አብዛኛውን ጊዜ በመኪና፣ በጀልባ እና በአየር ጉዞዎችን ስናደርግ አንዳንድ ሰዎች ላይ የማቅለሽለሽ ሁኔታዎች ሲያጋጥም ወዲያውም ሁኔታው በፍጥነት ወደ ማስመለስ ሲለወጥ እናያለን፤ በድንገትም “ፌስታል፣ ፌስታል የያዘ ሰው” የሚል የተለመደ ጥሪ እንሰማለን፤ እንደ ራስ ምታት ያሉ ሌሎች የጤና ችግሮችም ተያይዘው ሲያጋጥሙ ይስተዋላል፤ ይህ ሁኔታ የታማሚውን ስነልቦና የሚረብሽ እንዲሁም አብረው የሚጓዙ ሰዎችንም ምቾት የሚነሳ ሆኖ ይገኛል፤ በተለይ በታክሲና ከአገር አገር በሚደረጉ የሕዝብ መጓጓዣ አገልግሎቶች ላይ በስፋት ሲያጋጥም ይታያል፤ ጉዞ ላይ የሚጋጥም ሕመምና ምቾት ማጣት አንዳንዶችን ለምን ያጋጥማል? አንዳንዶችን ደግሞ ለምን ምንም አይላቸውም ?
በእንቅስቃሴ ምክንያት የሚፈጠር ህመም (motion sickness)
“ሰዎች በአውሮፕላን፣ በመኪና ወይም በጀልባዎች ጉዞ ሲያደርጉ፣ በአንዳንድ የመዝናኛ አሽከርካሪ ማጫወቻዎች ሲዝናኑ፣ የማስመለስና የማቅለሽለሽ፣ የማላብ እንዲሁም አጠቃላይ የሰውነት ምቾት ማጣት ያጋጥማቸዋል፤ ይህ ሁኔታ በአጠቃላይ በእንቅስቃሴ ምክንያት የሚፈጠር ህመም (motion sickness) ይባላል።”
መነሻ አእምሮአችን ከአካባቢውና ከእንቅስቃሴያችን ከሚያገኘው የተለያየ መረጃ በመነሳት የት አካባቢ እንደምንገኝ ለመወሰን ስራ ይሰራል፤ እነኝህ መረጃዎች በእይታ፣ ከውስጠ ጆሮ ከሚገኝ የሰውነት ሚዛን ጠባቂ አካልና ከሌሎች ምንጮች የሚገኙ ናቸው። ማንኛውንም እንቅስቃሴ ስናደርግ አእምሯችን እንቅስቃሴያችንን ስርዓተ ነርቭን በመጠቀም በሦሥት መንገዶች በኩል ሊረዳ ይችላል፤ አንደኛ፣ በውስጠ ጆሮ በኩል በሚላክ የሚዛን ጠባቂ ሲግናል (እንቅስቃሴ (sensing motion)፣ ጥድፊያ (acceleration) እና ስበት (gravity) ላይ በሚፈጠሩ ለውጦች፤ ሁለተኛ፣ ከእይታ የሚገኝ መረጃ (vision) በመጠቀም እና ሦሥተኛ፣ ከሰውነታችን ውጫዊ አካል ጠለቅ ብለው ከሚገኙ ሕብረ ህዋሶች ጠቃሚ አቋም (proprioceptors) የሚገኙ ናቸው።
ከውስጠ ጆሮ የሚገኝ የሰውነት ሚዛን ጠባቂ አካል
