“እንነሳና የፈራረሰውን ቅጥራችንን እንጠግን።
እጃችንንም ለመልካም ነገር እናበርታ።” (ነህምያ)
የታሪክ አረዳድ እውነታ፤
በርካታ ጸሐፍትም ሆኑ ተናጋሪዎች መቶም ሆነ ሺህ ዓመታትን ወደ ኋላ አፈግፍገው ያልኖሩበትን ዘመን በማስታወስ ከታሪክ መጻሕፍትና ባለታሪኮች የወደዱትን ወይንም ይጠቅማል ያሉትን የታሪክ ሰበዞች በመምዘዝ ለርዕሰ ጉዳዮቻቸው ማጎልበቻነት መጠቀማቸው የተለመደ አካሄድ ነው። የትናንትን ታሪክ ከዛሬ እውነታ ጋር እያጣቀሱ፣ እያነጻጸሩና እያወዳደሩ ማወደስም ሆነ መኮነን ለሰው ልጆች ብቻ የተሰጠ ተሰጥኦና ፀጋ መሆኑም እሙን ነው።
ትክክለኛ የታሪክ ምስክር ዋቢ ማቆሙ አግባብና ተገቢ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ችግርና ክፋት የሚሆነው አንዳንዴ ከታሪክ ገበታ ላይ ቆርሰን የምንጎርሰውና ሌሎችንም ሰዎች ለማጉረስ የሚዳዳን የሻገተ ማጣቀሻ መሆኑ ነው። ሲከፋም የምንቆነጥረው የታሪክ ጉርሻ እንደ ዘንጋዳ እንጀራ እውነቱ ፍርክስክስ ማለቱን እያስተዋልንም እንኳን ቢሆን ህሊናችንን ከማድመጥ ይልቅ አገንግነንና ልባችንን አደንድነን ለማጉረስ ስንታገል አጉራሹም ሆነ ጎራሹ በስሜት ተልከስክሰው መወናበዳቸው አይቀሬ መሆኑን ያለመረዳታችን ሌላው ግዙፍ ስህተት ነው። በዚያም ሆነ በዚህ ከሰፊውና ዘመናት ካስቆጠረው የታሪክ ማዕድ የምንቆርሰውን ጉርሻ ሚዛን በሳተ መልኩ በራሳችን ያልተገራ የስሜት ወላፈን እያሞቅንና እያጋልን እኛ በጎረስነው ልክ ሌሎችንም እየፈጃቸው እንዲያላምጡ “በሞቴ እያልን” በመታገል ለጉርሻ ማስገደዳችን ከክፋትም ላቅ ያለ የከፋ አመጽ ነው።
የታሪክ አረዳድ መልኩ ዝንጉርጉር ብቻ ሳይሆን ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚፈልግ ጉዳይ ስለመሆኑ ቀደምት የዘርፉ ጠቢባን ያሳወቁን ገና ከማለዳው ነበር። በግሪካዊያንና በፐርሽያዊያን መካከል የተካሄደውን ጦርነት ለመጀመሪያ ጊዜ በአስገራሚ ሁኔታ መዝግቦ ሙሉ ታሪኩን ያቆየውና “የታሪክ አባት” በመባል የሚወደሰው ግሪካዊው ሄሮዶቱስ (485-425 ዓ.ዓ) እና ታሪክን በሦስት ምድቦች በመከፋፈልና ትንታኔ በመስጠት የተደነቀው ኤቲይስቱ ጀርመናዊው ኒቼ (1844-1900) በታሪክ በጎነትም ሆነ ድክመት ላይ ለሰው ልጆች ሁሉ ምክራቸውን የለገሱት የአንዱን ገጽታ ጫፍ ብቻ አክርረን በመጎተት ራሳችንን ተብትበን የታሪክ እስረኛና የቀዳሚ በደል ተራኪ “ካዝናዎች” ሆነን እንዳንቀር አደራ በማለት ጭምር ነው። በዚሁ ጋዜጣ ላይ ደጋግሜ የጠቀስኩት፤ “ከታሪክ መሰዊያ ላይ አመዱን ሳይሆን ፍሙን እንጫር” የሚለው ተወዳጅ አባባልም ደጋግሞ ቢታወስ ለግንዛቤያችን ጥሩ ማጠናከሪያ ይሆናል።
ፍርስራሽ ቅጥር አዳሹ ነህምያ፤
