
በዘረመል ምሕንድስና የበለፀገ በቆሎ ለገበያ ሊቀርብ ነው የሚለው ሰሞነኛ ዜና ለዛሬ መጣጥፌ መነሻ ሆኖኛል። ከ20 ዓመታት በፊት የተዋወቀው በዘረመል ምህንድስና ዘዴ የተመረቱ የግብርና ምርቶች (GMO) ጥቅም ላይ ማዋል በዓለም አቀፍ ደረጃ ብዙ ክርክሮች የተነሱበት ጉዳይ ነው።በኢትዮጵያም ይህ ርዕሰ ጉዳይ ብዙ መከራከሪያ ሆኖ የቆየ ቢሆንም አሁን ላይ ግን ከሙከራ በዘለለ የጥጥ ምርት ቀደም ብሎ እንዲሁም የበቆሎ ምርት ደግሞ በቅርቡ ለገበያ እንዲቀርብ ፈቃድ ተሰጥቷል።
በዚሁ ርዕሰ ጉዳይ በኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ በተደረገ ምሁራዊ ክርክር መድረክ ላይ በተወያይነት የቀረቡት ፕ/ር ፍሬው በGMO ላይ የሚነሱት ክርክሮች ” ያለቀ ጉዳይ ነው ” ሲሉ በተለያዩ ሀገራት እና ተቋማት ተቀብለዋቸው እየተጠቀሙበት መሆኑን ገልጸዋል።ሌላኛው ተሳታፊ ፕ/ር ጥልዬ ፈይሳ ” የGMO ጉዳይ በህክምና ብዙ ጥያቄ አይነሳበትም ለምሳሌ ኢንሱሊን የሚመረተው በዚሁ መንገድ ነው ” ሲሉ በምርት ደረጃ አሁን ላይ በዓለም አቀፍ ደረጃ በ2024 ብቻ 209.8 ሄክታር መሬት በዚሁ ምርት መሸፈኑን ገልጸዋል።
ጥቅሙንም ሲያስረዱ ” ምርት ይጨምራል፤ በተባይ ለሚጠቁ ሰብሎች መፍትሔ ይሆናል ” ሲሉ አንስተው ተከራክረዋል። ለምሳሌም የጥጥ ምርት በተባይ በጣም ስለሚጠቃ ምርቱ እና ጥራቱ የወረደ ነበር ዘረመል ልውጥ የጥጥ ምርት (BT Cotton) ግን ይሄንን መቋቋም የቻለና ውጤታማ መሆኑን ይገልጻሉ።በተመሳሳይ የሙከራ ምርቱን የጨረሰው ድርቅና ተባይ ይቋቋማል የተባለው የበቆሎ ዝርያም በምርቱ ” 56 በመቶ የምርት ጭማሬ አሳይቷል ” ሲሉ በተለይም ለቲክቫህ ኢትዮጵያ በሰጡት ማብራሪያ ላይ አንስተዋል።
በተቃራኒ ጎራ ሆነው ሲሞግቱ የነበሩት ዶ/ር ጸደቀ ግን በዘረመል ምህንድስና ዘዴ የተመረቱ የግብርና ምርቶች ” ምርት አይጨምሩም ይህንን አምራቾቹም በራሳቸው አይናገሩም ” ሲሉ መከራከሪያ ሃሳባቸውን አንስተዋል።” ልማትን በሦስተኛ ወገን ልታስብ አትችልም” የሚሉት ዶ/ር ጸደቀ ” ምርት ይጨምራል የሚለውም ምርት አይጨምርም ማናጅመንቱ ነው በሙከራ ላይ ምርት እንዲጨምር የሚያደርገው ” ሲሉ ሃሳባቸውን አንስተዋል።” ያለንን ቴክኖሎጂ አሟጠን አልተጠቀምንም” ፤ ” የገበሬው ምርት እና ጥናቱ መካከል ልዩነት አለ ” ፤ ” አንዴ ከገባንበት ደግሞ መመለሻው ከባድ ነው ” ፤ ” የተቋማት ጥገኝነት ያመጣል (Corporate Dependency) ” የሚሉ መከራከሪያ ነጥቦችን አስቀምጠው ሞግተዋል።
በክርክር መድረኩ GMO ደግፈው የተሳተፉት ፕ/ር ፍሬው መክብብ፣ ፕ/ር ጥልዬ ፈይሳ እና ዶ/ር ታደሰ ዳባ ፣ ዶ/ር ጸደቀ አባተ ያነሷቸውን ነጥቦች ላይ ምላሽ ሰጥተዋል።ካነሷቸው ዋና ዋና ነጥቦች መካከል፦
