‹‹ከልብ ካዘኑ እንባ አይገድም›› እንዲሉ ከልብ ካዘኑ ሌሎችን ማገዝ የሚያስችል አቅም ከእያንዳንዱ ሰው እጅ ሞልቷል። የተቸገሩ ወገኖችን ለመርዳት ሐብታም መሆንን አይጠይቅም። ሐብታም እስኪሆኑ ከንፈር በመምጠጥ ማለፍም ለተራበ ሰው ጉራሽ ሆኖ የታጠፈ አንጀቱን አያቃናለትም። ሰዎች ባላቸው አቅም ለችግሮች ለተጋለጡ ወገኖቻችን ለመድረስ ቁርጠኛ ሲሆኑ አቅም ያገኛሉ።
ሰዎች ካላቸውና ከራሳቸው ቆርሰው ለሌሎች ሲጋሩ ቅንጣት ታህል የእነሱ አይቀንስም። ይልቁንም በሚያገኙት የመንፈስ እርካታ ሕይወታቸው በብርሃን እንዲሞላ በፍቅር እንዲንበሸበሽ ይሆናል። ለመስጠት የልብ ቁርጠኛ መሆን እንጂ ብዙ የሚሰጥ ነገር መያዝን አይሻም። በዛሬው የሐገርኛ ዝግጅት ለችግር ለተጋለጡ ወገኖቻችን እንዴት መድረስ እንደምንችል የመፍትሄ ቀዳዳዎቹን የሚያመላክት ነው።
ከእያንዳንዱ ሰው እጅ የሚገኙ የተለያዩ ቁሳቁሶች ሲደመሩ ለተራቡና ለታረዙ ወገኖች ታላቅ ማስታገሻ በመሆን ተስፋቸው እንዲለመልም ያደርጋሉ። ነገሩ እንዲህ ነው። በአንድ እለት ወይዘሮ ሐናን መሐመድ እና ጓደኞቻው ለግብዣ ተሰባስበዋል። በእናታዊ አስተሳሰብ በንጹህ ሕሊና ልብ ለልብ ይጨዋወታሉ። በዚህ ሂደት ውስጥ ቁርስና ምሳቸውን ከዚያ ቤት ያደረጉ የኔ ቢጤዎች እየመጡ ይወስዳሉ። ሌላም ይመጣል ይወስዳል። ሁኔታዎች ቀጠሉ፤ለቁጥር የሚታክቱ የራባቸው ሰዎች እየመጡ ምግብ ይወስዳሉ። ሰራተኞችም እጃቸውን ለመስጠት አልቦዘነም።
ቀኑ ነግቶ እስኪመሽ፣ ወሩ ገብቶ እስኪወጣ፣ ዓመቱ አልቆ ሌላ አዲስ ዓመት ሲተካ አቅም በፈቀደ ልክ ተግባሩ አይቋረጥም። ለረዥም ዘመናት የቀጠለ በሩህሩህ ልቦች የሆነ አስገራሚ ድርጊት ነው። የተሰባሰቡ ጓደኞሞች ልባቸው በሐዘኔታ ተሰበረ። ወገናችን በቁራሽ እንጀራ እጦት ጎዳና ላይ መውጣት ስሜታቸውን ረበሸው። በዚህ የተነሳም የእነሱ በልቶ ማደር ሳይሆን የወገናችን በልቶ ማደር ያሳስባቸው ያዘ። ከማዘን ባለፈም ‹‹ጋን በጠጠር ይደገፋል›› እንዲሉ የተሰባሰቡት ጓደኛሞች ከልብ ተመካከሩ። ወገኖቻችን ጎዳና ከመውጣታቸው በፊት እስኪ የአቅማችንን እናድርግ በሚል ለይተው ለሚያውቋቸው ከእነቤተሰቦቻቸው ለችግር ለተጋለጡት ሰዎች በየቤቱ በመሄድ ምግብና አስቤዛ መስጠትና መደጎም ተጀመረ። በዚህ ዐይነት ሁኔታ ሰባትና ስምንት ዓመታት ተቆጠሩ። ነገር ግን ችግሩ ሰፊ በመሆኑ እነሱ በተጠጉት ቁጥር የችግሩ ስፋትም እያየለ መጣ። ዓለም አቀፍ የሆነው ወረርሽኝ ሲከሰት ደግሞ በቋፍ ላይ የነበሩት ችግሮች ተባባሱ። ከነልጆቻቸው ጎዳና ላይ ወጥተው የሚለምኑት ሰዎች በረከቱ። በዚህ ሁኔታ የሚልሱት የሚቀምሱት የሌላቸው ወገኖቻችን ከነልጆቻቸው ጎዳና ላይ ወድቀው ለከፋ የጤና ችግር ከሚጋልጡ ይልቅ ንጽህናው የተጠበቀ ምግብ የሚበሉበት ‹‹ነጻ ምግብ አዳይ ድርጅት›› መክፈት ፈለጉ። ወጪውን ሲያሰሉት ግን በቀላሉ የሚሞከር አልሆነላቸውም። የእናትነት ልባቸው ግን ተስፋ አልቆረጠም። ማዘናቸውም ከልባቸው አልነጠፈም። ለርሃባቸው መፍትሄ የሚሆን ነገር የሚጀምር ሰው እንጂ የጠፋው የሚያዝን ሰው በየቦታው ማየት የተለመደ ነው ሲሉ ሐሳባቸው ተግባርን እንዲወልድ ተማጸኑ። ባለን ነገር ተግባሩን እንግባበት እና አቅም ያላቸው ሰዎች እንዲያግዙን እንማጸናለን ሲሉ ተስማሙ። ወይዘሮ ሐናን እና ጓደኞቻቸው የእያንዳንዳቸውን የወርቅ ጌጣጌጦች አሰባስበው ሸጧቸው። ያም ሆኖ የሚያስቡትን ማድረግ የሚያስችል የኢኮኖሚ አቅም ሳይፈጥር ቀረ።
ሐዲዱ ውስጥ ገብተን የሚገጥሙንን ችግሮች እየተፋለምን ፈጣሪንም ወገኖቻችንንም እየለመንን ቁራሽ እንጀራ ለሚለምኑት ወገኖቻችን መድረስ ይኖርብናል በሚል ወስነው ወደተግባር ቀየሩት። በዚህ ሂደት ተጸንሶም ‹‹ባቡል ኸይር›› የበጎ አድራጎት ድርጅት ተወለደ።
ወይዘሮ ሐናን መሐመድ የባቡል ኸይር በጎ አድራጎት ድርጅት መስራችና ዳይሬክተር ናቸው። ለመሆኑ ባቡል ኸይር ማለት ምን ማለት ነው? በመስራት ላይ ያለው ምንድን ነው ስንል ጠይቀናቸዋል።
ወይዘሮ ሐናን እንዳሉት፤ ባቡል ኸይር ማለት ትርጉሙ ‹‹የበጎ ስራ በር›› ማለት ነው። በጎ አድራጎት ማህበሩ ለትርፍ የተቋቋመ ሳይሆን በከፋ ድሕነት ለሚገኙና የሚላስ የሚቀመስ ለሚቸግራቸው ሰዎች የሚበላ ምግብ በማቅረብ ላይ የተሰማራ ነው። ምስር፣ ዱቄት፣ ዘይት፣ አልባሳት፣ የመጸዳጃ ሳሙናዎች እና የመሳሰሉትን መሰረታዊ ፍላጎት ማሟያ ቁሳቁሶች ለወር እና ለሁለት ወር መጠቀሚያ እንዲሆናቸው ለተቸገሩት ምስኪን ሰዎች መስጠት ከጀመሩ ከሰባት ዓመታት በላይ ማስቆጠራቸውን ይገልጻሉ።
መንግስት ለትምህርት ቤቶች ዩኒፎርም በነፃ መስጠት ከመጀመሩ በፊት የምስኪን ቤተሰብ ለሆኑ የመንግስት ትምህርት ቤት ለሚማሩ ተማሪዎች የደንብ ልብስ፣ ቦርሳ እና የትምህርት ቁሳቁሶች እንዲሟላላቸው ያደርጉ እንደነበር የገለጹት ወይዘሮ ሐናን፤ ከየቤቱ እና ከየድርጅቶች በአይነትና በገንዘብ በማሰባሰብ ድጋፍ ያደርጉ እንደነበር ያስረዳሉ። አሁን ላይ እነዚህን ቀዳዳዎች መንግስት መሸፈኑ የሚያስመሰግን ተግባር ነው። ነገር ግን በማህበረሰቡ ዘንድ ስር የሰደዱ በርካታ ችግሮች ያሉ በመሆናቸው እነዚህን ችግሮች ለማቃለል ከተቻለም ለመቅረፍ ማህበረሰቡ ያለውን አቅም አስተባብሮ ማገዝና መደገፍ ይኖርበታል። መንግስት እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ የአቅም ውስንነቶች ያሉበት ከመሆኑም በላይ በየአካባቢው ለችግር የተጋለጡ ወገኖችን የሚያስተውለው ማህበረሰቡ በመሆኑ በተለያዩ መንገዶች ለምሳሌ፡- መስራት ለማይችሉ ምስኪኖች ምግብ በማቅረብ፣ የተማሩ ልጆቻቸውን በተለያዩ ድርጅቶቻቸው ውስጥ ስራ በማስያዝ፣ ስራ ለመጀመር የሚያስችላቸው የኢኮኖሚ አቅም በመፍጠርና በሐሳብ በመደገፍ መርዳት የዜግነት ግዴታችን መሆን እንዳለበት ያብራራሉ።
