ግርማ መንግሥቴ
በኢትዮጵያ የአካል ጉዳተኞች ቁጥር ቀላል የሚባል አይደለም። እራሱን ችሎ በእቅድ ሊመራና ወደ ተግባር ሊወርድ የሚገባን ስራ ይፈልጋል። ይሁን እንጂ በእኛ አገር ምንም የተለየ ነገር ሲሰራ አይታይም። ይህ ባለመሆኑም በርካታ ችግሮች ይታያሉ። እነዚህ ችግሮች ደግሞ የግለሰብ ወይም የአንድ አካባቢ ችግሮች ሳይሆኑ የአገር ናቸውና ከወዲሁ የሁሉንም ርብርብ ይፈልጋሉ።
ለውጡን ተከትሎ የመጣው መንግስት በአይነቱ የመጀመሪያ መሆኑ እየተነገረለት ባለው የ 10 ዓመት መሪ እቅድ ውስጥ የአካል ጉዳተኞች ጉዳይ ትኩረት አግኝቷል። የመንግሥት የ 10 ዓመት መሪ የልማት እቅድ አካል ጉዳተኞችን ያሳተፈና ልዩ ትኩረት የሰጠ ሲሆን የፕላንና ልማት ኮሚሽን መሪ እቅዱን ሲያዘጋጅም አካል ጉዳተኞች ማህበራት ጋር ሰፊ ውይይት አድርጓል። እቅዱም የአካል ጉዳተኞች እኩል ተሳታፊነትን እንደሚያረጋግጥ ይጠበቃል።
እስካሁን ያለውን የአካል ጉዳተኞች ሁኔታን የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማህበራት ፌዴሬሽን ዋና ዳይሬክተር አቶ አባይነህ ጉጆ ከባለፈው ረብዕ ሪፖርተር እትም ጋር ባደረጉት ቆይታ “… አካል ጉዳተኞች ያላቸውን አቅም እንዲጠቀሙ ለማድረግ የሚያነሳሳ ተቋም ብዙም የለም።” በማለት ገልፀውታል። በአንፃሩ ደግሞ የዘንድሮው የአካል ጉዳተኞች ዓመታዊ በአል (ቀን) “የአካል ጉዳተኞችን ተሳትፎና መሪነት በማጎልበት የ2030 የልማት አጀንዳን ውጤታማነት እናረጋግጥ!” በሚል መሪ ቃል ተከብሯል።
እራሳቸው አካል ጉዳተኞች የተባሉት ወገኖች የችግሩ ሳይሆን የመፍትሄው አካል በመሆን ለበርካታ ችግሮች መፍትሄዎችን እየሰጡ፤ በመፍትሄዎቹም ማህበራዊ ችግሮችን እየፈቱና ማህበረሰቡን ተጠቃሚ እያደረጉ ይገኛሉ። ችግሩ እነዚህ አካል ጉዳተኞች ሁኔታዎች ካልተመቻቹላቸው፣ በፖሊሲ የተደገፉ አሰራሮች ካልተዘረጉላቸውና እነሱ ተሳታፊና ተጠቃሚ የሚሆኑበት እድል ካልተመቻቸና ሁሉም ነገር ዙሪያው ገደል ከሆነ ብቻ ነው። ይህ እንዳይሆን ደግሞ የውጡ የመንግስት ደንብና መመሪያዎችን በአግባቡ ስራ ላይ ከማዋል በተጨማሪ የጋራ ርብርብ በማድረግ አንድ ጠቃሚ ውሳኔና ውጤት ላይ መድረስ ተገቢ ይሆናል።
የዛሬ እንግዳችን አቶ እሸቱ መክብብ ይባላሉ። ነዋሪነታቸው በአዲስ አበባ ከተማ ልዩ ቦታው ልደታ ክፍለ ከተማ ወረዳ 4 ቀጠና ሶስት ጌጃ ሰፈር ተብሎ በሚታወቀው አካባቢ ነው። አቶ እሸቱ ባለ ትዳር እና የሶስት ልጆች አባትም ናቸው። ኑሯቸውን የሚደግፉበት ምንም አይነት ኢኮኖሚያዊ ገቢ የላቸውም። ወርሀዊም ሆነ እለታዊ ገቢ አያውቁም፤ ባጭሩ ድጋፍም ሆነ እርዳታ የሚያደርግላቸው ሰው የለም።
አቶ እሸቱን በጠባብ መኖሪያ ቤታቸው ተገኝተን ባነጋገርናቸው ወቅት እንደነገሩን፤ አሁን እየኖሩበት ያለውን ቤት ያገኙት በ1986 ዓ.ም ሲሆን ቤቱን ሰርቶ የሰጣቸው ደግሞ አንድ መንግስታዊ ያልሆነ የውጭ ድርጅት ነበር።
