አዲስ አበባ፡- የአሽዋና የጠጠር ማምረቻ ቦታዎች ለወጣቶች ተላልፈው በመሰጠታቸው በመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶች ላይ እንቅፋት መሆናቸውን የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን አስታወቀ።
ዋና ዳይሬክተሩ አቶ ሀብታሙ ተገኝ የባለስልጣን መስሪያ ቤቱን የስድስት ወር አፈፃጸም ለቋሚ ኮሚቴው ባቀረቡበት ወቅት እንደተናገሩት ከዚህ ቀደም ለመንገዶች ግንባታ ግብአት የሚሆኑ ጠጠርና አሸዋ በነጻ የሚወጣባቸው በተለያዩ ቦታዎች የሚገኙ ካባዎች ለወጣቶች ተላልፈው በመሰጠታቸው ለግንባታዎች መጓተትና መቆም ምክንያት ሆነዋል። ባለስልጣኑ ከተቋራጮች ጋር ስምምነት ውስጥ ሲገባ እነዚህን ግብአቶች በነፃ እንደሚያገኙ ታሳቢ አድርጎ ነው ያሉት ዳይሬክተሩ ተቋራጮቹ ለነዚህ ግብአቶች ገንዘብ ሲጠየቁ ስራ እያቆሙ መሆኑን ገልጸዋል።
አዲስ ውል ተፈጽሞ ተቋራጮች ገዝተው ይጠቀም ከተባለ የግንባታ ወጪው በትንሹ በአስር በመቶ የሚጨምር በመሆኑ በርካታ ፕሮጀክቶች ሊቋረጡ እንደሚችሉም ዳይሬክተሩ ተናግረዋል። ችግሩ ከዚህ ቀደም ዝቅተኛ አፈጻጸም ለነበራቸው ኮንትራክተሮች ስራ ለማጓተት በር እንደከፈተላቸው በመግለፅም በአሁኑ ወቅት ጥገና ለማካሄድም አስቸጋሪ ሁኔታዎች መኖራቸውንም ጠቁመዋል።
ዳይሬክተሩ ጨምረው እንዳብራሩት በአንዳንድ አካባቢዎች እነዚህን ምርቶች ለማውጣት ሲኬድ ወጣቶቹና ህዝቡ ተደራራቢና ለመመለስ የሚያስቸግሩ ጥያቄዎች ያነሳሉ። መሆኑም የየክልሉ አስተዳደሮች ችግሩን ለመፍታት መንቀሳቀስ አለባቸው። በቅርቡ ከይርጋ ጨፈ ሀገረ ማርያም ለሚሰራው መንገድ 90 ሚሊየን ካሳ ተጠይቆ ቢከፈልም አሁንም ተጨማሪ ጥያቄ መቅረቡን በማስታወስ ወጣቶቹ ስራ እያስቆሙ ስለሚደራደሩ ጉዳዩ የኪራይ ሰብሳቢነት ምንጭ እየሆነ እንደመጣም ገልጸዋል። በተመሳሳይ ከጭኮ ይርጋ ጨፌ የሚገነባው መንገድ አባያ የምትባል የጉጂ ዞን ወረዳ ላይ ከሶስት ወራት በላይ መቆሙን በማስታወስ ይህንንም የኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዚዳንትን ጨምሮ ለሚመለከታቸው አካላት ማስታወቃቸውን አስረድተዋል።
በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የከተማ ልማት ኮንስትራክሽንና የትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ንኡስ ሰብሳቢ ወይዘሮ አገሬ ምናለ በበኩላቸው በእኒህን መሰል ምክንያቶች ፕሮጀክቶች መቆምም ሆነ መዘግየት የለባቸውም ብለዋል። ሰብሳቢዋ እንደተናገሩት እነዚህ ቦታዎች የመንግስትና የህዝብ ንብረት ናቸው። የመንገዶች ባለስልጣንም እነዚህን እየገዛ እንዲጠቀም በህግ አልተፈቀደለትም። በመሆኑም ፕሮጀክቶቹ ከመጀመራቸው በፊት በስምምነት ወቅት እንደ አንድ ቅድመ ሁኔታ ከክልሎች ጋር ስምምነት መፈራረም ይጠበቃል ሲሉ ተናግረዋል።
አዲስ ዘመን ጥር 18/2011
በራስወርቅ ሙሉጌታ