ባቡል ኸይር የበጎ አድራጎት ድርጅት ዓላማ አድርጎ የተነሳው በልቶ ማደር የማይችሉ ምስኪን የሕብረተሰብ ክፍሎችን መመገገብ ነው። በመሆኑም ከመስከረም ጀምሮ በቀን ሁለት ጊዜ 575 አባዎራዎችን በመመገብ ላይ ይገኛል። መመገብ ብቻ ሳይሆን አልባሳትን እና የሕክምና ወጪያቸውንም ጨምሮ በመሸፈን እነዚህ የማህበረሰበ ክፍሎች ያለሐሳብ ደስተኛ ሕይወትን እንዲመሩ እያደረገ ነው።
ባቡል ኸይር የበጎ አድራጎት ድርጅት በዚህ መንገድ የደሃ ደሃ በሚል በመንግስት በኩል የተለዩትን የሕብረተሰብ ክፍሎች በማቀፍ ይሰራል። በተጨማሪ እምነት፣ ሐይማኖት፣ ቀለም፣ ወዘተረፈ ሳይገድባቸው ማንኛውንም የተቸገረ ዜጋ ማገዝ የሚቻልባቸውን እድሎች ይፈጥራል። ሰዎችም ሳይሳቀቁ እየመጡ የሚመገቡባቸው እድሎች ተፈጥረዋል። ከዚህ በፊት በነበሩት የምገባ ሂደቶች አቅምህ ሲፈቅድ እየረዳህ እጅ ሲያጥርህ ደግሞ ክፍተቶች ሊፈጠሩ ይችሉ ነበር። ባቡል ኸይር የበጎ አድራጎት ድርጅት ከተመሰረተ ወዲህ ግን 575 አባዎራዎችን በቋሚነት በቀን ሁለት ጊዜ የሚመግብ ሲሆን በሳምንት ለሶስት ቀን የክርስቲያን እና የሙስሊም ተለይቶ ስጋ ይሰራላቸዋል። ሌሎች ሩዝና መኮሮኒም ይቀርባል። እነዚህም ሰዎች ቤተሰቦቻችን በመሆናቸው ለቤተሰቦቻችን ከሚሰሩት ምግቦች እኩል ደረጃውን የጠበቀና ተመጣጣኝ የምግብ ይዘትን ታሳቢ ያደረገ ምግብ እንደሚዘጋጅም ነው ወይዘሮ ሐናን የተናገሩት።
ከዚያም በመቀጠል ተመጋቢዎች ከቤታቸው እየመጡ በተዘጋጀላቸው ቦታዎች እጃቸውን በመታጠብ የአፍና የየአፍንጫ መሸፈኛ በመልበስ፣ ርቀታቸውን ጠብቀው በተዘጋጁላቸው መቀመጫዎች ተቀምጠው እንዲመገቡ ሲደረግ መመልከት ችለናል።
ይሄን ያህል ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሰው እንደቤተሰብ ቀልቦ መምራትና ማስተዳደር ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቅ በመሆኑ የገቢ ምንጫችሁስ ምንድን ነው? በዚህ መንገድስ መዝለቅ ትችላላችሁ ወይ ስንል ጠይቀናቸዋል።
ወይዘሮ ሐናን ሲመልሱም፤ ወጪው እጅግ በጣም ከፍተኛ ነው። ድርጅቱ የራሱ የሆነ ቦታ የለውም። በዚህ የተነሳ በወር 35 ሺህ ብር ተከራይቶ ነው አገልግሎቱን በመስጠት ላይ የሚገኘው። ለዚያውም ተመጋቢዎችን በማሰልጠን እና ለእያንዳንዳቸው የስራ እድሎች በመፍጠር አብረው እየሰሩ፣ የገቢ ምንጪ እንዲኖራቸው ለማድረግ ጥረት እየተደረገ ነው። በስራ ላይ እየተሳተፉ ተደጋግፎ መስራት መቻሉ የሚፈጥረው የስነልቦና እርካታ ከፍተኛ ነው። በድርጅቱ በኩል ደግሞ አስፈላጊ የሆኑ ግብዓቶችን እንደ እንጀራ፣ ዳቦ፣ ኩኪስ እና መሰል ምርቶችን ማዘጋጀት ቢችል ወጪውን በከፍተኛ ደረጃ ይቀንስለታል። ጥራቱን ደግሞ ይጨምሩለታል። ነገር ግን እንጀራ መጋገር የሚያስችል የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት እንኳን እንዲገባላቸው ጠይቀው እስከ አሁን ምላሽ እንዳልተሰጣቸው ተናግረዋል።
ወይዘሮ ሐናን እንደሚሉት፤ ለተመጋቢ አባዎራዎች እና እማዎራዎች እንዲሁም በእነሱ ስር ለሚገኙ ልጆቻቸው እና ቤተሰቦቻቸው ሙሉ አልባሳት ከነመቀያየሪያው በመስጠት ንጽህናቸውን እንዲጠብቁ ይደረጋል። የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛዎች ይሰጣሉ። ከመደበኛ ተመጋቢዎች ሌላም ዝቅተኛ ደመወዝ ተከፋይ ለሆኑና ብዙ ቤተሰቦች በስራቸው ለሚያስተዳድሩ ሰዎች አልባሳት እና የበዓላት ጊዜ ወጪያቸውን እንደሚሸፍኑላቸው ይገልጻሉ።
የአመጋገብ ሂደቱን ሲገልጹም፤ ቤተሰብ ያላቸው ሰዎች ወደቤታቸው ይዘው የሚሄዱ ሲሆን ሕጻናት ያላቸው እና የጤና እክል ያለባቸው ደግሞ በተለያየ መንገድ እንዲዘጋጅላቸው ይደረጋል።
በአዲስ አበባ አዲስ ከተማ በተለምዶ ኳስ ሜዳ ወይም አበበ ቢቂላ ስቴዲየም በሚባለው አካባቢ የሚገኘው የባቡል ኸይር የበጎ አድራጎት ድርጅት 20 ሰራተኞች ያሉት ሲሆን ለነዚህ ሰራተኞች በወር 54 ሺህ ብር ወጪ ያደርጋል። በቤት ለቤት የለያቸውን አቅመደካሞች እና በቀበሌ የደሃ ደሃ በሚል ተለይተው የተሰጡትን ሰዎች ጨምሮ ከ600 በላይ ሰዎችን በነጻ በቀን ሁለት ጊዜ በመቀለብ ላይ ይገኛል። በተጨማሪም ለተመጋቢዎች በሳምንት አንድ ሳሙና ይሰጣቸዋል። ሕክምናም እንዲያገኙ ይደርጋል። የመብራት ክፍያ ለተቸገሩ ክፍያ ይፈጽማል።
በምግብ አቅርቦት በኩል ቀይ ወጥ ከተሰራ ሩዝ ወይም ፓስታ ተጨማሪ ይሰራላቸዋል። ደረጃውን የጠበቀ ተመጣጣኝ የምግብ ይዘት ያለው ምግብ ይሰራላቸዋል። ወተትም እንዲቀርብላቸው ይደረጋል። አንድም ተመጋቢ የቆሸሸ ልብስ እንዳይለብስና ለበሽታ እንዳይጋልጥ የሚያስፈልጋቸውን አሟልቶ በመስጠት ቁጥጥር ይደረጋል። በዚህ የተነሳም ባቡል ኸይር የበጎ አድራጎት ድርጅት ተመጋቢዎቹን ከማሳደር በስተቀር ሁሉንም ወጪያቸውን እንደራሱ ቤተሰቦች በወር 580 ሺህ ብር ወጪ እያደረገ በማስተዳደር ላይ እንደሆነ ወይዘሮ ሐናን አብራርተዋል።
አንዳንድ ባለሀብቶች እንጀራ አስጋግረው ሰደቃ (ስጦታ) ይሰጣሉ። እነዚህ የሚያደርጉትን ሳይጨምር በወር ለእንጀራ ብቻ 160 ሺህ ብር ወጪ እናደርጋለን ይላሉ። ተረዳድተን ይሄን ወቅት መሻገር ካልቻልን እንደአገር መቀጠል ይቸግራል ሲሉም ያለውን ችግር ያነሳሉ ወይዘሮ ሐናን።
