ውብሸት ሰንደቁ
አንድ ሀገር የሚያድገው በዜጎቹ ትትርና፣ ቁርጠኝነትና ብቃት ነው። ዜጎች የታጠቁት ክህሎትና ዕውቀት ሲኖራቸው ለሀገር ዕድገት የየራሳቸውን ጠብታ ያበረክታሉ። በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ከሕዝብ ብዛታቸው አብዛኛው ወጣት በሆኑ ሀገራት ይህን ኃይል እንደመልካም ዕድል መጠቀም ይኖርባቸዋል። ይሄን ሃይል የስራ ዕድል ፈጥሮ የኢኮኖሚው አንቀሳቃሽ ማድረግ ካልተቻለ ነገሮች ይለወጡና ጉዞው የኋልዮሽ ይሆናል፤ የሀገር ዕድገትም ይሽመደመዳል፡፡
ኢትዮጵያም ከዚህ ዓለም አቀፋዊ ሃቅ አትሸሽምና በዘርፉ ሥራ ይከውንልኛል በተለይ ደግሞ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎችን ወደ ከፍተኛ ኢንዱስትሪነት ያሻግርኛል ፤አጣምሮም የወጣቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠር በሚደረገው ጥረት ክህሎትና ዕውቀት አስታጥቆ በጎ አስተዋፅዖ ያበረከትልኛል ያለቻቸውን ተቋም አቋቁማ ወደ ሥራ ገብታለች። ይህ ተቋም የፌዴራል አነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ማስፋፊያ ባለስልጣን ይሰኛል።
ይህ መሥሪያ ቤት የተማሩትንም ሆነ በትምህርቱ ብዙ ያልገፉ ወጣቶችን የተለያዩ ክህሎቶችን በማስታጠቅ ለሥራ አጥነት እንዳይዳረጉ ይታትራል፤ የተደራጁትንም በተለያዩ ማዕቀፎች ደግፎ ከአነስተኛ ወደ መካከለኛ፤ ከመካከለኛ ወደሚቀጥለው ደረጃ ያሸጋግራል፡፡
አቶ ሓዱሽ ሓለፎም የፌዴራል አነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ማስፋፊያ ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ናቸው። የሚመሩት የማኑፋክቸሪንግ የማስፈፀም አቅም ግንባታ ዘርፍን ነው። ይህ ዘርፍ አምስት ዳይሬክቶሬቶች ያሉት ሲሆን በነዚህ ዘርፎች የተለያዩ ተግባራትን ያከናውናል። የሥራ ዕድል ፈጠራ ኢንተርፕሪነር ሺፕ፤ ኢንኩቤሽን፣ የመረጃና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ እና የመሳሰሉት ሥራዎች የሚከናወኑት በዚህ ክፍል ነው። ከነዚህም በተጨማሪ የአካባቢ ጥበቃና ኢነርጂ አጠቃቀም ዳይሬክቶሬት በሥሩ ተካትቶ ኢንዱስትሪ እና ኢንቫይሮሜንት እንዴት እየሄደ እንዳለ ትኩረት ተሰጥቶ የሚሠራበት ሌላው ዘርፍ ነው። ይህ የሚደረገውም በዋነኛነት ኢንዱስትሪው አካባቢን ሊጠብቅ የሚችል መሆን አለበት ከሚል እሳቤ ነው። ሌላው ደግሞ የጥናትና ሥልጠና የማስፈፀም አቅም ግንባታ ነው። በዚህ ዘርፍ የኢንዱስትሪ ማእቀፎችን ለዩኒቨርሲቲዎች፣ ለክልሎች፣ ለሙያተኞችና በዘርፉ ለተሠማሩ ኢንተርፕራይዞች እና በየደረጃው ላሉ አመራሮች ስለዘርፉ በቂ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ይደረጋል።
