መልካምስራ አፈወርቅ
አበው ሲተርቱ ‹‹የተናገሩት ከሚጠፋ የወለዱት ይጥፋ›› ይላሉ። ወዳጆቼ! ይህ አባባል የዋዛ አይምሰላችሁ። የሰው ልጅ ከምንም በላይ ለቃሉ ታማኝ መሆኑን ያመለክታል።ብዙዎች ከመናገራቸው በፊት ለአንደበታቸው ቃል ይጨነቃሉ። አንዳንዶችም ቀን ቆጥሮ፣ ጊዜ ታስቦ ስለሚከተላቸው መጠይቅ ቆም ብለው ያስተውላሉ። ለምን ? ካሏቸው ደግሞ የቃልን ታማኝነት ከሰማይና ምድር ማለፍ ጋር አያይዘው ከፈጣሪ ሀያልነት ጋር ያዛምዱታል። ደጋግመውም ‹‹ሰማይና ምድር ያልፋሉ ቃሌ ግን አታልፍም›› የምትለውን ሀረግ ይመዛሉ። እንዲህ ነው እንግዲህ የቃል ታላቅነት።
ወዳጆቼ! ዘንድሮማ ጉድ ፈልቷል። ቃል የምንለውን ታላቅ ጉዳይ ከመጤፍ ያልቆጠሩ እነ እንቶኔ ባሻቸው ሲበጠረቁ የኖሩበት ውሸት ያጋልጣቸው ይዟል። እናንተም መልሳችሁ እንዴት? ካላችሁኝ አብራችሁኝ ዝለቁ፣ ብዙ አወጋችኋለሁ።
እኔ እምለው! እንደው ባገሩ የትልቅ ቀላል በዝቷል ልበል ? ለነገሩ ታላቁስ ማን ሆነና ? ጉዳዩ የዕድሜ ነገር ከሆነ ማለቴ ነው። እንዲያ ከተባለማ ባለ እንጨት ሽበቶቹን ቆጥረን አንፈጃቸውም። እኛ እምናውቀው ብልሆች ስልጣን ሲይዙ ስለሚናገሩት እውነት መጨነቃቸውን ነው። እኛ የሚገባን ዘመን ካለፈ በኋላም እነ እከሌ ምን ብለው ነበር ? ተብሎ ታሪክ መወሳቱን ነው። እውነታውን ለባለታሪኮች እንተወውና በምላስ ጥሬ መቁላት መለያቸው ስለሆኑት ጁንታዎች ጥቂት እንታዘብ።
ወዳጆቼ! የውሸት ባህር ምንጩ ከወዴት ነው ? ቢባል መነሻውን ማወቅ ይቸግር አይመስለኝም። እነዚህ ‹‹ጁንታ›› ተብዬዎች በተለይ በሀገር ላይ ጦርነት ካወጁ ወዲህ ነጫጭ ውሸት ሲያጠግቡን ከርመዋል። ‹‹እኛን ብቻ እመኑን›› በሚል ትርክታቸውም ዓይናችሁን ጨፍናችሁ ስሙን ሲሉን ቆይተዋል።
እነሱ ሁሌም ታንክ ደምሳሽ፣ አውሮላን ጣይ ናቸው። እነሱ በየቀኑ መቶዎችን ማርከው፣ ሺዎችን ገዳይ ናቸው። ምን ይሄ ብቻ! ለዚህ ጀግንነታቸው ዓለም ሁሉ ከጎናቸው ስለመቆሙ ሲነግሩን፣ ሲደሰኩሩልን ከርመዋል።
ሁሌም እንደሚሉን ጦርነት ለእነ ጁንቴ ባህላዊ ጨዋታ ነው። ከደማቸው የተዋሀደ፣ ከአጥንታቸው የተማገረ ድንቅ ስጦታ። ያለ እነሱም በአገሩ ጀግና ይሉት የለም። ወንድነትና ጀብዱ ከጁንታ ወዲያ ላሳር ነው።
