
በተደጋጋሚ የሚያጋጥመኝ ነገር ነው። ታክሲ ውስጥ ከረዳት ጋር በጣም ነውር የሆነ ስድብ የሚሰዳደብ ሰው አለ። የጫማ ጽዳት ሥራ ከሚሰራ (ሊስትሮ) ጋር ክንዱን ሰቅስቆ ለፀብ የሚጋበዝ ሰው አለ። እንዲህ አይነት ሰው ፈሪ እና በራሱ የማይተማመን የበታችነት ስሜት ያለበት ሰው ነው። የመቆጣት እና የማስፈራራት ታሪክ እንዲኖረው የሚፈልገው በአቻዎቹ ላይ ሳይሆን ምስኪን መስለው በሚታዩት ላይ ነው። እንዲህ አይነቱ ሰው ከእሱ የበላይ የሆነ ሰው ቢናገረው፣ ቀና ብሎ አይናገርም፤ ይህ የፈሪዎች ባሕሪ ነው፤ ነገሮችን መናቅ አይችሉም።
በተመሳሳይ ብዙ ጊዜ የሚያናድደኝ ነገር የሚያጋጥመኝ ካፌ ውስጥ ከአስተናጋጅ ጋር የሚጣሉ፣ አስተናጋጅ የሚሳደቡ፣ አስተናጋጅ ላይ የሚደነፉ ሰዎች ናቸው። በስመ ‹‹ደንበኛ ንጉሥ ነው›› ደንበኛው ሁሉ የቤቱን አመል ምስኪን አስተናጋጅ ላይ ሊደነፋ አይገባውም።
ምግቡ ዘገየ ብሎ የሚደነፋው አስተናጋጇ ላይ ነው፤ አስተናጋጇ እኮ ተቀብሎ ማምጣት እንጂ እሷ አይደለችም የምታበስለው። መቼም ያን ያህል ያቆያት ከኪችን ጠረጴዛው ጋ ማድረሱ አይደለም፤ እሷም እኮ ቶሎ ቢመጣ አትጠላም፤ ችግሩ ግን ያለው ከአዘጋጆች ነው። የምግቡን ይዘትና ጣዕም በተመለከተም የሚደነፋው አስተናጋጇ ላይ ነው። አስተናጋጇ እኮ ጤፍ አቅራቢ አይደለችም፤ የእሷ ሥራ የታዘዘውን መናገርና የተዘጋጀውን ምግብ ለደንበኛው መስጠት ነው። እንዲህ እንዲህ አይነቱ አስተያየት ነው ለባለቤቱ የሚነገረው።
ፈሪዎች አስመሳዮች ናቸው። የሚደነፉት አቅም የላቸውም ብለው የሚያስቡት ላይ ነው። ለምሳሌ፤ አስተናጋጇ ላይ ሲደነፋ የነበረ ደንበኛ አንድ ወጠምሻ ሥራ አስኪያጅ መጥቶ ‹‹ምንድነው?›› ቢለው፤ በዚያው ሲደነፋ በነበረበት ድምጸት አይቀጥልም። እየተለሳለሰ ሊናገር ይችላል፤ ወይም ይባስ ብሎ ምንም ችግር እንደሌለ አድርጎ ሊናገር ይችላል። አለ ሲል የነበረውን ችግር የአስተናጋጇ ሊያደርገው ይችላል። አልታዘዘኝ ብላ ነው ብሎ ሊሸመጥጥ ይችላል፤ የፈሪ ባሕሪው እንዲህ ነው!
እዚህ ላይ ልብ መባል ያለበት ነገር የሚያናድዱ አስተናጋጆች የሉም ማለት አይደለም። አንድ የሚያውቃት ደንበኛ ጋ ሄዳ የኋላ ጥርሷ እስከሚታይ ድረስ እየሳቀች ቆማ የምታወራ ትኖራለች። እግርሽ፣ ዳሌሽ እያለ ከሚያሽበለብላት ጋር ቆማ የምትቆይ ልትኖር ትችላለች። ዳሩ ግን ይህን የሚያደርጉት እጅግ በጣም ጥቂቶች ናቸው። ብዙ አስተናጋጆች በጣም የሚፈሩ ናቸው። አንዳንዱ ዋልጌ ሊያዋራት ሲሞክር እንኳን ‹‹አይፈቀድም!›› ብለው የሚሄዱ ናቸው።
ይህም ሆኖ አጋጠመ እንበል። አንድ ደንበኛ አንዲት አስተናጋጅ አልታዘዘው ብላ ከሌላ እሷ ከለመደችው ደንበኛ ጋር ቆማ ስታወራ ታዘበ እንበል። እዚህ ላይ ሁለት ነገር ማድረግ አለበት ብዬ አስባለሁ። ደንበኛው ከቸኮለ (በእርግጥ ማንም ሥራ ፈት ደንበኛ የለም) ሌላ አስተናጋጅ መጥራት፣ ሌላ አስተናጋጅ ከሌለም እሷኑ ጮክ ብሎ መጥራት እና ትዕዛዙን ማዘዝ ነው።
ደንበኛው ኃላፊነት የሚሰማው ሆኖ፤ ምክረ ሀሳብ መስጠት ከፈለገ (የአስተዋይ ሰው ባህሪ ነውና) አስተናጋጇን ጠርቶ መምከር ነው። እንዲህ ስታደርጊ ባለቤቱ ቢያይሽ ችግር ነው። እኔም ብሆን ለባለቤቱ ብናገርብሽ ትቀጫለሽ። ደንበኛ ሲጠራሽ እየሰማሽ ዝም ማለት ነውር ነው፤ ወይም እንዳትሰሚ ሆነሽ መራቅ የለብሽም…. ብሎ መምከር ይችላል። ከዚህ ሁሉ የከፋ ችግር ካጋጠመው ባለቤቱን ጠርቶ በሠለጠነ መንገድ መንገር ይቻል ነበር፡፡
