በአንድ ቀበሌ የሚኖሩ ሰዎች ስብሰባ ተጠሩ ። አመራሮች ንግግር አደረጉ ።ተሰብሳቢዎች ደግሞ በውይይቱ ላይ አስተያየታቸውን ሰጡ ።በመሃከል አንድ ሽማግሌ የሰጡትን አስተያየት የመድረኩ መሪዎች አብጠለጠሉት፤ አጣጣሉት ።እንደውም አንደኛው ሰብሳቢ “ይሄ የነፍጠኛ አመለካከት ነው” ብለው ተቹት ።ሽማግሌው በንዴት ተነስተው “እኔ ነፍጠኛ ነኝ፤ አንተ ግን ንፍጣም ነህ “ አሉት ተብሎ አሁን በህይወት በሌለ አንድ አነስተኛ መፅሔት ላይ ማንበቤን አስታውሳለሁ፡፡
ኢህአዴግ ሥልጣን ሲይዝ በተደጋጋሚ ሲጠቀምባቸው የነበሩ አሉታዊ ቃሎች ነበሩ ።ከነዚህ ውስጥ ትምክህተኛ፣ ነፍጠኛ እና ጠባብ የሚሉት ቃላት ግንባር ቀደሞቹ ናቸው ።ትምክህት (chouvenesim) የሚለውን ቃል የከሳቴ ብርሃን ተሰማ የአማርኛ መዝገበ ቃላት “እንደ እኔ ያለ ግን አለ ?›› ብሎ ትምክህትን ማድረግ በሚል ይፈታዋል፡፡(ትልቁን የአፍሪካ ጦር የደመሰስን ማን ይችለናል? ጦር መሥራት እንችልበታለን በሚል ትምክህት የሚናገሩትን እንኳን እኛ ታሪክም አይዘነጋቸውም) ነፍጠኛ ሲተረጉመው ደግሞ “ነፍጥን የሚያነግት ወታደር፣ በነፍጥ ተኮሶ የሚገድል፣ በነፍጥ አነጣጥሮ የሚመታ” ይለዋል ።
በእነዚህ ቃላት የእገሌ ብሄር ነፍጠኛ የእንቶኔ ብሄር ደግሞ ጠባብ እየተባለ ተፈርጆ ነበር ።ይሄ ደግሞ ፅንፈኞች ብሄርን ከብሄር ለማለያየትና ለማጋጨት የተጠቀሙበት ደባ ነው ሲሉ የፖለቲካ ልሂቃን ይናገራሉ ።በእነዚህ ቃላት ስሁት ብያኔና ፍረጃ የትህነግ ቡድን ጎሳዎች ላይ የስነልቦና ጥቃት ለማድረስ ሲጠቀምበት ቆይቷል ።
ነፍጥ በአማርኛ የጠብመንጃ አቻ ስያሜው ነው። በግእዝ ነፍጥ ነዳጅ ማለት ነው። ፈሳሹ ነዳጅ ይሁንጠጣሩ (ጥይቱ) አላጣራሁም ።ነፍጥ በሀገራችን መጀመሪያ የታየው በኢማም መሀመድ አልገአዚ (ግራኝ መሐመድ) ጦር ውስጥ ነበር ።በወቅቱ ልዕለ ኃያላን የነበሩት ፖርቱጋልና ኦቶማን ቱርክ ቅኝ ለመያዝ ባላቸው ፍላጎት ሲፎካከሩ፤ ቱርክ ግራኝን ነፍጥ በማስታጠቅ ተጠቀመችበት ።
ዘግይቶም ፖርቱጋል ደግሞ የንጉሡን ጦር ነፍጥ በማስታጠቅ የድርሻዋን ተወጣች ።በወቅቱ በሀገራችን የነበረው ግጭት ለኔ የዘመኑ ልዕለ ኃያላን የውክልና ጦርነት ይመስለኛል ።ዓላማቸው ግን ተዋጊዎቹን ለመርዳት ሳይሆን አንዱ አሸንፎ ከወጣ እጃቸውን ሰደው ኃይል አሰማርተው ሀገሪቱን በቅኝ ለመያዝ እንደነበር ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡
ስለ ነፍጠኛ ካወራን ዘንዳ እንደ ትህነግ ፍረጃ በአንድ ጎጥ የሚደመደም አይደለም ።ጠባብ የሚለውን ቃልም እንዲሁ የደደቢት ደደቦች “ሲጠበቡበት” በአንድ ብሄር ላይ የፈረጁት ነው ።የደደቢት ደደቦች የሚለው ቃል አሁንም በስርጭት ላይ ያለ የግል ጋዜጣ ከአሥር ዓመት በፊት ከሚያወጣቸው ፅሑፎች የወሰድኩት መሆኑ ይሰመርበት፡፡
