ቀኑ እንደማንኛውም ቀን ነው፤ ምሽቱም እንዲሁ የተለየ ስሜት የለውም። አለወትሮዬ ማታ ቴሌቪዥን በቤታችን አልተከፈተም። ቤተሰቡ እርስ በእርሱ እየተጫወተ ነው። ቀን በሥራ ድካም የዛለውን ሰውነቴን ሶፋው ላይ እንዳሳረፍኩና ትንሹ የልጄ ልጅ ጭኔ ላይ እንቅልፍ እንደወሰደው እኔም ሸለብ አደረገኝና በባለቤቴ ቅስቀሳ ወደ መኝታዬ አለፍኩ። ሁለት ጊዜ ከሩቅ የሚሰማ በሚመስል ድምጽ ባንኔ ተመልሼ ተኝቻለሁ፤ በቃ።
ንጋት ላይ ግን ሻሸመኔ ያስነሳችኝ በሚያሳዝንና በሚዘገንን ድምጽ ነው። ወጥቼ በረንዳዬ ላይ ስቆም ከየትላልቁ ፎቅ የሚትጎለጎለው ጪስ አየሩን ይዞታል በለቅሶ እና ዋይታ የታጀበ የዘፈንና ለቅሶ ድምጽ አየሩን ሰቅዞ ይዞታል። አልቃሽም እኛ አስለቃሽም እኛ መሆናችንን ያወቅሁት ዘግይቼ ነው። ወደመኝታ ክፍል ተመልሼ ልብሶቼን ለባብሼ ስወጣ አትውጣ የሚል ተማጽኖ ተነገረኝ።
ምን መሆንሽ ነው ወላጆቼ እኔን የወለዱበት እኔም ልጆቼን የወለድኩበት የሶስት ትውልድ ሰንሰለት የሆነችው ከተማ ሻሸመኔዬ ዓይኔ ስር እየነደደች ነው እና ዝም ብዬ ልቀመጥና እሳቱ ደርሶ የእኛን ቤት እስኪበላ ልጠብቅ እንዴ። ምን እያላችሁ ነው? አልኩኝ ወደባለቤቴ ዞሬ። አሁን ለጡረታ በሚያበቃ እድሜ ላይ ነኝ። ከጡረታዬ በፊት ልሂድና ቢሮዬንም ትምህርት ቤቱንም ልየው አልኳት። በጣም በሚያሳዝን ሁኔታ ፊቷ በእንባ ተሞልቶ የጋሽ ጸጋዬ ልጅ እኮ ንጋቱ አካባቢ ላይ ደውላልኝ ነበረ። አንተ ደክሞህ እንደመጣህ ተኝተሃልና ማረፍ ይገባሃል ብዬ ነው ዝም ያልኩህ ስትለኝ፣ ምን ሆነው ነው የደወሉት፣ ስል ጠየቅኳት። ህንጻው እየጋየ ነው፤ የሰው ያለህ እያለች ነበረ፤ እየጮኸች እናም ምን ልናደርግ እንደምንችል ባስብ ባሰላስል አልመጣልሽ ሲለኝ፣ ሳልነግርህ ተውኩት፤ ስትል መለሰችልኝ ። ልክ አይደለሽም፤ ልክ አይደለሽም፤ አልኳት። መለስ አድርጋ እርሱን በኋላ እናያለን ብላኝ ወደቤት ተመለሰች። እግሬ ወዳደረሰኝ ወደ አፖስቶ ሰፈር ሄድኩኝ። ወደከተማው መውጫ አካባቢ ወዳለው ሰፈር ነው የሄድኩት። በቃል ለመግለጽ በሚያስፈራ ሁኔታ ሻሸመኔ ትላልቅ መዶሻ በያዙ ማፍረሻ በታጠቁ ቤንዚንና መድፍ በተኮሱ የጠላት ወታደሮችና የሌላ ዓለም ፍጥረታት የተወረረች ይመስል ሌት ከንጋት ስትፈራርስ አድራ ሶሪያን መስላለች። አንድ ጋዜጠኛ እንዳለው የሶሪያዋን ኤሌፖ ከተማን መስላ በአንድ አዳር አገኘኋት።
ለካስ መስራት እንጂ ማፍረስ ዘመንን አይጠይቅም፤ ለካስ መገንባት እንጂ ማውደም ሰዓታት አይጠይቅም፤ ለካስ መጠገን እንጂ መስበር ደቂቃ አይጠይቅም፤ ለካስ ፍቅር እንጂ መፋረስን የጸብ ምክንያትም አቅምም አይጠይቅም። ይችው በልጅነቴ የቦረቅኩባት፤ ከጓደኞቼ ጋር ትምህርት ቤት የነጎድኩባት፣ ተልክን ከሱቅና ከዘመድ ቤት እቃ ያመጣንባት፣ ሰዓት ሳያግደን ትራፊክ ሳያቆመን የቦረቅንበት ሜዳ ውሉ ባልታወቀ የጥላቻ ፈረስ በሚነዳ ወገን እየፈረሰች አደረች። እንባዬን መቆጣጠር አቃተኝ፤ እልህ ውስጤን ረበሸው፤ ተስፋዬ ሁሉ ፊቴ ሲከነበል ታየኝ።
