በሞገስ ጸጋዬ እና በኃይሉ አበራ
የህወሓት ጁንታ ቡድን በመከላከያ ሰራዊት ላይ የሰነዘረውን ጥቃት ተከትሎ አገር የማዳንና ህግ የማስከበር ዘመቻው ሲጀመር እና ሲጠናቀቅ ብቻ ሳይሆን በየአንዳንዱ አውደ ግንባር በነበረው ውዲያ ውስጥ ከፍተኛ የማድረግ አቅም የተገነባ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ገለጹ።
በዚህም በተወሰዱ ኦፕሬሽኖች በቴክኖሎጂ ታግዞ መስራትና ጥበብ የተሞላበት ወታደራዊ እርምጃ ባይካሄድ ኖሮ ንጹሃን ዜጎችን ብቻ ሳይሆን ከመከላከያ ታግተው የተወሰዱ ጓዶችን ጭምር ሊያሳጣ እንደሚችልም ጠቁመዋል።
እንደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለጻ፤ ወታደራዊ ቋንቋ መነጋገር ብቻ ሳይሆን ቴክኖሎጅካል ቋንቋ መነጋገር የሚችሉ ኮማንዶዎች ተፈጥረዋል። በዚህም ጀነራል አበባው ሽራሮን ከያዘ በኋላ አዲገዞም ላይ በነበረው ውጊያ ከዚህ ቀደም የነበረውን አይነት ዘፈን እንዳይደገም ዋነኛውን ማጥቃት ሳይፈጽም ቦታዎችን በትክክል ካሳየን በኋላ በቴክኖሎጂ አማካኝነት ጠላትን ማፍረስ ችለናል። በፈረሰ ጠላት ላይ እግረኛው ሜካናይዝዱ ምን አይነት እርምጃ ወስዶ ሰፋፊ ድሎች ማስመዝገብ እንዳለበት በተናበበ መንገድ መፈጸም ተችሏል።
አብዛኛው ኪሳራ እንዲቀንስ እና ጦርነቱ እንዲያጥር የሆነበት ምክንያት የመከላከያ አቅማችን ድሮ ሰዎች እንደሚያስቡት በነበረበት ሁኔታ ሳይሆን በስትራቴጅያችን እንዳስቀመጥነው በአራተኛና አምስትኛ ትውልድ ጦርነት የተቀናጀ፤ እግረኛውን ከአመራሩ ጋር አቀናጅቶ መምራት የሚያስችል ብቃት ስለፈጠርን ነው። ከሁሉም በላይ የሚያስደንቀኝ እና በጣም የሚያኮራኝ አንድ ሺህ የሚጠጉ የእኛ ኦፊሰሮች ተይዘው፤ ጠላት ይዟቸው ሲንቀሳቀስ እንደነበረ ታውቃላችሁ።
ማታ ማታ በምናደርገው ኦፕሬሽን በርከት ያለ ሰው በሚኖርበት ሰአት ይህ ሃይል የእኛ ኦፊሰር ሊሆን ይችላል ብለን ያቆየናቸው ሚሳኤሎች እና ቦምቦች ዛሬ ያኮሩናል። እነዛ ተለቀው ቢሆን፣ ዛሬ እነ አዳምነህን መካከላችን አናያቸውም ነበር። ይህ ብቃት ኢትዮጵያን የመታደግ፣ ኢትዮጵያን የማኩራት የተሰጠንን ተልዕኮ በአጭር የመፈጸም ብቃት የተቋማችን የሁል ጊዜ አርማ መሆን አለበት፤ ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተናገሩት።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በመቀሌ ከተማ ከከፍተኛ የመከላከያ ሰራዊት መኮንኖች ጋር ያደረጉትን ውይይት ሙሉ መልዕክት እንደሚከተለው አቅርበነዋል።
የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ልክ እንደ አባቶቹ በአገሩ ሉአላዊነት የማይደራደር፣ የተሰጠውን ሀገራዊና ህጋዊ ተልዕኮ በብቃት የሚፈጽም፤ ጠንካራ ቁመና ያለው፤ ለሀገር ኩራት የሆነ፤ አለፍኩበት ሲባል ለልጆቻችን በደስታ መናገር የሚያስችል ተቋም መሆኑን በተግባር አሳይታችኋል። ለዚህ መላው የኢትዮጰያ ህዝብ፣ የኢትዮጵያ መንግስት በናንተ ከፍተኛ ኩራትና ክብር የተሰማው መሆኑን እዚሁ መቀሌ ላይ ብገልጽላችሁ ብዬ ዛሬ እዚህ መቀሌ የመጣሁት።
በመጀመሪያ የቀድሞው ሀገር መከላከያ ሚኒስቴርን ያደራጁ፣ የመሩና በብዙ ነገር ውስጥ ያለፉ አራት ጀነራሎች መካከላችን አሉ። እነሱም ጀነራል አበባው ታደሰ፣ ጀነራል ባጫ፣ ጀነራል ዮሃንስ እና ጀነራል አለምእሸት ናቸው። እነዚህ ጀነራሎች ሁኔታው እንዳጋጠመ ኢትዮጵያ ትፈልጋችኋለች፣ ሙያችሁ አልነጠፈም፣ እንተማመንባችኋለን፣ ሰራዊቱም ይተማመንባችኋል፣
እናም ኑና አገልግሉ ሲባሉ በከፍተኛ ሞራልና ደስታ ተቀብለው የተሰጣቸውን ግዳጅ ተወጥተው አራቱም በመካከላችን አሉ።
ይሄ ለወጣት ጀነራሎች ትልቅ ትምህርት ይሆናል። ምክንያቱም ከዚህ ቀደም ስልጠና ላይ ታስታውሱ እንደሆነ ወታደር ጡረታ አይወጣም ብያችሁ ነበር። እነዚህ ጀነራሎችም ወታደር ጡረታ የማይወጣ መሆኑን ብቻ ሳይሆን ተመልሶ ሲመጣ የበለጠ ጥበበኛ፣ የበለጠ ጀግና፣ የበለጠ ድል የሚያሳካ መሆኑን ያሳዩ ጀግኖች ናቸው። እኛ በጣም ኮርተንባችኋል። እናንተንም እንኳን ደስ አላችሁ ማለት እፈልጋለሁ።
በሴንትራል ኮማንድ በአፍሪካ ዘመናዊ የሚባል ሲቹኤሽን ሩም ገንብተን ውጊያውን በሲቹኤሽን ሩም በቀጥታ በአይናችን እያየን ነው የመራነው። እንደምታውቁት አዲስ አበባ ቢሆንም እኛ ያለነው አልተኛንም ቀንና ማታ ከናንተ ጋር ነበር የነበርነው። ሆኖም በየለቱ በሚሰሩ ስራዎች እንዲከናወን ጀነራል ብርሃኑ ጁላ አጠቃላይ ለሰጡት አመራር እና ላሳዩት ቁርጠኝነት፤ እንዲሁም አብረዋቸው ለነበሩት ቲም ምስጋናና ክብር እናንተ ባላችሁበት ማቅረብ ተገቢ ይመስለኛል።
ብዙዎቻችሁ ስማችሁን ላልጠራ እችላለሁ፤ በተለይ ሶስቱ ጀነራሎች ሶስቱ ክፍለ ጦር ከነቲማቸው ይዘው ታላቅ ጀብድ የሰሩ፤ ባለፈው እንደሰማችሁት ስማቸውን ያነሳሁት (አልፎ አልፎ ሲዘነጋ ስማችሁን ያልተጠራኋችሁ ደግሞ እንዳትቀየሙ ዛሬ ደግሜ አልጠራም) ግን ሶስቱ ጀነራሎች ኢትዮጵያ ለዘላለም የምታከብረቸው ገድል ሰርታችኋል።
ክፍለጦሮቻችሁን አድናችኋል፤ ጀግና መሆናችሁን በሁለትና በሶስት ቀን ውስጥ ተደራጅታችሁ ተዋግታችሁ አሸንፋችኋል አሳይታችኋል። ለዚህ ለናንተ የሚሰጠው ክብር እና በኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት በናንተ ላይ
ያለው ኩራት ከፍተኛ መሆኑን፤ ብዙዎች የናንተን አርአያ እንዲከተሉ፤ እናንተ ሶስት ጀነራሎች የሰራችሁትን ገድል በቀላሉ የማናየው መሆኑን እና በኖርማል ጀግንነት የማይታይ መሆኑን በዚሁ አጋጣሚ ልገልጽላችሁ እፈልጋለሁ። ኮርተንባችኋል፤ ኢትዮጵያ ኮርታባችኋለች። ይህ ጀግንነት የሁሉም ወታደር እንደሆነ አውቃለው። ሶስት ክፍለ ጦር ሜካናይዝድ ማዳን ማለት ለዚህ ድል ያለው ትርጉም ከፍተኛ ነው። እና እናንተ ከፍተኛ ክብርና ምስጋና ይገባችኋል።
