በኢትዮጵያ የንግድ ማህበረሰብ ውስጥ ስማቸው ጎልቶ ከሚጠሩ ሰዎች መካከል አንዱ ናቸው። በተለይም ደግሞ በግል ኢንሹራንስና ባንኮች ምስረታ ፈር ቀዳጅ እንደሆኑ ይነሳል። አቶ ዛፉ እየሱስ ወርቅ ዛፉ። ከዛሬ 83 ዓመታት በፊት መርሃቤቴ ዓለም ከተማ ዝቅ ብሎ በሚገኝ ማቁር በተባለ ቆላማ ስፍራ ነው የተወለዱት። ዕድሜያቸው ለትምህርት እንደደረሰ ኮራ ገዳማ በተባለ ቤተክርስቲያን ገብተው የቄስ ትምህርት ተምረዋል። በመቀጠልም ደሴ በሚገኙት ንጉሥ ሚኪካኤል እንዲሁም መምህር አካለወልድ ትምህርት ቤቶች የመጀመሪያ ትምህርታቸውን ተከታትለዋል። አዲስ አበባ ጀነራል ውንጌት ትምህርት ቤት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን የተማሩ ሲሆን፤ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በአስተዳደር የትምህርት መስክ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል። ከአሜሪካ ባገኙት ነፃ የትምህርት ዕድል በልማት ኢኮኖሚ ዘርፍ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን መሥራት ችለዋል።
ኢምፔሪያል ኢንሹራንስ ኩባንያ፤ ብሉናይል ኢንሹራንስና የኢትዮጵያ መድህን ድርጅት በተቀጣሪነትም ሆነ በመመስረት ካገለገሉባቸው የአገር ውስጥ ድርጅቶች መካከል ይጠቀሳሉ። በተለይም በአዲስ አበባና የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤቶች በሠሩባቸው ረጅም ዓመታት ለግሉ ዘርፍ ድምፅ ሆነው በመሥራት ከፍተኛ እውቅናን አካብተዋል። በሱዳንና ናይጂሪያ በሚገኙ ትላልቅ የኢንሹራንስ ኩባንያዎችም ለረጅም ዓመታት አገልገለዋል። ከደርግ መንግሥት ውድቀትን ተከትሎም ለግሉ ዘርፍ የተፈጠረውን ምቹ ዕድል በመጠቀም ህብረት ኢንሹራንስና ባንክን ከሌሎች ባለሀብቶች ጋር በመሆን በመመስረት ረገድ ስማቸው በግንባር ቀደምትነት ይጠራል። ከፋይናስ ዘርፉ በተጨማሪ በትምህርትና በግብርና ልማት ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋር በመተባበር መዋለንዋያቸውን በማፍሰስ ለአገራቸው ዕድገት የበኩላቸውን ሚና በመጫወት ላይ ይገኛሉ። የህብረት ኢንሹራንስና ባንክ መስራችና የቦርድ አመራር ከሆኑት ከአቶ ዛፉ እየሱስ ወርቅ ዛፉ በህይወት ተሞክሯቸውና በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ሰፊ ውይይት አድርገናል። እንደሚከተለው ይቀርባል።
አዲስ ዘመን፡- ዘመናዊ ትምህርት ከመማርዎ በፊት ዲያቆን እንደነበሩ ሰምቻለሁ፤ እስቲ የድቁና ህይወትዎ ምን ይመስል እንደነበር ያስታውሱን?
አቶ ዛፉ እየሱስወርቅ፡- በተወለድኩበት አካባቢ ዘመናዊ ትምህርት ቤት ባለመኖሩ ወላጆቼ በቤተክርስቲያን የቅስና ትምህርት እንድማር አደረጉኝ። ድቁናውን ተምሬ መቀደስ ከጀመርኩኝ በኋላ ግን አንድ ከእኔ ዕድሜ የጎለበተ ዲያቆን አዲስ አበባ ብንሄድ በተሻለ ክፍያ ማገልገል እንደምችል ይነግረኝና እሱን ተከትዬ ከወላጅ እናቴ ጠፍቼ አዲስ አበባ ገባሁ። ያን ጊዜ ታዲያ እናትና አባቴ ተለያይተው ስለነበር አባቴ ደሴ ነበር የሚኖረው። አዲስ አበባ ከገባን በኋላ ግን ይዞኝ የመጣው ዲያቆን ቤተዘመድ በእኔ መምጣት አለመደሰታቸውን አየሁና ጥዬ ወጣሁ። እናም ኑሮዬን አራዳ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን አደረኩኝ።
አዲስ ዘመን፡- በድቁና እያገለገሉ ማለት ነው?
አቶ ዛፉ እየሱስወርቅ፡- አይደለም፤ እንዳሰብነው በቤተክርስቲያኑ ማገልገል ቀላል አልሆነልንም። በመሆኑም ቀን ላይ እየለመንኩ ማታ ላይ እዚያው ደጀ ሰላም ነበር የማድረው። በዚያው በልመና ህይወት ጥቂት ጊዜ እንደቆየሁ የአባቴን ዘመዶች አገኘሁና ከእነሱ ጋር መኖር ጀመርኩ። ይሁንና በዘመዶቼ ቤት ውስጥ የምትኖር ሴት በጨዋታ መልክ ልታገባኝ እንደምትፈልግ ስትናገር ሰማሁና ድቁናዬን ልታፈርስብኝ ነው ብዬ በሁለት ቀን የእግር ጉዞ ወደ ተወለድኩበት ቀዬ ተመለስኩ። በአጋጣሚ ደግሞ የእኔን አዲስ አበባ መምጣት አባቴ ሰምቶ ኖሮ እኔን ፍለጋ ወደ አዲስ አበባ ይመጣል። እኔ ግን ወደ ተወለድኩበት አካባቢ ተመልሼ ስለነበር ልንገናኝ አልቻልንም። አባቴ በዚህ ተስፋ ሳይቆርጥ መርሃቤቴ ድርስ በመምጣት ይዞኝ ወደ ደሴ ገባ። እናም በአስር ዓመቴ ዘመናዊ ትምህርትን ንጉስ ሚካኤል ትምህርት ቤት ጀመርኩኝ። ፈጣንና ቅልጣፋ እንዲሁም ትምህርትም ቶሎ የሚገባኝ በመሆኑ በሁለት ዓመት ውስጥ አራተኛ ክፍልን አገባደድኩኝ። ከአምስተኛ ክፍል ጀምሮ ደግሞ መምህር አካለወልድ ትምህርት ቤት መማር የጀመርኩ ሲሆን፤ እዚያም በተመሳሳይ በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ ስምንተኛ ክፍል ለመጨረስ ቻልኩ። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን ግን አዲስ አበባ መጥቼ ጀነራል ውንጌት አዳሪ ትምህርት ቤት ነው የተከታተልኩት።
የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተና በከፍተኛ ውጤት ባልፍም ጫማ የሌለኝ በመሆኑ ሙጀሌ የበላውን እግሬን ማሳየት ስላሳፈረኝ እንዲሁም በእዚያ ዕድሜዬ ቦላሌ ሱሪ ለብሼ ዩኒቨርሲቲ መግባት አልዋጥልህ አለኝ። በመሆኑም ለአንድ ዓመት በአየር ኃይል ተቀጥሬ በሂሳብ ክፍል ፀሐፊነት አገለገልኩኝ። እቁብ ገብቼም ገንዘብ ቋጠርኩ። እንዳሰብኩትም ጫማና ልብሴን እንዲሁም የሚያስፈልገኝን ሁሉ ከገዛሁኝ በኋላ ዩኒቨርሲቲው ገባሁኝ። ሦስተኛ ዓመት ስደርስ ግን አሜሪካ ነፃ የትምህርት ዕድል ለአንድ ዓመት አገኘሁና አካውንቲንግ አጠናሁ። ተመልሼ ለመምጣት ፈርሜ ስለነበርም ቃሌን አክብሬ ወደአገሬ ተመለስኩና በዩኒቨርሲቲው የአራተኛ ዓመት ትምህርቴን ቀጠልኩኝ። ሆኖም በወቅቱ አካውንቲንግ ትምህርት አምስት ዓመት ከምቆይ ይልቅ በአስታዳደር የትምህርት መስክ ገብቼ በአራት ዓመት ለማጠናቀቅ ፈለኩና ማመልከቻ አስገባሁኝ። ውጤቴ ከፍተኛ በመሆኑ «ዕድል ይሰጠው» ተብዬ ተፈቀደልኝና በአስተዳደር ዘርፍ ተምሬ በከፍተኛ ማዕረግ ተመረቅሁኝ።
አዲስ ዘመን፡- በተማሩበት የትምህርት ዘርፍ ታዲያ ሥራ አገኙ?
አቶ ዛፉ እየሱስወርቅ፡- አዎ፤ እንደተመረቅሁኝ ኢምፔሪያል ኢንሹራንስ በተባለ በኋላ በደርግ ጊዜ በተወረሰ ኩባንያ ነው የተቀጠርኩት። ሁለት ዓመት ካገለገልኩኝ በኋላ ግን በድጋሚ ነፃ የትምህርት ዕድል አገኘሁና ወደ አሜሪካ ሄድኩኝ። በአንድ ዓመት ተኩል ጊዜ ውስጥ በልማት ኢኮኖሚ የማስተርስ ዲግሪዬን ይዤ ተመለሱኩኝ። ወደ ኢትዮጵያ ከመጣሁኝ በኋላ ግን በተማርኩት የትምህርት ዘርፍ የሚመጥን ሥራ ማግኘት አልቻልኩም። በመሆኑም መጀመሪያ እሠራበት ወደነበረው የኢንሹራንስ ኩባንያ ተመለስኩኝ። ከፍ ባለ ደመወዝና መኪና ተመድቦልኝ ለአንድ ዓመት አገለገልኩኝ። ከኩባንያው ከወጣሁ በኋላ ከባንክ ተበድሬ ብሉናይል ኢንሹራንስ የሚባል ኩባንያ አክሲዮን ገዝቼ ገባሁኝ። በእዚያም የኩባንያው ምክትል ዳይሬክተርና የቦርድ ፀሐፊ ሆኜ መሥራቴን ቀጠልኩኝ። ቤት ሠራሁኝ፤ ሚስት አገባሁኝ፤ ልጆችም አፈራሁ።
አዲስ ዘመን፡- አገርዎን ጥለው የተሰደዱበት ምክንያትስ ምን ነበር?