ሰውነታችንን በፍቃዳችን አዘነው እንቅስቃሴ ስናደርግ፣ ለምሳሌ በመንገድ ላይ ስንራመድ፣ አእምሯችን ከሦሥቱም መንገዶች የሚያገኛቸው መረጃዎች ተመሳሳይ ናቸው፤ ማለትም በእንቅስቃሴ ላይ ነህ የሚል ነው፤ በመሆኑም መረጃዎቹ ሳይጣረሱ ወጥነት ባለው ሁኔታ ያለዝንፈት መራመድ እንድንችል የሚያስችሉ ናቸው፤ ነገር ግን ያለኛ ቀጥተኛ ተሳትፎ ወይም ፍቃድ የምናደርጋቸውን እንቅስቃሴዎች፣ ለምሳሌ በመኪና ተሳፍሮ መጓዝ ወቅት፣ አእምሯችን የተመለከትናቸውን በሦሥት መንገዶች የሚገኙ መረጃዎችን አቀናብሮ ወጥ መረጃ ማግኘት ይቸግረዋል፤ ከሦሥቱ መንገዶች የሚያገኛቸው መረጃዎች መጣረስ ያሳዩታል፤ ለምሳሌ በውስጠ ጆሮ ያለው ሚዛን ጠባቂ አካለ ክፍል፣ ለአንጎል በእንቅስቃሴ ላይ አይደለህም የሚል ሲግናል ሊያስተላለፍ ይችላል፤ አንጎል ከእይታ የሚያገኘው መረጃ ደግሞ በእንቅስቃሴ ላይ ነህ የሚል ይሆናል፤ ይህ መጣረስ ነው እንግዲህ በጉዞ ወቅት ለሚያጋጥሙን ማስመለስ፣ ማቅለሽለሽና ምቾት ማጣት እንደምክንያት የሚወሰደው። ይህ ጥናት የታወቀው በውስጠ ጆሮአችን የሚገኙት እንቅስቃሴን የሚከታተሉ አባል አካላት በሌሉበት ወይም በመድኃኒት በተጨቆኑበት ሁኔታ እንቅስቃሴ ሲደረግ ያጋጥሙ የነበሩ ችግሮች አለማጋጠማቸው ነው።
ሰውነታችንን በፍቃዳችን አዘነው እንቅስቃሴ ስናደርግ በጉዞ ወቅት የሚያጋጥመን ማስመለስና ምቾት ማጣት መንስኤው ምንድ ነው?
የጤና እክሉ የሚፈጠረው እንቅስቃሴ ስናደርግ በውስጠ ጆሮአችን ያለ ሚዛንን የሚጠብቅ ስርዓት፣ እንዲሁም ከአካባቢያችን በእይታና በሌሎች መንገዶች የምናገኛቸው ሌሎች መረጃዎች፣ ለአንጎል ተጣርሰው መልዕክት ሆነው ሲደርሱት ነው። ለምሳሌ በፒስታ መንገዶች ላይ ጉዞዎችን ስናደርግ መኪናው ደፋ ቀና ማለት ያበዛል፤ ነገር ግን በመኪናው ውስጥ ያሉ ነገሮች አይንቀሳቀሱም፤ ከመኪናው ውጪ ክልል ስናማትር ደግሞ በእንቅስቃሴ እየተዘዋወርን እንደሆነ ይሰማናል፤ በሌላ አነጋገር በዐይናችን እንቅስቃሴን እያየን፣ ነገር ግን ውስጠ ጆሮአችን ውስጥ የሚፈጠረው ስሜት ማለትም ወደ አንጎላችን የሚላከው ሲግናል እየተንቀሳቀስን እንዳልሆነ የሚጠቁም ሲሆን ሰውነት ምቾት ያጣል። በመሆኑም የማቅለሽለሽና የማስመለስ ስሜቱ ይፈጠራል። አንዳንድ ሁኔታዎችም አሉ፤ ለምሳሌ አእምሮአችን በእይታ የሚያገኘው መረጃ፣ በጉዞ ወቅት ምቾት ማጣትን ለማስከተሉ ዝቅ ያለ ግምት ይሰጠዋል፤ ምክንያቱ ደግሞ የዐይን ብርሃን የሌላቸው ሰዎችም ችግሩ ስለሚጋጥማቸው፤ ይህ ሁኔታ ደግሞ የሚያሳየው ችግሩ ከእንቅስቃሴ ጋር የተያያዘና ውስብስብ መሆኑን ነው።
አብዛኞቻችን በመኪና (በየብስ)፣ በአየር እና በውኃ አካላት ላይ ጉዞዎችን ስናደርግ ለምን ያስመልሰናል? ለምን ምቾት እናጣለን? መፍትሔስ አለው ወይ?
