አንተነህ ቸሬ
የኢትዮጵያ ጠላት ሆኖ ከሩብ ክፍለ ዘመን በላይ ኢትዮጵያን የገዛው ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህ.ወ.ሓ.ት) የኢትዮጵያን፣ በተለይም የትግራይን፣ ሕዝብ ከጠላት በሚጠብቀውና ለትግራይ ሕዝብ ብዙ ውለታ በዋለው የሀገር መከላከያ ሰራዊት የሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት ሰንዝሮ የክፍለ ዘመኑን ዋነኛ ክህደት ፈፅሟል።
የኢ.ፌ.ዲ.ሪ መንግሥትም ከሃዲውን ቡድን ለሕግ ለማቅረብ በወሰደው የሕግ ማስከበር እርምጃ ቡድኑ ያደራጀው ተዋጊ ኃይል ተደምስሶ ከቡድኑ መሪዎች አንዳንዶቹ እጅ ሰጥተዋል፤ ሌሎቹ ደግሞ እግሬ አውጭኝ ብለው እየሸሹ ነው።
እርምጃው ከተጀመረ ጊዜ ጀምሮ ብዙዎቹ ዓለም አቀፍ (የውጭ) መገናኛ ብዙኃን ስለጉዳዩ የሚያሰራጩት ዘገባ በእውነተኛ መረጃ ላይ ያልተመሰረተ፣ ነባራዊ ሁኔታዎችን ከግምት ውስጥ ያላስገባና ተገቢ ያልሆነ ነው። ቁጥራቸው ጥቂት የማይባሉ ዓለም አቀፍ ተቋማትም ስለጉዳዩ ያላቸው ግንዛቤ ከእውነታው በእጅጉ የራቀ ሆኖ ታዝበናል። ይህም ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ስለጉዳዩ የተሳሳተ ግንዛቤ እንዲይዝ (እንዲኖረው) አድርጎ ነበር።
ይህ የውሸት መረጃን የማሰራጨትና የተሳሳተ ግንዛቤን የመያዝ ችግር የተፈጠረው በመንግሥት ድክመት እና በዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃንና ተቋማት እንዲሁም በመንግሥታት ዓላማና የግል ፍላጎት ምክንያት ነው።
መንግሥት ስለጉዳዩ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በግልፅ ከማሳወቅ አንፃር የሰራው ስራ በቂ የሚባል አልነበረም (በእርግጥ መንግሥት ሁሉንም ኃላፊነት ብቻውን ሊወጣ አይችልም፤ አይገባምም። በተለይ እንዲህ ዓይነት ጠንካራ የዘመቻና የቅስቀሳ ስራ በሚፈልጉ ተግባራት ላይ የምሁራን፣ የተቋማት በአጠቃላይ የዜጎች ተሳትፎ እጅግ አስፈላጊ ነው)።
የውጭ መንግሥታት እና ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃንና ተቋማት የራሳቸው ዓላማ አላቸው። እነዚህ አካላት በሌሎች አገራት የሚፈጠሩ ክስተቶችን የሚመለከቱትና ብያኔ የሚሰጡት ከራሳቸው ጥቅም አንፃር ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ የተፈጠረውን ወቅታዊ ሁኔታም የሚመዝኑት ዓላማቸውንና ጥቅማቸውን መሰረት አድርገው ነው።
ሕግ የማስከበሩ እንቅስቃሴ ብዙ የሴራ ትንታኔዎችን የሚጋብዝና ነገሩ የአፍሪካ ቀንድ ጉዳይ ስለሆነ ጠንካራ የመረጃ ዝግጅትና ጥንቃቄን የሚፈልግ ተግባር ነው። ስለሆነም እርምጃው ከመንግሥት ጥረት ባሻገር የምሁራንንና የዳያስፖራውን ኅብረተሰብ ጨምሮ የመላ ዜጎችን ተሳትፎና ንቅናቄ ይፈልግ ነበር። ይሁን እንጂ የምሁራንና በውጭ አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ተሳትፎ እንደተጠበቀው ሳይሆን መቅረቱን ታዝበናል።