ሻሸመኔ ተወልዶ ያደገ፣ የሻሸመኔን ማደግ የሚናፍቅ የሻሸመኔ ፍቅር ያለው ሰው፣ መቼም ቢሆን መች፣ እንዲህ ዓይነቱን ጥፋት አይፈጽምም። ምክንያቱም ከተማው ስታድግ የምታቀርብለት የአቅርቦት አማራጭ አለዋ፤ ከተማው ስታድግ ሥራ አጥነት ቦታ አይኖረውማ፤ ከተማው ስታድግ በነበረው ላይ የጨመረ ስፋትና ድምቀት ይኖራታላ። ይህንን የማይመኝ ማነው? በብዙ ዓመታት ማለትም ሰላሳና አርባ ዓመታት የተደከመባት የሶስትና አራት ሌሎች የሐገር ክፍሎች መገናኛና መለያያ ከተማ፤ የብዙ የሐገር ውስጥና የውጭ ቋንቋዎች መናኸሪያዋ ሻሸመኔ፣ ደማቋና ሽሙንሙኗ ሻሸመኔ ድባቅ ተመታች። እና ማን መታት ? አንድ ነገር እርግጠኛ ነኝ፤ ሻሸመኔ ነገን ተስፋ በሚያደርጉ ባተሌ የኢትዮጵያ ልጆች ላብና ጥረት እንጂ በማንም ትእዛዝ ያልተቋቋመች ከተማ ነች። ስትኖር ያኖሯትና የኖሩባት፣ ስትጠፋ ደግሞ የሚያዝኑላት ከተማቸው ነች።
በዚህ ቅጥና ዓላማ የለሽ ጥፋት የሚያተርፈው ወገን ማንም ይሁን ማን ከተማዋን ከዜሮ ጀምሮ ለመገንባት አስቦ ከሆነ ገራሚ ነው። አውዳሚው መንፈሱ መቼም ከተማ ሰሪ እና አበልጻጊ አይደለምና። ሻሸመኔ የኦሮሞው፣ የአማራው የወላይታው፣ የጉራጌው፣ የትግሬውና የካምባታው ብቻ ሳትሆን በቆዳ ቀለም የነጩና ጥቁሩ፣ በባህል ከኩሽ እስከሴማዊና የካሪቢያን ሰዎች ወግ ድረስ ያዳቀለች፣ ድንበር አልባ የጥሮሰሪና ግሮ አዳሪ ብዙኃን አገር ነች። ሻሸመኔ “ተገብቶ ምንጠፍቶ” የሚባልላት ጥሬ ከብስል ከየአቅጣጫው ገብቶ የእህል ኬሚስትሪ የሚሰራባት የወጥ ወጥዋጮች የሚቀምሙባት፣ የባህል ጠቢባን ከደቡብ ከሰሜን ከመሐል ሐገር ተጠብበው ፍሬያቸውን ለወጪ ገቢው የሚያቀርቡባት መሬት ነች።
እና ምን ነካትና ነው፣ “አንተ ከእኛ አይደለህም፤ አንተ ከዚያ ነህ፤ “ የሚያባብል አጋንንት ሰለጠናባትና የእጇን ውጤት በአንድ አዳር አፍርሳው በውስን ሰዓት አቡንናው አደረች፤ ይባላል። ይህንን የነገረኝ ግርማ ፈይሣ (ለዚህ ዝግጅት ስሙ ለወጥ የተደረገ) የተሰኘ የድሮ የአባቴ የትምህርት ቤት ጓደኛው ነው። መጫወቻውን ሳይፈልግ የተነጠቀ ልጅ ተኝቶ እንደሚያሰማው የእልህና ቁጭት ሳግ ድምጽ ደጋግሞ ይሰማበት ነበረ። አሁንም አሁንም ደጋግሞ ይህ ነገር እንደሚመጣ እንዴት ሳላውቀው ቀረ? እኔስ ውስጤ ለምን ተዘናጋ? ብዙ ጊዜ እኮ ጥፋትና ውድመት ሊመጣ ሲል፤ የመኪና አደጋ እንኳን ሊያጋጥመኝ ሲል፤ የሚነግረኝ “መንፈስ” ነበረ። ምነው ቀልቤ ከላዬ ራቀና ከተማዬ ድንገት ከእጄ ላይ አምልጣኝ አደረች፤ አለና በረዥሙ ተንፍሶ ቀና ሲል እንባ ባይኖቹ ላይ ግጥም ብለው ነበረ። ተመልሶ አንገቱን ደፋ። ምነው፣ ስቅስቅ ብሎ ባለቀሰና በወጣለት ብዬ ተመኘሁ። ማባበል አልቻልኩም፤ ሰውን እንዴት በዚህ ጉዳይ ያባብሉታል። አልጋና መደብ እኮ አይደለም የፈረሰው። ከተማ ነው፤ በአንድ አዳር ፈርሶ ያደረው። ምንም አይደል፤ ቻለው በቃ፤ ይባላል?
