በእምነት
“ከቀላሚኖ እስር ቤት ወደ አግቤ በመቀጠልም ከትንሽ ቀን በኋላ ወደ ተንቤን መምህራን ኮሌጅ ወሰዱን። የመከላከያ ሠራዊትን የከባድ መሳሪያ ድምፅ ሲሰሙ የ 90 ኪሎ ሜትር የእግር ጉዞ አስጀመሩን። ልክ 40 ኪሎ ሜትር እንደተጓዝን ከምሽቱ 2 ሰዓት አካባቢ ሲኖ ትራክ መኪና ከኋላችን መጣ። ተጓዡ ወደ 1 ሺ200 ሰው ነበር።
ከአስፋልት እንድንወጣ ካለመፈቀዱም በላይ ከአስፋልቱ መሀል ከወጣን ልዩ ሀይል ተኩሶ ይመታን ነበር። ከግራና ከቀኝ ገደላማ የሆነ ጠባብ ቦታ ላይ ስንደርስ ሲኖ ትራክ መኪና ልከው ከኋላችን ነዱብንና የሚገድለውን እየገደለ፣ ያቆሰለውን እያቆሰለ ሄደብን።
ይህንን ንግግር በስፍራው ለሚገኘው የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ዘጋቢ የተናገረው የሰሜን እዝ የጥገና ባለሙያው የነበረው ሃምሳ አለቃ ደረጀ አንበሳ ነውⵆ ይህ ሰው በሙያው አገሩን ሌት ተቀን ከማገልገልና እንደማንኛውም የመከላከያ ሰራዊት አባል ለትግራይ ህዝብ በችግሩና በደስታው ጊዜ ከጎኑ በመቆም አጋርነቱን ከማሳየት ሌላ ማንን እንደበደለ አያውቅም።
የህዝብና የአገር ከለላና መከታ የሆነው የኢፌዴሪ መከላከያ አባል እንደመሆኑም አንድም ቀን በአገር ልጅ የክህደት ተግባር ይፈጸምብኛል ብሎም አልጠረጠረም፤ ነገር ግን ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም ባንዳው ህወሓት አስቦት የማያውቀውን በደል አደረሰበት ፤ ሊረሳው ከልቦናው ሊያወጣው የማይችለውን መከራና ስቃይ በእርሱና በጓደኞቹ ላይ አዘነበባቸው፤ ይህንን የጭካኔ ጥግ የሆነ ተግባር ደግሞ በአይኑ እንዲያይ ተገደደ።
በወቅቱ ስለነበረው ሁኔታ ሲያስረዳ “ሴቶችም ህፃናትም አብረውን ነበሩ ማን እንደሞተ ማን እንደተረፈ እንኳን አላውቅም ፤ በሕይወት የተረፋትም ተበታተኑ፤ አንዳንዶቹም ቆስለው ወደ ጫካው ገቡ፤ የሞቱትም እዛው ቀሩ። የሞቱ ልጆችን እንኳን ለመለየት አልቻልኩም፤ አጠገቤ ነው እየጮሁ የሞቱት፤ ምንም ልረዳቸው አልቻልኩም፤ እኔንም አንድ እግሬን አገኘኝና እግሬ ከተሰበረ በኋላ ተንከባልዬ ጉድጓድ ውስጥ ገባሁ”።
ታዲያ የጭካኔ ጥጉ የት ነው? ለዛውም በራስ ወገን ለ 20 ዓመታት ከጠላት በተከላከለ ፣ አርሶ፣ አርሞ፣ አጭዶና ከምሮ እህል ባበላ ሰራዊት ላይ በተለይም ደግሞ ኢትዮጵያዊ ነኝ ሃይማኖት አለኝ ከሚል አካል ይህ መሆኑ ያሳዝናልም ያሳፍራልም፣ በጣም የሚያሳዝንና የሚዘገንነው ለሰሚውም ግራ የሆነ ድርጊት ነው። ብቻ በሰማይ የፈጣሪ በምድር ደግሞ የሰው ፍርድ አለና እርሱን መጠበቁ ይሻላል።
ይህ የአገር ክህደት የእናት ጡት ነካሽነት በሰራዊቱ ላይ ብቻ የተፈጸመ ነው ማለት አይቻልም፤ ጥቃቱ በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ የተሰነዘረ ለህዝቡ ያላቸውን ጥላቻ ያንጸባረቁበት እኩይ ተግባር መሆኑን ዓለም ሊያውቅ ሊገነዘብ ይገባል።