ህ.ወ.ሓ.ት በተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ውስጥ ባሉ አገሮቹ በኩል አገሪቱ ልትበትን እንደሆነና የፌደራሉ መንግሥት በትግራይ ሕዝብ ላይ ጦርነት እንዳወጀ አስመስሎ በርካታ የውሸት መረጃዎች እንዲሰራጩ አድርጓል።
እነዚህን መረጃዎች ያዳመጡና የተመለከቱ ብዙ የውጭ አገራት ሰዎችና ዓለም አቀፍ ተቋማት ደግሞ መረጃዎቹን እንደወረዱ በመቀበል ከእውነት የራቀ ድምዳሜ ላይ ሲደርሱ ተስተውለዋል።
በሌላ በኩል ህ.ወ.ሓ.ት አንድ ጊዜ ተንታኝ፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ ጋዜጠኛ፣ ሲያሻቸውም አማካሪ ወይም ተማራማሪ ሆነው የሚንቀሳቀሱ ወዳጆችን አፍርቷል። እነዚህ ሰዎች ያልተደረገውን ነገር እንደተደረገ አድርገው የ‹‹በሬ ወለደ›› ውሸት በማሰራጨት ከሃዲውን ቡድን ከሞት ለማትረፍ ሲጋጋጡ ሰንብተዋል፤ አሁንም ቢሆን በአልሞት ባይ ተጋዳይነት እየተፍጨረጨሩ ነው።
ለመሆኑ «ሰዎቹ» እነማን ናቸው?
ሰዎቹ በአንድም ይሁን በሌላ መንገድ ከህ.ወ.ሓ.ት ጋር ግንኙነት ያላቸው፣ ‹‹ከኤርትራ መንግሥት ጋር ፀብ አለን›› የሚሉ፣ ራሳቸውን አንድ ጊዜ ተንታኝ፣ ዲፕሎማት፤ ሌላ ጊዜ ደግሞ ጋዜጠኛ፤ ሲያሻቸውም አማካሪ ወይም ተማራማሪ ብለው የሾሙና በዚሁ ጭምብል የሚንቀሳቀሱ ጥራዝ ነጠቅ የእጅ አዙር ቅኝ ግዛት አምባሳደሮች ናቸው።
የሕግ ማስከበር ዘመቻው ከተጀመረበት ቀን ጀምሮ እስካሁን ድረስ የሚያሰራጯቸው መረጃዎች እጅግ አሳዛኝም አሳፋሪም ናቸው። የሀገራችን ሰው ‹‹ነጭ ውሸት›› እንደሚለው ዓይነት መረጃ ሲያሰራጩ ነበር።
ማርቲን ፕላውት የተባለው ግለሰብ የጋራ ብልፅግና አገራት የጥናት ተቋም (Institute of Commonwealth Studies) ባልደረባ፤ የቢቢሲ አፍሪካ የቀድሞ አርታኢ እንዲሁም ‹‹Understanding Eritrea››፣ ‹‹Fighting Britain››፣ ‹‹Understanding South Africa››፣ ‹‹War in the Horn››፣ ‹‹Who Rules South Africa›› የተባሉና የሌሎች መጽሐፍት ጸሐፊ ነው ይባላል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከኤርትራው ፕሬዚዳንትና ከአማራ ክልል መሪዎች ጋር በጋራ ሆነው ትግራይን እንደወረሩ፣ የህወሓት ኃይል የፌደራል መንግሥቱን የጦር ጄቶች መትቶ እንደጣለ፣ የሕግ ማስከበር ዘመቻው እንዳልተጠናቀቀ … የሚገልፁ በርካታ የሐሰት መረጃዎችንና ማደናገሪያዎችን እየፈበረከ ቆይቷል።
ከዚያም አልፎ የትግራይ ሕዝብ የሽምቅ ውጊያ እንዲያደርግና የተራዘመ ጦርነት ውስጥ ገብቶ ለራሱም፣ ለፌደራል መንግሥትም በአጠቃላይ ለመላው ኢትዮጵያ ተጨማሪ ችግር እንዲሆን መክሯል። መቐለ በኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ቁጥጥር ስር መዋሏ በተሰማበት ወቅትም ልክ የህ.ወ.ሓ.ት ሰዎች ሲሉት እንደነበረው ‹‹ገና ምን ተነክቶ ውጊያው ገና ነው›› በማለት የከሃዲውን ውርደት ለማመን ሲቸገር ተስተውሏል። እንዲያው ለመጠቃቀስ ያህል እነዚህን አነሳሁ እንጂ የዚህ ‹‹ሰው›› ውሸትና አፍቃሬ-ህ.ወ.ሓ.ትነት ወደር የለውም።