– ለገበሬው አማራጭ እንስጠው፤
– የሦስተኛ ወገን ጫና ሳይሆን በራሳችን ፈልገን መርምረን ጥቅምና ጉዳቱን አገናዝበን ነው ጥቅም ላይ የዋለው፤
– ምርት እንደሚጨምር ISAA ጨምሮ ሌሎች በጥናት ያረጋገጡት ነው፣ ሳይንስን መሰረት አድርገን መነጋገር አለብን በቂ ጥናት ተደርጓል፤
– ከዋጋ አንጻር የጸረ ተባይ መድኃኒት ዋጋን ይቀንሳል፣ ተመራጭ ነው፤
– ሀገሪቱ ይህንን መቆጣጠር የሚችል ህግና የተቋቋመ ተቋም አለ፤
– የጥጥ ምርትን ገበሬው ፈልጎት ማንም ሳያስገድደው ነው እየተጠቀመ ያለው የሚሉ ሃሳቦችን አንጸባርቀዋል።
ከመድረኩ ተሳታፊዎችም ዘንድ ሁለቱንም ጎራ የሚመለከቱ ሃሳቦች ተንጸባርቀዋል።ኢትዮጵያ በዘረመል ምህንድስና ዘዴ የተመረቱ የግብርና ምርቶችን (GMO) መጠቀም አለባት የለባትም የሚለው ክርክር ወደ መደብዘዙ የሄደ ቢመስልም አሁንም ይህንን የሚሞግቱ ምሁራን ግን አልጠፉም ፤ ማኅበረሰቡም ከስጋት የተላቀቀ አይመስልም።በኢትዮጵያ በእንሰት ላይ እንዲሁም በጎመን ዘር ላይ የዘረመል ምህንድስና ዘዴን ተጠቅሞ ባክቴሪያን የሚቋቋም እንሰት እና ለዘይት ምርት የሚሆን ጎመን ዘር የማምረት ሂደት በሙከራ ላይ እንደሚ ገኙ ተገልጿል።
በኢትዮጵያ በዘረመል ምሕንድስና የበለፀገ በቆሎ ለገበያ ሊቀርብ ነው
‹‹በዘረመል ምሕንድስና የሚመረቱ የግብርና ምርቶች ጥቅሞችና ሥጋቶች›› በሚል የመወያያ ርዕስ መነሻ ሃሳብ ያቀረቡት፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮና ኮምፒትሽናል ሳይንስ ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ ጥልዬ ፈይሳ (ፕሮፌሰር)፣ ‹‹በኢትዮጵያ በቆሎን በዘረመል ምሕንድስና የማበልፀግ ሙከራ ብዙ ዓመታት ወስዶ ከተጠናቀቀ በኋላ፣ የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ለግብይት እንዲውል ፈቃድ ሰጥቷል፤›› ብለዋል።
በተደረገው ሙከራ ምርት 56 በመቶ መጨመሩን በመጥቀስ፣ ዘርቶ በማብቀል ለምግብነት የሚውል መሆኑንም አስረድተዋል፡፡ ይህ የተነገረው የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዴሚ ባዘጋጀውና ሐሙስ ግንቦት 14 ቀን 2017 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ እሸቱ ጮሌ መታሰቢያ አዳራሽ በተካሄደው የውይይት መድረክ ላይ ነው፡፡ በመሆኑም ከዚህ ዓመት ጀምሮ በዘረመል ምሕንድስና የበለፀገ በቆሎ ለአርሶ አደሮች ይቀርባል የሚል ተስፋ እንዳላቸው፣ ‹‹ነገር ግን የትኛው አርሶ አደር እንደሚጠቀምና እንደማይጠቀም የራሱ ቅደም ተከተል ይኖረዋል፤›› ብለዋል። ‹‹በዘረመል ምሕንድስና የበለፀገ በቆሎ ለአርሶ አደሮች እንደ አማራጭ ነው የቀረበው፣ መዝራት የማይፈልግ አርሶ አደር ካለ አይገደድም፤›› በማለት አስረድተዋል፡፡
