በጌታቸው በለጠ/ዳግላስ ጴጥሮስ
ማዋዣ፤
ዘመናዊዎቹ የዓለማችን መድኃኒት አምራቾች ጥበቡን ከእኛ ይውሰዱ ወይንም እኛ ከእነርሱ እንኮርጅ እርግጠኛ አይደለሁም። እንደሚመስለኝ ግን እነርሱ ከእኛ “የመነተፉ” ይመስለኛል። ካልሆነም ስማቸውን በከንቱ አንስቻለሁና “አፉ!” ብላችሁ “ለራስ ሲቆርሱ አያሳንሱ ሆኖበት ነው” ብላችሁ እለፉኝ።
ለማንኛውም ማንም ይዋስ ማን ጉዳዩ እንዲህ ነው። የሀገራችንን የባህል መድኃኒቶች ጉዳይ ስናነሳ በፈጣን ፈዋሽነታቸው ከሚጠቀሱት መካከል እንቆቆና መተሬን መሰል አንጀት አርስ ባህላዊ መድሃኒቶች ስለ መኖራቸው እርግጠኛ አይደለሁም። በጸሐፊው እምነት ሁለቱም የ“ሻምፒዮንነት” ክብር ቢላበሱ አይበዛባቸውም።
የሁለቱም መድኃኒቶች አገልግሎት ተመሳሳይ ሲሆን ልዩነቱ “የብራንድ” እንጂ በሆድ ውስጥ የተፈጠሩ ትላትሎችን ማጥፋት ዋነኛው ተግባራቸው ነው። ለጊዜው የእንቆቆን ጉዳይ በይደር አስተላልፌ ስለ መተሬ አዘገጃጀትና አጠቃቀም በተመለከተ የጸሐፊውን እናት ወ/ሮ ወሰኔን ዋቢ በማድረግ እነሆ ያየሁትንና የሞከረኩትን እውነት እንዲህ በማለት እመሰክራለሁ። የመተሬ መራራ ፍሬ ተወቅጦና ላቁጦ እየተድበለበለ የሚዋጠው በገንፎ ወይንም በሙዝ እየተጠቀለለ ነው። የገንፎው ድርሻ፤ “አንድም ለጉንፋን አንድም ለጥጋብ” ይሉት ዓይነት ግልጋሎቱን ለማረጋገጥ አይደለም። የሙዙም አገልግሎት እንደዚሁ።
የሁለቱ አጃቢዎች (የገንፎውና የሙዙ) ዋነኛ ድርሻ ከሬት በከፋ ደረጃ የሚመረውን መተሬ እያጣፈጡ ከጉሮሮ ለማውረድ ብቻ ነው። ሆድ ውስጥ ገብቶ ተልዕኮውን በድል የሚወጣው መተሬው እንጂ “መጠቅለያዎቹ” አይደሉም። ፈረንጆቹ ይህን መሰሉን ልፋታችንን ለመድገም ስላልፈለጉ ሳይሆን አይቀርም የኮሶ መድኃኒቶችን የፈለሰፉት የገንፎ እህል አስፈጭተው ወይንም የላንቴን (ከተባረኩት የጋሞ አካባቢዎች አንዱ) ጣፋጭ ሙዝ በማሰስ አይደለም።
ጠቢባኑ ባዕዳን መሠል መራራ ኪኒኖችን የሚያለዝቡት ላይ ላዩን በስኳር ቀባብተው (Sugar coated tablets እንዲሉ) ድካማቸውን በሳይንስ ፈጠራ በማቅለል ነው። ይህንን ወግ የተጠቀምኩት መራሩን ርዕሴን ለማዋዛት እንጂ ዋነኛው ጉዳዬ “የመተሬን ገድል” ለመተረክ አይደለም። ከዋናው ርእሰ ጉዳይ ይልቅ ማዋዣው ጣፍጦኛል የሚል አንባቢ አለሁ ካለም መግቢያውን ብቻ ቀንጭቦ በመውሰድ ላሻው ጉዳይ ሊገለገልበት መብቱ ነው።
ሀገሬና የተረት ወጌ ተመሳስሎ፤
የሚከተለው ተረት ከሩቅ ምሥራቅ የተገኘ ነው ይባላል። ከየትኛው ሀገር እንደሆነ ግን ንባቤ ደብቆኛል። ተረቱ ከመሠረታዊ የሃይማኖቶች አስተምህሮ ጋር መጋጨቱ እንደተጠበቀ ሆኖ ፈገግ የማስደረጉና የአስተማሪነት አቅሙ ግን የበረታ ነው። ደግነቱ የተረቶች ባህርይ “ለምን? እንዴት? መቼ? በምን ምክንያት?” ከሚሉ ምክንያት አሳሽ ጥያቄዎች የተፋታ ስለሆነ ብዙም አያስጨንቅም።
