(ጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ)
gechoseni@gmail.com
ከያኒያን “ያልከፈሉት ዕዳ”፤
ጀግናው የመከላከያ ሠራዊታችን በከሃዲያኑ የሀገር ፀሮች ላይ እያስመዘገባቸው ያሉት የሰሞኑ የድል ብሥራቶች ለዜግነት ክብር ከፍታ፣ ለሕዝቡ የአንድነት መንፈስ ማበብና ለኢትዮጵያዊነት ተሃድሶ ያበረከታቸው አስተዋጽዖዎች በጥቂቱና ተቆንጥረው ተወራላቸው እንጂ “የምርኮው አዝመራ” ገና በዝማሬ መግነንና መድመቅ አልጀመረም። የጉሮ ወሸባዬውና የዕልልታው ተቀዳሚ ፈጻሚዎችና አስፈጻሚዎች ደግሞ የሀገሪቱ የኪነ ጥበባት ባለሙያዎች ስለመሆናቸው ጎትጓችም ሆነ አስታዋሽ የሚያስፈልገው አይደለም።
በጸሐፊው መረዳት ሙዚቀኞች የዜማ መሣሪያዎቻቸውን እየቃኙ፣ ደራስያን የብዕራቸውን ቀለም ከወረቀት እያዋደዱ፣ ተዋንያን የትያትራቸውን ማንስክሪፕት እያጠኑ፣ ቀራጽያን ምስለ ጀግኖችን ለመቅረጽ እየተጠበቡ፣ የፊልም ባለሙያዎች መቼታቸውን በመወሰን በመድረካቸው ላይ ርብርብ እያደረጉ እንደሆነ እገምታለሁ።
የሀገር ኩራት የሆነው የጀግናው መከላከያ ሠራዊታችን ድልና ተጋድሎ እስካሁንም ከያኒያኑን ከእንቅልፍ አልቀሰቀስ ከሆነ ግን ውጤቱ በታሪክና በትውልድ ፊት የሚያጸይፍና የሚያስነቅፍ መሆኑን አስረግጦ ማስገንዘቡና ማስጠንቀቁ ተገቢ ይሆናል። የድል ሆታ እየሰማና የዕልልታ አጀብ እያደመጠ የሚያንጎላጅጅ ከያኒም ሆነ የብዕር ሰው አዚም ተብትቦታልና ሊፈወስ ይገባል።
የጥበብ ሠፈርተኞች ሆይ! የጀግናው ቀረርቶ ወኔያችንን ካላጋጋለ፣ የጀግኒት ተጋድሎ ነፍሳችንን ዘልቆ ካላነዘረንና መንፈሳችንን ቆስቁሶን ካላንተከተከን፣ ድል በድል እየተረማመደ በሞቱና በእንግልቱ ክብርን ያቀዳጀን የሠራዊቱ ድምጽ በምናባችን ግዘፍ ነስቶ ካልተሰማንና ካልታየን ታመናልና እንፈወስ፤ ደንዝዘናልና እንንቃ።
ይህንን ታሪካዊ አደራ ነው ከያኒያኑ ያልተከፈለ ዕዳ አለባቸው ለማለት የደፈርኩት። እውነትም አይደል ወገኔ!? የእግረ መንገድ ትዝታ ልቀስቅስና ለመሆኑ ድምጻዊ ታምራት ሞላና ሳክሲፎኒስቱን ስዩም ገብረየስን የመሳሰሉ አይረሴ ሙዚቀኞች ቤትኛ የነበሩበት ዝነኛው “የምድር ጦር ኦርኬስትራ” ከምን ደረሰ? አለ ወይንስ ታሪክ ሆኖ ቀርቷል? ካለስ ድምጹ ለምን አይሰማም? አቤቱታዬ ለሚመለከተው ይድረስልኝ!
ይህ ጸሐፊ “የተሸከመው የቃል አደራ!”
