በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)fenote1971@gmail.com
ከሀዲውና እፉኝቱ የትህነግ ጁንታ የጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም የሰሜን ዕዝ ጥቃት እና የጥቅምት 30ን የማይካድራን ትውልድና ታሪክ ይቅር የማይለውን የክፍለ ዘመኑን ታላቅ ክህደትና ጭፍጨፋ ለመፈጸም ዝግጅቱንና ልምምዱን የጀመረው ከደደቢት ውልደቱ ከየካቲት 11 ቀን 1967 ዓ.ም አንስቶ ነው። ለግማሽ ክፍለ ዘመን በዝግ የተዶለተበት የክህደት ደባ እና የጭካኔ ልምምድና ዝግጅት ውጤት ነው።
የከሀዲው ትህነግ ጁንታ የመማጸኛ ከተማ መቐለ ሕዳር 19 ቀን 2013 ዓ.ም በጀግና የመከላከያ ሠራዊት ነፃ በወጣች ፤ የጁንታው ግብዓተ መሬቱ በተፈጸመ በሳልስቱ ሕዳር 21 ቀን የምስጋና የአድናቆት የእውቅና ንፍገት ስስት የሚያሰቃየው የኢፌዴሪ የእንደራሲዎች ሸንጎ ረፋድ ላይ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢያ አህመድ ( ፒ ኤች ዲ ) ወደ አዳራሹ ሲገቡ ግዳይ ለጣለ ጀግና የሚገባውን ያህል ባይሆንም ቆሞ ሞቅ ባለጭብጨባ ተቀብሏቸዋል።
በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ለሁለት ሳምንታት የተካሄደው የሕግ የበላይነትና የህልውና ዘመቻ በአንጸባራቂ ድል እንዲጠናቀቅ ለሰጡት አመራር እውቅና ለመስጠት። የማድነቅ ስስት ስላለብን እንጂ ጉዳዩስ ከዚያ በላይ የሚገባው ነበር። እንደራሲዎች ላቀረቡላቸው በርካታ ጥያቄዎች ባልተለመደ ሁኔታ ጠቅለል ባለ ግን አስረጂ በሆነ አግባብ መልሰዋል።
“ … የመከላከያ ትጥቁም ስንቁም ለዓመታት እዚያ ብቻ እንዲከማችበት የተደረገበት ምክንያት አሁን የመጣው ለውጥ ቢመጣም ባይመጣም ፤ የሀገሪቱ መከላከያ እዚያ ብቻ እንዲሆን ታስቦ ነው።…” ይህ የክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ትንተና ከፍ ብሎ ክህደቱ ቀድሞ የታሰበበትና የተመከረበት ስለመሆኑ ያነሳሁትን ሙግት ያጠናክርልኛል። ክህደቱን ታሳቢ በማድረግ አበክሮ ዝግጅት ስለመደረጉ የምመለስበት ሆኖ፤ የክህደት ልምምዱ አሀዱ ብሎ ከጀመረበት እስከ ፍጻሜው የሚመዘዙ ቅጥልጥል ክህደቶችን ለማነሳሳትልሞክር።