‹‹በምግብ ራሳችንን የቻልን አይደለንም፣ እስከ 20 ሚሊዮን የሚደርሱ ሰዎች ተረጂ ናቸው፡፡ ስለዚህ የዘረመል ምሕንድስና ምርት ከጨመረልን፣ ከምግብ የሚገኙ ንጥረ ነገሮችን ካቀረበልንና የምግብ ህልውናንችንን ለማረጋገጥ እስካገዘን ድረስ መጠቀማችንን እንቀጥላለን፤›› ያሉት መምህርና ተመራማሪው፣ በዘረመል ምሕንድስና የበለፀገ የጥጥ ማምረት ሒደት በሚቀጥሉት ዓመታት ውስጥ በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚስፋፋ ጠቁመዋል።በውይይቱ ወቅት እንደ ሥጋት ከቀረቡ ጥያቄዎች አንዱ በጤና ላይ የሚኖረው ተፅዕኖ ነው።
በዚህ የማምረት ዘዴ ያለፉትን 30 ዓመታት ልምድ በመጥቀስ ጤና ላይ ችግር አልተስተዋለም በማለት ጥልዬ (ፕሮፌሰር) ገልጸዋል። በ30 ዓመታት ውስጥ ተፅዕኖ ካልታየ በሚቀጥሉት 40 ዓመታት የተለየ የጤና እክል ይኖራል ተብሎ እንደማይተነበይ ተናግረዋል። በኢትዮጵያ ከጥጥና ከበቆሎ በተጨማሪ እንሰት ላይ ተጀምሮ የመጀመሪያ ሙከራው እየተጠናቀቀ መሆኑን የገለጹት መምህርና ተመራማሪው፣ ከጎመን ዘር ዘይት ለማምረት የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አክለዋል። ሆኖም ከፍተኛ የሆነ የገንዘብ እጥረት በሥራው ላይ ቀላል የማይባል ተፅዕኖ እንዳለውም ሳይጠቅሱ አላለፉም።
ሌላው የውይይት መነሻ ሐሳብ አቅራቢ ፍሬው መክብብ (ፕሮፌሰር)፣ የዘረመል ምሕንድስና የሚገኝበት ባዮ ቴክኖሎጂ የኢትዮጵያን መፃኢ ዕድል የሚወስን እንደሆነ ተናግረዋል። ‹‹የጥጥና የበቆሎ ዝርያዎች ለሀገሪቱ ተስማሚ መሆናቸው ተለይቶ፣ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታቸው ታይቶ፣ እንዲሁም አርሶ አደሩ ፈልጓቸው የተዘጋጁ ናቸው፤›› ብለዋል። እነዚህ አዝርዕቶች ድርቅን፣ በተባይ የሚደርስ ጉዳትንና አረምን መከላከል እንዲችሉ ተደርገው መዘጋጀታቸውን የገለጹት ደግሞ ሌላው የውይይት መነሻ ሐሳብ አቅራቢው ታደሰ ዳባ (ዶ/ር) ናቸው። የዘረመል ምሕንድስና የምግብ ህልውናን አያረጋግጥም፣ እንኳን 50 በመቶ አንድ በመቶ ምርት አይጨምርም፤›› ሲሉ የሞገቱት ደግሞ የመወያያ ሐሳብ ያቀረቡት ፀደቀ አባተ (ዶ/ር) ናቸው። ‹‹የዘረመል ምሕንድስና የምርት መጠን ከጨመረ በሚቀጥሉት ዓመታት እናየዋለን፣ እኔ ግን ዘዴውን አልደግፍም፤›› ብለዋል።
