በመማር መማር

የባሌ ሮቤ ሀገረ ጳጳሱ አባ ሰላማ “የኔ ልጅ ትምህርቱን ያቋረጠና ሚስቱን የፈታ ሰው እድሜ ልኩን ሲቆጭ ነው የሚኖረው” ሲሉ የተናገሩት፤ ተግሳጽ ከጆሮው እያንቃጨለ ሕሊናውን በጸጸት በትር ሲሸነትረው ከደም የወፈረ እንባ ጉንጩን ያርሰዋል። በቀድሞ አጠራሩ እነማይ ቢቸና አውራጃ ሸበል በረንታ ወረዳ የዱሃ ከተማ በለው አምባ መንደር ከአባቱ አቶ ተስፋዬ ደበበና ከእናቱ ከወይዘሮ ፀሐይነሽ አባተ 1962 ዓ.ም በወርሐ የካቲት 14 የተወለደው ሸዋንግዛው ተስፋዬ፤ ሞፈርና ቀንበር ተከትሎ በተወለደ በስድስት ዓመቱ በትራኮማ ሰበብ ብርሃኑን ተነጥቆ ዓይነስውር ሆኗል።

እንደመጀመሪያ ልጅነቱ መቀማጠል ሳይሆን የገጠመው የልጅነት ምዕራፉን የሚያጎድፍ ብሎም ሞራልን ሰብሮ ከሰው በታች የሚያደርግ ክስተት ነበር፡፡ ሕይወቱን ያጠላበት፤ የኢትዮጵያ ዓይነስውራን ብሔራዊ ማኅበር ምስጋና ይግባው እንጂ እንደወላጆቹ ሃሳብ ቢሆንማ ስጦ ጠባቂ ሆኖ ዘመኑን ይፈጅ ነበር። “ማን ያውቃል ሞቼ ልረሳም እችል ነበር” ይላል የዛሬ እንግዳዬ ሸዋንግዛው የያኔውን ኹነት ሲያስታውሰው አሁን የሆነ ያህል እያንገሸገሸው።

ወላጅ አባቱ በውትድርና ቀዬውን ሲለቁና ሴት አያቱ ከዚህ ዓለም በሞት ሲያልፉ እንዲሁም እናቱ ሌላ ባል ሲያገቡ የሸዋንግዛው ዕጣ ፋንታ ማረፊያ ጎጆ እንዳጣች ወፍ ወዲያ ወዲህ መባከን ሲሆንበት የቆሎ ተማሪ ቤት ገባ። ወደ ትምህርቱ የዘለቀው መሪጌታ በመሆን ዓብይ ዓላማውን የዕለት ጉርሱን ለመሙላት ነው። ዘመዴ የሚላቸው ሁሉ ለእርሱ አልተጨነቁምና አንጀቱ ተቆርጦ ስለዘመዶቹ እርም ብሎ የቆሎ ትምህርቱን የሙጥኝ አለ። ይህ በእንዲህ እንዳለ ነበር አጋጣሚዎች የትናንት ታሪኩን ሽሮ፣ ዛሬን አሳምሮና ነገን አቆንጅቶ የሚያፈካ ዕድል ያጎናጸፉት።

በአንደኛው ቀን ከትምህርት መልስ ወደቤቱ በማዝገም ላይ እንዳለ ሁለት ሰዎች በመቅረብ ሰላምታ ሰጡት። አብሯቸው አዲስ አበባ ቢሄድ የተሻለ ኑሮ እንደሚኖርም አግባቡት። እሱም በሰማው ነገር እጅጉን ተደስቶ ሳያቅማማ እሽታውን ዘየራቸው። አብሯቸው የሚሄደው ግን አሁኑ ልብስ ከገዙለት ብቻ እንደሆነ ገለጸላቸው። እነርሱም ፈቃዱን ለመሙላት ከልብስ ሱቅ ወሰዱት። ያስተማሪው እማወራ ተመለከቱት። የሰዎቹ ሁኔታ አልተዋጠላቸውምና እርሱን ለማዳን “የሰው ልጅ ሰርቀው እየሄዱ ነው፤ ሀገር ያዝልኝ” ብለው ጮሁ። ሁለቱ ሰዎች ሸዋንግዛውን በቆመበት ትተውም “እግሬ አውጭኝ” አሉ።