አቶ ዛፉ እየሱስወርቅ፡- የ1966 ዓ.ም የመንግሥት ለውጥ ተከትሎ ግን ብሉናይል ኢንሹራንስ ኩባንያ በመንግሥት እንዲወረስና አገር አቀፍ እንዲሆን ተደረገ። በድምሩ 13 ኩባንያዎች ነበሩ የተወረሱት። እነዚህን የተወረሱ ኩባንያዎች አንድ ማድርግ አለበት ተብሎ ስድስት ሰው ያለበት ኮሚቴ ተዋቀረ። እኔም በዚያ ኮሚቴ ውስጥ ተካትቼ በማደራጀት ሂደት ለስድስት ወር ከቆየሁ በኋላ የኢትዮጵያ መድህን ድርጅት ዋና ሥራአስፈፃሚ ሆኜ ተመደብኩኝ። ይሁንና በተቋሙ የቆየሁት በጣት የሚቆጠሩ ወራቶች ብቻ ነው። በአገሪቱ በነበረው የፖለቲካ ችግር ምክንያት ባለቤቴንና ልጆቼን ጥዬ በመተማ በማድረግ ሱዳን ገባሁኝ። ሱዳን ውስጥም በአንድ የኢንሹራንስ ኩባንያ ተቀጠርኩኝ። በውጭ አገራት የሚያውቁኝ አንዳንድ ሰዎች ግን ናይጄሪያ ባለው ኩባንያ እንድሠራ ጋበዙኝ። ናይጄሪያም ለሰባት ዓመታት ከሠራሁኝ በኋላ ስምንተኛው ዓመት ላይ የአፍሪካ የጠለፋ ዋስትና የሚባል ተቋም የአፍሪካ መንግሥታትና የአፍሪካ ልማት ባንክ ያቋቋሙት ዓለምአቀፍ ድርጅት ችግር ያጋጣመውና እኔ በዚያ ቦታ በአመራርነት እንድሠራ ጠየቁኝ። በወቅቱ ደግሞ የኢትዮጵያ መንግሥት ድጋፍ ያስፈልግ ስለነበርና እኔ ደግሞ በስደት የወጣሁኝ በመሆኑ መንግሥት «አልቃወምም» የሚል ማረጋገጫ እንዳጽፍ ተጠየኩኝ። የኢትዮጵያ መንግሥትም አለመቃወም ብቻ ሳይሆን ድጋፍ እንደሚያደርግልኝም የሚገልጽ ደብዳቤ ጻፈልኝና ተዋዳድሬ ገባሁኝ። በመጀመሪያዎቹ አምስት ዓመታት የኮንትራት ጊዜ ከሌሎች ባልደረቦቼ ጋር ባደረግነው ብርቱ ትግል ድርጅቱን ከመውደቅ ለማዳን ቻልን። በዚህ ብቻ ሳልወሰን ድርጅቱ የመንግሥታት ተቋም ሆኖ ብቻ መቀጠል የለበትም፤ የግሉ ዘርፍም መግባት አለበት በማለት ብዙ ተሟገትኩኝ። ሁለተኛውን አምስት ዓመት ኮንትራት ተሰጥቶኝ መሥራት እንደቀጠልኩኝ ሙግቴ ሰሚ አግኝቶ ባንኩ የመንግሥታት ብቻ ሳይሆን የበርካታ አፍሪካውያን ጭምር ለመሆን ቻለ። እናም ዛሬ ላይ በአፍሪካ ትልቁና ጠንካራው የኢንሹራንስ ኩባንያ ለመሆን በቃ።
አዲስ ዘመን፡- ወደ አገርዎ የተመለሱበትን አጋጣሚ ያስታውሱን?
አቶ ዛፉ እየሱስወርቅ፡- የደርግ መንግሥት ውድቀትን ተከትሎ ባለሀብቶችና በውጭ የሚኖሩ ዜጎች አገራቸው ገብተው እንዲያለሙ በቀረብልን ጥሪ መሰረት ነው ወደ አገሬ የተመለስኩት። እርግጥ ነው በመጀመሪያ ላይ ኢትዮጵያ ላለመመለስ አንገራግሬ ነበር። ሆኖም የቀድሞ ኢህአዴግ አመራሮች ቃል በገቡልኝ መሰረት ኢትዮጵያውያን በአገራቸው ውስጥ ኢንሹራንስ ኩባንያ መክፈት የሚችሉበትን ረቂቅ ህግ ላኩልኝ። በዚህ መሰረት ኮንትራቴ አንድ ዓመት እየቀረው አቋርጬ ወደ አገሬ ተመለስኩኝ። ከተመለስኩኝ በኋላ ግን ህጉ ቶሎ ተግባራዊ ባለመደረጉ ለጥቂት ጊዜ ጥናት ሳደርግ ቆየሁኝ። ይሁንና የግል ባንኮችና ኢንሹራንስ ኩባንያዎችን የማቋቋሚያው አዋጅ በወጣ በአስራ አምስት ቀናት ውስጥ ስብሰባ ጠርተው ጥቂት ባለሀብቶችን ይዘው ህብረት ኢንሹራንስን ለማቋቋም ሞከርን። ይህንን መሰረት በማድርግም ህብረት ባንክን ማቋቋም ቻልን።
አዲስ ዘመን፡- እስቲ አሁን ደግሞ የህዳሴ ግድብ የመጀመሪያው ዙር የውሃ ሙሌት በስኬት መጠናቀቁ የፈጠሮቦትን ስሜት ይግለጹልን?
አቶ ዛፉ እየሱስወርቅ፡- በመጀመሪያ ለዚህ ታላቅ ቀን ያበቃንን ፈጣሪ ለማመስገን እወዳለሁ። በመቀጠልም መላው የኢትዮጵያን ህዝብ እንኳ ደስ አላችሁ ማለት ነው የምፈልገው። ቀድሞውንም ቢሆን እኮ ኢትዮጵያ ሱዳንና ግብፅ አንድ የሆነውን የአባይ እትብት ተጋርተው የሚኖሩ ህዝቦች እንደመሆናቸው ተሳስበን በጋራ የሚጠቀሙት እንጂ እዚህ የሚያድርስ ጉዳይ እንዳልነበር ግልጽ ነው። ሁሉም የአባይ ወንዝ ልጆች ናቸው። በአንድ እትብት ሲተነፍሱና ሲመገቡ የኖሩ ህዝቦች ናቸው። በመሆኑም አንዱ አገር ብቻ ሰለአባይ መወሰን አይቻለውም። እነዚህ አገሮች እንደአንድ አገር ማሰብ ነው የሚጠበቃባቸው። አንድ አገር ብቻውን ለእኔ ብሎ አስቦ የሚሠራው ነገር መኖር አይችልም። ግብፅ ይዛው የቆየችው አስተሳሰብ ከመጀመሪያውም ትክክል ያልሆነ መለወጥ የሚገባው ነበር። ተደጋግሞ እንደሚገለጸው በዚህ ግድብ መገደብ ኢትዮጵያ ብቻ አይደለችም ተጠቃሚ የምትሆነው፤ በተለይ ሱዳን በየዓመቱ የሚደርስባትን የጎርፍ አደጋ ከመከላከል አንጻር ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው እሙን ነው።
በነገራችን ላይ በሙያዬ ምክንያት ከግብፅ ሰዎች ጋር በምንነጋገርበት ጊዜ ሁሉ ይህንን እውነታ ላስረዳቸው እሞክር ነበር። በአባይ ጉዳይ ላይ አብረን ማሰብ እንዳለብን እነግራቸው ነበር። በተለይ ሦስቱ አገሮች በአንድ እትብት የታሰርን አገሮች ለየብቻችን ማሰብ እንደማንችል እገልጽላቸው ነበር። ኢትዮጵያ ከመሬቷ አቀማመጥ አኳያ በብዛት ከዚህ ውሃ መጠቀም የምትችለው ኃይል ማመንጨት ነው። ኢትዮጵያ የጋራ ተጠቃሚ እንሁን እንጂ ብቻዬን ልጠቀም አላለችም። ስለዚህ በዚህ ጉዳይ ላይ ይህን ያህል የከረረ እልህ ውስጥ መግባት አልነበረብንም። ግብፆች ለሌላው የሚያስቡ ቢሆኑ ኖሮ የህዳሴ ግድብ ባለአክሲዮኖች መሆን ነበረባቸው። ከሚያመጣላቸው ጥቅም አኳያ እንዳውም ባለቤት ሆነው ግድቡ ከጫፍ እንዲደርስ መደገፍ ነበረባቸው። ዞሮ ዞሮ አሁንም ቢሆን ትክክለኛውን ነገር ለማድርግ ዘገየ የሚባል ነገር የለም። የድሮ የቀኝ ገዢዎች አስተሳሰብ ተይዞ አባይ የእኔ ብቻ ነው ማለት አይቻልም። በየዓመቱ ኃይለኛ ዝናብ በሚዘንብበት ጊዜ እቺ ተራራማ አገር አፈሯ እየታጠበ ለም አፈሯ አሸዋማውን የግብፅ ምድር እያለማና እያበለፀገ ነው የኖረው። ይህንን ሁሉ ማሰብ ነበረባቸው።
አሁንም ሆነ ወደፊት አባይን ብቻ ሳይሆን ወደ አባይ የሚገቡ ወንዞች ላይ ኢትዮጵያ በመስኖ ማረስም ሆነ ግድብ መገንባት ያስፈልጋታል። ይህ እውነታ የማይቀር ነው። እርግጥ ነው፤ እነሱ የውሃው መጠን ይቀንስብናል የሚል ስጋት ነው ያላቸው። እንግዲህ ለዚህ ደግሞ በጥቅም ክፍያ መደራደር ነው የሚገባቸው እንጂ መከላከል አይችሉም። አገራችን ይህንን ያህል ዘመን ጨለማ ውስጥ ኖራለች። አሁን ደግሞ እምቢ የምትል ኢትዮጵያ እየተፈጠረች ነው። እምቢ፤ አሻፈረኝ ማለት የምትችል አገር መፍጠር ጀምረናል። የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በግርድፉ ብናየው የዛሬ 25 ዓመትና ዛሬ እኩል አይደለም። የአገሪቱ ኢኮኖሚ ዛሬ ትልቅ ነው፤ የህዝቡም ብዛት ከፍተኛ ነው። እናም አንድ ቀን በቀኝ ገዢዎች የተቀመጠ ውልና የግብፅ አስተሳሰብ አንድ ቀን እምቢ ማለት ነበረበት። የተባለችውን ሁሉ የምትቀበል አገር መሆኗ ቀርቷል። ስለዚህ የሚያዋጣው ቁጭ ብሎ መወያየት ነው ባይ ነኝ። ሁሉንም በሚጠቅም መልኩ ሁሉም አሸናፊ ሆኖ እንዲወጣ መወያየት መደራደር ነው ያለው አማራጭ። ድርድር ውስጥ ሲገባ ማንኛውም ወገን ሰጥቶ በመቀበል እንጂ መቶ በመቶ ብቻዬን አሸንፋለሁ ብሎ አቋም መያዝ አይገባም። የግድቡ ዲዛይን ቀድሞም የተሠራ ቢሆንም እስከአሁን አቅም ስላልነበረን አልገነባነውም ዛሬ ግን ያ ህልምችን እውን ሆኗል።
አዲስ ዘመን፡- እንደሚያውቁት ግድቡ ውሃ ሙሌት ተጀመረ እንጂ አልተጠናቀቀም፤ የግድቡ ግንባታ ከመጨረሻው ምዕራፍ እንዲደርስ የግሉ ዘርፍ ሚና ምን መሆን አለባት ይላሉ?
