የመጀመሪያዎቹ ዘመናት
የተወለዱት ከእናታቸው ከወይዘሮ የልፉዋጋ ደስታ እና ከአባታቸው ከአቶ ጥሩነህ ካሳ ገጠራማ በሆነችው ‹‹ግድልኝ ቀበሌ ደጋ ዳሞት ወረዳ›› ነው። ዕድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስም ለራሳቸው የአስኳላ ደጃፍን ያልረገጡት ወላጆቻቸው ከዘመናዊ ትምህርት ጋር አገናኟቸው። ‹‹በቀለም ትምህርት ሳይሆን በስብዕናና በመልካም ተቃኝቶ ከኖረ ቤተሰብ ነበር የተወለድኩት። እርሳቸውም ታዲያ ‹‹ሳይማሩ የትምህርትን ጥቅም የተረዱት ወላጆቼ የእውቀት በር ከፍተውልኛል።›› ይላሉ።
ለመጀመሪያ ጊዜ መኪና በአይናቸው ያዩት በ14 አመታቸው ነው። ይህ የሆነው ስምንተኛ ክፍልን አጠናቀው ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ለመማር ወደ ደብረ ማርቆስ በሄዱበት ጊዜ ነበር። ደብረ ማርቆስ ከመኖሪያ ቀያቸው 100 ኪሎ ሜትር ይርቃል፤ እስከ ደምበጫ 50ኪሎ ሜትሩ መኪና ስላልነበረው በዓመት አራት ጊዜ ደርሶ መልስ መመላለስ ነበረባቸው። የዓላማ ሰው በመሆናቸው የእግር መንገድና የገጠር ኑሮ ግን አልረታቸውም።
ለማንነቴ መሰረት
በ1966 ዓ.ም በአገራችን ልዩ የፖለቲካ ሁኔታ ተፈጠረ። ወጣቱ በተለያየ የፖለቲካ ድርጅት ውስጥ በመታቀፉ የአመለካከቱና የአደረጃጀቱ ሰለባ ሆነ። ይሄ ክስተት እርሳቸውንም ይጨምር ነበር። በዚህ ምክንያት ወደ ወህኒ ቤት ተወረወሩ። ደብረ ማርቆስ ለአምስት ዓመት ያህል ታሰሩ። በቆይታቸው ብዙ ተሰቃይተዋል። በአንዲት ጠባብ ክፍል ውስጥ 54 ታሳሪዎች የነበሩ ሲሆን ለጎን ማሳረፊያ፣ እግር መዘርጊያ እንኳን አልነበራቸውም። በቆይታቸው ከአንድ አመት ከስድስት ወር በላይ በእግር ብረት ታስረዋል።
‹‹ፖሊሶቹ የእግር ብረቱን ለመፍታት ሁለት ብር ጉቦ ይቀበሉ ነበር። ሌሎች እስረኞችም ይህን እየከፈሉ ይፈታሉ። እኔ ግን ሁለት ብር አልከፍልም ብዬ ለስድስት ወራት ሌሊት ተቀን ታስሬ በጥንካሬ ተወጣሁት›› ይላሉ ስለ ቆይታቸው ሲናገሩ። እግር ቢቆስል ስጋ ነውና የህሊና ቁስል ግን መዳኛ ስለሌለው፤ ሁለት ብር ለፖሊስ ጉቦ ከፍሎ የህሊና ቁስለኛ ከመሆን ነፃ ወጥቻለሁ ይላሉ። ታዲያ ይሄ ስብእናቸው የዛሬ ስኬት መሰረት ሆኗቸዋል።
የስራ ክቡርነት
የዛሬው ባለራዕይ ዶክተር ገበያው ከማረሚያ ቤት እንደወጡ ለስራ ፍለጋ ጉዟቸውን ያደረጉት ወደ አዲስ አበባ ነው። እዚህ በቀን ሶስት ብር እየተከፈላቸው የሸክም ቀን ስራ ከመስራት ጀምሮ ምንም ሳይንቁና ጊዜን ሳይጠብቁ ቀን ሊያወጣቸው የሚችለውን ሁሉ ሰርተዋል። አራት ኪሎ አካባቢ ያስጠጓቸው ሰዎች ጋር ሆነውም የሽመናም ስራን ሞክረውታል።