የባለስልጣኑ ዋና ትኩረት አነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸረሮች በተገቢው መንገድ በመደገፍ ወደቀጣዩ ደረጃ እንዲያድጉ ማስቻል ነው። ለዚህም ሲባል አሥር የድጋፍ ማዕቀፎች በንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አማካኝነት ፀድቆ ወደሥራ ገብቷል። እነዚህ ማእቀፎች በዋናነት የተዘጋጁት ኢንዱስትሪውን እንዲደግፉት ታስቦ ነው። ለምሳሌ ያህል የክላስተር ማዕከላት አደረጃጀትን በተመለከተ፤ ከሊዝ ፋይናንሲንግ ጋር የተያያዘ እና ሌሎችም ይገኛሉ። በነዚህና በሌሎች ማዕቀፎች በዘርፉ ግንዛቤ የሌላቸው ነገር ግን ፍላጎቱ ያላቸው አነስተኛና መካከለኛ አንቀሳቃሾች ግንዛቤ ተፈጥሮላቸውና ነገሮች ተመቻችተውላቸው ዘርፉን እንዲቀላቀሉ ይደረጋል። በተጨማሪም ሽግግር ላይ የሚሠራ ማዕቀፍ አለ። በዚህ ማዕቀፍ ከአነስተኛ ወደ መካከለኛ፤ ከመካከለኛ ወደ ከፍተኛ የሚሸጋገሩት እንዴት መሸጋገር እንዳለባቸው እና ምን ማሟላት እንደሚጠበቅባቸው መሥፈርቶችን በማጣቀስ ሽግግር እንዲያደርጉ የሚረዳ ነው። ገበያ ላይ የሚያተኩር ማዕቀፍም ተቀምሮ ከማኑፋክቸሪንጎች የገበያ ትስስር ጋር ተያይዞ የሀገር ውስጥም ሆነ ከሀገር ውጪ ያለ ገበያ ላይ ሥራዎች ይሠራሉ። ከማስተዋወቅና ከተሞክሮ ቅመራ ጋር እንዲሁም ከአካባቢ ጥበቃና ኢነርጂ አጠቃቀም ጋር የተያያዙ ሌሎች ማዕቀፎች አሉ።
ማዕቀፎቹ መተግበር ከጀመሩ ጥቂት ዓመታትን አስቆጥረዋል። ተቋሙ ከዚህ በፊት ጥቃቅን እና አነስተኛ የሚባል በመሆኑና በፊት የነበረው አሠራር መካከለኛ የሚባሉትን ማኑፋክቸሪንጎችን ያካተተ ባለመሆኑ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እነዚህ መካከለኛ ማኑፋክቸሪንጎች ተካትተው አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ላይ ትኩረት ሰጥቶ የሚሠራ ተቋም እንዲሆን ተደርጓል። ይህ የሆነው እያንዳንዱ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ባለው የካፒታል መጠን፣ የሰው ኃይልና በመሳሰሉት መመዘኛዎች አነስተኛ፣ መካከለኛ ወይም ከፍተኛ መሆኑን የሚያሳይ በግልፅ የተቀመጠ እና የማያምታታ አሠራር ለመዘርጋትና በሽግግር ላይ ጠንክሮ ለመሥራት ነው። በነበረው አሠራር አነስተኛ የሚባሉት ኢንተርፕራይዞች የካፒታል መጠናቸው ከ 101 ሺህ እስከ 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ካፒታል ያላቸው፤ መካከለኛ የሚባሉት ደግሞ ከ1 ነጥብ 51 እስከ 20 ሚሊዮን ካፒታል ያላቸው ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎች ናቸው።በሰው ኃይል ረገድም ከስድስት እስከ 30 የሰው ኃይል ያላቸው ከአነስተኛ የሚመደቡ ሲሆኑ ከ31 እስከ 100 የሰው ኃይል ያላቸው ደግሞ መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎች ይባላሉ። በእርግጥ ይህ የካፒታል መጠንና ትርጓሜ በሚመለከተው አካል ተጠንቶ እየተሻሻለ የሚገኝ ነው፡፡