ከሦሥቱ የመረጃ ምንጮች አእምሮ ስለእንቅስቃሴ የሚያገኘው የተጣረሰ መረጃ በአእምሮ ውስጥ እንዲሁም በስርዓተ ነርቭ ላይ ሲግናሎችን ወይም መረጃዎችን በሚያሳልጡ የኬሚካል እና የሆርሞን ውሕድ መጠን ወይም ልኬት ላይ የሚወሰን እንደሆነ የጥናት ውጤቶች ያሳያሉ፤ ሰውነታችን የሚለቃቸው በነርቭ ስርዓት ላይ የሚካሄዱ የመልዕክት ልውውጦች ላይ ተፅእኖ የሚፈጥሩ እነኝህ ኬሚካሎችና ሆርሞን ማለትም ሂስታሚን (histamine)፣ አሲቲልኮሊን (acetylcholine) እና ኒሮፒነፕሪን (norepinephrine) ሲሆኑ በምንገኝበት ዘመን በጉዞ ወቅት ለሚያጋጥሙ ምቾት ማጣቶች የሚታዘዙ መድኃኒቶች በአንጎል ውስጥ የነኝህን ኬሚካሎች ወይም ሆርሞን ሚዛን በመጠበቅ ሁኔታው እንዳይፈጠር የሚያደርጉ ናቸው። ምክንያቱም የነኝህ ውሕዶች ከፍዝቅ ነው የጤና መቃወሱን የሚፈጥረው። “ውስጠ ጆሮአችን ወይም ውስብስቢት (labyrinth) ሚዛንን ለመጠበቅ የሚያግዝ እንዲሁም በእንቅስቃሴ ወቅት ከቦታ ጋር ዝምድና የሚፈጥርልን የአካል ክፍል ነው። ይህ አካላችን በጉዞዎች ወቅት አብዛኛውን ግዜ ተፅእኖዎች ያጋጥሙታል።”
በጉዞ ወቅት የሚያጋጥሙ ምቾት ማጣቶችና የጤና እክሎች የሚያሳዩት ምልክት
በጉዞዎች ላይ ለሚያጋጥም ሕመም የሚታዩ ስሜቶችና ምልክቶች ማቅለሽለሽ፣ ማስመለስ፣ መጫጫን፣ ማዞር፣ ላበት፣ ማጥወልወል ወይም ሽቅብ ማለት እና ጠቅላላ ምቾት የሚነሳ ስሜት ናቸው። ከነዚህ በተጨማሪ ደግሞ አልፎ አልፎ ማዛጋትና ራስምታት ሊኖር ይችላል፤ ሲጠና ደግሞ የምራቅ መብዛት፣ የሰውነት መገርጣትና የለሃጭ መዝረብረብ ሊኖር ይችላል፤ የትንፋሽ ማጠርም ሌላው ምልክት ነው። ከዚህ በፊት እንዳየነው እነኝህ ስሜቶችና ምልክቶች ምክንያታቸው የነርቭ ስርዓታችን በአንድ ሁኔታ ላይ፣ ለምሳሌ ጉዞ ስናደርግ፣ በተለያዩ መንገዶች የሚጣረስ መረጃ ለአንጎል ሲያደርሰው እንደሆነ ተገንዝበናል፤ ማለትም ከውስጠ ጆሮአችን፣ ከእይታችን፣ በቆዳ ወይም ሰውነታችን ላይ በሚያጋጥም የሁኔታዎች ለውጥ እንዲሁም በተጨማሪ በመጋጠሚያና በጡንቻ አካላት ስሜት ተቀባዮች ላይ በሚኖር ለውጦች እንደሆነ አውቀናል።
“የሚሰሙ ስሜቶች ስንል ታማሚ የሚገልፃቸው ሲሆኑ፣ የሚታዩ ምልክቶች ደግሞ ሌላ ሰው ወይም ሐኪም በታማሚ ላይ የሚያስተውላቸው ሁኔታዎች ናቸው፤ ለምሳሌ ማቅለሽለሽ ስንል ስሜትን የሚገልፅ ነው፤ ማስመለስ ወይም የዐይን ብሌን መስፋት ስንል ግን ሐኪም በማየት የሚያስተውለው ምልክት ነው።”
በጉዞ ወቅት ያጋጠመን ሕመም በጉዞ ምክንያት የተፈጠረብን መሆኑ እንዴት ይለያል?