እ.ኤ.አ በ2024 በዓለም ከ210 ሚሊዮን ሔክታር በላይ በዘረመል ምሕንድስና መመረቱ በውይይቱ ላይ ተሰምቷል። በዓለም አቀፍ ደረጃ በ70 ሀገሮች ፈቃድ ማግኘቱ የተገለጸ ሲሆን፣ በዘረመል ምሕንድስና አብቃይ ሀገሮች የተወሰኑ መሆናቸው ተገልጾ እነሱም አሜሪካ፣ ብራዚል፣ አርጀንቲና፣ ካናዳና ህንድ ቀዳሚዎቹ መሆናቸው ተነግሯል። በአፍሪካ ደግሞ ደቡብ አፍሪካና ሱዳን ተጠቃሽ መሆናቸውን ለማወቅ ተችሏል። በኢትዮጵያ ምን ያህል መጠን ይመረታል የሚለው እንደማይታወቅ ጥልዬ (ፕሮፌሰር) ገልጸዋል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ እ.ኤ.አ በ2034 ከዘረመል ምሕንድስና ምርቶች አጠቃላይ ከ293 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ይገኛል ተብሎ እንደሚታሰብ፣ ከዚህ ውስጥ የግብርና ምርቶች እ.ኤ.አ በ2025 ብቻ 24.7 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ያስገኛሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ተጠቁሟል። በዘረመል ምሕንድስና መገኛቸው ኢትዮጵያ የሆኑ ምርቶች ላይ ሲተገበር ጥንቃቄ እንዲደረግ የመድረኩ ተሳታፊዎች አሳስበዋል። አሁን ስለዘረመል ምሕንድስና ከመናገር ይልቅ ዓለም የደረሰበት ባዮ ሳይንስና አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ (AI) ላይ ማተኮር እንደሚያስፈልግም ማሳሰቢያ ተሰጥቷል።
በሀገራችን የዘረ-መል ምህንድስና ውጤቶችን ለመጠቀም የሚደረገው ጥረት በአካባቢና በብዝሀ- ሕይወት ኃብቶች ላይ ሊያስከትሉ የሚችሉ ጠንቆችን በጥብቅ ቅድመ ጥንቃቄ እየተሠራ ነው ። ለዚህም ኢትዮጵያ የደህንነተ ሕይወት የህግ ስርዓትን በአዋጅ ቁጥር 655/2009 (በአዋጅ ቁጥር 896/2015 እንደተሻሻለው) አውጥታ መተግበሯን ገልፀዋል።
ይሄ ህግ የደህንነተ ህይወት ህግጋት ልውጠ ህያዋን (GMOs) ወይም የዘመናዊ ቴክኖሎጂ ውጤቶች በሚመረቱበት፤ በሚዘዋወሩበት፤ በሚጓጓዙበት፤ በሚከማቹበት እና ለምርምርና ለማስተማር በሚውሉበት ወቅት በብዝሀ ሕይወትና በአካባቢ ላይ ጠንቅ እንዳያስከትሉ ለማድረግ የተዘጋጀ የህግ ማሕቀፍ ነው።
የዘረ መል ምህንድስና ሳይንስ ልክ በብዙ ሀገሮች እየተስፋፋ እንዳለው በእኛም ሀገር አቅም በፈቀደ መጠን እና ሁሉንም “የደህንነተ ህይወት” (Bio Saftey) ጥንቃቄዎችን በጠበቀ መልኩ እንዲያድግ የምንፈልግበት ምክንያት ሳይንሱ ልክ እንደሌሎቹ ሳይንሶች ሁሉ በጥንቃቄ ካልተሰራ ምንም አይነት ጉዳት የለውም ብለን ሳይሆን ሳይንሱ በግብርና፣በህክምና፣በኢንዱስትሪ እና በሌሎች በርካታ ዘርፎች ያለው ጠቀሜታ እጅግ ጠቃሚና አስደናቂ በመሆኑ ነው።
ዛሬ በዓለማችን የዘረ መል ምህንድስና ሳይንስን የሚያስፋፉና በሳይንሱም የተመረቱ የግብርና ምርቶችን (Biotech Crops) ፣ የህክመና መድሃኒቶችንና የኢንዱስትሪ ምርቶችን የሚጠቀሙ ሀገራት ቁጥር እጅግ እየጨመረ ይገኛል። ይህም የሚሆነው በብዙ ምክንያቶች ነው፦