“ተረት ተረት?” ተብሎ ሲጠየቅ “የላም በረት” ከተባለ በቂ ነው። መቆስቆሻ ጥያቄዎቹ ሠፈራቸው አንድም ከሳይንስ መንደር አለያም በፍርድ ቤቶች ቅጥረ ግቢ ውስጥ እንጂ ከተረታ ተረቶች ጋር ዝምድና የላቸውም። ስለዚህም “ተረቴን መልሱ፤ አፌን በዳቦ አብሱ” ብዬ ትረካዬን ልቀጥል።
ቅዱሳት መጻሕፍት ከሰው ልጆች ሁሉ ቀድሞ የተፈጠረው አዳም (አደም) እንደነበር አስረግጠው ያስተምሩናል። ሔዋን ከአዳም አጥንት ተሰንጥራ እንደወጣች የሰንበት ትምህርት ቤት አስተማሪዎቻችን እያብራሩ እንዳሸመደዱንም መካድ አግባብ አይሆንም። ይህ ተረታችን የሚያጫውተን ግን ፈጣሪ አስቀድሞ የፈጠረው አዳምን ሳይሆን ሔዋንን እንደሆነ በማስረገጥ ነው።
እናም ሔዋን በግዙፉ ዓለም ውስጥ ብቻዋን ተፈጥራ ገነት ውስጥ ለመኖር ብትታደልም ፍርሃትና ብቸኝነቱ ስላንገሸገሻት የተዋበው የአትክልትና የአበቦች ውበት ትርጉም ሊሰጣት አልቻለም። ስለዚህም አንድ ዕለት ወደ ፈጣሪ ዘንድ በመሄድ ምርር ብላ በማልቀስ እንባዋን እያንዠቀዠቀች “በፈጠርከው ግዙፍ ዓለም ውስጥ ያለ ረዳት ለብቻዬ ስኖር እንዴት አይገድህም፤ ለብቻዬ ገነት ምኔ ነው?” በማለት የብቸኝነቷን ብሶት ለአምላኳ ዘረገፈች።
ሩሁሩሁ ፈጣሪዋም ብሶቷን ካዳመጠ በኋላ “ሰው ብቻውን ይሆን ዘንድ መልካም አይደለም” የሚለው ቅዱስ ቃሉን በማክበር መፍትሔ እንደሚፈልግላት ቃል ገብቶላትና ቀጠሮ ሰጥቷት ወደ ማደሪያዋ ሸኛት። የሔዋን እምባ ፋታና እረፍት የነሳው ፈጣሪም ቃሉን በማክበር የዝሆንን የጉልበት ምሥጢር፣ የአንበሳን አስፈሪነት፣ የበሬን የተዋጊነት መንፈስ፣ የአህያን የሸክም ብርታት፣ የጆፌ አሞራን ቀላዋጭነት፣ የነብርን ግልፍተኝነት፣ የጅብን ምንትስ፣ የአውራ ፍየልን የእንትን ባህርይ፣ የግመልን ጽናት፣ የአውራ ዶሮን በባዶ ሜዳ መጀነንና ቁንንነት፣ የገመሬ ዝንጀሮን መኮፈስ፣ የፈረስን ማሽካካት (አቤት አበዛዙ!) የእነዚህን ሁሉ እንስሳት ባህርያት በማዋሃድና በመቀመም አጋር የሚሆናትን ወንድ ሠርቶ በቀጠሮው ቀን ለሔዋን አስረከባት።
ሔዋንም በፈጣሪ ደግነትና ርሁሩህነት ተደስታ የተሰጣትን አጋሯን ይዛ እየፈነደቀች ከቤቷ እንደደረሰች አዳም (አደም) በማለት ስም አውጥታለት የመረዳዳቱን ኑሮና አልጋ መጋራቱን ሀ ብለው ጀመሩ። ጥቂት ቀናት የጨረቃ ማራቸውን (Honey Moon) እየገመጡ ከሰነበቱ በኋላ ደስታቸውና ሃሴታቸው ሳይበርድ በአጋርነት የተሰጣት የወንድ ባህርይ እንቆቅልሽ እየሆነ ይፈታተናት ጀመር።