ከዚሁ ሁሉ ፈተና በኋላ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ረዳት የቤተ መጽሀፍት ሰራተኛ ሆነው ተቀጠሩ። በዛን ሰዓት 12ኛ ክፍል የጨረሰ ሰው የተከበረ ስራ ያገኝ ነበር። እሳቸው ግን የአብዮታዊት ኢትዮጵያ ወጣቶች ማህበር (አኢወማ) አባል በመሆን አስተዋፆ ያደርጉ ስላልነበር ስራ ማግኘት አለመቻላቸውን ያስታውሳሉ። የህክምና ትምህርት ለመግባት እንኳ የአኢወማ የተሳትፎ መረጃ አስፈላጊ ነበር። ሆኖም ሰርተፍኬቱ ስላልነበራቸው ከትምህርት ገበታ ከተለያዩና ከስምንት ዓመት ስቃይና እንግልት በኋላ በያኔው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጎንደር የህክምና ሳይንስ ኮሌጅ ሜዳካል ትምህርታቸውን መከታተል ጀመሩ።
‹‹ትምህርቴን በጥሩ ውጤት አጠናቀቅሁ። ዩኒቨርሲቲው በጀማሪ አስተማሪነት እዚያዉ ቢያሰቀረኝም ወላጅ አባቴ ከዚህ ዓለም በሞት በመለየቱ ምክንያት በተፈጠረ የቤተሰብ ሃላፊነት ወደባህር ዳር በመምጣት በአውራጃ የጤና ጥበቃ ጽህፈት ቤት እና በባህር ዳር ጤና ጣቢያ ሃላፊነት ስራ ጀመርኩ›› ይላሉ። መለስ ብለው ስለሁኔታው እያስታወሱ።
ቀጥሎም ባህርዳር ከተማ የፈለገ ህይወት ሪፈራል ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተር ሆነው ተመደቡ። በቆዩበት የአምስት ዓመት የአገልግሎት ዘመናቸው ሆስፒታሉ እጅግ የተጎዳ ስለነበር ቀን ከሌት ሰርተው ብዙ አሻራዎችን ማሳረፋቸውን ያስታውሳሉ። ይህን የስራ ቦታ ታላቅ የአመራር ትምህርትና ልምድ ያገኙበት፣ ውጤታማ ስራ የሰሩበት፤ አሁንም እንደቤታቸው የሚያዩት ተቋም መሆኑን ይገልጻሉ።
የእውቀት መነሻ
አባታቸው የአገር በቀል እውቀቶች ያላቸው፣ ጥበብና አርቆ ማሰብ የተቸራቸው ብሎም ለማህበረሰብ አገልግሎት እራሳቸውን አሳልፈው የሰጡ ነበሩ። ልጃቸው ዶክተር ገበያው ከተወለዱ በኋላ በ42 ዓመታቸው ነው ፊደል የቆጠሩት። ቄስ ትምህርት ቤት ወይም ዘመናዊ ትምህርት ቤት ገብተው ግን አልነበረም። በአጋጣሚ በቃላቸው ሸምድደው የያዙት ፊደል እንዳይጠፋባቸው በራሳቸው ጥረት በቀርከሀ ተክል ሽፋን (ሽቆ) ላይ በሹል ነገር ቀርፀው ያጠኑ ነበር።
ዶክተር ገበያው የመጀመሪያ ደረጃ እየተማሩ አባታቸው በኩራዝ የማታ ሲማር ትዝ ይላቸዋል። አባታቸው ፊደል በመቁጠራቸው የተለያዩ ደብዳቤዎችን ለመንግስት አካላትና ለከፍተኛው ፍርድ ቤት ይግባኝ ይጽፉ ነበር።
ዶክተር ገበያው ስለ አባታቸው ተናግረው አይጠግቡም። ቤተሰባቸውን በመምራት፣ በአካባቢው ደራሽ፣ የተበዳይ ጠበቃ፣ የማህበራዊ ጉዳዮች አስፈጻሚ እንደነበሩ ይናገራሉ። ለዘመናዊ ትምህርት ልዩ ክብር ስለነበራቸው ወላጆችንና ልጆችን በማሳመን የትምህርት እድል እንዲያገኙ ማድረጋቸውን ይመሰክራሉ።
ዶክተር ገበያው ወደ ህክምናው ጎራ ያሉትም አባታቸው በሚያሳዩት ማህበራዊ አገልግሎት የተነሳ መሆኑን ይናገራሉ። ወረርሽኝ ሲከሰት የታመሙት ሰዎች በሽታውን እንዳያስተላልፉ ይለያሉ። ለኮሮና ‹‹ኳራንቲን›› እንደሚባለው ‹‹ውሽባ›› ገቡ ይባላል። ውሽባ የገቡትን ሰዎች ታዲያ ወረርሽኙን በመፍራት የሚጠይቃቸው የለም። እርሳቸው ግን ለሊት ተነስተው ምግብ ያቀብሏቸው ነበር። ይሄ ወደ ህክምናው እንዲያዘነብሉ አድርጓቸዋል።
ማህበራዊ ሀላፊነት
