ነገረኛ ሆነን ነው ወይስ ሃሳባዊ?

የውጭ ሀገራትን (በተለይም የምዕራባውያንን) የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች አስተያየቶች ልብ ብላችሁ ታውቃላችሁ? በጽሑፍም ሆነ በቪዲዮ የሚሰራጩ መረጃዎች፣ መዝናኛዎችና የተለያዩ ሃሳቦች ከአስተያየት መስጫው ሥር አስተያየት ይሰጥባቸዋል። እነዚህን አስተያየቶች ከሀገራችን አስተያየቶች ጋር እያነፃፀርኩ እከታተላለሁ። ልዩነታችን ሰፊ ነው።

የውጮቹ የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ላይ የሚሰጠው አስተያየት በብዛት አድናቆት እና ምሥጋና ነው። ይህ መሆኑን በበጎ ብቻ ልናየው እንችላለን። ዳሩ ግን የሃሳብ ፍጭት አላይበትም። እንደ እኛ ካልተሳደቡበት ማለት አይደለም። ዳሩ ግን ለተለጠፈው ጽሑፍ ወይም ለተለቀቀው ቪዲዮ ሞጋች የሆኑ አስተያየቶች ብዙም አያጋጥሙም። ሁሉም ለማለት በሚያስችል መልኩ አድናቆት እና ምሥጋና ናቸው።

በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ደግሞ ልብ በሉ፤ ስድድብ እና ነውር ነገሮች ያሉበትን ማለቴ አይደለም። ከእሱ በፊት ክርክሮችን ልብ እንበል። አንድ ታዋቂ ሰው የሆነ ነገር ሲጽፍ የአስተያየት መስጫው ላይ ሰዎች በምልልስ ይከራከራሉ። እነዚህ ሰዎች ሃሳባውያን ናቸው። ሞጋች ሃሳቦችን ይዘው ተጠይቃዊ(ሎጂካል) በሆነ መንገድ ይከራከራሉ። በቪዲዮ ለተለቀቀ ነገር የተሰማቸውን አስተያየት ይሰጣሉ። በእዚህ በኩል የኢትዮጵያውያኑ የተሻለ ይመስለኛል።

የእኛ የኢትዮጵያውያን አደገኛው ችግር ስድድቡ እና ነውር ቃላት መጠቀሙ ነው። አንድ ሀገር አቀፍ ሚዲያ ለለጠፈው ዜና የሚሰጠው አስተያየት ከዜናው ጋር ምንም ግንኙነት የሌለው ይሆናል። ተቋሙን በፈረጁበት መንገድ ይሳደባሉ። ለእነርሱ የሚወግን ዜና እንኳን ቢለጥፍ የሚሰጠው አስተያት ግን የስድብ ይሆናል።

ታዋቂ ግለሰቦች ሃሳባቸውን ሲያጋሩ፤ በጨዋነት ምክረ ሃሳብ ከመስጠት ይልቅ ሹፈት እና ቀልዶች ይበዛሉ። ይህ ስለተለመደ ይመስላል አንዳንድ ገጾች የፈጠራ ችግር ይለጥፋሉ። የፈጠራ ችግር ማለት ምክር የሚፈልጉ መስለው ያልደረሰባቸውን ነገር እንደደረሰባቸው አድርገው(ለምሳሌ የፍቅር ታሪክ፣ ከባሌ ጋር በወሲብ አልተጣጣምኩም…. አይነት ነገሮች) ይጽፋሉ። ዓላማው በሚሰጡ አስተያየቶች ለመዝናናት ይመስላል።

በውጮች የማህበራዊ ሚዲያ ግን ይህ ዓይነት ባሕል ያለ አይመስለኝም። አንዲት ሴት የምሯንም ይሁን በፈጠራ ከባሌ ጋር እንዲህ ሆንኩ ብትል፤ የሚሰጡት አስተያየቶች የምክር ናቸው። በኢትዮጵያ ሲሆን ግን ሹፈት እና ቀልድ ነው።