ባለፈውም እንዳነሳሁት ጦርነቱ እንደተጀመረ ከጥቂት ጀነራሎች ጋር ወደ ኤርትራ ተጉዘን ነበር። እዛ የነበረውን የወታደሩ ሞራል ዝግጅት ካየን በኋላ ውጊያው በሁሉም አቅጣጫ መሆን እንዳለበት ከጀነራል ብርሃኑ ጋር በተግባባንበት መሰረት ነው የኦፕሬሽኑ ፕላን የተሰራው። ባጠረ ጊዜ ውስጥ እንጨርስ የሚለው እቅዳችን የማንም ሀገር ወታደር ቢሆን በናንተ ልክ በእቅድ የሚያሳካ የለም። ሀብታም ሊሆን ይችላል፣ በቁጥር የበዛ ሊሆን ይችላል፤ በሁለት ሳምንት ኦፕሬሽን እንጨርሳለን ብሎ ነው ጀነራል ብርሃኑ ያቀረበው፤ ሶስተኛውን ሳምንት እኔ ነኝ የጨመርኩባችሁ። በተቀመጠው ጊዜ ውስጥ ይሄን ማሳካት ትልቅ ብቃትና ጀግንነት ነው።
ሆኖም፣ ያ ጊዜ ለምን ተጨመረ ለሚለው የኢትዮጵያ ህዝብ የሚያነሳው ጥያቄና እናንተ የምታነሱት ጥያቄ አንድ እንደማይሆን ተስፋ አደርጋለሁ። ምክንያቱም እናንተ ከወታደር አይን ታዩታላችሁ፤ በሌላ በኩል ከፖለቲካና ከዲፕሎማሲ አንጻር ይታያል። የሆነው ሁኖ ስድስት ቀን ተጨመረበት የራሱ የሆነ ብዙ መልክና ምክንያት ኖሮት የተጨመረ ቀን ቢሆንም፤ መከላከያ ባቀደው እቅድ መሰረት ጦርነቱን በድል ማጠናቀቅ ችሏል። ይህ ጦርነት ስንጀምረው እና ስንጨርሰው ብቻ ሳሆን፤ በየአንዳንዱ አውደ ግንባር በነበረው ውጊያ ውስጥ ከፍተኛ የማድረግ አቅም ገንብተናል።
ወታደራዊ ቋንቋ መነጋገር ብቻ ሳይሆን ቴክኖሎጅካል ቋንቋ መነጋገር የሚችሉ ኮማንዶዎች ተፈጥረዋል። እንደምታውቁት፣ ጀነራል አበባው ሽራሮን ከያዘ በኋላ አዲገዞም ላይ በነበረው ውጊያ ከዚህ ቀደም የነበረውን አይነት ዘፈን እንዳይደገም ዋነኛውን ማጥቃ ሳይፈጽም ቦታዎችን በትክክል ካሳየን በኋላ በቴክኖሎጂ አማካኝነት ጠላትን ማፍረስ ችለናል። በፈረሰ ጠላት ላይ እግረኛው ሜካናይዝዱ ምን አይነት ርምጃ ወስዶ ሰፋፊ ድሎች ማስመዝገብ እንዳለበት በተናበበ መንገድ መፈጸም ተችሏል።
አብዛኛው ኪሳራ እንዲቀንስ እና ጦርነቱ እንዲያጥር የሆነበት ምክንያት የመከላከያ አቅማችን ድሮ ሰዎች እንደሚያስቡት በነበረበት ሁኔታ ሳይሆን በስትራቴጅያችን እንዳስቀመጥነው በአራተኛና አምስትኛ ትውልድ ጦርነት የተቀናጀ፤ እግረኛውን ከአመራሩ ጋር አቀናጅቶ መምራት የሚያስችል ብቃት ስለፈጠርን ነው። ከሁሉም በላይ የሚያስደንቀኝ እና በጣም የሚያኮራኝ አንድ ሺህ የሚጠጉ የእኛ ኦፊሰሮች ተይዘው፤ ጠላት ይዟቸው ሲንቀሳቀስ እንደነበረ ታውቃላችሁ። ማታ ማታ በምናደርገው ኦፕሬሽን በርከት ያለ ሰው በሚኖርበት ሰአት ይህ ሀይል የእኛ ኦፊሰር ሊሆን ይችላል ብለን ያቆየናቸው ሚሳኤሎች እና ቦምቦች ዛሬ ያኮሩናል። እነዛ ተለቀው ቢሆን፣ ዛሬ እነ አዳምነህን መካከላችን አናያቸውም ነበር።