እንግዳችን ‹‹የህይወቴን ምሉዕነት የምለካው የቀን በቀን ውሎዬ ለሌላው በሚያበረክተው አስተዋጽኦ ነው›› ይላሉ እስር ቤት እያሉ የሸማኔዎች የህብረት ስራ ማህበር በማቋቋም ህብረተሰቡ በቅናሽ ዋጋ ሸማ እንዲለብስ ያደርጉ ነበር። መደበኛ ትምህርት ቤት እንዲቋቋም በትጋት ሰርተዋል። በዚህ ተግባራቸው ደርግ እንኳን ‹‹የበደሉትን አብዮት ክሰዋል›› የሚል ሰርተፍኬት ሰጥቷቸዋል።
በማህበራዊ አገልግሎት ብዙ አስተዋፆ አላቸው። በዋናነትም ለንግድ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ለአራት አመት፣ ዋይኤምሴ ፕሬዚዳንት ለስምንት አመት፣ ባህርዳር ቸሻየር ፋውንዴሽን የኤክስኪዩቲቭ ኮሚቴ አባል፣ ባህርዳር ኦክላንድ ሲስተርሲቲና ባህርዳር ክሌቭልንድ ሲስተር ሲቲ ኤክስኪዩቲብ ኮሚቴ አባል፣ የባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የቦርድ አባል፣ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የቦርድ አባል፣ አባይ ባንክ የቦርድ አባል በመሆን አገልግለዋል። አሁን ደግሞ በአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት የሙሁራን መማክርት ጉባኤ ፕሬዚዳንት፣ በተለያዩ ተቋማት ደግሞ የቦርድ አባልና የሙያ ማህበራት ስራ አመራር በመሆን በበጎ ፈቃድ እያገለገሉ ይገኛሉ።
ከመንግስት ስራ ጋር የተደረገ ፍቺ
የግል ክሊኒክ ከፍተው ከመንግስት ስራ እንዲለቁ ያደረጋቸው በተደጋጋሚ ያጋጠማቸው የስራ ላይ እንቅፋት መሆኑን ይገልጻሉ። ‹‹እኔ የገጠር ልጅ ነኝ ። ሲነገድም በቅርበት አይቼ አላውቅም፤ የሚነግድ ቤተሰብም የለኝም›› የሚሉት እንግዳችን፤ በህክምና ትምህርት ቤቱ ጥሩና ጎበዝ ተማሪ ብቻ እንደነበሩ ይናገራሉ። ስለዚህ እቅዳቸው በዩኒቨርሲቲው ውስጥ በአስተማሪነትና በሃኪምነት ፕሮፌሰር መሆን ነበር። ነገር ግን በመንግስት ቤት ያጋጠመኝ ሁኔታ የግድ የቢዝነሱን ዓለም እንዲቀላቀሉ ገፋፋቸው። በመንግስት ቤት ስመደብ የተሰጣቸው ሀላፊነት ከባድ ቢሆንም ይህን ለመወጣት የሚያስችል ስልጣን አልነበራቸውም።
በሆስፒታሉ ከ1984 እስከ 1987 የለውጥና የሽግግር ወቅት በመሆኑ ሁሉ ነገር የተዛባበትና በርካታ ክፍተቶችን ለመድፈን ሌት ተቀን መስራትን የሚጠይቅበት ጊዜ ነበር። ከዚህም የተነሳ ሆስፒታሉን በአግባቡ ለመምራት የሚያስችሉ ባለሙያዎችና የሌሎች ግብአቶች ከፍተኛ እጥረት ነበር። በዚህ የተነሳ ቀዶ ህክምና የሚካሄደው የመጠቀሚያ ጊዜ ባለፈበት የሰመመን መድሀኒት ነበር። መድሀኒቱ ህመምተኞች ላይ የከፋ ጉዳትና ሞት አላስከተለም እንጂ በስራቸው ወቅት ደም ቶሎ እንዳይረጋ ያደርግ ነበር። በዚህ ምክንያት እንግዳችን ለ816 ሰዎች በሰመመን መድሃኒት ኦፕራሲዮን ሰርተናል በሚል ችግሩን ባሳየ መልኩ በሬዲዮ መግለጫ ሰጡ።
በሁኔታው የጤና ሚንስትሩ ተበሳጩ። የተለያየ ችግርም ደረሰባቸው። በወቅቱ የተባሉት ‹‹መጠቀሚያ ጊዜው ያለፈ መድሀኒት መጠቀም ይቻላል›› ብለህ ለህዝብ እያስተማርክ ነው የሚል ነበር። እሳቸው ግን መጠቀሚያ ጊዜው ያለፈበት መድሀኒት ተጠቀሙ እያሉ ሳይሆን ‹‹የችግሩን ስፋትና ጥልቀት ለአብነት ያክል እየገለጽኩ ነው›› በሚል አለመግባባት ተፈጠረ።