በአዲስ አበባ ፒያሳ በኬቭ ካፌ በራድ ሻይ እፉት እያለ ሆነ በሌላ ቦታ ሆኖ ወደ “ትግል” ሜዳ ለመውጣት ሲወስንም ሆነ እንደወጣ ታሪክን፣ እውነትን፣ ሰንደቃላማን፣ አብሮነትን፣ ሰብዓዊነትን፣ ኢትዮጵያዊ ማንነትን፣ ፍቅርን፣ ሰውነትን፣ ፈጣሪን፣ ወዘተረፈ ሽምጥጥ አርጎ ክዶ የራሱን የፈጠራ ትርክት ነው የነበረው። የሀገሪቱን ታሪክ ወደ 100 ዓመታት አራክሶ ፤ እውነትን ኅልቁ መሳፍርት በሌለው ውሸት ተክቶ፤ ሰንደቅ ዓላማን ጨርቅና የአንድ ሃይማኖት ዓርማ ነው ብሎ ፤ አብሮነትን በመለያየት ቀይሮ፤ ሰብዓዊነትን በአረመኔነት ለውጦ ፤ ኢትዮጵያዊ ማንነትን በጎሳ ሰንጥቆ፤ የትግራይ ሕዝብ ጠላት የአማራው ገዥ መደብና ኦርቶዶክስ ነው ብሎ ፤ ፈጣሪን ክዶ ራሱን ወደጣኦትነት ቀይሮ እስከማምለክ የደረሰ ወዘተረፈ የራሱን ተረክና እውነት በይኖ በራሱ ዓለም ሲዳክር የኖረ ባተሌ ስብስብ ነው።
የእውነትን፣ ሀገራዊ ነባራዊ ሁኔታን፣ የዜጋውን የልቦና ውቅርና የታሪክን ፈለግ ተከትሎ ርዕዮት ዓለም መንደፍ የማታገያ ስልት መትለም ሲገባው፤ በተቃራኒው እውነትን፣ ሀገራዊ ተጨባጭ ሁኔታን፣ የዜጋውን ልቦና ውቅርና ታሪክ በድቡሽት ላይ ለተቀለሰ ማንፌስቶው እንዲመጥኑ እጃቸውን ጠምዝዞና አጣሞ እንደገና መበየኑ እና ካፈርሁ አይመልሰኝ በሚል በስሁት መንገዱ ልምምዱን መቀጠሉ የዚች ሀገር ጎልማሳው ከሀዲ አድርጎታል። ከጥፋቱና ከዕድሜው የማይማር ልበ ቢስ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት ያለፈውን ታሪክን የመርሳት አባዜ ስላለብን ዋና ዋና የትህነግ ክህደቶቹን ብቻ ላስታውስ።
ቢያንስ ወደ ስምንት ሺህ ዓመት የሚጠጋ ቀደምት ሀገረ መንግሥትና ታሪክ ያላትን ጥንታዊት ሀገር በልኩ ካሰፋው የታሪክና የርዕዮት ዓለም ቁምጣ ጋር ለማስኬድ ሲል ትላንት በአሳሽ የተገኘች ይመስል ታሪኳን የ100 ዓመት ነው ሲል በአደባባይ የካደ የነውረኞች ስብስብ ነው። የዛሬዋ ኢትዮጵያ ቅርጽ ስሪት በአጼ ምኒልክ የተፈጠረ ነው አለ። በጎሳ ላይ የተመሰረተው አስመሳይ ፌዴራሊዝም የተዋቀረው በዚህ ክህደት ላይ። የአንድ ሀገር ጥንታዊነት ተካደ ማለት የቁጥር ጉዳይ ብቻ አይደለም።
የዜጎችን አብሮነት፣ የሀገሪቱን የሀገረ መንግሥት ልምምድና አጠቃላይ ማንነቷን የሚያኮሰምን ክህደት ነው። ዜጋው በሀገሩና በታሪኩ ያለውን እምነት ለመሸርሸርና አንድ አርገው አጋምደው ያቆዩትን ወረቶች ለማስጣል የተከናወነ መሰሪ ክህደት ነው። ይህ ብቻ አይደለም ለሀገሪቱ ያለው ጥላቻ ግዘፍ ነስቶ የተገለጠበት ክህደት ጭምር ነው። በዓለማችን ላይ የሀገሩን ታሪክ አሳንሶ ሽንጡን ይዞ የተከራከረ እና አምርሮ የሚጠላትን ሀገር የገዛ እንደ ከሀዲው ትህነግ ያለ ቡድን የለም።
ይህን ጥላቻውን አገዛዝ ላይ እያለ በሚያራምዳቸው ስሁት ፖለቲካዊ አቋሞቹና ዓይን ያወጣ ዘረፋው አረጋግጧል። ከገዢነቱ በሕዝባዊ ማዕበልና በለውጥ ኃይሉ ከተሽቀነጠረ በኋላ እኔ ረግጬ የማልገዛትና የማልዘርፋት ሀገር ትውደም በሚል የሔደበትን እርቀት ታሪክም ትውልድም በቁዘማ ሲያስታውሰው ይኖራል።