የጤና ችግሩ የሚያጋጥመው በእንቅስቃሴ ምክንያት በሚፈጠሩ ለውጦች በመሆኑ፣ የላብራቶሪ ምርመራ አስፈላጊ አይሆንም፤ መለየት የምንችለው ስሜቶቻችንን በማድመጥና ምልክቶችን በማየት ነው፤ ይህንን ሁኔታ ለይተን ካወቅን የሕክምና ባለሙያዎች የሚስማማንን መድኃኒት ሊሰጡን ይችላሉ። በጉዞ ወቅት የሚጋጥመን ሕመም አብዛኛውን ጊዜ ለክፉ የማይሰጥና ጉዞው ሲያበቃ የሚተው ነው፤ ነገር ግን ጉዞ ካበቃም በኋላ ሁኔታው የሚጠና ከሆነ በተለይ በጆሮ፣ ሚዛንን በመጠበቅና በነርቭ ስርዓት ላይ ብቁ የሆኑ ሐኪሞች ጋር መታየት ያስፈልጋል።
ሁኔታውን የምንከላከልበት መንገድ አለ ወይ?
የጤና ችግሩን ከሚፈጥሩ ምክንያቶች ውስጥ አንደኛው እይታ ነው፤ በመሆኑም የእይታ ሁኔታን ማስተካከል ችግሩ እንዳይፈጠር ይረዳል፤ ይኸውም እይታችን በጉዞአችን አቅጣጫ መሆኑን ማረጋገጥ አለብን፤ በሌላ አነጋገር በምንጓዝበት አቅጣጫ የሚገኘውን አድማስ አሻግሮ በመስታዎቱ መስኮት መመልከት ማለት ነው። ይህ ሁኔታ ጉዞአችን በምናየው አቅጣጫ መሆኑንን ለአንጎላችን ያረጋግጥለታል፤ በተለይ ችግሩ ያለበት ሰው ከመኪና ፊት ለፊት ወንበር (ገቢና) ላይ መቀመጥ ተመራጭ ነው፤ ምክንያቱም የመረጃውን መጣረስ ይቀርፋል። ጉዟችን በምሽትና በጀልባ ወይም መርከብ ላይ ከሆነ፣ ዐይንን በመጨፈን ሸለብታ ውስጥ ለመግባት መሞከር ሊረዳን ይችላል፤ ምክንያቱም በእይታና በውስጠ ጆሮአችን መካከል የሚፈጠረውን የሲግናል መጣረስ ማስቀረት ይቻላል። በተጨማሪም ሸለብታ በስነልቦና ምክንያት እየጎላ የሚመጣውን “ሊያመኝ ነው” የሚል በማሰብ የሚባባስ ስሜት ሊያስቀር ይችላል። ሌላኛው ስሜቱን የሚቀንስ ተግባር መስቲካ ማኘክ ነው፤ መስቲካ ስሜትን በመጋራት የሚባባሱ የጉዞ ሕመም ስሜቶችን የማለዘብ አቅም አለው። ከመስቲካ በተጨማሪም ቀለል ያሉ ደረቅ ብስኩቶች፣ ቀዝቀዝ ያሉ መጠጦች ሁኔታውን የማረጋጋት አቅም አላቸው፤ በተጨማሪም ነፋሻማ አየር በመጠኑም ቢሆን የሚረዳበት ሁኔታ አለ።
ሁኔታውን የምንከላከልበት መንገድ አለ ወይ