ለካስ እነዚያ ሰዎች ልጆችን አታለው በመውሰድ ለልመና የሚጠቀሙ የሰው እንክርዳዶች ኖረዋል? ሸዋንግዛውም ቢሆን የገዛ ቤተሰቦቹ “ገና ሲፈጠር ውሃ ሆኖ በቀረ፤ የአርባ ቀን ዕድሉ በጨለጠው” እያሉ በነገር ሳማ ከሚለበልቡት ይልቅ ወንበዴዎቹ ጋር መሄድን መርጦ ነበር። ምክንያቱ ደግሞ ከጥሩ መኝታ በላይ ጥሩ አንደበት ይበልጣልና ነው።

“አዲስ አበባ ላይ ወድቄ ብነሳ፣

አካላቴ ሁሉ ወርቅ ይዞ ተነሳ።”

ሲል እየሰማ ያደገው ዘፈን ቀልቡን አሸፍቶት የአዲስ አበባን ምድር በብርቱ ናፈቀ። የጸና ምኞቱም እውን ይሆን ዘንድ ፈለገ። አንድ ቀን ምኞቱ ተሳካ፤ በባዶ ሜዳ አልቀረበትም። የኢትዮጵያ ዓይነስውራን ብሔራዊ ማኅበር ከሰበታ መርሐ ዕውራን አዳሪ ትምህርት ቤት በተጨማሪ ባኮና ወላይታን ከፍቶ ስለነበር ዓይነስውራንን ከተደበቁበት ጓዳ ፈልፍለው እንዲያወጡ ለየአውራጃው በሰጠው አቅጣጫ መሠረት አሰሳ ሲደረግ ሸዋንግዛው ተገኘና ከተሸሸገበት የጨለማ ሕይወት መውጣት ቻለ።

አሻግሬ ከተባለ እኩያው ጋር ከማኅበሩ ዘንድ የደረሰው ሸዋንግዛው ዕጣ ሲደለደል እሱ ወላይታ ጓደኛው ደግሞ ባኮ ዓይነስውራን አዳሪ ትምህርት ቤት ተመደበ። 1972 ዓ.ም እግሩ የወላይታ ሶዶን ምድር የረገጠው ሸዋንግዛው ቀለም አወጋጉ ይበል የሚያሰኝ ቢሆንም ስፖርትና ሙዚቃ ትምህርቶች ጋር ግን “ዓይንህን ላፈር” ተባባሉና ውጤቱ አሽቆለቆለበት። በዚህም ሳቢያ የሚቆጨውና የማይረሳው መጥፎ የእድሜ ምዕራፉ ትዝታ ሆኖበት ቀረ። ከሦስት ዓመታት ቆይታ በኋላ ማለትም 1975 ዓ.ም ላይ አንድ ተማሪ በጤና ምክንያት ከወላይታ ወደባኮ የሚቀይረው ሲያፈላልግ ከወዳጁ አሻግሬ ጋር ለመገናኘት ሲል ሸዋንግዛው ጥያቄውን በይሁንታ ተቀበለ። በባኮ አዳሪ ትምህርት ቤት እስከ ስምንተኛ ክፍል ድረስ የነበረውን ቆይታ አጠናቆ ለሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤትን ተቀላቀለ።

“አስረኛ ክፍል ሲሆን ጥጋብ የሚሉት እንቅፋት አደናቅፎ ጣለኝና ትምህርቴ ተሰናከለ” ብሎ በማስተዛዘን ሲያጫውተኝ ሆዴን ቆረጠኝና እንደምን ዓይነት ጥጋብ? አልኩት። እርሱም ታሪኩን እንዲህ ሲል አጫወተኝ። ዘጠነኛ ክፍል ሲሆን ከአዳሪ ትምህርት ቤቱ ተቀብሎ እጁን የዘረጋለት የዓይነስውራን ማኅበር የቤት ኪራዩን ከመሸፈን ባለፈ ለቀለብ ወርሐዊ የኪስ ክፍያ 60ብር እንዲሁም ለዓመት ልብስ 100 ብር እየከፈለ ያለሃሳብ ትምህርቱን እንዲማር አስችሎት ነበር። ሸዋንግዛው ግን የትምህርት መርጃ መሣሪያውን፣ አልባሳቱንና የቤት እቃውን በመሸጥ ወደጅቡቲ ለስደት ተነሳ።