አቶ ዛፉ እየሱስወርቅ፡- እስከአሁንም የግሉ ዘርፍ አስተዋጽኦ ሲያደርግ ቆይቷል። በመጀመሪያ ነገር የግል ዘርፍ ብለን የምንጠራው ዛሬ ወደድንም ጠላንም ኢኮኖሚው ተረክቦ የሚያስቀጠል ሚና ነው ያለው። በነገራችን ላይ ኢህአዴግ ሲመጣ በመጀመሪያዎቹ ጥቂት ዓመታት ላይ የግሉን ዘርፍ የፖለቲካ አጋራችን ሊሆን የሚችለው ‹‹ እኛ ራሳችን ደግፈን የምናሳድገው ብቻ ነው ›› ነበር የተባለው። ልማታዊ ባለሀብቱ ነው እንጂ የግሉ ዘርፍ በአጠቃላይ አጋር ይሆናል ብለን አናስብም የሚል አስተሳሰብም ነበራቸው። ይህም ሆኖ ግን ከደርግ ጋር ስታነፃፅሪው የተሻለ ነው። ከ500 ሺ ካፒታል በላይ ያለው ኩባንያ አይኖርም ብሎ አውጆ ንግድ ቤቶችን ሳይቀር ነበር የወረሰው። ደርግ ከመምጣቱ በፊት የግሉ ዘርፍ በትንሹም ቢሆን ማቆጥቆጥ ጀምሮ ነበር። ደርግ መጥቶ ያንን ዓይኑን አጠፋ። ኢህአዴግ እንደመጣም አንዳንድ ዘርፎች ላይ የደርግን ፖሊሲ ለወጠ። በተለይም በፋይናንስ ዘርፉ የግሉ ሴክተር እንዲገባ ፈቀደ። በዚህም መሰረት ብዙዎቻችን ለግድቡም ሆነ ለአገር ልማት የበኩላችንን አስተዋፅኦ እያደረግን እንገኛለን። በተለይም ዛሬ በባንክና በኢንሹራንስ ዘርፉ ያሉ ተቋማት ለህዳሴ ግድብ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አድርገዋል፤ እያደረጉም ናቸው።
በዚህ ህዳሴ ግድብ ሂደት ብዙ በጎ ነገሮች ለማድረግ የሚያስችል አቅም ተፈጥሯል። በአሁኑ ሰዓት እስከማውቀው ድረስ ያለፉትን ሁለት ዓመታት የህዳሴ ግድብ ጉዳይ በየቀኑ በየደቂቃው በዓይናችንም በጆሯችንም በዘፈኑም የሚንቆረቆር በመሆኑ ሁላችንም በከፍተኛ ሁኔታ የተነሳሳንበት ጊዜ ነው። እንደታሪክ አጋጠሚ ሆኖ ግንቦት 12 ከባለቤቴ ጋር ከተጋባን 50 ዓመት አከበርን። ወቅቱ የኮረና ቫይረስ የተስፋፋበት በመሆኑ መደገስ እንደማንችል ከባለቤቴ ጋር ተነጋገርን። ሰዎችን ጠርተን ብንጋብዝ ኖር ልናወጣ የምንችለውን ገንዘብ ስናስብ 1 ሚሊዮን ብር ይጠጋል። በመሆኑም ይህንን አንድ ሚሊዮን ብር ቦንድ ያለወለድ ብንገዛበት የሚል ስምምነት ላይ ደረስን። ይህንን ሃሳብ ይዤ አንዳንድ ሰዎችን ሳማክር አንድ ወዳጄ «ልክ እንደእርሶ አንድ 50 ሰው ቢገኝ 50 ሚሊዮን ብር ይሆናል» ብሎ ሃሳብ ሰጠኝ። ይህንን ታሳቢ አድርገን ባንኮች በተዘጋው በጀት ዓመት ከገባው 447 ቢሊዮን የተቀማጭ ገንዘብ ውስጥ 1 በመቶውን ለግድቡ ግንባታ የሚውልበትን ሃሳብ አቀረብኩኝ። ከዚህ ገንዘብ ውስጥ ለመጠባበቂያ አምስት በመቶው ብሄራዊ ባንክ ብቻውን የሚያዝበት ተቀማጭ ነው። ከዚህ ውስጥ 1 በመቶ ለህዳሴው ግድ ቦንድ ተገዝቶ እንደገንዘብ ቢያዝ በሚል የኢትዮጵያ የባንክ ዳይሬክተሮች ሥራ አስፈፃሚ የሆኑ ሰባት ባንኮች አባላት ተገናኝተን ሃሳቤን አማከርኳቸው። ሁሉም በሃሳቤ መቶ በመቶ ተስማሙ።
በመቀጠልም ብሄራዊ ባንክ በመሄድ ዶክተር ይናገር ደሴን አማከርኳቸው። እስቻውም ሃሳቡን እንደወደዱት፤ ነገር ግን ብቻቸውን የሚወስኑት ጉዳይ ስላልሆነ እስቲ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ልምከርበት አሉኝ። በስምተኛው ቀን ደውለው በጉዳዩ ላይ መወያታቸውን በወረቀት ጉዳዩን እንዳቀርብ ጠየቁኝ። በዚያ መሰረት ብሄራዊ ባንክ አዳራሽ አስፈቅጄ የባንኮች የቦርድ ሰብሳቢዎችንና ዋና ሥራ አስፈፃሚዎችን ሰብስቤ ሃሳቡን አካፈልኳቸው። እንሱም «ብሔራዊ ባንክ ከፈቀደና ቦንድ በመገዛቱ ተጨማሪ ገንዘብ አንጡ እንዳይለን ከተደረገ የተቀደሰ ሃሳብ ነው» የሚል ምላሽ ሰጡኝ። በማግስቱ ደብዳቤ ፅፌ ለብሄራዊ ባንክ አስገብተን መልስ እየጠበቅን ነው። ይህ የሚፈቀድልን ከሆነ 4 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር የህዳሴ ግድብ ቦንድ ይገዛል ማለት ነው። በነገራችን ላይ ይህ ገንዘብ ወትሮውን ዝም ብሎ የተቀመጠ ነው። ህዳሴ ግድብ የኤሌትሪክ ኃይል የምናገኝበት ብቻ ሳይሆን የልማታችን መሰረት ነው የሚሆነው። የመስኖ እርሻ በስፋት መሥራት ያስፈልገናል። መንግሥትም በ10 ዓመቱ የልማት እቅድን ለማሳካት የአገር ውስጥ አቅምን ማጠናከርን ዓለማ ነው ያደረገው። ከዚህ ውስጥ ደግሞ በመስኖ ልማት ላይ ትልቅ ትኩረት እንደሚደረግ አስቀምጧል።
አዲስ ዘመን፡-ይህ አገር በቀል ኢኮኖሚ ጉዳይ አዋጭ አይደለም ብለው የሚቃወሙ አሉ፤ ለእርሶ ይህ እቅድ አዋጭ ነው ብለው ያምናሉ?