ብሄሮችን በአካልና በስነልቦና ሲበድሉና ሲደበድቡ ስለነበረ ስያሜው ያንሳቸዋል የሚሉ እንዳሉ ሳይዘነጋ። አሰገደ ገብረሥላሴ የተባሉ የፓርቲው አባል የነበሩ እንደፃፉት ህወሓትና ማሌሊት በ1977 ለግምገማ ሲቀመጥ ከ800 በላይ ተሰብሳቢው በነበረበት በማሌሊት (ማርኪሳዊ ሌሊናዊ ሊግ ትግራይ)ጉባኤ ላይ ህወሓት ጠባብነት የተጠናወተው ድርጅት ነው በሚል ክርክር ጦፎ ነበር ይላሉ ።
ጠባብነት የራስን ጎጥ ከሁሉ እንዲበልጥ ሌላውን ግን እንዲደናገጥ ማናናቅና ማጣጣል፤ በስነልቦና ሲብስም አካላዊ ጥቃትና ጉዳት ማድረስ ነው ።በኢኮኖሚውም በማህበራዊም ሆነ በፖለቲካ የሌላውን ጎጥ ተሳትፎ እያዳከሙ በጎን ወገኔ ለሚሉት ጎሳ ተጠቃሚ የማድረግ ሙከራ ነው ።የጀርመኑ ናዚ ዕሳቤ እኛ ምርጥ ዘር ነን (arian rase) ከሚል አመለካከት የመነጨ ነው ።ይህ የጠባብነት ማሳያ ይመስለኛል ።የጠባብነት አመለካከቱ ዘር ማጥራት በሚል ሄዶ አይሁዶች እየተሰበሰቡ እንዲፈጁ ተደረገ ።ወላፈኑ ወደ ሌሎች ሀገሮች በመድረሱ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ተቀሰቀሰ ብዙ ህዝብ አለቀ ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ኅዳር 21 ቀን በፓርላማ በተደረገው ልዩ ስብሰባ ባደረጉት ንግግር “ ከለውጡ ወዲህ ባሉት ጊዜያት በመላ ሀገሪቱ 113 ግጭቶች ተካሂደዋል፡፡” ከ600 በላይ የሆኑ ሰዎች የተጨፈጨፉበት ማይካድራን ሳይጨምር ፤ከቀይ ሽብር የባሰ አሸባሪነት ተደገመ ማለት ነው ።ለተሰዉት እያዘንን ድርጊቱ ግን የጠባብነትና የነፍጠኝነት ማሳያ ነው ብንል አያንስበትም።
ነፍጠኛ እያለ የሚጨናነቀውና የሚጨቃጨቀው ትህነግ ወደ ደደቢት ለትግል ሲሰማራ የተጠቀመው በነፍጥ ነው ።በ17 ዓመት የትግል ዘመናቸው በለስ እየበሉ መከራውን ረሃብና ችግሩን ጦሩን (የደርግን) አመለጡ ።(በግሌ ወደ ገጠር አካባቢዎች ስሄድ እሾክ ስላለው እረኞች እንዲልጡልኝ እየለመንኩ በለስ በፍቅር እበላለሁ) በለስ እየገመጡ መጡ በለስ ቀናቸውና ሥልጣን ጨበጡ።
መቼም በዚያ ዘመናቸው ሲታገሉ በየቦታው ቄጠማና አበባ እያርከፈከፉ እንዳልመጡ ቢያውቁትም ሥልጣን ሲቆናጠጡ ይዘነጉታል ብዬ አስባለሁ ።(በምቾት ማለቴ ነው)። አራት ኪሎ የገቡት በየሀገሩ ነፍጥ እያርከፈከፉ (እየተታኮሱ) ነበር ።ስለዚህ ለኔ እንደ ትህነግ ፍረጃና አሉታዊ ትርጓሜ ከሄድን ቁጥር አንድ ነፍጠኛ ፣ጠባብና ትምክህተኛ ትህነግ ነበረች ።ግን አቅጣጫውን አዞረችና ሌሎችን ፈረጀች፡፡
ፖሊስ መጀመሪያ የተቋቋመው የአራዳ ዘበኛ በሚል ስያሜ በዳግማዊ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት ነው ።ፖሊስ ከመመስረቱ በፊት የገበሬውና አርብቶ አደሩ ከቦታ ቦታ ነፍጥ አንግበው ይንቀሳቀሱ ነበር ።የሀገራችን ሲራራ ነጋዴዎችም ምርታቸውን በግመሎቻቸው ጭነው የበረሃውን መንገድ ሲንቀሳቀሱ ነፍጥ አይለያቸውም ።ሌላውን ሊዘርፉ ሊያስገብሩ ሳይሆን ራሳቸውን ከጥቃት ከአውሬ ለመከላከል ።አሁን በየቦታው በፖሊስ ተያዘ እየተባለ የሚነገረው የመሣሪያ ብዛት በዴሞክራሲ ሥርዓት ሳይሆን በነፍጥ ሊያነጥፉን ፈልገው ነበር እንዴ ያሰኛል።
አዲስ ዘመን ህዳር 27/2013