ከሀዲው የትህነግ ቡድን ብሔርን የትግሉን የማዕዘን ራስ አድርጉ መነሳቱ የሀገሪቱን ቀጣይ የፖለቲካ መልክዓ በአሉታ በይኖታል። ገለባብጦታልም። የሚያሳዝነው ይህን ያደረገው ለብሔር መብት ተቆርቁሮና ጠበቃ ሆኖ ሳይሆን ከፋፍሎ ለመግዛት እንዲያመቸው መሆኑ ነው። ለእነሱ መብት ግድ የሚሰጠው ቢሆን ኖሮ በውሸት ፌዴራሊዝም ለ27 ዓመታት የግፍ ጽዋ ባላስጎነጫቸው። የሚገባቸውን ፖለቲካዊ ውክልናና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ባልነፈጋቸው። ከሁሉም በላይ እርስ በርስ በጥርጣሬ እንዲተያዩ እንዳይተማመኑና እንዲጋጩ ሌት ተቀን ባልሠራ።
በፌዴራል ስርዓቱ ትልቁን ድርሻ ሊይዙ በሚችሉት አማራና ኦሮሞ ላይ የጥል ግድግዳ ከመገንባት ባሻገር ወደ ማይታረቅ ግጭት እንዲገቡ ጥሯል። የሚገርመው ትህነግ ይህን ሁሉ ሴራ ይሸርብ የነበረው በሀገሪቱ ይስተዋል የነበረውን የመደብ ጭቆና በብሔር ጭቆና በመተካት ነው። በዚች ሀገር ታሪክ አንድ ብሔር ገዢ መደብ ሆኖ አንድ የተወሰነ ብሔርን ጨቁኖ ገዝቷል የሚል መረጃም ሆነ ማስረጃ የለም። የገዥው መደብ አማርኛ ይናገር ስለነበር አማራ ገዝቷል ከሆነ መከራከሪያው ውሃ አያነሳም።
እንግሊዝኛ የሚናገር ገዥ ሁሉ እንግሊዛዊ እንዳልሆነው ሁሉ። ከአፄ ምንሊክ እስከ ደረግ የነበሩ አገዛዞችን ገዥዎች የማንነት ስብጥር በአብነት ማንሳት ይቻላል። አማራው፣ ኦሮሞው ፣ ትግሬው ፣ ጉራጌው ፣ ወዘተረፈ የገዥው መደብ አባል ነበሩ። ሆኖም ትህነግ ስልጣን ላይ ለመቆየት ሲል እነ ዋለልኝ ከእነ ስታሊን የኮረጁትን የብሔር ጥያቄ ለጥጦና አጉኖ የስውር ዓላማው ማስፈጸሚያው አድርጎታል።
ይህ የትህነግ ስሁት የማንነት ፖለቲካ ዛሬም እንደጥላ የሚከተለንና ወደፊትም በቀላሉ የማይፋታን መሆኑ እንደ ዜጋ ያሳስባል። ከዚህ አዙሪት የምንወጣበት በር ላይ መስማማት አለመቻላችን ደግሞ ነገሩን በእንቅርት ላይ ቆረቆር ያደርገዋል። የትህነግ የክህደት ጉዞ በዚህ አጭር መጣጥፍ አይደለም ራሱን በቻለ ዳጎስ ያለ ባለ ተከታታይ ክፍል መፅሐፍም ስለማይዘለቅ በዚህ ገታ አድርገን ለጥቅምት 24ቱ ክህደት መከላከያውን እንዴት አበክሮ ያዘጋጀው እንደነበር እንመልከት።