ይህንን የአባቴን የትምህርት ቤት ጓደኛ ያገኘሁት ከረዥም ዓመት በኋላ ነው። የመኖሪያ ቤታቸውና የንግድ ሱቃቸው ተቃጥሎ፣ ባዷቸውን ቀርተው ወደ ሐዋሳ ከተማ ሸሽተው የመጡ አብሮ ኗሪዎቹን ሊያጽናና መጥቶ ነው ያገኘሁት። (ስሜን ጠርቶ) ስማ፣ እኔ ሳልጽናና እንዴት ነው፤ ሰው የማጽናናው አለኝ፤ ፈርጠም ብሎ። መከራ እስኪያልፍ ነው የሚያለፋው፤ አልኩት። ቀጠል አድርጎም ሻሸመኔ እኮ ልዩ ናት። ደሃ ሳይበላ የማያድርባት፤ ድሃ ሳይለብስ የማይታረዝባት ልዩ ከተማ ናት። አእምሮውን የሳተ ዕብድ፣ ካልሆነ በስተቀር ሻሸመኔ ላይ ሰው በርዶት ማደሪያ አያጣም፤ ርቦት ምግብ አይቸግረውም እኮ። አሁን ግን ከተማዬን ሰው ራባት፤ ሰው ራቃት። ቀጥሎ ምን እንደሚሆን መገመት አልችልም፤ የረበሹትም ያስረበሹትም ወገኖች ይህንን ፈልገው ከሆነ “እንኳን ደስ አላቸው” በዚህ ቃጠሎና ውድመት፣ የሚያተርፉት ፖለቲካዊ እሴትም ሆነ ድል ግን አትጠራጠር፤ የለም። በመግደል አሸናፊነት፣ በማውደም አናጺነት አይታሰብም። ምናልባትም የሰራው ሰው ነው፤ ያፈረሰው ሰው ነው፤ የሚገነባውም ሰው ነው፤ ሊሉ ይችሉ ይሆናል፤ ይሁንናም በነበረው ላይ በሥርዓት አፍርሶ በመገንባት፣ ደምሮ በማሳደግና አውድሞ በመገንባት መካከል ትልቅ ልዩነት አለ። አሁን ባለው መጠነ ሰፊ ውድመት ላይ ከተማዋን ለማቆም ከማሰብ ይልቅ፤ ሌላ ሻሸመኔ ሌላ ስፍራ መገንባት ይቀላል። የሃጫሉ ሞት የቀና ወጣት ሞት ነው፤ ቀና ሰው ሲሞት ለህይወት እንጂ ለሞት እንዴት ይነሳሷል።
አዎ፣ በከተሞች አገነባብ ወይ አመሰራረት ሀ-ሁ ወይም (ኮርስ 101) ላይ ከተሞች በሌጣ ወይም አንድ ህዝብ ብቻ አይገነቡም። በአንድ ህዝብ፣ በባለ አንድ ቋንቋ፣ በባለ አንድ ባህል ሰዎች የተገነቡ ከተሞች፣ በየትኛውም የዓለም ክፍል የለም፤ አይገኝምም። ታላላቆቹ የዓለም ከተሞቻችን ዓለምአቀፋዊ መልክ መነሻ ዓለምአቀፋዊ አተያይና የባህል መስተጋብር ውጤት ነው። ገበያና ከተማ አንድ ናቸው፤ አንድ ገበያ እንኳን፣ ድንች ይዞ በመጣ ነጋዴ ብቻ አይቆምም፤ ከድንቹ ሌላ ቃሪያው፣ ሽንኩርቱ፣ ጤፉ፣ ሜጣጢሱ፣ ቦይናው፣ በርበሬው፣ ቅመሙ፣ በቆሎው፣ ጎመኑ፣ ካሮቱ፣ ሸንኮራው፣ ቲማቲሙ፣ የቀንድ ከብቱም ሆነ የጋማው በነጋዴውም በገበሬውም ተቋጥረውና ተጭነው መጥተው ነው፤ ገበያውን የሚያደምቁት። ህዝቡም ከማዶ ከሰፈሩ፤ ከሩቅም ከቅርብም፣ ከሰሜን ከደቡብ መጥቶ ነው፤ የሚገበያየው። እዚህ ላይ አንድ ግጥም ሐሳቤን ስለሚያጠናክርልኝ መዋስ ፈልጋለሁ።
