የተወለዱት ወራሪው ፋሺት ኢጣሊያ ከኢትዮጵያ በተባረረበት በ1933 ዓ.ም ምዕራብ ሸዋ ጅባትና ሜጫ አውራጃ በጨሊያ ወረዳ ነው። አስተዳደጋቸው እንደማንኛውም የአርሶአደር ልጅ ከብት እየጠበቁና ወላጆቻቸውን እያገዙ ሲሆን፤ ልክ 12 ዓመት ሲሆናቸው አምቦ ከተማ ለትምህርት ይላካሉ። የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርትቸውን የተከታተሉት እዚያው አምቦ ከተማ በሚገኘው ማዕረገ ህይወት ዘቀዳማዊ ኃይለስላሴ 1ኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ነው። ከልጅነታቸው ጀምሮ እንደ ጃገማ ኬሎ የመሳሰሉ ጀግኖች አርበኞችን ታሪክ ሲሰሙ በማደጋቸው ለወታደሮች ልዩ የሆነ ፍቅርና ከበሬታ ነበራቸው። በተለይም ደግሞ በአካባቢያቸው በርካታ ኮሪያ ዘምተው የተመለሱ ወታደሮች ስለነበሩ በአለባበሳቸውና በአረማመዳቸው ተማርከው እንደእነሱ የመሆን ህልም ከወዲሁ ሰነቁ። ይህ ህልማቸው ደግሞ ህልም ብቻ ሆኖ አልቀረም። ዘጠነኛ ክፍል ሲደርሱ ለውትድርና የመመልመል ዕድሉ ትምህርት ቤታቸው ድረስ መጣላቸው፤ ሳያመነቱ ተጠቀሙበት፡፡
እነመንግስቱ ንዋይ መፈንቅለ መንግሥት በሞከረቡት በ1953 ዓ.ም ላይ ሆለታ በሚገኘው የጦር ማሰልጠኛ ገብተው ለአንድ ዓመት ሰልጥነው ወጡ። ምክትል መቶ አለቃ ሆነው ሦስተኛ ክፍለጦር አንበሳ ግንባር ቢመደቡም የክፍለ ጦሩ አዛዥ ሌፍተናንት ጀኔራል አማን አንዶም እሳቸውም ሆኑ ሌሎች አዲስ መኮንኖች ሠራዊቱን ከመቀላቀላቸው በፊት አየርወለድ ዝላይ መሰልጠን እንደሚገባቸው በማዘዛቸው ደብረዘይት ተላኩ። በዚህ ብቻም አላበቃም፤ አዋሽ አርባና ሃዋሳ የኮማንዶ ትምህርት እንዲሁም አማሬሳ በሚባል ስፍራ የሻለቃ አመራር ስልጠና ለሦስት ወራት እንዲሰለጥኑ ተደረገ፡፡
ከስልጠናቸው ማግስት ጀምሮ ጠንካራና ከባድ በሚባሉ የጦርነት መስኮች ላይ ተመድበው ብቃታቸውን ማስመስመስከር ቻሉ። በተለይም በኢትዮ ሱማሊያ ጦርነትና ከሻቢያ ጋር በሚደረጉት የኤርትራ ግንባሮች ላይ ድንቅ ችሎታቸውን ማሳየት በመቻላቸው ከተራ መኮንንነት ወደ ሻለቃ አዛዥነት ብሎም እስከ ሜጀር ጀኔራልነት ለመድረስ ቻሉ። የሦስተኛው አብዮታዊ ሠራዊት ምክትል አዛዥ፥ የ18ኛው ክፍለ ጦር አዛዥ እንዲሁም የቴዎድሮስ ግብረኃይል ዋና አዛዥ ሆነውም በቀድሞው ሠራዊት ውስጥ አስተዋፅኦ አበርክተዋል። በተለያዩ ክፍለ ጦሮች ተመድበው በሚሠሩበት ጊዜም ችግሮችን አስቀድሞ በብልሃት መፍታትን የሚመርጡት እኚሁ የአገር ባለውለታ ታዲያ በጦርሜዳ አጋሮቻቸውና አለቆቻቸው «አባ መላ» የተባለ ቅፅል ስም ማግኘት ችለዋል።