ሌሎች መሰሎቹም አሉ። ራሱን ‹‹የግጭት ጥናት ፕሮፌሰርና አማካሪ (Professor Of Conflict Studies/ Conflict Advisor)›› ሲል የሰየመውና ‹‹የጨረቃ ምርጫ›› ታዛቢው ሽቲል ትሮንቮል፣ ጋዜጠኛና ተማራማሪ ብሎ ለራሱ ሹመት የሰጠው ዊልያም ዴቪሰን፣ የአቶ መለስ ዜናዊ አድናቂና ወዳጅ የሆነው አሌክስ ዲ ዎል፣ ‹‹ተንታኝ፣ ጋዜጠኛ፣ ኢኮኖሚስት … ነን›› የሚሉት ሲሞን ማርክስ፣ ረሺድ አብዲ፣ ዊል ብራውን፣ ዴክላን ዎልሽ …፣ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ምስቅልቅል ሴረኛ አሻራቸውን ያኖሩት፣ እ.ኤ.አ ከ1989 እስከ 1993 ዓ.ም ድረስ በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ሚኒስትር የነበሩትና ዛሬ የተናገሩትን ነገ የማይደግሙት አቋመ ቢሱ ኸርማን ኮኸን … በውሸታምነታቸው ህ.ወ.ሓ.ትን የሚያስንቁ የከሃዲ ጠበቃዎች ናቸው። እነዚህና ሌሎች ህወሓታውያንና ፀረ-ኢትዮጵያውያን የከሃዲውን ወንጀል በመሸፈን ዓለም መላው ኢትዮጵያውያን ስለደገፉት የሕግ ማስከበር እርምጃ የተሳሳተ ግንዛቤ እንዲኖረው ለማድረግ ያልፈነቀሉት ድንጋይ የለም።
የምሁራንና የዳያስፖራ ኢትዮጵያውያን ተሳትፎ
በውጭ አገራት ከሚኖሩ በሚሊዮኖች ከሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን መካከል የውጭ መንግሥታት፣ ዓለም አቀፍ ተቋማትና ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ስለሕግ ማስከበሩ እርምጃ እውነተኛና ሚዛናዊ መረጃ እንዲኖራቸውና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም ለድርድር እንደማይቀርብ የሞገቱ ተቋማት፣ ምሁራን፣ ቡድኖችና ግለሰቦች እጅግ በጣም ጥቂት ናቸው።
በዚህ ረገድ በአውሮፓ የተለያዩ ተቋማት የሚሰሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ለአውሮፓ ኅብረት ፓርላማ ፕሬዚዳንት የፃፏቸው ደብዳቤዎች እንዲሁም የኢትዮጵያውያን ዳያስፖራ የኮቪድ-19 ከፍተኛ የአማካሪዎች ካውንስል (Ethiopian Diaspora High Level Advisory Council On COVID-19) እና የኢትዮ-አሜሪካ ሲቪክ ካውንስል (Ethiopian- American Civic Council) ያወጧቸው መግለጫዎች ይጠቀሳሉ።
የአውሮፓ ኅብረት ፓርላማ በኢትዮጵያ የተከሰተው ግጭት እንዲቆም፣ የእርዳታ ድርጅቶች እርዳታ ወደሚያስፈልጋቸው አካባቢዎች እንዲገቡና በትግራይ ክልል የተቋረጡ የስልክና ኢንተርኔት አገልግሎቶች እንዲጀመሩ የሚጠይቅ የውሳኔ ሃሳብ (2020/2881(RSP)) ማሳለፉን ተከትሎ በአውሮፓ የተለያዩ ተቋማት የሚሰሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ለአውሮፓ ኅብረት ፓርላማ ፕሬዚዳንት ዴቪድ ሳሶሊ በፃፉት ደብዳቤ፤ ኅብረቱ በኢትዮጵያ እየተከናወነ ስለሚገኘው የሕግ ማስከበር እርምጃ የውሳኔ ሃሳብ ሲያሳልፍ ከግምት ውስጥ ያላስገባቸው ነገሮች እንዳሉ በዝርዝር አስረድተዋል።