አቶ ዛፉ እየሱስ ወርቅ፡- ስለአገር በቀል ኢኮኖሚ ጉዳይ ሲነሳ እንደአጋጣሚ ሆኖ ተጋብዤ በውይይቱ ላይ ተሳትፌ ነበር። ተጠይቄም ሃሳቤን ሰጥቻለሁ። እኔ በመሰረተ ሃሳብ ደረጃ ልማት፥ ዕድገትና ስልጣኔ በአንድ መንገድ ብቻ ይመጣል ብዬ አላምንም። የዶክተር አብይ መደመር ፍልስፍና ፈረንጆችም ቢሆኑ ለእድገት የተጠቀሙበት ሃሳብ እንደሆነ ነው የምረዳው። በእኔ አስተሳሰብ መደመር ባለ ነገር ላይ መጨመር ማለት። አየሽ የአገራችን የእስከአሁኑ ጉዞ አንድ አስተዳደር ተሸንፎ ሌላው ሲመጣ ያንን የፊተኛውን ማጣጣል ይወዳል። የፊተኛው ምንም እንዳልሠራ ጨለማ አድርጎ ማለፍን ይመርጣል። ይህ ትክክል አይደለም። ከዛሬ 25 ዓመት በፊት በነበርንበት አይደለም አሁን ላይ ያለነው። ከፍተኛ እድገት አስመዝግበናል። ይህንን መቀበል አለብን። እርግጥ ነው ጉድለቶች ነበሩ። እኔም ከሚጮሁት ሰዎች አንዱ ነበርኩ። በተለይም በግሉ ዘርፍ በኩል አዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት በነበርኩበት ጊዜ ስጨቃጨቅ ነው የቆየሁት። ባገኘሁት አጋጣሚ ሁሉ የግሉን ዘርፍ እንደጠላት አድርጋችሁ አትዩት በማለት እሟገት ነበር። ይህንን ስል ግን የግሉ ዘርፍ መረን ይልቀቅ እያልኩ አይደለም። ነገር ግን የግሉ ሴክተር ሥራ የሚያሳራ ካባቢ ይፈጠርለት፤ በእውቀት ላይ የተመሰረተ አስፈላጊው ክትትል ደግሞ ይደረግበት ነው እያልኩ ያለሁት።
እናም አገር በቀል ኢኮኖሚ መሪ እቅድ ውጤት እንደሚያመጣ አምናለሁ። እስከአሁን ድረስ የተሠሩ ሥራዎች ይዘን በእነሱ ላይ እሴት መጨመር ያስፈልገናል። ካለፈው ሂደት ጋር ቁርጥርጥ አድርጎ መለያየት አይቻልም። ሕፃን ልጅሽን ያጠብሽበትን ውሃ ለመድፋት ብለሽ ውሃውን ከነሕፃኗ እንደማትደፊያት ሁሉ ጥሩን ከመጥፎው ጋር ደምረሽ ወዲያ ልጣለው ማለት አትችይም። ስለዚህ ለእኔ እንደፍልስፍናም ቢሆን አገር በቀል ሂደቱ ትክክል ነው። እስከአሁንን ድርስ የተገኙ ጥሩ ውጤቶን ይዘን በእሱ ላይ መገንባት ላይ ያጠነጠነ በመሆኑም ሊደገፍ የሚገባው ነው ባይ ነኝ ። ሆኖም ውጤቱ ፍጹም ይሆናል ብሎ መጠበቅ አይቻልም። እሱን ለፈጣሪ ነው መተው ያለብን። ሰዎች እንደመሆናችን እንሳሳታለን፤ መሳሳትም መብታችን ነው። መጥፎው ነገር ግን አንድ ሰው ያጠፋው ጥፋት ሲታወቅበት መቀበል ሲያቅተው ነው አደጋው። በመሆኑም ስለዛሬ ስናወራ ዛሬ ከየት መጣች ብለን መጠየቅ አለብን። እኔና አንቺ የተገናኘንበት ደቂቃ የሺ ዓመታት ውጤት ነች። ዛሬ ላለንበት ሁኔታ ሁላችንም ኃላፊነት አለብን። መጥፎ መጥፎ ብቻ መርጠሽ፤ ያለፈውን በመጥፎ ብቻ መስለሽ እኛ ፍፁም ነን አናጠፋም ማለት ትክክል አይደለም።
እኔ ቀደም ሲልም የዶክተር ዓብይን ሂደት ትክክል ነው ብዬ ያልኩት እስከአሁን ያለው መጠፋፋት ሲሠራ የነበረውን ነገር ሌላው ስለሠራው ብቻ መናድ የሚለውን አካሄድ የማልስማማ በመሆኑ ነው። እኔ የማምነው ባለው ላይ መጨመር ነው። የእኛ አገር ከዚያ አስተሳሰብ ለመውጣት ብዙ ይቀረዋል። ይህን የአስር ዓመት የልማት እቅድ በበኩሌ እደግፈዋለሁ። የግሉ ዘርፍም ዕድል የሚያገኝበት ጊዜ ነው የሚሆነው። ሌላው ቢቀር ከዚህ ቀደም ዓይተነው በማናውቀው መልኩ በአሁኑ ወቅት እየተሞከረ በመሆኑ ልናመሰግን ይገባል። ዕድሉን ከተጠቀምንበት ደግሞ ለግሉ ዘርፍ የበለጠ የተሻለ ተስፋ ይኖረዋል። በሃሳብ ደረጃ እንኳን ከዚህ ቀደም የማንነጋገርባቸውን ነገሮች በአሁኑ ወቅት በግልጽ እየተወያየንባቸው ነው። እኔ ትክክለኛ ልማት የሚያመጣ የተስፋ ጭላንጭል ይታየኛል። ይህ ማለት ግን መንግሥት ሁሉንም አድራጊ ፈጣሪ ሆኖ ይቀጥላል ማለት አይደለም። ይህ አስተሳሰብ ዘመኑ ያለፈበትና አዋጭ ያልሆነ አሠራር ነው። ሶቭየት ዩኒየኖች 70 ዓመት ሞክረውት እንደገና ተመልሰው ነው ነገሮችን ማጤን የጀመሩት። እናም ከውልደት እስከ ሞት ድርስ መንግሥት ሁሉን ነገር ያደርግልሃል እያሉ ህዝብን መምራት ጊዜ ያለፈበት ፋሽን ነው። እናም የግሉ ዘርፍ የተሻለ ዕድል ኖሮት የተሻለ ሥራ ይሠራ የሚል እምነት ነው ያለኝ።
አዲስ ዘመን፡- አንዳንድ ሰዎች «መንግሥት እንደ ኢትዮ-ቴሌኮምንና የኢትዮጵያ አየር መንገድን ፕራይታቬይዝድ ማድረጉ ተገቢ አይደለም» ሲሉ ይደመጣሉ። እርሶ በዚህ ሃሳብ ይስማማሉ?
አቶ ዛፉ እየሱስወርቅ፡- እንዳው ሁሉንም አንድ ላይ በጅምላ መኮነን አልፈልግም። ግን አብዛኛውን ጊዜ በዚህ አስተሳሰብ አክርረው የማያቸው ስለግሉ ዘርፍ በመፅሐፍ ከሚያነቡት ውጭ ምንም የማያውቁ ሰዎች ናቸው ባይ ነኝ። የግሉ ዘርፍ ወድቆ መነሳት እንደሚችል አይምሯቸው ውስጥ አይመጣም። እንዲህ የሚሉ ሰዎች ደግሞ ብዙውን ጊዜ ተቀጣሪ ሆነው የኖሩ ናቸው። ስለካፒታሊዝም ምንአልባት የሚያስቡት የድሮው መንግሥት እጁን ማስገባት የለበትም ከሚል ነው። ይህንን ዓይነቱን ሃሳብ አንዳንዴ አዳምጣለሁ። በነገራችን ላይ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ፕሬይቬታይዜሽን አማካሪዎች ምክርቤት አባል በመሆኔ ስለዚህ ነገር ብዙ የተረዳሁ ይመስለኛል። አንደኛ ይህች አገር ችግር ውስጥ ነው ያለችው። የማክሮ ኢኮኖሚ የሚዛን መዛባት ወደፊት እንዳትሄድ ይዟታል። በተለይ የውጭ ምንዛሬ ችግራችንና ያለባት ዓለምአቀፍ እዳ ጉዳይ አሳሳቢ ነው። የገባችበትን እዳ አለመክፈል ማለት ደግሞ ለወደፊቱም ብድር የምታገኝበትን ዕድል ይዘጋባታል ባይ ነኝ። ስለዚህ ሳንወድ በግድ አንዳንድ ተቋማትን ለግሉ ዘርፍ ማስረከብ ይገባናል። እርግጥ ነው በጣም የምንኮራባቸውን እንደኢትዮጵያ አየር መንገድ ዓለም የሚያደንቃቸውን ተቋማት በተወሰነ ደረጃ ፕራይቬታይዝ ማድርግ ይጠቅመናል እንጂ አይጎዳንም።
እንዳልሽው ግን ብዙውን ጊዜ ፕራይፔታይዜሽን ሲባል ሙሉ ለሙሉ ለግሉ ባለሀብት መስጠትና ከመንግሥት እጅ የሚወጣ ተደርጎ ይታሰባል። በመጀመሪያ ደረጃ ቅደም ተከተል አለው። ለምሳሌ ኢትዮ- ቴሌኮምን ፕራይቬታይዝ አደረግነው ሲባል ሙሉለሙሉ ሸጥነው ማለት አይደለም። ብዙ ሰው የሚያስበው የግሉ ዘርፍ ኢትዮቴሌኮምን ገዝቶ ኪሱ ከቶ ይዞት የሚሄድ ነው የሚመስለው። ስህተት ነው። አጋርነት ነው የምንፈጥረው። በእኔ አረዳድ ኢትዮ-ቴሌኮም አሁን ባለበት ሁኔታ በጣም ብዙ ድክመት አለበት። ለግሉ ዘርፍ ቢሰጥ በብዙ መልኩ ሊሻሻል የሚችልበት ዕድል አለ። መሻሻሉ ደግሞ ለወደፊት ዕድገታችን ወሳኝ ነው። ለምሳሌ ስለዲጂታላይዜሽን እናወራለን፤ ዲጂታላይዜሽን ያለብቃት ያለው ቴሌኮም አገልግሎት ሊሳካ አይችልም። በየባንኩ ቅርንጫፉ የሲስተም መቆራረጥ ችግር አለ። በመሆኑም ድርጅቱን በከፊልም ቢሆን ለግሉ ባለሀብት መስጠቱ አዋጭ ነው ባይ ነኝ። በአሁኑ ወቅት ደግሞ ተቋሞቹን የሚከታተልና ፈቃድ ሰጥቶ የሚቆጠጥር አካል ተፈጥሯል። በመሆኑም የቴሌኮምን አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት በኮንትራት መልኩ ማስገባት ይችላል።
አዲስ ዘመን፡- በኢትዮጵያ ተሞክሮ አብዛኛው ባለሀብት ለራሱ ጥቅም ማካበት እንጂ ለደሃው ህብረተሰብ ፍትሐዊ አገልግሎት ሲሰጥ ባልታየበት ሁኔታ እነዚህን ተቋማት ለግሉ ዘርፍ ማስተላለፉ ጉዳቱ አያመዝንም? በተለይ እንደኢትዮ-ቴሌኮም ያሉ ተቋማትን ለግሉ ዘርፍ ማስተላለፍ የአገር ደህንነትን ጥያቄ ውስጥ አይከትም ይላሉ?