ይህ ብቃት ኢትዮጵያን የመታደግ፣ ኢትዮጵያን የማኩራት የተሰጠንን ተልዕኮ በአጭር የመፈጸም ብቃት የተቋማችን የሁል ጊዜ አርማ መሆን አለበት። በተደጋጋሚ እንዳልኩት ይህ መከላከያ ሰራዊት የብልጽግና ሰራዊት አይደለም። ይህ ሰራዊት የአብይ ሰራዊት አይደለም። የኢትዮጵያ ህዝብ ኩራትና መከታ የሆነ መከላከያ ነው። እኛ ከእናንተ የምንፈልገው ፕሮፌሽናል ጠንካራ ሰራዊት እንድትሆኑ እንጂ ለአንድ ፓርቲ የሚወግንና የሚገዛ እንዲሆን ትናንት እንዳልኳችሁ ዛሬም ደግምላችኋለው አንፈልግም።
ምክንያቱም ኢትዮጵያ ከብልጽግና በላይ ናት፤ ከፓርቲ በላይ ናት፤ እናንተም ትልቋን ሀገር የመታደግ ሃላፊነት ተጥሎባችኋል። ፖለቲካው የተበላሸ ነው፤ የማያውቀውን የደም ስርና የደም ሀረግ እየፈለገ የሚቧደን ነው። እናንተ ግን ጀግኖች ብቻ ሳትሆኑ ንጹህ ኢትዮጵያውያን ናችሁ። በያንዳንዱ ጦር ግንባር ኦሮሞ አማራን ለማዳን፣ አማራው ወላይታውን ለማዳን፣ ወላይታው ሲዳማውን ለማዳን፣ ሱማሌውን ለማዳን ያሳያችሁት ጀግንነት እንኳ ልትመሩ ለመላው ፖለቲከኛና ኢትጵያውያን አርአያ የሚሆን ስራ ሰርታችኋል። ይህ መቀጠል አለበት። ይህ ሁል ጊዜ ከእናንተ መወሰድ የለበትም፤ አንድ ሆናችሁ ሀገር አንድ የምታደርጉ መሆን አለባችሁ።
በርግጥ ጀግንነታችሁ በውጊያ ብቻ አይደለም። በውጊያ ካሳያችሁት ጀግንነት በላይ የሚያኮራኝ መብራት እንዲመለስ፣ መንገድ እንዲጠገን፣ ቴሌኮም እንዲገባ በትግራይ ያለው ህዝባችን በወያኔ ሥርዓት የደረሰበት መከራ የደረሰበት ስቃይ በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዲቆምና ወደ ልማት ወደ ሰላም እንዲገባ እያደረጋችሁ ያላችሁት ጥረት በእጅጉ የሚያኮራ ነው። ሁላችሁም እንደምታውቁት፣ ጦርነቱን ስንጀምር በጣም ብዙ ሰዎች ባጠረ ጊዜ ብቻ ሳይሆን ማሸነፍ ይከብዳል የሚል ግምገማና ግምት ይናገሩ ነበር። ይህ የሆበት ምክንያት እኛን የሚዋጉን ሰዎች ዘመናዊ ጦርነት አያውቁም፤ የጦርነት ሳይንስ አያውቁም። የሚያውቁት የሽምቅ ውጊያ ነው። እሱ የሽፍቶች ውጊያ ነው። እሱ በተተኳሽ ቁጥርና በሰው ሃይል ቁጥር ብዛት ማሸነፍን የምናረጋግጥበት ውጊያ ነው።
ሁላችሁም የተሳተፋችሁበት እኔም በደንብ የማው ቀው የኢትዮጵያና ኤርትራ ጦርነት ስንት ሺህ ወጣት እንዳስከፈለን፣ ስንት ጊዜ እንደወሰደ እና፤ የአሁኑን ኦፕሬሽን ደግሞ በምን ያህል ባነሰ የሰው ሃይል መስዋእትነት ለድል እንደበቃን ታውቁታላችሁ። ከሁመራ መቀሌ በእግር መጓዝ ማለት ብዙዎች አዲስ አበባ ሆነው ዝም ብለው ጀግና እንደሚሉት አይመስለኝም። በዚህ በረሃና በዚህ ሙቀት ትጥቅ ስንቅ ተሸክሞ ይሄን የሚያክል ጉዞ መጓዝ የማንም ዓለም ወታደር አይደግመውም።
እናንተ ግን አድርጋችሁታል። እናም ይሄን ጀግንነታችሁን ግን አሁንም በአንድ ነገር መድገም አለባችሁ። አሜሪካ ከኢራቅ ጋር ስትዋጋ ኢራቅን አሸንፋ ከያዘች በኋላ ሳዳምን ለመያዝ ስምንት ወር ገደማ ፈጅቶባታል። ድልን ግማሽ የሚያደርገው ጦርነት ካሸነፉ በኋላ ወንጀለኞቹን መያዝ ሲዘገይ ተጨማሪ ወጪ ተጨማሪ ኪሳራ ያስከትላል። ይሄ ሰራዊት የተሰጠውን የመጀመሪያውን ሚሽን መቶ በመቶ አሳክቷል። ነገር ግን ወንጀለኞች መያዝ አለባቸው።
