ለዘመናት አልሰማም፤ ጆሮዬን አልሰጥም ብሎ ለም አፈራችንን ይዞ ሲጋልብ የነበረው አባይ፤ በዛሬው ትውልድ እንዲሰማ ተነግሮት የዛሬ ዘጠኝ አመት አቤት ማለቱ ተሰምቶ ነበር።አዎ ዛሬ በኢትዮጵያውያን ታላቅ ተጋድሎ ቀድሞ ሲነገረው እንቢኝ ብሎ የእነሱን ሰምቶ ለሚሄድላቸውም ሆነ። ለራሱ ዋነኛው ቦታ የት እንደሆነ አውቋል።እናት ምድሩ ከየት እንደሆነ በተግባር እንዲረዱት ተደርጓል።
ያኔ የዓባይ መሸምጠጥ ሊገታ መሆኑ የሰሙት ኢትዮጵያውያን ቃል ገቡ።እንደሌሎቹ የአገሩ ልጆች በእሱ ለመጠቀም ማቀዳቸው ለትግበራውም መንቀሳቀስ መጀመራቸው ሰምቶ ኢትዮጵያዊ ከዳር እስከ ዳር ነቅሎ በመውጣት ግድቡን እናደርገዋል አሉ።የሚሊዮኖች ተስፋና ጥረት፤ የእልፎች የላብ ውጤት፤ የሕዝቦች የአንድነት ማሰሮ የሆነው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በውጫዊና በብዙ ውጣ ውረዶች አልፎ ዛሬ የመጀመሪያ ብስራት ተሰምቷል።
በወንዙ ብቻችንን እንጠቀም ያሉ የታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ከግድቡ ጅማሮ አንስቶ እስከዘሬ ድረስ ለማስቆም የተቻላቸውን አድርገዋል።በውጭም በሀገር ውስጥም ያላቸውን አማራጭ ሁሉ በመጠቀም ለማስቆም ያላሰለሰ ጥረት አድርገዋል።ደግነቱ ቀድሞም ነገር ምንም ማድረግ የሚችሉት ኢትዮጵያውያን የጀመሩት ማጠናቀቅ ልማዳቸው ነውና በብዙ ፈተና ውስጥ አልፈውም ቢሆን ዛሬ የግድቡ ሶስት አራተኛው ስራ እንደ ቃላቸው እውን አድርገዋል።
ወንዙን የብቻዬ ያሉቱ፣ ከእነርሱ ጋር ልቁም ስለ ኢትዮጵያ አይገደኝ ያሉቱ፣ ጥቅሜን እንጂ እውነት የሚሉት ነገር አላውቅም ፣ፍትህ ይሉት ነገር አይገባኝ ያሉቱ በብስራት ዜናው ከከፍታቸው ወርደዋል።የማይሆን ድካማቸው ተገልጦላቸዋል።በእነርሱ ሰፊ አሻጥርና ጋሬጣ ያልተበገሩት ኢትዮጵያውያን እንደ ከዚህ ቀደሙ ሰርተው በማሳየት ወደፊት በመገስገስ ላይ ይገኛሉ።
እንደኛ እውነትን የያዙና የሚገባቸውን ለማሳካት የጣሩ ሀገራት የተጋረጠባቸውን ችግር ተሻግረው በትውልድ ቅብብሎሽ ዘመናትን ተሻግረዋል።ጉባ ላይ የተጀመረው ታላቅ ዜና ነገ ተጠናቆ ዘላለማዊ ታሪክና ድል ሆኖ ስለ ኢትዮጵያውያን አለም ያወራል።ቆራጥነትና ትጋታቸው በስፋት ይቀባበላል።ኢትዮጵያውያንም የትጋታቸው ፍሬ ተጠናቆ ያያሉ።
ዛሬ የሰከነ የፖለቲካ ስርዓት፣ ላቅ ያለ አገራዊ መግባባት ያለው ትውልድ መፍጠር አለመቻላችን የምናገኘው ድል በልበ ሙሉነት እንዳናጣጥም ምክንያት ፈጥሮብናል።ዛሬ ሀገሬን ብሎ የሚሞተው ያህል ስለ አገሩ ደንታ የሌለው
