በትግራይ የተጀመረው ህግ የማስከበር ዘመቻ በድል ተጠናቋል። ይህንኑ ህልውናና ህግ ማስከበር ዘመቻ በማጠናቀቅም የመከላከያ ሰራዊታችን መቀሌ ገብቶ የማረጋጋትና የመልሶ ማቋቋም ስራዎችን ከትግራይ ህዝብ ጋር በማከናወን ላይ ይገኛል። ይህንኑ አስመልክቶም የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጄኔራል ብርሃኑ ጁላ በመቀሌ መግለጫ ሰጥተዋል። የመግለጫቸው ሙሉ ቃልም እንደሚከተለው ይቀርባል።
ይሄ ጦርነት እኛ የፈለግነው እኛ የጀመርነው ጦርነት አይደለም። ለሁለት ዓመት ያው እናንተም እንደምታውቁት መንግስትም ከፍተኛ የማባበልና ችግሮቹን በሰላማዊ መንገድ የመፍታት ስራ ሲሰራ ነው የቆየው። አንዳንድ የመከላከያን እንቅስቃሴን የሚያደናቅፉ ስራዎች ጁንታው እየሰራ መከላከያም ከፍተኛ ትዕግስት አድርጎ እንቅስቃሴውን ተገቶ እያለ ቢሆንም በመነጋገርና በመደራደር ስራውን ለመስራት ሲሞክር ቆይቷል። ያቨሁሉ ሲደረግ የነበረው ወደ ጦርነት ወደ ውጊያ ላለመግባት ነው።
በዚህ አገር ተደጋጋሚ ጦርነት የተካሄደበት አገር ነው። ከአሁን በኋላ ጦርነት ለዚህ አገር አይመጥንም። ይሄን አገር ወደ ኋላ ይመልሳል። የእስከ ዛሬው ታሪካችን ይበቃል። በይቅርታ መንፈስ አገራችንን እንገንባ የሚል ነበር የመንግስት አቅጣጫ። በሰራዊቱም ተግባራዊ ሲደረግ ነው የነበረው ይህው ነው። ያም ሆነ ይህ ግን ሰዎቹ ከመጠን በላይ አብጠው፣ የገዢ መደብ መንፈስ ተላብሰው ስለነበር የእኛን ትእግስት ከዕቁብ አልቆጠሩትም። ገዢ መደብ ነገር አይገባውም፣ ህዝብ አያዳምጥም፣ ተጓዳኝ ነገር አያዳምጥም በጣም ትምክህተኛ ነው። ይሄ የገዢ መደብ ባህሪ በጣም ስለተጠናወታቸው የማይሞከር ድርጊት በመከላከያ ሰራዊታችን ላይ ፈጸሙ።
ከነገ ከነገ ወዲያ ይቀዘቅዛሉ፣ ይሻሻላሉ ችግሩን በሰላማዊ መንገድ ይፈታሉ ተብሎ እየተጠበቀ እያለ እነርሱ ህገ መንግስቱ በሰጣቸው መብት የጸጥታ ኃይል አደራጅተው የጸጥታ ኃይሉን ወደ መከላከያ አዘመቱ። መከላከያው ቀደም ሲል እነሱ 27 ዓመት ስልጣን ላይ በነበሩበት ወቅት የገነቡት ነው። የእነርሱ ልጅ ነው፤ እነርሱ ቀስቅሰው ሀገር ተከላከል ብለው ቃለመሃላ አስገብተው ያደራጁት ነው።
አብረን ነው ያደራጀነው። ሰው መልሶ ልጁን አይበላም። ይሄ እነርሱን የሚጠብቅና የሚከላከል ሰራዊት፣ የእነርሱን ደህንነት ለመጠበቅ የመጣ ሰራዊት የትግራይ ህዝብን ጨምሮ እነርሱን የሚያገለግልና የሚያከብር በኢኮኖሚውም ላይ የራሱ ከፍተኛ የሆነ እገዛ ያለው ኃይል፣ በጣም ታዛዥና ህዝባዊ ሰራዊት የነበረውን ኃይል ሰብአዊነት በጎደለው መልኩ አጠቁት። በጣም ክህደት በተሞላው ምንም ጭላጭ ሰብዓዊነት የሌለው ኃይል ስለሆነ የራሱን ልጅ እራሱ መልሶ የበላ ኃይል ነው።
ይሄ ኃይል የኢትዮጵያ ህዝብ ጠንቅ ነው። ለትግራይ ህዝብም ጠንቅ ነው። አሁን ለመከላከያም ጠንቅ ሆኗል። መከላከያ እራሱን የመከላከል ግዴታ አለበት። መጀመሪያ አገር ለመጠበቅ እራሱ መከላከያ ደህንነቱ መጠበቅ አለበት። የመከላከያ ደህንነት ነው የተደፈረው። ያም ሆነ ይህ በዚህ መንገድ አድርገው ወደ ማንፈልገው ውጊያ አስገብተውናል።
ወደ ውጊያ ከገባን በኋላ ደግሞ በጀግንነትና በእልህ፣ በቆራጥነት በተጠቂነት መንፈስ ሰራዊታችን ከጫፍ እስከ ጫፍ ተነቃንቆ አንድ ወታደር እራሱን አባዝቶ ደምስሷቸዋል። ተደምስሰዋል። ለሁለት ዓመት ያደረጉት ዝግጅት በሙሉ ዜሮ ገብቷል። የመከላከያን ትጥቅ ይዘን ፌዴራልን እንገለብጣለን ብለው የነበረ ቢሆንም ትጥቁን በሙሉ አራግፎ ሸሽቷል። ትጥቅ ማራገፍ ብቻ ሳይሆን ምንም አይነት አደረጃጀት ሳይኖራቸው በእስተእርጅና ተበትነዋል።
አንድ ድራማ በስተርጅና ጣራ ላይ የሚል አለ፣ በስተርጅና ጣራ ላይ የሚለው ምን ማለት ነው ፤ያረጀ ሰው ጣራ ላይ አይወጣም ። ያረጀ ዝንጀሮ ገደል አይዘልም እና እነሱ ግን ይህንን በሚጻረር መንገድ ነው አስበው ያለ እኛ ጀግና የለም፤ ያለ እኛ የጦር ስልት አዋቂ የለም ፤ ያለ እኛ የውጊያ ጥበብ የሳይንስ ወታደራዊ ሳይንስ የሚያውቅ የለም ብለው ተነፋፍተው በቅርብ ቀን አዲስ አበባ እንገባለን ብለው አወጁ። አባሎቻቸውን አነሳስተው የመለመሉአቸውን መዋቅሮቻቸውን በዚህ ቀርጸው ሰው መቼ ነው አዲስ አበባ የሚገቡት እያለ ሲጠይቅ ቆይቷል። ከሳምንት በኋላ አዲስ አበባ ይገባሉ ተብሎ ነበር ሲጠብቅ የነበረው።
ይህ እነሱ የሰሩት ፕሮፖጋንዳ ነው ። በጎረቤት ሀገርም ይህንኑ ሰርተዋል። ጎረቤት ሀገሮች ላይም 250 ሺ ሰራዊት አደራጅተናል ፣ ሰሜን እዝን ደምስሰን ትጥቁን ወስደናል። ስለዚህ የፌዴራል መንግስት አቅም የለውም። ከአሁን በኋላ ኢትዮጵያ እኛ እጅ ላይ ትወድቃለች ብለው ነበር የፕሮፓጋንዳ ስራ ውስጥ ለውስጥ ሲሰሩ የቆዩት።
