ሳምንቱ እንዴት ነበር? መቼም ከባለፈው ሳምንት ጋር እንደማታነፃፅሩት እርግጠኛ ሆኜ መናገር እችላለሁ። በሰቆቃ መሃል እፎይ የሚያስብል ዜና መስማትን የመሰለ ነገር ምናለ ወዳጄ! ባለፈው ሳምንት 2012ን የኋሊት ለመታዘብ አንዳንድ ነጥቦችን ለመነካካት ምክሬ እንደነበር ታስታውሳላችሁ ብዬ አስባለሁ።
ያሳለፍናቸው ሁለት ሶስት ሰኔዎች ጥሩ እንዳልነበሩ በባለፈው ፅሁፌ አንስቼላችሁ ነበር። የዘንድሮውንም ጨምሮ ማለት ነው። የዝነኛውን የኦሮምኛ ሙዚቀኛ ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያን ተከትሎ ያለው ጊዜ እስካለፈው ሳምንት ድረስ እንደ ክረምቱ ሁሉ ጭፍግግ እና ሰቅጣጭ ሁኔታዎችን ያስተናገድንበት ወቅት ነበር። የኮሮና ሳያንሰን እዚህም እዚያም በምናፈነዳው የፖለቲካ ድማሚት በተለይም ደግሞ የሃጫሉን ሞት ታክኮ በተፈጠረው ብጥብጥ በኮሮና ያላጣነውን ሰው አጥተናል። በመቶዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያን ህይወት በጥቂት ቀናት እንዲቀጠፍ ሆኗል። ይህ እጅግ አሳፋሪና አሳዛኝ ነው። ዓለም በኮሮና ምክንያት አንድም ሰው መሞት የለበትም ብሎ ሲታገል እኛ ግን እርስበርስ ለመጠፋፋት ስንታትር ከርመናል።
ይኸው የሰቆቃ መዓት ከክረምቱ ዝናብ ጋር አኮስምኖ እያስቆዘመን ሳለ ድንገት ደግሞ እፎይ የሚያስብለን ብስራተ ዜና ታወጀ። ኢትዮጵያም ከሀዘኗ ትንሽ ቀና አለች። ፈጣሪዋንም አመሰገነች። አዎ ለዘመናት ከውስጥም ከውጭም በእንቅፋቶች ተከበን ስናነሳ ስንጥል የነበረው የአባያችን ጉዳይ ድንግት “ሆነኮ” ሲባል ስንሰማ ችግሮቻችንን ሁሉ ለአፍታም ቢሆን ወዲያ ትተን በሐሴት መስከራችን አይቀሬ ነው። ባይሆን ኖሮ ከሰኔ 22 አንስቶ የነበረውን የመከራ ደመና ማለፍ እጅግ ከባድ ነበር። የሃጫሉ ነገር አሁንም ድረስ በደስታ ውልብ ሲልብኝ ሁሉ ነገሬን ያጨልመዋል። ግን ደግሞ ማምሻም እድሜ ነውና ይህንን ድል ስናጣጥም እና እውቅና ስንሰጥ ነው ለላቀ ድል የምንበቃው።
