በጋዜጣው ሪፖርተር
ሰሜን አፍሪካዊቷ አገር ግብጽ ባለፉት ጥቅምትና ኅዳር ወራት ብቻ 57 ሰዎችን በስቅላት ቀጥታለች። ከዚህ ጋር በተያያዘ ግብጽ በሞት የምትቀጣቸው ፍርደኞች ብዛት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በከፍተኛ ሁኔታ እያሻቀበ መሄዱን አምንስቲ ኢንተርናሽናል ገልጿል።
ቢቢሲ እንደዘገበው፣ የሰሜን አፍሪካዊቷ አገር ግብጽ ባለፉት ጥቅምትና ኅዳር ወራት ብቻ 57 ሰዎችን በስቅላት ቀጥታለች። ይህም በፈረንጆች 2019 በስቅላት ከተቀጡ ጠቅላላ ሰዎች እጥፍ በ2 ወራት ብቻ መፈጸሙን ያሳያል። በዚህም በግብጽ በሞት የሚቀጡ ፍርደኞች ቁጥር እያሻቀበ መምጣቱን አምንስቲ ኢንተርናሽናል ዘግቧል፡፡ በአምንስቲ ዘገባ ላይ ግን ግብጽ ያለችው ነገር የለም።
አምንስቲ ባለፈው ወር ባወጣው አንድ ሪፖርት፣ በግብጽ የሰብአዊ መብት አያያዝ ማሽቆልቆል ላይ የሰላ ትችት ሰንዝሮ ነበር። የሰብአዊ መብት ተሟጋቹ አምንስቲ እንደሚለው በቁጥር በርከት ያሉ ተቃዋሚዎች እና የመብት ተቆርቋሪዎች በግብጽ ብዙ ውጣ ውረድ እየደረሰባቸው ነው።
በዚህም ግማሾቹ የታሰሩ ሲሆን፣ ቀሪዎች ደግሞ ከአገር እንዳ ይወጡ ተደርገዋል። አንዳንዶቹ ደግሞ በአልሲሲ መንግሥት ሀብትና ንብረታቸው እንዳይንቀሳቀስ ተወ ስኖባቸዋል። የአምንስቲ ጥንቅር እንደሚያስረዳው በግብጽ በስቅላት የሚቀጡ ሰዎች ቁጥር በአንድ ጊዜ ማሻቀብ የጀመረው በካይሮ እጅግ ጥብቅ እንደሆነ ከሚነገርለት ከቶራ እስር ቤት ፍርደኞች ለማምለጥ ከሞከሩ ወዲህ ነው። በዚህም ከእስር ቤት ለማምለጥ ሞክረው በርካታ የሞት ፍርደኞችና ፖሊሶች መሞታቸው አይዘነጋም።
ግብጽ በቅርብ ሳምንታት ውስጥ በሰብአዊ መብት ድርጅቶች የሚሰሩ በርከት ያሉ ዜጎቿን በማሰሯ ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብና ከመብት ተሟጋቾች ዘንድ ከፍ ያለ ወቀሳ ሲቀርብባት ከርሟል። የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ግን ሕግን የማስከበር እርምጃ ተወሰደ እንጂ ሌላ የሆነ ነገር የለም ይላሉ።
አልሲሲ፣ በዲሞክራሲያዊ መንገድ ሥልጣን ላይ የወጡትን ሟቹን መሐመድ ሙርሲን በመፈንቅለ መንግሥት ከጣሉ በኋላ በ2013 ወደ ሥልጣን የመጡ ሲሆን፤ በአብላጫ ድምጽ ወደ ሥልጣን መጥተው የነበሩት ሙሐመድ ሙርሲ ግን በእስር ቤት ሳሉ ታመው ብዙም ግልጽ ባልሆነ ሁኔታ መሞታቸው ይታወሳል::
አዲስ ዘመን ህዳር 25 ቀን 2013 ዓ.ም