ሌላው ደግሞ የሜዲካል ተማሪ በነበሩበት ወቅት አንድ የቦይንግ ኩባንያ ንብረት የሆነ ጀት ባህር ዳር ላይ ወድቆ ነበር ። ጀቱ በወደቀ ጊዜ ለመንገደኞች አገልግሎት የሰጠው ፈለገ ህይወት ሆስፒታል ነበር። ይሄንኑ ውለታውን ጠቅሰው ሆስፒታሉ ያጋጠመውን ችግር በማንሳት ድጋፍ እንዲያደርግላቸው ደብዳቤ ጽፈው ለቦይንግ ኩባንያ ላኩ። ኩባንያው አንድ ነጥብ ስምንት ሚሊየን ዶላር ግምት ያለው ዕቃ እርዳታ ሰጠ። የተላከውን ዕቃ ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት ከቀረጽ ነጻ ይግባ የሚል የድጋፍ ደብዳቤ ያስፈልጋል። ይሄን ከሚፈቅዱት የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ጋር በሰጡት መግለጫ አለመግባባቱ አለ። መድሀኒቱም መጋዘን ውስጥ ለዓመታት ቆየ። ሚኒስትሩ ሲቀየሩ ሌላዋ ሚንስትር ድጋፍ ቢያገኙም ‹‹የመጋዘን ኪራይ ክፈሉ›› ተባለ። ሆስፒታሉ የተባለውን መክፈል አይችልም። ስለዚህ ወደ ገንዘብ ሚኒስቴር ሄዱ። በወቅቱ የነበሩትን የገንዘብ ሚንስትር ለ14 ቀን ደጅ ጠንተው በነፃ እንዲወጣ ተደረገ።
ሆኖም ጣጣው በዚህ አልተቋጨም። እቃው ሲወጣ ወደ150ሺ ባግ የሚሆን አይቪ ፍሉድ የመጠቀሚያ ጊዜው አልፎበት ተገኘ ። ይሄንን እዛው መተው አይቻልም፤ ተሸክመህ ውሰድ ተባሉ። ጤና ጥበቃን ኮሜቴ ይቋቋምና እዚህ ይወገድ በማለት ቢጠይቁም የሚቀበላቸው አላገኙም። የባህርዳር ጤና ቢሮም ኮሚቴ ሊልክ ፈቃደኛ አልነበረም። በዚህ ምክንያት መድሃኒቱ ባህርዳር ሄዶ ተወገደ። ይሄና በርካታ ችግሮች ከመንግስት ጋር አብሮ ላለመስራት የመጨረሻ የውሳኔ ቀን ሆናቸው።
የንግድ ሀሁ
‹‹የዛሬ 25 ዓመት ወደ ግል ስራ ስገባ እንደ እኔው ብሶት ካላቸው አራት ጓደኞቼ ጋር ተነጋግረን ነው›› የሚሉት ዶክተር ገበያው፤ ነገር ግን ሀብታም የሚጠላበት፤ የሚሰራ ብዙም የማይደነቅበት ወቅት በመሆኑ ተግዳሮቱ ከፍተኛ እንደነበር ይገልፃሉ። ሆኖም አምስቱም ባዋጡት 39 ሺ ብር ካፒታልና እርሳቸው ከጓደኛቸው በተዋሱት ማይክሮስኮፕ ስራ ጀመሩ። በመጀመሪያው ቀን ስድስት በሽተኛ አይተዋል። በዚህ የተጀመረው ስራ አሁን አድጎ በሶስት የተለያዩ ተቋሟት ማህበረሰቡን በጤናው፣ በስልጠና እና በመድሀኒት፣ የህክምና መገልገያዎችና መሳሪያዎች አቅርቦት ሰፊ አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል። ከሶስቱ አንዱ ጋምቢ ቲቺንግ ጀነራል ሆስፒታል በቀን ከ300 እስከ 400 ህሙማንን ያስተናግዳል። በሚሰጠው አገልግሎትም በሀገር አቀፍ ደረጃ ለሶስት ተከታታይ ዓመታት በጥራት የክብር ዋንጫ ተሸላሚ ናቸው። ሁለተኛው ጋምቢ የመድሀኒት፣ የህክምና መሳሪያዎችና መገልገዎች ማከፋፈያ ድርጅት ነው።
