እንደመግቢያ
‹‹ስትሪንግ አርት›› የተጀመረው በቀደምት ዘመናት በህንዳዊያን እንደሆነ ይነገራል። ስትሪንግ አርት የመስሪያ ጣውላ፣ ክር እና ሚስማር እንደግብዓት በመጠቀም የሚሰራ ሲሆን ሁለት ዓይነት ስትሪንግ አርት አለ። ጂኦሜትሪካል ስትሪንግ አርት እና ነፃ ስትሪንግ አርት (Free hand) ናቸው። ጂኦሜትሪካል ስትሪንግ አርት የሚባለው ጂኦሜትሪን ( circle, ellipse, rectangle and triangle) እና ክሮችን በተለያየ pattern (ፎርሙላ) በማጣመር የተለየዩ ቅርጽ እና ምስሎችን የመፍጠር ሂደት ነው። Free hand ስትሪንግ አርት የምንለው የፈለግነውን ጽሁፍ ምስል እና አርማ የተለየ ፎርሙላ ሳንጠቀም ያንኑ ምስል በክር እና ሚስማር በመጥቀም የመስራት ሂደት ነው።
በአሁኑ ወቅት ሁለቱም የጥበብ ሥራዎች በሰፊው የሚዘወተሩ ሲሆን በዓለም ዙሪያ ከፍተኛ ተቀባይነት ማግኘት ችለዋል። ይሁንና ኢትዮጵያን ጨምሮ በበርካታ አገራት ዕድገት አላሳየም። በአንዳንድ አገራት ደግሞ እጅግ በረቀቀ ደረጃ ተመንድጎ ከፍተኛ ገቢ የሚገኝበትና በርካታዎች ሥራ ዕድል የሚፈጠርበት የጥበብ ዘርፍ ነው። ዛሬ ‹‹እንዲህም ይኖራል›› አምድ የሥራ ጫና ሲበዛበትና መጨናነቅ ሲበረታበት ራሱን ዘና ለማድረግ ‹‹youtube›› ላይ ገብቶ የተወሰኑ ቪዲዮዎችን ሲመለከት ‹‹ስትሪንግ አርት›› ድንገት ቀልቡን ስቦት በኋላ ከነብስያው ጋር አዋህዶት የህይወቱ አካል ስላደረገው አንድ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ምህንድስና መምህር በጥቂቱ እንዳስሳለን።
ሕይወት በቢሾፍቱ
አማኑኤል ለሚ ቢራ ይባላል። ተወልዶ ያደገው በቀድሞ አጠራሩ ‹‹ደብረዘይት›› የአሁኗ ‹‹ቢሾፍቱ›› ከተማ ቀበሌ 05 ልዩ ስሙ እጥቤ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ነው። የመጀመሪያ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በአፄ ልብነ ድንግል ትምህርት ቤት የተማረ ሲሆን፤ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ደግሞ በቢሾፍቱ መሰናዶ ትምህርት ቤት ተከታትሏል። ከዚህ በኋላ ወደ ከፍትኛ ትምህርት ተቋም ተሸጋግሮ የሚፈልገውን እውቀት ቀሰመ። ከትምህርት ጋር የገባውን ውል አጠናከረ። የመጀመሪያ ዲግሪውንም ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በሲቪል ምህንድስና በጥሩ ውጤት አጠናቀቀ። አሁንም ከትምህርት ጋር ያለውን ወዳጅነት እያጠናከረ መጣ። ሁለተኛ ዲግሪው ደግሞ በስትራክቸራል ምህንድስና ተመረቀ። ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ በተማረበት አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ‹‹በሌክቸረርነት›› እያገለገለ ይገኛል። በትምህርቱ ጎበዝ ከሚባሉ ተማሪዎች ተርታ የሚመደብ ሲሆን ከሰዎችም ጋር በእጅጉ ተግባቢ ነው፤ አክብሮትንና ትህትናን በሰፊው ተላብሷል ይሉታል በቅርበት የሚያውቁት ጓደኞቹ።
አማኑኤል እና ጥበብ