ወንጀለኞች መያዝ አለባቸው፤ ሲያዙም በሕግ አግባብ ለሕግ ቀርበው መጠየቅ አለባቸው። ከዚህ አንጻር የትግራይ ሕዝብ ከፍተኛ ኃላፊነት እንዳለበት ይሰማኛል። እናም የተደበቁ ሰዎች አሁን በአሃድ መልክ የሉም፤ በዩኒት መልክ የሉም። በየግላቸው ከመኪና ወርደው የተበተኑትን ኃይሎች ካሉበት ቦታ ለትግራይ ክልል አስተዳደር እና ለሀገር መከላከያ ሚኒስቴር ማቅረብ ከሁሉም ዜጎች ይጠበቃል።
ያ ካልሆነ በስተቀረ ወታደሩ ሀገር የመገንባት ጊዜውን መንገድ የመጠገን ጊዜውን ወንጀለኛ እያሰሰ ጊዜ ይባክናል። እዛ ውስጥ ዜጎች ይጎዳሉ። ከኢትዮጵያ መንግስት ልማት ከኢትዮጵያ መንግስት ድጋፍ መጠየቅ
ለዜጎች ተገቢ ነው። ነገር ግን ዜጎችም ወንጀለኞችን ካሉበት አሳልፎ የመስጠት ግዴታ አለባቸው። ይሄ ስምም ካለ ብቻ ነው በአጭር ጊዜ ጨርሰን ወደ ልማታችን የምንገባው። ይሄ እንዲሆን ለሕዝባችን አደራ እላለሁ።
እናንተም ወንጀለኞችን ይዛችሁ በርካታ ሰዎች እየያዛችሁ እንደሆነ መረጃ አለኝ፤ ብዙዎች ያሉበት አካባቢ መታወቁም መረጃ አለኝ፤ ይሄንን በአጠረ ጊዜ ጨርሰን ወደ ዋናው የሀገር መከላከያ ሰራዊት ግንባታ ስራችን እንድንመለስ ኦፕሬሽኑ ማጠር አለበት። ከዚያ በኋላ በጋራ እያንዳንዱን ሂደት (ኢንሲደንት) እንገመግማለን። በዚህ ውስጥ ማን ጀግና ነበር? ማን ጀግንነትን ከእውቀት ጋር አዳብሎ ሰራ? እውቀትና ጀግንነት ብቻ ሳይሆን ማን ጉዳት ቀነሰ? እንዴት ሊያሳከው ቻለ? የሚለውን እንወያይበታለን፤ እንማማርበታለን፤ እንገመግማለን። በጥቅሉ ግን የሀገር መከላከያ ሰራዊት የኢትዮጵያ ሕዝቦች ኩራት፣ በዚህ ቀጠና የሚነሳ ማንኛውንም አደጋ በሚፈለግበት ጊዜ ለመመከት የሚያስችል ብቃት ያለው ጦር መሆኑን በድጋሚ አረጋግጧል።
የጁንታው ኃይል በቁጥር ከ80 ሺ በላይ ይገመታል። የጁንታው ኃይል አዳዲስ ትጥቆች ታጥቋል፤ ከፍተኛ የተተኳሽ ዲፖዎች ነበሩት፤ ከኮማንዶ እስከ ሜካናይዝድ፣ ሮኬት መተኮስ የሚችሉም ሰዎች ከእኛ አስኮብልሏል። ያው ሁላችሁም እንደምታውቁት መቀሌ እስከገባንበት ቀን ድረስ እኛ ሮኬት አልተኮስንም። በእኛና በጁንታው መካከል ያለው ልዩነት እኛ መቀሌን እስከምንይዝ አንድ ሮኬት አልተኮስንም። ምክንያቱም ህዝባችን እዚህ እንዳለ እናውቃለን። እኛ ሮኬት የተጠቀምነው ጁንታው መቀሌን ለቆ በረሃ ለበረሃ ለማምለጥ ሲሞክር ብቻ ነው። ይሄ የህዝባዊነት ልዩነት፤ ይሄ የእውነት ልዩነት፤ ይሄ የፍትሐዊነት ልዩነት አሸናፊ አርጎናል እኛን። እንጂ ትጥቅ አለን ብለን ከተማው ላይ ተኩሰን ቢሆን ኖሮ፤ ውጊያውን እዚህ አድርገን ቢሆን ኖሮ ዛሬ በዚህ ሞራል መቀሌ ውስጥ አንወያይም።
