ግርማ መንግሥቴ
ርእሳችን ግልፅ ነው። ሁሉም ያውቀዋል ብቻ ሳይሆን ብዙዎች ቀምሰውታል፤ ወይም ጠጋ ብለው አይተውታል። በዚህም ሆነ በዛ ማንም ለጦርነትም ሆነ ስለ ጦርነት አዲስ አይደለም። ይህን ስንል ቢያንስ ቢያንስ የማንም ጆሮ ጦርነት መጥገቡን መሰረት በማድረግ ነው።
በጉዳዩ ላይ አብዝተው የለፉ ሰዎች እንደሚሉት ሰውና ጦርነት እጅና ጓንት ናቸው እንኳን ባይባል ፍቅራቸው የጠና ነው። አብሮ አደግነታቸው ለፍቅራቸው መነሻ እንደሆነ የሚገልፁት እነዚሁ ትጉሀን ሰው ሰው መሆን ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ አንድም ጊዜ ወደ አንድ ነገር ሳይወረውር፤ ካለውም ሳይተኩስ አይውልም።
ቢሆንም ቢሆንም እንዲህ እንደ አሁኑ ዘመን ቅጥ ያጣ ሳይሆን ባብዛኛው ምክንያታዊነትን የተንተራሰ ነበር። ወይ ህይወቱን ለማቆየትና ለኑሮው ይሆነው ዘንድ ለአደን አልያም እራሱን ከጠላት ለመጠበቅ። ይኸው ነው፤ ከዚህ ባለፈ ጠብ ያለሽ በዳቦ የሱ፣ የጥንታዊው ሰው ባህርይ አይደለም። ይህ የአሁኑ ዘመን (በተለይም ከ1800 ዓ.ም ወዲህ) ሰው ተግባር እና አስተሳሰብ ነው።
የኋላውን እንተወው፤ የዛሬውን እንመልከት። ከተባበሩት መንግስታት ሰነድም እንጀምር፤ ከዛ ወደ ተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ጉዳይ መረጃ ፍተሻ፤ ከዛም ምን ላይ እንዳለን ባጭሩ እንመልከት። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ይፋ እንዳደረገው በአሁኑ ሰዓት ዓለማችን በተለያዩ ሰው ሰራሽ (አመጣሽ) ምክንያቶች እየተናጠችና ማህበራዊ ምስቅልቅሎሽ እየተፈጠረ ሲሆን በዋናነት ጦርነት፣ የህፃናት መብት ረገጣ፣ የስርአተ ፆታ ኢ-እኩልነት፣ ረሀብ፣ ግድያ እና የመሳሰሉት ገፊ ምክንያቶች ናቸው።
እንደ ድርጅቱ ወቅታዊ ሪፖርት በእነዚህና መሰል ችግሮች ምክንያት በአሁኑ ሰዓት 82 ነጥብ አምስት ሚሊዮን ህዝብ ከቀዬው የመፈናቀል ጉዳት ሳቢያ እርዳታ ፈላጊ ሲሆን ድርጅቱም ይህንን አስከፊ ችግር ለመቅረፍ ለጋሽ አገራትን በማስተባበር እርዳታ እያቀረበ ይገኛል። ይህ ብቻም አይደለም፣ ይኸው ድርጅት እንደሚለው በአሁኑ ሰዓት ከ40 ሚሊዮን በላይ ወገኖች በዘመናዊ ባርነት ስር የሚገኙ ሲሆን ይህም ከመቶ ሰው አንዱ በዚሁ ማህበራዊ ቀውስና ኢፍትሀዊ አሰራር ተፅእኖ ስር ይገኛል፤ ወይም የዘመናዊ ባርነት ሰለባ ሆኗል።
በተመድ የስደተኞች ጉዳይ ወቅታዊ መረጃ ደግሞ በአሁኑ ሰዓት በአጠቃላይ ዓለማችን ከ70 ሚሊዮን በላይ ህዝብ በተለያዩ ምክንያቶች (በዋናነት በጦርነት) ከአካባቢው ተፈናቅሎ በከፍተኛ ደረጃ እርዳታ ፍለጋ ላይ ይገኛል። ከእነዚህ ውስጥ ደግሞ አብዛኞቹ ህፃናትና ሴቶች መሆናቸው ምስቅልቅሎሹን ከፍ አድርጎታል፡፡
