ኢራን ኤጀንሲው ገለልተኛና ፍትሃዊ እንዲሆን ጠየቀች

ኢራን ከዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ ጋር የነበራትን ትብብር ለመቀጠል ኤጀንሲው ገለልተኛና ፍትሃዊ ሆኖ እንዲሠራ አሳስባለች። የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት መሱድ ፔዝሽኪያን ኤጀንሲው ኢራን በኒውክሌር መርሃ ግብሯ ጉዳይ ላይ ትብብር እንድታደርግለት ከፈለገ ገለልተኛ ካልሆነው ተግባሩ መቆጠብ እንዳለበት አሳስበዋል።

ፔዝሽኪያን ከአውሮፓ ካውንስል ፕሬዚዳንት አንቶኒዮ ኮስታ ጋር ባደረጉት የስልክ ውይይት፣ ኢራን ከኤጀንሲው ጋር የሚኖራት ትብብር ቀጣይነቱ የሚወሰነው ኤጀንሲው የኒውክሌር ልማቱን በተመለከተ የሚያራምደውን የፖለቲካ ተልዕኮ ያለው አቋም ለማስተካከል በሚኖረው ፍላጎትና ቁርጠኝነት ላይ እንደሆነ ገልፀዋል። ከዚህ በተጨማሪም በኢራን ላይ የሚቃጣ ሌላ ወረራ አደገኛና የሚፀፅት ምላሽ እንደሚያስከትል ፕሬዚዳንት ፔዝሽኪያን አስጠንቅቀዋል።

ባለፈው ወር ከተካሄደው የእስራኤልና የኢራን ውጊያ በኋላ በኢራንና በዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ መካከል ያለው ግንኙነት በእጅጉ ሻክሯል። ከሦስት ሳምንታት በፊት እስራኤል በኢራን የኒውክሌር ተቋማትና ወታደራዊ ጣቢያዎች ላይ ጥቃት መፈፀሟን ተከትሎ ሁለቱ ሀገራት ለ12 ቀናት የዘለቀ የአየር ውጊያ አካሂደዋል። እስራኤል በፈፀመቻቸው ጥቃቶች በርካታ የኢራን ከፍተኛ ወታደራዊ አመራሮችና የኒውክሌር ሳይንቲስቶች መገደላቸው እና የኢራን የኒውክሌር ተቋማትና ወታደራዊ ተቋማት መጎዳታቸው ተገልጿል።

የእስራኤልና ኢራን ውጊያ በተጀመረ በዘጠነኛው ቀን አሜሪካ በኢራን የኒውክሌር ጣቢያዎች ላይ ጥቃት መፈፀሟ ይታወሳል። ፕሬዚዳንት ትራምፕ ጦራቸው በፎርዶው፣ ናታንዝና ኢስፋሃን የኒውክሌር ጣቢያዎች ላይ የተሳኩ ጥቃቶችን መፈፀሙንና ጣቢያዎቹን ከጥቅም ውጭ ማድረጉን መናገራቸው ይታወሳል።

ይሁን እንጂ ትራምፕ ይህን ቢሉም ከአሜሪካ የስለላና ደህንነት ተቋማት ሾልኮ በወጣ ምስጢራዊ መረጃ፣ የአሜሪካ ጥቃቶች በኢራን የኒውክሌር ጣቢያዎች ላይ ያደረሱት ጉዳት ትራምፕ አክብደው በተናገሩት ልክ እንዳልሆነ ተገልፆ ነበር። በኒውክሌር ጣቢያዎቹ ላይ የደረሰው የጉዳት መጠን አወዛጋቢ ሆኖ ቀጥሏል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአቶሚክ ኃይል ኤጀንሲ ኢራን የኒውክሌር ቦምብ ለመሥራት የሚያስችል ዩራኒየምን እንደገና በወራት ጊዜ ውስጥ ማበልፀግ ለመጀመር የሚያስችል አቅም እንዳላት ይፋ አድርጓል። የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ራፋኤል ግሮሲ፣ አሜሪካ በሦስት የኢራን የኒውክሌር ተቋማት ላይ ያደረሰችው ድብደባ ከባድ ቢሆንም አጠቃላይ ውድመት አለመድረሱን ገልጸው ነበር።