መች ይሄ ብቻ! በታሪካቸው ጠላትን ከመደምሰስ ውጭ የእነሱ ጫፍ ተነክቶ አያውቅም። ሁሌ የሚቀነቀነው ዘፈናቸውም በምሽጎቻቸው ጠላቶቻቸው ብቻ እንደሚቀበሩ ነው። በእነሱ ቤት ምሽጉና ዋሻው የእንግዶች መቀበያ መሆኑ ነው። ጉድጓዱ ደግሞ የእረፍት ማሳለፊያ። ‹‹ኡኡቴ!›› አለች ሴትየዋ። ድንቄም ምሽግ ! አየነው እኮ መደበቂያውን፣ ለክፉ ቀን እንደ አይጥ መማስ የጀመሩት ሸለቆ ማለፊያ ሳሎን አይደል እንዴ ? ሸጋ መኖሪያ።
የዛሬን አያድርገውና አንድ ሰሞን በቴሌቪዥን መስኮቶቻቸው ብቅ እያሉ አሳፋሪ ወሬዎቻቸውን ጋቱን። ባላሳዩን ምስል፣ የሰላ ምላስ አክለውም ‹‹በሞቴ እመኑን›› አሉ ። ባናምናቸውም ሰማናቸው ። እየሰማንም ታዘብናቸው። በመቶ ሺዎች የሚቆጠር ሰራዊት ማረክን፤ አውሮፕላን ጣልን፤ ጄኔራሎችን አቆሰልን፤ በሚሳኤል አዲስ አበባን ልንደበድብ ነው የሚሉ የምላስ ጀብዱዎች አንድ ሰሞን በሳቅ የሚያፈርሱ ጥሩ መደበሪያዎቻችን ነበሩ።
ውጊያው በተጀመረ ሰሞን በአፋቸው የደረደሩትን ምርኮ ለማየት ተጣድፈን የተባለውን እስኪታክተን ልንቆጥር ጣቶቻችንን አሰላን። የበዙ ምርኮኞችን ፈለግን፣ ጥለነዋል ያሉንን አይሮፕላን ጭስ አሻግረን ቃኘን፣ አንዳቸውም የሉም። አንዳቸውም።
ከእሱ ይልቅ በአርባ አምስት ደቂቃ ኦፕሬሽን የወገንን ጦር እንዴት እንደከዱት በሙሉ ልብ ሲተርኩ አንገታችንን ደፋን። በማይካድራ ሰማይ ስር የፈጸሙትን ጊዜ አይሽሬ ታሪክ ሰምተን ከልብ አነባን፤ በአሳፋሪው ጉዳቸው ተሸማቀንም፤ በእጅጉ አዘንን። ደግሞም መለስ አሉና በሀገር ላብና ወዝ የተገነቡ ሀብቶችን ስለማውደማቸው አሳዩን።
አለፍ ብለው ደግሞ ‹‹እንሞትልሀለን›› ሲሉት የነበረውን ህዝብ እንዴት እየገደሉት እንደሆነ አስመሰከሩ። ለእስትንፋሳቸው ማራዘሚያ ሲሉም ህዝቡ አለኝ የሚለውን መሳሪያ ይዞ እንዲዘምት ቀሰቀሱ። እነ አጅሬው በዘመናዊ መሳሪያ ታጅበው የድሀውን ልጅ ድንጋይና ማማሰያ ይዘህ ውጣ አሉት። የእነሱን ልጆች ከባህር ማዶ አስቀምጠው ህጻናትን ከእናቶች ጉያ ነጠሉ። ለማይጠቅመው ጦርነትም በእሳት ወላፈን ማገዱ።
እናንተዬ! ‹‹ለሀገርና ለወገን እንሞታለን›› ባዮችን ጉዳይ ሳወሳ የአፍቃሪው አዝማሪ ግጥም ትውስ አለኝ። አዝማሪው ባልንጀራው ከልብ ትወደው መስሎት ብዙ ሲያስብ ኖሯል አሉ። ይህች ሴት ባገኘችው አጋጣሚ በውሸት ‹‹ልሙትልህ፣ ልቀበርልህ›› ስትለው ከርማለች። ታዲያ አንድቀን ነገሩ ሁሉ እንዳልሆነ ሲገባው መሰንቆውን ከተሰቀለበት አውርዶ ይገዘግዝ ያዘ።
እሞትልሀለሁ አላልሽም ወይ፡-
እንኳን ልትሞችልኝ ታመምሽልኝ ወይ፡-