ቀደም ሲል ባህርዳር ከተማ ላይ ዓለም አቀፍ ስብሰባ አይካሄድም ነበር። ለዚህ ብዙ ምክንያት ሊኖረው ቢችልም ደረጃውን የጠበቀ ሆስፒታልና ሆቴል አለመኖር ዋነኛ ምክንያቶች ሊሆኑ እንደሚችሉ ዶክተር ገበያው ያነሳሉ። አሁን የጋምቢ ቲቺንግ ጠቅላላ ሆስፒታል በመቋቋሙና መስፈርት አሟልቶ በመገኘቱ ዓለም አቀፍ ስብሰባ እየተካሄደ ነው። ይህም ታላቅ የሆነ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታን ብቻ ሳይሆን ከፍተኛ የሆነ የአገርና የከተማ ገጽታ ግንባታ ነው። እንደ ሲቲ እስካንና ኤምአርአይ የመሳሰሉ ዘመናዊ መሳሪያዎች በመንግስት ሆስፒታሎች አልነበሩም። አዳዲስ ነገሮች በማምጣት፣ ከፍተኛ ደረጃ የደረሱ ባለሙያዎችን በመሳብና በማሰልጠን፣ ህዝብ ለህክምና እና ለትምህርት ፍላጎት ብዙ ቦታ ርቆ እንዳይሄድ ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጓል።
‹‹የህዝቦች ራዕይ የአገር ሀብት ነው›› የሚሉት ዶክተር ገበያው፤ መንግስት ደግሞ ያንን ራዕይ ውሀ ማጠጣት፣ መኮትኮትና ማሳደግ ይኖርበታል ይላሉ። አሁን የእነርሱ ካምፓኒዎች የአገር ሀብት መሆኑንና በግብር ሁልጊዜ ከ60 በመቶ በላይ ለመንግስት ገቢ እንደሚደረግ ያነሳሉ። ይሄ የዜጎች ራዕይ የአገር ሀብት ለመሆኑ አንደኛው ማሳያ ነው ይላሉ።
አንዱ ለሌላው መንገድ
ከእለታት በአንዱ ቀን በምሳ ሰዓት ወደ መኪናቸው እየሄዱ ነበር። በድንገት የአንዲት ሴት ከባድ ጩኸት ይሰማል። የምትጮኸውን ሴት ለማየት ሲሞክሩ ልጅ አቅፋለች። ወደምትጮኸው ሴት ሲጠጉ ልጁ ይፈራገጣል፤ ልጁንም ከእናቱ እቅፍ ሲቀበሏት በጣም ከፍተኛ ትኩሳት አለው። የትኩሳት ማብረጃም ሰጡት። በመድሀኒቱ መፈራገጡን አላቆመም። ስለዚህ ሌላ መድሀኒት ሊሰጠው ይገባል። ያ መድሀኒት ግን በመለስተኛ ክሊኒክ ደረጃ መያዝ ስለማይቻል ያላቸው አማራጭ ልጁን ይዘው ወደ ፈለገ ህይወት ሪፈራል ሆስፒታል መሄድ ነበር። እዛም ሀኪሞች ለምሳ ወጥተዋል፤ ተረኛው ሀኪም ስራ ላይ ስላልነበረ ቶሎ ማግኘት አልቻሉም። ነገር ግን ባገኟቸው ነርሶች አማካይነት መድሀኒቱን ለልጁ ተሰጠውና ትኩሳቱ በረደ። ሆኖም ግን በወቅቱ ማግኘት የሚገባውን ባለማግኘቱ የተነሳ የአእምሮ ችግር አጋጠመው። ይሄም የተከሰተው በቅርበት መድሀኒቱን መያዝ ባለመቻላችን ነበር። በዚህ ምክንያት ፋርማሲ ለማቋቋም አስገዳጅ ምክንያት ተፈጠረ። የፋርማሲው መከፈት ደግሞ ለህብረተሰቡ የመድሀኒት ዋጋ ማረጋጋት እና ውድድርን ፈጠረ። ጋምቢ የመድሀኒት፣ የህክምና መገልገያዎችና መሳሪያዎች ማከፋፈያ ድርጅትን በማቋቋምም በተጨማሪ በአካባቢው ላሉ የመንግስትና የግል የጤና ተቋማት ማከፋፈል ጀመርን። ይህ ደግሞ ትልቅ እፎይታ ፈጠረ።
ሌላው ደግሞ ክሊኒኩ እያደገ የተጠቃሚው ቁጥር እየጨመረና ስራውም እየሰፋ ሲሄድ የሰው ሀይል ፍላጎት አደገ። የሰለጠነ የሰው ሀይል ማግኘት ደግሞ አስቸጋሪ ሆነ። ስለዚህ የቀድሞ ጋምቢ የህክምና ሳይንስ ኮሌጅ የአሁኑን ጋምቢ የህክምናና ቢዝነስ ኮሌጅን ከፈቱ። ለራሳቸው በቂ ሃይል ካሟሉ በኋላ ለሌሎችም መትረፍ ጀመሩ። ፍላጎቱን እያዩም በተለያዩ የህክምና መስኮች በመጀመሪያ ዲግሪ፣ ሜዲካል ዶክትሬት ዲግሪን ጨምሮ የጤናና የቢዝነስ መስኮች ሁለተኛ ዲግሪ ፕሮግራሞችን በመክፈት ማሰልጠን ቀጠሉ።
የትምህርት ጥማት እስከምን?
