የውዳሴ መጻሕፍት ማዋዣ፤
ታላላቅ ሰዎች ስለ ታላላቅ መጻሕፍት ብዙ መስክረዋል፤ ብዙም አስነብበዋል፡፡ ታናናሾችም እንዲሁ ስለ እኩያቸው መጻሕፍት የአቅማቸውን ያህል እየሰነዘሩ ለብጤዎቻቸው የሚመጥናቸውን ብሂሎች ፈጥረውላቸዋል፡፡ “የመጻሕፍት ጠቀሜታ እያበቃለት ነው” በማለት የሚዘይሩ “የዕውቀት ጥላ ወጊዎች” የመኖራቸውን ያህል “ዘለዓለማዊ ዕድሜ ለመጻሕፍት!” እያሉ በመዘመር አንብበው የሚያስነብቡ አፍቃሬ ጥበብ ልሂቃንም ቁጥራቸው ዘያሪዎቹን ሺህ ጊዜ ያስከነዳል፡፡
ስለ መጻሕፍት “ማን ምን ብሎ መስክሮ ነበር?” ለሚለው ግዙፍ ጥያቄ “የጥበባት ጉባዔ” በሚለው መጽሐፌ ውስጥ የቅምሻ ያህል የጠቃቀስኳውን እውነታዎች መለስ ብሎ ማንበቡ ያግዝ ይመስለኛል፡፡
በቅርቡ ያነበብኩት አንድ መጽሐፍ ስሜቴን ሰቅዞ በመያዝ በተወሰኑ ገፆች ላይ ዓይኔን ተክዬ እንድቆይ አስገድዶኝ ነበር፡፡ የይዘቱ ዝርዝር ትንሽ ሰፋ ያለ ቢሆንም “ጭማቂ ይዘቱ” በሚከተለው ሃሳብ ሊወከል ይችላል፡፡ “ቁስልን የሚያኩ መጻሕፍት ስሜትን አጥቁረው ያስለቅሳሉ፡፡ ፍቅርን የሚሰብኩ ገፆች የዳመነውን ስሜት ገፈው ያስፈነድቃሉ፡፡ የድብርት ጫና የሚያሸክሙ መጻሕፍት ከጠቆረው ስሜት ውስጥ የበቀል ካፊያ ያዘንባሉ፡፡
ዕውቀት የሚመግቡ መጻሕፍት ሰብዕናን ያፋፋሉ፡፡ የሀገርን ጓዳ ፈትሸው ጥበብ የሚዘሩ መጻሕፍት የሚዘከሩት ግን ከፍ ያለ የሕዝብ ባለውለታ እንደሆኑ እየታሰበ ነው፡፡ በአልባሌ እጅ ላይ የወደቁ ክቡር መጻሕፍት የመደርደሪያ ጌጥ ሆነው ከማርጀት በዘለለ የሙታን ትንሳኤ ወግ ሳይደርሳቸው የመቃብር አቧራ እንደተጫናቸው መዝለቃቸውም አይዘነጋም፡፡” “ቀስት እንደ ወርዋሪው፣ ልጅ እንዳሳዳጊው፣ ሀገር እንደ መሪው” እንዲሉ መሆኑን ልብ ይሏል፡፡
በውዳሴ መጻሕፍት መንደርደሪያነት ለማንዣበብ የፈለግሁት ለመልዕክቱ ሙሉ ይዘት ባእድ ሆኜና ተኳርፌ አብሬው የኖርኩት አንድ መጽሐፍ ሰበብና ምክንያት ሆኖኝ ነው፡፡ ይህን መጽሐፍ የገዛሁት ወድጄ ሳይሆን የመምህሬ ትዕዛዝ ስለሆነብኝ ነበር፡፡ ውጭ ሀገር በትምህርት ላይ በነበርኩበት ወቅት አሜሪካዊው ፕሮፌሰር መምህሬ ፊል ፍሬዘር የኮርሳቸው ማጣቀሻ መሆኑን በመግለጽ መጽሐፉን ገዝተን በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ አንብበን ለክፍል ውስጥ ውይይት እንድናቀርብ ቀጭን ትዕዛዛቸውን እንደ መርግ አሸከሙን፡፡