አቶ ዛፉ እየሱስወርቅ፡- እኛ ነን እንዴ በዓለም የመጀመሪያዎቹ ፕራይቬታይዜሽን አድራጊዎቹ? አብዛኛው አገር በዚህ መንገድ ነው ያደገው። ለሚነሳ ችግር ሁሉ ሁልጊዜ መፍትሔ አለ። ስለመፍትሔውም ማሰብ አለብን። ሠርተን ጎጂ ሁኔታዎች ሊያጋጥሙን ይችላሉ። ኢትዮጵያ አየር መንገድ ፕራይቬታይዝድ ይደረግ ሲባል እንሸጠዋለን ማለት አይደለም። ነገር ግን ለምሳሌ የአፍሪካ መንግሥት 10 በመቶ ድርሻ እንዲኖራቸው ብናደርግ እንጠቀማለን አንጎዳም። ለናይጄሪያ እንኳ ድርሻ ብናካፍል ከ100 ሚሊዮን ህዝብ በላይ ገበያ አስረን የምንይዝው። ደንበኞቻችን ነው የሚሆኑት። የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዛሬ ባለበት ቦታ ስኬታማ ነው። በእኛ አገር ብቻ ሳይሆን በሌሎችም አገራት ስኬታማ ተደርጎ የሚጠቀስ ነው። በመንግሥት ይዞታ ስር ሆኖ ግን ብቃት ያለው አገልግሎት የሚሰጥና ትርፋማ ተቋም ነው። በዚህ ሁኔታ እንሽጠው ቢባል እኔም እሺ አልልም። ነገር ግን አጋር ቢኖሩት በተወሰነ ደረጃ ጥሩ ነው። አሁን ባለው ሁኔታ ለምሳሌ እንበልና 200 አውሮፕላኖችን ይዞ እየሠራ ከሆነ ድርሻውን ለሌሎች ቢያካፍል ደግሞ እጥፍ ይዞ መሥራት ይችላል። በመሆኑም ጥሩውን ነገር እጥፍ ነው የምታደርጊው። ምንድን ነው ችግሩ ታዲያ? እናም አስተሳሰባችን በእውነቱ ላይ የተመሰረተ አይደለም። የመንግሥት ወይም የዓለምአቀፍ ተቋማት ተቀጣሪዎች ሆነው የቆዩ የእኛው ባለሙያዎች የግሉን ዘርፍ ሚና በትክክል መረዳትም ማየትም አይችሉም። በንግድ ሥራ ወድቆ መነሳት ትልቅ ልምድ ነው። የአገሪቱን ሁኔታ ከግምት ውስጥ ማስገባት ይገባል። እሴት በሚጨምር መልኩ ነው አጋርነት የሚፈጠረው።
ሌላ ምሳሌ ልስጥሽ፤ ከዛሬ 40 ዓመት በፊት የአሜሪካን ኩባንያዎች አሜሪካን ሆነው ሁሉንም ነገር እያመረቱ ሲሸጡ ሲቸረችሩና ከጊዜ በኋላ ሌሎች አገሮች የሰው ኃይል ርካሽ የሆነበትና እነሱ የሚሠሯቸውን ዓይነት እቃዎች በጣም ባነሰ ዋጋ ሌላ አገር ሲጫን ሲመለከቱ ጎበዞቹ የአሜሪካ የንግድ ሰዎች ወደ ቻይና እና ታይዋን ሄደው የሚፎካከሯቸው ጋር አብረው ሠርተው ዳግም ተዋዳደሪ ሆነው መቀጠል ቻሉ። ዝም ብለው ቢቀመጡ ኖሮ በቻይና መቶ በመቶ ይበለጡ ነበር። ስለዚህ አጋር ሆኖ መሥራት አዋጭ መሆኑን ነው ያሳዩን። እኛ አገር ያሉ ባንኮች አሁንም ድርስ የውጭ ባንክ እንዳይገባ እያሉ ሲጯጯሁ ትሰሚያለሽ። ይልቁኑም የውጭ ባንኮች እንደሚገቡ ታሳቢ አድርገን እንዘጋጅ። ዝግጅታችን በደንብ ታጥባ ታጥና እንደተሞሸረች ሙሽራ ነው መሆን ያለበት። ምክንያቱም ተወዳዳሪ ሆነን ለመሥራት ያስችለናል። የውጭ ባንኮች መጥተው ብቻቸውን ከሚያቋቁሙ እዚሁ ካለነው ጋር አብረው እንዲሠሩና አጋር ሆነው አክሲዮን እንዲገቡ ማድርግ ነው የሚገባን። ይህንን ስናደርግ እናሸንፋለን። የእነሱን ቴክኖሎጂ ታመጪያለሽ። ልምድ ትቀስሚያለሽ። የአገርሽን ሰው ትቀጥሪያለሽ። ይህንን ስታደርጊ የሚፈልገውን ምርት ወይም አገልግሎት ታቀርቢያለሽ ማለት ነው።
አዲስ ዘመን፡- ባለፉት ሁለት ዓመታት ከነበረው የፖለቲካ አለመረጋጋት ጋር ተያይዞ የኢኮኖሚ መዛባት መከሰቱ ይታወቃል፤ ይህንን መዛባት በምን መልኩ ነው ማስተካከልና ወደ ዕድገት እንዲያመራ ማድርግ የሚቻለው?
አቶ ዛፉ እየሱስወርቅ፡- ባለፉት ዓመታት የነበረው ችግር እንዳለም ሆኖ ስድስት በመቶ ዕድገት ማስገብ ተችሏል። በአሁኑ ሰዓት ይህንን ዕድገት ማስመዝገብ ማቻሉ በራሱ ትልቅ ነገር ነው። ቀደም ሲል ባለሁለት አሃዝ ዕድገት አስመዘገብን ይባል ነበር፤ ይህን ስል መንቀፌ አይደለም፤ ይሁንና አትኩሮቱ ትክክል አልነበረም። የመንግሥት ኢንቨስትመንት ነው። በመንግሥት ተቋምም ሆነ በግሉ ዘርፍ ተሠራ ውጤቱ መቆጠሩ አይቀርም። ነገር ግን ሚዛኑን የጠበቀ አልነበረም። በአብዛኛው የነበረው የመንግሥት ኢንቨስትመንት ነው። በእርግጥ ኢንቨስትመንቶቹ አያስፈልጉም አልልም። ነገር ግን ሚዛኑ ትክክል አልነበረም። ዕድገት ወይም ልማት አኀዝ ብቻ አይደለም። ምክንያቱም ኢትዮጵያ የምንለው እኮ ህዝቧን ነው። ለህዝቧ ምን ጠብ አለላት? ብለሽ ማሰብ አለብሽ። ሁሉንም ነገር በመሰረተ ልማት ዝርጋታ ከመዘንሽው እርግጥ ነው መሰረተ ልማት ለዘለቂታዊ ዕድገት አስፈላጊ ነው፤ መሰረተ ልማት ስንገነባ ለወደፊቱ ተጨማሪ ምርትና አገልግሎት ለመስጠት እያመቻቸን ነው ማለት። ህዝቡ ከዕድገቱ አልተቋደሰም። ውሎ ሲያድርም የመደማመጥ ችግር መጣ። ሁለት አስቸኳይ ጊዜ ወቅቶች ታውጆ ሲያልቅ ኢትዮጵያውያኖች ምንዓይነት ሁኔታ ላይ ነበርን ብለሽ ብትጠይቂ ልንባላ ተፋጠን ነበር የሚል ምላሽ ታገኚያለሽ። ቢከፋም ቢለማም የአገሪቱ ሂደትና ሁኔታዎች በአጠቃላይ አሁን ያለንበት ወቅት የተሻለ ነው። ለዚህ ደግሞ ኃላፊነቱ ለአንድ ሰው መስጠት አልፈልግም። ግን ብዙ ሁኔታዎች ናቸው ዛሬ ላለንበት ደረጃ ያደረሱን። እርግጥ ነው አሁንም ከፍተኛ ችግር አለ፤ ባለፈው 87 ሰዎች ማለቃቸውም ሆነ ሌሎች የሚያሳዝኑ ነገሮች አለፉ። ግን 110 ሚሊዮን ህዝብ ባለበት አገር ውስጥ የአንድም ሰው ህይወት ቢሆን ክቡር ነው። ሞቱ ያሳዝናል፤ ግን ዋናው ችግር የአፍ ጦርነቱ ነው የባሳው። እስካከአን ድርስ ብዙ መጥፎ ነገሮችም አልፈው ቢሆን ላለንበት ሁኔታ የሚያበረታታ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ባለመረጋጋት ምክያት ከደረሱት ችግሮች አንፃር ኢኮኖሚው ሊያንሰራራ የሚችልበት ዕድል ይኖራል ተብሎ ይታመናል?
