችላሉ። ጊዜው ፈቀድኩ ሲለን የጊዜን ድምጽ ሰምተን የሚሻለውን ማድረጉ ይበጃል፡፡”
ከቡርነታቸው እንዳሉትም ከአንድ ዓመት በኋላ ቅዱስነታቸው ራሳቸው የቦርዱን አባላት ጠርተው ችግሩን አስመልክቶ እንዲህ በማለት እልባት ሰጡ። “አባቶቼ ሆይ (አባቶቼ ማለታቸውን ልብ ይሏል)! የተፈጠረውን ስህተት በተመለከተ የእኔን ልብ ለማሸነፍ ብዙ ጥረት አድርጋችኋል፡፡ ችግሩን የፈጠረውና ያጋጋለው ማን እንደሆነ በሚገባ ጊዜው ገልጦልን እውነቱን ተረድተነዋል።እናንተ አባቶች እኔ ልጅ ሆኜ ስላስቸገርኳችሁ እባካችሁ ይቅርታ አድርጉልኝ፡፡ ጊዜ ሁሉንም ገላልጦታል፡፡ ለጊዜ ስትሉ ተሸነፉልኝ፡፡” የቅዱስነታቸው ንግግር ከአንድ የሃይማኖት ተቀዳሚ መሪ የሚጠበቅና ልብ የሚነካ ትህትና የተስተዋለበት ነበር፡፡
ይህን መሰሉ ምሳሌነት ያለው የቅዱስነታቸው ተግባር ለክቡር ቢተወደድ አስፍሃ ሪፖርት ሲደረግላቸው የመለሱት መልስ እንዲህ የሚል ነበር። “አባቶቼና ልጆቼ! ችግሩን የፈታው ማንም ሳይሆን ጊዜ ነው፡፡ የተወሳሰበ ችግር በመገጠማችሁ ጊዜ ሁሉ ከመታወክና ተገቢ ያልሆነ እርምጃ ከመውሰዳችሁ አስቀድሞ ስሜታችሁን ዋጥ አድርጋችሁ ለጊዜ ጊዜ ስጡት፡፡ እንዲህ ሲሆን ጊዜ በራሱ ጊዜ ለችግሮች ሁሉ መፍትሔ አለው፡፡”
ይህ መልእክት ለጊዜያችን ጥሩ ማስተማሪያ ስለሆነ ጊዜው ሲደርስ እነሆ ለዝክር በቅቷል፡፡ ከጠቅስኳቸው ጎምቱ አባቶች መካከል ዛሬ በሕይወት ያሉት ሊቀ ጳጳሱ አባ ፀጋዬ ቀነኒ ብቻ ናቸው፡፡ ሌሎቹ ሁሉም የምድር ጉዟቸውን ጨርሰው በአጸደ ሥጋ ተለይተውናል፡፡ ምክራቸውና ለሀገራቸው ያበረከቱት አስተዋጽኦ ግን ሁሌም በታሪክ ሲታወስ ይኖራል፡፡
ጊዜ የፈታው የሀገር ችግር፤
የህወሓት ቡድን ከበረሃ ቁጥቋጦ ሥር በቅሎ ከንግስና ወንበር ላይ ተደላድሎ ለሃያ ሰባት ዓመታት ያህል ሀገሪቱን በብረት በትር ሲቀጠቅት የኖረው “ጊዜ የፈቀደለት ቅል ድንጋይ ይሰብራል” እንዲሉ ግዙፉን የደርግ መንግሥት ገፍትሮ ነበር፡፡ እርግጥ ነው የወያኔ ድርሻ የነበረው ጥንጣን እንደ በላው ግዙፍ ዛፍ የሕዝብ ሮሮና ስቃይ እርቃኑን ያስቀረውን የደርግ ሥርዓት በጠመንጃ አፈሙዝ ገፋ አድርጎ ስለ ጣለው እንጂ ድሉማ የመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ነበር፡፡
ጊዜ ያጀገነው ያ ጫካ ወለድ የህወሓት ቡድን በሥልጣን ላይ ከተፈናጠጠ ዕለት ጀምሮ የፈጸማቸው ግፍና ውድመት ገና ተገላልጦ አላበቃም፡፡ እስከ ዛሬ እያስተዋልንና እየሰማን ያለነው የግፎቹን ቅንጭብጫቢ ትራዤዲዎች እንጂ የዋናው ሀገራዊ የበደል ተውኔት መጋረጃማ ገና ሙሉ ለሙሉ ተገልጦ ትእይንቱ ለሕዝብ አልቀረበም፡፡