ከቤት ሲወጡ እንኳን ከስም በቀር አካላዊ ገጽታቸውን የማያውቃቸው አባቱ በውትድርናው ዓለም አሰብ እንደሚኖሩ ሲሰማ ጊዜ “በዚያውም አገኘዋለሁ” ሲል አሰበና የዔሊዳርንና የባንዳምን ሐሩር አቆራርጦ ከስፍራው ደረሰ። ነገር ግን የአባቱ ነገር እንደሰሜናዊት ኮከብ ሲቀርበው የሚርቅ ሆነበትና ተስፋው ነጥፎ ወደ አንዳባ ተሻገረ። በጉዟቸው መሐል እግሩ ለስልሶ ዳተኛ የሆነባቸው ሸዋንግዛው ወደኋላ ሲጎትታቸው በግመል አቆናጠጡትና ጎዳናውን እንዲጠቁማቸው ለአንድ አፋሬ አወጣጥተው በመክፈል ወደ ጅቡቲ ድንበር ሩጫ ሆነ።

ጅቡቲያውያን እንደሁለተኛ ከተማ ከሚገለገሉበት ተጆረራ ሲደርሱ ፀጉረ ልውጥ ናቸውና የአካባቢው ሰው ሰርቆ ሲያመልጥ እንደተያዘ ቀማኛ ከቦ ሲያጨናንቃቸው ተደናግጠው በአቅራቢያቸው ካገኙት ቤት ዘለው ገቡ። አንዲት የሀበሻ ወይዘሮ “ቤት ለእንግዳ” አለቻቸውና የተነጠቀች ነፍሳቸውን መልሳ ከሥጋቸው አዋሓደቻት። በተጆረራ ከተማ ሦስት ቀናትን ካረፉ በኋላም ሁኔታውን ሲያስተያዩት ሥራ እምብዛም በመሆኑ ወደ ጅቡቲ በሚሻገር መርከብ ተሹለክሉከው በውድቅት ሌሊት ማምለጥ ቻሉ።

ጅቡቲ ከተማም ብትሆን በሰፊ መዳፏ አልተቀበለቻቸውም። የነዋሪው መግባቢያ ቋንቋ ፈረንሳይኛ በመሆኑ በቀላሉ ከሰዎች ጋር መግባባት አልቻሉም። ከሰው ተገልለውም ብቻቸውን ቁልጭ ቁልጭ ሲሉ ያያቸው አንድ ግለሰብ በሚያውቃት ርጋፊ እንግሊዘኛ አርሂባ መስጊድ ከተባለው መንደር ቢሄዱ በርካታ ሀበሾችን እንደሚያገኙ ገልጾ አቅጣጫ ጠቆማቸው። ይህ ደግሞ ከመሰሎቻቸው ጋር መደመር እንዲችሉ አገዛቸው። ከጥቂት ቀናት መዋተት በኋላ ሸዋንግዛው ባልንጀራው ሥራ አግኝቶ ሲለየው ባይተዋርነት ደቆሰውና ለድባቴ ዳረገው። ይህን ጊዜ የቀረቡት ኢትዮጵያውያን ሁሉ ወደሀገሩ እንዲመለስ በማግባባት ያላቸውንና አቅማቸው የፈቀደውን ሳንቲም አጋጭተው ረጠቡትና ለቀዬው አፈር አበቁት።

ሸዋንግዛው ከትምህርቱ ይሁን አሊያም በሕልም ዓለም ከዋኘበት የሀብት ባሕር ሳይሆን በመቅረቱ እንደረመጥ ፈጅቶ ውስጥ ውስጡን ያደበነው ቁጭት እልሁን አንሮት በደወሌና አርፋ ከተሞች እየተዘዋወረ የኮንትሮባንድ ሥራውን ማጧጧፉን ተያያዘው። ይህም ቢሆን የዕለት ጥቅም እንጂ በዘላቂነት የጠረቃ የገቢ ምንጭ ሊፈጥርለት አልቻለም። በዚያ ላይ ከሕግ አስከባሪዎች ሌላ ከሱ አቅም የሚበልጡ ጎረምሶች እያስፈራሩ የሚወስዱበት እቃ እልቆ ስፍር የለውም።