“እግዜር ይስጣቸውና ይህችን ቤት ሰርተው ባይሰጡኝ ኖሮ እኔ ምንም ነገር የሌለኝ ሰው ነበርኩ” የሚሉት አቶ እሸቱ አልፎ አልፎም በአንዳንድ በጎ አድራጊ ድርጅቶች የሚደረግላቸውን ድጋፍና ትብብር እንዳለም ይናገራሉ።
በጁንታው የ27 የአገዛዝ ዘመን ግፍ ሲደርስባቸው፣ ሲታሰሩና ሲገረፉ የነበሩ ወጣቶች ከለውጡ በኋላ በመሰባሰብና እኛ ለቂም ሳይሆን ለፍቅር ነው መስራት ያለብን ከሚል የአርአያነት ተግባር የመነጨና “ፍቅር ያሸንፋል” በሚል ስያሜ የተቋቋመው የአካባቢያቸው በጎ አድራጎት ድርጅት በቅርቡ ቤታቸውን እንዳደሰላቸውም ይጠቅሳሉ።
ከላይ ከማህበራዊ ችግሮችና ሃላፊነቶች አኳያ ለማየት እንደሞከርነው አቶ እሸቱ አካል ጉዳተኛ ይሁኑ እንጂ ይህ ማህበራዊ ሃላፊነታቸውን ከመወጣትም ሆነ የተለያዩ ሙያዎች ባለቤት ከመሆን አላገዳቸውም።
አቶ እሸቱ ከማህበረሰቡ ጋር በቀጥታ የተያያዙ ስራዎች በተለይ ህብረተሰቡን የማንቃት ስራዎች በነፃ እያከናወኑ ይገኛሉ። በዚህ ተግባራቸው ደግሞ እጅግ ደስተኛ ናቸው። አገልግሎት መስጠት፣ የተቸገረን መርዳት፣ ላጣ መድረስና መስጠት ከምንም ከማንም በላይ የሚያረካውና የሚያስደስተው እራሱ አድራጊውን ግለሰብ ወይም ማህበረሰብ ነው የሚል ጠንካራ እምነት አላቸው። እሳቸውም ሲሰሩ በዚሁ እምነትና መንፈስ ሲሆን ባላቸው ሙያና እውቀት ሁሉ ማህበረሰቡን ቢያገለግሉ ደስተኛም ናቸው።
“የተለያዩ ሙያዎች ባለቤት ነኝ። ብዙ ነገሮችን ሰርቼ አውቃለሁ። የሙዚቃ መሳሪያዎችንም እጫወታለው። የምግብ ዝግጅት እውቀትም አለኝ። በጋራ የምግብ አቅርቦት ድርጅትም ነበረን።” የሚሉት አቶ እሸቱ፤ ይህ ሁሉ ፍላጎት ሙያና አቅም እያላቸው ግን በሁሉም ዘርፍ መስራት አልቻሉም። በእነዚህ ዘርፎች የሚያሰራቸው አካል ካለ ግን አብረውም ሆነ በግል ሊሰሩ ዝግጁ መሆናቸውን ይናገራሉ።
አቶ እሸቱ እንደሚናገሩት፤ ከዚህ በፊት መንግስት በሰጣቸው ቦታ ላይ በማህበር ተደራጅተው “እሸቱ ፋንታነሽና ጓደኞቻቸው የምግብ ዝግጅቶችና የሀብት ሽርክና ማህበር” በሚል ስያሜ የምግብና ተያያዥ ነገሮችን፤ በተለይም በዋናነት እንጀራ በመጋገርና ለተለያዩ ድርጅቶችና ግለሰቦች በማቅረብ ስራ ላይ በመሰማራት እራሳቸውንና ቤተሰቦቻቸውን ደጉመው ይኖሩ ነበር። ይሁንና ቦታው ለመልሶ ማልማት በመፈለጉ ምክንያት ከአካባቢው ሊነሱ ችለዋል። በምትኩ ሌላ አካባቢ ቦታ ቢሰጣቸውም ለግብይት ምቹ ባለመሆኑ ምክንያት ገበያ ማግኘት አልቻሉም።
በምትክ የተሰጣቸው ቦታ ወደ ውስጥ የገባና በምንም መልኩ እነሱ ከሚሰሯቸው ስራዎች ጋር አብረው የሚሄዱ ባለመሆናቸው ምክንያት ገበያ መቀዛቀዙን ይናገራሉ። ይሁንና እነ አቶ እሸቱ አሁንም ድርጅቱን አልዘጉትም፤ ወደ ፊት ጥሩ ቀን ይመጣል በማለት እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ። እርግጥ ነው የተወሰኑ አባላት ስራው በመቀዛቀዙ ምክንያት እየወጡ ወደ ሌላ ቢሄዱም በቀሩት አባላት ድርጅቱ ጨርሶ እንዳይዘጋ በማድረግ እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ።