“የፍቼው ነጋዴ ከብቱን ለከረዩ፣ የወለጋው ወርቁን ካልሸጠ ለትግራዩ፤ ጎጃም ጤፍ አቅርቦ ለባሌው ካልሸጠ፤ በማረቆ በርበሬ ወጡ ካልጣፈጠ፤ ያም ሰጥቶ ያም ዘርቶ ካልተቀባበለ፤ ሐገርና ህዝቡ ባንድ እንደምን ዋለ……?” እያለች ያንዳችንን ላንዳችን ገበያነት በማውሳት ትቀጥላለች። ይኼኛው ገበያ ያልሸፈነውን ሸቀጥ ቀጣዩ ገበያ እየሸፈነው፤ ይኼኛው ከተማ ያላቀረበውን እህል ሌላኛው ከተማና ልዩ ልዩ የህዝብ ወገን እንደባህልም እንደ ወግም እንደንግድ እንደ ስልትም አያቀረበው ነው፤ የሚነጋገዱት። በዚያ ላይ ግንኙነቱ ወደጋብቻና አምቻ ይዘልቃል፤ ፍቅርም ገበያ ነውና። ታዲያ ከተሞችም የዚያኑ ያህል ከልዩ ልዩ የዓለም ክፍል የቀረቡ ሸቀጦችን ብቻ ሳይሆንና ባህልንና ቋንቋን በማስተሳሰር ነው፤ የሚሰራው። ለንደን እኮ እንግሊዘኛ ይነገርበት እንጂ፣ የእንግሊዞች ብቻ አይደለችም፤ የአውሮፓውያኑ ሁሉ ናት፤ ፓሪስ የፈረንሳዮች ብቻ አይደለችም፣ የአውሮፓውያኑና የፍራንኮ ፎን እንዲሁም የአንግሎ ፎን ተናጋሪ ህዝቦች ሐገር ናት። የዓለም ህዝብ በአንድ ቃል ልቡ የሚቀልጥባት የፖለቲካ፣ የንግድና የማህበረሰብ ወግ መናኸሪያና ማቅለጫ እሳቷ ከተማ ደግሞ ኒውዮርክ ትባላለች። ኒውዮርክ ላይ የማይነገድ፣ የማይሰራና፣ የማይነገር፣ የማይቋጠርና የማይፈታ የዓለም ጉዳይ የለም። በአጭሩ አንድ ከተማ በአንድ ቋንቋ፣ በአንድ ሃይማኖት፣ በአንድ ወገንና ዘርም ብቻ፣ ብቻውን አይቋቋምም ለማለት ነው።
ሻሸመኔ ከነፈረሠ ቁመቷ ስትታይ ባለቤት የሌላት ወይም ተጠሪዎቿ አፍረው የተሸኮረመሙባትና ወሬሳ የዓመታት የመሰለችው ገዢዎቿ የኔ ናት ስላላሏት ብቻ አይደለም፤ ሁላችንም ተገቢ ድርሻችንን ስላልተወጣን ይመስለኛል። የከተማውም ሆነ የመስተዳድሩን ጣጣ ለአንድ ለተወሰነ ወገን ስለተውነው መከራ ሲመጣ እነርሱም ራሳቸውን ለማዳን ሸሹ። በዚህ ውስጥ ምናልባትም በዚህ የንብረት ውድመትና ዘረፋ የታሰበባቸው ሰነድ የማጥፋት እስረኛ የማስመለጥ፤ ሙከራዎች ሊኖሩ ችላሉ። በእነዚያም ሰነዶች መጥፋት ሳቢያ ባለቤትነትንና ባለንብረትንትን ለማድፈንፈን የታሰበ ተንኮልም ሊኖር ይችላል። ከፖለቲካዊ እሳቤና ከፖለቲካዊ ሸር ባለፈ የተወጠኑ ድብቅ ነገሮች ሊኖሩ ይችሉ ሆናል። እንዳይሆን ግን ጸልያለሁ፤ አበክሬ እመኛለሁ፤ ይህንንም ክፋት መጠርጠር አያስከፋም፤ የላቁ ተንኮሎችን በሩቁ ለማምከንም ይረዳ ይሆናል። ስመጥሩው፣ የሬጌ ሙዚቃ አቀንቃኝ ቦብ ማርሌይ፣ ወደኢትዮጵያ በመጣ ጊዜ ወደ ሻሸመኔ ጎራ ማለቱ ይጠቀሳል። እነዚህ ጃማይካውያን፣ እምነታቸው ምንም ኣይነት ይሁን፤ ዕይታቸው በምንም መንበር ላይ ይቀመጥ፤ ኢትዮጵያን ቅድስት ምድራችን ሲሏት ሻሸመኔን ደግሞ “እየሩሳሌማቸው” አድርገው እንደሚያስቧት ማሰብ ልብን ምንኛ ያሞቃል።
ይህንን የመማጸኛ ከተማነት፣ የመጠጊያ፣ የመጠለያ ብሩክ ስም ነው፤ ይህ ክፉ ነውጥ ሊነጥቃት በሯ ላይ የቆመው። እንዲያውም ከቦብ ማርሌይ ሐሳብ ሳልወጣ፤ “አንድ ሌሊት በሻሸመኔ” (One night in Shashmane) በሚለው ዜማው ላይ፣ ለሻሸመኔና ኢትዮጵያ የተቀኘው ቅኔ ላይ ሻሸመኔን፣ የመሰላት በጸጥታ፣ ሰላም፣ ፍቅር፣ መተሳሰብንና ህብረትን ማመላከቻ በማድረግ እና በማድነቅ ሌሊትሽ አጠረብኝ፤ ግን ሁሌ በውስጤ ይዝሻለሁ፤ ሻሸመኔ፤ ሲል ነው ያሞካሻት።
የሻሸመኔ ነዋሪዎች፣ ጓደኛዬና ቤተሰቡ እርሱን መሰልና የማይመስሉ ሻሸመኔያውያን ግን፣ ያችን የነውጥና የጩኸት ሌሊት ማግስቷና መሰንበቻዋ እንዴት እንደረዘሙባቸው ማሰብ ለማንም አያቅትም። ያ፣ ሁሉ ውድመት ግን ለማነው የሚሞቀው፤ ያ ሁሉ ቃጠሎ ግን ማንን ነው የሚደላው፤ ያ ሁሉ ዘረፋ ግን ማንን ነው የሚያደልበው።
አንዱ ንብረቱ ተዘርፎ፣ ቤቱ የተቃጠለበት የሻሸመኔ ሰው፣ 43 ዓመት ሙሉ ከሊስትሮ ጀምሬ ያፈራሁት የበርካታ ዘመናት ሀብት ፊቴ ላይ በአንድ አፍታ አመድ ሆነብኝ። መቼ እና በየትኛው እድሜዬ ነው፤ መልሼስ የምገነባው፤ ገንብቼስ ያለስጋት የምኖረው፣ እንዴት ነው ሲል ያጠይቃል። አስተኳሾቹ፣ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት እብሪተኞቹ የናዚ ወንጀለኞች ዓላማቸውን ለማሳካት ያደረጉትን ጥረት ካደረጉ በኋላ የያዟቸውን ከተሞች እየለቀቁ ሲሄዱ፣ ተመልሰን እንመጣለን እያሉ፣ እስከ በርሊን ድረስ መገፋታቸውን አያስቡትም ወይም አልሰሙ ይሆናልም። ከወረሯቸው ከተሞች ህዝብ ጋር የነበረው አኗኗራቸው የሚያስመልሳቸው ባይሆንም እየዛቱ ነበረ የሚለቁትና፤ ወደመቃብራቸውም በመጨረሻ የተገፉት።
