ተገኝ ብሩ
ገና በወጣትነት ዘመኑ በብዙዎች አድናቆት ተችሮታል። በሚሳተፍባቸው ስራዎቹ በሚያሳየው ልዩ የትወና ችሎታው ዝነኛና ተወዳጅ ተዋናይ መሆን የቻለ ድንቅ አርቲስት ነው። ውልደትና ዕድገቱ አዲስ አበባ አምባሳደር ዙሪያ ፍልውሀ አካባቢ ነው። ልጅ ሆኖ ዛሬ ላይ ተገኝቶበት ራሱን ታላቅ ደረጃ ላይ ስላስገኘለት ተዋናይነት ግን አስቦትም አያውቅም፤ተዋናይ ለመሆን ተመኝቶም እንዲሁ።ለሲኒማ ግን ጥልቅ ፍቅር ነበረው።
እንደ እድል ሆኖ ተወልዶ ባደገበት አምባሳደር አካባቢ በሚገኘው አምባሳደር ሲኒማ ያዘወትር ነበር። ፊልም ለማየት ያለው ፍቅር የፊልም መመልከቻ መግቢያ ገንዘብ ሲያጣ የሲኒማ ቤቱን አዳራሽና ዙሪያውን ያጸዳ የነበረበት ሁኔታ ፊልሞችን እንዲያይ አስችሎታል።
በወጣትነት ጊዜው የራሱ ፊልም ማሳያ ቤት ነበረው፤ ፊልም ሲያሳይ በዚያው እየመረጠ የአገር ውስጥና የውጪ ፊልሞች መኮምኮም የዘወትር ተግባሩ ሆነ።በቀለም ትምህርት ላይ ብዙም የማይሆንለት ይህ ብላቴና ፣ ከሰዎች ጋር ባለው ጥሩ የመግባባት ችሎታው ከሰፈሩ ጎበዝ ተማሪዎች ጋር ቀርቦ መፎካከርና እነደነሱ ጥሩ ውጤት ማምጣት የዘወትር ጥረቱ ነበር።
የጥበብ ጅማሮ
ቀስ በቀስ የትወና ፍላጎትና ፍቅር ያደረበት ሄኖክ ከጓደኛውና ከስመ ጥሩ ተዋናይ ግሩም ኤርሚያስ የትወና ትምህርት እንዲወስድና ትወና እንዲሞክር ሀሳብ ቀረበለት።እሱም ምክሩን ወደ ተግባር ለወጠው። ለትወናየሚያስፈልገውን ትምህርት ኪነ ጥበብ ትምህርት ቤት ገብቶ በመቅሰምና ራሱን ለትወና ብቁ በማድረግ ሙያውን ሀ ብሎ ጀመረ።
ሙያውን አክብሮና ልዩ ትኩረት በመስጠት መስራቱ በቀላሉ የስኬት መንበርን መቆናጠጥ እንዲችል ያደረገው ሄኖክ ከ15 በላይ የተለያዩ ፊልሞች ላይ በመተወን በተመልካች ተወዳጅነትን አትርፏል። ትራፊኳ፣ የማትበላ-ወፍ፣የትሮይ ፈረስ፣ የፀሀይ መውጫ ልጆች፣ ወደው አይሰርቁ፣ ሼፉ፣ የእኛ ሰፈር፣ የፈጣሪ ጊዜ፣ የእግዜር ድልድይ፣ ሶማሌው ቫንዳም፣ ጳጉሜ 7 ፣ ኑርልኝ እና ሌሎች የተሳተፈባቸው ፊልሞቹ ናቸው።
ለሙያ አጋሮቹና ለፊልም ሙያተኞች ትልቅ ክብር እንዳለው የሚገልፀው ሄኖክ፤በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሙያውንለማሳደግ በትጋት መስራታቸው እንደሚደንቀውም ይናገራል። በተለይም ሙያውን ያስጀመረው ሁሌም የተሻለ ሰው እንዲሆን ምክንያት ለሆነው ጓደኛው ተዋናይ ግሩም ኤርሚያስ ትልቅ ክብር እንዳለው ይገልፃል።
የዝነኛው እርፍት ጊዜ
ህይወትን ቀለል አድርጎ መኖር የሚመቸው ሄኖክ አብዛኛው የእረፍት ጊዜውን ቤት ውስጥ ራሱን በማዝናናት ማሳለፍ እጅጉን ይወዳል። ከቤተሰቦቹና ከጓደኞቹ ጋር የሚያሳልፋቸው ጊዜያት ለሱ ደስታ ይፈጥሩለታል። ከሰዎች ጋር የተለያዩ ጉዳዮች ላይ መወያየትና የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግም የሚያዘወትረው ተግባሩ ነው።