የጀግናው ሠራዊታችን የድል ፌሽታ ይህንን ጸሐፊ አብዝቶ ቢያስፈነድቀውም ያልተከፈለ የአደራ ዕዳ እርሱም በፊናው ተሸካሚ ስለሆነ በወይ ነዶ ጸጸት መዘፈቁን ቢሸሽግ ኅሊናው ስለሚያኮርፈው ደግ አይሆንም። ጸሐፊው የጀግና ወታደር ልጅ ነው። ውልደቱ በካምፕ ውስጥ፣ እድገቱም በወታደር ሠፈር ውስጥ ስለሆነ በታዳጊነቱ ሲያንጎራጉር የበጃው የወታደራዊ ድሎችን ገድል ነው።
በወጣትነቱና ጎልምሶም ቢሆን ያነበባቸውና እያነበባቸው ያሉት መጻሕፍትም በአብዛኛው ርዕሳቸውም ሆነ ጭብጣቸው በጀግኖች ታሪክና ግለ ታሪክ ላይ የተመሰረቱ ናቸው።
የሆለታ ጦር ትምህርት ቤት አሥራ አምስተኛ ኮርስ ተመራቂ መኮንን የነበረው ወላጅ አባቱ ለሀገሩ ሕይወቱን የሰዋው የማዕረግ አቻዎቹና አለቆቹ ከሆኑ መኮንኖች ጋር በግዳጅ ላይ እያሉ ነበር። ከወደቁበት የሀገር አፈር ጋር የተደባለቀው የጀግኖቹ አጽም ተሰባስቦ በቁም ብቻ ሳይሆን በሞታቸውም ጭምር ተቃቅፈው በአንድ መካነ መቃብር ውስጥ በክብር ያረፉት በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ቅጥረ ግቢ ነው። ከቶውንስ የእናት አባታቸውን ጉልበት ስመው ጀግናውን ሠራዊት እያንጎራጎሩ የተቀላቀሉት፤
የወታደር እናት ታጠቂ በገመድ፣
ልጅሽን አሞራ እንጂ አይቀብረውም ዘመድ።
እያሉ አልነበረም። ይሄው የጸሐፊው አባት ከወታደራዊ የጦር ሜዳ ግዳጆቹ ጎን ለጎንም በተለያዩ የሠራዊቱ የጦር ት/ቤቶች ውስጥ ያስተምር ስለነበር ዛሬም በሕይወት ያሉና እስከ ጄኔራል መኮንን ማዕረግ የደረሱ ከፍተኛ የሀገር ባለውለታ ጀግኖችን ማፍራቱን ጥቅምት 8 ቀን 2012 ዓ.ም “አስገራሚ፣ አስደናቂና አሳዛኝ እውነተኛ የሀገራችን ታሪኮች” በሚል ርዕስ ሌ/ኮሎኔል አበበ ወልደ ተንሳይ ያሳተሙት ድንቅ መጽሐፍ በብሔራዊ ቴያትር አዳራሽ ውስጥ በተመረቀበት ዕለት ተማሪዎቹ ነበርን ያሉ ሁለት የተከበሩ ጄኔራል መኮንኖች ምስክርነት ሲሰጡ ጸሐፊው በተቀመጠበት ቦታ በሲቃ የታጀበ እምባ ማፍሰሱን ምን ግዜም አይዘነጋውም።