እናንተን እንድናከብራችሁና እንድንኮራባችሁ ከሚያደርገን ነገር አንዱ በእያንዳንዱ ከተማ በሁመራ፣ በሽሬ፣ በአክሱም፣ በአድዋ፣ በአዲግራት፣ በመቀሌ በጦርነት ምክንያት ሊደርስ የሚችል ጥፋት በከፍተኛ ደረጃ እንዲቀንስ በጥበብ የተሞላ አመራር ሰጥታችኋል። ባግዳድ ፈርሳለች፤ ባድዳድ የፈረሰችው ዘመናዊ ወታደር እየተዋጋ ነው፤ ሶርያ ፈርሳለች፤ ዘመናዊ ወታደር እየተዋጋ ነው። እናንተ ግን ሕዝባዊ ሰው ናችሁ፤ አንድም ከተማ ላይ ጥፋትና ውድመት ሳይደርስ ሁሉም ባለበት ሆኖ ማሸነፍ መቻላችሁ የወታደራዊ ጥበብ ብቃት ብቻ ሳይሆን ሕዝባዊነት ያለው ሰራዊት መሆኑን ያሳያል።
በቀጣይም ይሄው ጥበብና ጥንካሬያችሁ፣ እንዲሁም አንድነታችሁ ይጠበቅ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት
የሀገር መከላከያን ከነበረበት ሁለንተናዊ አቅም በላይ ለማጠናከር አስፈላጊውን ሥራ ይሰራል። ነገር ግን ኢትዮጵያን የመታደጉ ጉዳይ በአንድ ጊዜ ድል በአንድ ጊዜ የጦር አሸናፊነት የሚጠናቀቅ አይደለም። ሁልጊዜ ወትሮ ዝግጁ የሆነ ወታደር ትጥቁም የዩኒት ቅንጅት ያለው፣ የአመራር ጥበቡን የሚያውቅ፣ የሚከባበር፣ የሚዋደድ መሆኑን ማወቅ ያስፈልጋል።
አደራ ልላችሁ የምፈልገው የእኛን ጨምሮ በብዙ ሀገር የጦርነት ታሪክ ውስጥ (የእኛን ጨምሮ) ያለው ውድቀት ከድል በኋላ የሚመጣ መከፋፈል ነው። በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ መኢሶንና ደርግ ወደ ሶማሌ ሲሄዱ አንድ ነበሩ። በኢትዮጵያ ጉዳይ አንለያይም ብለው አብረው ዘመቱ። አሸንፈው ሲመለሱ ግን አብረው መቀጠል አልቻሉም። የጁንታው ኃይል ታቃላችሁ ወደ ኤርትራ ለውጊያ ሲሄድ አንድ ነበረ። ከኤርትራ ጦርነት በኋላ ግን አዲስ አበባ ሲመለስ አብሮ መቀጠል አልተቻለም አንጃ ተፈጠረ። መማር አለብን። በጦርነት ያገኘነው አንድነት እና የወንድማማች ስሜት መቀጠል አለበት።
በዚህ ጦርነት ለብቻው ከበደ ጀግና ተሰማ ፈሪ የሚባል የለም። ሁላችንም በጀግንነት ተዋግተናል። ሁላችንም በተሰጠን ሚሽን ማድረግ የሚገባንን አድርገናል። አየር ኃይላችን የሰራውን ሥራ ታውቃላችሁ፤ ስፔሻል ፎርስ የሰራውን ስራ ታቃላችሁ፤ ሎጂስቲክሱ የሰራውን ስራ ታውቃላችሁ። እዚህ የነበረውን ዲፖዎች ተይዘው ጥይት እዚህ እንዳለ ስለሚያውቅ ጠላት እኮ ይል የነበረው ከሁለት ቀናት በኋላ ጥይት የላቸውም ነው። እናንተን ተዋጉ እያልን ጥይት ባናዘጋጅ ኖሮ የተሟላ ድል አናመጣም።
ሎጂስቲክስ እንደምታውቁት አቅም በፈቀደ መጠን የተሟላ እንዲሆን የተናበበ እንዲሆን ተሰርቷል። ይህ ነገር በልማት መደገም አለበት። የትግራይ ሕዝብ ህዝባችን ነው ነጻ ወጣ ስንል ቀልድ አይደለም። አይታችኋል የታፈነ ህዝብ ነው። ብዙ አምባገነን መንግሥታት በአፍሪካ ያሉ ሕዝብ ከእኛ ጋ ነው ይደግፈናል ይሉና እዚህ እንደሚታየው ከወደቁ በኋላ ነው የሕዝብ ቁጣ የሚታየው። አንዳንድ አባላትና ቤተዘመድ አሁን ላይገባቸው ይችላል። የትግራይ ህዝብ ግን የሚገባው አሁን የተፈጠረው አስተዳደር በአጠረ ጊዜ ውስጥ የትግራይ ሕዝብ የራሱን ልጆች በፈቀደው መንገድ መርጦ ዴሞክራሲያዊ መንግስት ሲቋቋም ይሄ ነጻነት ከማንም በላይ የሱ እንደሆነ ያውቃል።
