የተወለዱት እና እስከ ስምንተኛ ክፍል ድረስ የተማሩት ጎንደር ነው።በመጀመሪያ ደብረሰላም አንደኛ ደረጃ ት/ቤት ቀጥለውም ፋሲለደስ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መማር ጀምረው በመሀል ላይ በጊዜው የተማሪዎች ረብሻ ስለነበር በቤተሰብ ዝውውር ወደ አዲስ አበባ መጡ።ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት እስከ 12ኛ ተምረው በኋላም አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በመግባት በአርክቴክቸርና የከተማ ፕላን ትምህርታቸውን በማጠናቀቅ በዲግሪ ተመረቁ፤ የዛሬ እንግዳችን ተባባሪ ፕሮፌሰርና አርክቴክት ፋሲል ጊዮርጊስ፡፡
መሀል ጎንደር መወለዳቸው በአርክቴክቸር ሙያ ላይ ተጽእኖ እንዳሳደረባቸው ይናገራሉ።የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከያዙ በኋላ በረዳት መምህርነት በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ አስተምረዋል።በትርፍ ጊዜያቸውም በተለያዩ ቢሮዎችም ሰርተዋል፡
በመቀጠል ፊንላንድ ሀገር የትምህርት እድል አግኝተው ሄልሲንኪ ዩኒቨርስቲ በመግባት በማስተርስ ዲግሪ ተመርቀዋል።በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በአርክቴክቸርና የከተማ ፕላን ክፍል በተባባሪ ፕሮፌሰርነት እየሰሩ ይገኛሉ።በርካታ የኪነ ሕንጻ ተማሪዎችን ያስመረቁ ቀደምት የሙያው ባለቤት ናቸው።በኢትዮጵያ ጥንታዊ ኪነ ሕንጻና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ከአዲስ ዘመን ጋር ያደረጉትን ቆይታ ይዘን ቀርበናል ።ይከታተሉት
አዲስ ዘመን፡-የውጭ ትምህርትዎን ጨርሰው ወደ ሀገር ቤት ከተመለሱ በኋላ ያለውን ቢገልጹልን ?
አርክቴክት ፋሲል (ተባባሪ ፕሮፌሰር)፡- በመምህርነት ተመልሼ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ቀጠልኩ።ብዙ አመታት አስተምሬአለሁ፡፡የረዥም ጊዜ ፍላጎቴ በኢትዮጵያ ታሪካዊ ሕንጻዎች ላይ ትኩረት ሰጥቶ ጥናትና ምርምር ማድረግ ነበር። በዚህ መስክ ጥናት አድርጎ ለየት አድርጎ የሚያስተምር ተቋም በሀገራችን ብዙ የለም።ስለዚህ አብዛኛውን ጊዜ በምርምርና በጥናት በግል ጥረቴ ነው ለመማር የሞከርኩት።በማስተማር ብዙ ረዥም ጊዜ ስለቆየሁ አሁን በተባባሪ ፕሮፌሰርነት አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ አርክቴክቸርና ከተማ ፕላን የሚያስተምርበት ማለት ነው የራሴን አንድ የትምህርት ክፍል የከተማና የሕንጻ ጥገና ትምህርት የሚባል የማስትሬት ፕሮግራም ከፍቼአለሁ።ሁለተኛ ደረጃ ዲግሪ እያስተማርን ነው።መንግስት ባለፉት አመታት ከዩኒቨርስቲ መስፋፋት ጋር በየሙያው አዳዲስና ለሀገሪቱ አስፈላጊ የሆኑ መስኮች ክፈቱ ባለው መሰረት እኛም ፍላጎት ነበረንና የሀገር ውስጥም የውጭም ባለሙያ መምህራንን ሰብስበን እኔ ራሴ የምመራው የማስትሬት የትምህርት ፕሮግራም ጀምረናል፡፡
አዲስ ዘመን፤- የትምህርት ክፍሉ ምን ያህል ጊዜ ሆነው? ስንቴስ አስመረቀ ?
አርክቴክት ፋሲል፡- ስድስት አመት ሆነው።ሶስት ዙር ወደ 12 ተማሪዎች ገደማ አስመርቀናል።በሂደት ላይ ያሉም አሉ። ዘንድሮ በኮቪድ ምክንያት ያልጨረሱ ወደ 10 የሚሆኑ ልጆች አሉ።በየዩኒቨርስቲውና በየክልሎች የእኛ ምሩቆች እየሄዱ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ተማሪዎቹ ከተመረቁ በኋላ ምን ላይ ነው የሚሰሩት ?
አርክቴክት ፋሲል፡- በየክልሉ ባሉት ታሪካዊ ሕንጻዎች ላይ ምርምር ያደርጋሉ። ባህል ቢሮዎች ለምሳሌ ቅርስ ጥናትና ጥበቃ ውስጥ የሚሰሩ አሉ።በየዩኒቨርስቲዎችም ውስጥ አሉ።እስከአሁን በዛ አካባቢ የነበረውን ክፍተት ለመሙላት እየሞከርን ነው። ድሮ ፈረንጆች ነበሩ ስለእኛ የሚጽፉልን።
አዲስ ዘመን፡-በሙያዎት የት የት ሰርተዋል?