ስለህዳሴ ግድብ ሲነሳ በርካቶች -እኔንም ጨምሮ- ‘የሞተ ጉዳይ’ አድርገን መቁጠር ከጀመርን ሰንበትበት ብለናል። በየእለቱ ከሚረጨው የሀሰት ወሬ ጋር ተያይዞ ግድቡ እንዳበቃለት ማሰባችንም ሆነ የዚህ ፕሮፓጋንዳ ሰለባ መሆናችን የሚጠበቅ ነበር። ድንገት “የግድቡ የመጀመሪያ የውሃ ሙሌት ሥራ በስኬት ተጠናቀቀ” የሚል ዜና ስትሰማ ግን ከቁዘማ ትወጣና ዳግም የተስፋ አየርን ትምጋለህ። “ይቻላል” ነበር ያለው ኃይሌ እውነትም ትክክል መሆኑን ታረጋግጣለህ።
እዚህ ጋር አንድ ነገር ግን ግርታን ፈጥሮብኝ ማለፉ አልቀረም። በወዲያኛው ጫፍ ያለው ጩኸት ረጭ ማለቱ ምን ይሆን የሚለው ማለቴ ነው። ይህ የኢትዮጵያዊያን ድል ከአባይ ማዶ ያሉትን ፈርኦኖችን ጭራ ማስበቀሉ እሙን ነው። ግና ያለወትሮአቸው ዝምታን መምረጣቸው “ምን አስበው ነው” የሚል ጥያቄ አጭሮብኛል። ምክንያቱም ቀደም ብሎ ያሰሙት የነበረው ፉከራና ቀረርቶ ከግድቡም አልፎ ሞያሌ ድረስ የሚተረተር ነበር የሚመስለው እና። የሆነው ሆኖ እኛ የድል ምዕራፍ ላይ እንገኛለን። ይህ ታሪካዊ ድል ነው። ልክ እንደ አድዋ ሁሉ ማለት ነው። ይህን ድል ጠብቆ ለላቀ ድል ማብቃት ደግሞ የእያንዳንዳችን ኃላፊነት ሆኖ ይቀጥላል።
አስቡት እንግዲህ በአንደኛው የጦር ሜዳ ስትረታ በሌላኛው ደግሞ ትረታለህ። ሰው ነህና በአንድ ጊዜ ከአንድ በላይ የጦር ሜዳዎችን ተሰልፈህ መርታት እጅግ ከባድ ነው።
የህዳሴው ስኬት በኮሮና የጦር ሜዳ ግን እጅ ሳያሰጠን እንዳልቀረ ይሰማኛል። አንዳንዴ ኮሮናና ፖለቲካ በሂሳብ እንደሚባለው “ቀጥተኛ ተዛማጅ” ወይም “ዳይሬክትሊ ፕሮፖርሽናል” ናቸው ያስብላል የምታየው ነገር። ፖለቲካ ሲጦዝ የኮሮና ወረርሽኝ ከፍ ብሎ ሲመዘገብ ታስተውላለህ። ከሰኔ ሃያ ሁለቱ ክስተት በፊት በመቶ ቤት የምንሰማው እለታዊ በበሽታው የተያዙ ዜጎች ቁጥር ከሃጫሉ ግድያ በኋላ በተፈጠረው ብጥብጥ አድብቶ ሲያጠቃን የከረመው አጅሬ ኮሮና እንደቀልድ አምስት መቶ፣ ስድስት መቶ፣ ሰባት መቶ እያለ ሺህ ቤት ለመግባት ጥቂት አኃዞች ብቻ ቀርተውታል። ይህ የመዘናጋት እጅግ ውዱ ዋጋ ነው። አዋጭ ያልሆነ ውድነት ልንለው እንችላለን። በተቀሰቀሰው ግጭት የሞቱ ሰዎችን ቁጥር ስትመለከት ደግሞ ከኮሮናም በላይ ገዳያችን የኛው የሰፈር ፖለቲካ መሆኑን ትረዳለህ።