ልክ ለማሸነፍ ብዙዎች እንደጠረጠሩን ሁሉ፤ አሁን የምንናገረውን የልማት እና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የመገንባት ጉዳይ ሁሉም በአንዴ የሚቀበለውና የሚያምነው ጉዳይ አይደለም። ጊዜ ይጠይቃል። እሱን በተግባር እናሳያለን። የኢትዮጵያ መንግስት የሚናገር ብቻ ሳይሆን የሚተገብር መሆኑን በተደጋጋሚ አሳይቷል።
እናንተ ጀግኖች የምለምናችሁ አንድ ነገር ነው። ጀግና አይፎክርም እንዳትፎክሩ። ጀግና አይኩራራም፤ ጀግና ያደርጋል እንጂ አይፎክርም። ጁንታውን ጉድ የሰራው በምላስ ኃይል ማሸነፍ የሚቻል መስሎት ነው። እኛ መዘጋጀት አለብን፤ መሰልጠን አለብን፤ ማንበብ አለብን፤ መድከም አለብን፤ ጉራና ፉከራ ውስጥ መገኘት የለብንም። ከገጠምን እናሸንፋለን፤ እስከምንገጥም ግን አንፎክርም።
ይህንን ልምምድ የጦር መሪዎች በደምብ ከልባችሁ መኖር አለባችሁ። ጀግና የሚፎክር ከሆነ ጀግና አሸንፋለሁ እያለ ቀድሞ የሚናገር ከሆነ ነገር ይበላሻል። ጀግና ይራራል፣ ያዝናል፣ ያለቅሳል፣ ይስቃል፤ ሲዋጋ ደግሞ ሕይወቱ እስኪያልፍ ይዋደቃል። ይሄንን ነው ስፔሻል ፎርስ ያሳየን። ጥይት ጨርሰው መሸሽ እጅ መስጠት ሳይሆን፤ በእጃቸው ጠላት ማነቅ የሚችሉ ስፔሻል ፎርሶች የፈጠርነው ጀግና አይፎክርም በሚል ብሂል ነው። ሳትፎክሩ፣ ሰራዊቱ ሳይፎክር የተሰጠውን ሚሽን የሚያደርግ መሆኑን ካሳያችሁ፤ ለአፍሪካ ኩራት ይሆናል።
ስትመለሱ ዘርዘር ያለ በሳይንስ በቴክኖሎጂ ውጊያ የተወራበትን መንገድ ከሞላ ጎደል ሰፋ ያለ ጊዜ ወስደን ውይይት እናደርጋለን። አሁን በነበረው ሁኔታ ግን ይበልጥ አንድ ሆናችሁ፣ ተዛዝናችሁ፣ ተዋዳችሁ፣ ተከባብራችሁ እቺን ታላቅ ሀገር፤ እቺን ታሪኳ ከብዙዎች በላይ የሆነ ሀገር መጠበቅ ከቻላችሁ በሚቀጥሉት አስርና ሀያ ዓመታት ኢትዮጵያን ከልመና አውጥተን ረጂ እናደርጋታለን፤ የምትለምን ሀገር አናደርጋትም። ይህን ልክ እንደጦርነቱ በተግባር እናሳያለን። ከእናንተ የሚጠበቀው አንድ መሆን፣ እራስን ስሜትን መግዛት፣ እራስን ማሸነፍ፣ የጓድ ፍቅርና የጓድን ፍላጎት ማስቀደም፣ በወታደር እውቀት ውስጥ ያለውን ልምምድ ማጠናከር ነው። ይህን ካረጋችሁ በበጀት በስልጠና በእውቀት እንደግፋለን። ጥሩ ጥሩ አመራሮች አግኝተናል። በጦርነት ተፈትነው ያሸነፉ አመራሮች አግኝተናል።