አርክቴክት ፋሲል ፡- መጀመሪያ ስራ የጀመርኩት አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ነው።በግራአዱኤት አሲስታንት (በረዳት መምህርነት)።በተመሳሳይ ጊዜ ደግሞ አፍሪ ኮንሰልት የሚባል የአርክቴክት ቢሮ በትርፍ ጊዜ እሰራ ነበር።በዩኒቨርስቲ ደረጃ ያለው እውቀት ቲዮሪ (ንድፈ ሀሳብ ) ነው።ሙያው ተግባራዊ ልምምድ ማድረግ ያስፈልገዋል።ተግባራዊ የሆነውን ደግሞ ባለችኝ ትርፍ ጊዜ እዛ አስራ ነበር።በትርፍ ሰአት በተለያዩ የግል ቢሮዎችና ከአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤትም ጋር ሰርቻለሁ፡፡
አዲስ ዘመን ፡- ሌሎች ቦታዎችስ ?
አርክቴክት ፋሲል፡- አፍሪ ኮንሰልት፤ ናሽናል ኮንሰልት (የግል)፤ ናሽናል ኢንጂነርስ፤ ከዛ በኋላ ደግሞ የአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት በተለይ ድሮ የውጭ ሀገር ኤክስፐርቶች መጥተው በሚሰሩ ጊዜ በሀገር ቤት በኩል ባለው እንደ ባለሙያ ኤክስፐርት ሰርቻለሁ።በተለይ ደግሞ በኮሚቴና በጥናት ደረጃ የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ክለሳ ጥናት ላይ ነበርኩ።ከአዲስ አበባ የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ጋር የተለያዩ ፕሮጀክቶችን ሰርቼአለሁ።ከሁለት አመት በላይ የኢትዮጵያ ባህል ጥናት ፕሮጀክት የሚባል የዛ ቡድን መሪ ሆኜ አክሱም ላይ ሰርቼአለሁ፡፡
አዲስ ዘመን፡-ምንድን ነበር የምታጠኑት ?
አርክቴክት ፋሲል፡- የኢትዮጵያ መንግስት ከአለም ባንክ ብድር ወስዶ አክሱም ጎንደርና ሀረር ላይ የተለያዩ ቅርሶችን የማደስ ለቱሪስቶች አመቺ እንዲሆኑ የማድረግ ስራ ነው ስንሰራ የነበረው። አብዛኛውን የጎንደሩንና የሀረሩን ስራ የሚመሩት ፈረንጆች ነበሩ።በሆነ አጋጣሚ ይሄንን ቡድን የሚመራው ኢትዮጵያዊ መሆን አለበት የሚል ነገር ተወሰነ።ከዚህ በፊት የነበሩትን ተመሳሳይ ጥናቶች በሙሉ የሚመሩት ፈረንጆች ናቸው።
ፕሮጀክቶች የተግባር ስራዎች ናቸው፡፡ፕሮጀክቱም የሚመራው በኢትዮጵያዊ መሆን አለበት የሚል ውሳኔ ተላለፈ።ለእዚህ የሚመጥን ሰው ሲፈለግ የእኔ ልምድ በአጋጣሚ ከስራው ጋር የተዛመደ ሆነ።በዚህ ምክንያት የቡድን መሪ ሆኜ ተመረጥኩ።በስሬ ከ8 ሀገር በላይ የውጭ ሀገር ዜጎች ነበሩ።የእንግሊዝ፤ የጣሊያንና የተወሰነ ጊዜም አሜሪካኖች ነበሩ። በተለይ እንግሊዝና ጣሊያኖች ይበዙ ነበር።ሌሎችም ነበሩ። አርኪዮሎጂስቶች፤ የቅርስ ጥበቃ ባለሙያዎች፤ እነዚህን ሰዎች ይዘን ነበር የምንሰራው።ፕሮጀክቱን ሲቀርጹ ያንን ማለታቸው ተገቢ ውሳኔ ይመስለኛል።ሌሎቹንም ፕሮጀክቶች ኢትዮጵያውያን ይምሩ ቢሉ ጥሩ ነበር።
አዲስ ዘመን፡-ምን ምን ሰራችሁ ?
አርክቴክት ፋሲል፡- አክሱም ሄዳችሁ ስትጎበኙ ካያችሁት ከሀውልቱ ስር ያለውን መቃብር እኛ ነን የከፈትነው።ሀውልቱ ስር አስር የመቃብር ቦታ ያለው የቀብር ስፍራ አለ።እንደሚባለው ከሆነ በሶስተኛውና በአራተኛው ክፍለዘመን የተቀበሩ ናቸው።
አዲስ ዘመን፡-እንዴት አገኛችሁት ?