አቶ ዛፉ እየሱስወርቅ፡- አስቀድሜ እንደነገርኩሽ ናይጄሪያ ብዙ ዓመት ነው የቆየሁት፤ ናይጄሪያዎች መጥፎ ነገር ደርሶባቸው ስትጠይቂያቸው «ተመስገን ነው ከዚህም ሊብስ ይችል ነበር» ይላል። እናም ቆም ብለን ነገሮችን ተመስገን ማለቱ ይቸግረናል። እኔ በበኩሌ እስከአሁን ያለፍንበት ሁኔታ አልጋ በአልጋ አይደለም፤ ነገር ግን ከዚህ የባሰ ሊሆን ይችል ነበር ባይ ነኝ።11 በመቶ ሲያድግ የነበረ ኢኮኖሚ አሁን ስድስት በመቶ ሆነ ብለሽ ልታንቋሽሺው ትችያለሽ። እኔ ግን እንደሱ አይደለም የማየው። ካለንበት ሁኔታ አንፃር ጥሩ የሚባል ነው። ከዜሮ በታች አልሆንም። ደግሞም ጎበዝ ለማኝ ጠቅላይ ሚኒስትር አለን። እሳቸው ባይኖሩ የባሰ ሊሆን ይችል ነበር። እንደሚመስለኝ ከአሁኑ ደግሞ ይዞታችንና አትኩሮቶቻችን የአገር በቀል ኢኮኖሚ በተለይም ግብርናው ላይ መሆኑ ለዕድገታችን ተስፋ የሚሰጥ ነው። እኔ የተያዘው መንገድ ይሰማማኝል። የኢትዮጵያ ዕድገት ዞሮ ዞሮ ዋልታና ምሰሶ ግብርናው ነው። ግብርና ነው ስንል ግን እስከአሁን ድርስ በምናውቀው ብቻ ሳይሆን የፈጣሪን ዝናብ ብቻ ጠብቆ ሳይሆን መስኖን በማስፋፋት ነው ውጤታማ መሆን የሚቻለው።
ከዚህ አንፃር እንግዲህ የተያዘው መስመር ትክክል ነው ባይ ነኝ። ማኑፋክቸሪንግ በእሱ ላይ ተደግፎ ነው መሄድ የሚችለው። የቻይና የህንድን ተሞክሮ ብናይ ቻይና የውጭ ንግድ መር ኢኮኖሚ በመከተሏ ማደጓን አይተን እኛም ይህንን እንደአብነት ወስደን በተመሳሳይ መንገድ ለማደግ ጥረት ስናድርግ ቆየን። ግን የውጭ ንግዱ ወደቀብን። የህንድን ተሞክሮ ስናይ የሀገር ውስጥ ፍላጎትን በማርካት ላይ የተመሰረተ የልማት አቅጣጫ ነው የሚከተሉት። እነሱም ዕድገት አስመዝግበዋል። በመሆኑም እንደእኔ እምነት ሁለቱንም ያገናዘበ አካሄድ ብንከተል ተጠቃሚ እንሆናለን። ፈረንጆቹ እንደሚሉት ተፈጥሮ አጠገባችን እያለ እንደገና እሱን ለመፍጠር መሞከር ከአላዋቂ ነው የሚያስቆጥረው። ከሁሉም በጎ ነገሮችን መውሰድ ወይም መደመር ያስፈልጋል። ግብርናው በመስኖ ቢታገዝና መከናይዝድ ቢደረግ እንዲሁም የበሬ ግንባር የሆነ መሬት በተናጠል ከማረስ ይልቅ በክላስተር ማረስ የበለጠ ውጤታማ ያደርገናል። በተናጠል የሚደረግ ሩጫ አሁንም ከእጅ ወደአፍ ከሆነው ኑሯችን አያላቅቀንም። በመሆኑም ኩታ ገጠም የሆኑ መሬቶችን በጋራ ሆኖ ማሳረስና ማምረት ነው የሚገባን። ወደ ገበያ መር ምርት ማምረት ይገባናል። ዘመናዊ አስተሳሰብ እየመጣ ነው። የውጭ ምንዛሬ እኮ ብናገኝም መልሰን ስንዴ ነው የምንገዛበት። እናም በእኔ እይታ አሁን በእውነቱ የአገራችን የዕድገት ፕላን ጨርሼ ሙሉ ለሙሉ ፍፁም የተዋጣለት ነው ብዬ ባልናገርም ልኮንነው የምችለው ግን አይደለም።
አዲስ ዘመን፡- በኮረና ምክንያት የተዳከመውን የግሉን ዘርፍ ከማነቃቃት አኳያስ ምንስ መሥራት አለበት ይላሉ?
አቶ ዛፉ እየሱስወርቅ፡- እስከአሁን ድርስ እውነቱን ለመናገር የኢትዮጵያ መንግሥት እንደመንግሥት ብዙ ጥንቃቄ አድርጎ እየሄደ ነው ያለው ኮረናን በሚመለከት። አንዳንድ አገራት የሆኑትን ስንመለከት አደጋው ገና ያለፍነው አይደለም። ሁላችን ዛሬ ቁጭ ብለን በየቤታችን የምንጸልየው የዚህ መቅሰፍት መድሃኒቱ እንዲገኝ ነው። እንደእኔ እይታ ገና ብዙ ሀብት ይጠይቀናል ብዬ ነው የማስበው። ችግራችንን ገና ጀመርነው እንጂ መጨረሻውን እያየን አይደለም።
የኮረና ቫይረስ ጉዳት እስከአሁን ድርስ ከአገራችን ህዝብ ብዛት፥ የአኗኗር ዘይቤ አንፃር ተመስገን የሚያሰኝ ነው። እርግጥ ነው አሁንም ቢሆን ምርመራው ከፍ ቢል አሁን ከሚነገረው በባሰ በዚህ በሽታ ብዙ ሰው በተያዘ ነበር። ደግሞም ሰዎች ከሞቱ በኋላ በኮረና መሞታቸው መታወቁ ሲታይ በጣም አስፈሪ ነው። የሰው ህይወት ማጣት አሳዛኝ ነገር ነው። ግን የምንከፍለው ክፍያ በእነዚህ ሰዎች ብቻ የሚወሰን አይደለም። አሁን ባለንበት ሁኔታ እንኳን ኢኮኖሚያችን በጣም እየተጎዳ ነው ያለው። የውጭ ምንዛሬ ገቢያችን (ሬሚታንስ) ወርዶ ነው ያለው። ምክንያቱም በውጭ የሚኖሩ ዜጎች ገቢም ቀንሷል።
ይህ ብቻ አይደለም፤ ወደውጭ የምንልካቸው ግብዓቶች እንኳ በተቀባይ አገር ተቀባይነታቸው ቀንሷል። ለምሳሌ አበባን ብትወስጂ ክፉኛ ነው የተጎዳው፤ ቱሪዝሙም ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ የምናገኘውን ገቢ አሳጥቶናል። የኮረና ጉዳይ ገና ሂሳቡ ተሰልቶ ያለቀ አይደለም። ለዚህም ነው አስቀድሜ የህዳሴ ግድብ የልማታችን መሰረት ነው ያልኩሽ።
ይህም ሆኖ ወደድንም ጠላንም የኮረና ቫይረስ መወገዱ አይቀርም። ምናልባት ሁላችንም ይህንን ጊዜ ላንሻገር እንችላለን። ከታች ቢጀመርም መንገዶችን በተቻለ መጠን ማስተካከልና ተመልሰን ማንሰራራታችን አይቀርም። ደግሞም እንደሰው እንደዚህ ብለን ማሰብ አለብን። እንደሚባለው አስር ሞት መጣ ቢሉት አንዱን ግባ በለው እንደሚባለው ሞት ይመጣል ብዬ ሞቼ መጠበቅ አልፈልግም። እንደሚመሰለኝ ሀገራችን ይህንን ችግር አልፋ ወደ ተሻለ የልማት ሁኔታ ትሄዳለች ብዬ አስባለሁ። እርግጥ ነው አንዳንድ አገራት ችግሩን ለመቋቋም የተሻለ አቅም አላቸው። ጤነኛ ሆነን እንደአገር ለመቀጠል ችግሩንም ተቋቁመን ወደፊት መሄዳችን አይቀርም ብለን ማሰብ አለብን። እዚሁ እጃችንን ሰጥተን መቀመጥ አማራጭ አይደለም። ብዙ እንደምንቸገር ይገባኛል። ነገር ግን ኢትዮጵያ እዛ ላይ ታቆማለች፤ ህዝቦቿም ይጠፋሉ ማለት አይቻልም። እኔ በተፈጥሮዩ ወደፊት ብሩህ ቀን እንደሚመጣ ማሰብ ነው የምፈልገው። ወደ ተሻለ ሁኔታ እንሻገራለን የሚል እምነት ነው ያለኝ።
በሌላ በኩልም አገራችን ውስብስብ በሆነ ሁኔታ ውስጥ ነው የምትገኘው። በየቦታው ግጭትና ሁከት ተበራክቷል። ህዝቡ በያለበት እየተጯጯኸ ነው ያለው። በእኔ እምነት ሁሉም ነገር ለከት ሊኖረው ይገባል። ቀደም ሲል እነዚህ 87 ሰዎች ከማለቃቸው በፊት የህግ የበላይነት ማረጋገጥ በጣም አስፈላጊ ነው እንል ነበር። አንድ ህግ መጥፎም ጥሩም ሊሆን ይችላል። ህግ ነው ተብሎ እስከተቀመጠ ድረስ ግን ማስፈፀም ይገባል። ህጉ ጎጂ ነው ሲባል ማሻሻል ወይም መለወጥ ነው የሚያሻው እንጂ ህግን አስቀምጦ ያ ህግ እየተጣሰ ህዝብና ንብረት እንዲያለቅ መፍቀድ አይገባም ነበር። ይህ ምናልባት እንግዲህ የሁላችንም የትዕግስት ዳርቻ እኩል አይደለም። አንዳንዶቻችን ከሌላው ሰው በበለጠ እንታገስ ይሆናል፤ ግን ህግ የበላይ ካልሆነ በአንድ አገር ውስጥ የትም አይደረስም።
አዲስ ዘመን፡- አንድ ቃለምልልስ ላይ ገና በሽግግር ዘመን «የፌዴራሊዝም ስርዓት አንድ የተዳፈነ እሳት ሆኖ ይፈጀናል» የሚል ስጋት እንደነበሮት አንስተው ነበር፤ ይህ ንግግሮ አሁን ላይ ከተፈጠረው ችግር አንፃር ትንቢታዊ መልዕክት ነበር ማለት እንችላለን?