የህወሓት ቡድን የመንበረ ሥልጣን ወንበሩ ላይ ገና አረፍ ከማለቱ በመጀመሪያ ያደረገው የሀገር መከላከያ ሠራዊትን መበተን ነበር፡፡ በመቀጠልም በፖለቲካ አባልነት ስም ብዙዎችን አስለቅሷል፣ ከሥራቸው ላይ አፈናቅሏል፣ በርካታ ዜጎችንም ለስደትና እንግልት ዳርጓል።በንጹሐን ደም ህሊናውንና እጁን ተለቃልቋል። አንዱን ብሔር ከሌላኛው ጋር በማጋጨት “የሰይጣንን ዋነኛ ተልዕኮ” በመወጣት በእንባና በደም ተነክሯል። የፖለቲካ ቡድኖችን እየፈለፈለና እንደ ድመት ሙጭጭላዎች አንዱን ካንዱ እያባለ እድሜውን አርዝሟል፡፡
የሀገርን ሀብትና ንብረት ያለርህራሄ ዘርፎ አዘርፏል፤ ግጦ አስግጧል፡፡ ዜጎች ብቻ ሳይሆኑ ምድሪቱ ራሷ አፍ አውጥታ እሪ ብላ ጮኻለች፡፡ ሀገራዊ የኢኮኖሚውን አውታር ሙሉ ለሙሉ ተቆጣጥሮ እንደ በለስ ፍሬ ገምጦና አስገምጦ አርቃናችንን አስቀርቶ ለልመና አጀግኖናል።
በማህበራዊ መስተጋብር ላይ የክፋት አሲድ እየነሰነሰ ሕብረ ብሔራዊነትን ብል እንደ በላው ጨርቅ ብጥቅጥቅ እንዲል ሰርቷል፡፡ ዝርዝሩን በአጭሩ ለመደምደም ያህል ኢትዮጵያንና የኢትዮጵያዊነትን ክብርና ሞገስ ገፎ ሕዝቡን በጎጥ አረንቋ ውስጥ በመድፈቅ ራሱን ሲያገዝፍ ኖሯል፡፡
የራሄሏ የኢትዮጵያ እምባ ወደ ፀባዖት ደርሶ ከመንበረ ዙፋኑ ላይ ተፈንግሎ በመውደቅ በተከበረው የትግራይ ሕዝብ መካከል ለሁለት ዓመታት ያህል ተሸሽጎ ምን ሲሰራ እንደኖረ መዘርዘሩ ለቀባሪ ማርዳት እንዳይሆን በመስጋት እንጂ ብዙ ማለት ይቻላል። የግፍ ተግባሩና እብሪቱ ዋንጫ መገንፈል ደረጃ ላይ የደረሰው ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በሰሜን ዕዝ የመከላከያ ሠራዊታችን ላይ ክህደት በፈጸመበት እለት ነበር፡፡
የገነፈለው እብሪቱ ወደ አራዊትነት ባህርይ ዝቅ አድርጎት በማይካድራና በተለያዩ አካባቢዎች የፈጸማቸውና ያስፈጸማቸው የንጹሃን ጭፍጨፋዎችና የንብረት ውድመት ጥፋቶችን ለጊዜው ለመጠቋቆም ተሞከረ እንጂ ዝርዝሩን ገና ጊዜ ይገልጠዋል፡፡
ግፈኛው የህወሓት ቡድን በትግራይ ሕዝብ መካከል ተሸሽጎ ለፈጸመውና እየፈጸመ ለነበረው ሰይጣናዊ ድርጊቱ “የመንግሥት ያለህ! መንግሥት ለዘብተኛ ሆነ! ትዕግሥት ልክ አለው! የመንግሥት ሆደ ሰፊነት መጠኑን አለፈ ወዘተ.” እያለ ሕዝቡ ሲጮኽና እኛም በብዕራችን ስንፋለም መንግሥት ሰምቶ እንዳልሰማ ምላሽ ለመስጠት ያልሞከረው ለካንስ ክቡር ቢተወደድ አስፍሃ እንዳስተማሩን ለጊዜ ጊዜ እየሰጠ ኖሯል፡፡
የቁርጡ ቀን ደርሶ ጊዜ በጊዜ ላይ አምርሮ ከመሰልጠኑ በፊት ግን የእብሪተኛው ቡድን ፀሐይ ደም ለብሳ በደም እንዳትነክራቸው ለማስጠንቀቅ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከመጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም የበዓለ ሲመታቸው ዕለት ጀምሮ እስከ ህዳር 4 ቀን 2013 ዓ.ም ድረስ በርካታ የሰላም ጥሪ ተላልፎላቸው ነበር፡፡ ጥቂቶቹን እናስታውስ፡፡
ራሳቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሚያዝያ 5 እና ሰኔ 2 ቀን 2010 ዓ.ም በመቀሌና በአክሱም በመገኘት እጃቸውን ለሰላም በመዘርጋት እና ልባቸውን ለፍቅር በመክፈት ከእብሪታቸው እንዲሰክኑ ጥሪ ቢያስተላልፉላቸውም ጆሮ ዳባ ልበስ በማለት የእብሪታቸውን ባሉን ይበልጥ አግዝፈው አሳበጡ፡፡
የካቲት 4 ቀን 2011 ዓ.ም የእርቀ ሰለም ኮሚሽን መቋቋሙን በመግለጽ የሽምግልና ወግ እንዲከበር መልእክት ቢተላለፍላቸውም የደነደነው ልባቸው ይበልጥ እንደ ጭንጫ ድንጋይ ጠጠረ እንጂ ሊለዝቡ አልቻሉም፡፡
ሰኔ 9 ቀን 2012 ዓ.ም 50 አባላት የተካተቱበት የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች የልዑካን ቡድን መቀሌ ድረስ ተገኝቶ ለእርቅ ልባቸውን እንዲከፍቱ ቢጠየቁ የሰላሙን በር ጠርቅመው ስለዘጉባቸው እያዘኑ አንገታቸውን ደፍተው መመለሳቸውን እናስታውሳለን፡፡
ጥቅምት 12 ቀን 2012 ዓ.ም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፓርላማ ባደረጉት ንግግር ተቀዳሚ መልእክታቸው እንዲደርስ ያደረጉት ለእነዚሁ በእብሪት ለሰከሩት የህወሓት ቡድንተኞች ነበር፡፡ ጥቅምት 24 ቀን 2012 ዓ.ም የተፈጠረውን ሀገራዊ ቀውስና የ86 ንፁሐን ዜጎችን ጭፍጨፋ አስመልክቶም እጃቸውን ከደም፣ ተግባራቸውን ከአመፅ እንዲሰበስቡ ጠንከር ያለ መልዕክት ተላልፎላቸው ነበር፡፡
በዚሁ ዓመት ሚያዝያ 29፣ ሰኔ 1፣ ሰኔ 4፣ ሐምሌ 21፣ እና ለ2013 የአዲስ ዓመት ዋዜማ የሰላም ጥሪ ቢዥጎደጎድላቸውም ጆሯቸውን ደፍነው አልሰማም በማለት “የሰላም ተምሳሌት እርግብ” የሆነውን የመከላከያ ሠራዊት ተተናኩለው ክህደት በመፈጸማቸው የጊዜያቸው ጀንበር ጠልቃ የታሪካቸውና የእብሪታቸው እስትንፋስ ህልውና ማክተሚያ መቃረቡ ግድ ሆነ፡፡
ለጊዜ ጊዜ የሰጠው ትእግስተኛው መንግሥት ጊዜው ሲደርስ ሊፈጸም ግድ የነበረውን የሕግ ማስከበር እርምጃ ወስዶ ምክርና ሰላም ያላሸነፈው የእብሪት ተራራ በጀግናው ሠራዊታችን ተንዶ የታሪካቸው ምዕራፍ ለአንዴና ለዘላለም እንዲዘጋ ጊዜው ራሱ ፍርድ ሰጠ፡፡
ጸጋዬ ገ/መድህን እንደተቀኘው በምክርና በሰላም ቃል “ሀ!” በል ሲባል አሻፈረኝ ብሎ በነፍጥ መፋለምን ተቀዳሚ ምርጫው ያደረገው የህወሓት ቡድን “ዋ!” ብሎ የአሳሩን አዝመራ ሊያጭድ ጊዜ የወለደው ጊዜ ፈርዶበታል፡፡ እኛም ለጊዜ ጊዜ እንዳለው በሚገባ ተረድተን “ቦ ጊዜ ለኩሉ!” ብለናል፡፡ መማር የወደደ ሁለት ምርጫ እንዳለው ለሦስተኛ ጊዜ ደግሞ ማስታወሱ አይከፋም፡፡ “አንድም በሣር “ሀ!” በማለት፤ አንድም በአሳር “ዋ!” በማለት” – ሰላም ይሁን!
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 10/2013