በ2009 ዓ.ም የማስተርስ ትምህርቱን እየተከታተለ በነበረበት ወቅት ትምህርት እና ስራ አንድ ላይ ሲደመሩ የሚፈጥሩት ጭንቀት እንዳለ ሆኖ የጥናታዊ ጽሁፍ ሲጨመርበት ደግሞ ጭንቀቱ ይጨምራል። በዚህ የተነሳ አማኑኤል ከራሱ ጋር መነጋገር ይጀምራል። ጊዜውን ሲያስታውሰው ‹‹ራሴን ለማዝናናት youtube መጠቀም አዘወትር ነበር። ካየኋዋቸው ቪዲዮዎች ውስጥ ቀልቤን የሳበው ስትሪንግ አርት የሚሰራበት ቪዲዮ ነበር። እናም ከሱ ጋር የተገናኙ ፊልሞችን ደጋግሜ መመልከት ጀመርኩ። በሥራው ተመስጬ ስለነበር ራሴን በደንብ አስተማርኩ ደጋግሜ በመስራትም ይህን ድንቅ ጥበብ ተለማመድኩኝ። በኢንጂነሪንግ ዘርፍ መማሬ የተሰሩ ሥራዎችን አሠራር በቀላሉ ለመረዳት ረድቶኛል። ራሴን በደንብ ካስተማርኩ በኋላ የምሰራቸውን ሥራዎች ለሰዎች በስጦታ በመስጠት እና በመሽጥ ለሰዎች በደንብ ማስተዋወቅ ጀመርኩኝ።›› ሲል የነበረውን ሁኔታ ያስታውሳል። ታዲያ ማህበራዊ ሚዲያንና ዘመን የወለዳቸውን ቴክኖሎጂን በአግባቡ በመጠቀምና ከዚያ የሚገኘውን መልካም እውቀት በማጎልበት ሌሎችን መጥቀም እንደሚቻል በተግባር አሳየሁ፤ ሌሎችም ይህን መንገድ ቢከተሉ ሲል ይመክራል። አማኑኤል በአሁኑ ወቅት ባለትዳር እና የአንድ ወንድ ልጅ አባት ሲሆን ጥበብን እየተጠበባት ቤተሰቡንም በጥበብ እያዝናና እንደሚኖርና ይህም ለቤተሰቡ ተጨማሪ ደስታ እንደሆነም ይነገራል።
ስትሪንግ አርት
አሁን በአሁኑ ወቅት በጣም ጥሩ በሚባል ደረጃ እና ጥራት ለእይታ የሚማርኩ ሥራዎችን በመስራት ለግለሰቦች፣ ለሆቴሎች እና ለተቋማት እየሰራ ይገኛል። ‹‹ሰዎች እንዲሰራላቸው የሚፈልጉትንም ሆነ እኔ የሚያስደስቱኝን ሥራዎች ሃገራዊ ቀለማትን በተላበሰ እና ኢትዮጵያዊ ገጽታን አላብሼ እየሰራሁ ለጊዜው በ ዲቲ የህትመት እና ማስታወቂያ ሽያጭ ቢሮ ስራዎቼን ለገበያ እያቀረብኩ እገኛለሁ ይላል። በቅርቡም ከወንድሜ እና ባለቤቴ ጋር በመሆን የራሳችንን መሸጫ ሱቅ በመክፈት የተለያዩ የሥዕል እና ስትሪንግ አርት ሥራዎችን የምናቀርብበት ሁኔታ እያመቻቸን እንገኛለን።›› ከዚህ በተጨማሪም ሥራውን ከቤተሰብ በዘለለ በርካቶች ተጠቃሚ እንዲሆኑ በሂደት ሌሎች እውቀቱን ቀስመው የኑሯቸው መሠረት እንዲሆን፤ ጥበቡም በኢትዮጵውያንም እንዲለመድ በሰፊው የመሥራት ሰፊ እቅድ እንዳለው ይናገራል።
ኢትዮጵያ ምን ትጠቀማለች?
እንደ አማኑኤል ሃሳብ፤ በሃገራችን አብዛኛው ማህበረሰብ ወጣት መሆኑ ይታወቃል እናም ያለውን የኢንተርኔት አጠቃቀም ከመዝናኛ የዘለለ አይደለም። ነገር ግን ያለውን ጊዜ እና ሃብት በአግባቡ በመጠቀም ራሱን ብዙ ሙያዎች ማስተማር ይቻላል። እንደዚህ ዓይነት ሙያዎች ደግሞ ተደጋጋሚ ልምምድን እንጂ የተለየ ተሰጥዖ ስለማይፈልጉ ወጣቱ ጊዜውን አልባሌ ቦታ ከማጥፋት በተጨማሪ የራሱን እሴት በመጨመር የራሱን ገቢ ማመንጨት ይችላል። ከዚሀም ባለፈ ሃገራዊ የሆኑ ቀለሞችን በመጠቀም ውበትን እና ኢትዮጵያዊነትን በማጣመር ሃገራችንን ልክ እንደ ስዕል ሁሉ በዓለም አቀፍ ደረጃ ማስተዋወቅ ይቻላል። ይህን ለማድረግ ግን ከምንም በላይ ተነሳሽነትና በማናቸውም ሥራ የመለወጥ ዕድል እንዳለ በሚገባ መረዳት ያስፈልጋል ባይ ነው።