ይህ ጠቅላይ ሚኒስትራችን “ታሪካዊ” ያሉት የመጀመሪያው ዙር የግድቡ የውሃ መሙላት ተግባር እንደ ግብፅ እና ሱዳን ባሉ የታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ዘንድ ፍጥጫው እንዲያይል አድርጓል። ይሁን እንጂ የባለፈው ማክሰኞ የኢትዮጵያ ክተት ጥሪ ተስፋ ሳያስቆርጣቸው እንዳልቀረ መገመት አይከብድም። ባይሆን ኖሮ ያ ሁሉ ዛቻና ሽለላ የውሃ ሽታ ሆኖ ተንኖ ባልጠፋ ነበር። አምላክ ከሐቅ ጎን ነውና እውነት ታሸንፍ ዘንድ ግድ ነበር። የቱን ያህል የኃያላን ብርቱ ወዳጅ መሆንና የሃብታሞች ባለሟልነትም ሐቅን ደፍጥጦ ተረቺ ሊያደርገን እንደማይችል ያየንበት ክስተት ነውና እጅጉን እንኮራበታለን። የዚህ ታሪክ አካል በመሆናችንም እድለኛ ትውልድ ያደርገናል። የህዳሴ ግድባችንን እውን በማድረጉ ሂደት የብልጽግና ጉዟችንን ለማደናቀፍ ያልተሞከረ ትንኮሳ እንደሌለ በዚህ አጋጣሚ ማስታወሱ አይሰነንም። ይህ ትላንት ግድባችንን ስንጀምር የተወለደ ሰሞነኛ ክስተት አይደለም። የተንኮሉ ድርሰት ከአንድ መቶ ዓመታት በላይ የነበረው ራሱን የቻለ የታሪክ መድብል ነው ማለት ይቻላል። ብቻ ታሪካዊውን የሴራ ጥንቅር በታሪካዊ ክንድ መድፈቅ ችለናል።
የህይወት ዑደት አይቆምም። ይነጋል ይመሻል። ታሪክ ይሰራል። ታሪክም በባለታሪከኞች ተፅፎ ለታሪክ ይቀመጣል።
የእኔን አይነቱን ባለፊደል ጦማሪ ቃላትን እንደ ተራኪ መውሰድ ይቻል ይሆናል። ይህን ርእስ ለመተረክ ትክክለኛው ሰው ነኝ ብዬ ባላስብም የታሪኩ አካል መሆኔ ግን የማይካድ ነውና ለዘመድም ለባዳም የምለው ነገር ቢኖር የብልጽግና ዑደት ተፈጥሯዊ ነው። ማንም ሊያስቆመው የማይችል የታሪክ ጅረት። ልክ እንደ አባያችን።
ይህን ሁሉ የምናወራው በወረርሽኝ ተውጠን የፖለቲካ ጉዟችንም ከጅምሩ በተመሰቃቀለበት ሁኔታ ውስጥ ቆመን መሆኑ የታሪክ አወቃቀሩን ልብ አንጠልጣይ ያደርገዋል። 2012 በብዙ መልኩ ጥሩ ዓመት እንዳልነበር ደጋግመን ስንናገር መቆየታችን አሌ አይባልም። ግና ልንሻገረው ነሐሴን በመስከረም መተካት ብቻ ይጠበቅብናል። አዎ ከነሐሴው ድቅድቅ ጨለማ ወዲያ ማዶ አሻግረን ማየት ከተቻለን በአበቦች የፈካው ጸደይ ከፊታችን አለ። አምላክ እድሜና ጤና ሰጥቶን ለ2013 በሰላም ያድርሰን እንጂ የማንወጣው መከራ አይኖርም። በኮሮና ማዕበል ውስጥ ሁነን የህዳሴን ግድብ እናበስራለን ብሎ ማን ጠበቀን? ያውም በራሳችን አቅም። ማንም!