የመጽሐፉ ደራሲ ማርቲን ቡበር (Martin Buber, 1878 – 1965 ) ይባላል፡፡ ከደራሲነቱ በተጨማሪ የመጠቀ አእምሮ እንዳለው የሚመሰከርለት ቡበር የፍልስፍና ሊቅ፣ ተርጓሚ፣ ኃያሲና የፖለቲካ አንቂ እንደነበር ግለ ሰብእናው ይመሰክራል፡፡
መጽሐፉ በመጀመሪያ የታተመው በጀርመንኛ ቋንቋ እ.ኤ.አ በ1923 ዓ.ም ሲሆን ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ እንግሊዘኛ የተተረጎመው እ.ኤ.አ በ1937 ዓ.ም ነበር፡፡ “I and Thou” የሚል ርዕስ የተሰጠው ይህ መጽሐፍ የዘውጉ መደብ ከሰው ለሰው ግንኙነትና ፍልስፍና ጋር የተጎዳኘ ሲሆን የሚያነሳቸው ሃሳቦችም እጅግ ረቂቅና ውስብስብ ከመሆናቸው የተነሳ ሲነበብ ብዙ ጥሞናና ማሰላሰል ይጠይቃል፡፡
የመጽሐፉ ርዕስ በጥሬ ትርጉም በቀጥታ ወደ ቋንቋችን ሲመለስ “እኔ እና አንተ/አንቺ” የሚል ይዘት ቢኖረውም በመጽሐፉ ትንታኔ ውስጥ በጎላ መልኩ ትኩረት የተደረገባቸው ሃሳቦች “እኛ ማለት እነርሱ” የሚለው በጎ ሃሳብና “እኛ እና እነርሱ” የሚሉ አሉታዊ ጽንሰ ሃሳብ ያቀፉ ሰፋፊ ሃሳቦችና ዕውቀቶች በተነፃፃሪነት እየተተነተኑ ነው፡፡
በይዘቱ የጠነነውን፣ በፍልስፍና ሃሳቦቹ የረቀቀውን ይህንን መጽሐፍ አንብቤ ለመጨረስ ብቻም ሳይሆን የፍልስፍናውን የይዘት አስኳል በአግባቡ ፈልቅቆ ለመረዳት የፈጀብኝ አንድ ሳምንት ብቻ ሳይሆን ሁለት ዐሠርት ዓመታትን ያህል ነው፡፡ ዛሬም ቢሆን ሙሉው ይዘት ተገልጦልኛል ለማለት ድፍረቱ የለኝም::
ለማንኛውም መጽሐፉን እንደገና አንስቼ ለማገላበጥ ምክንያት የሆነኝ ሀገሬ ዛሬ ያለችበት ሁኔታ ምክንያት ሆኖኝ ነው፡፡ ደራሲው ማርቲን ቡበር “እኛ እና እነርሱ” የሚል ትንታኔ ከሰጠባቸው መሠረታዊ የፍልስፍና ጭብጦች መካከል አንድ ሰበዝ በመምዘዝ ከሀገራዊ ዐውዳችን ጋር በማያያዝ ጥቂት ሃሳቦችን ለመፈንጠቅ እሞክራለሁ፡፡
መዘዘኛው “የእኛ እና የእነርሱ” አስተሳሰብ፤
እንደ ደራሲ ቡበር እምነት “እኛ እና እነርሱ” የሚለው ጽንሰ ሃሳብ መፈተሽ ያለበት ሰብዓዊና ሰዋዊ ግንባታችንንና ማንነታችንን መሠረት በማድረግ እንጂ የውክልና ያህል መለያ የተሰጣቸውን ምልክቶች በማጉላት መሆን የለበትም፡፡ ይህ አመለካከት እንደ ደራሲው እምነት “I Thou” ሳይሆን “I It” ይሆናል ማለት ነው፡፡