- የዘረ መል ምህንድስና ሳይንስ እና “የደህንነተ ህይወት” ሥራ እየዘመነ መምጣቱና በአሁኑ ወቅት የዘረመል ምህንድስና እና synthetic biology ዘርፍ በተለያዩ የኮምፒውተር ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች በመታገዝ በተለየና በፈጠነ መልኩ እየዘመነ መቷል። ለምሳሌ ዛሬ የዘረመል ምህንድስና ሳይንቲስቶች እንደ ክሪስፐር (CRISPR) ሞለኪዩል ያሉ ዘዴዎችን በመጠቀም የዘረ መል ምህንድስናን ፍፁም በሚባል ደረጃ በጥራት በመሥራት ላይ ይገኛሉ። ይህ ክሪስፐር የተሰኘው ሞለኪዩል ባለሙያዎቹ በአንድ ሴል ክሮሞዞም ውስጥ የሚገኙትን እያንዳንዱን የዲ ኤን ኤ የሞለኪውል አንጓዎችን በሚገባ በመለየት እና ካስፈለገም ለይቶ ቆርጦ በማውጣት በሚፈለግ መልኩ አንጓዎችን በማስተካከል ተፈላጊውን የዲ ኤን ኤ ለውጥ ለማድረግና ተፈላጊውን ውጤት ለማምጣት አስችሏቸዋል።
በቤተ ሙከራና በተከለለ ከባቢ የሚደረጉ የመስክ ጥናቶች (Confined field trial) እንዲሁም የካርታኼናው የደህንነተ ህይወት ፕሮቶኮልና በሌሎች ተመሳሳይ ሀገራዊ ህጎችና መመሪያዎችም አፈፃፀም በተለያዩ ሳይንሳዊ ዘዴዎች እየዘመኑና ይበልጥ አስተማማኝ በሚባል ደረጃ እያደጉ በመምጣታቸው የዘረ መል ምህንድስና ሳይንስን ተፈላጊነት ጨምሯል።
በሀገራችን ደህንነተ ህይወት (Biosafty) የብዝሀ ኃብቶችን ምህንድስና(Biotechnology) ውጤቶች ለታለመላቸው ዓላማ እንዲውሉ ታስቦ የዘረ መል ምህንድስና የተካሄደባቸው ውጤቶች በአካባቢና በብዝሀ ህይወት ሀብት ላይ ሊኖራቸው የሚችልን አሉታዊ ተፅኖ ለመቀነስ ወይም ለማስቀረት በቅድመ ምርምር፣ በምርምር ወቅትና ከምርምር በኋላ በሚኖሩ የስርፀት ጊዜያት የሚከናወን ሳይንሳዊ የክትትልና ቁጥጥር ስርዓትም ተዘርግቷል።
- ግሎባላይዜሽን፦
በዘመናችን የሀገራት ኢኮኖሚ በእጅጉ የተሳሰረና የተቀራረበ ነው። የሰዎች ዝውውርና የንግድ ልውውጡም ከምን ጊዜውም በላይ ሰፍቷል። በመሆኑም በአሁኑ ጊዜ በአለማችን በስፋት እየተመረቱ የሚገኙት የዘረ መል ምህንድስና ውጤቶች ከአንድ ሀገር ወደሌላኛው በቀላሉ የሚገቡበት እድልም በጣም ሰፊ እየሆነ ነው።
ለምሳሌ ከሀገራችን ጎረቤቶች መካከል እንደ ኬንያ ያሉት ሀገራት የዘረ መል ምህንድስና ውጤት የሆኑ ሰብሎችን በብዛት እየተጠቀሙ ነው ። የኛና የኬንያ ዜጎች በድንበር በኩል ሰፊ ግንኙነት ያላቸው እና እርስ በርስም በንግድና ማህበራዊ ትስስር የሚያደርጉ እነደሆኑ ይታወቃል። ይህ ሰፊ ግንኙነት የዘረ መል ምህንድስና ውጤቶችን በቀላሉ ለመቀያየር የሚያስችል እንደሆነና ለቁጥጥርም አስቸጋሪ እንደሆነ ይነገራል ። ስለዚህ የዘረ መል ውጤቶችን እስከ ዛሬም ሀገራችን እንዳይገቡ የተደረገው ክልከላ ምን ያህል ውጤታማ ነበረ ብለንም መጠየቅ ይገባናል።
