ማሸነፍና መሸነፍ በብዙ ነገር የሚለካ ቢሆንም የእኔ መነሻ ጉዳይ ወቅታዊ ስለሆነው የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ነው፡፡ ታላቁን የህዳሴ ግድብ በተመለከተ ከግብፅ፣ ከአሜሪካና ከአንዳንድ የግብጽ ደጋፊ ሀገራት በላይ በሀገራችን ያሉ ስልጣን ናፋቂዎች የሀሰት ፕሮፓጋንዳ እየነዙ በመንግሥትና በህዝብ መካከል መተማመን እንዳይኖር ሲወጡ ሲወርዱ ታይተዋል፡፡ ግብፅ የግድቡ ግንባታ እውን ከሆነ ወታደራዊ እርምጃ እወስዳለሁ ፤ማዕቀብ እንዲጣል እሰራለሁ እያለች ኢትዮጵያን ለማስፈራራት ሞክራለች።የጦር ሠራዊቷን፣ የጦር መሳሪያዋን ጭምር በመገናኛ ብዙኃን ስታስጎበኝ ከርማለች።አጋዥ አጋር ይሆኑኛል ላለቻቸው ዓለም አቀፍ ድርጅቶችና ሀገሮች ግድቡ እውን ከሆነ የግብፅ ስደተኞች ሀገራችሁን ያምሳሉ በማለት ጮሀለች።
አሜሪካም ብትሆን እርዳታ አቆማለሁ፤ እርዳታ የሚሰጡ ሀገሮች ላይም ማዕቀብ እጥላለሁ እያለች ግድቡን ለማጨናገፍ አብራ አሲራለች፡፡ ዓለም አቀፍ እርዳታ ለጋሽ ድርጅቶችም የብር ድጋፍ በመከልከል ለግብፅ ተባባሪነታቸውን ያሳዩት ገና የግድቡ ግንባታ ሳይጀመር ጀምሮ ነው።ይሄ ሁሉ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵ ያውያንን አላስደነበረም፤ አላንበረከከም። ይልቁንም የልብ ልብ ሰጣቸው ያለ ማንም ደጋፊና አጋዥ ግድቡን በራሳችን አቅም እንሰራዋለን የሚል ወኔ ታጠቁ። እንዳሉትም አድርገው አሳዩ።
‹‹ግመሎች ይሄዳሉ ውሾች ይጮሀሉ›› እንደሚባለው ይሄ ሁሉ ሴራ ኢትዮጵያ ካሰበችበት ለመድረስ አንድ ስንዝር ወደ ኋላ አላስቀራትም፡፡ ያለ ስጋትና መደናገጥ ግድቡን የታለመለት ቦታ ለማድረስ ኢትዮጵያውያን ታጥቀው ተነስተዋል፡፡ ማሳያውም የመጀመሪያውን የውሃ ሙሌት መጠናቀቅ ነው፡፡ 4 ነጥብ 9 ቢሊዮን ሜትር ኩዩቢክ ውሃ ታቁሯል፡፡
ግብጽ በሀገር ውስጥ ካኮረፉ ቡድኖች ጋር ሌት ተቀን በመስራት በግድቡ ላይ እክል ለመፍጠር ማማተሯ ግን አሁንም ሆነ ወደፊት አይቀሬ ነው። ምንም ይሁን ምን ግን ማን ያሸንፋል ከተባለ ያው እውነት ነዋ።እውነትን የያዘ በጋራ እንጠቀም ብሎ በቅንነት ለተነሳ ሁሉም ነገር ቀላል እንኳን ባይሆን አይከብድም።
ወደ ተነሳሁበት ልመለስ በህዳሴው ግድብ አለመጠናቀቅ ከግብጽ በላይ የሚያስደስታቸው የሀገራችን ባንዳዎች ቀድሞውንም የህዝቡን ስሜት ለማጨናገፍ አሲረዋል። ግድቡ ተሸጠ ብለው የሀሰት ፕሮፓጋንዳ ነዝተዋል። አብዛኛው ሀገር ወዳድ ግን የህዳሴው ግድብ ውሃ መያዙን በይፋ የምንሰማው መቼ ይሆን እያሉ እያንዳንዱን ቀን፣ደቂቃና ሰከንድ በንቃትና በጉጉት ሲጠብቁ ቆይተዋል። በተቃራኒው በህዳሴው ግድብ ውሃ ሙሌት ጋር በተያያዘ አሉታዊ ዜና ለመስማት ደቂቃዎችን በናፍቆት የሚጠብቁ እንደነበሩ አንዘነጋም። ምክንያቱም ተሸጠ ያለ ባንዳ የመጀመሪያው ዙር ውሃ ሙሌት በድል ተጠናቀቀ የሚለውን ቢሰማም አይቀበለውም።
የአንድ ሀገር ህዝብ የተለያየ የሀሳብ ልዩነት መኖር ወግ ነው፡፡ ሰው ሁሉ ከአንድ የጠርሙስ ፋብሪካ የወጣ እቃ አይደለምና የሀሳብ ልዩነት ፣ የርዕዮተ ዓለም ተለያይነት ሊኖር ይችላል፤ ደግሞም ይገባል። ግን በሀገር ልማትና ሉአላዊነት ላይ መደራደር ይቅርታ የሌለው ነው፡፡
አሁንም እነዚህ ባንዳዎች ዓይናችንን ግንባር ያድርገው ብለው እያሉ ነው። ከግድቡ ተርፎ በአናቱ ላይ ውሃ ሲተም እያየን አትመኑ ይሉናል።ፕሮጀክት ጨርሶ የማያውቅ ሀገር እንዴት ብሎ እያሉ ሊያሳምኑ ይሞክራሉ፣ ለማንኛውም ህዝብ ቀድሟላ። ጃል አትጃጃል የተነገረውን ብቻ ማድመጥ ድሮ ቀርቷል። አሁን ግራ ቀኙን ያያል፣ የተለያየ መገናኛ ብዙኃን ይከታተላል እንጂ ግመል ጎታችና ተከታይ ግመል የለም። የህዳሴ ግድባችን እያለቀ ነው። ቀሪውን ሥራ ደግሞ በሶስት ዓመታቱ እናጠናቅቃለን። ባንዳዎች ኩም በሉ።አሁንም ግመሎች ይሄዳሉ ውሾች ጩኸቱን ይቀጥላሉ።
አዲስ ዘመን ሐምሌ 26/2012
ሞገስ ፀጋዬ