ጥቂት ላብራራው “It” የሚወክለው የሰብዕና ቅመሞችን ወይንም ማንነታችን የተሸመነበትን ተፈጥሯችንን ሳይሆን ውጫዊና ከሌላ አካል፣ ተገደንም ይሁን ፈቅደን የምንቀበላቸውን ሽፋኖች ነው፡፡ ለምሳሌ አንዲትን በጎዳና ላይ ላስቲክ ቤት ወጥራ የምትኖርን ቤት አልባ ግፉዕ እህትን በምትኖርበት ጣሪያና ግድግዳ ወይንም በአካባቢዋ በሚስተዋሉ ትዕይንቶች (በ“It”) ፈርጀናት “የጎዳና ተዳዳሪዋ” ብሎ ከመበየን ይልቅ የራሷ ታሪክ፣ ብርታትና ሽንፈት፣ ፍልስፍናና ዕውቀት የተካነች “እናት፣ እህት፣ ሚስት” መሆኗ ቀድሞ ሊታሰበን ይገባል፡፡ ይህ አመላካከት “እርሷ ማለት እኔ ነኝ፤ እኔ ማለት እርሷ ነች፡፡
ይሄ ሁሉ ጉስቁልና የደረሰባት እኔ/እኛ/ገዢው መንግሥት/ ማሕበረሰቡ ሰብዓዊና ሕጋዊ ድርሻውን ባለመወጣቱ እንጂ ሀገሯ እርሷን ማኖር አቅም ስለሌላት ወይንም ተፈጥሮ መሠረታዊ ፍላጎቶቿን ለእርሷ ለማሟላት ንፉግ ስለሆነች አልነበረም ወደሚል ፍልስፍና ይወስደናል:: የ “I Thou” መሠረታዊ ፍልስፍና አስኳልም በአጭሩ ይህንን ይመስላል፡፡
የግለሰቦችን የስሜት ሕመም ለመፈወስም ሆነ የማሕበራዊ ጉስቁልናና ደዌ ተደርገው የሚቆጠሩ ህፀፆችን ለማከም ካስፈለገ በቅድሚያ ሊወሰድ የሚገባው እርምጃ ውጫዊ ሽፋኖችን ከማራገብ ይልቅ በተሸረቡ የጋራ ሰብዓዊ ተፈጥሯችንና እሴቶቻችን ላይ ማተኮሩ ለመፍትሔው የሚጠቅም ውጤታማ የሕክምና ዘዴ ሊሆን ይችላል፡፡
አንዳንድ ሀገራዊ ማሳያዎች፤
አንድ፤ በማሕበረሰባችን ውስጥ “እኛ ማለት እነርሱ” ከማለት ይልቅ “እኛ እና እነርሱ” እየተባባልን የምንገፋፋባቸውን በርካታ ልዩነቶች መጠቃቀስ ይቻላል፡፡ ለዚህን መሰሉ መሠረታዊ ሀገራዊ ችግራችን ቀዳሚ ማሳያ ሊሆን የሚችለው ሀገሪቱ እየተመራችበት ያለው ሕገ መንግሥት ነው፡፡
“እኛ የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች” በሚል ከፋፋይ መነሻ የሚንደረደረው የሕጎች ሁሉ “አባት” ተደርጎ የሚቆጠረው ይህ የሕገ መንግሥት ሰነድ ያደረሰብን አሳር እነሆ ዛሬም ድረስ ለምንጋተው መከራ ዋናው ተጠቃሽ ሰበብ እንደሆነ በስፋት ይታመናል፡፡
ይህ የሀገሪቱ ዋና የችግር ምክንያት ተደርጎ እየተፈረጀ ያለው ሕገ መንግሥት “በማር የተሸፈነ መርዝ” እንዲሉ ለክፋቱ መገለጫ ያደረገው (የራሱ ከፋፋይ ይዘት እንደተጠበቀ ሆኖ) እርሱን ተመሥርተው የተዘጋጁት ክልላዊ ሕገ መንግሥታት እንደ ዋና የዓላማ ተልእኮ ማስፈጸሚያ ተደርገው መቀረጻቸው ነው፡፡ ለምሳሌ፤ አንዳንድ ክልሎች “እኛ ብሔረሰቦች” በማለት በሕገ መንግስታቸው ውስጥ ያሰፈሩት “ነባር” እየተባሉ