መጀመሪያ በጎንደር የህክምና ሳይንስ ኮሌጅ የሜዲካል ዶክትሬት ዲግሪያቸውን ወሰዱ። ጎንደር ዩኒቨርሲቲና በእንግሊዝ አገር የሚገኘው ሌስተር ዩኒቨርሲቲ በጋራ በከፈቱት የፖስት ግራጁዌት ፕሮግራም በማህበረሰብ ጤና ክብካቤ የማስተርስ ዲግሪ አጠናቀቁ። ቀጥለው አሜሪካን አገር በሚገኘው ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ካሊፎርኒያ ሳንፍራንሲስኮ በግሎባል ሄልዝ ሳይንስ ሌላ ማስተርስ ዲግሪ ሰሩ። ታዲያ የሁለተኛ ዲግሪ የማህበረሰብ ጤና ክብካቤ ስርአተ ትምህርት ላይ Introduction and Foundations of Global Health Sciences ትምህርት ክፍል ቢጨመር የዓለም ጤናን አስመልክቶ እርሳቸው የተማሪዎችን አይን ሊከፍት ይችላል ብለው አሰቡና ይሄንን በካሪኩለሙ እንዲካተት ተደረገ።
ደብረማርቆስ ዩኒቨርሲቲና ጋምቢ የህክምናና ቢዝነስ ኮሌጅ በጋራ በከፈቱት የማህበረሰብ ጤና ክብካቤ የማስተርስ ፕሮግራም ውስጥ ማስተማር ቀጠሉ። በጊዜው ይሄንን ትምህርት የሚሰጡት ዶክተር ገበያው ብቻ ስለነበሩ ከአዲስ አበባ ደብረማርቆስ እየተመላለሱ አስተምረዋል።
በአንድ አጋጣሚ ወደ አዲስ አበባ ሲመለሱ ሁለት ተማሪዎች ጋር ተገናኙ። በእርሳቸው አማካኝነት ደብረማርቆስ የተከፈተውን አዲስ ፕሮግራም ለመከታተል እየተመላለሱ የሚማሩ ተማሪዎች መሆናቸውን አጫወቷቸው። ተማሪዎቹ በመንግስት ስራ ላይ ያሉ የጤና ባለሙያዎች ናቸው። ይሄ ትምህርት የሚሰጠው በወቅቱ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ብቻ ነው። በዛን ዓመት ከተመዘገቡት 800 ተማሪዎች መካከል 100 ወስዶ ሌሎቹን አልተቀበለም። በዚህ ምክንያት ሰፊ የትምህርት እድል አለመኖሩን በመስማታቸው በዚህም መነሻነት ይህን ፕሮግራም አዲስ አበባ ላይ እንዲከፈት አደረግሁ ሲሉ ይጠቅሳሉ።
ምክር ለወጣቱ
ዶክተር ገበያው ወጣትነት ማንነት ለእራስ የሚገለጥበት፣ ለማወቅ ከፍተኛ ጉጉት የሚታይበት እምቅ ሀይል ባለቤት መሆኑንም ይረዳሉ። ይህ ሃይል ለጥቅም የሚውለው ግን ትክክለኛውን ስብእናና አስተሳሰብና ወጣቱ ሲጨብጥና የመልካም እሴቶቻችን ባለቤት ሲሆን ነው ይላሉ። ከተሞክሯቸውም ሆነ ከንባቦቻቸው እንደተረዱት የእያንዳንዱ ሰው ማንነትና የወደፊት ተስፋ 90 በመቶ የሚወስነው በራሱ ነው። የሌሎች ተጽዕኖ ያለው ጫና ከ 10 በመቶ እንደማይበልጥ የሚከተለውን አባባል ጠቅሰው ይናገራሉ። ለዚህም ነው በአንድ ወይም በተመሳሳይ ችግር ውስጥ የገቡ ሁለት የተለያዩ ሰዎች ለአንደኛው ችግሩ የመወጣጫ መሰላል ሲሆነው ለሌላው ደግሞ ወደታች መውረጃ ሸርተቴ የሚሆነው ይላሉ። ችግራችን በእራሱ ችግሩ ሳይሆን ችግሩን የምንገነዘብበትና ምላሽ የምንሰጥበት አመለካከት እንደሆነም ይገልፃሉ። ስለዚህ ወጣቱ የተሻለ ሆኖ ለመገኘት ዋነኛውን ሚና የሚጫወተው እራሱ መሆኑን አውቆ አመለካከቱን በመቀየር ለለውጥ መትጋት አለበት ሲሉ ይመክራሉ።