አርክቴክት ፋሲል፡- አርኪዮሎጂስቶች ናቸው ያገኙት።በእኛ አቆጣጠር በ1965 ዓ.ም ነው።ቺቲክና ዴቪድ ፊሊፕሰን የሚባሉ እንግሊዛውያን ቆፍረው ካገኙት በኋላ ደፋፍነውት ሄዱ።ሲሄዱ ሪፖርታቸውን ጽፈው ነው የሚሄዱት።ያ መረጃ ነበረ።እንደሚታወቀው እንዲህ አይነት የቅርስ ቦታዎች ላይ አርኪዮሎጂስቶች ግኝቱን ያገኙና ሪፖርት አድርገው ይሄዳሉ። የእኛ ስራ ግን ቅርስን ለጎብኚ በሚመች መልኩ ማቅረብ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ምን አደረጋችሁ ?
አርክቴክት ፋሲል፡- እኛ ያደረግነው የመቃብር ቦታዎቹን ታሪካዊ ፍረስራሾች ስርአት አስይዘን የሚፈርሱትም እንዳይፈርሱ በቅርስ ጥበቃ እውቀት መሰረት ድንጋዮቹን አስተካክለን ግምቦቹን በደምብ ገንብተን ፍርስራሾቹን እየሞላን ሰራነው።አሁን ሰው ሲያየው ድሮ የነበረና እንደዚህ የነበረ ነው የሚመስለው።ከ1996 ዓ.ም አስከ 1998 ዓ.ም ድረስ ነው የሰራነው።ከዩኒቨርስቲ ተፈቅዶልኝ በሙሉ ጊዜ ነው የሰራሁት።ስራው ከ2 አመት ተኩል በላይ ፈጅቷል።
አዲስ ዘመን፡– ከነዚህ ውጪ የሰሯቸው የኪነ ሕንጻ ስራዎች አሉ ?
አርክቴክት ፋሲል፡- ብዙ ሕንጻዎች አሉ።ለምሳሌ ያህል የቀይ ሽብር ሰማእታት ሀውልት ዋናው አርክቴክት እኔ ነኝ።አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የኢትዮጵያ ጥናት ቤተመጽሐፍት በቅርብ ነው የተከፈተው፡፡ ዋናው የጃንሆይ ቤተመንግስት በዋናው በር ገብተህ /ገነት ልኡል ማለቴ ነው/ ታሪካዊ መልክ እንዲኖረው ተደርጎ የተሰራ ዘመናዊ ቤተመጽሐፍት አለ።መጽሐፍቱ በኢትዮጵያ ጉዳይ በአማርኛ በግእዝ በውጭ ሀገር ቋንቋዎች የተጻፉ ለተማሪዎች ለተመራማሪዎች የሚሆኑ ናቸው፡፡
የፕሮጀክቱን መሰራት ሀሳብ ያነሱት የኢትዮጵያ ምሁራንና እነ ፕሮፌሰር ፓንክረስት ናቸው።ብዙ ተለፍቶበት መጨረሻ ላይ እኔ ለቅርስ ካለኝ ቀረቤታ አንጻር እሱ ቢሰራው ይሻላል ብለው ወደ እኔ አመጡት፤ ሰራሁት።ዘመናዊ ቢሆንም የላሊበላና የጎንደር የመሳሰሉት የኢትዮጵያ ቅርስ እሴቶች አሉበት፤ በቀጥታ አልቀዳሁም። ያደረኩት በመረዳት መተርጎም ነው።
ያንን ተርጉሞ ከህንጻው ግልጋሎት ጋር እንዲጣጣም ማድረግ ያስፈልግ ነበር።ይሄን ለማድረግ ስራና ምርምር ይጠይቃል። ከአዲስ አበባ ውጭ ጎንደር ታዬ በላይ የሚባል ሆቴል አለ። እሱ ከፋሲል ቤተመንግስት ከቅርሱ ወደላይ እንዳይወጣ ተብሎ ባለቤቱ ትልቅ ፎቅ ነበር የፈለጉት እኔ እየተጋፋሁ የዩኔስኮ የቅርስ መመሪያም አለ እሱንም ጠብቀን ነው የሰራነው።አዲስ አበባም ሌሎችም ቦታዎች የሰራኋቸው ብዙ አሉ፡፡
አዲስ ዘመን፡-ከሥነ ሕንጻ ጥበብ ( አርክቴክቸር) አንጻር ስናየው በዛን ሩቅ ዘመን የጎንደርን ድንቅ ቤተመንግስት ማን ሰራው ?