እንኮኮ የተባሉትን ውሱን ብሔረሰቦች በመነጠል እንጂ የሰብዓዊነት መገለጫ በሆኑትና በመዋለድ፣ በመጋባት፣ በመዛመድ፣ አብሮ በመኖርና የጋራ ታሪክ በመጋራት የተጋመዱትን፣ በክልሉ ውስጥ አብረው የሚኖሩትንና “በመጤነት” የተፈረጁትን ወንድም የብሔረሰብ አባላት በማካተት አይደለም፡፡
የሁሉም ክልሎች ሕገ መንግሥታት ይዘት በአጭሩ “እኛ እና እነርሱ” በሚባል የተጣመመ ፍልስፍናና መርህ ላይ ስለተመሰረቱ ባስከተሏቸው ውጤቶች “ከእከሌ ክልል የተፈናቀሉ፣ የተሰደዱና ንብረታቸው የወደመባቸው” የሚሉ ገለጻዎች የተለመዱ የእለት ቋንቋችን እስከ መሆን ደርሰዋል፡፡
ኑሮ ከተባለ በአብዛኞቹ ክልሎቻችን ውስጥ “ከእኛ” ውጭ የሚኖሩትና “እነርሱ” በመባል የሚታወቁት ኢትዮጵያውያን ልክ እንደ ባእዳን መጤዎችና ፍልሰተኞች ስለሚቆጠሩ በሚኖሩበት ክልል ውስጥ ለፖለቲካ ሥልጣን ተጋሪነትንም ሆነ ለማኅበራዊ ትሩፋቶች ተካፋይነት መብት እስከማይኖራቸው ድረስ “ተፈርዶባቸዋል፡፡”
በዚህ ዐውድ መሠረት “እኛ” የሚወክለው ሥር የሰደደውን ክፉ ፍልስፍናና ገዢነትን ሲሆን ተገዢዎቹ፣ ተሳዳጆቹ፣ ተፈናቃዮቹና መጻተኞቹ ደግሞ “እነርሱ” በሚለው ፍረጃ ውስጥ የሚወድቁት ናቸው፡፡
ሁለት፤ ሰሞኑን ተከብሮ የተጠናቀቀውን የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን አከባበር ልብ ብለን አጢነን ከሆነ በንግግሮችም ሆነ በትዕይንቶች ውስጥ ሲስተዋል የነበረው “በእኛነት ውስጥ የእነርሱም ፍልስፍና ንብርብር” ወይንም የአንዲት ኢትዮጵያ የውበት መገለጫ ኅብረ ጥበባት ሳይሆን የ“እኛ” እና የ“እነርሱ” ፍልስፍና አፍጥጦ ወጥቶ ነበር፡፡ ሃሳቡን ይበልጥ ግልጽ እንዲያደርግልን አንዳንድ እውነታዎችን ላስታውስ፡፡
ባለፈው ሳምንት ጽሑፌ ውስጥ ለማሳየት እንደሞከርኩት በባህል የጥናት ዘርፍ “ቱባ ባህል” ብሎ ለመበየን እጅግ ጥንቃቄ ያስፈልጋል፡፡ የግድ ባህሌ “ቱባ ነው” ብሎ ለመከራከር ቢያስፈልግ እንኳን የባህሉ መገለጫዎች ሙሉ ለሙሉ (ሊሆን አይችልም እንጂ ከሆነ) ከባለ ባህሎቹ የአኗኗር ዘይቤ የተቀዳ ሊሆን ግድ ነው:: በምሳሌ እናብራራው፡፡ የሀገራችንን አንደ የብሔረሰብ ባህል ለአብነት እንውሰድና እንፈትሽ፡፡