በጉዞ ምክንያት የሚያጋጥም የጤና ችግር አብዛኛውን ጊዜ ጉዞውን ስናቆም ይተወናል፤ ነገር ግን ይህ ሁኔታ አንዳንዶች ላይ ላይሰራ ይችላል፤ ምክንያቱም ሁኔታው ፀንቶባቸው ከጉዞ በኋላም ለተወሰኑ ቀናቶች ከስሜቱና ከምልክቱ ጋር የሚቆዩ ሰዎች አሉ። እንዲህ ያለ ሁኔታ ሲያጋጥም እስክናገግም ፈሳሽ በብዛት መውሰድና እረፍት ማድረግ ጥሩ መፍትሔ ነው።
ዝንጅብል
ዝንጅብል በጉዞ ወቅት የሚያጋጥሙ ምቾት የማጣት ሕመሞችን እንደሚቀንስ በጥናት ተረጋግጧል፤ በመሆኑም በዝንጅብል ጣዕም የተዘጋጁ መስቲካዎች ወይም ለምለም የሆነ ዝንጅብል ማኘክ በብዙ ሊረዳ ይችላል። ከዚህ በተጨማሪም ከመዳፋችን ስር የሚገኘውን አካባቢ ደጋግሞ ማሻሸት እንደሚረዳ ሌሎች ጥናቶች ያመለክታሉ፤ ግልፅ ምክንያቱ ያልታወቀ ቢሆንም። ዝንጅብል በጉዞ ወቅት የሚያጋጥሙ ምቾት የማጣት ሕመሞችን እንደሚቀንስ በጥናት ተረጋግጧል
ቀድሞ መከላከል
በጉዞ ወቅት በመኪና ውስጥ ገቢና ወይም ከፊት በመቀመጥ ዐይን በጉዞ አቅጣጫ አሻግሮ ወደ አድማሱ እንዲያማትር ማድረግ፤ አንጎል ላይ የሚፈጠረውን የመረጃ መጣረስ ሊያስቀር ስለሚችል ሁነኛ ዘዴ ነው። ምክንያቱም ይህንን ካደረግን ውስጠ ጆሮ፣ ሰውነታችን እና እይታችን ሁሉም ተመሳሳይ መረጃ ለአንጎል ስለሚያደርሱ የመጣረስ ሁኔታ ላይፈጠር ይችላል። በጀልባ ላይ ከሆንን ደግሞ ከፍ ያለ ወለል ላይ በመቀመጥ ወደ አድማሱ አርቆና አሻግሮ ማማተር ሁኔታው እንዳይከሰት ያደርጋል፤ በአውሮፕላን የምንጓዝ ከሆነ ደግሞ ከመስታወት መስኮት ጋር በመቀመጥ ወደ ውጭ መመልከት ይረዳል። በጉዞ ወቅት የሚያጋጥም የጤና ችግር ያለብን ከሆነ መጽሐፍ ለማንበብ መሞከር የለብንም፤ እንዲሁም ፊታችንን ከጉዞ አቅጣጫ በተቃራኒ አድርገን መቀመጥ የለብንም፤ ሌሎች ተመሳሳይ ችግር ያለባቸው ሰዎች አብረውን የሚጓዙ ከሆነ ልናያቸው ወይም ልናናግራቸው መሞከር የለብንም፤ ምክንያቱም ሁኔታው ከእይታ በሚመጣ ስነልቦና ችግር ሊባባስብን ይችላል። ማንኛውንም መጥፎም ሆነ ጥሩ የሆነ ጠንካራ ሽታ ያላቸውን ነገሮች፣ ቅመምና ቅባት የበዛቸው ምግቦች፣ ከጉዞ በፊትም ሆነ በጉዞ ወቅት መመገብ የለብንም።
የጉዞ መድኃኒቶችን መጠቀም