እያለ አንጎራጎረ። በወቅቱ ዜማውን የሰሙና ጉዳዩን የሚያውቁ፤ ከልብ አዘኑ። ወዳጅ ተብዬዋ ግን ወትሮም አፍቃሪው አልነበረችምና ቅኔው አልገረማትም። የጁንታዎችና የትግራይ ህዝብ ጉዳይም ቢሆን እንዲሁ ነው። አስቀድመው ከልብ ባልሆነ ፍቅር ሲያሞኙት ኖረዋል። በቃላት ደልለውም ሀብት ንብረቱን፣ ጉልበትና አቅሙን በዝብዘዋል። የጣፈጠውን ሰልቅጠውም፣ ትራፊያቸውን ነፍገዋል።
አዝማሪው እንዳለው እነሱ ለህዝቡ ሊሞቱለት ቀርቶ የዕንቅልፍ ታህል እንኳን ሸለብ አላደረጋቸውም። ትናንት ለራሳቸው ጥቅም እንደሮጡት ሁሉ ዛሬም ‹‹እግሬ አውጭኝ›› ሲሉ ፈርጥጠዋል። አሁን ምቾት ይሉት መንደላቀቅ ህልም ሆኗል። ጦጣ ይመስል የሚዘሉበት ገደል ሳይቀር የተጸየፋቸው ይመስላል።
ይገቡበት ይደበቁበት የጠፋቸው ጁንታዎች ከቀናት በፊት ይንደላቀቁባቸው የነበሩ ዘመናዊ መኪኖቻቸው ኩራት አልሆኗቸውም። ፊታቸውን በሽርጥ ሸፍነው፣ ማንነታቸውን ደብቀው የሚባዝኑባት ምድር የወገኖችን የስደትና ስቃይ እውነታ ልታሳያቸው ቆርጣለች።
ትናንት በግፍ የገረፏቸው፣ በሀዘናቸው የተሳለቁ፣ በዕንባቸው የሳቁ ክፉዎች ዛሬ ጊዜ ጠብቆ ይከፍላቸው ይዟል። ባሰሩበት ገመድ ሊታሰሩ፣ በሰፈሩት ቁና ሊሰፈሩ፣ እንዲህ ሆኖ ጽዋው ሞልቷል። አሁን ሁሉም ኢትዮጵያዊ ፍትህን ይፈልጋል፣ የእውነት ፍርድንም ይሻል።
እናንት ጁንታዎች! እስከዛሬ የዜጎችን ነጻነት በግፍ አፍናችሁ ቆያችሁ። የስልጣን ክብራችሁን ተጠቅማችሁ ህዝቡን የደም ዕንባ አስነባችሁ። ሀገርን በብሄርና ቋንቋ ከፍላችሁ እርስ በርስ አፋጃችሁ። ያም ሆኖ እውነቱን አሳምራችሁ ታውቁት ነበር። ለመላው ህዝብ የክፉ እከክ ያህል መሆናችሁን። ደግነቱ እንደሾላ ፍሬ እርግፍ ማለት ይዛችኋል። እንግዲህ ጎበዝ ! ‹‹የጊዜ እንጂ የሰው ጀግና የለም ይሏል›› ይህ ነው።
‹‹ጁንታዎች ሆይ !›› ዛሬ ላይ በእናንተ ናፍቆት ዓይናችን እንዲህ ሊዋትት ትናንት በመከረኛ ሚዲያችሁ ብዙ ብላችሁን ነበር። በፍጥነት ከአራት ኪሎ ቤተመንግስት ገብታችሁ ከአረንጓዴው ሳሎን የቀጥታ መልዕክት ልታደርሱን ቀጠሮም ነበራችሁ። ከድል ብስራቱ አጋርታችሁን ስታበቁ እልም አላችሁሳ ! የታላችሁ ! ‹‹አረ ቃል ይከበር! ቃል ይከበር ›› አለ ዘፋኙ።
ቆዩኝማ ! ለመሆኑ የትናንትናዎቹ አጨብጫቢ ወዳጆቻችሁ ወዴት ሄዱ። እነ አክቲቪስት ነን ባዮች፣ እነ ፖለቲካ ተንታኞች፣ እነ ተቃዋሚ ደጋፊዎች፣ ምን ዋጣችሁ? ገባ ገባ በሉ እንጂ። ወይ ክፉ ቀን ! ትናንት የጁንታዎችን ዙሪያ እንደ እሳት እንዳልከበባችሁ፣ ዛሬ ውዶቻችሁ ብርድ ብርድ ሲላቸው ዝም ይባላል እንዴ? ዝም…፣ ጭጭ…።