አርክቴክት ፋሲል፡- እኔ ባደረኩት ጥናት መሰረት ጥንታዊውን የጎንደር አጼ ፋሲል ቤተመንግስት በተመለከተ ሁለት እርስ በእርስ የሚጣረሱ አተያዮች አሉ።አንዳንዶቹ የውጭ ሀገር ባለሙያዎች ፖርቹጊዞች ናቸው ሰርተው የሄዱት ብለው ደምድመው የሚናገሩ አሉ።የለም የሠሩት የእኛዎቹ ኢትዮጵያውያን ናቸው ብለው ድርቅ የሚሉም አሉ።ይሄንን ጉዳይ በተመለከተ የተወሰነ አመት ወስጄ በጥልቀት ለማጥናት ሞክሬአለሁ።በአርክቴክቸር ቋንቋ ሀይብሪድ (በከፍተኛ ደረጃ ከሌሎች የተቀላቀለ፤ ክልስ) ማለት ነው፡፡
የጎንደርን ቤተመንግስት ሕንጻ አሰራር ታሪኩን ወደኋላ መለስ ብለን ስናየው የቆየ የሕንጻ ቅርስ ታሪክ የነበረን ሰዎች መሆናችንን የሚያረጋግጥ ነው።ከግራኝ አሕመድ ሠራዊት ወረራ በኋላ ሀገሪቷ በጣም ተዳክማ የሀይላንዱ (ደገኛው) ቅርሶችም በጣም ተዳክመው ነበር።በዛም ምክንያት ፖርቹጊዞች ወደ ሀገራችን መጥተው ነበር።ታሪኩ እንደሚገልጸው፤ ፖርቹጊዞች ደግሞ በሀይማኖት በኦርቶዶክሱና በካቶሊክ ጦርነት ምክንያት ተመልሰው ሄደው ነበር።
አጼ ፋሲል ቤተመንግስቱን ሲሰሩ ፖርቹጊዞች በፍጹም አልነበሩም።በዚህ ምክንያት ፖርቹጊዞች የጎንደርን ቤተመንግስት አልሰሩትም።በዛን ጊዜ ንጉሱ ያደረጉት ምንድነው ካልን እነዚህ ፈረንጆች የሀገሬን ሕዝብ እንደዚህ ስላፋጁ በሚል ነጮች ከሀገር እንዲወጡ አድርገዋል።ከተማውን ሲቆረቁሩ ሌላው ያደረጉት ነገር ፊታቸውን ወደ ምስራቅ አዞሩ፤ ወደ ሕንድ።ከሕንድም ሞጉል ኢንዲያ የሚባሉት ወደ ሰሜን ሕንድ ያሉት ሙስሊም የሆኑ ሕንዶች ናቸው።ከእነሱ ጋር የንግድ ግንኙነትም ነበራቸው።
በዛን ጊዜ የእደ ጥበብ ባለሙያዎችንም አስመጥተዋል።መሪ የሆኑት ማስተር ክራፍትስ ማን ( የእደ ጥበቡ መሪዎች) የአጼ ፋሲል ቤተመንግስት ሲሰራ ብዙም ባይሆኑ ታዋቂ ባለሙያዎች ከህንድ እንዲመጡ ተደርጓል።
ፖርቹጋሎች ኢትዮጵያ ውስጥ ከ80 አመት በላይ ኖረዋል። የጎንደር ዳይናሲቲ ስርወ መንግስቱ ሲመሰርት ሁሉ በዛን ጊዜ ፖርቹጊዞች ነበሩ።ጦርነቱ ያለቀው በአጼ ገላዲዎስ ጊዜ ነው። ይሄን ሁሉ ዘመን ፖርቹጊዞች ሚሲዮኖች ናቸው ብዙም ሌላ የላቸውም እዛው ጎንደር ኖረዋል።
በኋላ ነው እንግዲህ እንደነ ፔድ ፖይዛ አይነት በጣም የታወቁ ሰዎች የወጡት።አንዱ አላማቸው ሀይማኖት ማስቀየር ነው።ሀይማኖት የሚያስቀይሩት ጀስዊቶቹ ቄሶቹ ናቸው። በተለይ ብዙ የግንባታ ስራ የሰሩት በአጼ ሱሰንዮስ ጊዜ ነው።የአጼ ፋሲል አባት ናቸው።እሳቸው ደንቀዝ ላይ ጣና ሐይቅ አካባቢ ቤተመንግስት ሰርተዋል።ጎርጎራ አካባቢም ሌላ ሰርተዋል።ጥንታዊ ጎርጎራ የሚሉት በጣም የፈረሰ ቦታ አለ፡፡ ጎንደር ደግሞ ገነተ ኢየሱስ ወደ አዘዞ መውጪያው ላይ ሰርተዋል፡፡
ያንን በሚሰሩበት ጊዜ በእኛ የኪነ ጥበብ ሕንጻ ውስጥ ያልነበሩ አዳዲስ የህንጻ አሰራሮችን አስገቡ፡፡ለምሳሌ ኢትዮጵያ ለኖራ አዲስ አይደለችም።አንዳንድ ጽሑፎች ሳይ ፖርቹጊዞች ኖራ ኢትዮጵያ አስገቡ ይላሉ፤ ስህተት ነው፤ በአክሱማውያን ዘመንም ነበረ።በኋላም ወደ ላስታ ነበረ።
በጎንደር ዘመን እኛው ጋ የነበረውን እንደገና አስተዋወቁት ማለት ይሻላል።እኛ የራሳችን የኖራ ሀብት አለን።ሙያውን እንዲመጣ ያደረጉ አንዳንድ ሕንዶችን ያመጡ ነበረ።ፖርቹጊዞች ክርስቲያን ሕንዶችን ነበር የሚያመጡት።ፖርቹጊዞች ጎበዞች /ጥይት/ ናቸው።ሌሎች የእደ ጥበብ ባለሙያዎችንም ያመጣሉ። የእኛም ሰዎች አብረው ይሰራሉ።ጥበቡን ተማሩ፡፡ይሄ ብቻ አይደለም። ቀደም ሲል በቤተክርስቲያን በተለያየ ቦታዎች ሲሰሩ የነበሩ የእኛ የቀድሞ የእደ ጥበብ ባለሙያዎችም ይሳተፋሉ።ሕንዶችም ይሳተፋሉ፡፡
ስለዚህ የአጼ ፋሲል ቤተመንግስት በሚሰራበት ጊዜ በመሪ ባለሙያነት (ማስተር ክራፍት ማንስ) በምንለው የተወሰኑ ሙስሊም ሕንዶች ነበሩ።አብዛኛው ሰራተኛ ግን ኢትዮጵያዊ ነበር።ግንበኛው ኢትዮጵያዊ ነው።የተፈጠረው የሙያ መጣመር ነው።ንጉሱን አስቡ።እንግዲህ አሁን ላይ ሆነን የአጼ ፋሲልን ቤተመንግስት ስናየው በጣም ትልቅ ስራ ነው።አንዳንድ ቦታ ግምቡ መሬት ላይ እስከ 2 ሜትር ውፍረት ያለው አለ።በኖራ ነው የተሰራው።
አዲስ ዘመን፡- የአጼ ፋሲል ቤተመንግስትና ግምቡ ኖራና እንቁላል ተቀላቅሎ መሬት ውስጥ ብዙ ጊዜ ተቀብሮ ከበሰለ በኋላ(ፈርመንትድ) ነው የተሰራው የሚባለውስ ?