የዚህን ጉዞ ስኬት ከወዲሁ የሚያረጋግጥልን እና ከኋላችን ትተን የምናልፈውን የመከራ መዓት የሚሸኝልን አንድ መድረክ ቀርቶናል። ታላቁ የአረፋ በዓል። ምናልባትም 2012ን የምንሰናበትበት የመጨረሻው የመከራ ሽኝት ይሆናል። የአባይ ጉዳይ ወሰድ አደረገኝ እንጂ ትልቁ አመጣጤም በዋናነት ስለታላቁ የአረፋ ክብረበዓል ጥቂት ለማለት ነበር።
“የምድራችን ታላቁ የመደመር ቀን” ብለውት ነበር እለቱን ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ አምና ልክ በዚህ ሰዓት ለመላው ሙስሊም ኢትዮጵያዊያን በዓሉን በማስመልከት ባስተላለፉት የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት። እድሜ ለኮሮና ያንን ሁሉ ወደ ኋላ መለሰው እንጂ።
በሙስሊሙ ማህበረሰብ ዘንድ ትልቁን ስፍራ የሚይዘው ይህ በዓል የእርቅና የመስዋዕትነት በዓልም ተደርጎ ይቆጠራል። እንደ እምነቱ አስተምህሮ አዳምና ሄዋን በገነት ውስጥ በነበራቸው ቆይታ የፈጣሪን ትዕዛዝ ባለማክበራቸው ከገነት ሲባረሩ ለመጀመሪያ ጊዜ በምድር ላይ የተገናኙት ዓረፋ በሚባለው ተራራ እና ዛሬ ሙስሊሞች የሐጅ ስርዓተ ፀሎታቸውን በሚያከብሩበት ቦታ ነው። ዓረፋ የሚለው ቃል ከአረብኛ ቋንቋ የተወሰደ ሲሆን ወደ አማርኛ ስናመጣው አወቀ የሚል ትርጉም ይሰጠናል። ዛሬም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሙስሊም ምዕመናን ከሁሉም የዓለማችን አቅጣጫ ተሰባስበው እርስበርስ የሚተዋወቁበት፣ አንድነታቸውን ዳግም የሚያጠናክሩበት እለት ነው። ሐጃጆች በብሔር፣ በጎሳ፣ በዘር፣ በቀለም እና በኢኮኖሚ አቅም ሳይለያዩ ሁሉም አንድ አይነት ጨርቅ ለብሰው በአላህ ጥላ ስር በፍቅር የሚደመሩበት ቀን ነው አረፋ። አላህ በቅዱስ ቁርዓን “ዮውመል ሐጂ አል አክበር” ብሎ እንደተናገረው ትልቅ ግምት የሚሰጠው እለት ነው። ትርጉሙም ታላቁ የሐጅ ቀን ማለት ነው።
ከዚህም በተጨማሪ እለቱ የመስዋዕትነት ቀን ተብሎ ይጠራል። መንፈሳዊ አባታችን የምንለው ነቢዩ ኢብራሂም በስተርጅና ያገኘውን ብቸኛ ልጁን ኢስማኤልን እንዲሰዋ ከአላህ የተሰጠውን ትዕዛዝ ለመፈጸም ያለ አንዳች ማቅማማት ሲሰናዳ አምላክም ይህንኑ መስዋዕትነት ወዶለት የልጁን መስዋዕት በበግ እንዲተካ ማድረጉን የምንዘክርበት እለት ነው። እንግዲህ የበዓል ነገር ሲነሳ እኛ ኢትዮጵያዊያን የምንታወቅበት ድንቅ ባህል አለ። በተናጠል የሚከበር በዓል የለንም። በሙስሊሙም በክርስቲያኑም ዘንድ በዓልን የምናሳልፈው በጋራ ያለንን ተቋድሰን ከወዳጅ ከዘመድ ጋር አብረን በደስታ በማክበር ነው። ዛሬ ኮሮና ያንን ሁሉ የሰዎች አብሮነት እና የመደመር አቅምን ሙሉ በሙሉ እንዲቀር አድርጎታል። በርካታ ሚሊዮን የዓለማችን የሐጅ ፀሎት አድራሽ ሙስሊሞችን የምታስተናግደው ቅድስት መካ እንኳ ዘንድሮ ለሚደረገው የሐጅ ስርዓተ ፀሎት በአንድ ሺህ ሰዎች ብቻ እንዲካሄድ መወሰኗን ሰምተናል። ለእምነቱ ተከታዮች ከዚህ በላይ ውድቀት የለም።