ሁለቱም ሆኑ ሌሎች በተመሳሳይ ተግባራት ላይ የተሰማሩ ተቋማት በሚያወጧቸው መግለጫዎችና በሚያስተላለፏቸው ተከታታይ መልእክቶቻቸው እንደሚሉት ይህ ሁሉ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፤ ከሁሉም በላይ ሰብአዊ ተመሰቃቅሎ የሚፈጠረው እዚህ ግቡ በማይባሉና ከጠረጴዛ ውይይት ከማያልፉ ጉዳዮች ሲሆን፤ መንግስታትም ሆኑ አገራት፣ አማፂያንም ሆኑ ተቃዋሚዎች ምን ግዜም አማራጫቸው የጠረጴዛ ዙሪያ ውይይት መሆን ያለበት መሆኑን ነው አጥብቀው የሚያሳስቡት።
በአህጉሪቱ ሰላም ያለበትን አገርና አካባቢ ከመፈለግ በሰላም እጦት የሚታመሰውን አካባቢ መፈለግ ይሻላል። ለምን ቢሉ፣ የት ሰላም አለና ነው ሰላማዊ ቦታ የሚፈለገው? ከሁሉም አሳሳቢው ደግሞ ወትሮም ሰላም መሆን የቃታቸው አገራት ወደ ለየለት ቀውስ ሊገቡ አፋፍ ላይ መሆናቸው ነው።
ለዚህም ናይጄሪያ ያለችበት ወቅታዊ ሁኔታ በቂ ማሳያ ሲሆን፤ በ2019 (በፈረንጆች አቆጣጠር) ከአህጉሩ በአንደኝነት ረድፍ ላይ የነበረችው የገጠማትንም ችግር አለማቀፉ ማህበረሰብ ችላ ያለባት (“The most neglected crisis in the world in 2019» የተባለላት)ና አሁንም በተሟላ ጤንነት ላይ የምትገኘው ካሜሩን (ሌሎቹን የዚህ ፅሁፍ አንባቢ በሚገባ ያውቃቸዋል ተብሎ ስለሚታሰብ ታልፈው ማለት ነው) ተጠቃሽ ናቸው።
ይህን ስንል በከፋ ረሀብ እየተሰቃየ ያለውን አፍሪካዊ ደምረን ሳይሆን በግጭትና ጦርነት፤ ኢሰብአዊ አያያዝና መብት ረገጣ ወዘተ ምክንያት የሚደርሰውን ማህበራዊ ተመሰቃቅሎ ታሳቢ በማድረግ ነው። አሁን ወደራሳችን።
በአጠቃላይ ሲታይ ኢትዮጵያ ለየት ያሉ ችግሮች አጋጥመዋታል ተብለው ከሚጠቀሱት ጊዜያት መካከል አንዱ ይህ ያሁኑ ክፉና ማህበራዊ ተመሰቃቅሎን ያስከተለ ጊዜ ነው። በመሆኑም እሱው ላይ አተኩረን እንዝለቅ፤ እንታዘብም።
ጁንታው ትህነግ “ሀ” ሲል የጦርነት ፊሽካውን ከነፋበት ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ በርካታ ሰብአዊ ቀውስና ቁሳዊ ውድመት ደርሷል። ይህ በተለይ በሰሜኑ የአገራችን ክፍል ይስተዋል እንጂ ላለፉት 27 ዓመታት በሁሉም የአገራችን ክፍሎች ሲስተዋል የነበረ አሰቃቂ ክስተት ነው። ከኮንሶ እንጀምር።