ከዚህ በተጨማሪም የውሳኔ ሃሳቡና ውጤቶቹ ኢትዮጵያውያንን በተለይም ደግሞ የትግራይን ሕዝብ እንደሚጎዱ፣ የኢትዮጵያንና የአውሮፓ ኅብረትን መልካም ወዳጅነት እንደሚያበላሹና የውሳኔ ሃሳቡ ተገቢ እንዳልሆነም ገልፀዋል።
ህ.ወ.ሓ.ት ከፌዴራል መንግሥት በተቃራኒ ሕገ- ወጥ ምርጫ ማድረጉን፣ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ግድያዎችና መፈናቀሎች እንዲፈፀሙ ማስተባበሩን፣ ሉዓላዊት አገር በሆነችው ኤርትራ ላይ ጭምር ጥቃት መሰንዘሩን፣ በመከላከያ ሰራዊት የሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት ከፍቶ ግድያ፣ የንብረት ውድመትና ዝርፊያ እና እገታ መፈፀሙን እንዲሁም በማይካድራ ከ600 በላይ ንፁሃንን መፍጀቱን በማስረጃ አስደግፎ የጠቀሰው የኢትዮጵያውያኑና የትውልደ-ኢትዮጵያውያኑ የማኅበረሰብ መሪዎች ደብዳቤ፤ ህ.ወ.ሓ.ትን ለመደገፍ የሚደረግ ማንኛውም ሙከራ የዘር ማጥፋትና የዝርፊያ ወንጀሎችን መደገፍ እንደሆነ በአፅንዖት አስጠንቅቋል።
ከዚህ በተጨማሪም ‹‹የአውሮፓ ኅብረት ለኢትዮጵያ የፀጥታ ሁኔታ ትኩረት መስጠቱን ብናደንቅም የውሳኔ ሃሳቡ የኢትዮጵያ መንግሥት በግዛቱ ውስጥ ሕግ የማስከበርና የዜጎቹን ደህንነት የማስጠበቅ ኃላፊነት እንዳለው መዘንጋቱ በእጅጉ አሳዝኖናል፤ ረብሾናል … ኢትዮጵያውያን ተቆጥሮ የማያልቅ ሰቆቃ ያደረሰባቸውን የህ.ወ.ሓ.ት አመራር ቡድን ለሕግ ለማቅረብ በጀመሩት ሕጋዊና ፍትሐዊ እርምጃ ላይ የአውሮፓ ኅብረት ከጎናቸው እንዲቆም እንጠይቃለን …የሕግ ማስከበር ዘመቻው ንፁሃንን ሳይጎዳ ተጠናቋል።
ከ110 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ያላትና የአውሮፓ ኅብረት ስትራቴጂካዊ አጋር የሆነችው የኢትዮጵያ መረጋጋት ለቀጣናውና ለአውሮፓ ኅብረት እጅግ ጠቃሚና አስፈላጊ ነው። ስለሆነም የአውሮፓ ፓርላማ፣ የአውሮፓ ኮሚሽንና የአውሮፓ ካውንስል ለኢትዮጵያ መንግሥት ሕግ የማስከበር ኃላፊነት እውቅና እንዲሰጡና የኅብረቱ የሰብዓዊ ድጋፍ ተቋማት ስደተኞችን መልሶ ለማቋቋም የሚደረገውን ጥረት ሊያግዙና ድጋፍ እንዲያደርጉ እንጠይቃለን›› ብለዋል።
ከ20 በላይ አንጋፋ ምሁራንና ተመራማሪዎች የተካተቱበት የኢትዮጵያውያን ዳያስፖራ የኮቪድ- 19 ከፍተኛ የአማካሪዎች ካውንስል በበኩሉ ባወጣው መግለጫ፤ ህ.ወ.ሓ.ት በሰሜን ዕዝ ላይ በፈፀመው ጥቃት እጅግ ማዘኑን ገልፆ፤ የመንግሥትን የሕግ ማስከበር እርምጃ እንደሚደግፍ አስታውቋል።
ባለፉት 30 ዓመታት በአሸባሪው ህ.ወ.ሓ.ት ፊታውራሪነት በአገሪቱ የተፈፀሙ ሕገ ወጥ ተግባራት ዘርን/ጎሳን መሰረት አድርጎ በፀደቀውና በኢትዮጵያውያን ላይ በግዳጅ በተጫነው ሕገ መንግሥት አጋዥነት በመሆኑ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በሚሳተፍበት ሕዝባዊ ውይይት ሕገ መንግሥታዊ ማሻሻያ እንዲደረግ አበክሮ አሳስቧል።
