ዋቅሹም ፍቃዱ
በሳዉዲ ዓረቢያ ከተለያዩ አገራት ተሰደው የመጡና ህጋዊ ፍቃድ የሌላቸው በመቶዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች በአገሪቱ ማጎሪያ ጣቢያ ውስጥ በርካታ የመብት ጥሰት እየተፈጸመባቸው እንደሚገኙ አልጀዚራ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅትን ሪፖርትን ጠቅሶ የዘገበ ሲሆን፤ እንደ ዘገባው ከሆነ ስደተኞቹ ከኤሺያ እና ከተለያዩ የአፍሪካ አገራት የተሰደዱ ሲሆኑ ከአፍሪካም በርካቶቹ ኢትዮጵያዊያን ናቸው።
የአገሪቱ ፖሊሶች ህጋዊ ያልሆኑ ስደተኞችን አሳደው በመያዝ ወደ አገራቸው እንዲመልሷቸው የሳውዲ መንግሥት ባዘዘው መሰረት ወደ ማጎሪያ ጣቢያ ካስገቡ በኋላ በርካታ የመብት ጥሰቶችን እየፈፀሙባቸው እንደሚገኙ የአልጀዚራ ዘገባ አስታውቋል፡፡
የሳዉዲ ፖሊሶች ህገ ወጥ ያሏቸውን በርካታ ስደተኞች በማጎሪያ ጣቢያው ጠባብ ክፍል ውስጥ በማስገባት በብረት የተለጠፈ ዱላን በመጠቀም እንደሚደበድቧቸው ብቻ ሳይሆን የተለያዩ አካላዊ ጥቃቶችንም እንደሚፈጽሙባቸው አልጀዚራ የድርጅቱን ሪፖርት ጠቅሶ የዘገበ ሲሆን፤ ባለፍው ጥቅምትና ህዳር ወር ብቻ በደረሰባቸው የከፋ ጉዳት ሶስት ስደተኞች ህይወታቸው ማለፉንም አመላክቷል፡፡
የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቱ በማጎሪያ ጣቢያው የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ወደ አገራቸው እየተመለሱ ሁለት ህንዶችን አናግሮ ይፋ ባደረገው መረጃ እንዳስታወቀውና አልጀዚራ እንዳቀረበው በማጎሪያ ጣቢያው በአንድ ጠባብ ክፍል ውስጥ እስከ 350 የሚደረሱ ስደተኞች ተፋፍገው ይኖራሉ። በዚህ ስቃይ ውስጥም ዓመት ያህል የቆዩ ሁለት ስደተኞች የሚገኙ ሲሆን፤ በማጎሪያው ውስጥ ከኮሮና ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ የሚደረግ ምንም አይነት ጥንቃቄ ባለመኖሩ አንዳንዶች ላይ የበሽታው ምልክት መታየት ጀምሯል። ይሁን እንጂ እስካሁን ምንም አይነት የተወሰደ እርምጃ የለም።
ስደተኞቹ ታፍነው በአንድ ጠባብ ክፍል ውስጥ በመሆናቸው በቂ እንቅልፍ አያገኙም።የሚተኙት ተራ በተራ ሲሆን፤ ግማሾቹ ቀን ሌሎቹ ደግሞ ማታ ይተኛሉ።በጣም የሚያሳዝነው ነገር ደግሞ ለስደተኞች ፍራሽ አይቀርብም።በተጨማሪ ማጎሪያ ጣቢያው ሰው ለአፍታም የሚቆይበት አይደለም፤ በጣም ከመቆሸሹ የተነሳም ሽንት ቤት ይመስላል ሲልም ይሄው የአልጀዚራ ዘገባ አመልክቷል።
በአጠቃላይ ሳውዲ ከሀብታም አገሮች ተርታ ብትመደብም ለስደተኞች አንደማትጠነቀቅ፣ በስደተኞች ላይ ኢሰብዓዊ ተግባራትን እንደምትፈፅምና አካላዊ ጉዳትን እንደምታደርስ በሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቱ ስር የሚገኙት የስደተኞች ጉዳይ ተመራማሪ ነድራ ሀርድማን መግለፃቸውን፤ ከአገሪቱ አጠቃላይ 33 ነጥብ 4 ሚሊዮን ህዝብ 12 ነጥብ 6 ሚሊዮን የሚሆኑና የገልፍ አገራት የኢኮኖሚ ጀርባ አጥንት በመባል የሚታወቁ ከሌላ አገር የመጡ ሰዎች መሆናቸውን አልጀዚራ ዘግቧል።
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 8/2013