ከጠፋው የሰው ህይወትና የወደመው ንብረት ውጪ በኮንሶ ዞንና አካባቢው (በተለይ ጉማይዴ አካባቢ የሚባለው) በተከሰተው የእርስ በእርስ ግጭት ከሁለት ሺህ 500 በላይ የቤተሰብ አባላት ከመኖሪያቸው ተፈናቅለዋል፡፡ እዚህ ላይ “በደቡብ ክልል ቤንች ማጅ ዞን ጉራ ፈርዳ ወረዳ ‘ከአካባቢያችን ውጡልን’ በሚል ምክንያት ከተከሰተው ሁከት እና ብጥብጥ ጋር በተያያዘ የወረዳው አስተዳዳሪን ጨምሮ የተለያዩ የስራ ሃላፊዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል” (ጥቅምት 8 እና ጥቅምት 11 ቀን 2013 ዓ.ም) የሚለውን የወቅቱን ሰበር ዜና ከሰሙና 15 ሺህ 86 የቡራዩ ተፈናቃዮች (መስከረም 2011) የሚለውን ዜና (ይህ የአንዱ ቀን ግጭት መሆኑን ልብ ይሏል) ከጨመሩበት ሀዘንዎ ከፍ ይላልና እንለፈው።
(አይ የሚል ካለ ለአይነት ያህል “የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ መስፍን እርካቤ በወቅቱ ለመገናኛ ብዙሀን “በአጠቃላይ በዞኑ 51ሺህ 18 ተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸው ተፈናቅለዋል” (የካቲት 2011 ዓ.ም) ሲሉ የገለፁትን መጨመር ይቻላል። በዚህ ላይ “በአሰቃቂ ሁኔታ …”፣ “በሚዘገንን አኳኋን”፣ “በግፍ የተገደሉ” … የሚሉትን ድርጊት ገላጭ ቃላት ካከሉበት ማህበራዊ ምስቅልቅሎሹ የት እንደደረሰ ይረዱበታልና ለአንባቢ ትተነዋል።
አገራችን ያጋጠሟትን መከራዎች መዘርዘር ሳይሆን ርእሰ ጉዳያችንን በተወሰኑ ማሳያዎች አማካኝነት ወደ መሬት ማውረድና ትዝብታችንን ማካፈል ነው። በእነዚህ ሁለቱ ክስተቶች ብቻ እንኳን ማህበራዊ ምስቅልቅሎሹን ብንመዝነው ያለው ጉድ ከአእምሮ በላይ ነውና “እድሜ ለአገራችን የዘር ፖለቲካ” ባዮች ቢበዙ ምንም የሚገርም ነገር አለመኖሩን መገንዘብ ይቻላል።“ያሁኑ ይባስ” እንዲሉ ለዛሬው ጽሑፋችን መነሻ የሆነው ያሁኑ ነውና እሱን እንቃኝ።
ድሮም ያላማረበት የአገራችን ፖለቲካ ከለውጡም በኋላ እንኳ እንከን አልተለየውም። ምናልባት እኛንም ሆነ ፖለቲካውን እረፍት ማጣታችንን ለየት የሚያደርገው እረፍት ያሳጣን ሀይል ከለውጡ በፊት ስለ እረፍት፣ ህግና ህጋዊነት ሳያሰልስ ሲነግረን የነበረ፤ መንግስት ሆኖ የገዛን አካል መሆኑ ነው።
በርካቶች በፍቅር የሚጠቅሷት የማርቲን ሉተር ኪንግ “በማንኛውም ላይ ጸረ-ፍትህነት ከተፈጸመ የሚያስከትለው ስጋት ለሁሉም ነው (Injustice anywhere is a threat everywhere” አባባል በየትኛውም አካባቢ፣ ቦታና ጊዜ የሚፈፀም ወንጀል፣ የሰብአዊ መብት ጥሰት፣ የህግ የበላይነት አለመከበር፣ አጉራ ዘለልነት፣ ሽፍትነት፣ ዘረፋ፣ ግድያ፤ በእነዚህም ምክንያት የመከሰት አስከፊ ማህበራዊ ምስቅልቅሎሽ በዛው አካባቢና በዛው ህብረተሰብ ብቻ ተወስኖ የሚቀር ሳይሆን ለአጠቃላይ አገሪቱና ዜጎች ነውና “እኔ ምኔ ተነካ” ሊባልም ሆነ ጭራሹንም ሊታሰብ አይገባውም። ይህ ከሆነ ጉዳዩ ከማህበራዊ ምስቅልቅሎሽ አልፎ አገራዊ ብሎም አህጉራዊ ከመሆን አይቀርምና የጋራ ጥንቃቄንና ሀላፊነትን ሁሉ ይሻል ማለት ነው።