ግንዛቤ ለማስጨበጥ በማዕቀፎቹ ዙሪያ ለሁሉም ክልሎች ሥልጠና መሰጠቱን ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ይጠቅሳሉ። በዚህ ምክንያት የነበረውን የአሠራር ክፍተት ለማስተካከል ተችሏል። በየደረጃው ያሉ አካላት በዘርፉ እንዴት መደራጀት እንደሚቻል፤ የመሥሪያ ካፒታልና ብድሮች እንዴት እንደሚገኙ፤ ቢዝነስ ፕላን እንዴት መሠራት እንዳለበት፤ ከልማት ባንክ የተፈለገውን ብድርና ትብብር ለማግኘት ምን መሥፈርቶች መሟላት እንዳለባቸው፤ ብድሩ በምን መንገድ እንደሚመለስ፤ የሽግግር መመሪያዎች እንዴት መፈፀም እንዳለባቸው እና በመሳሰሉት ጉዳዮች ላይ የተሻለ ግንዛቤ ተፈጥሯል።
ባለሥልጣኑ በዋናነት የሚደግፋቸው በማኑፋክቸሪንግ ላይ የተሰማሩ የህብረተሰብ ክፍሎችን ነው።ሁሉም ተመሳሳይ ግንዛቤ አግኝተዋል ማለት ባይቻልም በተለይ በዘርፉ ላይ የሚሠሩ ባለሙያዎች በቂ ግንዛቤ እንዲጨብጡ ተደርጓል። በሁሉም ክልል ከተሞችና የዞን ከተሞች ላይ የሚገኙ ባለሙያዎች በቂ ሥልጠና ወስደው ምሥክር ወረቀት ተሰጥቷቸው የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪውን እንዲደግፉ ጥረት ተደርጓል ብለዋል።
አቶ ሓዱሽ እንደሚሉት በሀገራችን በአሁኑ ወቅት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ ያለው ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪው ላይ ነው።አነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንጎች የኢንዱስትሪ መሠረት ናቸው። ሌሎች ያደጉ ሀገራትም ከነዚህ ዓይነት ማኑፋክቸሪንጎች ተነስተው ነው ወደ ትላልቅ ኢንዱስትሪዎች የገቡት።ስለዚህም ነው እነዚህ የድጋፍ ማዕቀፎች ተዘጋጅተው ኢንዱስትሪውን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማምጣት ጥረት እየተደረገ ነው የሚገኘው። ኢንዱስትሪውን ለመደገፍ መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ነው ያለው።
በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍ በተደረገ ጥረት በማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪው ላይ ያሉ የአደረጃጀትና ሌሎች ችግሮች፤ በኤክስፖርቱ ዘርፍ እያጋጠማቸው ስላለ ችግር፤ ከብድር አሰጣጥ አኳያ ያሉ መሰናክሎች፤ የገበያ ትሥሥር በመፍጠር ረገድ ባሉ ድክመቶች ዙሪያ ጥናቶች ተጠንተዋል። ጥናቶችን መሠረት ተደርጎ የተለያዩ ሥራዎች እየተሠሩ ነው ያሉት። በዘርፉ የነበረው የአነስተኛና መካከለኛ ትርጓሜ (አረዳድ) አንዱ ችግር እንደነበር አስታውሰዋል። በዚያ ላይ በአነስተኛም ይሁን በመካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ላይ እንደመሥፈርት የተቀመጠው የገንዘብ መጠን ቀደም ብሎ በመጠናቱና በሌሎች ምክንያቶች የካፒታል መጠኑ ሊያሠራ የማይችል ሆኖ ተገኝቷል። ይህ የካፒታል መጠን እንዲስተካከል ጥናቱ ተጠንቶ የተስተዋለው ችግር እንዲቀረፍ ወደሚመለከተው አካል እንዲቀርብ በዝግጅት ላይ ይገኛል። በዚህም የመካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎች የካፒታል መጠን ከ 1 ነጥብ 5 ወደ 4 ሚሊዮን ከፍ እንደሚል ይጠበቃል። በተጨማሪም ተቀናጅቶ የመሥራት ክፍተት ታይቶ ነበር። ይህንንም የሚመለከታቸው አካላት በሚኒስቴር ደረጃ ያሉና ሚኒስቴር ዴኤታዎች በተገኙበት የጋራ ውይይት በማድረግ መሥመር እንዲይዝ ተደርጓል። ከግብዓት አቅርቦት አኳያ የሚከሰቱ ችግሮችን ለመፍታት ሥራዎች ተጀምረው በሂደት ላይ ይገኛሉ።
ባለሥልጣኑ በሀገሪቱ እስከታች ባሉ ክፍሎች አደረጃጀት አለው። በዚህም ክልሎችን የመደገፍ፣ የመከታተልና የመቆጣጠር ኃላፊነት ተሰጥቶታል። ተቋሙ ቢያንስ በየሩብ ዓመቱ መደበኛ ግንኙነት ያደርጋል ያሉት አቶ ሓዱሽ በአሁኑ ወቅት ዲጂታላይዝድ በሆነ ሁኔታ ሁሉንም መረጃዎቻቸውን አካተው የያዟቸው ከ19 ሺህ በላይ ኢንዱስትሪዎች በሀገር ደረጃ እንዳሉ ገልጸዋል።በእርግጥ እነዚህ መረጃ አደራጅተው የያዟቸው እንጂ ቁጥራቸው ከዚያ በላይ ነው። ከነዚህ ውስጥም ከ15 ሺህ በላይ የሚሆኑት አነስተኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎች ሲሆኑ ወደ ሶስት ሺህ አካባቢ የሚሆኑት ደግሞ መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎች ናቸው። እነዚህን ወደተሻለ ደረጃ ለማድረስ አመራሩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየተገናኘ ተገቢውን ድጋፍና ክትትል በማድረግ ላይ መሆኑንም ይናገራሉ።
የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎች ምቹ ሁኔታ ተፈጥሮላቸው ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ማድረግ ዋና ተግባራችን ነው ያሉት አቶ ሓዱሽ በርግጥ የተቋሙ ራዕይም በ2017 በአፍሪካ ቀዳሚ የሆነና በዓለም ተወዳዳሪ የሆነ ኢንዱስትሪ መፍጠር ስለሆነ እዚያ ላይ ትኩረት ሰጥተን እየሠራን ነው ብለዋል። አክለውም የበለፀገ፣ ያደገ፣ ተወዳዳሪ ሊሆን የሚችልና የሚያመርተው ምርትም ጥራቱን የጠበቀ አምራች ኢንዱስትሪ እንዲፈጠርና ያሉት ችግሮች ተፈተው ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪውን ወደ ላቀ ደረጃ ለማምጣት ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር እየተሠራ ነው ብለዋል።
ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ እንዳሉት የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ በጣም ወሳኝና አስፈላጊ ነው። ምክንያቱም ኢንዱስትሪው እያደገ በሄደ ቁጥር ምርቶችን በሀገር ውስጥ የመተካትና ኤክስፖርት እያደገ ስለሚሄድ ነው።በዚያው መጠንም የሀገሪቱ ኢኮኖሚ እያደገና እየበለፀገ ይሄዳል ማለት ነው። ዘርፎቹ ተመጋጋቢ በመሆናቸው የተነሳ የኢንዱስትሪው ማደግ ግብርናውን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማምጣት ጉልህ አስተዋፅዖ አለው።