አቶ ዛፉ እየሱስወርቅ፡- ይህንን ንግግር መጀመሪያ ላይ የተናገርኩት ሌጎስ ነው። እ.ኤ.አ 1992 ዓ.ም ላይ ነው የተናገርኩት። ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ፥ ዶክተር ኃይሌ ወልደሚካኤል፥ አምባሳደር ገነት ዘውዴና አንድ ሌላ ሰው ሌጎስ መጥተው ባነጋገሩኝ ሰዓት ነው የተዳፈነ እሳት ነው ያልኳቸው። የሚያቀራርበን እየረሳን፤ የሚያራርቀን ላይ እያተኮርን ነው አልኳቸው። እነሱ በወቅቱ የእነሱን ትንታኔ ሲያስረዱኝ የበፊቶችን መንግሥታት መጥፎነት ገልጸው በብሄር ብሔረሰቦች መካከል ያለ ጭቆና እና ግፍ መፍትሔ የብሔር ብሄረሰቦችን መብት የሚያከብር ስርዓት መፍጠር እንደሆነ ነገሩኝ። ዞሮ ዞሮ የሚመራው የተመረጠ መንግሥት ነው፤ እኛ ያልተመረጥን በመሆኑ ስርነቀል ለውጥ አናድርግም ነበር ያሉኝ። ይህንን ብለው ሲጨርሱ እኔም ሃሴባን ለመግለጽ ስልነው ያችን ነገር የተናገርኩት። እናም ብዙ በታሪክ ሂደት ውስጥ ስታልፊ የምታያቸው ነገሮች አሉ። ብዙ መጥፎ ነገሮች ውስጥ አንዳንድ ጥሩ ነገሮች ታያለሽ። የህይወቴ ፍልስፍና ይህ ነው። መጥፎውን አውጥተሽ ጥሩውን ይዞ በመቀጠል ነው የማምነው።
እኔ በዘጠኝ ዓመቴ አዲስ አበባ መንገድ ላይ «በእንተ ስለማርያም» እያልኩ እየለመንኩና አራዳ ጊዮርጊስ እጀጠባብና ትንሽ አንገት ልብስ አድርጌ ነው በልመና ጊዜውን ያሳለፍኩት። ነፃ ትምህርት ባይኖር ኖሮ ወደዚህ መምጣት አልችልም ነበር። የፊውዳሊዝም ጊዜ በጣም ብዙ ጥሩ ነገሮች አሉት። ፊውዳል የሚባሉት የነግሥታቱ አመራሮች የባላባቶችን ልጆች በግድ እየነጠቁ አምጥተው ትምህርት ቤት ያስገቡ ነበር። አዳሪ ትምህርት ቤት ሲፈጠር ከያለበት ተሰብሰብን ነው የተማርነው። እኔ ውንጌት አዳሪ ትምህርት ቤት ስማር ነው ለመጀመሪያ ጊዜ የብረት አልጋ ፍራሽና አንሶላ ላይ የተኛሁት። በክረምት አባቴ ጋር ስሄድ ግን የምተኛው መደብ ላይ ነው። ጓዳኞቼም ከኢትዮጵያ ከሁሉም አካበቢ የመጡ ነበሩ። ኃይሌ ፊዳ፤ ገበየሁ ፈይሳ ነበሩ ጓደኞቼ። «ከየት መጣህ» አንባባልም ነበር። ሁላችንም በአንድ አዳሪ ትምህርት ቤት ውስጥ ስንኖር ዋነኛ ዓላማችን ትምህርትቻን እንጂ ስለመጣንበት ብሄር ጉዳይ አልነበረም። የመጣንበት ማህበረሰብ የተለያየ ቋንቋ ተናጋሪ ቢሆንም ሁላችንም በአንድነትና ኢትዮጵያዊነት ስሜት እንደቤተሰብ ነበር የምንኖረው። እኔ በበኩሌ ብሄርህ ማነው ተብዬ ስጠየቅ በጣም ያበሳጨኛል። ግራም ይገባኛል። ያደኩበት ደሴ ከተማም ወለዬዎች ብቻ ሳይሆን ከኤርትራም ሆነ ከአፋር የመጡ የህብረተሰብ ክፍሎች ይኖሩበት ስለነበር ስለአን ብሄር ጉዳይ አስቤ እንድኖር አልተደረኩም፤ አላውቅውም። ያ እሴት ነው ኢትዮጵያዊ ሆኜ እንዳድግና በዚያ አስተሳሰብ ተቀርፄ እንድኖር ያደረገኝ። ይህ ብዙ ዋጋ ተከፍሎበታል።
ያኔ ታዲያ ስርነቀል ለውጥ አናደርግ «ና» ብለው ሲጠይቁኝ ለመመለስ ፍቃደኛ አልነበርኩም። ምክንያቱም የፋይናስ ዘርፉ በመንግሥት ቁጥጥር ስር እያለ እንዴት እመጣለሁ አልኳቸው። ግን በብሄር ላይ የተመሰረተው ፌዴራሊዝም አካሄድ አዝማሚያው ጥሩ እንዳልሆነ ነግሬያቸው ነበር። የሚያቀራርቡንን ነገሮች ወዲያ እየወረወራችሁ ወደፊት ሊያጣሉንና ሊያባሉን በሚችሉ ነገሮች ላይ ማተኮራችሁ ትክክል አይደላችሁም አልኳቸው። ደግሞ የኢትዮጵያን ካርታ ዳግም መሳላችሁ ተቀባይነት እንደማይኖረው ነግሬያቸዋለሁ። አገሪቱ በክልል መዋቀሯን አልሰማማም ነበር። ህገመንግሥቱ ሊፀድቅ ሲል የዲፕሎማቲክ ደረጃ ስለነበረኝ በራሴ ወጪ ለመታደም ጥያቄ ባቀርብም «የፖለቲካ ፓርቲ አባል ስላልሆንክ ታዛቢ ሆነህ መግባት አትችልም» ተብዬ ተከለከልኩኝ።
አንቺም እንደጠቀስሺው ከዓመታት በፊት የተናገርኩት ነገር አሁን ላይ የተከሰተውን ችግር ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ነው። ችግሩ እዚህ ደረጃ ከመድረሱ በፊት የቀድመው ኢህአዴግ በተዘጋጀ መድረክም የዘሩት ዘር ያስከተለውን አስከፊ አደጋ በግልጽ ተናግሬ ነበር። በየቦታው እየፈነዳ የምናየው ማንነት ላይ ያጠነጠነ ነውጥ የዚያ ፌዴራሊዝም ውጤት ነው። በመጀመሪያ ነገር ኢትዮጵያዊም ከመሆኑ በፊት አማራም ሆነ ትግሬም ከመሆኑ በፊት ሰው ነው። በንጉሡ ጊዜ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ይሉኝታና ፈሪሃእግዚአብሄር ነበር። አሁን ላይ ይህ አስተሳሰብ የለም። እኔ አንቺን መጀመሪያ የማከብርሽ በሰውነትሽ ነው። አጭር ሁኚ ረጅም፤ ቀይም ሁኚ ጥቁር፤ ከየት መጣሽ ከየት ለኔ ደንታ አይሰጠኝም። እኔ ላይ እንዲደረግብኝ የማልፈልገውን ሰው ላይ ለማድርግ በፍፁም መታሰብ የለበትም።
ከሰሞኑ የተፈጠረው ነገር እፈራው የነበረ ጉዳይ ነው የሆነው። ምናልባት እኔ አሁን ሽማግሌ እንደመሆኔ በዚህ ጉዳይ ላይ መናገሬ አንዳንዶችን ቅር ሊያሰኝ ይችላል። ግን አሁን ላይ የተፈጠሩ ብሄር ተኮር ግጭቶች እንደሚፈጠሩ ቀድሞውን ነገር ይታይ ነበር። ለዚህ ደግሞ የበዛውን መንግሥት አባብሶታል ባይ ነኝ። ህግን ማስከበር አለመቻሉ ነው የሀጫሉን ግድያን ተንርሶ በሃይማኖትና በዘር ላይ የተመሰረተ ግጭት ገንፍሎ የወጣው። ሰሞኑን በየሚዲያው ላይ ያለሐጥያታቸው በብሄራቸው ምክንያት በደል የደረሰባቸው ሰዎች ሳይ በጣም ነው ልቤ የሚነካው። ይህ ነው እንግዲህ በእኛ አገር ፌዴራሊዝም። ከመጀመሪያውንም ይህንን ዓይነት ችግር ሊፈጥር እንደሚችል ታስቦበት የተሠራ ነው የሚመስለኝ። የታዳፈነ የእግር እሳት ነው ያልኩት ለዚያ ነው። ወደፊትም ሊብስ የሚችልበት ዕድል በመኖሩ ከአሁኑ ልንቆጠጠረው ይገባል። አለበለዚያ «ትሻልን ፈትቼ ትብስን አገባሁ» ነው የሚሆነው። እኔ ዶክተር ዓብይ ጋር የመገናኘት ዕድሉ አጋጥሞኛል። ለአገራችን ዕድገት እውን መሆን ከፍተኛ አቅምም ሆነ የአገር ፍቅር ያለው ብርቱ መሪ መሆናቸውን ለመረዳት ችያለሁ። አሁን ላይ ከዚህም ከዚያም የሚደርስበት ትችትና ውርጅብኝ ግን የባሰው ነገር እንዳያመጣብን ስጋት አለኝ።
አዲስ ዘመን፡- ከዚሁ ጋር አያይዘው የዶክተር ዓብይን መምጣት ተንተርሰው ይጠብቁት የነበረው ታዓምር እውን እንድሆነ ተናግረው ነበር፤ ይህን ጉዳይ እስቲ ያብራሩልን?