ከፍ ብሎ በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር እንደተገለጸው ደግሜ እጠቅሰዋለሁ ፤ “ … የመከላከያ ትጥቁም ስንቁም ለዓመታት እዚያ ብቻ እንዲከማችበት የተደረገበት ምክንያት አሁን የመጣው ለውጥ ቢመጣም ባይመጣም ፤ የሀገሪቱ የመከላከያ እዚያ ብቻ እንዲሆን ታስቦ ነው። …” የትህነግ ቡድን ክህደቱን በወታደራዊ ኃይል ለማፈርጠም የሸረበውን ሴራ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በእንደራሲዎች ሸንጎ ሲያብራሩ ፤ “ … በሌሎች አካባቢዎች የሚገኙ የመከላከያ ዕዞች ተደምረው በትግራይ ክልል የሚገኘውን የሰሜን ዕዝ የሰው ኃይል አያክልም። …” ይህ ሰሜን ዕዝ ከመከላከያ ሠራዊት እኩሌታም የሚበልጥ መሆኑን ያሳያል። ለምን ቢባል ትህነግ አንድ ቀን ይሄን ክህደት እንደሚፈጽም ያውቅ ስለነበር አበክሮ ማመቻቸቱ ነው።
የዕዙ ትጥቁም ሆነ ስንቁ ከተቀረው መከላከያ ይበልጥ ስለነበር ለዚህ እኩይ ዓላማው ቀድሞ አደላድሏል። የመከላከያ የጦር መሳሪያ መጋዘን፣ ታንኩ፣ ሮኬቱና ሚሳየሉ ሆን ተብሎ በትግራይ ክልል መከዘኑ፤ የነዳጅ ዲፖው በዚያ መሆኑ፤ የዕዝና የክፍለ ጦር አዛዦች ከትግራይ ብቻ መሆናቸው፤ ከጀነራሎች 60 በመቶ ፣ ሌተናል ጀነራሎች 40 በመቶ፣ በሜጀር ጀነራል 45 በመቶ ፣ ወዘተረፈ መሆኑ ከፍ ብሎ ለመግለጽ እንደተሞከረው ከሀዲው ቡድን ለዚህ ጥቃት ቀድሞ ሲዘጋጅ፣ ሲመሰረትና ሲደላደል መኖሩን ያለምንም ውልውል ያረጋግጣል።
ከሀዲው የትህነግ ቡድን የሰሞነኛው የሀገር፣ የሕዝብና የሰራዊት ክህደት ላይ የደረሰው ከ46 ዓመታት ልምምድና ዝግጅት በኋላ ነው። ማንነቱን በመካድ አሀዱ ያለው ቡድን፤ በመቀጠል የትግል ጓዶቹን፤ በመሰለስ ሌሎች የትግራይ ድርጅቶችን እነ ኢዲዩን ፣ አህአፓን ፣ ኦነግንና ሸዓብያን ወደ መክዳት ተሸጋግሯል። በኢትዮጵያ አንድነት የሚያምኑ፤ የኤርትራን መገንጠል ይቃወሙ ፤ በውስጠ ድርጅት ዴሞክራሲ እንዲጎለብትና አውራጃዊነት እንዲወገድ ይሟገቱ የነበሩ ሀገር ወዳዶችን አንድ ባንድ አስገድሏል። የራራለቻውንም አሰድዷል።
በ1977 ዓ.ም ድርቅና ርሀብ የትግራይ ሕዝብ እንደ ቅጠል እየረገፈ የእርዳታ እህል ፣ አልሚ ምግብና ዘይት ሽጦ የጦር መሳሪያ የሸመተ አረመኔ ነው። ነፃ አወጣዋለሁና እታገልለታለሁ የሚለውን የትግራይ ሕዝብ ስም መነገጃ ማድረግን የተለማመደው ከዚያ ሩቅ ዘመን አንስቶ ነው። በእውኑም ሆነ በህልሙ አስቦት የማያውቀው በለስ ቀንቶት ስልጣን ከያዘ በኋላ ለ27 ዓመታት በትግራይ ሕዝብ ሲነግድ የግል ጥቅሙን ሲያሳድድ ኖረ እንጅ ዘወር ብሎ አልጠየቀውም።