ያልተከፈለ የአደራ ዕዳ ታሪኩ ዝርዝር እንዲህ ይታወሳል። ይህ ጸሐፊ ከመወለዱ አስቀድሞ “ወንድ ልጅ የሚወለድ ከሆነ ወታደር ጋዜጠኛ ወይንም ደራሲ እንዲሆን ጉጉት አለኝ!” የሚል የአደራ ቃል አባቱ በጽሑፍ አስፍሮ ያቆየለትን ወላጅ እናቱ ነፍስ ሲያውቅ እንዳስረከቡት አንጋፋው የኢትዮጵያ ደራስያን ማኅበር “ማኅደረ ደራስያን” በሚል ርዕስ በ2011 ዓ.ም ባሳተመው መጽሐፍ ውስጥ የጸሐፊው ግለ ታሪክ በተዘከረበት ክፍል ውስጥ ተጠቅሷል። እውነት ነው ጸሐፊው በሕይወቱ ሳይፈጽማቸው ከቀሩ አኩሪ ተግባሮች መካከል በቀዳሚነት ወታደር ያለ መሆኑ እያስቆዘመውና እያስቆጨው እንደሚኖር በብዙኃን መገናኛ ሳይቀር የንስሃ ያህል ደጋግሞ ለመግለጽ ሞክሯል።
ምኞቱን ወደ ተግባር ለመለወጥ ያደረገው የአንድ ወቅት ሙከራም ባለመሳካቱ እንዲሁ ይጸጽተዋል። የጊዜው ስሌት ልክ አራት ዐሥርት ዓመታት ሆኖታል። ጸሐፊው የ12ኛ ክፍል ተማሪ በነበረበት ወቅት ጀግናው የአየር ኃይላችን ወጣቶችን ለአብራሪነት እንደሚመለምል ባስነገረው ማስታወቂያ መሠረት ያልተከፈለ ዕዳውን ለማራገፍ ዛሬ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (EBC) ባልደረባ ከሆነው አብሮ አደጉ ጋር አየር ኃይላችንን ለመቀላቀል ደብረ ዘይት ድረስ ተጉዞ ለፈተና ቢቀመጥም ምንም እንኳን የወጣትነት ቁመናው ለወታደርነት ባያንስም “የእግሩ መዳፍ ልሙጥነት” ሰበብ ሆኖ ውድድሩን ሳያልፍ በመቅረቱ ምኞቱ ሊጨነግፍ ችሏል። ይህ የአደራ ቃል ሳይተገበር የጉልምስና ዕድሜው ቢያዘናጋውም ጀግኖችን የማወደስ አደራውን ግን እስከ ዕለት ሞቱ ድረስ በፍጹም የሚዘነጋው አይደለም።
ዝክረ ጀግናዬ፤
“ለዛሬ ለነገ እውነት፤ ፈተናዋ ፈተናው ሆኖ፣
የፍቅሩን ፅናት ዘምሯል የድንበር ግንባር ሆኖ፣
የሰማይ የምድር ዘብ ሆኖ አጥንት ሥጋውን ሰትሯል፣
ሕይወቱን ለእሷ ፋሲካ ለእሷ ትንሳኤ ገብሯል።
ለሥነ ምግባሯ ኩራት ኖረ እንጂ ከፊት ሲቀድም፣
ለነገ የታሪክ ዕዳ ምትክ አድርጓት አያውቅም።
ጀግናዬ!” (ሻለቃ ክፍሌ አቦቸር)
አብዛኞቹ ቀደምት ሥነ ቃሎቻችንና የጥበብ ሥራዎች ጀግናንና ጀግንነትን ሳይዘክሩ አያልፉም። ስለ ሳተና ጀግኖች ውሎ ያልጻፈ ደራሲ፣ ያላዜመ ድምጻዊ፣ ተዋናይና ሠዓሊ በታሪካችን ውስጥ አልነበረም ማለት ፍጹም ክህደትና ድፍረት ይሆናል። የብዙ ከያኒያን የጥበብ ሥራ ማሟሻ በጀግኖች ገድል ትረካ ላይ የተመሰረተ ነው ቢባልም ከእውነት አያርቅም።
ጀግንነት ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያዊነት ተቀዳሚ መገለጫ ነው። ሀገሬ በታሪኳ ውስጥ የወረሯትን ጠላቶቿን አሳፍራ ስትመልስ እንጂ የሌላውን ዳር ድንበር ደፍራ ያለማወቋም ሌላው መለዮዋ ነው። ጀግንነት ክብሯ፣ እንግዳ ተቀባይነቷና አክባሪነቷም የሺህ ዘመናት ባህሏ ሆኖ የሚነገርላት በዚሁ ምክንያት ነው።