አምስት ጓደኛሞች የዳቦ መጋገሪያ ማሽን ገዝተው ለድርጅቱ ሰጥተዋል። በዚህ ማሽን ለራሱ የሚሆን ዳቦ በማምረት ላይ ይገኛል። ከዚህ በተጨማሪም ኩኪስ መጋገሪያ ማሽን በመግዛት 10 እናቶችን በማሰልጠን ኩኪስ እያመረቱ በመሸጥ የገቢ ምንጭ ተፈጥሮላቸዋል ይላሉ ወይዘሮ ሐናን። በጎ ስራውን ከሚደግፉ ባለሀብት ግለሰቦች እና በውጭ አገራት ከሚገኙ አብሮ አደግ ጓደኞቻቸው በሚገኝ ገንዘብ የምገባ በጎ ስራው እንደሚከናወንም ተናግረዋል።
በድርጅቱ የመመገቢያ አዳራሽ ምሳቸውን ሲመገቡ ያገኘናቸው አቶ ተክሌ ተመስጌን እንደገለጹት፤ ‹‹ይሄን ድርጅት እኔ ፈልጌ መጣሁ እንጂ እሱ አይደለም የፈለገኝ ሲሉ ሐሳባቸውን ይጀምራሉ። አክለውም “ልብስና እንጀራ ካገኘሁ ሌለ ምን እፈልጋለሁ። ይሄን ከዘራ የገዙልኝም እነሱ ናቸው። እንደዚህ የሚጣፍጥ ምግብ በልቼ አላውቅም። በሳምንት ሁለት ሶስት ጊዜ ስጋ እንመገባለን። ከዚያ በተጨማሪ ፓስታ፣ ሩዝ፣ ክክ፣ ምስር በተመጣጠነ መንገድ እየተሰራልን እንበላለን። መመገብ ከጀመርኩ ስምንት ወር አልፎኛል። አሁን በጸሎት ላይ ነው ያለሁት። ጸሎቴም ፈጣሪ እነዚህን ሰዎች እድሜያቸውን እንዲያረዝምልኝ እና መንግስትንም የወገኖቻችንን ሰላም ማስጠበቅ እንዲችል ፣ አቅሙን እንዲፈጥርለት ነው” ሲሉ በጧት በማታ እየጸለዩ እንደሆነ ተናግረዋል።
ወይዘሮ ዙበይዳ አወል በበኩላቸው፤ “አልሃምዱሊላህ ፈጣሪ ስራ የሌለኝ ደካማ እንደሆንኩ አውቆ እነዚህን ሰዎች ሰጠኝ። እንደልቤ እያበሉ፣ እያለበሱ ይዘውኛል። ጤና የለኝም ነበር አሳክመውኛል። ከነልጆቼ እያለበሱ፣ እያበሉ ሕይወቴ እንዲኖር አድርገውኛል። መሪያችን የተባረከ ይሁን። እነዚህ ሰዎችም የተባረኩ ይሁኑ። ፈጣሪ ሁላችንንም አዋድዶ በሰላም ያኑረን” ሲሉ መርቀዋል።
ሌሎች አገራት ሰዎች ምግብ ሲቸግራቸው የሚመገቡበት ድርጅት ያቋቁማሉ። ለዚህም ባለሀብቶችና የፋብሪካ ባለቤቶች የተወሰነ መጠን ያለው ገንዘብ በዘላቂነት እንዲቆርጡ ማህበራዊ ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ በመንግስት በኩል ግዴታ ይጣልባቸዋል። እንኳን እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ብዙ የሚርባቸው ወገኖች ባሉበት አገር ሀብታም አገራትም የመመገቢያ ጣቢያዎች ያቋቁማሉ። ስለዚህ አዲስ ነገር ተደርጎ ሊታይ አይገባም። መንግስት ደግፎ እንዲህ አይነት ለራባቸው ሰዎች የሚሆኑ የነጻ መመገቢያ ጣቢያዎችን ማስፋፋት አለበት። በእነዚያ አገራት ድርጅቶችና ባለሀብቶች ግብዓት ያቀርባሉ። የሚመግበው ድርጅት ያለ ሰቀቀን አብስሎ ያቀርባል። ባቡል ኸይር በጎ አድራጎት ድርጅት አዲስ እንደመሆኑ በዚያ ደረጃ የመንግስት እገዛ ባይጠብቅም በተወሰኑ ቀዳዳዎች ላይ ደግሞ የመንግስት ድጋፍም ሊታከልበት እንደሚገባ ወይዘሮ ሐናን አስረድተዋል።