ዘንድሮ በሂጅራ አቆጣጠር መሰረት ለ1441ኛ ጊዜ የሚከበረው የኢድ አል አድሃ ወይም አረፋ በዓል በኮሮናና በሌሎች በርካታ መርገምቶች ጥላ እንዳጠላበት የምንቀበለው መሆኑ ግድ ነው። ቀድሞውኑ ለአምላካዊ ህግጋቶች መገዛት ተስኖት እምቢተኛ የሆነው የሰው ልጅ ከዚህም በላይ ቁጣ ቢወርድበት የሚገርም አይሆንም። አምላክ ግን እንደ ሰው አይደለምና ምህረቱ ሁሌም ይከጀላል። ለበዓሉ ዝግጅት የምናደርገውን እንቅስቃሴ በሙሉ ከዚህ አኳያ ልንቃኘውና ምህረቱን አጥብቀን የምንመፀንበት እንዲሆን ምኞቴ ነው።
በአጠቃላይ ያለንበት ሁኔታ እንደ ሀገርም እንደ ማህበረሰብም አሳሳቢ ደረጃ ላይ ይገኛል። ለበዓሉ ድምቀት የምናዘጋጀው ሁሉ ወንድም እህቶቻችንን ታሳቢ ያደረገና ከሁሉ በላይ የጠቅላይ ሚኒስትራችንን የማዕድ ማጋራት ጥሪ ተቀብለን ከአቅመ ደካሞችና ከድሃ ወገኖቻችን ጋር የምንቋደስበት እንዲሆን ምኞቴ ነው። እንደ ወትሮው እንኳ አንድ ላይ ተሰባስበን ማክበር ባንችልም ድሃ ወገኖቻችንን ግን ያለንን አካፍለን በፍቅር መደመር ግን ይቻላል። ሁሉም ያለውን አካፍሎ በፍቅር ገመድ ለመተሳሰርም ሆነ ወደ ብልፅግና የሚያዳርሰንን የመደመር ድልድይ በዚህ ረገድ ለመገንባት አረፋ ትልቁ መድረክ እና አይነተኛ አጋጣሚ ነው።
ከፍ ሲል የጠቀስኩትን የህዳሴ የጦር ገድል በኮሮናም በመድገም የብልጽግና ጉዞን በአዲሱ ዓመት ለመቀበል ሁላችንም ተስፋን ሰንቀን ፅናትን መታጠቅ ጊዜው አሁን ነው። ያለበለዚያ ከኮሮና የጦር ሜዳ የምንተርፍ አይሆንም።
በስተመጨረሻም ለመላው የሀገሬ ሙስሊም ወንድም እህቶች የእንኳን አደረሳችሁ መልካም ምኞቴን ከመግለፄ በፊት አንድ ነገር አደራ ማለት እፈልጋለሁ። የበደላችን መብዛት የአላህ ቁጣም እንዲበረታብን አድርጓል። ዛሬ የሐጅ ሥርዓተ ፀሎት በወረርሽኙ ምክንያት እንዲቋረጥ ከመደረጉ በፊት በየሳምንቱ የምናከናውነው የጁምዓ ሰላት ነው የተከለከለው። በማን የተባለ እንደሆነ በኛው በራሳችን ጥፋት። የክፋት መብዛት ውጤት ነው ኮሮና ቢባል ማጋነን አይሆንም። መጀመሪያ ከራሳችን ሲቀጥል ከወንድም እህቶቻችን ጋር ከልብ መታረቅ ይኖርብናል። ያኔ ከአላህ ጋርም መታረቅ ይቻለናል። እርሱ ይቅር ባይ ነውና። ለዛሬ ጨርሻለሁ። አምላክ ቸር ያቆየን።
በድጋሚ ለመላው ሙስሊም ኢትዮጵያዊያን እንኳን ለ1441ኛው የዓረፋ በዓል በሰላም አደረሰን አደረሳችሁ።
ዒድ ሙባረክ!
አዲስ ዘመን ሐምሌ 24/2012
ሐሚልተን አብዱልአዚዝ