አርክቴክት ፋሲል፡- ይሄንን አባባል ዩኒቨርስቲ ተማሪ ሆኜ ከዛም ከወጣሁ በኋላ ስሰማ ይህቺ አፈታሪክ ናት ነበር የምንለው። ኋላ ግን ሳጠና አንዴ ምን አገኘሁ ሞጉል ኢንዲያ የምንላቸው ሕንዶች የተሰሩትን ቴምፕሎች መስጊዶችና ቤተመንግስቶችን ሲሰሩ እንቁላልና አጃ ይቀላቅሉ ነበር።ለምንድነው የሚቀላቅሉት ካልን ኖራው የተሻለ የማጣበቅ ባህርይ እንዲኖረው ነው፡፡
ኖራው ለረዥም ጊዜ ይቀበራል።ሁለት ሶስት አመት ሙሉ።ብዙ ፕሮሰስ አለው። ትልቅ ጥበብ ነው።ከዛ በኋላ በእሱ እያደረጉ ሰሩ።ፖርቹጊዞች ያስተማሯቸው ኢትዮጵያውያን ቀደም ሲል የጥንት የቤተክርስቲያን አሰራር ልምድ የነበራቸው ነበሩ።ሕንዶች አሉ።
ስለዚህ የፖርቹጊዝ እውቀት በተዘዋዋሪ መንገድ ገብቷል። ድልድዩን ስታይ ግን ከዛ ቀደም በእኛ የተሰራ እንደዛ ለየት ያለ ድልድይ አላየንም።አንገረብ ወንዝ አባይ መገጭም ላይ አለ።ባህርዳር ወደ አባይ ፏፏቴ ስንሄድ አለ።የፖርቹጊዝ ድልድይ ይሉታል።ትክክል ነው።እኛ በኋላ ላይ ባህሉን አሰራሩን ወረስነው።
ለእዚህ ጥሩ ምስክር የሚሆነን ደግሞ ደንቀዝ ነው።ደንቀዝ ላይ ፖርቹጊዞች አጼ ሱሰንዮስን ከፍና የበላይ የማድረግ ስራ ሰርተዋል። አንዱ ያደረጉት ለእሳቸው ሕንጻ መስራት ነበር።ገነተ እየሱስ ላይ የሠሩት ቤት በኋላ ፈረሰ እንጂ በጣም ውብ የሆነ ግቢው በአትክልት የተሞላ ውሀ የነበረው ነው። አሰራሩን በተመለከተ ፖርቹጊዞች የጻፉት አለ። በዛን ዘመን ፖርቹጊዞቹ ስለእኛ የጻፉት ሲተረጎም ብዙ እንሰማለን።በጣም ትልቅ ቅጥር ግቢ ያለው ብዙ ነገር የነበረው ነው።ሰውየው ኃይማኖታቸውን ቀየሩ። ለሀገሬው ላለማሳየት እሳቸውን ለማግለል ብለው ብዙ ነገር ሰርተውላቸዋል።
አዲስ ዘመን፡- ደንቀዝ ላይ የነበረውን የፈራረሰ ጥንታዊ የኪነ ጥበብ ስራ በምን ሁኔታ ላይ ይገኛል ?