የመረጥነው የብሔረሰቡ አባላት “የእኛ” ብለው የሚለብሷቸው አልባሳት የተሸመኑት ወይንም የተፈበረኩት በሌላ ብሔረሰብ ወይንም በባዕድ ሀገራት ዐውድ ውስጥ ሊሆን ይችላል፡፡ የመዋቢያ ቁሳቁሶችም እንዲሁ የተፈጠሩት ምናልባትም እንዳለ በሚባል ደረጃ ባህላችንን በማያውቁ ሀገራት ውስጥ ሊሆን ይችላል፡፡ ቁሳቁሶቹ ሲፈበረኩም “ለማያውቁት የኢትዮጵያ አንድ ብሔረሰብ” ብቻ ግድ ብሏቸው ሳይሆን በመላው ዓለም እንዲሰራጭና ገበያ ውስጥ ገብቶ እንዲያተርፋቸው ተዘጋጅተውበት ሊሆን ይችላል፡፡
በዚህ መሠረታዊ ሃሳብ የምንስማማ ከሆነ “የአለባበስ ቱባነቱ” ምኑ ላይ ነው? ለግብርና የምንጠቀምባቸውን መሳሪያዎችና የአስተራረስ ባህላችንን፣ አመጋገባችንንና የባህላዊ ጭፈራችንን ወዘተ. በሙሉ እየነጠልን “ይሄ ለእከሌ ብቻ የተሰጠ የቱባ ባህሉ ሃብት ነው” ብሎ የጭፍን ለመበየን መሞከር በእጅጉ ያሸማቅቃል፡፡ “የባህላዊ አልባሳቶቻችንን አዝራር (ቁልፎች)”፣ የአደን መሣሪያዎች ወዘተ. ሳይቀር “ባዕዳን ከምንላቸው” ሀገራት ገበያዎች እየጎረፉልን “ባህላችን ቱባ ነው!” ብለን ብንፎክር ከስሜት ቀረርቶ የሚያልፍ ፋይዳ አይኖረውም፡፡
“እኛ” ብለን የምንናገረው “በእነርሱ” ውስጥ ተዋህዶ እስካልተሸመነ ድረስ በፖለቲከኞች “አሀዳዊነት፣ ጨፍላቂነት” ማስፈራሪያ በመደነጋገር ብቻ “እኛን” ሰማይ ሰማያት ላይ አጉነን “እነርሱ” ከምንላቸው ሌሎች ባህሎችና ወገኖች የምንፋታ ከሆነ ነገራችን ሁሉ የእምቧይ ካብ” ከመሆን አይዘልም፡፡ በብሔረሰቦች በዓል ላይ ሲስተጋባ ከረመ ያልኩትም ይህን መሰሉን “እኛ” እና “እነርሱ” የሚለውን “በቱባ የታጀበ” መነጣጠል ነው፡፡
በሐመር ብሔረሰብ የአኗኗር ዘይቤ ውስጥ ሲዳማውም፣ ጌዲዮውም፣ ወላይታውም፣ አማራውም፣ ኦሮሞውም፣ ጉራጌውም ወዘተ. የተሸመኑት አብረው ነው፡፡ አማራው ለብቻ “እኛ” ቢል ያለ ኦሮሞው፣ ያለ ትግሬው፣ ያለ ከፍቾው፣ ያለ ሃዲያው፣ ያለ ከምባታው አያምርበትም፡፡ ማማር ብቻም ሳይሆን ምልዑ ሊሆንም አይችልም፡፡ በባህል ተወራርሷል፣ በደም ተቀላቅሏል፣ በጋብቻ ተጣምሯል፣ በሥነ ልቦና ተጋምዷል፣ በታሪክ ተነባብሮ ተሸምኗል፡፡
እንዲያው በደምሳሳው አንድነቱ የብዙኅነት ውጤት ነው፡፡ የየብሔረሰቡ ባህል “የግሉ ነው! ቱባ ነው!” ብሎ ጮክ ብሎ የሚያዳምቅ ተከራካሪ ከተነሳም “የቱባነቱ ድሮች” የተጋመዱት “እነርሱም በእኛ ውስጥ አሉ” በሚል ፍልስፍና ላይ ተመስርቶ እንጂ “እኛ ብቻ፣ የእኛ ብቻ” በሚል ነጠላ አመለካከት እያስተጋቡ መሆን አይገባም፡፡