በተጨባጭም ከዚህ በፊት ከልውጥ ህያዋን (GMOs) የተሰሩ የምግብ ዘይቶችና ሌሎቸም ምርቶች ሀገራችን ገብተው በሚዲያም ጭምር ሲነገር ሰምተናል። አሁንስ ምን ያህል የቁጥጥር አቅምና የሰለጠነ የሰው ኃይል አለን ብሎ ማየቱም ጥሩ ነው።
- የዘረ መል ምህንድስና ሳይንስ ከጉዳቱ ጥቅሙ መብለጡ (Misconceptions amd myth)
ሌላው ብዙ ሰው የማይገነዘባችውና ስለ ልውጥ ህያዋን (GMOs) የተሳሳቱ አመለካከቶች በዓለም ላይ ብዙ መሆናቸውና “የአካባቢ ጥበቃ ተሟጋቾች” ደግሞ ይህንኑ አላዋቂነት ሆን ብለው ማራገባቸው ትልቅ የሳይንስ እንቅፋት ነው።
-ባለፉት አስር እና ሃያ ሺህ አመታት ገበሬዎች በራሳቸው መንገድ ሳያውቁት የብዙ እፅዋት ዝርያዎችን የዘረ መል ቀይረዋል፤
-የዘረ መላቸው የተስተካከለ እፅዋትን መመገብ የሰዎችን የዘረ መል ይቀይራል ብሎ ማመን የተሳሳተ ነው።
-የዘረ መል የተስተካከሉ እፅዋትን ዘር መልሶ መጠቀም አይቻልም የሚለው የተዛባ ሃሳብ ነው።
-የዘረ መል ቴክኖሎጂ ጠቅላላ አላማ የዓለም አቀፍ ግዙፍ ኩባንያዎች ጥቅም ማስከበሪያ እንጂ ለልማት የሚበጅ ታላቅ ሳይንስ እንዳልሆነ ማሰብ፤
-የዘረ መል ቴክኖሎጂ በበቂ ሁኔታ ፍተሻና ማረጋገጫ አይደረግበትም ብሎ ማሰብ
-የዘረ መል ቴክኖሎጂ ከተፈጥሮ የራቀ አድርጎ ማሰብ
-በዘረ መል ቴክኖሎጂ የተመረቱ ምግቦች በቂ ንጥረ ነገር የላቸውም ብሎ በተሳሳተ መንገድ ማሰብ
-ባጠቃላይ የዘረ መል ምህንድስና ሳይንስ ሳይንስ ሳይሆን ጭራቅ አስመስሎ ማቅረብ ወ•ዘ•ተ የሳይንሱ ትልልቅ ተግዳሮቶች ናቸው።
የሕዝብ ቁጥር በፍጥነት መጨመር የሀገራችን የሕዝብ ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሻቀበ በመሄድ ላይ ነው። በአንፃሩ ደግሞ የግብርናው ምርት ለሀገሪቱ ሕዝብ ፍጆታ በቂ ስላልሆነ መንግሥት በየጊዜው ምግብ ከውጭ ያስገባል። በገጠር ብቻም ሳይሆን በከተማም የምግብ ተረጂው ቁጥር አሁንም አልቀነሰም። ለምሳሌ ባለፈው ዓመት መንግሥት ሰፊ የምግብ ዋስትና ፕሮግራም ጀምሯል።
ፕሮግራሙ ከዓለም ባንክ 300 ሚሊዮን ዶላር ብድር፣ ከኢትዮጵያ መንግሥት 150 ሚሊዮን ዶላር ደግሞ በተመደበ በጀት የተጀመረ ነው። በፕሮግራሙ የታቀፉት 11 ከተሞች አዲስ አበባ፣ አዳማ፣ ሐዋሳ፣ ደሴ፣ ድሬዳዋ፣ ሐረር፣ ጅግጅጋ፣ ሰመራ፣ ሎጊያ፣ ጋምቤላና አሶሳ ናቸው። ይህ የሚያሳየው ግብርናችን በዘመናዊ ሳይንስ አለመታገዙን ነው። ብዙዎች እንደሚስማሙበት ደግሞ በራስ አቅም የሚሠራ የዘረ መል ምህንድስና ዋነኛውና ውጤታማው ነው።
- ልውጥ ህያውነት በተፈጥሮም ሊከሰት መቻሉ ልውጥ ህያውነት
በብዙ ቫይረሶችና በሌሎችም ህያዋን እንደምናየው ከሁኔታዎች ጋር ራስን ከማስማማት ጋር በተያያዘ ፣ ከጤና ችግር እና በሌሎችም ምክንያቶች ከሰው ጣልቃ ገብነት ውጭ ያለ ዘረ መል ምህንድስና ሊከሰት ስለሚችል ሁል ጊዜ የዘረ መል ምህንድስና ሳይንስ ብቻ ለተፈጥሮ መዛባት ተጠያቂ አድርጎ ማሰብ ተገቢ አይደለም።