አርክቴክት ፋሲል፡- የሚያሳዝነው ነገር እዛ ላይ በቂ ስራ አልተሰራም። ጉዛራ ላይ ትንሽ ተሰርቷል።የጎንደር የባህል ቢሮ ባለሙያዎች ጠግነውታል።አሁን ትንሽ እያስቸገረ ያለና ወደፊት ልምዱን ማስፋፋት ያለብን የኖራው ስራ ነው።ድሮ አባቶቻችን ሲሰሩ የነበረው እንዴት እንደነበረ መቶ በመቶ አግኝተነዋል ብለን አናስብም።ገና ምርምር እየተደረገ ነው።ከአምስት ኪሎ የማቴርያል ምርምር ጋር እየተነጋገርን ነው።ኖራውን ወስደው በላብራቶር አጃውና እንቁላሉ ከተሞከረ ውጤቱ ይገኛል።አሁን አንዱ ይዘነው ያለነው ነገር እሱ ነው።የግድ መሞከር መፈተሽ አለበት።
ስለኖራ ስናወራ በሀገራችን አፈታሪክ ነው እያልን የምንጥለው ነገር አለ። ሳይንሳዊ ማረጋገጫ ከሌለው ደግሞ አንቀበልም ይላል አካዳሚውና ዩኒቨርስቲ ጠቀስ የሆነው ምሁር።አፈታሪክ የሚባለው እኔ በተለያዩ አጋጣሚዎች እንዳየሁት ምንጩ መሰረቱ በሀቅ ላይ ነው።ዝም ብለን የምናጣጥለው አይደለም። አክሱም ላይ ገጥሞኛል።ጎንደርም ላይ ብዙ ቦታ አይቼዋለሁ።ያን ይዘን ታሪካችን በዚህ ነው የሚተረጎመው ማለት የለብንም።ያንን ለማረጋገጥ መሞከር ነው ትልቁ ነገር።
አዲስ ዘመን፡-ጥንታዊ የቤተክርስቲያን ስእሎች ከኪነሕንጻ ስራው ጋር እንዴት ይሰሩ እንደነበር ይታወቃል ? ጎንደር የጥንታዊ ስልጣኔዎች ምንጭ ነበረች ለማለት ያስችለናል ?
አርክቴክት ፋሲል፡- አዎን ያስችለናል።መነሻው አይደለም።ጥበቡ ከዚህ ቀደም ነበር።ይሄ ጥበብ ጎንደር ላይ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደረሰ።የቤተክርስቲያን ስእሎቹን ለመሳል እጽዋት፤ አፈር፤ የጭስ ጥላሸት፤ በመጠቀም የተለያዩ ቀለሞች ይሰሩ ነበር። በጣም ያስቸግራቸው የነበረው ሰማያዊ ቀለም ለመስራት ነበር።ሰማያዊ ቀለም ለመፍጠር ከውጭ የሚመጡ ኮባልት የሚባሉ ነገሮች /መስታወትነትና ድንጋይ ነገር ያላቸውን/ እየፈጩ ተጠቅመዋል። አብዛኛውን ነገር የእኛው ሰዎች ራሳቸው ነበር የሚሰሩት። እጽዋትና አሻሮ እየተቆላ ከእሱ ሁሉ ብዙ ነገሮችን እየቀመሙ ነበር ሲሰሩ የነበሩት።እግረ መንገዳቸውን ኬሚስቶችም ነበሩ ማለት ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- የኢትዮጵያን ኪነ ሕንጻ( አርክቴክቸር) እንዴት ይመለከቱታል ?
አርክቴክት ፋሲል፡- የረዥም ጊዜ ታሪክና ስልጣኔ ያለው ማንኛውም ሀገር አንዱ መገለጫው ኪነ ሕንጻ (አርክቴክቸር) ነው።እኛ በአፍሪካ ውስጥ እንደ ጥቁር አፍሪካውያን በጣም የሚያኮራ የረዥም ጊዜ የኪነ ሕንጻ ታሪክ አለን፤ ከቅድመ አክሱም ጀምሮ።አሁን ደግሞ በሂደት ላይ ያለ ስራ ነው። ብዙ ነገሮች ማወቅ አለብን።የምንሰራው ነገር አለ።
ከተወሰኑ አመታት በፊት ከሰሜን ሸዋ ጀምሮ ከዛም በታች ባሉ ስፍራዎች የእስልምና ተከታዮች ጥንታዊ መኖሪያ ቤቶችና መስጊዶች ሁሉ ተገኝተዋል።እነዚህ ነገሮች በበቂ ሁኔታ አልተጠኑም። መጠናት አለባቸው።በኪነ ሕንጻ ካየነው ኢትዮጵያ በጣም ሀብታም ነች።ብዙ መስራት ብዙ መፈተሽ ብዙ መቆፈር ግን ይቀረናል።በድንጋይ በጭቃና በእንጨት የተሰሩ ሕንጻዎች፣ የአፋሮች ተንቀሳቃሽ የመኖሪያ ድንኳኖችን ስናይ ይሄ ከመኖር ከሂደት ከባህሉ ሀብታምነት የሚመጣ የእውቀት ደረጃ ነው።
ወደ ሲዳማ ስንሄድ በሸምበቆ /ቀርከሃ/ የሚሰራው ቤት፤ ኮንሶ፤ ጉራጌ ሀገር ያለውን ስታይ ሕዝቡ በጣም ሰፊ በሆነው የራሱ የቤት አሰራር ላይ የህንጻ ጥበብ አዳብሯል።ነገስታቱም በአብያተ ክርስቲያናትም መስጊዶችም በዛ ደረጃ የመጠቀ ኪነ ጥበብ የምንለው በላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያኖችን ተመልከት። ከትግራይ ጀምሮ ወደ 120 አብያተ ክርስቲያናት አሉ፡፡ላስታ ስትመጣ ከ23 በላይ አሉ።እስከ ሸዋ እዚህ አዳዲ ማርያም ድረስ የሄደ ባህል ነው።