አክሎግ ቢራራ (ዶክተር) የተባሉ ፀሀፊ የአፄ ኃይለሥላሴን የሊግ ኦፍ ኔሽን “አንድ ዘር ከሌላው ዘር ይበልጣል፤ ይሻላል የሚባለው እምነት ዋጋ እንዲያጣ ሆኖ ካልተወገደ” የሚለውን ዓለምን ያናጋና ቆም ብሎ እንዲያስብ ያደረገ፤ በታሪክ መዝገብ ላይ በወርቅ ቀለም የተፃፈን ንግግር በመጥቀስ እንዳሉትና “ሰላም፤ እርጋታ፤ የጋራ ደህንነት ስኬታማ” ሊሆን አይችልም። የዚህ ሁሉ ችግር እናት ደግሞ የዘር ፖለቲካ ከምንችለውና ከምንሸከመው በላይ መዘራቱ ነው። ይህን የዘራው አካል የእስከ ዛሬው አልበቃ ብሎት ዛሬም አጉራህ ጠናኝ ብሎ እዛው ውስጥ በባሰ ሁኔታ ተነክሮ ይገኛል።
እጅግ የሚያሳዝነው የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሁሪያ አሊ “በትግራይ ክልል ባለፉት 46 ዓመታት የተለያዩ ጦርነቶች ተካሂደዋል። በዚህም ምክንያት የትግራይ እናቶች የወላድ መካን ሆነዋል። አሁን ላይም አጥፊው ቡድን በፈጠረው ችግር የፌደራል መንግስት ሕግ የማስከበር እርምጃ ውስጥ ገብቷል” በማለት ሰሞኑን ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ የሰጡትን አስተያየት ስናነብና ሌሎች መሰል የሀዘንና ዋይታ ድምፆችን ከወደ ማይካድራ ስንሰማ ማህበራዊ ተመሰቃቅሏችን የደረሰበት ጣራ እጅግ አሳዛኝ በመሆኑ ያሳስባል።
የኢትዮጵያን ህዝብ፣ በተለይም ከፖለቲካ ውጪ ያለው ምን ማህበረሰብ ይህ የእርስ በእርስ ጉዳይ ያስጨነቀውን ያህል ምንም ነገር ሲያስጨንቀው ቀርቶ ሲያሳስበው እንኳን ታይቶ አይታወቅም። የአሜሪካው መሪ ከነጩ ቤተ መንግስት ሊሰናበቱ አንድ ሀሙስ እንደ ቀራቸው እያወቁ “ግብፅ የሕዳሴ ግድብን ቦምብ ታወድም” ዘንድ ሲመክሩና ከግብፃዊያን በላይ ግብፃዊ ለመሆን ሲሞክሩ እንኳ ሀበሻ ሊጨነቅ ቀርቶ ሆዱ እንኳ ዶጭ እንዳላለ ሁሉ በውስጥ ችግራችን ግን ያልተብሰለሰለ የለም።
“ለምን?” ለሚለው ድሮስ ቢሆን እርስ በርስ መተጋገዝ እንጂ ማን ማንን ሊያወግዝ ተፈጠረና ነው ወደ ትርጉምም ሆነ ትርፍ የለሽ ግጭትና ውጊያ (መቸም ይህ አሳፋሪና እኩይ ተግባርም ሆነ ያስከተለው ማህበራዊ ምስቅልቅሎሽ በፖለቲካውም ሆነ በአጠቃላይ አገራችን ታሪክ ጥቁር ነጥብ ሆኖ እንደሚጠቀስ ከወዲሁ ለመናገር ነብይ መሆን አያስፈልግም) መገባቱ? ነገሩ ዶክተር አክሎግ “ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያዊነት ዋና አደጋ የሆነው የዘውግና የኃይማኖት ጽንፈኞች/ሽብርተኞች ክፍሉ ነው” እንዳሉት ነውና “የዘውግና የኃይማኖት ጽንፈኞች/ሽብርተኞች” ከድህነት በላቀ ደረጃ የጋራ ጠላታችን እየሆነ ያለ ይመስላልና በጋራ አንድ ልንለው እንደሚገባ ያስገነዝበናል።