ገርብ ሻለቃ፣ ነበልባል፣ ተራራና በመሳሰሉት ክፍለ ጦሮች ተመድበው ለአገራቸው አንድነት ብርቱ ትግል ሲያደርጉ የኖሩት እኚሁ ግለሰብ በተለያዩ ጊዜያት በጠላት በተተኮሱ ጥይቶች ቆስለዋል፤ ህይወታቸውንም እስከማጣት ለሚያደርሱ አጋጣሚዎችም ተዳርገው ያውቃሉ። ከእነዚህ መካከልም የደርግ ሠራዊት ከህወሓት መራሹ ሠራዊት የመጨረሻውን ግብ ግብ በሚያደርግበት በ1983 ዓ.ም ግንቦት የመጀመሪያዎቹ ቀናት ላይ የቆሰሉበት አጋጣሚ ተጠቃሽ ነው። የደርግ ሊቀመንበር ኮሎሬል መንግሥቱ ኃይለማርያም ስልጣናቸውን ጥለው ወደ ዚምባቡዌ ከሸሹና ስርዓቱም ከተገረሰሰ በኋላ በኢህአዴግ መንግሥት በቀረበላቸው ጥሪ መሰረት መሳሪያቸውን አስረከቡ። ይሁንና ልክ እንደብዙዎቹ የትግል ጓዶቻቸው የደርግ ሠራዊት ነበራችሁ በሚል በአዲሱ መንግሥት ለእስር ተዳረጉ። ያለምንም ክስና ፍርድ ለዘጠኝ ዓመታት በወህኒ ቤት እንዲማቅቁ ተገደዱ።
ለአገራቸው ሉዓላዊነትና ለህዝባቸው ደህንነት ብዙ መስዋዕትነት የከፈሉት እኚሁ የአገር ባለውለታ ታዲያ ምንም እንኳ በገዢው መንግሥት የከፈሉት ዋጋ አጥቶ ቢቆይም ውለታቸውን ያስታወሰ አንድ ኢትዮጵያዊ ድርጅት አሜሪካ ዋሽንግተን ዲሲ ድረስ ጋብዞ ከነኮሎኔል ካሳ ገብረማርያም ጋር «የአገር ባለውለታ» በሚል ሽልማት አበርክቶላቸዋል። ሜጀር ጄነራል መርዳሳ የውትድርና ህይወታቸውንና ያለፉባቸውን የጦርነት ውጣውረዶችን የሚያትት «የኢትዮጵያዊነቴ ትውስታ» በሚል መፅሐፍ ለማሳተም በቅተዋል። እኛም የዛሬው የዘመን እንግዳችን አድርገን በመጋበዝ በውትድርና ዘመናቸው የነበራቸውን ገጠመኞቻቸውንና በወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት አድርገናል። እንደሚከተለው ይቀርባል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ወላጆቾት ካወጡሎት መጠሪያ ስያሜ ውጪ «አባመላ» እየተባሉ ይጠራሉ፤ ይህን ስያሜ በምን አጋጣሚ ሊያገኙ እንደቻሉ ቢያስታውሱንና ውይይታችንን ብንጀምር?
ሜጀር ጀኔራል መርዳሳ፡- በመሰረቱ እኔ ከልጀነቴ ጀምሮ የሚያጋጥሙኝን ችግሮች በዘዴና በብልሃት መፍታትን እመርጣለሁ። ይህንን ያየ አባቴ «ይሄ ልጅ መለኛ ነው» ይለኝ ነበር። ይህ ልምዴ ታዲያ እያደገ ሄዶ በጦርነት ሜዳም ችግሮችን በጥይት ከመፍታት ይልቅ አስቀድሜ በብልሃት መፍታት አዘወትር ስለነበር የጦርሜዳ ጓደኞቼና አለቆቼ «አባ መላ» እያሉ ይጠሩኝ ነበር። ይህ ስያሜዬ በይፋ ይታወቅ የጀመረው ግን በወያኔ ታስሬ በወህኒ ቤት ከቀድሞ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ከነበሩት ጓድ ፋሲካ ሲደልል ጋር አብረን አንድ ክፍል ውስጥ ታስረን ስለነበር፤ ያሳለፍኳቸውን ውጣ ውረዶች ሲሰሙ እውነትም አንተ አባ መላ ነህ ብለው በዚያው ስም ይጠሩኝ ጀመር። ከዚያ ወዲህ ብዙዎች በዚሁ ስያሜ ይጠሩኛል። በነገራችን ላይ ይህንን ጉዳይ በሚመለከት “የኢትዮጵያዊነቴ ትውስታ” በሚል ርዕስ ባሳተምኩት መፅሐፍ ላይ አስፍሬዋለሁ።
አዲስ ዘመን፡- በተሳተፉባቸው የጦርነት አውዶች ሁሉ የሚያጋጥሞትን ችግር በዘዴ በማለፍ ስኬታማ መሆን እንደቻሉ ይነሳል። ከእነዚህም መካከል በጎጃም ተነስቶ የነበረውን የባላባቶች አመፅን በዘዴ ማስቀረቶት ይጠቀሳል።እስቲ ያቺን አጋጣሚ ለአንባቢዎቼ ያስታውሱልኝ?