አዳም በሰላም ይውልና ድንገት የአንበሳ ባህርይው ትዝ ሲለው ያለምንም አሳማኝ ምክንያት “ዘራፍ” በማለት የቤቱ ንጉሥ መሆኑን እያወጀ መፎከር ይጀምራል። ይሄኔ በመጤው እንግዳ ወንድ ባህርይ ግራ የምትጋባው ሔዋን ጓዝ ኮተቱን አሸክማ አዳምን አንጠልጥላ በመውሰድ ከምሬት ጋር ለፈጣሪ አስረከበችው። ሁለተኛ ዓይኑን ላለማየትም በእንባ እየታጠበችና በመሃላ እያረጋገጠች ወደ ቤቷ ተመለሰች።
ውላ ስታድር ግን ያ መከረኛ ብቸኝነት ሊውጣት ሲደርስ ወደ ፈጣሪ ዘንድ ተመልሳ፤ ይቅርታ በማስቀደም፤ “የሰጠኸኝን ወንድ አባክህ መልስልኝ? እንዳመጣብኝ እችለዋለሁ” በማለት ፈጣሪን ትማጸናለች። ፈጣሪም ለጥያቄዋ ፈጣን ምላሽ በመስጠት አዳምን መልሶ ያስረክባታል።
አጋር ተብሎ ለሔዋን የተፈጠረው አዳም ሳይውል ሳያድር ከአውራ ዶሮ የተሰራው ባህርይው ግንፍል ብሎ አሳር ሲያበላት አሁንም ወደ አምላኳ ዘንድ ሮጣ “ተቃጠልኩ! ተቃጠልኩ!” እያለች በምሬት ረዳቷን አዳምን አስረክባ ትመለሳለች። ባዶ ቤት ከፍታ ስትገባ ግን የወንድ ጠረን የለመደው ትዳሯ ኦና ሆኖ ባዶነት ስለተሰማት እንደምንም እፍረቷን ዋጥ አድርጋ ፈጣሪ ዘንድ ተመልሳ “አዳምን እንዲመልስላት” ለብዙኛ ጊዜ ትማጠነዋለች።
የአውራ ፍየል ባህርይው ሲያገረሽበት ወስዳ ስትመልሰው፤ ፈጣሪም የአዳምን ባህርይ የገራ መስሎት አንዴ ሲመክረው፣ አንዴ ሲያስረውና ሲፈታው ከሔዋን እኩል መከራውን ማየቱ አልቀረም።
በመጨረሻም “አጋር እንዲሆናት ከፈጣሪ ተመርቆ በተሰጣት አዳም” ባህርይ ጉዳይ የተሰላቹት ፈጣሪና ሔዋን መላ ለማግኘት ምክክር ማድረግ ይጀምራሉ። ፈጣሪ እዝን እንዳለ ለሔዋን እንዲህ አላት፤ “ልጄ ሆይ ለአንቺ የጠቀምኩ መስሎኝ ይህን ሞገደኛ ፈጥሬ አሳር አበላሁሽ። መክሬም ሆነ ለእሱ ስል ብቻ ባቋቋምኩት እስር ቤት ከትቼ እንዲታረም ብሞክርም የባህርይ ለውጥ ሊያመጣ አልቻለም። እንዲያው ምን ይበጅ ይመስልሸል?” በማለት ሔዋን መፍትሔ እንድትጠቁም ዕድል ይሰጣታል።
ሔዋንም የፈጣሪ ጭንቀት ተሰምቷት እየተከዘችና እምባዋን እያፈሰሰች መፍትሔ ያለችውን ዘዴ እንዲህ በማለት ትጠቁመዋለች፤ “አምላኬ ሆይ ከወንድ ጋር መኖር እንደማይቻል መረዳት ብቻ ሳይሆን ያለ ወንድ እርዳታም መኖር እንደማይቻል ስለገባኝ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ አጋሬን አዳምን መልስልኝና እንዳመጣብኝ ወድጄ ብቻም ሳይሆን በግድም ቢሆን ችዬ አብሬው በመኖር ሕይወትን በጋራ እንገፋለን” በማለት እቅጩን ተናግራ አዳምን ተረክባ እነሆ ለዘለዓለም አብራው እኖረች ነው። ተረቴን ! የወደዳችሁ አንባቢያን “ሀገር ስጡኝና” ጥቂት ልቆዝምበት።
እናታችን ሔዋን ሆይ!