በቅርቡ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ አስተያየታቸውን የሰጡ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችና የተቋማት ሀላፊዎችም ይህንኑ የዶክተር አክሎግን አስተያየት የሚካፈሉ ሲሆን በተለይ ለዚህ ሁሉ አበሳና ፖለቲካዊ ጦስ ከሁሉም በላይ ተጠያቂው አጀንዳውን ይዞ ወደ መሀል የገባውና አገሪቱን ለ27 ዓመታት በበላይነት የመራው የህወሓት ጁንታ ቡድን እንደሆነ ይናገራሉ። አገሪቱን በመራባቸው 27 ዓመታትም በአገሪቱና ዜጎች ላይ ያደረሰው ግፍና እልቂት እጅግ የከፋ ሲሆን ይህንንም በየራሳቸው መንገድ ገልጸውታል።
አስተያየታቸውን ከሰጡት አንዱ አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ ሲሆኑ እንደ እሳቸው አገላለፅና ምዘና ይህ የወያኔ/ትህነግ ጁንታ ቡድን በአሁኑ ሰዓት በመከላከያና ሌሎች ንፁሀን ወገኖች ላይ በማይካድራ በፈፀመው እጅግ አረመኔያዊ ተግባሩ ብቻ ሳይሆን እስከ ዛሬ በሰራቸው ወንጀሎች ሁሉ ዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት ቀርቦ ሊጠየቅ ይገባል።
የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር ፕሬዘዳንትና ደራሲ አበረ አዳሙም ከዚሁ የአንዳርጋቸው አስተያየት በሚስማማ መልኩ አስተያየታቸውን የሰጡ ሲሆን በየኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ወያኔ (ጁንታው)ን የሚያክል አስፀያፊ ታሪክ የሰራ አንድም ኢትዮጵያን የመራ አካል የለም። እነዚህን አስተያየቶች እጅግ ብዙ (ምናልባትም የህዝቡ ሁሉ) ሲሆኑ ለማሳያ ያህል እነዚህን ከጠቀስን ወደ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ እንሂድ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ ውጊያው በድል መጠናቀቁን ባበሰሩ ማግስት በፓርላማ ማብራሪያቸው እንደገለፁት ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም ጁንታው ቡድን የሰሜን እዝ መብራት በጣጥሶ፣ ወታደራዊ ተቋማቱም ሆኑ የሰራዊቱ አባላት ከበላይም ሆነ እርስ በእርስ እንዳይገናኙ ግንኙነት አቋርጦ፣ ብዙዎችን በግፍ ገድሎ ብዙዎችን አፍኖ፣ በኢትዮጵያ ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ አሳዛኝ ስራ ሰርቷል። በዚህም ምክንያት እንዲመታ ተደርጓል።