ጥቅምት 24 ቀን እና በተከታታይ ቀናት በሰሜን ዕዝ ሠራዊታችን ላይና በንጹሐን ዜጎቻችን ላይ የተፈጸመው የከሃዲው ሕወሓት የእንግዴ ልጆች ወረራና የግፍ ተግባር ግን እንኳን በራሳችን ምድር ቀርቶ በሌላ ሀገራት ታሪክ ውስጥ ስለመፈጸሙ እርግጠኛ መሆን አይቻልም።
ለእናት ሀገር ክብር ዘብ ለመቆም በመሃላ ያረጋገጠ፣ ለሉዓላዊታችን ጽናት ምልክት የሚሆን መለዮና አርማ የለበሰ፣ “አንተ ትብስ አንቺ ትብሽ” እየተባባለ ፍቅር በሰፈነበት የጋራ ካምፕ ውስጥ ከአንድ የሬሽን ማዕድ እየተጎራረሰ፣ ከአንድ የጋራ ኮዳ እየተጎነጨ አብሮ የኖረ፣ የአካባቢውን ማኅበረሰብ በገንዘቡ፣ በእውቀቱና በጉልበቱ እየረዳና እየደገፈ በሚኖር ወንድምና እህት የሠራዊት አባልና ንፁሐን ዜጎች ላይ “የራሴ በተባለ ወገን” እንዴት በጭካኔ ቃታ ይሳባል? ለአሰቃቂ ግድያና እልቂትስ እንዴት “ከአንድ የሀገር ማህፀን የወጣ” እጅና ስሜት ይታዘዛል? ከሃዲያኑ የሕወሓት ቅጥረኛ ሆድ አደሮች በታሪካችን ውስጥ ይህንን መሰሉን አሰቃቂና ዘግናኝ ድርጊት ሲፈጽሙ ማስተዋልና መስማት ለእኛ ዜጎች እፍረት፣ ታሪኩ ለሚደርሳቸው ባዕዳንም እንቆቅልሽ መሆኑን መግለጹ በራሱ አሳቅቆ አንገት ያስደፋል።
ጀግናው ሠራዊታችን በከሃዲያኑ የጁንታው አባላት የደረሰበት ክህደትና ግፍ የወኔውን ረመጥ ቆስቁሶ በማጋጋል ድል በድል አጎናጸፈው እንጂ “ገበርኩ” ብሎ ለሽንፈት አልዳረገውም። የትግራይ ተራሮችና ዋሻዎች፣ የቆላና ደጋ የአየር ንብረቶች ፈተናዎቹ ከመሆን ይልቅ የድሉን ዝማሬ ከአድማስ አድማስ አስተጋቡለት እንጂ መሰናክል ሆነው ከፍጥነቱ አልገቱትም።
ጀግናው የመከላከያ ሠራዊታችን፣ ከጎኑ አለንልህ ያሉት የአማራና የአፋር የሚሊሽያና የልዩ ጦር የቃል ኪዳን ጓዶቹ የከሃዲያኑን ሰይጣናዊ ተግባር በአጭሩ ለመግታት ነበልባል ስሜታቸውን አጋግሎ ተናዳፊ አደረጋቸው እንጂ በሽንፈት አላንበረከካቸውም። ጀግናዬ የሠራዊቱ አባል፣ ጀግኒት አንፀባራቂዋ ወታደር፣ በየደረጃው ያሉት አመራር ሰጭ አዛዥ መኮንኖችና የበታች ሹሞች፣ ለሀገር፣ ለትውልድና ለታሪክ ክብርና ኩራት ሆናችኋልና እንኳን ደስ ያላችሁ! እንኳን ደስ ያለን!