በውጮች የማህበራዊ ሚዲያ ብዙ ነገሮች ትምህርታዊ ናቸው። ለምሳሌ፦ በዋናዎቹ ሚዲያዎች የማይፈቀዱ ከባሕልና ወግ ጋር የሚቃረኑ ከመራቢያ አካላት ጋር የተያያዘ ምክር የሚሰጡ የሕክምና ባለሙያዎች አሉ። በእርግጥ አሁን አሁን በኢትዮጵያም በቲክቶክ እየተለመደ መጥቷል። በውጮቹ ያለው ጥሩ ነገር፤ አስተያየት የሚሰጡት ሰዎች የሚያበረታቱ ናቸው። ምሥጋናቸውን ይገልጻሉ፤ ጥሩ ትምህርት እንዳገኙበት ይናገራሉ። ኢትዮጵያ ውስጥ ሲሆን ግን አንዱ ዝም ብሎ ድንገት ተነስቶ ‹‹አንተን ብሎ ሐኪም!›› ሊል ይችላል። ‹‹አንተን ብሎ ሐኪም›› ከማለት ግን የተሳሳተበትን ቦታ መናገር ይሻል ነበር፤ ችግሩ ተሳዳቢው ሰውዬ ሐኪሙ ትክክል ይሁን ስህተት የት አውቆት?

ያም ሆኖ ግን ከውጮች ለምን አላደረጉትም ብዬ የምገረምበት ነገር አይሞግቱም። ምናልባት በዋናዎቹ ሚዲያዎቻቸው የሃሳብ ፍጭት ነፃነት ስላለ ማህበራዊ ሚዲያዎቻቸውን ለአድናቆትና ምሥጋና ብቻ እየተጠቀሟቸው ይሆን?

በሌላ በኩል ደግሞ የእኛ ሃበሾች የተለየ እንፈላሰፋለን ማለት ነው? ብዬ አስባለሁ። ከነጮች የተሻለ እንፈላሰፋለን ለማለት የሚያስደፍር አይመስልም። ዳሩ ግን ቀልዶች እና የሹፈት መልሶች ደግሞ ብዙ የማሰብ ውጤቶች ይመስላሉ። አሳዛኝ ክስተት ላይ ሳይቀር የሚቀልዱ ሰዎች አሉ። ይህኛው ነውር ነው። ቀለል ባሉ ነገሮች ላይ የሚቀለዱ ቀልዶች ግን ‹‹ሐበሻ ይህን ያህል ፈላስፋ ነው እንዴ!›› የሚያሰኙ ናቸው።

ይህን ጽሑፍ ስጽፍ በውጭው ዓለም ያሉትን አስቂኝ አስተያየቶች ከበይነ መረብ ለመበርበር ሞክሬ ነበር። አስቂኝ አስተያየቶች ተብለው ተመርጠው በተለያዩ ድረ ገጾች የተሰነዱ ከ100 በላይ አየሁ። ከሐበሻ ቀልዶች ጋር አይነፃፀሩም። ብርቅ ሆኖባቸው እንጂ ሐበሻ ውስጥ ማንም ሊቀልደው የሚችለው ነው። ለምሳሌ አንድ ቦታ ላይ ያገኘሁትና የተሻለ ፈገግ ያሰኘኝ፤ አንዱ ስለቤተሰቦቹ ጽፎ ‹‹ዛፍ ራሱ የአንተን ቤተሰቦች ያህል ቅርንጫፍ የለውም›› የሚል ነው። በተረፈ አብዛኞቹ በጣም ግልጽ የሆኑ እና ማንም ሰው ሊላቸው የሚችሉ ናቸው።

የሐበሻ ግን ቀልድ ይበዛዋል። በቁም ነገር ለተጠየቀ ጥያቄ የሚሰጠው መልስ የሹፈት ነው። ለምሳሌ፤ አንዱ ቆየት ባሉ ዘፈኖች ውስጥ የሚታወቀውን ‹‹አራት መቶ ፍቅር ሦስት መቶ ትዝታ›› ጠቀሰና ‹‹ምን ማለት ነው ግን?›› ብሎ ጠየቀ። አንዱ የሰጠው መልስ፤ ‹‹አራት መቶ ሴቶችን ታፈቅራለህ፤ ትዝ የሚሉህ ግን ሦስት መቶዎቹ ብቻ ናቸው›› የሚል ነበር።

አንዱ ደግሞ በባሕላዊ ዕቃ(ሰፌድ) ምግብ እየበላ ‹‹እንብላ›› ብሎ ለጠፈ። ሰፌዱ ከጫፉ በኩል እንደማለቅ ብሎ ሰበዞች ተነቃውለዋል። አንዱ የሰጠው መልስ ‹‹አባ ምግቡ እስከሚመጣልህ ድረስ ሰፌዱን እየበላኸው ነበር እንዴ?›› የሚል ነበር።