በተቋሙ ከክፍያ ነፃ የሆኑ ለዜጎች የሚበጁ በርካታ ሥልጠናዎች ይሰጣል። የጨርቃ ጨርቅ፣ የቆዳና የቆዳ ውጤቶች፣ በጌጣጌጥ፣ በሚስማር ምርት፣ በአጥር ሽቦ፣ በሥጋጃና በቀርከሃ ሥራ፣ በልብስ ስፌት፣ በሸክላ ፣ በካልሲ ምርት እና በመሳሰሉት ሙያዎች ሥልጠናዎች ይሰጣሉ። ይህም የሚደረገው አነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎች ለሀገሪቱ ዋነኛ የውጭ ምንዛሬና የሀብት ምንጭ ሆነው ትላልቅ ኢንዱስትሪዎች ጋር ሊደርሱ የሚችሉበት መንገድ ለመፍጠር ታልሞ ነው።ተቋሙ ለብዙ ወጣቶች የሥራ ዕድል ያገኙ ዘንድ በነፃ ሥልጠና የሚሠጥና እየሠጠም የሚገኝ ነው። ወጣቶች ወደተቋሙ ሄደው ሥልጠና ቢወስዱ አንደኛ በሠለጠኑበት ሙያ ተደራጅተው መሥራት ይችላሉ ፤ ያም ካልሆነ ደግሞ ተፈላጊ ሙያዎች ላይ ሥልጠና ስለሚወስዱ በሌሎች ኢንዱስትሪዎች ላይ የመቀጠር ዕድሉ የሰፋ ይሆናል። በኮቪድ ምክንያት አንዱ የተጎዳው ማኑፋክቸሪንግ ላይ የተሠማራው የህብረተሰብ ክፍል በመሆኑ ምክንያት የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ከመጣ በኋላ በተለይ ለማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ ትኩረት ተሰጥቶታል፡፡
ኢንዱስትሪን የተሻለ ደረጃ ላይ ማድረስ በአንድ ተቋም ብቻ የሚወሰን ነገር አይደለም። የብዙ ተቋሞች ቅንጅታዊ አሠራር ወሳኝ ነው። ብድር መስጠት፣ ግብዓት ማቅረብ፣ ሥልጠና መስጠትና እና ሌሎች በርካታ ተግባራት የሚከናወነው በየተለያዩ ዘርፎች በመሆኑ ዓላማውን ማሳካት የሚቻለውም በቅንጅት በመሥራት ነው።
የመፈፀምና የማስፈፀም አቅም ግንባታን ወደተሻለ ደረጃ ማምጣት ዋናው ቁልፍ ተግባራችን ነው ያሉት አቶ ሓዱሽ አቅም መገንባት ሲባል ብዙ ነገሮችን ያቀፈ ነው። በገንዘብ፣ በቴክኖሎጂ፣ በግብዓት እና በሌሎችም ዘርፎች የመፈፀም አቅም ሊያድግ ይገባል።ሥልጠና ግብ ሊሆን አይችልም፤ ግብ ሊሆን የሚችለው የሠለጠነው የሰው ኃይል ሊሠራበት የሚችል ሁኔታ ተፈጥሮለት ወደሥራ ሲገባ ነው። ይህ ብቻ ሳይሆን በሥራ ላይም ተከታታይ የሆነ ድጋፍና ክትትል የሚጠይቅ ነው። አነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ በስማ በለው ሊመራና ሊያድግ የሚችል ዘርፍ አይደለም፤ በውስጡ የተገነባና በዕውቀት የሚመራ አካል ይፈልጋል ብለዋል።
በዘርፉ በዋናነት የሚነሱትን ተግዳሮት ሥልጠናዎችን እስከ ታች አለማውረድ፤ ሥልጠናዎቹን ወደ ተግባር መቀየር አለመቻል፤ የፋይናንስ አቅርቦት ውስንነት መኖር፤ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ናቸው። ስለዚህ በማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ ላይ ሁሉም ጉዳዩ የሚመለከተው አካል በርብርብ መሥራት ይኖርበታል። ከልማት ጋር ያለው የማሽነሪ እና የብድር አቅርቦት ፈጣን አገልግሎት ከመስጠት አኳያ የሚታዩ ውስንነቶች መቀረፍ ይኖርባቸዋል ሲሉ አሳስበዋል።
አዲስ ዘመን ህዳር 25 ቀን 2013 ዓ.ም