ትውልድ መፍራቱ ሲታይ ድሉ የጎደለ ያስመስለዋል።እርግጥ ኢትዮጵያን የሚወዱ ብዙዎች እዚች ሀገር ላይ ከበቀሉ ያንሳሉና ውሎ አድሮ እርካሽ አሳባቸው መዋጡ አይቀሬ ነው።
ያኔ ከኢትዮጵያ ሰማይ ስር ያጠላው ከል ተገፎ ፣ደመናው ተገልጦ ሰማዩ ይጠራል።የአገሬ ሰው አገራዊ ራዕዩን ለማሳካት ሩቅ አልሞ ለህልሙ ስምረት ሲተጋ ከፊቱ የተደቀነበት ፈተና ተሻግሮ ልክ አሁን አባይ ላይ እያስመዘገበ ያለው አይነት ታላቅ ድል ደጋግሞ መስማቱ አይቀርም።
የብዙዎች አሻራ ውጤት የሆነው ታላቁ ግድብ የሀገሪቱ ዜጎች የአንድነት ቃልኪዳን ማሰሪያ፤ የህብረታቸው ማሳያ ሀውልት ነው።ግድቡ የቀረውን ስራ ይጠናቀቅ ዘንድም ዛሬ ተቸግረንም ለግድቡ የምንወረውረው ጠጠር ነገ ድጋፋችን መሆኑ አይቀሬ ነው።ሁሉም ኢትዮጵያዊ ለሀገሩ ለውጥ በቆመ ልክ ነው ሀገሩ ተለውጣ ማየት የሚችለው።
አሳድጋ ለወግ ማዕረግ ያበቃችውን አገሩን የካደ ከውጫዊ ጠላቶችዋ ጎን ቆሞ እስዋን ለማክሰም የሚጥሩ በልቶ ካጆች ማሳፈር የምንችለው ዛሬ ለስዋ ለውጥ በምናደርገው ብርቱ ትግል ነው።ሀገራዊ ፍቅር ዘርፈ ብዙ ችግር መፍታት የሚያስችል ቁልፍ መሳሪያ ነው።ሀገር ካደገች ሀገራዊ ብልፅግና ማረጋገጥ ከተቻለ የሚቀርቡ ችሮችን በቀላሉ ማስቆም ባይቻል እንኳን የመቋቋም አቅም ይፈጥራል።
እንደ ህዳሴው ግድብ ጅምር ድል የበዙ ሀገራዊ ስኬቶች ለመቆናጠጥ ሀገር መውደድ መቅደም ይገባዋል።ሀገሩን የሚወድ ዜጋ ደግሞ ሀገሩን ለማሳደግ ያለውን ሁሉ ይሰጣል።ሀገራዊ ብልፅግና ውስጥ ሰላምን ማረጋገጥና መጠበቅ፣ የዴሞክራሲን ባህልን ማጎልበት መተግበር፣ ሀገራዊ አንድነት ማጠናከርና ማስቀጠል፣ ኢኮኖሚን በጠንካራ መሰረት ላይ ማኖር፣ ፍትህን ማረጋገጥና ሀገራዊ ክብርን መቀዳጀት የላቀ ድልም ማስመዝገብ ይቀላል።
ለዚህ ሁሉ ደግሞ የዛሬው ትውልድ መንገድ መግራት ተገቢ ነው።አዎ የሀገር ፍቅር ላይ ጥርጣሬ የሚፈጥር ወጣት በየመንደሩ በርክቷል።ይህንን ማስተካከል ይህን ትውልድ የሀገር ክብርና ታላቅነት እንዲረዳ ማድረግ ይገባል።ያኔ ሁሉም ይቀላል።
ከሁሉም በፊት ሀገሩን የሚያስቀድም ትውልድ ማፍራት ይገባል።ከዚያ ሀገራዊ ልማትና ለወጣቱ ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር መደላደል ፣ ወጣቱ አልሚ ካልሆነ ወደ ጥፋት የሚያሰማራው አካል ጋር ላለመውደቁ ማረጋገጫ የለንም።ለዚህም ነው ሀገራዊ ልማት መሰረታዊ ጉዳይ የሚሆነው።
እንደ ሀገር የምናደርገው የልማት ግስጋሴ ማሳያ ደግሞ የህዳሴ ግድብ አንዱ ነው።ሀገራት የመጨረሻ ግባቸው