እነ ጀነራል ብርሃኑ ጁላ በሃያ አራት ሰአት ውስጥ የሁለት ሳምንት ፕላን ማዘጋጀት የሚያስችል ብቃት አሳይተዋል። ጦርነት የሚመራበት ብቃት አሳይተዋል። እነ አበባው እቅዶቻችን በየሁኔታው በየመድረኩ ከመልካዓ ምድሩ ጋር ማናበብና ማስኬድ የሚያስችል ብቃት አሳይተዋል። እነ አለምሽት የተኩስ ጥበብ ለእኛም ለጠላትም አስተምረዋል። የተኩስና ሞብሊቲን አቅም አሳይተዋል። እነ ባጫ በነበሩበት መድረክ፣ ጆን (ዮሐንስ) ቀን ቀን የተሰጠውን የማደራጀት ስራ እየሰራ ማታ ማታ በያንዳንዱ ቀን የናንተን ድል ይከታተል ነበር። እነዚህ ሰዎች ትልቅ ኀብት (እሴት) ናቸው። ያስፈለጉን ነበር እንኳን ተመለሱልን። ከነሱ በቂ ልምድ አልወሰድንም ነበር፤ እናም እነዛን ልምዶች መቀመር አለብን።
ሆኖም ከእነሱ የምንፈልገው ቋሚና ዘላለማዊ ነገር የለም። ምክንያቱም እድሜም አለ። ስለዚህ ጦሩን ቶሎ ቶሎ መገንባት ከናንተ ይጠበቃል። ቶሎ ገንብታችሁና አቅማችሁን አከፍላችሁ ነገም ሆነ በቀጣይነት በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ተከብራችሁ የምተጠሩ እንድትሆኑ ዋናው ሃላፊነታችሁ ጦሩን መገንባት ነው። ይህን ስራ እንደምታሳኩ ሙሉ እምነት አለኝ። በተሰራው ስራ በጣም ደስተኞች ነን። መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ኩራት ይሰማዋል። አሁን ግን በድል ስካር ውስጥ ከሆንን ከፊታችን ያለው ሚሽን ከፍተኛ ስለሆነ ድልን በልኩ አስተናግደን ወደ ሚቀጥለው ምዕራፍ እንድንሄድ አደራ እላችኋለው።
ጀነራል ጌታቸው ጉዲና ኤርትራ ውስጥ በነበርንበት ጊዜ ጦሬ ተመቶ አልመለስም ብሎ እምባው የፈሰሰበት፣ አበባው ከጦሩ ጋር ነው የምሄደው ያለበት፣ መካከላችን ስላሉ ስለምታውቋቸው የቆሰሉ ጀግኖች ቁስላቸውን ይዘው አንመለስም ያሉበት ነው። ይህ እንደ ተራ ታሪክ ተነግሮ የሚታለፍ አይደለም። እነዚህ ታሪኮች የሚፃፉ፣ በገድል ውስጥ የሚተረኩ፣ ሰዎችን ስናሰለጥን ሰራዊቶቻችንን የምንገነባበት መሆን አለበት። እናም ብዙዎቻችሁ የሚያኮራ ነገር አድርጋችኋል ጻፉት፤ አዘጋጁት፤ በግምገማ አዳብሩት።
አሁንም አዲሱን የትግራይ ክልክ አስተዳደር አግዙ። ጠንክሮ እራሱን ችሎ ፖሊስ አቋቁሞ እናንተ ወደ ዋናው ስራ እንድትገቡ አድርጉ። በዚህ መንገድ የኢትዮጵያን መጻኢ ጉዞ የምናሳምር፣ ልማቷን የምናመጣ፣ ሰላሟን የምናረጋግጥ፣ ሊነኳት የሚፈልጉ ሰዎችን ሁለት ሶስቴ ደግመው እንዲያስቡ ሳንዋጋ ዲተር ማድረግ የምንችል መሆናችንን ዳግም ለማረጋገጥ በአንድ ልብ በአንድ መንፈስ አብረን እንስራ።
ወታደር በመሆኔ በጣም ኮርቻለው። በእናንተ ውስጥ በማደጌ በጣም ኮርቻለው። ከጀግና መገኘት በራሱ ያኮራል፤ እናንተ ጀግና ናችሁ እና እንኳን ከናንተ የተገኘ ባጠገባችሁ ያለፈውም ይኮራል። በድጋሚ በጣም ደስታ የተሰማኝ መሆኑን እየገለጽኩ፤ ተባብረን ሀገራችንን እናሳድጋት፤ እንጠብቃት፤ በርቱ ለማለት ነው፤ በጣም አመሰግናለሁ።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 6/2013