“ጉሮ ወሸባዬ ጉሮ ወሸባ፣
ጀግናው ድል አርጎ ሲገባ።”
የሚለው የድል ማግሥቱ ብሥራትና ዝማሬ ከሀገራችን ዳር እስከ ዳር የሚስተጋባውና ከዓለማት አጥናፍ እስከ አጥናፍ የሚዘከረው ብዙ በጎ ውጤቶችን አስከትሎ ስለመሆኑ ከወዲሁ መገመት ይቻላል። አንዳንድ አብነቶችን ልጠቃቅስ።
አንድ፤ በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ (ዶ/ር) ቁጭትና ሀዘን በሚነበብበት ስሜት ለፓርላማ አባላት ባደረጉት ንግግራቸው ውስጥ “ሠራዊቱን በሰው ኃይል ለማጠናከር ታቅዶ ከሁለት የሀገራችን ሰፋፊ ክልሎች ውስጥ አንድ ሺህ ወጣቶችን ለመመልመል ተፈልጎ ፈቃደኛ በመጥፋቱ ዕቅዱ እንደታሰበው ያለመከናወኑን” ቅሬታ ባረበበት ገጽታ እያዘኑ መግለጻቸው አይዘነጋም። በጀግናው ሠራዊታችን የድል ማግሥት ግን ወጣቶቻችን ወደ ሠራዊቱ ለመቀላቀል የሚያሳዩት ዳተኝነት ሙሉ ለሙሉ ተወግዶ የጀግናውን ሠራዊት መለዮ ለመልበስ እንደሚሽቀዳደሙ ለማረጋገጥ “ነብይነት” አይጠይቅም።
ሁለት፤ በዘመነ ኢህአዴግ/ወያኔ የአገዛዝ ዓመታት ተገቢውን ዋጋና ክብር መነፈግ ብቻም ሳይሆን ሠራዊቱ ያልተገባ ስም እየተሰጠው በሕዝቡ ዘንድ በአሉታዊ መልኩ እንዲታይ የተሸረበው ክፉ ሴራ ተገፎ ጀግናው የመከላከያ ሠራዊታችን ሞገሱ ደምቆ፣ የዝናው ጠረን እያወደን በጀግንነቱ ውሎ መኩራት ብቻም ሳይሆን በአለኝታነቱም ይበልጥ በመተማመን ሀገርና ዜጎች በትልቅ አለኝታነት ይደገፉበታል። ወዳጅ ሀገራትም በሞቀ ጭብጨባ ማድነቅ ብቻም ሳይሆን ለእነርሱም የክፉ ቀን ደራሽ መሆኑን አጥብቀው ያምናሉ።
ሦስት፤ የጀግናው ሠራዊታችን ድል በጦር ሜዳ ገድል ብቻም የሚተረክ ሳይሆን በሕዝቡ ውስጥ መሰሪው ሕወሓት ሲዘራ የኖረው መገፋፋት፣ ዘረኝነትና ጎጠኝነት ቀጭጮ አንደሚመክን ድሉ በጥሩ አጋጣሚነት ይጠቀሳል።
አራተኛ፤ በዘውጌ የብሔር ፍልስፍና “እኔ እበልጣለሁ” የሚለው ንፉግነት፣ እኛ እና እነርሱ እየተባባልን በመጠቋቆም የኖርንበት ክፉ ዘመን ታሪክና ተረት ሆኖ ኢትዮጵያዊነት ከፍ ብሎ እንደሚገዝፍ የጀግናው ሠራዊታችን ድል ሌላው የተስፋ ስንቃችን ሆኗል። አምስተኛ፣ ስድስተኛ፣ ሰባተኛ እያልን የምንዘረዝራቸው የሠራዊታችን የድል ማግሥት ሀገራዊ ውጤቶች በተከታታይ እንደሚመዘገቡ ተስፋችን ከፍ ያለ ነው። ጀግናዬ ክበርልኝ! ጀግኒት ድመቂልኝ! ሰላም ይሁን
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 8/2013