ኢትዮጵያዊነት በደስታም ሆነ በመከራ ጊዜ ደስታንና ችግርን አብሮ መካፈል ነው። ኢትዮጵያውያን በዘመናት የአብሮነት ቆይታቸው ጠላትን አብረው መክተዋል፤ በዱር በገደሉ ተዋድቀዋል፤ ጠላትን አሳፍረውና ድል ተቀዳጅተው በጀግንነት ማማ ላይ አብረው ነግሰዋል። ሀገራቸውን አላስደፍርም ብለው ደማቸውን አፍሰዋል፤ አጥንታቸውን ከስክሰዋል።
የትግራይ ህዝብም በተለያዩ ዘመናት የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት በማስከበርና ሀገሪቱን ከውጭ ወራሪ ኃይል በመታደግ ረገድ የማይተካ ሚና ሲጫወት የቆየ ህዝብ ነው። በሀገር ውስጥም ቢሆን የፊውዳልና የደርግን አምባገነን አገዛዝ በመታገልና ነጻነትና ፍትህ በሀገሪቱ እንዲሰፍን በርካታ መስዋዕትነቶችን የከፈለ፤ ለነጻነቱ ቀናኢ የሆነ ኩሩ ህዝብ ነው።
በተለይም አምባገነኑን የደርግ አገዛዝ ገዝግዞ ለመጣል በተደረገው እልህ አስጨራሽ ትግል ውስጥ የትግራይ ህዝብ የከፈለው መስዋዕትነት በቀላሉ የሚታይ አይደለም። ይህ ህዝብ ከ60-100 ሺህ የሚገመቱ ልጆቹን ህይወት ገብሮና በሚሊየን የሚቆጠሩትን ለአካል ጉዳት ዳርጎ ለፍትህ፤ ለነጻነትና እኩልነት ታግሏል።
ሆኖም ግን የትግራይ ህዝብ የከፈለው መስዋዕትነት በህወሃት ጁንታ ተጠልፎ ከዳር ሳይደርስ መክኖ ቀርቷል። የትግራይ ወጣቶች የሞቱለት እኩልነት፤ ዴሞክራሲና ፍትህ ተዘንግቶ በአንጻሩ በጀግኖቹ ደላይ አምባገነንነት፤ ሌብነት፤ አድርባይነት፤ ከፋፋይነትና ጸረ ኢትዮጵያዊነት ነግሶ ህዝቦች የከፋ ህይወት እንዲገፉ ተፈርዶባቸው ቆይቷል። ከሁሉም በመረረ መልኩ ደግሞ የትግራይ ህዝብ ፍጹም ፈላጭ ቆራጭ በሆነ የጁንታ መዳፍ ውስጥ ወድቆ የመከራ ጽዋ ሲጨልጥ ቆይቷል።
የትግራይ ህዝብ ሌላው ቢቀር ንጹህ የመጠጥ ውሃ እንኳን በወጉ አግኝቶ አያውቅም። ዛሬ በርካታ የሀገራችን ከተሞች ያሳኩት የመጠጥ ውሃ አቅርቦት ለመቀሌና አክሱም ነዋሪዎች ዛሬም የቅንጦት ያህል ሩቅ ነው። ይባስ ብሎ ደግሞ ጁንታው የትግራይ ህዝብ የሚገለገልባቸውን መንገዶች፤ ድልድዮች፤ ሰልክ፤ መብራት፤ ባንክ እና አውሮፕላን ማረፊያ በማውደም አሳፋሪ ተግባር ፈጽሟል። ግብዓተ መሬቱ መቃረቡን ያወቀው ይህ የጥፋት ኃይል የህዝቡን መገልገያዎች በማውደም እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል ካለችው እንስሳ የከፋ አስተሳሰብ እንዳለው አሳይቷል።
ዛሬ የትግራይ ህዝብ ጨቋኝ ከሆነው አገዛዝ ተላቆ የነጻነት አየር መተንፈስ ቢጀምርም ጁንታው ትቷቸው የሄዱ የስነልቦና ጠባሳዎች በጋራ ክንድ ሊታከሙ ይገባል። በኢትዮጵያዊነቱ የማይደራደረው የትግራይ ህዝብ ዛሬ የኢትዮጵያን ህዝብ የሞራል ድጋፍ የሚፈልግበት ወሳኝ ወቅት ላይ ይገኛል። በዚህ ወሳኝ ወቅት ፍቅርን፤ መተሳሰብን፤ መተባበርንና አለሁልህ ባይነትን ይፈልጋልና ሁሉም ኢትዮጵያዊ ከትግራይ ወገኑ ጎን መቆሙን በገቢር ሊያሳይ ይገባል።
በሌላም በኩል የህወሃት ቡድን የጥፋት ሃይል በመከላከያ ሰራዊት ላይ በከፈተው አሳፋሪ ጥፋት ክልሉ ከአንድ ወር ላላነሰ ጊዜ በቀውስ ውስጥ ቆይቷል። ስለሆነም ዕለታዊ እንቅስቃሴዎች በመስተጓጎላቸው ዕለት ተዕለት አስፈላጊ የሆኑ ፍጆታዎች እጥረት አጋጥሟል። ይህንኑ ሰብኣዊ ቀውስ ለመታደግም የኢትዮጵያ መንግስት የምግብ፤ አልባሳትና የህክምና ቁሳቁሶች ድጋፍ እያደረገ ቢሆንም ኢትዮጵያ ህዝብ የዜግነት ግዴታ ያለበት በመሆኑና ችግሩን መንግስት ብቻውን እንዲወጣው ከመተው ሁሉም የዜግነት ድርሻውን ቢወጣ ችግሩን በአጭር ጊዜ ማለፍ ይቻላል። ስለዚህም የኢትዮጵያ ህዝብ ያለውን በማካፈል ወገናዊነቱን ሊያረጋግጥ ይገባል።