ግርማ መንግሥቴ
ታላቁ የብሪታንያ ባለቅኔ እና ጸሐፌ ተውኔት ሚሊያም ሼክስፒር (ኤፕሪል 1564 – ኤፕሪል 1616) “አለም ትያትር ናት” ካለ አራት መቶ አመት ቢያልፈውም ይህ ወርቃማ አባባሉ አሁን ድረስ ከማህበረሰብ የዕለት ተዕለት የቋንቋ አጠቃቀም ማማ ላይ ወርዶ አያውቅም። ከፀሐፊ እስከ ደራሲ፣ ከጋዜጠኛ እስከ ፖለቲከኛ ወዘተ ሁሉም ሲቀባበለው ነው የሚውለው። ይህ በበለጠ መልኩ ወደ ፊትም እንደሚቀጥል ደግሞ ምንም ጥርጥር የለም።
ይህ “አለም ትያትር ናት” አባባል እንደ ተዋቀረባቸው ቃላትና ፊደላት ውሱንነት (ጥቂትነት) አይደለም ትርጋሜውም ሆነ ፋይዳው፤ ጥልቅና ረቂቅ፣ ሁሉን ገላጭና ሁሉን አካታች ነው፤ ልክ እንደ እራሷ፣ ውጥንቅጧ እንደ በዛው አለም።
“አለም ትያትር ናት” ልክ እንደ ትያትር ቤቱ ትያትር በልዩነት ያሸበረቀና በአንድነት የደመቀ አስተሳሰብ የሚንፀባረቅበት ሲሆን ሰርግና ሞት፣ ሀዘንና ደስታ፣ ማጣትና ማግኘት፣ መውጣትና መውረድ፣ መጥገብና መራብ፣ መውደድና መጥላት ወዘተርፈ ሁሉ በዚችው አለም በተባለችው መድረክ ላይ የሚከወኑ፤ ሲከወኑም የሚውሉ ናቸውና የልዩነቱም ሆነ አንድነቱ መሰረቶች እነዚህ ለመሆናቸው ከራሳቸው በላይ ማስረጃ የለም።
በዚህ ሁሉ ሂደት ውስጥ፣ በእነዚህ ሁሉ ክስተቶች ቁልፉ ጉዳይ ደግሞ አንድ ነው፤ ህይወት። በሼክስፒር “አለም ትያትር ናት” የተባለላት አለምም ውክልናዋ ይህንኑ “ህይወት”ን ሲሆን፤ በውክልናው የተወከሉትም ሆኑ የተካተቱት (ትያትረኞቹ) ከላይ የገለፅናቸው አንኳር የህይወት ፈርጆች ብቻ ሳይሆኑ “ሕይወት ከነ ቡግሯ” እንደሚባለው ከነ ምኗም ምናምኗም ነውና በውስጧ ያልተካተተ ምንም መጥፎም ሆነ ጥሩ ነገር የለም ማለት ነው። ይህንንም በሚቀጥሉት አንቀፆች በመረጃ አስደግፈን እንየው።
ለነገሩ “መረጃ” አልን እንጂ እኛ አገር ችግር ሞልቶ የገነፈለበት የመሆኑን ያህል በመረጃ ድርቅም ክፉኛ የተመታ አገር ቢኖር ከቀዳሚዎቹ ተርታ ስለመሆናችን አሌ ማለት አይቻልም። እንዴት ይቻላል? ለዚህ ደግሞ መረጃችንም ሆነ ማስረጃችን በምንናገራቸውም ሆነ በምንፅፋቸው ማናቸውም፤ በተለይም እንደዚህ አሁን እየተነጋገርንበት እንዳለው ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ ስንሰራ መረጃ ዙሪያችን ተከምሮ እንደ ልባችን እየጨለፍን ልንጠቀምበት ሲገባ እየሆነ ያለው ግን በተቃራኒው መሆኑ ነው።
የሚገርመው ይሄ አይደለም፤ የሚገርመው ምንም አይነት መረጃ (ዳታ) በሌለበት በቃላት ድርደራ ብቻ የመጨረሻ መፍትሄን የምንፈልግ ሰዎች ብዛታችን የትየለሌ መሆኑ ነው።
ይሁን እንጂ አንዳንዴ ሳይታሰብባቸውም ቢሆን ድንገት ሹልክ የሚሉ መረጃዎች እጃችን መግባታቸው አይቀርምና እነሱን እንደ አንድ ማሳያ አድርገን መጠቀማችን አልቀረም። በመሆኑም ጉዳያችንን መሬት ለማስረገጥ የአንድ ክፍለ ከተማን መረጃ እንጥቀስ።