እሱ ብቻ አይደለም።ዋሻ ውስጥም ተገንብተው የተሰሩ የኪነ ሕንጻ ጥበቦች አሉ። በኪነ ሕንጻው በጣም ሄደናል።ትንሽ የሚያሳዝነኝ ምንድነው ሀገራችን እንደምታውቁት ያላት የጦርነት ታሪክ ስለሆነ እየሰሩ ማፍረስ አለ።አንዱ ይሰራል፤ ሌላው ያፈርሳል። እንዲህ አይነት ነገር ስለሆነ ነው እንጂ ቀጥ ብሎ አውሮፓ ውስጥ አንዳንዱ ስልጣኔ እንደሄደው ቢሄድ ኖሮ ብዙ ነገር ላይ እንደርስ ነበር።አንዱን በአንዱ ላይ እየገነባን በጣም እናድግ ነበር።ጦርነቱ በአካባቢያችን ከነበረው ሁኔታ ጋር የተደረገ ስለነበር ብዙ ጉዳት አድርሷል ለማለት እንጂ ሀገራችን ብዙ ሀብትና የኪነ ሕንጻ ጥንታዊ ጥበብ ባለቤት ናት፡፡
አዲስ ዘመን፤- በተለያዩ የኢትዮጵያ ክልሎች ጥናት ምርምር ቁፋሮ የሚጠይቁ ብዙ በጣም ጥንታዊና ተቀብረው ያሉ ያልተፈተሹ የኪነ ሕንጻ ሀብቶች እንዳሉ ይገለጻል፡፡እርስዎ በእዚህ ላይስ ምን ይላሉ ?
አርክቴክት ፋሲል፡- ጥናቶች በየአቅጣጫው እየተደረጉ ነው። ሕንጻዎቹ በአብዛኛው የተሰሩት በድንጋይና በአፈር ነው። አፈርን በማጣበቂያነት በመጠቀም።የተወሰኑት ናቸው ኖራ ያላቸው። በተለይ ጎንደር ላይ ኖራ ብዙ ነው።የድንጋይና የአፈር ሕንጻ ሲፈርስ ከመሬቱ ጋር አንድ ነው የሚሆነው፤ ይቀላቀላል። እዛ ላይ ሰፊ በሆነ መልኩ የአርኪዮሎጂና የአርክቴክቸር ሙያ በጥምረት ብዙ ስራ መስራት ይጠበቅበታል።
እኛ ተማሪዎቻችንን በመስክ ስራ አብረው እንዲሰሩ እያለማመድን ነው።እኔ ወደፊት ተስፋ የማደርገው የአርኪዮሎጂና የአርክቴክቸር ተማሪዎች አብረው እንዲሰሩ ነው። ተቋሞቻችን እየተጣመሩ አብረን ብንሰራ ብዙ ነገር እናገኛለን። በነገራችን ላይ አብያተ ክርስቲያናቱ አንዳንዶቹ ደበቅ ብለው መገኘታቸውን እንደ እሴት ነው የሚቆጥሩት።አሁን ላለው አለማዊ እውቀት ማወቁም ጥሩ ነው።ያንን ጥንታዊና የኖረ እሴት ሳናጠፋ።
ጎንደር ዩኒቨርስቲ የአርክቴክቸር ዲፓርትመንት ከፍቷል። አርኪዮሎጂ መከፈት አለመክፈቱን እርግጠኛ አይደለሁም። መጀመሪያ ከገለጽኩት ዲፓርትመንት ተመርቀው የወጡ የእኛ ሁለት ተማሪዎች ወይም ሶስት ልጆች እዛ ይሰራሉ። በመላው ኢትዮጵያ በዚህ ረገድ ወደፊት ብዙ የቤት ስራ አለብን። እያጓጓን መስራት አለብን።ጀመርነው ጫፍ ጫፉን ነካ ነካ አደረግነው እንጂ ኪነ ሕንጻ በጥልቀት ሲሄድ የታሪክ ምሁራን ማለት ነው።
በነገራችን ላይ አርክቴክቸር ስንማር ብዙ ሰው እንደ ኢንጂነሪንግ ቴክኒክ ይወስደዋል።አርክቴክቸር ስናጠና ታሪክ ብቻ የሁለት አመት ኮርስ እንወስዳለን። የአርክቴክቸር ታሪክ። ስለሰው ስለሁኔታው ታሪክ ሳታውቅ ሕንጻውን ብቻ ማጥናት አትችልም።በምን ሁኔታ ተሰራ፤ እንዴት ተሰራ፤ ማን ሰራው፤ ይሄ ሁሉ መመለስ አለበት።
በእኛ ሙያ የሚነገር ትልቅ አባባል አለ፤ ከተሞች ወይም ሕንጻዎች እንደ እጅ አሻራ ታሪካቸውን እንደዚህ ይዘው ያስቀምጣሉ ይላል፤ እውነት ነው።ጎንደርን ቤተመንግስቱን ስናይ እኮ እነዚህ ሰዎች ምን ላይ ነበሩ? ምንድን ነበር ፍላጎታቸው ምኞታቸው የሚል ጥያቄ ያጭራል።የገዘፈ ትልቅነትን ያሳያል።ከስልጣኔ ከእድገት አንጻር ልቀትና ምጥቀትን የላቀ ከፍታን ያመለክታል።የዛን ዘመን እንዲያ የከፍታው ማማ ላይ ተቆናጠን የነበርን ሰዎች ከዛ በኋላ በነበረው የታሪክ ዘመን ምን ነካን የት ደረስን ያሰኛል።
አዲስ ዘመን፡-ለማደስ ምን ተደረገ ?