አዳዲስ የሚወጡ የአገር ውስጥና የውጪ ፊልሞችን መመልከት ያዝናናዋል። ከፊልም ዘውጎች ውስጥ ድራማ ከሌሎች ለየት ባለ መልኩ ትኩረቱን ይስበዋል፤ በተመስጦ እንደሚከታተለውም ነው የሚናገረው። ሌላኛው አዝናኙ የእረፍት ጊዜ ልምዱ ደግሞ መፅሀፍት ማንበብ እና ከመፅሀፍቱ የሚገኙትን ልዩ ልዩ ልምዶች መቅሰም እንደሆነም ያስረዳል። ሰዎች ራሳቸውን በተለያየ መልኩ ለማነፅና እውቀታቸውን ለማዳበር ማንበብ ማዘውተር እንደሚገባቸው የሚናገረው ሄኖክ፣ ለደራሲያን ልዩ ክብር እንዳለው ይናገራል።
ለንባብ ልዩ ፍቅርም አለው።ለማንበብ የሚመርጠው የመፅሀፍ አይነት የለም፤ ያገኘውን ሁሉ ያነባል፤በተለያየ ርዕሰ ጉዳይ ላይ የተፃፈ መፅሀፍ መመርመር ይወዳል። ሁሉም መፅሀፍት የራሳቸው የሆነ መነሻ ዓላማ እንዳላቸውና ከሁሉም የሚገኝ የተለየ ጠቃሚ ጉዳይ መቅሰም እንደሚያስችሉ ያስረዳል።
ለፀሀፍት ልዩ አድናቆትና ክብርም አለው። ሰዎችየራሳቸውን ተሞክሮና የሚያውቁትን ለሌሎች ለማካፈል መጣራቸው በራሱ ትልቅ ጥንካሬ መሆኑንም ይናገራል።
ለሰዎች ደስታን መፍጠር ይወዳል። ሰዎችንም በተለየ መልኩ አዲስ ነገር ፈጥሮ ማስደሰት (ሰርፕራይዝ) ሁሌም የሚተገብረው አዝናኝና አስደሳች ልምዱ ነው። ሄኖክ የእረፍት ጊዜውን በመልሶ ማልማት ራቅ ብለው ከሚገኙት ወላጆቹና ቤተሰቦቹ ጋር ያሳልፋል፤ ከዚህ በተጨማሪም ለተለያዩ ማህበራዊ ችግሮች ከተጋለጡ ወገኖች ጋር አብሮ ማሳለፍንም ይመርጣል።
በጎ ተግባር ላይ ከተሰማሩ ግለሰቦች ጋር የተለያዩ በጎ ተግባራት ላይ በመሳተፍና ማህበራዊ ችግሮች ላይ የመፍትሄ ሀሳቦችን በማቅረብና የሚፈቱባቸው ጉዳዮች በመመርመር ሰዎችን የመርዳት ስራም ላይ ንቁ ተሳታፊ ነው።
ትኩረት ለኪነ ጥበብ
ኪነ ጥበብ በወጉ ከተሰራበት ጠቀሜታው የላቀ በመሆኑ ላይ የሚያምነው ተዋናይ ሄኖክ፣ የሀገራችን የኪነ ጥበብ ኢንዱስትሪ ገና በእድገት ላይ ያለና ብዙ የሚጠበቅበት መሆኑን ያመለክታል። ለዘርፉ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባም ያሳስባል። በፊልም የተለያዩ ማህበራዊ ጉዳዮችን በማንሳት አገርን በማስተዋወቅ፣ ማህበረሰብን ማነፅና፣ ባህልን ማስፋፋት እንደሚቻልም ያስረዳል።
በሙያው ላይ ተሳታፊ የሆኑ አካላት በሙሉ ለዘርፉ ልዩ ትኩረት በመስጠት ለእድገቱ ሊሰሩ እንደሚገባ አመልክቶ፣ በተለይ ሙያተኛው ስራውን አክብሮና በጋራ ለመለወጥ እንዲተጋ በዚህም ትልቅ ለውጥ ለማስመዝገብ እንዲረባረብ ለአጋሮቹ ምልዕክቱን አስተላልፏል።
ቸር ይግጠመን።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 4/2013