የአዲስ አበባ መስተዳድር የ2013 በጀት አመት የመጀመሪያውን ሩብ ዓመት ስራ አፈፃፀም በሃያት ሬጀንሲ ሆቴል በገመገመበት (የአዲሷ ከንቲባ አዳነች አቤቤም ትውውቅ በእግረ መንገድም ነበር) ክፍለ ከተሞች ሪፖርት ያቀረቡ ሲሆን (በወቅቱ እንደሰማነው ከሆነ የሁሉም ሪፖርት ፎርማት የተለያየ ይመስላል፤ ምክንያቱ ደግሞ አንዱ ጋር የሚነሳው አፈፃፀም ሌላው ጋር ሲነሳ አለመነሳቱ ነው።)፤ ከእነዚሁ ክፍለ ከተሞች አንዱ ከሆነው ጉለሌ ክፍለ ከተማ (ብቻ) አንድ ለየት ያለ መረጃ ፍንጥቅ አለ፤ “በእኛ በጉለሌ ክፍለ ከተማ 103ሺህ የደሀ ደሀ አለ።” በማለት የክፍለ ከተማው አስተዳዳሪ ለጆሯችን አበቁ። አሁን ስለዚህ ጉዳይ ዝርዝር ውስጥ ለመግባት አይፈለግም፤ ይህን እዚህ መጥቀስ ያስፈለገበት አቢይ ምክንያት አዲስ አበባ የድሆቿ ቁጥር ብቻ አይደለም ጣራ የነካው፤ ከጣራ በላይ የሆነው “የደሀ ደሀ”ዎቿም ቁጥር ጭምር ነው ለማለት ያህል ነው።
(ለ”ቦነስ” ያህል፤ 103ሺህ የደሀ ደሀዎቿም በአንድ ክፍለ ከተማ ብቻ። ለመሆኑ ይህ ቁጥር አዲስ አበባ ውስጥ ስለሆነ እዚህ ግባ የሚባል ቁጥር ላይመስል ይችል ይሆናል፤ በክልል ወረዳዎች ባሉ ከተሞች የሕዝብ ቁጥር አንፃር ቢሰላ (በአማካይ አንድ ከተማ 10ሺህ ቢሆን) ስንትና ስንት “የደሀ ደሀ ከተሞች” ይወጣው ይሆን? የሼክስፒር “አለም ትያትር ናት” እዚህም ጋ ይሰራልና ማጥናት ለሚፈልግ ጉዳዩ አዋጭ ነው።
በቅርቡ ‘78ሺህ ቤቶች በሕገ ወጥ መንገድ ተሰርተው ባለቤት አልባ ሆነው ተገኙ’ የሚለውን የአዲስ አበባ መስተዳድርን ሪፖርትም ከዚሁ አንፃር መመልከት ይቻላል። አንዱ ቤት በአማካይ አራት የቤተሰብ አባላትን ቢይዝ፤ ስንት ሕዝብ ያዘ ማለት ነው? ያን የሕዝብ ቁጥር በመደመርና ማካፈል ስሌት ቢሰራና ከላይ በገለፅነው አማካይ የከተሞች ሕዝብ ቁጥር መሰረት ቢሰላ ስንት ከተሞች በህገ ወጥ መንገድ ተመስርተዋል ወይም ተዘርፈዋል ማለት ነው? የደሀ ደሀው ቁጥርና የህገ ወጡ ቁጥር በተፃራሪ ፅንፍ እንዲህ እየጨመሩ የመሄዳቸውስ ምስጢር ምንድን ነው? ለመወያየት የፈለገን ያወያያል፤ ለመመራመር የጓጓንም ያመራምራል።
አነሳሳችን “ደግ የታደገው ቤተሰብ” በመሆኑ እሱኑ በሚገባ አስተዋውቆና አጠናክሮ ወደ ዋናው ጉዳይ ለመግባት ነበርና ወደ እዛው እንሂድ።
የዛሬ ጉዟችን ቅርብ ነው፤ ከአራት ኪሎ እስከ ፒያሳ። ከፒያሳም በሲኒማ አምፒር ወደ ሰራተኛ ሰፈር ቁልቁል ወረድ፤ ከዛም ወደ ቀኝ በመታጠፍ ወደ ውስጥ ከሚያስገቡት ባለ ኮብልስቶን ንጣፍ መንገዶች አንዱ በሆነው የውስጥ ለውስጥ መንገድ ወደ ወንዙ ዳር አካባቢ። ከዛ አላለፍንም።
እዛ አካባቢ በቆርቆሮ በተሰሩ ቤቶች ውስጥ ከሚኖሩ በርካታ ቤተሰቦች መካከል አንዱ ወደ ሆነው ወደ እነ ወይዘሮ እመቤት አለሙ ቤት አመራን። ወይዘሮ እመቤትን የአንድ አመት ህፃን ልጃቸውን ደረታቸው ላይ አድርገው አገኘናቸው፤ ጡት እየጠባ ሲሆን፤ የጠይም ቆንጆ ነው፤ ያምራል።
በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ አስር ቀጠና ስድስት፤ በተለይም ወደ እነ ወይዘሮ እመቤት ቤት እንድንመጣ ከመጀመሪያው እስከ መጨረሻው አብረውን የነበሩት ታዳጊ ወጣቶች ኤልሀም ሙባረክና አብረሀም አስራት ሁኔታውን ያመቻቹልን ሲሆን ለትብብራቸው ከወዲሁ እያመሰገንን ከወይዘሮ እመቤት ጋር ወዳደረግነው አፍታ ቆይታ እንዝለቅ።
ወይዘሮ እመቤት ባለትዳርና እና የአራት ልጆች እናት ናቸው። እናት ከመሆናቸውም በፊትና በኋላም በከፍተኛ ችግር ውስጥ በመሆን የህይወትን መራራ ፅዋ ተጎንጭተው ያውቁታል። ሰማይ ምድሩ እስኪዞርባቸው ድረስ አሳስቧቸዋል፣ አስጨንቋቸዋልም። ይሁን እንጂ ምንም አይነት መፍትሄ ሳያገኙለት በዛው ህይወት ውስጥ አመታትን አሳልፈዋል።
ይሁንና “ከእለታት አንድ ቀን . . .” እንደሚባለው አንድ ቀን ወደ ተሻለ ህይወት እንደሚመጡ ተስፋ ነበራቸውና ያ ቀን መጣ። ሲመጣ ግን ዝም ብሎ ከች-ከተፍ አይደለም ያለው። ሰው በመሆናቸው ብቻ ሰው ለመርዳት እራሳቸውን፤ ከሁሉም በላይ ውድ ጊዜያቸውን፣ ጉልበታቸውን፣ እውቀታቸው . . . አሳልፈው ለወይዘሮ እመቤትና ቤተሰባቸው አይነት ቤተሰቦች እና ሌሎች እርዳታ ፈላጊ ወገኖች ለማዋል፤ እነሱንም ለመታደግ ሲሉ በተሰባሰቡና በተደራጁ የ”ደግ ፒያሳ” በጎ አድራጎት ድርጅት አባላት አማካይነት እንጂ።
ወይዘሮ እመቤትና ቤተሰቦቻቸው ረዥም ዘመን በስቃይ ከኖሩበት ዛሬ ከወንዝ ዳርና ላስቲክ ቤት ወጥተው እጅግ በተሻለ በሚባል፣ ለእሪ በከንቱ በቀረበ አካባቢ፣ ቀበሌ በመደዳ ከሰራቸው ቆርቆሮ ቤቶች መካከል በአንዱ ውስጥ በመኖር ላይ ሲሆኑ የኑሯቸውን ሁኔታም “እግዚያብሄር ይመስገን በጣም ደስተኛ ነኝ።
እድሜ ለ’ደግ ፒያሳ’ በጎ አድራጎት ድርጅትና አባላቱ ዛሬ በጥሩ ሁኔታ ላይ እገኛለሁ። ኑሮዬም ጥሩ ነው። ይሄው በእነሱ መረዳት ከጀመርሁ ከአንድ አመት ከሶስት ወር በላይ ሆኖኛል። በየወሩ ፓስታውንም ሁሉንም እያመጡ ይሰጡኛል።” በማለት ይገልፁታል።
“የራሴ የሆነ ምንም ነገር የለኝም። ባለቤቴም የደም ግፊት በሽተኛ ነው። ስራ የለውም። አራት ልጆች አሉኝ። የመጀመሪያው ወደ ዘጠነኛ ክፍል ተዛውሯል። ልጆቼ ይማራሉ። መንግስት የትምህርት ቤት አያስከፍለኝም። ደብተርና እስኪሪብቶም ያገኛሉ።” በማለት ያስረዱን እማወራ እመቤት ባለቤታቸውም የነፃ ህክምና አገልግሎት እንደሚያገኙ ነግረውናል።
የቀድሞው ኑሯቸው ትንፋሽ እንዳይቆም እንጂ ከኑሮ የሚቆጠር እንዳልነበረ የሚናገሩት ወይዘሮ እመቤት ኑሯቸውን ይገፉ የነበሩት ድንች በመቀቀል፣ እሱንም እያዞሩ በመሸጥና በመሳሰሉት እንደነበር ይገልፃሉ። “እግዚአብሄር ይመስገን ዛሬ ያ ሁሉ የለም። ሁሉንም ነገር የ’ደግ ፒያሳ’ በጎ አድራጐት ድርጅት አባላት የሚያገኙትን እቤት ድረስ እያመጡልኝ ከነቤተሰቦቼ እየተመገብን እንኖራለን።
