ከራማአ ማዶ
ኢትዮጵያዊያን ቀለም፣ ዘርና ቋንቋ ሳይለያቸው ጎረቤት ከጎረቤት አንቺ ትብሽ አንቺ ተባብለው ተከባብረውና ተፈቃቅረው ከየትነህ/ሽ ከየት መጣህ/ሽ ሳይባባሉ ልዩነታቸውን ውበታቸው አንድነታቸውን ኃይላቸው አድርገው ከሦስት ሺ በላይ ዘመናት ድርና ማግ ሆነው የአገራቸውን ሉዓላዊነት ሳያስደፍሩ አኩሪ ታሪክ የሰሩ የጥቁር ህዝብ የነጻነት አርማ ናቸው።
ይህ የነጻነት ተምሳሌት የሆነ ህዝብ በተለያዩ ዘመናት በከፍታም በዝቅታም ያለፈችባቸው ጊዜያቶች እንደተጠበቀ ሆኖ በተለይ በደደቢት በረሃ በሴራ ተጠንስሶ በሴራ ዙፋን ላይ የወጣው ፋሽሽቱና ከሃዲው የህ.ወ.ሓ.ት ጁንታ ከምስረታው ጀምሮ የርዕዮት ዓለም መርሃ ግብር (ማንፌስቶ) ቀርጾ በጨቋኝና ተጨቋኝ ትርክት አንድን ብሄር በጠላትነት በመፈረጅ፣ በከፋፍለህ ግዛው ፋሺስታዊ አስተምሮ የጎሳ ፌዴራሊዝምን ተክሎ ህዝብን ከህዝብ፣ ብሄርን ክብሄር፣ ኃይማኖትን ከኃይማኖት እያናከሰና እያባለ ህዝቡ አንድ ሆኖ መብቱን እንዳያስከብር በማድረግ ባለፉት 27 ዓመታት ቆራጭ ፈላጭ ሆኖ መላ የኢትዮጵያን ህዝብ ሲገል፣ ሲያ ፈናቅል፣ ጥፍር ሲነቅል፣ ሲያኮላሽ፣ አገር ሲሸጥ ኖሯል።
የማፊያው ቡድን በትጥቅ ትግል ላይ በነበረባቸው 17 ዓመታት በሃሳብ የማይመስሉትን የትግል ጓዶቹን ረሽኗል። ባቀነባበረው ሴራ ለገበያ የወጣን አንድ ገበያ ህዝብ በቦንብ አስጨፍጭፏል።
ባንዳው ትህነግ በስልጣን ላይ በነበረባቸው 27 ዓመታትም ሆነ ከስልጣኑ በህዝብ ተቃውሞ ተገርሶ በመማጸኛ ከተማው ከመሸገባቸው ከሁለት ዓመት በላይም ሆነ በትጥቅ ትግል ላይ በነበረባቸው 17 ዓመታት በተለይ የማራና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያንን ኢላማ ያደረገ ህልቆ መሳፍርት የሌላቸው ለማየት የሚዘገንኑ ለመስማት የሚሰቀጥጡ ጥቃቶችን ፈጽሟል አስፈጽሟል።
ይህ ቡድን ከሱ አመለካከት ውጭ የተለያየ የፖለቲካ አመለካከት ያላቸውን ውድ የኢትዮጵያ ልጆችን በአገራቸው በነጻነት እንዳይንቀሳቀሱና ሃሳባቸውን በነጻነት እንዳይገልጹ ሲያፍን ብሎም በስደት አገራቸውን ጥለው እንዲጠፉ ሲያሳድድ እንዲሁም አድኖ እስር ቤት አስገብቶ ጨለማቤት አስሮ ሲገርፍ ጥፍር ሲነቅል ሲያኮላሽ ሲገል ኖሯል።
በአጠቃላይ ባለፉት 27 ዓመታት ዲያቢሎስ እንኳን ሊያደርገው የሚጸየፋቸውን ግፍና በደልን በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ሲያበዛ ኖሯል። ይህ ግፍና በደል ያንገሸገሸው የኢትዮጵያ ህዝብ ሆብሎ አደባባይ ወጥቶ ደረቱን ለጥይት ሰጥቶ የዚህን አረመኔያዊ አገዛዝ መቶ በመቶ በህዝብ ድምጽ ተመርጫለሁ ባለ ማግስት በውድ የኢትዮጵያ ልጆች በከፈሉት መራራ መስዋትነት ከአራት ኪሎ ቤተመንግስት እቃውን ጠቅሎ ትግራይ ክልልን ምሽግ አድርጎ ቆይቷል።