እንደ ዶክተሩ ገለፃ፤ ወጣቱ ሊገነዘበው የሚገባው በአሁኑ ሰአት ፖለቲካ፣ ስልጣንና በተለይም በዘውግ ላይ የተመሰረተ ፉክክር ነው። ይህ ደግሞ ቀላል የማይባል ቁጥር ያለውን የወጣቱን ጉልበት እያባከነ ይገኛል፤ ወጣቱ የሚወስዳቸው እርምጃዎችም ማህበረሰቡንም ሆነ አገርን ወደ ኋላ የሚጎትቱ እንጂ ወደፊት የሚወስዱ አይደለም። ትኩረቱ ወደ ምጣኔ ሃብት ላይ ቢሆን ኖሮ ብዙ ለውጦችን ማስመዝገብ ይቻል ነበር። በእንግሊዝ አገር ሄነሪ ስምንተኛ የተባለ ንጉስ ምሁራንን ጠርቶ ‹‹ሀያል እንድሆን ምን ላድርግ ሲላቸዉ›› በምላሹ ‹‹በመጀመሪያ ሀብት ፍጠር እርሱም ሃያል ያደርግሀል›› ይህም ሀይል እንደገና ሀብትን ይፈጥርልሀል እንዳሉት ሲነገር ይሰማል። ስለዚህ ለወጣቱ በቅድሚያ ትኩረቱን በምጣኔ ሃብት እድገት ማድረግ አለበት።
አያይዘውም አሁን ያለን ደካማ ምጣኔ ሃብት፣ ፍትሀዊ ያልሆነ የሀብት ክፍፍል ብሎም የማህበራዊ ህይወት መዋቅሮችና ስርዓቶች (Social Infrastructures) ባልበለጸጉባት ኢትዮጵያ ነው። ችግሩ ሰፊና ውስብስብ ነው። ወጣቱም በርካታ ያልተሙዋሉለት ጉዳዮች አሉት። ሆኖም ግን ክፍተቶችን ለመሙላትም ሆነ ጥያቄዎቹ እንዲመለሱ ጥያቄውን በህግ አግባብ መጠየቅ፣ ሰላማዊ ትግል ማድረግና ችግሩ ውስብስብ ከመሆኑም አኳያ የመፍትሄውም አካል ለመሆን መዘጋጀት ይኖርበታል። ከጥፋትና በሀይል ከሚወሰድ እርምጃ የሚገኝ ጥቅምም ሆነ ለውጥ የለም። ይልቁንም ያለውን ደካማ ኢኮኖሚ የባሰ ወደቁልቁለት ይዞት ይሄዳል። ስለዚህ ለጥፋት የሚያነሳሳ ነገር ሲመጣ ለምን? እንዴት? ምክንያቱ ምንድንነው? ውጤቱስ ምን ይሆናል? ብሎ መጠየቅ ይኖርበታል። ‹‹እህ›› ብሎ በማሰብና በማሰላሰልና ውጤቱን በጸጋ ለመቀበል መዘጋጀት ግድ ይላል።
የደስታ ዘመን
‹‹በህይወቴ በጣም የተደሰትኩባቸውም፤ በጣም ያዘንኩባቸውም ጉዳዮችና ዘመኖች አሉ›› የሚሉት ዶክተር ገበያው፤ ነገር ግን በጣም የተደሰቱባቸው እንደ ሰው ከወህኒ ቤት ሲወጡ፤ ከሞት በመትረፋቸው ነው። የሰው ልጅ አካሉ ቢታሰር ሀሳቡ አይታሰርምና ከዚያም በኋላ ህይወት እንዳለ ያስቡና ተስፋ ያደርጉ ነበር። በትውስታውም ደስታቸው እጥፍ ድርብ ይሆናል። የራሳችንን መቀበሪያ ጉድጓድ ቀን ላይ ስንቆፍር እንውላለን በማለትም፤ ሌሊት በዚያ ጉድጉዋድ የሚቀበሩ ሰዎች ስም በመስኮት ይጠራል ይላሉ። በጊዜው እርሳቸው መቼ እንደሚጠሩ እንደማያውቁትም ይገልፃሉ። ይሄን የስቃይ ዘመን አልፈው ለመፈታት በመቻላቸውና በህይወት በመትረፋቸው ደስተኛ ናቸው። በዚያ በተቆፈረ ጉድጉዋድ የገቡትንና አገር ያጣቻቸውን በርካታ የአገር ሃብቶች ሲያስቡ ደግሞ እስካሁን ጥልቅ ሀዘን ይሰማቸዋል።