ይህ ኃይል ልኩን የማያውቅ ነው። ውትድርና ራሱ የዛሬ 27 ዓመት 30 ዓመት በፊት በነበረው እሳቤ ለመዋጋት ራሱን ያዘጋጀ እና ደርግ ሲደመስስ ደርግን ለመደምሰስ ያስቻለውን አስቻይ ሁኔታ ምንድን ነው የሚለውን ያልገመገመ ኋላቀር ቡድን ነው። አሁን ያለውን ሁኔታ ደግሞ በሚገባ ያላየ እና የትምክህት የገዢ መደብ የድንቁርና ውሳኔ ነው የወሰነው።
የድንቁርና ውሳኔ ሁል ጊዜ እንደ ጉም ነው የሚበተነው። እና የእነሱ ዕቅድ፣ የእነሱ ፍላጎት ፣ የእነሱ ግብ ሁሉ ከሽፎ እነሱም ዛሬ ተበትነው በስተርጅና በየጫካው እየተንከራተቱ ነው ያሉት። ይህ ራሳቸው ያመጡት ነው። አሁን የኢትዮጵያ ህዝብ እፎይታ አግኝቷል። በመላ አገሪቱ አሁን ሰላም ነው። ድሮ በየቦታው እነሱ ለኩሰውት የነበረው ግጭት እነሱ በመመታታቸው ምክንያት ሁሉም አካባቢ እፎይታ ሰፍኗል። የኢትየጵያ ህዝብ ተገላግሏል። ከእነዚህ መሰሪ ከእነዚህ በጣም አስቸጋሪ ከሆኑ ሰዎች ተገላግሏል። የትግራይ ህዝብም ነጻ ወጥቷል።
ሰራዊታችን በእውነቱ ታይቶ በማይታወቅ ጀግንነት ግዳጁን ተወጥቷል። ይህ ጦርነት በሁለት ፣ ሶስት ሳምንት ያልቃል ብሎ የገመተ ማንም ዓለምአቀፋዊ ማህበረሰብም ይሁን ማንኛውም ፖለቲከኛ አልነበረም።
አንዳንዶቹ እንደውም ልትሸነፉ ስለምትችሉ ተደራደሩ ሲሉ የነበረው። እኛ ግን ሃቅ ስላለን፣ ፍትህ ስላለን ፣ ስለካዱን የተካደ ሰው ሃለኛ ይሆናል። ስለካዱን በእልህ እና በወኔ ባደረግነው ውጊያ ይሄ ጁንታ ላይመለስ ለመጨረሻ ጊዜ ተደምስሶ አሁን ወጀለኞችን ፈልጎ ለህግ የማቅረብ ስራ በመስራት ላይ ነው የምንገኘው።
እሱንም ጠራርገን እጅ የሚሰጠውን እጁን ተቀብለን ወደ ህግ የሚቀርበውን አቅርበን እምቢ ያለውን ደግሞ እርምጃ ወስደን ቀጠናውን ወደ ነበረበት እንዲመለስ እና ቶሎ ብሎ የትግራይ ህዝብ ውሃ ፣ መብራት፣ ቴሌኮሙኒኬሽን አገልግሎት እንዲያገኝ ሌት ከቀን እየሰራን ነው። ከፍተኛ የሆነ የኑሮ መዛባት አለ። ኑሮ መዛባቱ እንዲስተካከል እና ራሱን መልሶ እንዲያደራጅ እና እንዲያጠናክር የማድረግ ስራ እንሰራለን። ይህንን የእርዳታ ድርጅቶችና አደጋ መከላከልና ዝግጁነት መስሪያ ቤት ይሄን በጋራ እየሰሩ ነው ።