ልክ እንዳንቺ ታሪክ ሁሉ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ተሞክሮ ተግባብተን ለመኖር አልቻልንም፤ ያለ ፖለቲካም ለመኖር የሚቻል አይመስለንም። ፖለቲካችን እንደ መተሬ እንደመረረንና እንዳስመረረን፤ ፖለቲከኞቻችንና ርዕዮተ ዓለማቸውም እንዲሁ እንዳንገሸገሸን የእፎይታ ወግ ሳናይ መስከረም መጥቶ ጳጉሚት ወንበሩ ላይ ፊጥ እያለች ስንትና ስንት ዘመን እንደተቆጠረ ካላንደሩን ለማስላት የምንቸገር አይመስለኝም።
ምን ይሄ ብቻ ርዕዮተ ዓለም ወለድ የሆነው ደዌያችን እንደጠናብንና ለጦሰኛው የፖለቲካችን አስማትም “መፍትሔ ሥራይ” ጠፍቶብን “ያንተ ያለህ!” እያልን ጩኸት ማሰማት የጀመርነው ከዘመነ ስብስቴ ጀምሮ ነው። ኢህአፓ፣ መኢሶን፣ ወዝ ሊግ፣ ኢዲዩ፣ ማሌሊት፣ ኢሠፓ፣ ቅንጅት፣ መአሕድ፣ ኢዴፓ፣ ኢዜማ፣ አረና፣ ብልጽግና (አቤት የታሪካቸውና የቁጥራቸው አበዛዝ) እንደውም ሰሞኑን የፓርቲዎች ቁጥር አነሰ ተብሎ እንዲጨመር ማስታወቂያ እየታወጀ ነው።
ግማሹ ተወልዶ፣ ግማሹ ሞቶ፣ ግማሹ ጨንግፎ፣ ግማሹ ከስሞ፣ ግማሹ ብን ብሎ ጠፍቶ በየተራ ተፈራርቀውብናል። መጥኔ ፖለቲካ አልዋጥላት ብሎ በርእዮተ ዓለም ቃር ግራ ተጋብታ ለምትሰቃየው ሀገሬ።
የሰለጠኑት ሀገራት ፖለቲካን “ግምኛ ጨዋታ ነው! Politics is a bad game” ለሚለው ወግ እንኳን “መታደል” ተስኖን ፖለቲካችን ለሀገርና ለሕዝብ ገዳይ ጠላት Politics is a killing game” ሆኖብን እንደ ሬት እንዳንገፈገፈን ልጅ፣ ወላጅ፣ አያት፣ ቅድመ አያት… ምንጅላት እስከመባል ወግ ደርሰናል።
የተረታችንን ገፀ ባህርይ ሔዋንን እንደገጠማት ሁሉ እኛም ዜጎች ከፖለቲካ ጋርም ሆነ ያለ ፖለቲካ መኖር ተስኖን እስከ መቼ እንደቆዘምን እንኖራለን? ፖለቲካችን ሰበብ እየሆነስ እስከ መቼ ሁለት አፍ ባለው ሰይፍ እየተሞሻለቅን እንኖራለን? ካፒታሊዝም፣ ሶሻሊዝም፣ ኮሚዩኒዝም፣ ሊበራሊዝም ወዘተ. በሚሰኙ “ኢዝሞች” መሞከሪያ እንደሆንስ እስከ መቼ ይዘለቃል?