የኢትዮ-አሜሪካ ሲቪክ ካውንስል ደግሞ ሰላምና ፀጥታን ለማስፈን አስተማማኙ መንገድ የሕግ የበላይነትን ማስከበር እንደሆነ ጠቅሶ ለሕግ ማስከበር እርምጃው ድጋፉን ገልጿል። ህ.ወ.ሓ.ት ቀደም ሲል የፈፀማቸውን ወንጀሎች የዘረዘረው መግለጫው፤ ቡድኑ አሁንም ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ስለሕግ ማስከበር እርምጃው የተሳሳተ ግንዛቤ እንዲኖረው በማድረግ በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ተገቢ ያልሆነ ጫና እንዲፈጠር ለማድረግ እየሞከረ ነው ሲል ተቃውሞውንና ወቀሳውን ሰንዝሯል።
ስለሕግ ማስከበር እርምጃው ትክክለኛ ገጽታና ስለተገቢነቱ ለዓለም አቀፍ ተቋማትና መገናኛ ብዙኃን ለማሳወቅ ሙከራ ያደረጉ የመንግሥት ጥቂት ባለስልጣናትና ምሁራን አሉ። እነዚህ ግለሰቦች ለመገናኛ ብዙኃን ጽሑፍ በመጻፍና ቃለ ምልልስ በመስጠት የህ.ወ.ሓ.ትን ወንጀሎችና ቡድኑ በቅርቡ ስለፈፀመው ክህደት በመጠኑም ቢሆን ለዓለም አቀፉ ኅብረተሰብ ለማስረዳት ሞክረዋል። በቂ ግን አይደለም!
ህ.ወ.ሓ.ት በተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ውስጥ በሚገኙ ወዳጆቹ በኩል ስለሕግ ማስከበር እርምጃው የተዛባ መረጃ ሲያስተላልፍና በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ጫና ሲፈጥር ነበር። የዓለም ጤና ድርጅት ዳይሬክተሩም የዚህ ህወሓታዊ ዘመቻ አካል እንደነበሩ ተነግሯል።
ግብጽ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ስለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የተዛባ መረጃ እንዲኖረው ያደረገችውና ‹‹ብሔራዊ ጥቅሜን አስከብራለሁ›› ብላ ስትንቀሳቀስ የቆየችው በተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ውስጥ በሚሰሩ ዜጎቿና ምሁራኗ በኩል ነው። ህ.ወ.ሓ.ትም ይህንኑ አካሄድ ለመድገም ሲፍጨረጨር ታይቷል። ይህ የክህደት ዘመቻው ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ስለሕግ ማስከበር ዘመቻው የጠራ መረጃ እንዳያገኝና መሰናክል ሲሆንና በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ቀላል የማይባል ጫና ሲፈጥር ታዝበናል።
በውጭ አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ስለሕግ ማስከበር እርምጃው ለዓለም አቀፉ ኅብረተሰብ መልዕክት ለማስተላለፍና ለእርምጃውም ያላቸውን ድጋፍ ለማሳየት የዓለም አደባባዮችን በሰላማዊ ሰልፍ ያጥለቀልቋቸዋል ብለን የጠበቅን ሰዎች የሻትነው ሳይሆን እንደቀረ ታዝበናል።
ለወትሮው ለአንድ ብሔር መብት መከበር ድምፃቸውን ለማሰማት አደባባይ ይወጡ የነበሩት ኢትዮጵያውያኑና ትውልደ ኢትዮጵያውያኑ እጅግ ፍትሐዊና ተገቢ ለሆነው ለሕግ ማስከበር ዘመቻው ድጋፋቸውን ያልገለፁበት ምክንያት ምን እንደሆነ እስካሁን ድረስ ማወቅ አልቻልንም። አስተዛዝቦናልም!