በጉዞ ላይ ለሚያጋጥሙ ሕመሞች መድኃኒቶችን ከጉዞ በፊት መጠቀም ሊረዳን ይችላል፤ ሁኔታውን ለመከላከል የተለያዩ ብዙ መድኃኒቶች ያሉ ሲሆን የመድኃኒት ባለሙያን በማማከር ሊወሰዱ ይችላሉ። እነኝህ መድኃኒቶች ለጉዞ የሚጠቅሙን ቢሆንም የራሳቸው የሆነም የጎንዮሽ ስሜቶች አላቸው።
ጉዞ ላይ ለሚያጋጥሙ ሕመሞች መድኃኒቶችን ከጉዞ በፊት መጠቀም ሊረዳን ይችላል
ስኮፖላሚን (Scopolamine (Transderm Scop)፡- ይህ መድኃኒት አብዛኛውን ጊዜ በጉዞ ወቅት ለሚያጋጥሙ ሕመሞች የሚታዘዝ መድኃኒት ነው፤ መድኃኒቱ መወሰድ ያለበት ምልክቶች መታየት ከመጀመራቸው በፊት ቀድሞ መሆን አለበት። ይህ መድኃኒት ውጤቱ እስከ ሦሥት ቀን ሊዘልቅ ይችላል። በተለይ ለረዥም ጉዞዎች ተመራጭ ነው።
ፕሮሚታዚን (Promethazine (Phenergan))፡- ከጉዞ በፊት 2 ሰዓታት ቀድሞ መወሰድ አለበት፤ ውጤቱ ከ6-8 ሰዓታት ሊቆይ ይችላል።
ሜክሊዚን (Meclizine (Bonine)፡- ከጉዞ በፊት አንድ ሰዓት ቀድሞ ቢወሰድ ውጤታማ ነው፤ ይህ መድኃኒት እድሜያቸው ከ12 ዓመት በታች ለሆኑ ሕፃናት አይሰጥም።
ሳይክሊዚን (Cyclizine (Marezine))፡- ውጤታማ የሚሆነው ቢያንስ ከጉዞ በፊት ከ30 ደቂቃ ቀድሞ ነው፤ እድሜያቸው ከ6 ዓመት በታች ለሆኑ ሕፃናት አይሰጥም።
ማስታወሻ
ማቅለሽለሽ በራሱ በሽታ አይደለም፤ ነገር ግን የአንዳች ያልታወቀ የጤና ችግር ሁኔታ ምልክት ተደርጎ ይወሰዳል፤ ምክንያቱም ማቅለሽለሽና ማስመለስ ከ700 በላይ ለሚሆኑ የጤና እክሎች ምልክት ሊሆኑ ይችላሉ፤ ለምሳሌ የምግብ መመረዝ፣ ማይግሬን፣ የሃሞት ጠጠር፣ የእርግዝና ጅማሬ፣ የቫይረስ ወይም የባክቴሪያ ልክፍት፣ ፍርሃት፣ መርዛማ ንጥረነገሮች ወይም የስሜት መረበሽ ሊሆን ይችላል፤ ከነዚህ ሁኔታዎች ለየት ባለ ሁኔታ ግን በመኪና፣ በአየር ወይም በጀልባ ጉዞዎችን ሲያደርጉ የማቅለሽለሽና የማስመለስ ሁኔታ ያጋጥማል፤ በመሆኑም አንዳንድ ረዘም ያሉ የማቅለሽለሽና የማስመለስ ስሜቶችን ሐኪም ዘንድ ጎራ በማለት ምንጫቸውን ማወቅ ጥሩ ልማድ ነው።
አዲስ ዘመን ሐምሌ 25 ቀን 2012 ዓ.ም