ሀገሬን በሻሞ ፖለቲካ ሊቀልቡ የተዘረጉ መዳፎች፤
በማዋዣ ማለዘቢያ የመንደርደሪያ አንቀጽ ውስጥ እንደጠቀስኩት እንደ መተሬ የመረረው ትዝብቴ እነሆ እንዲህ ይነበባል። ምን ያህሎቻችን ልብ ብለን አስተውለን እንደሆን ባላውቅም ሁሌም እንዳስገረመኝ የሚኖር አንድ ፖለቲከኞቻችንን ጠቀስ የሆነ የተለመደ አባባል አለ። በታሪካችን ውስጥ በተለይ እንዳቅማቸው ሥልጣን ላይ ጉብ ያሉ ፖለቲከኞችን በሙሉ ስንጠቃቀስባቸው የኖርነው “የጊዜው ሰዎች” እያልን በመጠቋቆም ነው። በዘመነ ደርግ የኢሠፓ አባላትን ቀጥሎም ተተኪ የኢህአዴግ ቁንጮ ካድሬዎችን፣ ሹማምንቱን፣ ጥገኞቻቸውንና ጋሻ ጃግሬዎቻቸውን በሙሉ ስንጠራቸው የኖርነው “የጊዜው ሰዎች” በማለት ነበር።
ስንማረርባቸውና ስንረግማቸው የባጀነውም እየሰረቁን፣ እያሰሩን፣ እየገረፉን፣ እያሳደዱን፣ እያስለቀሱንና እየገደሉንም እንኳን ቢሆን “የጊዜው ሰዎች” መሆናቸውን አንክድም ነበር። የግርምታችን “ሆ! ሆ!” የጭንቀታችን “እህህ!” እና “ህምም!” እያልን በፌዝ ማጉተምተማችን የባለጊዜነታቸው ውጤት ነበር።
ድህረ ኢህአዴግ ያሉ አንዳንድ የብልፅግናው የቅርብ ልጆች፣ ካድሬዎችና ሹመኞችም ቢሆኑ ሲንቀባረሩ፣ መሬት አይንካን እያሉ ማኅበረሰቡን ቁልቁል እየተመለከቱ ስሜታችንን ሲያጎመዝዙ ማስተዋል ብቻም ሳይሆን በአገልግሎት አሰጣጣቸው ጭምር ቆሽታችን እርርና ድብን እያልንም ቢሆን “የዘመነኛነትን የሊቼንሳ” ቅጽል ከመስጠት “ቸርነታችንን” አላጓደልንባቸውም።
ይህ ጸሐፊ አብዛኞቹን የጊዜያችንን የፖለቲካ ሠፈርተኞች እንደሚከተለው የመደባቸው ሥራቸውንና ሰብእናቸውን ከፈተሸ በኋላ ነው። አንዳንዶች ከፖለቲካ ጋር ያላቸውን የጋብቻ ፍቺ (Divorce) በቃል እያወጁና ካላመናችሁን እያሉ ሰንገው ሊያሳምኑን እየሞከሩ በተግባር ግን “ሰማኒያዬን ቀድጃለሁ” ባሉበት ጓዳ ውስጥ ሲርመጠመጡ ስናስተውል ለእርሱ ሳይሆን ሰብእናቸውን ከፈጠረ ፈጣሪ ጋር እስከመቀያየም እንደርሳለን።
አንዳንዶች የሙት ፖለቲካ ባሎች (Widowers) ወይንም ሚስቶች (Widows) መሆናቸውን እየቆዘሙ ካረዱን በኋላ ሞቷል ካሉት ትዳራቸው ጋር “በውሽምነት – ‹ለቃሉ አጠቃቀም ይቅርታ እጠይቃለሁ›” ሲዳሩ እያስተዋልን በሙት ኅሊናቸው በመሸማቀቅ ከንፈር ስንመጥባቸው እንኳን ለመባነን ሞራል አላገኙም።
አሉ አንዳንዶችም፤ የሟች ፖለቲካ ልጆችን (Orphans) ሰብስበው የሚያንጫጩና አልቅሰው የሚያላቅሱ ሙሾ አውራጆች። እነዚህን መሰል ፖለቲከኞች የዕለት እንጀራቸውን ሲያገኙ የነበረው በሟች ድርጅታቸው አማካይነት ስለነበር ማዕዳቸው ሲነጥፍባቸው ዘዴ ያሉትን ብልሃት የሚጠቀሙት “ሆደ ባሻ” ቢጤዎቻቸውን በመሰብሰብ ማንጫጫት ነው።