‹‹በእርግጥ ያን የወህኒ ዘመንም በአግባቡ እንደኖርኩት አስባለሁ ችግሩ ከባድ ይሁን እንጂ የማንነቴ መሰረት የተጣለበትና ችግሩ ለእኔ የህይወቴ መሰላል ሆኖኝ ወደከፍታ የወጣሁበት ስለነበር ታላቅ ትዝታ አለኝ›› በማለትም፤ የሰው ልጅ ሁልጊዜም ላለፈው ዘመኑ ካልተጸጸተ፣ የአሁኑን ጊዜውን በእርካታና በምስጋና በአግባቡ ከኖረ እና ነገውን ደግሞ ካልፈራ ፍሬአማ ህይወት፣ ለሌሎች የሚተርፍ ህይወትና በመከራም ውስጥ ሆኖ በደስታ የሚኖር ይሆናል ይላሉ። አራት ኪሎ ሸማ ሲሰሩ ከዋሉ በኋላ ወገባቸውን ለማፍታታትና የሰውነት እንቅስቃሴ ለማድረግ በእግራቸው ፒያሳ ደርሰው ይመለሳሉ። አይተውት የማላውቁትን ወይም ገብተውበት የማያውቁትን የሰው መኪና በመንገድ ላይ እያዩ፣ የልብስና የጫማ ሱቅ በመስኮት እየጎበኙ መግዛትና መልበስና ማድረግ ያማይችሉትን ልብስና ጫማ በመስኮት እያዩ፣ እጅግ ደስ ይላቸው ነበር። በብዙ ስቃይ ውስጥ ቢያልፉም ሁልጊዜ የነበሩበትን ደረጃ በጣም ነው የሚወዱትና የሚያመሰግኑት። አሁን ያላቸው ደስታ ያኔ ሸማ እየሰሩ ወይም የቀን ስራ እየሰሩ የሚያገኙትን ያህል ነው።
ቀጣዩ ራዕይ
እንግዳችን ዛሬ የደረሱበት የስኬት ማማ ላይ ቢገኙም ህዝብና አገርን የማገልገል ስብዕናቸው ግን አልረካም። አሁንም የማህበረሰብ ችግር ባዩበት ሁሉ መፍትሄ ይዞ ለመምጣት አያቅማሙም። አሁን በመምራት ላይ ያሉትን የጤና አገልግሎትና የስልጠና ተቋም ወደ ቴሪሻሪ ኬር ደረጃ ለማሳደግና በጤና አገልግሎት፣ በከፍተኛ ትምህርትና ምርምር በአፍሪካ ቀንድ የህክምና ቱሪዝም መዳረሻ እንዲሁም የልእቀት ማእከል ለማድረግ የሰባት ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ የማስፋፊያ ስራ ለመስራት በዝግጅት ላይ ይገኛሉ። በቅርብ ጊዜም ይህን ተግባራዊ ለማድረግ ቁርጠኛ መሆናቸውን ይናገራሉ። ወደ ውጭ አገር ለህክምና አገልግሎት ፍለጋ የሚሄዱትን የአገር ልጆች ብቻ ሳይሆን የአፍሪካ ቀንድ አገራትን ለማስተናገድ እንደሚችሉ በሙሉ ልብ ይናገራሉ።
ተደራሽ ያልሆኑ የህክምናና የምርመራ ዓይነቶችን ወደ ህዝቡ ደጃፍ ለማቅረብ ተግተው እየሰሩ የሚያነሱት እንግዳችን፤ ከመሰናክሉ ብዛት ስራዎች በፍጥነት ባይሄዱም እንደ ‹‹ኤም አር አይ እና ሲቲ ስካን›› የመሳሰሉና ሌሎችንም እጅግ ውድና አስፈላጊ መሳሪያዎችን በመያዝ መሰል መሳሪያ የሌሉባቸውን አምስት ከተሞች ለመድረስ የመጀመሪያውን ‹‹ባህር ዳር ንስር ዲያግኖቲክስ›› በሚል ስያሜ ማቋቋማቸውን ተናግረዋል።
ይህ ብቻ አይደለም ታታሪው ዶክተር ገበያው፤ የህጻናት መቀንጨር በስፋት የሚገኝባት ኢትዮጵያ አገራቸውን ችግር ለመፍታት በሚደረገው ርብርብ ላይ በመሳተፍ፤ በእንስሳት መኖር ምርት፣ የወተት ከብት እርባታና ተዋጽዖ ማቀነባበሪያ አግሮ ኢንዱስትሪው ለማቋቋም ጀምረዋል። ስለ ህይወት መንገዳቸውና አስተዋፆ በስተመጨረሻ እንዲህ በማለትም ይደመድማሉ ‹‹የህብረተሰብን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት ቁልፉ ማህበራዊ ግብ አለኝ››
የዝግጅት ክፍላችንም የዶክተር ገበያው ራዕይ ተቆነጠረ እንጂ አልተነካም ብሎ ያምናል። ስራቸውና አስተማሪ ሃሳባቸውን በሙሉ ለመግለፅ ያለን ቦታ ቢገድበን አባይን በጭልፋ ብለን ለዛሬው በዚህ አብቅተናል።
ሰላም!
አዲስ ዘመን ሐምሌ 26/2012
አልማዝ አያሌው