ሞገስ ጸጋዬ
የበረሃ አንበጣ መንጋ ዳግም በአፍሪካ ቀንድ በመከሰት ሰብሎችን በማውደም በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎችን የምግብ ዋስትናቸውን አደጋ ሊጥል እንደሚችል የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አሳሰበ።
ባለፈው ወር በኢትዮጵያ እና በሶማሊያ በሰፊው ለመራባት አመቺ የአየር ሁኔታ እና የዝናብ መጠን ስላለ የአንበጣ መንጋው በሚቀጥሉት ወራት የበለጠ እንደሚጨምር እና ጉዳት ሊያደርስ እንደሚችል አስገንዝቧል፡፡
አዲሱ የአንበጣ መንጋ በሰሜናዊ የኬንያ አካባቢን ምልክቶች እየታዩ ሲሆን፤ ለኤርትራ፣ ለሳውዲ አረቢያ፣ ለሱዳን እና ለየመን አዲስ ስጋት ሆኗል ብሏል፡፡፡ በተደጋጋሚ በድርቅ፣ በግጭት፣ የምግብ ዋጋ እና በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ለተጎዱ የአፍሪካ ቀንድ የህብረተሰብ ክፍሎች፣ በፈረንጆች አዲስ ዓመት መጀመሪያ ላይ እጅግ ለከፋ ችግር ሊደርስበት ይችላል ሲል ግምቱን አስቀምጧል፡፡
በከፍተኛ የምግብ እጥረት እና በድህነት በተጎዱ ሀገሮች ውስጥ በዓመት 18 ሚሊዮን ሰዎችን ለመመገብ የሚያስችል በግምት ወደ 2 ነጥብ 7 ሚሊዮን ቶን የሚገመት የእህል መውደምን መቆጣጠር ቢቻልም፤ ‹‹በሰብል አውዳሚ ተባዮች ላይ የሚደረገው ውጊያ ገና አልተጠናቀቀም›› ሲሉ የፋኦ ዋና ዳይሬክተር ክ ዶንግዩ ተደምጠዋል፡፡
እኛ ማወላወል የለብንም አንበጣዎች ቀን ከሌት እያደጉ በመሆናቸው እና አደጋዎችን በሚደርሱ ቦታዎች ሁሉ የምግብ እጥረትን እያባባሱ ነው ብለዋል፡፡
ከአጋሮች ጋር በመሆን በክትትልና ማስተባበር፣ በቴክኒክ ምክሮች፣ በአቅርቦቶች እና በመሳሪያዎች ግዥ እየረዳ ነው የሚለው ድርጅቱ በተጨማሪም የተጎዱ ማህበረሰቦችን የግብርና ፓኬጆችን፣ የእንስሳት እንክብካቤ፣ ለተራቡ እንስሳት የመኖ አቅርቦት በማቅረብ እስከ ቀጣዩ መኸር ድረስ መቋቋም እንዲችሉ ይደረጋል፡፡
በተጎዱት ሀገሮች የከፋ የምግብ እጥረትን ለመቀነስ ጥረቶች ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው የሚለው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በአንበጣ ለተጎዱ ሀገሮች ኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ሶማሊያ፣ ሱዳን እና የመን ውስጥ የክትትልና የቁጥጥር እንቅስቃሴን ለማሳደግ ተጨማሪ 40 ሚሊዮን ዶላር ያስፈልጋል፡፡
ያለ ተጨማሪ የገንዘብ ድጋፍ የቁጥጥር ጥረቶች ከጥር 2021 መጨረሻ ጀምሮ ሊቀዘቅዙ ወይም ሊቆሙ ይችላሉ፣ ይህ ደግሞ ከአንበጣ በተጨማሪ በአንዳንድ አካባቢዎች ሰብል የሚያወድሙ ተባዮች ቁጥር እንዲጨምር ሊያደርግ ይችላል ሲል አስጠንቅቋል። “ኑሯቸው ተጽዕኖ ያሳደረባቸው አርሶ አደሮች ተጨማሪ የበረሃ ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል እንዲሁም የበረሃ አንበጣን ለመቆጣጠር ሀገሮች አቅም መጠናከር አለበት” ብሏል፡፡
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 10/2013