አንዳንዶችም የፖለቲካ ጎዳና አደሮችን (Street politicians) ከየአደባባዩ በድምጽ ማጉያ ፕሮፓጋንዳቸው እያሰባሰቡ አብሾ በመጋት ሲያሳክሩ እየተመለከትን “ይብላኝላቸው!” በማለት ለኩነኔ ስናጫቸው ኖረናል።
በርካቶቹ የፖለቲካ ዘማዊያንና አፍቃሬ ድሪያ ሴሰኞችም የእከሌን የፖለቲካ ድርጅት ነፍሴ እስኪጠፋ ወደድኩት፣ የእከነሌን ጠላሁት፣ የእኛን ድርጅት ተጸየፍኩት የእነ እከሌን አቋም መረጥኩት አያሉ እንደ ጠላ ቂጣ እየተፈረካከሱ ሲገለባበጡ አስተውለን “ምነው አንድዬ እድሜያቸውን ለማርዘም ቸር ሆነ?” በማለት ቁጭታችንን የምንገልጠው ፈጣሪን ደፍረን በማማት ነው።
እንደነዚህ ዓይነት “ፖለቲከኞች” የዕለት እንጀራቸውን ለመጋገር የሚሽቀዳደሙት ምጣዱ የሰማበትን ጓዳ እየመረጡ በማንኳኳት የርዕዮተ ዓለም እንኩሯቸውን በማነኮር ነው። ለእነርሱ ይብላኝላቸው እንጂ እኛስ የተለገሰንን ዕድሜ ፈጅተን ተጨማሪ ዓመታትን ከልጆቻችን ተበድረን በመኖር ታዝበን ንቀናቸዋል። ከነገ ሥራቸው ሁሉ የሚገርመው “ዴሞክራሲ የሚገነባው በሂደት ነው!” የሚለው ፌዛቸው ነው። “ሂደት” የሚወክለው ስንት ዓመትን ነው? ኦ ዲሞክራሲ በስምህ ስንት ግፍ ተሰራ! (በዚህ ርዕስ የጻፍኩት ቀዳሚ አርቲክሌ እንደሚታወስ ተስፋ አደርጋለሁ።)
ምነው ሀገሬን ፖለቲካና ፖለቲከኞች አልዋጣልሽ አሏት? ምን ይሆን ተቆራኝቶ፣ ተብትቦና ቀስፎ የያዛት ድግምትና ሟርት? እንደምንስ ለፖለቲካችንና ለፖለቲከኞቻችን ልክፍት ማርከሻውን “መፍትሄ ሥራይ” የሚጠቁም ጎበዝ ጠፋ? የሥልጣን “ሌባ ሻይ”ን እየተጋቱ ከሚቅበዘበዙ “የኢ-ዲሞክራሲ ፀሮችስ” ነፃ የሚያወጣን ነፃ አውጭ እንዴትና ከየት ማግኘት ይቻል ይሆን? ጸሐፊው በብዕሩ ብቻም ሳይሆን በሌት ሕልሙም ጭምር እነዚህን መሰል የጥያቄ ተራራዎች ቧጦ ለመውጣት ሲፍጨረጨር እነሆ የጉልምስናውን ዕድሜ አጋምሶ የሽምግልናውን ምርኩዝ ሊቀበል የቀሩት የተወሰኑ ዓመታት ናቸው።
ይህቺ መከረኛ ሀገሬ በፖለቲካ አብሾ በናወዙና በፈዘዙ ምንዱባን እጅ ወድቃ ላለማየት ጸሐፊው በፆም በጸሎት ብቻም ሳይሆን ስዕለትም ጭምር አክሎበት ከፈጣሪው ጋር ሙግት መግጠም የጀመረው ገና ከወጣትነት ዕድሜው ጀምሮ ነው። በተለይም “የሀገራዊ ምርጫን” መቃረብ በሰማ ቁጥር መንፈሱ የሚንዘረዘረው ልክ እንደ ነሐሴ ብርድ ውስጡ በፍርሃት ቆፈን እንደተቆራመደ ነው። እናንተስ አንባቢያን ከዚህ ስሜት ነፃ ናችሁ? ከሆናችሁ ታድላችሁ! ሰላም ይሁን!
አዲስ ዘመን ህዳር 30/2013