እንመለሳለን ጠብቁን እያሉ ግን እየሸሹ ነበረ፤ የወጡት። በመጨረሻም በተባበሩት ሃይሎች (Allied Foreces) ከተማቸው ስትወረር፣ ራሳቸውን ያጠፉት አጠፉ፣ የቀሩት ደግሞ በበርሊን ፍርስራሽ ክምር ላይ ቆመው ነው፤ እጃቸውን የሰጡት። በማፍረስ መገንባትም መቆምም አይቻልም፤ እጅ መስጠትና ውርደት እንጂ፤ ታሪክም ያስተማረን ይህንኑ ነው። ሻሸመኔ አዎን መገንባቷ አይቀርም፤ ነገር ግን እንደቀደመው በሆነ መልክና እሳቤ፣ በተድፈነፈነ መንገድ ሳይሆን፣ ከተማዋን የሚያስተዳድረው ወገን የነዋሪው ደህንነት በሚያስጠብቅ ንቃትና በጀት የሚቆምና ከነዋሪው ጥፋት በፊት ራሱን ለማስቀደም የተዘጋጀና ቆራጥ መሆን ይጠበቅበታል።
ከተማ ስሙ ትልቅ ነው። ጥፋቱም የዚያን ያህል ገዝፎ ይሰማል። ሲያጠፉ ምህረትን ሳይሆን ተጠያቂነት ያለበት መሆኑን ጠንቅቆ የተገነዘበ ሰው ነው፤ ወደሃላፊነት ስፍራ መምጣት ያለበት። ያኔም ባለበት ተጠያቂነት ራሱን ለህግ አቅርቦ እንደሚጠየቅ ተጠባቂ፣ በመቁጠር ካልሰራ አጥፍቶም ተወድሶም ለመኖርና ለማደግ ከመጣ ግን “ውሃ ቢወቅጡት እንቦጭ” ነው፤ የሚሆንበት፤ የሚሆንብን። ልጅ ሆኜ ያነበብኩት አንድ ለአንድ ሰው የድጋፍ ደብዳቤ የተሰጠው የምስክርነት ወረቀት ግርም ይለኛል። አብረን ወደ ከፍተኛ ትምህርት ስንገባ የድጋፉ ደብዳቤና የትምህርት ማስረጃው አብሮ ይሰጠናል። እናም እንዲህ ይላል፤ ከረዥሙ ቀንጭቤ ሳቀርብላችሁ።
የድጋፍ የምስክር ወረቀት… ይልና “ጓድ እንትና የድጋፍ ደብዳቤ ለተመደቡበት የከፍተኛ ትምህርት ተቋም እንድንጽፍላቸው በጠየቁን መሰረት፣ ጓዱ በቀይ ሽብር ወቅት ሳያሰልሱ ትግሉን በማፋፋም የስታሊን በትር በአናርኪስቶችና ጠላቶች ላይ እንዲያርፍ ከጓዶች ጋር መፋለማቸውን እየገለጽን ይህንን የምስክርነት ወረቀት ሰጥተናቸዋል።”
ከፊርማው በታችም፣ ከስሩ በቀጭኑ እዛም አካባቢ አናርኪስት ካለ ጠቁሟቸውና በስታሊን በትር አቀጣቀጡን ያሳዩዋችኋል፤ የሚል ነገር ያለበት ይመስለኛል። ልጁ በኩራት ደብዳቤውን መያዙን አንድ በሉልኝ፤ ሁለትም መዝጋቢዎቹ ይህንን ደብዳቤ ሲያዩ ገራፊዎችና አብዮት ጠባቂዎች ካልሆኑ በስተቀር ባይንቀጠቀጡም ሳይቀፋቸው እንደማይቀር አስባለሁ። ጎንዶሮ … ሰው ሰው ገድያለሁ የሚል የድጋፍ ደብዳቤ ማስጻፉ አይገርምም? አሁንስ እነዚህኞቹ ያስጽፉ ይሆን? ፈጣሪዬ፣ ከዚህ አውዳሚ ወገን በወገን ላይ ከሚያስነሳ የፉከራ አዙሪት ሐገራችንን አውጣት። በጥፋቱ ከሚያቅራራ ወጣት ሰውረኝ ማለት የተገባ ይመስለኛል።
አዲስ ዘመን ሐምሌ 25 ቀን 2012 ዓ.ም