ድንች መሸጡም ሆነ ሌላው ነገር ሁሉ ቀርቷል።” ሲሉም አሁን ያሉበትን የኑሮ ሁኔታ ያስረዳሉ።
ይሁን እንጂ ወይዘሮ እመቤትም ሆኑ ቤተሰቦቻቸው “ደግ ፒያሳ” በጎ አድራጐት ድርጅት አባላት አማካኝነት የእለት ጉርስ ያግኙ እንጂ፣ ለልጆቻቸው የትምህርት ቁሳቁሶች ድጋፍ ይደረግላቸው እንጂ፣ ሌሎች የተጋፈጧቸው ችግሮች የሉም ማለት ግን አይደለም፤ መሰረታዊ ችግሮች አሉባቸው።
ወይዘሮ እመቤት እንደሚናገሩት ቤት ይሰጣቸው እንጂ የቤት ቁጥር ያላቸው፣ መብራት ከጎረቤት ነው ጠልፈው የሚያበሩት፣ የመብራት ቆጣሪም ሆነ ውሀ ማስገባት አይችሉም። ይህ ብቻም አይደለም፣ እንደ ወይዘሮ እመቤት አለሙ ማብራሪያ እሳቸውም ሆኑ ቤተሰቦቻቸው የቀበሌ መታወቂያ የላቸውም።
“ታዲያ ለዚህ መፍትሄው ምንድን ነው?” ብለን ጠይቀናቸው፤ መፍትሄው የቀበሌው መስተዳድር ውሀና መብራት እንድናስገባ ቢፈቅድልን፣ የቤት ቁጥሩንም ሆነ መታወቂያውን ቢሰጠን እነዚህም ሆኑ ሌሎች ችግሮች ሁሉ ይፈቱ ነበር።” በማለት የመለሱልን ሲሆን እኛም ጥያቄያቸውንም ሆነ መፍትሄ ያሉትን ሀሳብ ለሚመለከተው ይደርስ ዘንድ ይኸው ብለናል።
እዚህ ላይ አንድ የታዘብነውና እጅጉንም የገረመን ቀደም ሲል ከላይ እንደገለፅነው ወይዘሮ እመቤት አለሙን፣ ቤተሰባቸውንና እነሱን መሰሎች እየታደገ ያለው “ደግ ፒያሳ በጎ አድራጎት ድርጅት” ጉዳይ ሲሆን፤ እሱም የመስራቾቹና አገልግሎቱን እየሰጡ ያሉ ወጣቶች ሁኔታ ነው። አባላቱ ለመገመት በሚያስቸግር ደረጃ ልጆች ሲሆኑ፣ አርአያነታቸው ለአለም የሚተርፍ ነው።
ከቀበሌ ጀምሮ ያሉት የመስተዳድር አካላት አስፈላጊውን ድጋፍና እገዛ ቢያደርጉላቸው፤ ሚዲያዎች ስራዎቻቸውን እየመዘኑ በህብረተሰቡ ዘንድ ቢያስተዋውቁላቸው ደግሞ የት በደረሱ ነበርና አለመደረጉ ይቆጫል። አሁንም ጊዜ አለና ያደርጉታል ብለን እንጠብቃለን።
ሌላውና የዚህ ጽሑፍ የመጨረሻ ማሳሰቢያ ከጤና ጋር የተያያዘው የስነ ተዋልዶና የቤተሰብ ምጣኔ ጉዳይ ነው። እንደምንመለከተውና እንደምናውቀው የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር እያሻቀበ ነው። ያ ደግሞ የሁሉም ሕዝብ ችግር ሲሆን የቤተሰብ ምጣኔ ግንዛቤ ብዙዎች ጋር አናሳ ነው ማለት ነው።
በአጠቃላይ ችግሩ የሁሉም ይሁን እንጂ የገቢ አቅምን ባላገናዘበ መልኩ የሚመጣ የቤተሰብ ቁጥር ማሻቀብ ግን አደጋው ከባድ ሲሆን ችግሩ ከቤተሰብም አልፎ የአገር ነው። በመሆኑም ከእርዳታው፣ ድጋፍና እገዛው ጎን ለጎን የቤተሰብ ምጣኔ ትምህርትም ያስፈልጋልና የጤና፣ የረጂ ተቋማትም ሆኑ አጋዥ ድርጅቶች በዚህ በኩል ቶሎ ብለው ሊሰሩ ይገባል እንላለን። እርዳታን በሚሻ ቤተሰብ ላይ ሌላ እርዳታ ፈላጊን (ለዛውም ህፃናትን) ወደ እዚህ ምድር ማምጣት በሁሉም መልኩ ተገቢ ነው ማለት አይቻልምና ጉዳዩ አስቸኳይ ትኩረትን ይሻል።
አዲስ ዘመን ታኅሳስ 3/2013