አቶ እሸቱ ከድጋፍ ጉዳይ ጋር በተያያዘም የምጣድና የጣሪያ እድሳት የሚያደርግላቸው ሰው ቢገኝ እንደገና በሚገባ መንቀሳቀስ እንደሚቻል ይጠቁማሉ። ‹‹የገበያ ትስስር የሚፈጥርልን አካል ቢገኝ የበፊቱን አይነት ገበያ መልሶ ማምጣት ቀላል ነው። ችግሩ እነዚህን ወገኖች ማግኘት፤ ወይም ከእንደዚህ አይነት ሰዎች ጋር መገናኘትና መስራት አለመቻሉ ነው። የኢትዮጵያ ህዝብ ቸር ነው። መረዳዳትና መደጋገፍ ይወዳል፤ ያደርጋልም። ችግሩ መገናኘት አለመቻሉ ነው።›› ይላሉ።
‹‹እኛ በያዝነው ሙያ ብዙ መስራት እንችላለን። ካስፈለገም በትንሽ ስልጠና እንደገና የሚያበቃን ቢገኝ የበለጠ እንሰራለን›› የሚሉት አቶ እሸቱ፤ በአሁኑ ሰአት “ፍቅር ያሸንፋል”ን አይነት ብዙ በጎ አድራጎት ድርጅቶች እየተፈጠሩና በተለይ ወጣቱ በዚሁ ዘርፍ እየተሰማራና አቅመ ደካሞችንም ሆነ አካል ጉዳተኞችን በመርዳት ላይ መሆኑንና ይህም የሚደነቅና የሚበረታታ እንደሆነም ይናገራሉ።
አካል ጉዳተኝነትን በተመለከተም “የበረንዳው መብራት ጠፋ እንጂ የሳሎኑ ይበራል” ያሉት አቶ እሸቱ፤ አይነ ስውር መሆናቸውን ከአይናማዎች ያነሰ አድርገው ባለመውሰድ እየኖሩ እንደሚገኙ ያስረዳሉ። ‹‹አካል ጉዳተኝነት፤ ወይም አካል ጉዳተኛ መሆን ምንም ማለት አይደለም። አካል ጉዳተኝነት ማለት የሃሳብ ማጣት ማለት ነው። አንድ ሰው ሃሳብ ካጣ ነው አካል ጉዳተኛ የሚባለው። ሃሳብ ያለው ሰው አካል ጉዳተኛ አይደለም። ሃሳብ ካለ ምንም የሚያግድ ነገር የለም። እኔ አንድም ቀን አካል ጉዳተኛ ነኝ ብዬ ለልቤ ነግሬው አላውቅም።›› ይላሉ።
አንድ ሰው አካል ጉዳተኛ ሊባል አይገባውም። መባል ያለበት “ጉዳተኛ” እና “ጉዳት አልባ” ነው። አካል ጉዳተኝነት ከሁለት በኩል ሊመጣ ይችላል፤ ወይ ከፈጣሪ፣ ወይም ከሰው ሰራሽ አደጋ። ስለዚህ ማንኛውም ሰው ከአደጋና አካል ጉዳተኝነት ነፃ ነኝ ማለት አይችልም። ጤነኛ እስከሆነ ድረስ ዝም ብሎ መስራት እንዳለበት ያመለክታሉ።
አቶ እሸቱ እንደሚናገሩት ከሆነ የቤት ተመንን በተመለከተ ያለው አሰራር ሁለት አይነት ሲሆን፤ እሱም “ተመን” እና “ተመን አልባ” በሚሉት ስር የሚያርፍ ነው። በዚሁ በወረዳው አሰራር መሰረት የእሳቸው ቤት በተመን አልባ ስር በማረፏ ምክንያት እስካሁን አልተተመነችም።
ይህ ደግሞ በአቶ እሸቱና መሰሎቻቸው ላይ ቅሬታን ፈጥሯል። የቅሬታቸው ምንጭም ቤታቸው እንደማንኛውም ሰው ቤት ሊተመንላቸው፣ ግብር ሊከፍሉና የባለቤትነት መብታቸው ሊከበር፣ ቦታው ለልማት ተፈልጎ እንኳን መነሳት የግድ ቢሆን በምትኩ ሌላ ተለዋጭ ቦታ ተሰጥቷቸው ሊነሱ ይገባልና ነው።
በእርግጥ “’አሁን ጉዳዩን እያየነው ነው’ የሚል ነገር ሰምቻለሁ፤ በመሆኑም ጥሩ ነገር፣ እኛን የማይጎዳ ውሳኔ እጠብቃለሁ።” የሚሉት አቶ እሸቱ፤ ወደ ፊት ይህ ሁሉ ችግር ተፈትቶ ቢያንስ ልጆቻቸው ከእንደዚህ አይነት ኑሮ በመውጣት የተሻለ ህይወት እንደሚኖሩ ተስፋ እንዳላቸው ተናግረዋል። እኛም ለአቶ እሸቱና ቤተሰቦቻቸው ይህንኑ እንመኛለን።
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 10/2013