እንደው እኮ! የሰው ነገር ይገርማል። አንዳንዱ እውነታውን እያወቀው ዓይኑን በጨው አጥቦ ላሞኛችሁ ማለትን ለምዷል። አንዳንዱ ደግሞ ‹‹ዶሮ ሲያውቅ ዶሮ ማታ›› ሆኖ መለፍለፍን ያውቃል። የጁንታዎችም ጉዳይ እንዲህ ሆኖ ከረመ። ዙሪያቸውን እንደ ገና ዳቦ እሳት እየነደደባቸው፣ በሱፍና ከረባት ታንቀው ሰላም ነን ሊሉን ሞከሩ።
በየቀኑ በሚያጎርሱን ሙዳ፣ ሙዳ መግለጫም የተለመደውን ድል በእጃቸው እንዳስገቡት ሲያወሩልን ከርመዋል። ፊታቸው ስጋት አጥልቶበት እያየን እንኳን ሊዋሹን ሲሞክሩ ነበር። በየጉድጓድ የወሬ ማቀናበሪያቸው መሽገው የአልሞት ባይ ተጋዳይነታቸውን ገጽታ አስኪበቃን አስነብበውናል።
ደግነቱ ጉምቱ ባለስልጣኖቹ በጀመሩት ዝነጣ አልቀጠሉም። ዋል አደር ብለው የአንገታቸውን ከረባት አሽቀነጠሩ። ከትከሻቸው የቀድሞ ሽርጣቸውን ጣል አድርገውም እንደለመዱት ድሉ በእጃችን ነው አሉ። ዳሩ በፊታቸው ያለው ፍርሀት ማሳበቁን አልተወም። የአንደበታቸውን ንግግር የግንባራቸው እውነት እያጋለጠው ራሳቸውን ሲሸነግሉ ቆዩ።
በሞቀ ሙዚቃና በደመቀ ከበሮ የጦፈው ንግግር እንደጅምሩ አልቀጠለም። ጥቂት ቆዩና እንዳልተመቸው ቤት ተከራይ ቦታ ተቀያይረው አሳዩን። ንግግር አሳመርን ባዮቹ አሁንም ገጽታቸው አደናቅፎ ይጥላቸው ያዘ። እያሰለሱ በሚከፍቱት የሚዲያ አውታር ብቅ እያሉ ‹‹ አለን፣ ስሙን፣ እዩን አሉን።
ወዳጆቼ ! ለካስ ውሸት ከተጀመረ ማለቂያ የለውም። በየቀኑ ማረክን፣ ገደልን፣ ድል ነሳን ይሉት ጨዋታ አልታከታቸውም። የበሬ ወለደ ጨዋታቸው እንደደራ ቀናት ተቆጠሩ። ይህን ሲያደርጉ ከሞት አፋፍ የደረሰ ትንፋሻቸው ስቅታ አልያዘውም። ውሸት የለመደ አንደበታቸው ሁሌም ተስሎ እንደተዘጋጀ ካራ ነው። አይደንዝም፣ አይደነዝዝም። ማን ነበር ጁንታው ሞቶም መዋሸቱን አይተውም ያለው፤ ድንቅ አባባል።
‹‹ ከደጃፋችን ደረሰ ›› ያሉን የድል ዜና ውሎ አድሮ ደብዛው ጠፋ። እነሱም መደበቂያቸውን ምሰው ከጉድጓቸው መሸጉ። በሞት አፋፍ ላይ ሆነው ግን ንሰሀን አላሰቡም። ተላላኪያቸውን አሰማርተው የሀገር ሀብት እንዲወድም ተልዕኮ ሰጡ። ተወንጫፊ ሮኬቶች አስፈንጥረው ያሰቡትን ሞከሩ። ቦንብና ፈንጂ አዘጋጅተው የወገን ሞትን ደገሱ።
በዚህ ብቻ አልበቃም። ሊሰሙት የሚያስደነግጥ፣ ሊያዩት የሚከብድ የክፋት ድርጊት አከታትለው ቀጠሉ። ፋሺስቶች እንኳን በሌሎች ወገኖች ላይ ያደርጉታል የማይባል የጅምላ ጭፍጨፋን አካሄዱ። ሺዎችን ከነህይወታቸው በሲኖትራክ ወጡባቸው። የተረፉትን እያሳደዱ አሰቃይዋቸው።