ሜጀር ጀኔራል መርዳሳ፡- ጊዜው ሚያዝያ 9 ቀን 1967 ዓ.ም ነው። የተወሰኑ መኮንኖችንና ምልምል ወታደሮችን ይዤ ወደ ጎጃም እንድሄድ ታዘዝኩኝ። በዚያኑ ቀን ሌሊቱን እነዚያን ወታደሮች ሳደራጅ ቆየሁኝ። በወቅቱ ታዲያ ፍኖተ ሰላም ላይ በመሬት አዋጅ ምክንያት ኢዲዩ የደርግ አባሎችንና ኤክስፐርቶችን እንዲሁም ጓድ ወርቅነህ መንገሻ በሙሉ በደፈጣ ውስጥ ሊደመስስ ስለሆነ ፈጥነህ ድረስላቸው ተባልኩኝ።በዚያን ጊዜ የኢዲዩ ሰዎች ከፍተኛ አመፅ በመቀስቀስ ከግምጃ ቤት መሳሪያ፤ ገንዘብም በመሰብሰብ ህዝቡን መበጥበጥ ጀምረው ነበር። ትዕዛዙን ተቀብዬ ስንጓዝ አድረን ጎሃፂዮን ላይ ልክ ከንጋቱ 12 ሰዓት ላይ ስደርስ ዕረፍት ለማድረግ ጉዟችንን ገታን። በዚያ ወቅት የተለያዩ ሰዎች በየቦታው ቁጭ ብለው ተመለከትኩና ሁለቱን ሰዎች ጠራሁና ምንድንነው? ብዬ ጠየኳቸው። ሰዎቹም «ሚስቶቻችን ፀሐይ ሳይወጣ ውሃ የሚቀዱ በመሆኑና በዚህ ጊዜ ፀጉረ ልውጦች እንዳይጎዳቸው በተራ እየጠበቅናቸው ነው» አሉኝ።
እግረመንገዴን ከአባይ ማዶ ምንአዲስ ነገር እንዳለ ጠየኳቸው። እነሱም ቀኛ አዝማች ስሜነህ ደስታ ህዝቡን እየቀሰቀሱ በደርግ መንግሥት ላይ ከፍተኛ ችግር እየፈጠሩ ስለመሆናቸው አስረዱኝ። ምክንያታቸውንም ስጠይቅ «ደርግ ዕርስታችንን ወሰደብን፤ ጠመንጃችንንና ሚስቶቻችንንም ሊወስድብን ነው፤ ሃይማኖትም የለውም፤ አረመኔ ነው፤ ይላሉ» ብለው ነገሩኝ። ይህን ከሰማን በኋላ ወታደሮቼን ይዤ ወደ ደጀን ዘለቅን።እዚያ እንደደረስንም ሰዎቹ ከነገሩኝ ችግሮች መካከል ደርግ ሃይማኖት የሚያጠፋ መንግሥት ነው የሚል ስለነበር ክር አስገዛሁኝና ከሙስሊም አባላት ውጪ እኔን ጨምሮ ሙሉ ጦሩ የክርስትና መገለጫ የሆነውን ክር እንዲያስሩ አደረኩኝ። በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ የፆም ወቅት ስለነበር ከያዝነው ምግብ ውስጥ የፍስግ ምግቦችን ቀን ቀን እንዳይበሉ ትዕዛዝ ሰጠሁኝ። ይህም ሙስሊሞችን አያካትትም ነበር። በተጨማሪ ዲያቆን የነበሩ ወታደሮች ዕሁድ ዕሁድ ቤተክርስቲያን ሄደው አገልግሎት እንዲሰጡ ፈቀድኩላቸው። ይህም ህብረተሰቡ ዘንድ የተፈጠረውን ሃይማኖት አጥፊ መንግሥት መጣብን የሚለውን አስተሳሰብ እንዲሸረሸር ትልቅ አስተዋፅኦ አበረከተልኝ።