ከአራት ኪሎ ቤተ መንግስት በምን ታምር ተነቅሎ ትግራይ ክልል እንደከተመ እንቆቅልሹ ዛሬ ድረስ ያልተገለጠለት የወንበዴው ቡድን እኔ ከሞትሁ ሰርዶ አይብቀል በሚል የሞኞች ብሂል አገሪቱን ካልመራሁ አፈርሳታለሁ በሚል እሳቤ በአገሪቱ ለውጥ ከመጣ ጀምሮ ለውጡን ቀልብሶ አራት ኪሎ ቤተ መንግስት ፊጥ ለማለት አልያም ባልበላውም ጭሬ ላበላሸው እንዳለችው እንስሳ ኢትዮጵያን ገነጣጥየ የዘርፍሁትን ሀብት በጎጥ ተከልየ እየበላሁ እኖራለሁ በሚል እሳቤ ከህዝብ የዘረፈውን ገንዘብ አዕምሯቸው ለተደፈነና ሆዳቸው አምላካቸው ለሆኑ አረመኔዎች እየረጨ ህዝብን ከህዝብ ማናከሱን፣ ማፈናቀሉን፣ በጅምላ ሰውን ማስገደሉን ቀጥሎበታል።
መንግስት ተረጋግቶ አገሪቱን በለውጡ ምህዋር አስገብቶ ወደ ብልጽግና ጎዳና እንዳያሻግር ባንዳው ከለውጡ ዋዜማ ጀምሮ በእያንዳንዱ ሳምንት በሚፈጽመው የሽብር ድግስ የመንግስት ስራ እሬሳ መቅበር እና ማልቀስ እንዲሆን በማድረግ ከትግራይ ክልል በስተቀር በሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች 113 ግጭቶችን በመቀስቀስና በማቀጣጠል እንዲሁም ለገዳዮችና ለአራጆች የስልጠና የሎጅስቲክ ድጋፍ በማድረግ በአገሪቱ ሰው ተዘቅዝቆ ተሰቅሎ ተገሏል። ሴቶችና ህጻናት ሳይቀር ተገለዋል። በጥቅሉ አገሪቱን አኬልዳማ አድርጓል።
መንግስት በተደጋጋሚ ያቀረበውን የሰላም ጥሪ እንደ ፍርሃት በመቁጠር ግፍና በደሉን ግፋ በለው ያለው አገር ገንጣዩ የማፊያው ቡድን ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በሰሜን እዝ የአገር መከላከያ ሰራዊት ላይ የፈጸመውን የአገር ክደት ወንጀልና ዳግም ወደ ቤተመንግስት ለመመለስ ያሰበውን ቀቢጸ ተስፋ ተከትሎ መንግስት በትግራይ ክልል ህግን የማስከበርና የህልውና ዘመቻ ላይ ይገኛል።
ይህ ተገንጣይ ቡድን መከላከያ ሰራዊቱን ከውስጥ በክሃዲዎች ከጀርባውና ከውጭ በቅጥረኞች ከፊት ለፊቱ አስወግቶ የአገርን ህልውና አደጋ ላይ ከመጣል ባሻገር ትግራይን ከፌዴሬሽን ምክር ቤት በኃይል ገንጥሎ እራሷን የቻለች ሀገር ትሆናለች በሚል ቅዠት የፈጸመውን የአገር ክህደት ወንጀልና በመከላከያ ሰራዊት ላይ የፈጸመውን የከህደት ጥቃት ተከትሎ መንግስት በትግራይ ክልል እየወሰደ ያለውን ህግ የማስከበር እርምጃ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በአንድ ድምጽ ተስማምቶ ለጀግናው መከላከያ ድጋፍ እያደረገ ይገኛል።