ችግሩ ግን ወዲህ ነው! የበታችነት ስሜት ያለበት ሰው እልሁን ሁሉ የሚወጣው በምስኪኗ አስተናጋጅ ነው። አስተናጋጇን ጠርቶ እጅግ ነውር የሆነ ስድብ ይሳደባል። ምናልባትም እሱን ራሱን የሰደቡትን ስድብ እሱ ደግሞ በሚያሸንፋቸው ሰዎች ላይ ይወጣዋል ማለት ነው። እንዲህ አይነት ሰው ከእኩያው ጋር ሊጣላ አይችልም። ያቺ ምስኪን አስተናጋጅ ግን እንደማትደበድበው ስለሚያውቅ የመሳደብ ምኞቱን ሁሉ ይወጣባታል፤ ግፋ ቢል ዕድሏን እየረገመች ብታለቅስ ነው።
አንዳንዱ ደግሞ ዝም ብሎ አልቃሻና ብሶተኛ ይሆናል። በትንሽ ትልቁ ‹‹ባለቤቱን ጥሩልኝ›› የሚል ይሆናል። ደንበኛ ሁሉ ንጉሥ አይደለም። አንዳንዱ ደንበኛ ‹‹ምነው ባልመጣብኝ›› የሚያስብል ነው፤ ‹‹ከእሱ የሚገኝ ገንዘብ በአፍንጫዬ ይውጣ›› የሚያሰኝ ነው። እንዲህ አይነቱን አመለቢስ ደንበኛ፤ ንጉሥ ነው ማለት አያስኬድም። መጠቀም ያለበትን ነገር በሥነ ሥርዓት መጠቀም የማይችል ከሆነ ችግር ነው። ፀባዩ አስቸጋሪ ከሆነ ንጉሥ ሊሆን አይችልም። ለምሳሌ ከተዘጋጀ በኋላ ያየዙትን የሚቀይሩ አሉ፤ ምግቡ ተሰርቷል ሲባሉ ‹‹እሪ›› ብለው ይደነፋሉ፤ ይሳደባሉ። የዚህን ጊዜ አስተናጋጇ ትሳቀቃለች።
በተለይም በቡድን ሆነው የሚታዘዝ ትዕዛዝ ደግሞ በጣም አስቸጋሪ ነው። እንዲህ አይነት ጭቅጭቅ የሚያጋጥመውም ከሁለት በላይ ሆነው ሲስተናገዱ ነው። ለሚያዝዙት ነገር የጋራ ውሳኔ ላይ አይደርሱም። አንዱ ይሄ ነው ሲል ሌላው አይ ይሄ ነው ይላል፤ እነርሱ ሲጨቃጨቁ አስተናጋጇ ሥራ ፈታ ነው የምትቆመው። ይህኔ ደግሞ ሌላኛው ደንበኛ ዘገየሽ ብሎ ይደነፋል። እስከምትወስኑ ብላ ስትሄድ ደግሞ ራሳቸው ሲጨቃጨቁ የነበሩትም ይቆጧታል።
እዚህ የቡድን መስተንግዶ ላይ ሌላው የሚገርመኝ ነገር አንድ ጊዜ አያዙም። መጀመሪያ ይህን ያህል ይበቃናል ይባልና ይታዘዛል፤ እሱን ከታዘዘ በኋላ ሌላ ይጨመር ይባልና ይጨመራል። ያ ዘግይቶ የተጨመረው ከመጀመሪያው ትዕዛዝ እኩል እንዲመጣ ይጠበቃል። በመሃል ደግሞ የሌላ ደንበኛ ትዕዛዝ ይኖራል። ደንበኞች ግን ይሄን እንኳን አይረዱም።
በእዚህ ሁሉ ነገሮች ውስጥ ጨዋነት ይጎላቸዋል። ልክ ያልሆነውን ነገር በሥርዓት ከመናገር ይልቅ የሚሳደቡት ይበዛሉ። ምግብ ላይ መሰዳደብ እጅግ በጣም ነውር ነው። ምንም እንኳን የሚበላው ከፍሎ ቢሆንም፤ ዳሩ ግን እሱም ቢሆን የሚያዘውን ነገር በሥርዓት ማዘዝ አለበት፡፡
በዚያው ልክ ደግሞ እጅግ በጣም ይሉኝተኛ የሆኑ ደንበኞችም አሉ። ያዘዙት ነገር የተሳሳተ ወይም የተበላሸ ሆኖ፤ ባለቤቶችም ይህን ችግር አምነው ይቅርታ ጠይቀው ይቀየር ሲሉት ‹‹በፍፁም!›› የሚል ደንበኛ አለ። የአስተናጋጇ ጥፋት ሆኖ ሳለ፤ አስተናጋጇን ላለማሳጣት ሲል ‹‹የራሴ ስህተት ነው›› ብሎ አስተናጋጇን ከባለቤቱ ቁጣ የሚያድን ደንበኛም አለ። እያወራን ያለነው ስለፈሪዎችና አስመሳዮች ስለሆነ ነው።
የፈሪዎች ቁጣ ዓይን አወጣ ነው። በዙሪያቸው ያለ ሰው ይታዘበናል እንኳን አይሉም።
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ሰኞ ሚያዝያ 20 ቀን 2017 ዓ.ም