አልመው መድረስ የሚፈልጉበት ዋነኛ መዳረሻ ራዕይ የስኬታቸው መለኪያና ማሳያቸው ህብረተሰባዊና ሀገራዊ ሁለንተናዊ ለውጥ ነው።
ባንወድም ማመን የሚገባን አንድ እውነት አለ።ድሆች ነን።ድህነት ደግሞ እጅን ይጠመዝዛል፤ነፃነትን ይነሳል።መቸገር የነገን ራዕይ በሰፊው ከማለም ያሰናክላል።እኛ አትዮጵያውያን በቂ የተፈጥሮ ሀብት ተችሮን፣ ምርታማና የሰጡትን የሚያበቅል ለም መሬት ይዘን፣ ማልማት የሚችል ለውጥን ማቀጣጠልና በአጭር ጊዜ ጥሩ እመርታን ማስመዝገብ የሚችል የሰው ኃይል እያለን ሀገራዊ የሆኑ ሀብቶችን ለይቶ ባግባቡ መጠቀም ተስኖን ለዘመናት ቆይተናል።
ይህ ታሪክ የሚያስለውጥ የዛሬ ዘጠኝ አመት የጀመርነው ታላቁ የህዳሴ ግድብ በብዙ ሀገራዊ ፍቅር ተደግፎ በውጫዊ ሀይላት ጥርስ ተነክሶበትና እውን መሆኑ ተጠልቶ ከ70 በመቶ በላይ የሆነውን የግድቡ ግንባታ ሂደት ላይ ተደርሷል።ታዲያ በዚህ ወቅት የገጠመን የኮሮና ወረርሽኝ ተፅዕኖና ስጋት የግድቡን ፍፃሜ ሂደት እንዳያዘገየው ማህበረሰባዊ ድጋፉ መቀጠል ያስፈልጋል ።
የአባይ ወንዝ ለመገደብ ስንነሳ ከፊት የሚገጥሙን ከባድ ችግሮች ሳይታዩን ቀርተው ሳይሆን እሱን ተከትሎ የሚመጣው ታላቅ ለውጥ ናፍቆን ነበር።ዛሬ በተገኘው ድል እንኳን ምን ያህል የሞራል ስንቅ እንደተላበስን ማየት ችለናል።ሲያልቅ ደግሞ አስቡት ከፍ ያለ ስኬትና ውጤት ከዚያ አግኝተን መልማታችን ሲሰናሰል ደግሞ ዋው።
ከዚህ ብዙ እንማራለን። ሀገራዊ እድገት በማረጋገጥ ሂደት ውስጥ ፈተና ሁሌም የሚጠበቅ ነውና ለተሻለ ስኬት ፈተናዎቹን ተቋቁሞ ማለፍ ይገባል።አዎ! ለውጥ ሁሌም አልጋ ባልጋ ሆኖ ሊመጣ አይችልም ።ይልቁንም በሩጫችን መደናቀፋችን፣ በሂደታችን መሰናከላችን አይቀሬና የተለመደ ጉዳይ ነው።በፈተናው ላለመውደቅ ደግሞ ይበልጥ ማለምና ጠንክሮ መስራት የሚጠይቅ መሆኑ አያጠያይቅም።
እንደ ሀገር ዛሬ የገጠሙን ፈተናዎች ተቋቁመንና ተሻግረን ነገ ከዛሬና በፊት ከነበረው በተሻለ ሁለተናዊ ሀገራዊ ለውጥ ለማስመዝገብ መትጋት ፣ ይበልጥ ማቀድ የተሻለ ሀገር የሚለውጡ ሀሳቦችን ማመንጨት ይኖርብናል።
ከልምዳችን ተምረናል በፈተና ውስጥ የሚመጣ ውጤት በራስ ለመቆም የሚያስችል ጠንካራ ምሰሶ ነውና በፈተናችን ውስጥ መዘንጋት የሌለብን ሀገራዊ ግብ አለ።ያ ግባችን ደግሞ ሀገራዊ ለውጥ ነው።ለዚያ ደግሞ ሀገራዊ ፍቅርን በመላበስ አብረን መትጋትና ታላቅ ሀገር ማድረግ የውዴታ ግዴታችን ሊሆን ይገባል።አበቃሁ ቸር ይግጠመን።
አዲስ ዘመን ሐምሌ 19 ቀን 2012 ዓ.ም