እነዚህ የእናት ጡት ነካሾች ለዓመታት ያገለገላቸውን ሰራዊት በዚህ መልኩ ክብሩን ገፈው ህይወቱን አካሉን አሳጥተውታል ፤ ይህ ሰራዊት እኮ ሌሊት እየተነሳ አጨዳ የሚያጭድ፤ ኮረና ገባ ሲባል ካለው ላይ ሳይሆን ከሌለው ላይ ገንዘብ እያዋጣ ህዝቡን የሚደግፍ ፣ ከደሞዙ እያስቆረጠ የልማት ስራዎችን የሚሰራ ነበር፤ ዳሩ እነሱ ለትግራይ ህዝብ ቆምን ይበሉ እንጂ የራሳቸውን ኪስ ሲሞሉ፣ ልጆቻቸውን አውሮፓና አሜሪካ ሲያንደላቅቁ፣ አማርጠው ሲበሉና ሲጠጡ አልፎ ተርፎም እኩይ ምግባራቸው ነገ የት እንደሚያደርሳቸው ስለሚያውቁ ምሽግና ዋሻ ሲገነቡ ነው የኖሩት።
ለትግራይ ህዝብ ልማት ወደ ኋላ ብሎም የማያውቀውን ሰራዊቱን በዚህ መልኩ ማጥቃታቸውም ህዝቤ የሚሉትን እንኳን እንደማይወዱ ይልቁንም በስሙ እንደሚነግዱ ነው የሚያሳየው። ይሁንና ጁንታውና ተላላኪዎቹ በሰው ላይ ሊፈጸም ቀርቶ ለማሰብ የሚከብድ ድርጊት ፈፀሙ። የውጭ ጠላት እንኳን በመኪና ሰውን ደፍጥጦ ስለመግደሉ የተጻፈም ሆነ በአፈ ታሪክ የተነገረ ነገር አልሰማሁም።
ለዚህ የጭካኔ ተግባር ስያሜ ያጡለት የጦር ሃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጀነራል ብርሃኑ ጁላ “ጁንታው ባደረገው ልክ ሰው አውሬ ይሆናል ብለን አልገመትንም ነበር ” ሲሉ ተደምጠዋል፤ አዎን ሰው በዚህ ልክ በወገኑ ላይ አውሬ ይሆናል ብሎ ማንም ሊገምት አይችልም? የገመተም ካለ “ጠንቋይ” ሊሆን ይችላል ነው ያሉት።
ልክ ናቸው ይህንን ለመገመት ከባድ ነው፣ ይህንን አሳፋሪ የጭካኔ ተግባር ሰው በወገኑ ላይ ይፈጽመዋል ብሎ መገመት ቀርቶ አሁን ከሆነ በኋላ እንኳን ማመን የከበደን ብዙዎች አለን ፤ ምክንያቱም ሰው ናቸው ብለን ስለምናስብ፣ ያም ሆነ ይህ ግን እነሱም የጭካኔያቸውን ልክ አሳይተውናል፤ የህዝብ ልጅ የሆነው መከላከያ ሰራዊታችንም እንዳልነበሩ አድርጎ ከአፈር ቀላቅሏቸው ጀግንነቱን ዓለም እንዲመሰክር አድርጓል፡፡
ከዚህ በኋላ ያለው ቀሪ ስራ ጀነራል ብርሃኑ ጁላ እንዳሉት “የጁንታው ቡድን ከመኪና ወርዶ እግረኛ ሆኗል”፤ ይህንን እግረኛና የት እንደሚሸጎጥ የጠፋበትን የዙር ድንብር የያዘውን ባንዳ አሳዶ በመያዝ ለፍርድ ማቅረብ ነው፣ ይህ ደግሞ በኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች እንዲሁም በህዝቦች ድጋፍና ትብብር በጥቂት ጊዜ ውስጥ ፍጻሜውን አግኝቶ ለፈጸሟት እያንዳንዷ ጭካኔ ላሳዩን ንቀትና ጥላቻ በህግና በህግ ብቻ የእጃቸውን ያገኛሉ የሚል እምነት አለኝ፡፡
ትእግስትና ፍቅር ፍራቻ የመሰላቸው ከእነሱ በላይ ጀግና እንደሌለ የታሰባቸው የጁንታው አባላት አሁን መውጫ ቀዳዳው ጠቧቸዋል፤ በቀጣይም አለን የሚሉትና በገንዘባቸው የገዙት የውጭ ተላላኪዎቻቸው ሳይቀሩ እንዲያፍሩባቸው ይሆናል፣ ያሳዩንን የጭካኔ ጥግ እኛ ደግሞ ህግና ህግን ብቻ መሰረት በማድረግ የእጃቸውን ልንሰጣቸው ይገባል፡፡
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 10/2013