ሸዋንግዛው የማትሪክ ውጤት አልመጣ ብሏቸው በተስፋ መቁረጥ ውስጥ ሆነው ድሬዳዋ ላይ ያገኛቸው የቀደሙት ጓደኞቹ በጣም ስላሳዘኑት በጣም ቀረባቸው። አንድ ሁለት በማለትም ያጠራቀመውን ጥሪት ዳግም ላያፈጅ ሙልጭ አድርጎ አጠፋው። በዚህ ሳያበቃም ጓደኛ መምረጥ እንዳለበት ልብ ቢልም ከረፈደ ሆነበትና “ካፈርኩ አይመልሰኝ” በሚል እሳቤ ከዞረው ያልኮል ሱስ ውስጥ ጭው ብሎ ገባ።

“አንተ ደግሞ! ያራዳ ልጅ አይደለህም እንዴ? ብርና ወጣትነትን ሳያልፍ በጊዜ ነው ውብ ትዝታ መሸመት ያለብህ” እያሉ ካንጀት ባልሆነ ሸርዳጅ አንደበታቸው እየካቡ የያዘውን እንጥፍጣፊ ገንዘብ አለቡት። እሱም ቢሆን “ጌታዋን ያመነች በግ ላቷን ከደጅ ታሳድራለች” የሚሉት ተረት ደረሰበትና ከአንገት በላይ ያሳዩት ውዴታ እውነት መስሎት ልቡንም ኪሱንም እንዲያዙበት ፈቀደላቸው። ይህ ደግሞ ከማይወጣው አዘቅት ውስጥ ዘፈቀው። የዚህ ጦስም የኑሮውን ዙሪያ ጥምጥም በመከራ እሾህ አጥሮ ከራሱ አልፎ ለሰሚውም ለማመን በሚከብድ ከልመና የሕይወት ባሕር ውስጥ በጥልቁ አሰጠመው።

የሃሳብ ማዕበል በጸጸት ውቅያኖስ ሲደፍቀው በምን አልባት የያዘውን የትምህርት ማስረጃ ይዳብስና በእንባ ይታጠባል። “ኑሮ ካሉት” ይሉት አባባል የኑሮ መልኩን ዓይነቱን አበዛበትና አልጨበጥ ቢለው ድሬዳዋን ለቆ ወደ አዳማ ለመሻገር በባቡር ተነሳ። ወቅቱ የደርግ ሥርዓት ወድቆ ኢሕአደግ የገባበት ጊዜ ነበርና አሰቦት ሲደርሱ ጫካ ውስጥ ያደፈጡ ሽፍቶች የከፈቱት ተኩስ ባቡሩን ወንፊት አደረገው። ሸዋንግዛው ግን የሰማው የተኩስ ድምፅ ባቡሩን ካጀቡት የፀጥታ ኃይሎች መስሎት ወሬ ለማዳነቅ ከወንበሩ ሲነሳ ካጠገቡ ያለው ወታደር ገፍትሮ መሬት ባያሲዘው ኖሮ የሚንደቀደቀው የጥይት እሩምታ በልቶት ነበር።

በዚህ መሐል ነው ከርታታው ሸዋንግዛው የትምህርት ዶክመንቱ እስከወዲያኛው ከጁ ሾልኮ የጠፋው። የትምህርቱን ነገር ዳዋ እንደዋጠው አምኖ ባለበት ወቅት ደግሞ ሌላ አሳዛኝ ዜና ሰማ። የጎዳና ሕይወትን በአዳማ ሲገፋ ያገኛቸው ዓይነስውራን ነበሩ አቀማጥሎ ያስተማረው የኢትዮጵያ ዓይነስውራን ብሔራዊ ማኅበር መፍረሱን ያረዱት። መቼም “ወይ ድንግርግር ተጓዝ ያለው እግር ነውና ለማኙ በዝቶ ገቢዬ ሲቀንስ አዳማን ለቅቄ ባሌ ሮቤ ተሻገርኩ” ይላል ባለታሪካችን ሸዋንግዛው ተስፋዬ።

ደጅ ጠንቶ ያለበትን ሁኔታ ያዋያቸው የባሌ ሮቤ ሀገረ ጳጳስ አባ ሰላማ “የኔ ልጅ ትምህርቱን ያቋረጠና ሚስቱን የፈታ ሰው እድሜ ልኩን ሲቆጨው ነው የሚኖረው” ሲሉ በመገሰጽ፤ ከመቃብር ቤት አስጠጉትና ለዕለት ጉርሱ ጥቂት ፍራንክ ረጠቡት። ይህ ልማዳዊ ሕይወት ሲደጋገምበት ታከተውና በስም ብቻ ወደሚያውቃት አርባ ምንጭ አመራ። እዚያ እንደደረሰ በቀን ሃምሳ ሳንቲም እያስከፈሉ ወለል ከሚያሳድሩት እማማ ብርሃኔ ቤት ሲዘልቅ ተከትሎት የመጣ የቁጣ ድምፅ ከጆሮው ጥልቅ አለ።