ድርጅቱ በራሱ ተነሳሽነት መንግስትና ማህበረሰቡን በነጻ እያገለገለ ከመሆኑ የተነሳ ምን እገዛዎች ተደረጉለት? በቀጣይስ በዚህ በጎ ተግባሩ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ምን መደረግ አለበት ይላሉ? በሚል ላቀረብንላቸው ጥያቄም እንዲህ ሲሉ ምለሽ ሰጥተዋል።
በመንግስት በኩል እስከአሁን ድረስ የተለየ ድጋፍ አልተደረገም። ሌላው ቀርቶ ድርጅቱ በዚህ ደረጃ ለአቅመደካሞች እደርሳለሁ ብሎ ሲነሳ የሚያስፈልጉትን ማሟላት አለበት። የመንግስት ተቋማት በሕጋዊ አሰራሩ መሰረት ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት ቢችሉ ያም እንደ እገዛና ድጋፍ በተቆጠረ ነበር። ነገር ግን መብራት እንኳን አግኝተን እንጀራ መጋገር አልቻልንም ይላሉ። የመስሪያ ቦታ ችግራቸውንም መንግስት መፍትሄ እንዲሰጥበት ይጠይቃሉ። በሌላ በኩል ጠቅላይ ሚኒስትሩን ለኢትዮጵያ ሕዝብ ከፈጣሪ የተሰጠው ስጦታ አድርገው የሚመለከቱት ወይዘሮ ሐናን ኢትዮጵያ ተለውጣ ማየት ከፈለግን የእሳቸውን ጥረት በያለንበት የሥራ ዘርፍ መደገፍና ማገዝ ይገባናል ይላሉ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በነጻ ይሄን በጎ ተግባር እየሰራ መሆኑን ሰምተው በኢድአልፈጥር በዓል በአካል ተገኝተው ለተመጋቢዎቻችን የበግ ስጦታዎች አበርክተውልናል ያሉት ወይዘሮ ሐናን፣ ከዚያ በተጨማሪ የአዲስ ከተማ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ይታያል ስራችንን ተመልክተው በአገልግሎት አሰጣጣችን ተደስተዋል። በቀጣይ ጉብኝታቸው ደግሞ የማብሰያ እቃዎች፣ ሮቶዎች፣ ምስርና ዱቄት አበርክተውልናል። የተለያዩ አልባሳትንም ወይዘሮ አዳነች አበቤ ገቢዎች ሚኒስትር በነበሩበት ወቅት ድጋፍ እንዳደረጉላቸው በመጥቀስ አመስግነዋል።
በኢትዮጵያ እየተስፋፋ ከመጣው የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ጋር ተያይዞም በርካታ ዜጎች ኑሮአቸውን መሸፈን አልቻሉም። ከዚህ ጋር ተያይዞ በርካታ ዜጎች ከነልጆቻቸው ጎዳና ላይ ይወድቃሉ። በዚህ የተነሳ ለወገናቸው ችግር የሚደርሱ እንዲህ አይነት ድርጅቶች መቋቋም መቻላቸው ይበል የሚያሰኝ ነው። ይሁን እንጂ በአገራችን ተግባሩ የተለመደና የሰፋ ባለመሆኑ የሁሉንም አካል ድጋፍ ካላገኘ መቀጠል እንደሚሳነው ጥርጥር የለውም። መንግስትም እንዲህ አይነት ድርጅቶች ቋሚ ገቢ እንዲኖራቸው፣ መስሪያ ቦታ እንዲኖራቸው ማድረግና ሌሎች ሃላፊነቶች መወጣት ይኖርበታል ሲሉ ወይዘሮ ሐናን መልዕክት አስተላልፈዋል።
አዲስ ዘመን ሐምሌ 24/2012
ሙሐመድ ሁሴን