“እኛ በእነርሱ ውስጥ” የሚለውን የረቀቀ ፍልስፍና ሳልዘነጋ የድምጻዊት እጅጋየሁ ሽባባው የቅኖችን ቅንዓት ያስተጋባችበትን አንድ የዜማ ግጥም ባስታውስ ቦታው ይመስለኛል፡፡
ጎጃም ያረሰውን ለጎንደር ካልሸጠ፣
ጎንደር ያረሰውን ለጎጃም ካልሸጠ፤
የሸዋ አባት ልጁን ለትግሬ ካልሰጠ፣
የሐረር ነጋዴ ወለጋ ካልሸጠ፤
ፍቅር ወዴት ወዴት ወዴት ዘመም ዘመም፣
ሀገርማ አለችኝ ሀገር የእኔ ህመም፡፡
በመጨረሻም በመጽሐፍ ወግ ተንደርድሬያለሁና ከመጻሕፍት ጋር በሚጎዳኝ አንድ ሃሳብ ጽሑፌን ልደምድም፡፡ ለተለያዩ ጉዳዮች መድረክ ላይ ከተጋበዝኩባቸው ኩነቶች እጅግ የሚበዛው ለመጻሕፍ ምረቃ የታደምኩበት መርሃ ግብር ነው፡፡ ብዙ ደራሲዎች መጽሐፋቸውን ሲያስመርቁ የመልካም ምኞት መልዕክት ለማስተላለፍ ዕድል አግኝቻለሁ፡፡
ከተገኘሁባቸው ፕሮግራሞች መካከል አንዳንድ ደራሲዎች በማወቅም ይሁን ባለማወቅ በሥራዎቻቸው ውስጥ “እኛ” እና “እነርሱ” የሚል ፍልስፍና አጉልተው ለማስነበብ የተዘጋጁ ስለነበሩ ማዘኔ አልቀረም፡፡
እንዲያውም አንዳንድ ደራሲዎች በድፍረትና በንቀት ጭምር አንዱን ብሔር ከአንዱ እያፋቱ “እኛ ከእነርሱ ጋር ድርሻና ዕድል ፈንታ አንጋራም፤ እኛ የተለየንና ምንትስ ነን …” የሚሉ ዓይነት ክፉ ዘሮችን ዘርተው ትውልዱ ላይ የሚጠዘጥዝ ጠባሳ እንዳኖሩም ለመገንዘብ ችያለሁ፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ክፉ የእንክርዳድ ዘር በትውልዶችና በታሪክ ፊት የሚያስወቅስ ብቻም ሳይሆን “በእነርሱ ውስጥ እኛ” የሚለውን እውነታ መበከል ስለሆነ በወንጀል የሚያስጠይቅም ጭምር ነው::
“እነርሱ ማለት እኛ ነን፤ እኛ ማለት እነርሱ ናቸው!” የሚለው እውነት እስካልበራልን ድረስ “እኛ” እና “እነርሱ” እያልን በነጠላ ሃሳብ የምንጓዝ ከሆነ ከአብሮነት ብቻ ሳይሆን ከእድገትና ከብልጽግና መደነቃቀፋችን አይቀሬ ይሆናል፡፡ ይህንን መሠረታዊ ፍልስፍና የርዕዮተ ዓለሙ መርህ የሚያደርግና “እኛ በእነርሱ ውስጥ” የሚለውን መርህ ከፍ አድርጎ የሚያውጅ ተሟጋች ፓርቲ እስካልተፈጠረ ድረስ “የራሳችን ቱባ” ወግ ብቻ እያሉ የሚፎክሩ ቡድኖች በሚፈጥሩት ሴራ እየተጠለፍን ለመኖር መገደዳችን አይቀሬ ይሆናል፡፡ ማርቲን ቡበር ለመነሻ ሃሳቡ አመሰግናለሁ፡፡
ሰላም ይሁን::
አዲስ ዘመን ታኅሳስ 03 /2013