ጅጋ የሚባል ስፍራ ስንደርስ ደግሞ እነዚያ የደርግ ሰዎች መባላቸውን ሰማን።እኛም ከፊት የተወሰነውን ኃይል ልከን ከኋላ አካባቢውን ኃይል ያዝን። 60 የሚሆኑትን ማረክናቸው። እነሱን ለማስፈታት ዋስ የመሆን ሰው እንዲያመጡ ነገርናቸውና ሰው ላኩ። እንደተባለውም ትላልቅ ሰዎች መጡና አነጋገሩኝና በዋስ ተፈቱ። በሌላ በኩል ከህብረተሰቡ ጋር እየተወያየን የተከበቡ ሰዎችን ለማስፈታት በምናደርገው ጥረት ውስጥ ሁሉም ወረዳ ነዋሪዎች ተስማምተው አሳ አንድ ኋሊት የሚባል ወረዳ ብቻ ያምፃል። ሶስቴም ተጠርቶ ቢጠየቅም አሸፈረኝ ይላል።በመሆኑም በወረዳው ያለውን ጦር እንድናስፈታ ትዕዛዝ ተሰጠን። እንዲያውም በወረዳው የሚኖሩ ህብረተሰቦች በእምቢተኝነታቸው ከፀኑ ዕርምጃ እንድንወስድ ተነገረን። ይህን ጊዜ በጣም ደነገጥኩኝ፤ እንዴት ከህዝብ ጋር እንጋጫለን ብዬ ተጨነቅኩኝ።
በጉዳዩ ላይ ብዙ ካሰብኩበት በኋላ እነዚህ ሰዎች በሰላም ጦራቸውን የሚፈቱበትን ዘዴ አገኘሁ። በወረዳውና በገበያው መካከል ያለ አንድ ኬላ እንዲዘጋ አደረኩና ያለንን መሳሪያ ሁሉ ፊት ለፊት እንዲቀመጥ አደረኩኝ። ሰዎቹን ደግሞ አንድ ከፍታ ቦታ ላይ እንዲቀመጡ አደረኩና ልጆቻቸው የያዙትን ኋላቀር መሳሪያ ካላስረከቡና ከእኛ ጋር ግጭት ውስጥ ከገቡ የያዝናቸው ዘመናዊ መሳሪያዎች ከፍተኛ ጉዳት ሊያደርሱባቸው እንደሚችሉ ገለፅኩላቸው። እኛ የያዝነው መሳሪያ በርካታ ጋሻ መሬት የሚያቃጥልና እህልም እንዳያበቅል የሚያደርግ መሆኑን አስረዳ ኋቸው። በመሆኑም ይህ ከመሆኑ በፊት የልጆቻቸውን ትጥቅ በሁለት ሰዓት ውስጥ አስፈትተው መንግሥትን ቶሎ ምህረት እንዲጠይቁ ነገርኳቸው። ሁለት ሰዓት ካለፋችሁ አገር የሚያጠፋና ጨለማን ወደ ብርሃን የሚለውጥ መሳሪያ እንደምተኩስባቸው ነገርኳቸው።እነሱ ግን ስላለመኑኝ በተቀጣጠርንበት ሰዓት አልመጡም።በመሆኑም ወደ ሰማይ ስድስት የሞርተር ጥይት ተኮስኩኝ። ያን ጊዜ እነዚያ ሰዎች የተባለው ነገር ደረሰ ብለው ቤተክርስቲያን ገብተው ደውል ደውሉና «ኡ …ኡ» አሉ። ታቦትም ተሸክመው መጡና ምህረት እንዲደረግላቸው ጠየቁኝ። እኔ ግን ምህረት መስጠት የእኔ ሥራ እንዳልሆነ ነገር ግን ጊዜ እንደምሰጣቸውና በአፋጣኝ የልጆቻቸውን ትጥቅ አስፈትተው እንዲያመጡ ነገርኳቸው። እናም በተባለው መሰረትም አንድም ጥይት ሳይተኮስ ትጥቅ አስፈታን።ይህ ክስተት በውትድርና ዘመኔ ከማልረሳቸው አስገራሚ ገጠመኞቼ አንዱ ነው።
አዲስ ዘመን ህዳር 26 ቀን 2013 ዓ.ም