እነዚህ የክፋት ሀይሎች እንደህልማቸው ያልሰመረ ዕቅዳቸው ቢከሽፍ በቃንን አልመረጡም። የመንግስትን ወሳኝ መሰረተ ልማቶች ለመቆጣጠር ሞከሩ። ድርጊቱን ለመከወን ደግሞ ለእነሱ ቀላል ነበር። ባለሙያው፣ ቆራጩና ፈላጩ በእጃቸው ነው። ጦር መሳሪያው፣ አውዳሚውና አጥፊውም በቅርባቸው።
ስለ ጁንታዎች ግፍና በደል ለመዘርዘር አመታት ላይበቁ ይችላሉ። ብዙዎች እንደሚሉትም ሰማይና ምድር ብራና ሆነው ታሪክ ይጻፍ፣ ቢባል የቀን ከሌት ጉዞ ኢምንት ይሆናል።
ወዳጆቼ ሆይ! ሀያ ሰባት የግፍና የመከራ ዓመታት ምንኛ ከባድ ነበሩ? ‹‹እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል›› ባዮቹ በራሳቸው ፍቅር ነደው ሀገርን ሲገድሉ ኖረዋል። ወገን በድህነት ቀንበር ተጠፍሮ ሲዋትት እነሱ አገር አሳድገናል፣ ለውጥ አምጥተናል፣ በሚል ትርክት ዓለምን ሲያሞኙ ኖረዋል። ለዚህ ደግሞ ዛሬ እንደደረቀ ዛፍ በየቦታው ተገትረው የቆሙ ህንጻዎቻቸውና በየሀገራቱ ከምረው ያስቀመጡት ዶላርና ወርቅ በትንሹ ምስክር ነው።
‹‹ሁሉን ቢያወሩት ሆድ ባዶ ይቀራል›› እንዲሉ ሆኖ የግፈኞችን ስራና ተግባር ዘርዝሮ ለማውራት ይህች ጊዜ በቂ አትሆንም። ደስ የሚለው እውነት ግን የትናንቱ ዘናጭ ጁንታ ዛሬ ባለኩታ ተጓዥ መሆኑ ነው።
ሁሌም መልካም ሰዎች በሌሎች ፊት ቀና ብለው ለመሄድ አያፍሩም። ይህ ሲሆን ትናንት የተጓዙበት መንገድ ለእነሱ የምቾት ትራስ ይሆናል። እነጁንታና ጁንቲት ግን አሁን የትናንቱ ግፍና በደል እየተከተላቸው ነው። ማንነታቸውን ቀብረው አካላቸውን የሸፈኑበት ሽርጥና ኩታም ከወገን ደምና ለቅሶ አይታደጋቸውም።
ጁንታዎች ሆይ! አሁን የፍጻሜው ጦርነት ተጠናቋል። እናንተም ከመጨረሻው የገደል አፋፍ ላይ ቆማችኋል። ከዚህ በኋላ ውሳኔው የእናንተ ይሆናል። ወደገደሉ መወርወረ፣ አልያም ወደሜዳው መመለስ።እነ ጁንቴ! ምርጫው አንድና አንድ ብቻ ነው። ጊዜ ይሉት የለም። ሀገራችን እናንተ ያወደማችሁትን ለመገንባት ሩጫ ላይ ነች። አሁን የልማትና የሰላም ብርሀን መፈንጠቅ ጀምሯል። ሁሉም በተጠንቅቅ ላይ ነው። ጊዜው አልቋል። ጁንታዎች! በጀግኖች ተከባችኋል ‹‹እጅ ወደላይ››
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 8/2013