አርክቴክት ፋሲል፡- ቅርስ ጥገና ላይ ሁለት አይነት የአስተሳሰብ ጎራዎች አሉ።አንደኛው የምትጠቀሙበት ማቴሪያል ኦርጅናሉን መምሰል አለበት ይላል።ሁለተኛው ደግሞ ቅርሱን እንዳይሞት አድርጋችሁ ዘመናዊም ነገር ይዛችሁ ጠብቁት፤ መቀየር የለበትም የሚል ነው።እዛ ላይ ውዝግብ አለ።
በእኛም ሀገር የተለያየ እይታ አለ።የእኔ አመለካከት ታሪኩን ማቆየት ካለብን የእያንዳንዱ ዘመን ኃላፊነት አለብን። አዲስም መልሰን ብንከት የድሮውም አይነት ብናደርግ ዋናው እይታው ራሱን መሆኑ መቀየር የለበትም።አዳዲስ ቴክኖሎጂ መጠቀም ክፋት የለውም።ምክንያቱም ይህን ማድረግ ካልቻልን ሕንጻው መኖር አይችልም፤ ይሞታል።
የጎንደር ሕንጻ በ1720ዎቹ ውስጥ ነው የተሰራው። አሁን ወደ አራት መቶ አመት ገደማ ይሆነዋል።የእምነት ጽናት ሀገርን ከልብ የመውደድ ነገር አለ።ትንሽ የማዝነው የእኛ የፊውዳሉ ዘመን ለባለሙያዎችና ለእደ ጥበብ ሰዎች በቂ ክብር አልሰጠም።ያው የፊውዳል አስተሳሰብ ስለሆነ ነው።በዛን ዘመን የነበሩትን የጥበብና የእደ ጥበብ ባለሙያዎች ቢያከብሩዋቸውና ቢንከባከቧቸው ጥሩ ነበር። ለምሳሌ በጎንደር ዘመን የመጨረሻዎቹ አካባቢ ከባካፋ በኋላ እቴጌ ምንትዋብ የእደ ጥበብ ትምህርቱን እውቀቱን እንዲከታተሉ ለተማሪዎች እንደ ስኮላርሽፕ አይነት ሁሉ ይሰጡ ነበር።በዛን ጊዜ ጥበቡ ወደላይ ሲያድግ ይታያል። የጎንደር ስእል አሰራርም አለ።የደብረብርሀን ስላሴን የስእል አሰራር አይተሃቸዋል።እሱ ስሙ ራሱ ሁለተኛው የጎንደር ስታይል የሚባል ነው፡፡(ዘ ሰከንድ ጎንደሪያን ስታይል) ነው የሚባለው።የመጀመሪያው ነበረ።ሁለተኛው ደግሞ ራሱን ይዞ ወጣ።ያንን ለማድረግ ጥበብ አጋዥ አጋር ይፈልጋል።
ጣሊያኖች እስከአሁን በአለም ላይ የሚያስጠራቸው የጥበብ ሰዎቻቸው ብቻ ሳይሆኑ የጥበብ ሰዎቹን የደገፉት ባለሀብቶችና የአመራር ሰዎችም ናቸው።ለምን አደረጉት ሲባል እነሱ ሀብታቸውን የሚገልጹበት መንገድ ጠቢባን የሚያምር ቤተመንግስት ሲሰሩ ያላቸውን ሀብትና የስልጣኔ ደረጃ ይገልጹበታል።የእኛዎቹም ያን ነገር ተረድተውታል።ግን ለጠቢባኖቹ ክብር ቢሰጡ ኖሮ የበለጠ ያገኙ ነበር።
ሞሮኮም ላይ አይቻለሁ።ብዙ ትላልቅ ቤቶችና መስጊዶች አሉ። ሀብታሞቹ ራሳቸው ጎበዝ የሆነውን የተሻለውን የኪነ ሕንጻ ጥበብ ያለውን ሰው የተሻለ እየከፈሉ የበለጠ እንዲጠበብ ስራውን የበለጠ እንዲያወጣ ያደርጉታል።ይሄ ለአንድ ሀገር እድገት በጣም አስፈላጊ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ስለሰጡን ቃለምልልስ እናመሰግናለን፡፡
አርክቴክት ፋሲል ጊዮርጊስ ፡- እኔም አመሰግናለሁ፡፡
አዲስ ዘመን ሐምሌ 28/2012
ወንድወሰን መኮንን