አቶ ዛፉ እየሱስወርቅ፡- ከኢህአዴግ እጠብቃለሁ ያልኩት ፌስቡክ ላይ ነው፤ በወቅቱ ዶክተር ዓብይ ከመምጣታቸው ጋር ተያይዞም ኢህአዴግ ታዓምሩን አሳይቶናል ብያለሁ። የጠበቅኩት ታዓምር የዚያን ጊዜ ሁኔታውን በምትመለከችበት ጊዜ « ይህችን አገር ማን ይምራት?» የሚለው ነገር አጠያያቂ ነበር። ከማምንበት ነገር ወደኋላ ማለት አልችልም። ኢህአዴግ ዓብይን መምረጥ አለበት የሚል አቋም ነበረኝ። ከዓመታት በኋላ
ስለኢትዮጵያዊነት ጎልቶ በወጣበት ሁኔታ ዳግም በማየቴ ደግሞም ከፍተኛ የህዝብ ቁጥር ካለው የኦሮሞ ማህበረሰብ የመጡት ዶክተር ዓብይ እንጂ ሌላ አማራጭ ይኖራል ብዬ አላስብም ነበር። በእኔ አመላካከት ሌላ ሰው ተመርጦ ቢሆን ኖሮ ሌላ ቀውስ ውስጥ እንገባለን ብዬ ነበር የማስበው። ባለፉት ሁለት ዓመታት ከተከሰቱት ችግሮች በላይ ሊከሰት ይችል ነበር። ሲመረጥ ኢህአዴግ ታዓምሩን አሳየን አልኩ። ከዚህም ከዚያም መጣ ሳንለው ዱብ ነው ያለልን። በዚህ በጣም ተገርሜ ነበር። ከመጣ በኋላ የሚናገራቸው ብዙዎቹ ነገሮች ወደበጎ ነገር ያመራናል ብዬ ነው ያመንኩት። በተለይ የቀድሞውን ክርር ያለ አብዮታዊ ዴሞክራሲ አስተሳሰብ ያለዝበዋል የሚልም ፅኑ እምነት ነበረኝ። እኔ ኢህአዴግ በጎ ነገር ሲሠራ አሞግሼ ትክክል ሳይመስለኝ ሲቀር ፊት ለፊት የምንቅፍ ሰው ነኝ። ዛሬም የእኔ አመለካከት ያው ነው። ዓብይን ስትነቅፊ ጥሩ ነው፤ ግን የተሻለ የሚተካው ካለ ደግሞ ማቅረብ አለብሽ። ይህ ማለት ኢትዮጵያ ምንም ሰው የላትም ማለት ላይሆን ይችላል። ነገር ግን በይፋ ራሱን ያወጣ ሰው አላየንም።
አዲስ ዘመን፡- አሁን ላይ ያሉ ፖለቲከኞች አገር ለመምራት የሚያስችል ብቃት የላቸውም እያሉኝ ነው?
አቶ ዛፉ እየሱስወርቅ፡- እስከአሁን አላየንም። የሚያስፈልገን ግራና ቀኝ ጥግ ይዘው የሚታኮሱ ሰዎች አይደሉም አሁን የሚያስፈልጉን። እስከአሁን ባለው ሁኔታ ማንም ከደሙ ንፁሕ ነኝ የሚል ፖለቲከኛ ሊኖር አይችልም። ሁላችንም ዛሬ ላለችው ኢትዮጵያ ኃላፊነት አለብንም። ለድርድር ስንነሳ አገሪቱ ለገባችበት ችግር እኔ ከደሙ ንፁኽ ነኝ ብለን ማለት አንችልም። ሁላችንም አስተዋፅኦ አድርገናል በማወቅም ሆነ ባለማወቅ። ቢያንስ ቢያንስ ይህችን እንቅበል። መነጋገር ያለብን ይህችን አንድ አገር በጋራ እንዴት እንኑርባት በሚለው ላይ ነው። ስለዚህ ፖለቲከኞች ተሰብስበው አንዲቷን ኢትዮጵያ በምናስቀጥልበት ጉዳይ ላይ መግባባት ያለባቸው። አሁን ላይ እኮ አንዱ ሌላውን ከእኔ አካባቢ ውጣልኝ እያለ የሚያባርርበት የሚገድልበት ጊዜ ነው። አገራችን ሁላችንንም አቅፋ መኖር እየቻለች ምድሪቱም ለሁላችን በቂ ሆና ሳለ በማይረባ ነገር እርስ በእርስ እንባላለን። ስለዚህ በክብ ጠረጴዛ ዙሪያ በመጀመሪያ ደረጃ መነጋገር ያለብን አገሪቱ ሳትከፋፈል በአንድነት መቀጠል በሚቻልበት ጉዳይ ላይ ነው።
አዲስ ዘመን፡- አሁን ካነሱት ሃሳብ ተያይዞ እንደሚያውቁት በህወሓትና በብልጽግና መካከል የነበረው አለመግባባት በመክረር በአንድ ወገን የጦርነት ነጋሪት እየተጎሰመ መሆኑን እንሰማለን፤ ይህ እርሶ የሚሉት ድርድር በዚህ ሁኔታ እንዴት ነው ውጤት ሊያመጣ የሚችለው?
አቶ ዛፉ እየሱስ ወርቅ፡- እኔ ወደጦርነት ያመራሉ የሚል እምነት የለኝም። እኔ ህወሓት ውስጥ ብዙ ወዳጆች አሉኝ። ሆኖም እነሱም ሆኑ ሌላው ሁላችንም ኢትዮጵያ ዛሬ ለደረሰችበት ሁኔታ ኃላፊነት አለብን ብለን መጀመራችን ነው የሚያዋጣን። መጠቋቆሙ ለማናችንም አይበጀንም። በሌላ በኩል ኢትዮጵያ የምትባለው አገር ትግራይ የሌለችበት ትርጉም የሚሰጥ አይሆንልኝም። ሊሆን የማይችል ነው። በአሁኑ ወቅት አክራሪዎች በሚነዙት ሃሳብ ሰዎች ከያሉበት አንዴ በሃይማኖት አንዴ በጎሳ እንዲሰቃዩ እየተደረገ ነው። እኔ የዚህ ጎጥ ሰው ነኝ የምል ሰው አይደለሁም። ነገር ግን በየቦታው አማራ ሲጠቃ እመለከታለሁ። ይህም በደንብ አጥብቆ ለሚያስብ ኢትዮጵያዊ አማራም ከሚፈለገው በላይ ከተገፋ ከህወሓቶች ጋራ ሊያብር ይችላል። ይህ የፖለቲካ ጨዋታ ነው። አንድ ቦታ ላይ ትዕግስት ሲያልቅ የድሮው አካሄድ ሊቀጥል አይችልም። ይሄ ሁኔታ ጨርሶ አርቀው ማሰብ ያቃታቸው የሚፈጥሩት ነው። ተቻችሎ መኖር እንጂ ይሄ ጥግ ይዞ መሄድ ለማናችንም አይጠቅመንም።
በእኔ እምነት የህወሓት የቀደሞዎቹ አመራሮች በጊዜያቸው የሚችሉትን አድርግዋል። ዝም ብለን ምንም ውለታ እንዳላበረከቱ አድርገን መቁጠር የለብንም። ከእሱ በመለሰ ግን ስልጣናቸውን ለአዲሱ ትውልድ ማካፋል እንዳለባቸው አምናለሁ። ማሸነፍ ማለት እኮ ጠበንጃ ተኩሶ ወይም ጦር ሰብቆ ሌላውን መግደል አይደለም። አንዳንድ ጊዜ እኮ በመሸነፍም ማሸነፍ የሚባል ነገር አለ። ሁላቸውም የሚችሉትን ያህል አስተዋፅኦ አድርግዋል። አብዛኞቹ በማሸነፍ ብቻ ነው ሲያምኑ የቆዩት። እዚህ ካደረሱ በኋላ እንዳውም ማክረር የሚፈልጉትን መካሪ ሆነው ሽምግልና ውስጥ ነው መግባት ያለባቸው። ዛሬም በባዶ እግሩ የሚሄድ፥ የነተበ ልምብስ የሚለብስና የተራበ ህዝብ እያለን ለስልጣን ሲባል ብቻ መባላት አለብን ብዬ አላምንም። ያንን ደሃ ህዝብ አስተዳደርኩኝ ለማለት ነው? የትግራይ ህዝብ ብዙ ዋጋ ከፍሏል፤ ሌላውም በተመሳሳይ ሁኔታ ከፍሏል። እኔ ፖለቲከኛ አይደለሁም። እኔ ዕድሜ ከሰማኒያ አልፏል፤ ሹመትም አልፈልግም። ሰላም የሰፈነባት አገር የህዝብ ህይወት የሚሻሻልበትን ተስፋ ማየት ነው የምፈልገው። የወደፊቷ ኢትዮጵያ ልታሳስበን ይገባል። ያ እስከሚሆን ድርስ ሁላችንም ስለመገንጠል ማውራት የለብንም። በቴሌቪዥን በጮሌ ቋንቋ መወራረፍ መፍትሔ ሊሆነን አይችልም። ሁሉም ቁጭ ብለው መነጋገር አለባቸው።
አዲስ ዘመን፡- ግን ለዚያ ዝግጁ የሆነ ኃይል አለ ብለው ያምናሉ?
አቶ ዛፉ እየሱስ ወርቅ፡- ሁሉም ለእራሱ ሲል ዝግጁ መሆን አለበት። የተጀመረው የእርቅ መንገድ አልተሳካም ተብሎ መቆም የለበትም። መቀጠል ነው ያለበት። የጉልበት ጉዳይ አይደለም። ከሁለቱ አንዱ በጦርነት ቢያሸንፍ ለኢትዮጵያ ሽንፈት ነው። ሁለቱም በክፉ መንገድ ደም ተፋሰው አሸነፍኩ ቢሉ ከድል ልንቆጥረው አንችልም። ሁለቱም ተሸንፈው ማሸነፍ ነው ያለባቸው። ይህችን አገር ለተጨማሪ ደም ማዘጋጀት በፍፁም አይገባቸውም። ጦርነት የመጨረሻው አስፈሪ ቅዥት ነው።
አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ረጅም ቆይታ በአንባቢዎቼና በዝግጅት ክፍሉ ስም ከልብ አመሰግ ናለሁ።
አቶ ዛፉ እየሱስ ወርቅ፡- እኔም እንግዳችሁ ስላደረ ጋችሁኝ ከልብ አመሰግናለሁ።
አዲስ ዘመን ሐምሌ 25 ቀን 2012 ዓ.ም
ማህሌት አብዱል