“የምታሳድሪያቸው ሰዎች ለመሞት ያልቦዘኑ እንደሆነ እኛ በመቅበር አቅማችን መዛል አለበት?” አለ የቀበሌ ሹሙ። ሸዋንግዛው የሰማው ነገር አስደንብሮት መላ ሰውነቱን በማማተብ ውዳሴ ማርያም እያነበነበ ሲወጣ ያዩት አባ ኃይሉ ተቀበሉትና የዘወትር ጸሎትን እንዲያስተምራቸው በማሰብ በረንዳውን አንጥፎ ይተኛ ዘንድ ፈቀዱለት።

በእንዲህ መልኩ እየኖረ ሳለ በአንደኛው ቀን የአባ ኃይሉ ልጅ ከከፈተችው መሸታ ቤት ጎራ ሲል ፍሬው ከተባለ ሰው ጋር ተዋወቀ። ውሉ የጠፋውን የትምህርት መንገድ መራው። በፍሬው አማካኝነት የተዋወቀው ገዛኸኝም በአርባ ምንጭ ትምህርት ጽሕፈት ቤት የልዩ ፍላጎት ዘርፍ ተጠሪ በመሆኑ የጠፋውን የሸዋንግዛውን ዶክመንት በማሟላት ከትምህርት ገበታ መለሰው። ይሁን እንጂ አሁንም ቢሆን ከትምህርት ጋር ተጎራበጡ። ምንም ዓይነት ድጎማ ስላልነበረው ለረሃብና ርዛት ተጋለጠ።

ገዛኸኝ የወላይታ ሶዶ ዓይነስውራን አዳሪ ትምህርት ቤትን ሲያናግርለት ርዕሰ መምህር የነበሩት እንደሻው ካሣ ለካስ ሸዋንግዛውን ያውቁት ኖሯል። ባየው መከራ እጅጉን አዝነው ከዞኑ ትምህርት ቢሮ ጋር በመነጋገር ትምህርቱን እንዲቀጥል አስቻሉት። እሱም ያሳለፈው ስቃይ ትምህርት ሆኖት 10ኛ ክፍል ላይ ጥሩ የኮሌጅ መግቢያ ውጤት በማምጣት ሃዋሳ መምህራን ኮሌጅን ተቀላቀለ።

የሁለተኛ ዓመት ተማሪ ሳለ የጀመረው ፍቅር ልጅ ጠራበትና “ምን ሳይጠና ጉተና” ሆነበት። ምን ይደረጋል ጥርሱን ነክሶ በመማር ተመረቀና በወላይታ ዞን ሁንቦ ጣባላ ወረዳ ሆብቻ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በእንግሊዘኛ ቋንቋ መምህርነት ተቀጠረ። በጥረቱ ውዴታን ያተረፈው ሸዋንግዛው በዚያው ዓመት ለዲግሪ ትምህርት አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ገባ። ሕይወት ያስተማረችው ሸዋንግዛው ትምህርቱን አጥብቆ በመያዝ ጎን ለጎን አዲስ አበባ ለመግባት ማስታወቂያ መከታተል ጀመረ። ልክ ትምህርቱን እንደጨረሰም ዕድል ቀናውና በሽመልስ ሀብቴ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በሥነዜጋ መምህርነት ተጠራ።

ለሸዋንግዛው ሁሌ ዕድል አትቦዝንም። ሌላኛውን የትምህርት ምዕራፍ ከፍታለታለች። ይህም በኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርስቲ ለሁለተኛ ዲግሪ መርሐ ግብር ያለፈበት ነው። በ2016ዓ.ም ተመርቆም ሦስት ልጆቹን ያስተምራል። ከራሱ አብራኮች አልፎ እሱ ያሳለፈውን ሕይወት እንዳይደግሙ ቀላል ለማይባሉ ሕጻናት የትምህርት መርጃ መሣሪያዎችን ድጋፍ ያደርጋል። እኛም ከእድሜው ተምረን ቁምነገር እናተርፍ ዘንድ በማሰብ የሕይወት ገጹን አስነበብናችሁ።

ሰላም!!

ሃብታሙ ባንታየሁ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሐምሌ 12 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You