እኛ እነዚህ ተቋማት የሚሰሩትን ስራ በማገዝ ህዝቡ እንዲያገግም የማድረግ ስራ እስራለን።ፖሊስ ተመልሶ እንዲደራጅ እና ፖሊስ ጣቢያዎች ፖሊስ እንዲኖራቸው ፤ትራፊክ የትራፊክ ስራ እንዲሰራ፤ የመንግስት ሰራተኛ ወደ ስራ እንዲመለስ የማድረግ ስራ እንሰራለን። ሰራዊታችን የመልሶ ማቋቋም ስራ እየሰራ ወንጀለኞችን የመልቀም ስራ ይቀጥላል። የገቡበት ነው የምንገባው፤ በግለሰብም ይሁን አራት አምስትም ይሁኑ የገቡበት ግብተን ለቅመን ይሄን ኃይል ታሪክ ካላደረግነው ትግራይም ኢትዮጵያም ሰላም የሚሆኑበት ሁኔታ የለም። ይሄ ጸረ ሰላም ኃይል ነው፤ አደገኛ ጁንታ ነው። ይሄ ጁንታ መደምሰስ አለበት መጥፋት አለበት።
በርካታ ሰዎች የታሉ ሰዎቹ ይላል፤ አይጥ መፈለግ በጣም ከባድ ነው። ወደ ጎሬ የገባ አይጥ መፈለግ በጣም ከባድ ነው። መያዛቸው አይቀርም። መደምሰሳቸው አይቀርም ግን ጊዜ ይጠይቃል። ሰራዊታችን አንዳንዶቹን ተቆጣጥሯል። አንዳንዶቹ ማሊያ ቀይረው ወደ ከተማ ገብተዋል። ሰራዊታችን እየተከታተላቸው፤ እየያዛቸው ነው። ጦርነቱ በድል ነው የተደመደመው። እንደዚህ አይነት ግዙፍ ኃይል ያደራጀን ጁንታ እንደዚህ በቀላሉ በሁለት ሳምንት፤ ሶስት ሳምንት የሚያልቅ ውጊያ ብዙ ጊዜ በታሪክም አይታወቅም።
በጣም አጫጭር ውጊያ የሚባሉት በዚህ አይነት ኃይል የተጀመሩ አይደሉም። ብርጌዶች የመደምሰስ፤ ክፍለ ጦሮች የመደምሰስ ስራ ነው እንጂ እንደዚህ አይነት ትልቅ ክልል፤ ትልቅ አቅም ያለው ኃይልን በአጭር ጊዜ ታሪክ ማድረግ ብዙ ጊዜ የተለመደ አይደለም። እራሳችንን ለማድነቅ ሳይሆን በታሪክም ሊመዘገብ የሚገባ የውጊያ ፍጥነት ነው። ይህ ሊሆን የቻለው በውጊያ ጥበብ ብልጫ፤ በወኔ ብልጫ እና ሀቅና እውነት ስላለ ነው። የሚሊቴሪ ሳይንስ በሚገባ ተግባራዊ አድርገን ያመጣነው ነው።
እንደኛ አይነት ጀግና የለም፤ እንደኛ አይነት ተዋጊ የለም ሲሉ የነበሩ ጄኔራሎች፤ ጡረተኞች ፤ ከድተው የገቡ የጦር አበጋዞች በሚገባ ሁኔታ ሳያነቡ የገቡበት ጦርነት ስለሆነ በጦርነቱ ተለብልበዋል። ትምክህት፤ እብሪት፤ እኔ ብቻ ነኝ የምችለው፤ እኛ የሆነ አካል ተምሳሌት ነን፤ የሚል ጉራና ትምክህት መጨረሻ ለውድቀት ይዳርጋል።በዛ መንገድ ነው ለውድቀት የተዳረጉት።
ስለዚህ ሰራዊታችን የቀረውን ስራ ጨርሶ ወደ መደበኛ ስራው ይመለሳል። መቀሌ ስብሰባ አድርገን በሚቀጥሉት ሳምንታት ምን ሰርተን ምን አድርገን ወደ መደበኛ ስራችን የምንመለሰው የሚለውን ተመካክረን እንወስናለን።
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 6 /2013 ዓ.ም