ማህበራዊ ሚዲያን በብልሃት
አማኑኤል በመጀመሪያ ስራዎቹን በቀላሉ ለማስረዳት አልተቻለውም ነበር። ወደ ገበያ ለመውጣትም በእጅጉ ፈተና ሆኖበት ነበር፤ ነገር ግን ማህበራዊ ሚዲያን በመጠቀም በርካታ ተከታዮችንና አድናቂዎችን አለፍ ሲል ደንበኞችን ማፍራት እንደሚችል አሰበ። እያለም ሥራዎችን ማየት እና ማዘዝ ለሚፈልጉ በፌስቡክ sontera string art እንዲሁም በቴሌግራም @vernadit ላይ ማግኘት እንደሚችሉ አስተዋወቀ። ይህ ነገር በሂደት ተቀባይነት እያገኘ መጣ። የጥበብ ውጤቶቹንም የሚፈልጉ ደንበኞቹ መበራከት ጀመሩ። ‹‹እንዲህም ይኖራል፤ እንዲህም መላ ይዘየዳል›› ሲል ጥረቱ ውጤት እያፈራ መሆኑን ተገነዘበ።
ፈተናዎች
ሙያው በሃገራችን እምብዛም ያልታወቅ በመሆኑ ሰዎች ለስዕል ያላቸው አመለካከት ያህል ለስትሪንግ አርት የላቸውም ይላል። ይህ ደግሞ ሥራዎችን ሰዎች በቀላሉ እንዲረዱ ለማድረግ አስቸጋሪ ያደርገዋል። እናም ማህበረሰቡ ለሙያው ያለው አመለካከት የተሻለ እንዲሆን በተለያዩ መንገዶች ማስተዋወቅ ያስፈልጋል። የኮሮና ወረርሽኝ እንደጠፋ (ስጋቱ እንድቀነሰ) ሙያውን በደንብ ለማስተዋወቅ ከጓደኛው ተሾመ ኃይሉ ጋር በመሆን የስትሪንግ አርት ኤግዚቢሽን ለማዘጋጀትም ውጥን እንዳላቸው ይነገራል። በዚህም በርካታ ሰዎች ሁኔታውን ሲረዱ ወደ ጥበቡ ይሳባሉ የሚል ተስፋ አሳድሯል።
ምሥጋና
ወጣት አማኑኤል ይህን ጥበብ በአንድ ወቅት ከጭንቀት ለመገላገል ብሎ ማህበራዊ ሚዲያዎችን ሲያስስ አጋጣሚውን ወደ መልካም ሁኔታ በመቀየር ዛሬ ላይ መድረሱን ይነገራል። ይሁንና ይህን ሥራውን የተመለከቱ ቤተሰቦቹ ደግሞ ድጋፋቸው አልነጠፈም። ይልቁንም እነርሱም በሥራው ተስበው አጋዥ እና አድናቂ ሆነውለታል። አባቱ አቶ ለሚ ቢራ እና እናቱ ትዕግስት ተሰማ የአብራካቸው ክፋይ ራሱን በራሱ አስተምሮ ሌላ ተጨማሪ እውቀት በመቅሰሙ ደስታቸው እጥፍ ድርብ ነው። የትዳር አጋሩ ኤልሳቤጥም በተቻላት ሁሉ ሥራውን በማገዝ ከአጠገቡ ናት። እርሷም በጥበቡ እየተመሰጠች በሥራውም እየተደነቀች የብርታት ተምሳሌት ሆነዋለች። ወንድሞቹ ዮሴፍ እና ብሩክ እንዲሁም ብቸኛዋ እህቱ ቬርናዲት ለሚ እና ጓደኛው ተሾመ ኃይሉ በእያንዳንዱ ሥራዎቹና እንቅስቃሴ ላይ የብርታት፣ ሞራልና ፅናት ተምሳሌት ሆነው ሥራውን በበለጠ እንዲያሳድግ አብረውት ስለሆኑ ሊመሠገኑ ይገባል ይላል፤ ለእርሱ ጥረት ተጨማሪ ብርታት ስለሆኑለት።
ቀጣይ ዕቅዶች
አማኑኤል ወደፊት ከሚያስባቸው ነገሮች ውስጥ በማህበረሰቡ ዘንድ በቂ የሆነ ስትሪንግ አርት ዕውቀት እንዲኖር እና ለስዕል የሚሰጠውን ዓይነት አመለካከት ለስትሪንግ አርት እንዲሰጠው ማስቻል ነው። ይህንንም ለማድረግ ተደጋጋሚ የሆኑ ኤግዚቢሽን በማዘጋጀት የስትሪንግ አርትን ተቀባይነት የተሻለ እንዲሆን ማስቻል ነው። ለዚህም መልካም አስተዋፅኦ ማበርከት የሚችሉ አካላት ጋር ተቀራርቦ ለመሥራት ዝግጁ መሆኑን ይናገራል። ‹‹ድር ቢያብር አንበሳ ያስር›› እንደሚባለው፤ በመተባበርና በመመካከር ጥበቡን ወደላቀ ደረጃ ማሸጋገር ይቻላል የሚል ፅኑ እምነት አለው።
አዲስ ዘመን ሐምሌ 25 ቀን 2012 ዓ.ም
ክፍለዮሐንስ አንበርብር