እንደተኩላ ልጆቹን ከጉያው ሲነጥቅ የገባለትን ቃል ኪዴንም ሲክድ ጊዜ አልወሰደበትም። ለዚህ ነው የትህነግን አፈጣጠርና አስተዳደግ ቀረብ ብለው የሚያውቁ በሰሞነኛ ክህደቱ እንደኛ ያልደነገጡት። ያልተገረሙት። አዎ ! የከሀዲውን ማንነት ጠንቅቀው ለሚያውቁት ክህደቱ የሚጠበቅና ጴጥሮሳዊ ነበር። ለዚህ ነው እንደ አረጋዊ በርሔ (ዶ/ር) ያሉ ነባር ታጋዮች እና የሸዓብያ ጉምቱ ሰዎች ትህነግን ከፍጥርጥሩ ጀምረው ስለሚያውቁት በዚህ አሳፋሪ ክህደት እንደተቀረው ኢትዮጵያዊ ያልደገነጡት።
ያልተገረሙት። ይሁንና ኢትዮጵያውያንን ያለ ልዩነት በድንጋጤ እጃቸውን በአፍ ያስጫነው ፤ በፍርሀት ያስራደው ክህደቱም ሆነ ጭካኔው በሀገሪቱ ታሪክ ተከስቶ የማያውቅና ከሕዝቡ የስነ ልቦና ውቅር ፍጹም ያፈነገጠ ስለነበር መሆኑን ብዙዎች ይስማማሉ።
እንደ መውጫ
ከሀዲው የትህነግ ቡድን ከደርግ ጋር እየተዋጋ ለሰሞነኛው ጦርነት ይዘጋጅ ነበር። ዝግጅቱ ተደጋግሞ እንደተገለጸው የሁለት ዓመት ከመንፈቅ ብቻ አይደለም። የ46 ዓመታት እንጂ። ከሀገሪቱ ሕዝብ አምስት በመቶውን ብቻ ወክሎ ሕዳጣን ሆኖ ሕዝብን እየከፋፈለና እያለያየ ፤ ፈላጭ ቆራጭ ሆኖ ቀጥቅጦ እየገዛ ፤ እየዘረፈ ፤ በገዛ እጁ ጠላት እየቀፈቀፈ ፤ ወዘተረፈ ዘላለም ስልጣን ላይ መቆየት ስለማይችል ፤ በዚህም ሕዝባዊ ተቃውሞ ሊነሳበት እንደሚችል ጠንቅቆ ስለሚያውቅ ሁል ጊዜም ለጦርነት ዝግጁ ነው።
የኢትዮ ኤርትራን ጦርነት ተጠቅሞ በቅርብ ሊቆጣጠረውና አንድ ቀን ሊጠቀምበት ወይም ሊክደው የሚችለውን ሰሜን ዕዝ አደራጀ። ኤርትራ ትወረኛለች ብሎ ካሰብ በአሰብ መስመር አፋር የሚገኘውን የቡሬ ግንባር ለምን እንደ ሰሜን ዕዝ አላደራጀውም። መልሱ ቀላል ነው ኤርትራ እንደማትወረው ግጥም አርጎ ያውቃል። ለዚህ ነው ሰሜን ዕዝን ለዚህ ክህደት ማስፈጸሚያነት ሲገነባው የኖረው።
አበክሮ ኢኮኖሚውን በመቆጣጠር እንደ ኤፈርት ያለ ግዙፍ ኩባንያ በዘረፋ የገነባው ፤ የስነ ልቦና ዝግጅት ሲያደርግ የኖረው ይህ ቀን እንደሚመጣ ስለሚያውቅ ነው። በነገራችን ላይ በሕዝባዊ አመፅና በለውጥ ኃይሉ በኢፍትሐዊነትና አላግባብ ከያዘው ስልጣን ያለምንም ማንገራገር ጓዙን ጠቅልሎ መማፀኛ ከተማው መቐሌ የገበው ተመልሶ ስልጣን ላይ እንደሚመጣ እርግጠኛ ስለነበር ነው።
መጨረሻው ደመ ከልብ ሆኖ ቀረ። የዚችን ሀገር ፖለቲካ ፣ ኢኮኖሚና ማህበራዊ ተራክቦ ለግማሽ ክፍለ ዘመን በአሉታ እንደበየነ ድርጅት ሳይሆን መንገድ ሲያቋርጥ ተገጭቶ እንደሞተ ውሻ ደሙ የውሻ ደም ( ደመ ከልብ ) ሆኖ ቀረ። ለነገሩ እሱም ቀዩን መስመር አልፎ ነው የተገጨው።ሀገራችን ኢትዮጵያ በጀግኖችና በሀቀኛ ልጆቿ ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር !!!
አሜን።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 7/2013