ህያዋን አንዳንድ ጊዜ ለአደገኛ ለጨረራዎች ሲጋለጡ ወይም ከተለያዩ ኬሚካሎች ጋር በራሳቸውና ባጋጣሚ ሲገናኙ የዘረመል አቀማመጥ ለውጥ ወይም ተፈጥሯዊ ልውጥነት(spontaneous/naturalmutation) ያጋጥማቸዋል።
- የምርት ጥራት ፍላጎት
የዘረመል ምህንድስና ቴክኖሎጂ ተግባራዊ ከተደረገ የግብርናን ምርትና ምርታማነት እንዲሁም ጥራትን ከማሳደግ ባለፈ የሰብሎች በሽታን የመቋቋም አቅምን እንደሚያጎለብት ግልፅ ነው። በአሁኑ ወቅት ለኢንዱስትሪ ግብዓት በሚሆኑ ተክሎች በዋነኛነትም በጥጥ ላይ ተግባራዊ ለማድረግ እየተሠራ ነው።የአርሶ አደሮቻችንን ጉልበት ሊያግዙ የሚችሉ ቴክኖሎጂዎችን ለማቅረብ እየተሠራም ይገኛል።
የብዝሀ ህይወት ህጉን ማሻሻል ያስፈለገበትም አንዱ ምክንያት የኢንዱስትሪውን ልማት ለመደገፍ ሲሆን በተለይ በማኑፋክቸሪንግ ንዑስ ዘርፍ ማነቆ ተደርጎ የሚጠቀሰውን የግብአት እጥረት በዘላቂነት ለመቅረፍ ያለመ ነው። ለምሳሌ የጨርቃጨርቅ ንዑስ ዘርፍን ዋና ግብአት የሆነውን የጥጥ ምርት የሚታይበትን እጥረት በዘላቂነት ለመቅረፍ እንደ መፍትሔ የቀረበው ደግሞ ቢ.ቲ ኮቶን ተብሎ የሚታወቀውንና በዘረ መል ምህንድስና የሚመረተውን የጥጥ ምርት ለማስፋፋት ሲባል ነባሩን ህግ ማሻሻል ማስፈለጉ ይታወቃል።
ባጠቃላይ በአንድ በኩል በፍጥነት እያደገ ያለ የህዝብ ቁጥር ያላትና በርካታ የልማት ፍላጎቶች በሁሉም ዘርፍ ማለትም በግብርና ፣ በኢንዱስትሪና በህክምና ዘርፎች እየመጡ ያሉባት ሀገራችን ኢትዮጵያ በሌላ በኩል በርካታ ዩኒቨርሲቲዎችን ጨምሮ የተለያዩ የትመህርት ተቋማትን በማስፋፋት ላይ ትገኛለች ። የተቋማቱ መስፋፋትም ሀገራችን በቂ የሰውና የቴክኖሎጂ አቅም እንዲኖራትና የዘረመል ምህንድስና ሳይንስን በብቃት እና የደህንነተ ህይወት መርሆዎች በተከተለ መልኩ እንድታጠናክር ይረዳታል።
ይህም በሌላ በኩል ደግሞ የሌሎች የታላላቅ ሀገራት ታላላቅ ኩባንያዎች (Multinational Corporations) የራሳቸውን የዘረመል ምህንድስና ውጤቶች ለኛ በማስለመድና ገበያችንን በመቆጣጠር ያመጡብናል ለሚለው ስጋትም በራስ አቅም በዚህ ሳይንስ በመጠቀም የራሳችንን የቴክኖሎጂ (የዘረመል) ውጤቶች እንድናመርት ያስችላል። ስለዚህ ሳይንሱን በሩቁ ከመፍራትና ትክክለኛ ያልሆነ አስተሳሰቦችና ትርክቶች (Misconceptions and myth) ከማስፋፋትና ችግሮቹን ከማጋነን ይልቅ አስደናቂና ጥልቅ የሆኑትን ከሳይንሱ ትሩፋቶች በተገቢው ለመጠቀም እንሞክር።ለዚህ መጣጥፍ መኮንን ተሾመ ቶሌራን፣ጊዎን መጽሔት እና ሪፖርተር ጋዜጣን በምንጭነት ተጠቅሜያለሁ ።
ሻሎም ! አሜን
በቁምላቸው አበበ ይማም(ሞሼ ዳያን) fenote1971@gmail.com
አዲስ ዘመን ሐሙስ ግንቦት 21 ቀን 2017 ዓ.ም