
ሞገስ ፀጋዬ
አዲስ አበባ፡- የህዋሓት ጁንታ ላለፉት 27 ዓመታት የራሱን ድርጅቶች አላግባብ እንዲፈረጥሙ፤ ሌሎችን ደግሞ አላግባብ እንዲቀጭጩ ሲያደርግ እንደነበር የኢኮኖሚክስ ባለሙያው ዶክተር ዳዊት ሀየሶ አስታወቁ። በዚህም በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ የከፋ የሚባል ችግር መፍጠሩን ጠቆሙ።
በዲላ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ መምህር የሆኑት ዶክተር ዳዊት ሀየሶ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፣ ባለፉት 27 ዓመታት የሀገሪቷን ሀብት ከመጠቀም አንጻር ፍትሐዊነት አልነበረም። ጁንታው ባልተገባ መልኩ የራሱን ድርጅቶች ፈርጣማ እንዲሆኑ አድርጓል። ፍትሐዊ ባለሆነ የገበያ ውድድር የግል ድርጅቶች ከንግድ ስርዓቱ እንዲወጡና ጤናማ ያልሆነ ገበያ ስርዓት እንዲፈጠር አድርጓል።
በጁንታው የንግድ ስርዓቱም እድገቱም ፍትሐዊ እንዳይሆን ተደርጓል የሚሉት ዶክተሩ፣ የሀገሪቱን ሀብት አጠቃቀም ለቡድኑ ያጋደለ ስለነበር ፍትሐዊ አልነበረም ብለዋል። ይህም ከባድ የሚባል ኪሳራን በሀገር ኢኮኖሚ ላይ ማድረሱን አመልክተዋል።
በፖለቲካ ድርጅት የተያዙ የንግድ ተቋማት መኖራቸው የግል ድርጅቶች ላይ አሉታዊ ተጽእኖ እንዳለው ያመለከቱት ዶክተሩ ፣ ይህ ደግሞ ሀገሪቷን ከእድገት ብዙ ዕርምጃ ወደ ኋላ እንደጎተታት ገልጸዋል። በተለይ የግል ሴክተሩን እንደገደለው ጠቁመዋል።
ለማንኛውም ከውጭ ለሚመጣ እቃ ለጁንታው የፓርቲ ድርጅቶች ኃላፊነት በመስጠትና እንዲያሰራጭ በማድረግ ኢፍትሐዊ በሆነ መንገድ ሀብት ሲያካብቱ ቆይተዋል። የግል ድርጅቶች ተወዳድረው አትራፊ እንዳይሆኑ፣ እንዳይጠቀሙና ፍትሐዊነት እንዳይኖር በማድረግ የሀገር ኢኮኖሚን ክፉኛ ሲጎዱት መቆየታቸውን ገልጸዋል።
ጁንታው ለራሱ ድርጅቶች የተሻለ የመጫወቻ ሜዳ በማመቻቸት ራሱ ተጫዋችና ዳኛ ሆኖ የንግዱን ስርዓት ጤናማ እንዳይሆን ማድረጉን ያመለከቱት ዶክተር ዳዊት፣ በዚህ ምክንትም ከነጋዴው ባልተናነሰ ደሃውን ህዝብ ሲጎዳው ነበር ብለዋል።
መንግሥት አገልግሎት በማቅረብ አምራቹንና ሸማቹን ማገናኘት ሲገባው ጣልቃ በመግባት የንግድ ስርዓቱን ሲረብሽ ነበር የሚሉት ባለሙያው፣ የንግድ ስርዓቱ ቅርቃር ውስጥ ገብቶ መውጣት እንዲያቅተው የሆነው መንግሥት በአንድ በኩል ነጋዴ፤ በሌላ በኩል ደግሞ ለንግዱ ማህበረሰብ ምቹ ሁኔታን የማያመቻች አካል በመሆኑ እንደሆነ ጠቁመዋል።
ይህ ሁኔታ ደግሞ ጤናማ የሆነ የኢኮኖሚ ስርዓት ከመገንባት አንጻር ሲታይ መንግሥት ነጋዴ መሆን የለበትም ብለዋል። ባለፉት 27 ዓመታት ጁንታው የሚያወጣቸው ህጎች ሁሉ የራሱን ድርጅቶች ብቻ ተጠቃሚ የሚያደርግ ነበር። በቀኝ እጅ እየነገደ በግራ እጁ ህግ የሚያወጣ ስለነበረ ተወዳዳሪነትን የሚያበረታታም አልነበረም ብለዋል። ጁንታው እንደ መንግሥት ራሱ አበዳሪ ራሱ ተበዳሪ በመሆን የራሱ ድርጅቶች ብድር አላግባብ እንዲያገኙ በማድረግ ከልክ በላይ የፈረጠሙ የራሱን ድርጅቶች ፈጥሯል ሲሉ ገልጸዋል።
አዲስ ዘመን ህዳር 25 ቀን 2013 ዓ.ም