በአንፃሩ የሕግ ማስከበር እርምጃው ትግራይንና የትግራይ ሕዝብን የመውረርና የማጥፋት እንደሆነ፣ ህ.ወ.ሓ.ት ምንም ጥፋት እንዳልፈፀመ … የሚናገሩ ሰልፈኞች በተለያዩ የአውሮፓና የአሜሪካ ከተሞች የክህደት ጩኸታቸውን አስተጋብተዋል። ይባስ ብሎም ማይካድራ ላይ በአሰቃቂ ሁኔታ በህ.ወ.ሓ.ት የተጨፈጨፉትን ዜጎች ‹‹እነርሱ’ማ ወራሪዎች ናቸው፤ ዋጋቸውን አግኝተዋል›› ብለው አስደንጋጭና አሳፋሪ ንግግር ተናግረዋል።
ታዲያ በሰው ልጅ ታሪክ ከተሰሙ የክህደት ተግባራት መካከል አንዱን (ከጠላት የሚጠብቀውንና ብዙ ድጋፍ የሚያደርግለትን የራሱን የመከላከያ ኃይል የመውጋት ክህደት) የፈፀመው ህ.ወ.ሓ.ት ዓይኑን በጨው አጥቦ (ለነገሩ የስኳሩ ጌታ የቡድኑ ዋነኛ ሰው ስለሆኑ ዓይኑን በጨው ብቻም ሳይሆን በስኳርም ለማጠብ አይገደውም) ምንም ጥፋት እንዳልሰራ ሲያስመስልና ክህደቱን ለማስተባበልም ደጋፊዎቹን በየፊናው ሲያሰማራ ምሁራንና በውጭ አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በተቀናጀ ዘመቻ የከሃዲውንና የደጋፊዎቹን አፍ ማዘጋት የተሳናቸው ለምን ይሆን?! የከሃዲው የውሸት መረጃዎችና የሀሰት ዘመቻዎች ዓለም አቀፉን ኅብረተሰብ ሲያሳስቱ በወገን በኩል የነበረው የቅድመ ጥንቃቄና የአፀፋ እርምጃ እጅግ ደካማ ሆኖ ታይቷል።
ማርቲን ፕላውት፣ ኸርማን ኮኸንና መሰሎቻቸው የውሸት መረጃ በማሰራጨት ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ስለሕግ ማስከበር ዘመቻው የተሳሳተ ግንዛቤ እንዲኖረውና በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ጫና እንዲፈጠር ለማድረግ ሲሞክሩ የነበረው በእነርሱ ጥንካሬ ሳይሆን በወገን ድክመት መሆኑ ልብ ሊባል ይገባል። የሆነው ሆኖ ይህ ዓይነቱ ግዴለሽነት ዋጋ እንደሚያስከፍልና መደገም እንደሌለበት … ‹‹ምሁርነት›› እና ‹‹ኢትዮጵያዊነት››ም በተግባር መገለፅ እንዳለባቸው በጥብቅ ታዝበናል!
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 5/2013