አዲስ አበባ፡- የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር የ100 ቀናት እቅዶቹን በያዘው የጊዜ ሰሌዳ በውጤታማነት እያከናወነ መሆኑን ገለጸ፡፡
የሚኒስቴሩ የህዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኢትዮጵያ በዴቻ ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፤ ከእቅዶቹ አብዛኞቹ በስኬት የተከናወኑ ሲሆን፤ ቀጣይነት ያላቸው ሥራዎች በሂደት ውጤታማነታቸው የሚታይ ይሆናል፡፡
ከእቅዶቹ መካከል በምግብ ዋስትና ፕሮግራም በ11 ከተሞች የሚገኙ 141ሺ115 ዜጎች ተጠቃሚ ለማድረግ ምልመላ የማጠናቀቅ፣ የከተማ ፕላን አዋጅ ተፈጻሚነትን በመፈተሸ በ116 ከተሞች የፕላን ጥሰት ያጋጠማቸውን የማስተካከያ ሃሳብ መስጠት፣ በ25 የኮንስትራክሽን ፕሮጀክቶች ኦዲት በማድረግ የፕሮጀክት አመራር ውጤታማነትን መገምገም፣ ለ660 ተቋራጮች፣ ለ91 አማካሪዎችና ለ303 ፈፃሚዎች ተግባር ተኮር ስልጠና የመስጠት ሥራዎች ስኬታማ ሆነው መከናወናቸውን የጽህፈት ቤት ኃላፊው ተናግረዋል፡፡
ኃላፊው የግንባታ ፈቃድ አሰጣጥ እንዲሁም የመሬት ምዝገባ ሥርዓትን ዘመናዊና ቀልጣፋ ለማድረግ ዝርዝር የማሻሻያ ስራዎችና የንብረት ግብር መተግበሪያን በሁለት ክልሎችና በተመረጡ ከተሞች ሙከራ የማድረግ ሥራዎች ሙሉ ለሙሉ የተከናወኑ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ የከተማ ፕላን ዝግጅትን በሚመለከት በክልልና ከተማ አስተዳደሮች ክልላዊ የከተማ ስፓሺያል ፕላንና የክላስተር ፕላን ዝግጅት እንዲጠናቀቅ ከክልል አመራሮች ጋር መግባባት ለመፍጠር ታቅዶ ከድሬዳዋ፣ ከአማራ፣ ከሐረሪና ከሶማሌ ክልሎች ጋር መግባባት ላይ መድረስ መቻሉን ጠቁመዋል፡፡
ኃላፊው ከተሞች የስራ ዕድል ፈጠራና የምግብ ዋስትና ለ411 ሺ ወጣቶች ቋሚ የስራ እድል መፍጠር፣ የተቀናጀ የመንግስት ድጋፍ በማድረግ 43ሺ ኢንተርፕራይዞች እንዲቋቋሙ ማስቻል፣ ህብረተሰብን በማሳተፍ 191 የተለያዩ ከተሞች ፕላን ማዘጋጀት፣ የከተሞች የመሬት አቅርቦት ሥርዓት በችግር የተሞላ በመሆኑ የከተማ መሬት ምዝገባ ሥርዓቱን በማጠናከር 52 ሺ ይዞታዎች የመብት ምዝገባ ማካሄድ፣ የከተሞች መሬት አቅርቦት ለኢንቨስትመንትና ለግል አገልግሎት የሚውል 6ሺ ሄክታር መሬት ማቅረብና የከተሞች አረንጓዴ ልማት ስራዎች ደግሞ ሳይንሳዊና የተቀናጀ የቆሻሻ ማስወገድ ሥርዓት በመዘርጋት የቆሻሻ አሰባሰብና አያያዝን 86 በመቶ ማሳደግ የመሳሰሉት አሰራሮች በከፊል የተከናወኑ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡
በእቅድ የተያዙ ስራዎች በአብዛኛው ከክልሎች ጋር የሚሰሩ በመሆኑ በታቀደው ጊዜ የሚፈለገውን ያህል ለማከናወን የመቀናጀት ችግር መከሰቱንና በቀጣይ ችግሮቹን በመፍታ የተሻለ ማከናወን እንደሚቻል ሃላፊው አስታውቀዋል፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 18/2011
በሰላማዊት ንጉሴ