በስልጣንና ገንዘብ ጥሙ የተነሳ “ስግብግቡ ጁንታ” ስያሜንና ሌሎች በርካታ “የእናት ጡት ነካሽ” አይነት ቅፅሎችን ያተረፈው ጁንታው ትህነግ፤ በከፈተው አገርን የማፍረስና ስልጣንን በሀይል የማስመለስ ጥረት ሳቢያ በገዛ አገሩና ወገኖቹ ላይ ጦርነት ማወጁን ተከትሎ እስከ ተደመሰሰበት እለት ድረስ (በሶስት ሳምንታት) በርካታ መረጃዎች የወጡበት ሲሆን፤ ከእነዚህም አንዱ ያሰለፈው የሰው (ጦር) ሀይል ብዛትና ያስከተለው ማህበራዊ ተመሰቃቅሎ ነው።
ከተለያዩ ምንጮች መረዳት እንደተቻለው ጁንታው ትህነግ በአጠቃላይ 250ሺህ ሰራዊት ለውጊያ አሰማርቷል። ይህን ያህል ቁጥር ያለው ሰራዊት ያሰማራ እንጂ ከዚህ መሀል ለአቅመ ውጊያ ደርሷል ተብሎ የሚጠበቀውና መዋጋት ይችላል ተብሎ የተለየው ከ50 እስከ 60 ሺህ ያህሉ ብቻ ሲሆን ሌሎቹ እናቶችና ህፃናት በመሆናቸው ምክንያት ለውጊያ ብቁ አይደሉም ብቻ ሳይሆን መጀመሪያውኑም ወደ እዚህ ተግባር ሊገቡ የሚገባቸው አልነበሩምና ነው፡፡
ከላይ ያሉትን የአዲስ ዘመን አስተያየት ሰጪዎች አስተያየቶች ደግመን እዚህ ልንጠቅስ የምንገደደው፤ አስከፊውን የሰብአዊ መብት ጥሰት ብቻ ሳይሆን ያደረሰውንም ማህበራዊ ተመሰቃቅሎ፣ ኢፍትሀዊነትን፣ ዓለም አቀፋዊ የሰብአዊ መብት ጥሰት ወዘተ ወዘተ ለመጠቆም እየሞከርን ያለነው። ዝርዝሩ ብዙ ነው፤ ወደፊት የምናይ የምንሰማው ተቆጥሮ የሚያልቅ ተለክቶ የሚሰፈር አይመስልምና ሁሉንም ለጊዜ ትተን ትዝብታችንን እናጠቃለው።
ጁንታው በማን አለብኝነት በከፈተው ጦርነት ምክንያት ስንትና ስንቶች ለተለያዩ ማህበራዊ ምስቅልቅሎች እንደተዳረጉ ቤቱ ይቁጠረው ብለን የምንተወው ጉዳይ አይደለም። ይልቁንም አንድ ሁለት … ብለን ነቅሰውን በማውጣት ለታሪክም ለትዝብትም ማብቃት ይጠበቃል። ለጊዜው ግን ይሄው ቡድን በጫረው እሳት ምክንያት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ወገኖች ከመኖሪያ አካባቢያቸው እንደ ተፈናቀሉ፤ መፈናቀሉም እስከ ሱዳን ድረስ እንደዘለቀ ጠቅሰን ማለፍ ይገባናል።
መንግስት ጦርነቱን በአጭር ጊዜ በማጠናቀቁ፣ በተለይም (ምናልባት ወደ ፊት የሚያሸልምና በታሪክም በወርቅ ቀለም የሚፃፈው፤ “አንድም ሲቪል ሳይገደል” የሚለው) ከተጠናቀቀም በኋላ ተፈናቃዮችን በአስቸኳይ ወደ ነበሩበት መልሶ የማቋቋሙ ጉዳይ ትኩረት ተሰጥቶት ሊሰራበት እንደሚገባም ታዝበናል።
አዲስ ዘመን ህዳር 28/2013