አንዴ ደግሞ እንዲህ ብሎ ለጠፈ። ‹‹የሕክምና ተማሪዎች የሚያሳዝኑኝ 5 ማርክ ብቻ ለሚይዝ ጥያቄ ሁለት ሺህ ገጽ የሚያነቡት ነገር›› ሲል፤ ለእዚህ ሰው አንዱ የሰጠው ምላሽ ‹‹ሳያነቡ የዘለሉት ገጽ ላይ ያለው በሽታ በያዘህ!›› የሚል ነበር።

አንዳንዶቹ እንዲህ ብሽሽቅ በሚመስል መንገድ ሆነውም የሚያዝናኑ ናቸው። ከማሳቅ ባለፈ እግረ መንገዳቸውንም የሚያስተምሩ ናቸው። ለምሳሌ፤ ለ5 ማርክ ብለው 2000 ገጽ መጽሐፍ ለምን ያነባሉ? ያለው ሰው ሰነፍ ተማሪ ነበር ማለት ነው። ለሰነፍ ተማሪ የማጥናት ዋናው ዓላማ ማርክ(ነጥብ) ነው ማለት ነው። ሕክምና ደግሞ ጥንቃቄ ይፈልጋል። የምርም አንድ ያላነበቡት ነገር ቢኖር ችግር ይፈጠራል ማለት ነው። ምንም እንኳን የጻፈውም፤ አስተያየት የሰጠውም ለቀልድ ብለው ቢሆንም፤ እግረ መንገዱን ግን የአስተማሪነት ሚናም አለው።

አንዳንዶቹ ደግሞ በራሳቸው ላይ በመቀለድ የሚያስቁም አሉ። የሚሰጡት መልሶችም እንደዚሁ በራስ ላይ በመቀለድ ይሆናል። ለምሳሌ፦ አንዱ ‹‹አልጋ ላይ ተኝቼ በቴሌቪዥን የአካል ብቃት እንቅስቃሴ የምከታተለው ነገር ነው የሚገርመኝ›› ብሎ ለጠፈ። አንዱ መልስ ሲሰጥ፤ ‹‹እኔ አለሁ አይደል ሎተሪ ሳልቆርጥ አሸናፊ ቁጥር የምከታተል›› የሚል ነበር።

በእርግጥ እንዲህ አይነት ነገር በየሀገሩ ይኖራል። እንደ ሰው የጋራ የሚያደርጉ ነገሮች ይኖራሉ። ምናልባት የሐበሻውን በቅርበት ስለማውቀው ሊሆን ይችላል። የሐበሻ ‹‹መፎጋገር›› ግን ጠንከር ያለ ሳይሆን አይቀርም። እዚህ ላይ ለመጥቀስ የማይመቹ ከፆታዊ ጉዳዮች ጋር የሚያያዙ፣ ከብሔር ጋር የሚያያዙ… ቀልዶች አሉ። ከብሔር ጋር የሚያያዙ ሲባል ግን ሁሉም ነውር ነው ማለት አይደለም። ከሥራ ባሕል ጋር፣ ከአካባቢው ሰዎች ስነ ልቦናዊ ባሕሪ ጋር የሚቀለዱ ቀልዶች አሉ። ለምሳሌ፦ ከጉራጌ ሥራ ወዳድነት ጋር፣ ከምሥራቅ ኢትዮጵያ ሰዎች ግልፅነት ጋር፣ ከሰሜን ኢትዮጵያ ሰዎች ተግደርዳሪነትና ወግ አጥባቂነት ጋር…. የተያያዙ ቀልዶች ይቀለዳሉ።

እኛ ሐበሾች እንዲህ የሆንነው ነገረኛ ሆነን ነው ወይስ የሃሳብ እና የቀልድ ጨዋታ ሰዎች ሆነን ይሆን? መሰዳደቡ እና አንዳንድ በማይቀለዱ ነገሮች የምንቀልደው ነገር ነውር ቢሆንም፤ እንዲህ መጨዋወቱ ግን ሰዋዊ ነው። አንባቢዎችም አንዳንድ ነገሮችን ከማክረርና ፀጉር እየሰነጠቁ የብሔርና የሃይማኖት መልክ ከማስያዝ ቀለል አድርገው በቀልድ ብቻ ቢያልፉት ጥሩ ነው።

ከምንም በላይ ግን አዎንታዊ አስተያየቶች፣ ምሥጋና እና መደናነቅም ይልመድብን!

ዋለልኝ አየለ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሚያዝያ 18 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You