‹‹እውነቱን ለመናገር አንድ ሰው ሁሉም ነገር እንወደመ እና ምንም የቀረ ነገር የለም ብሎ መናገር አይችልም። በወራት ጊዜ ውስጥ ጥቂት ማብላያዎችን በማሽከርከር የበለፀገ ዩራኒየም ያመርታሉ። የኢንዱስትሪ እና የቴክኖሎጂ አቅሞችን ይዘዋል። ስለዚህ ከፈለጉ ይህንን እንደገና መጀመር ይችላሉ›› ብለው መናገራቸው ይታወሳል።

ኤጀንሲው ገለልተኛ አይደለም ያለችው ኢራን ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአቶሚክ ኃይል ኤጀንሲ ጋር ያላትን ትብብር ለማቋረጥ የሚያስችሏትን ርምጃዎች እየወሰደች ነው። የኢራን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሀገሪቱ ከኤጀንሲው ጋር ያላትን ትብብር እንድታቆም ወስነዋል። ፕሬዚዳንት መሱድ ፔዝሽኪያንም የሀገሪቱ ምክር ቤት ባወጣው ሕግ ላይ ፈርመዋል። በሕጉ መሠረት የኤጀንሲው ባለሙያዎች ከኢራን ብሔራዊ የደህንነት ጠቅላይ ምክር ቤት ፈቃድና እውቅና ውጭ የኒውክሌር ጣቢያዎችን መጎብኘት አይችሉም። የኤጀንሲው ባለሙያዎችም ኢራንን ለቀው ወደ ቬይና ተመልሰዋል።

ከዚህ በተጨማሪም ኢራን የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ራፋኤል ግሮሲ የኢራን የኒውክሌር ጣቢያዎችን ለመጎብኘት ያቀረቡትን ጥያቄ ውድቅ አድርጋዋለች። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አባስ አራግቺ ‹‹የግሮሲ በቦምብ የተደበደቡ ጣቢያዎችን የመጎብኘት ጥያቄ ጎጂና ትርጉም የለሽ ነው። ኢራን ሕዝቧን፣ ሉዓላዊነቷንና ጥቅሟን ለመጠበቅ ማንኛውንም ርምጃ የመውሰድ መብት አላት›› ማለታቸው የሚታወስ ነው።

የኢራንን የኒውክሌር ጣቢያዎች የደበደበችው አሜሪካ ኢራን ጣቢያዎቹን ለኤጀንሲው ክፍት እንድታደርግ አሜሪካ ጠይቃለች። የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ታሚ ብሩስ፣ ኢራን ከኤጀንሲው ጋር የነበራትን ትብብር ለማቋረጥ መወሰኗ ተቀባይነት እንደሌለው ተናግረዋል። የፈረንሳይ፣ የጀርመንና የብሪታኒያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በጋራ ባወጡት መግለጫ ደግሞ፣ ኢራን የኤጀንሲውን ዋና ዳይሬክተር ጥያቄ ውድቅ ማድረጓን አውግዘው፣ ለኤጀንሲው ሙሉ ድጋፋቸውን ገልፀዋል።

ባለፈው ግንቦት ወር የወጣው የኤጀንሲው ሪፖርት እንዳመለከተው፣ ኢራን ባለፉት ሦስት ወራት የዩራኒየም መሣሪያዎች ምርቷን በ50 በመቶ አሳድጋለች። ይህ መጠን ለኑክሌር መሣሪያዎች ምርት በቂ ባይሆንም ለኃይል ማመንጫ ተግባር ከሚያስፈልገው የዩራኒየም መጠን ግን እጅግ የበለጠ ነው። ኢራን ግን ሪፖርቱን ‹‹ፖለቲካዊ ዓላማን ያነገበና መሠረተ ቢስ ውንጀላ›› ነው ብላ አጣጥላዋለች።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ዓርብ ሐምሌ 4 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You