አስመረት ብስራት
ልጆች እንዴት ናችሁ? ሰላም አላችሁ? ወደፊት ትልቅ ሰው ስትሆኑ ምን ለመሆን ነው የምታስቡት? አንዳንዶቻችሁ ዶክተር፤ ሌሎቻችሁ ደግሞ ኢንጅነር፣ መምህር እያላችሁ እንደመለሳችሁ አልጠራጠረም። የሚገርመው በኤቢ አካዳሚ ተገኝቼ ያነጋገርኳቸው ልጆች የተለያየ ፍላጎትና ህልም ያላቸው ናቸው። ፍላጎታቸውንም እውን ለማድረግ የራሳቸውን ጥረት ያደርጋሉ። ቤተሰቦቻቸውም ድጋፍ ያደርጉላቸዋል።
ተማሪ ሚካኤል ዋለልኝ ይባላል። የስነህዋ ምርምርና በሜካኒካል ኢንጂነሪንግ የስራ ዘርፍ ተሰማርቶ በዘርፉ ያሉ ስራዎችን የመስራት ህልም አለው። ይህን ፍላጎቱን ደግሞ ለማሳደግ የሚያስችሉ ድረ ገፆች ላይ የሰፈሩ የተለያዩ ሳይንሳዊ
ምስሎችንና ፅሁፎችን በማንበብ የራሱን ሙከራዎች ያደርጋል። ለምሳሌ አካባቢ ላይ ቆሻሻ ሲጣል አይቶ ምልክት ሊሰጥ የሚችል የሮቦት ዲዛይን፤ መብራት ቢጠፋም በአጠራቀመው ሀይል ስራውን ለመቀጠል የሚችል የሽንኩርት መፍጫ ወይም የበረበሬ መደለዣ እና ሌሎች በልቡ የሚያስባቸውን ነገሮች በሙሉ በወረቀት ላይ ያሰፍራል። በተግባርም ለመቀየር የተለያዩ ሙከራዎችን ያደርጋል።
በእረፍት ጊዜ የተለያዩ መፅሐፎችን እንዳነበበ የሚናገረው ተማሪ ሚካኤል፤ ቤተሰቦቹ መፅሐፍ ከመግዛት አንስቶ በተለያዩ የፈጠራ ስራ ሀሳብ ይዞ ሲያቀርብ የተሻለ ግንዛቤ እንዲኖረው ይረዱታል። እነሱ ከሚያደርጉለት እገዛ በተጨማሪ ራሱን በትምህርት ብቁ ለማድረግ ጥረት ያደርጋል። ጎበዝ ነው አይደል? እናንተስ ከዚህ ልጅ ምን ትማራለችሁ?
ከሚካኤል በተጨማሪ ኤልዳና የምትባል ግጥም መፃፍም ማንበብም የምትወድ ተማሪ በኤቢ አካዳሚ አግኝቻለሁ። ስታድግ ታላቅ ገጣሚ የመሆን ህልም አላት።
ተማሪ ኤልዳና ስንታየሁ ትባላለች። ትምህርት ቤት የኮሮና ወረርሽኝ ከመጣ ጊዜ አንስቶ በቤት ውስጥ መቀመጥ ግድ ሲሆንባት የተለያዩ ይዘት ያላቸውን መፃህፍት በማንበብ የስነፅሁፍ ክህሎቷን ለማዳበር የተለያዩ ፅሁፎችን ትፅፋለች። የግጥም ችሎታዋን በተደጋጋሚ በመፃፍ የምታዳብረው ኤልዳና፤ አባቷ ስራዎቿን በማንበብ አስተያየት መስጠታቸው በየቀኑ የተሻለ ፅሁፍ እንድትፅፍ እያደረጋት እንደሆነ ትናገራለች።
ኤልዳና ከስነፅሁፍ ስራ በተጨማሪ ዶክተር የመሆን ትልቅ ምኞት አላት። ይህን ምኞቷን ለማሳካት በየእለቱ መምህራኖቿ የሚሰጧትን የቤት ስራ ትሰራለች። በደንብ ትምህርቷን በማጥናት ጥሩ ውጤት ለማምጣት ትጥራለች።
ልጆቹ በጣም ጎበዝ ናቸው አይደል? አዎ እናንተም ወደፊት ለመሆን የምታልሙትን ነገር እንድትሆኑ ዛሬ ላይ ትምህርታችሁን በደንብ መከታተል ይኖርባቸኋል። ልጆች የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በልጅነታቸው ጠቅላይ ሚኒስትር የመሆን ህልም እንደነበራቸው ታውቃላችሁ? ህልማችሁ የተሳካ ይሆን ዘንድ ጎበዝ ልጆች ሁኑ እሺ። መልካም የትምህርት አመት እንዲሆንላቸሁ እመኛለሁ። ደህና ሁኑ።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 4/2013