መንግስት እየወሰደ ባለው ህግን የማስከበር ዘመቻ ይህ ተገንጣይ ቡድን የትግራይን ህዝብ መከለያ እንጂ የትግራይን ህዝብ የማይወክልና ለትግራይ ህዝብ ቁጥር አንድ ጥላቱ መሆኑን በተግባር አስመስክሯል። የጁንታው አባላት ልጆቻቸውን አውሮፓና አሜሪካ ቅንጡ በሆነ ኑሮ አንደላቀው እያኖሩ ነገር ግን ቆሎ በልቶ ማደር የተሳነውን የትግራይ ወጣት በትምህርቱ ልቆ በቴክኖሎጂ ተራቆ ዓለም ላይ ተወዳዳሪ ሆኖ ህይወቱን እንዳያሻሽል በወጣቱ ደም ቀቢጸ ተስፋውን ለማሳካት ከ18 ዓመት በታች የሆኑ ህጻናትን ሳይቀር አስታጥቆ ጦርሜዳ አሰልፏል፣ አዋግቷል፣ አስገድሏል።
ከሃዲው የትግራይ እናት የትናንቱ ጠባሳዋ ሳይድን ዛሬም ልጆቿን ነጥቆ የጥይት ማብረጃ ሲያደርግ ታይቷል። ህግ በማስከበር ዘመቻው የመከላከያ ሰራዊቱ አብዛኛውን የትግራይ ክልል እየተቆጣጠረ መምጣቱን ተከትሎ ቡድኑ የትግራይ ህዝብ የጦር መሳሪያ ያለው የጦር መሳሪያውን ይዞ፣ የሌለው እንደ ቢለዋ፣ አካፋ፣ ዶማ፣ ገጀራ የመሳሰሉ የቤት ቁሳቁሶችን ይዞ በነፍስ ወከፍ ወጥቶ ከደጀኑ ከአገር መከላከያ ሰራዊት ጋር ይፋለም ሲል የሞት አዋጅ በትግራይ ህዝብ ላይ አውጇል።
የማፊያው ቡድን የማምለጫ ዋሻ አዘጋጅቶ የጦርነት ነጋሪት ሲጎስም ቆይቶ የጭቁን የትግራይ ልጆችን ወደ ጦርነት ማግዶ እቆምለታለሁ ያለውን ህዝብ ከድቶ እግሬ አውጪኝ ብሎ ባዘጋጀው ዋሻ ከመፈርጠጡ በላይ ተሸንፎ በወጣባቸው ከተሞች ሁሉ መንገድ፣ ቴሌ፣ መብራት፣ ኤርፖርት የመሳሰሉ መሰረተ ልማቶችን በማውደም በግልጽ የትግራይ ህዝብ ቁጥር አንድ ጠላት መሆኑን አሳይቷል።
ነገር ግን የትግራይ ክልል ህዝብ መከላከያ ሰራዊቱ በደረሰበት ከተሞች ሁሉ ለራበው እንጀራ እያበላ፣ ለጠማው ውሃ እያጠጣ በደስታ ከመቀበሉ ባለፈ ወንበዴዎቹ የተደበቁበትን ዋሻ በመጠቆም፣ ያስታጠቁትን ነፍጥ ለመከላከያ ሰራዊቱ በማስረከብ በተግባር ህወሓትና የትግራይ ክልል ህዝብ የተለያያ መሆኑን አሳይቷል።
በህግ ማስከበር ሂደቱ የተገኝው ድል ከህወሓት እርዝራዦች ውጭ ለመላ የትግራይ ህዝብ ድል ነው። በመሆኑም ጦርነቱን ወደው ለገቡት የማፊያው ቡድን ትተን ወንድምና እህቶቻችን የትግራይ ተወላጆችን ከሚያሸማቅቁ ንግግሮችና ድርጊቶች ተቆጥበን እንደትናንቱ ከጎረቤቶቻችን ጋር አንቺ ትብሽ አንተ ትብስ ተባብለን በፍቅርና በአንድነት እንኑር። አበቃሁ።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 5/2013