ግሪካዊው ሄሮዶቱስ በኖረበት በቅድመ ልደተ ክርስቶስ ተቀራራቢ ዘመን በአምስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን አጋማሽ የኖረውና ሙሉ ታሪኩ በቅዱስ መጽሐፍ ውስጥ የሰፈረው ነህምያ በእምነቱ አስተማሪዎች ብቻም ሳይሆን በመላው ዓለም በሚገኙ ምሁራን ዘንድ ሳይቀር አዘውትሮ ይታወሳል። ነህምያ በፐርሽያዊያን ተማርከው ወደ ባቢሎን ከተጋዙት አይሁዳዊያን ምርኮኞች መካከል አንዱ ነበር። በዓለማችን ላይ ገናና ስም የተጎናጸፉ በርካታ የሥነ አመራር (Leadership) አስተማሪዎችና ጸሐፊዎች ስለ ውጤታማ የአመራር ጥበብ ሲተነትኑና ሲያስተምሩ የነህምያን ታሪክ ሳይጠቅሱ አያልፉም። ይህ ጸሐፊም “የአመራር ጥበብ” በሚል ርዕስ ባሳተመው መጽሐፉ ውስጥ ስለዚህ ታላቅ ስትራቴጅስት ከአንድ ምዕራፍ ያላነሰ ትንተና ሰጥቷል።
ነህምያ በንጉሥ አርጤክስስ የአገዛዝ ዘመን (465-
424 ዓ.ዓ) ከወገኖቹ ጋር በምርኮኝነት የተጋዘ ቢሆንም በማራኪው ንጉሥ ፊት ሞገስ በማግኘቱ በቤተመንግስቱ ውስጥ ትልቅ ኃላፊነት ለመቀበል የበቃ ታላቅ ሰው ነበር። ይህ ሰው በተሻለ የኑሮ አቋም ላይ በነበረበት በዚያ ወቅት የትውልድ ሀገሩን የኢየሩሳሌምን ቅጥር መቃጠልና መፍረስ እንደሰማ፤ “ተቀምጬ አለቀስሁ፣ አያሌ ቀንም አዝን ነበር በሰማይ አምላክም ፊት እጾምና እጸልይ ነበር።” በማለት የልቡን ስብራት በግልጽነት ይነግረናል።
የሀገሩ ውድመትና ጥፋት ከለቅሶ፣ ከሀዘንና ከትካዜ በላይ የሆነበት ነህምያ ማራኪውን ንጉሥ በማስፈቀድ ወደ ሀገሩ ካቀና በኋላ ከምርኮ የተረፈውን ሕዝብ ከትንሽ እስከ ትልቅ በመሰብሰብ የፈራረሰውን ቅጥር ለማደስ መወሰኑን እንዲህ በማለት ይገልጽላቸዋል፤ “ያለንበትን ጉስቁልና ኢየሩሳሌምም እንደፈረሰች፣ በሮቿም በእሳት እንደተቃጠሉ ታያላችሁ፤ አሁንም ከእንግዲህ ወዲህ መሳለቂያ እንዳንሆን ተሰባስበን የፈረሰውን ቅጥር እንስራ።”
የአካባቢው ተቀናቃኝ ጠላቶቹ (ሰንበላጥ፣ ጦቢያና ጌሳም) “እነዚህ ደካሞች የሚሠሩት ምንድን ነው? እንዴትስ ዝም ይባላሉ? የተቃጠለውንስ ድንጋይ ከፍርስራሹ መልሰው ያድኑታልን? በድንጋይ በሚሰሩት ቅጥራቸው ላይ ቀበሮ ቢዘልበት ያፈርሰዋል?” እያሉ ቢሳለቁባቸውም እሱና ሕዝቡ ግን በዘባቾቹ ዛቻና ማስፈራሪያ ተበግረው ሸብረክ ሳይሉ፤ “የሰማይ አምላክ ያከናውንልናል፤ እኛም ባሪያዎቹ ተነስተን እንሰራለን” በማለት ቁርጠኝነታቸውን ለጠላቶቻቸው በይፋ አስታወቁ።
ተቀናቃኞቻቸው ግን ከፉከራም አልፈው ሊያጠፏቸው እንደሚችሉ ሁሉ ሲደነፉባቸው፣ አንዳንዴም ተመካክረን ብንረዳዳ እኮ ሥራው ለእናንተም ይቀላል በሚል ሽንገላ ሊያሞኟቸው ቢሞክሩም በፍጹም እንዳልተበገሩላቸው ታሪኩ ያስረዳናል። እንዲያውም ከፊሉ ሕዝብ ቀስቱን ገትሮ ቃፊር በመቆም፤ ከፊሉ ደግሞ በቅጥሩ የእድሳት ሥራ ላይ በመረባረብ ተልእኳቸውን በሃምሳ ሁለት ቀናት የሌት ተቀን ትጋት በስኬት አጠናቀው ፍርስራሹን በማደስ ድላቸውን አበሰሩ።
ለሀገራዊ ፍርስራሾቻችን ምን ትምህርት መውሰድ ይቻላል?
የነህምያ ታሪክ ለሀገራችን ወቅታዊ ዐውድ ጥሩ ማሳያ ይምስለኛል። ቅጥር በእንጨት፣ በጡብ፣ በድንጋይ ወይንም በብረት የሚታጠር ግቢን ወይንም አካባቢን ብቻ የሚወክል አይደለም። ቅጥር ትርጉሙ ሰፊ እሳቤውም እጅግ ረቂቅ ነው። ማንኛውም ሰው “የእኔና ለእኔ” ብቻ ብሎ ራሱን የሚከልልበት አይደፈሬ ቅጥር ሊኖረው ይችላል። መብቱ ነው። ቡድኖችም ሆኑ ማሕበረሰቦች የራሳቸው ቅጥር ሊኖራቸው መቻሉም እርግጥ ነው። በእያንዳንዱ ሀገርም እንዲሁ ዜጎችና መንግሥቱ የሚመራባቸው የኢኮኖሚ፣ የሶሻልና የፖለቲካ ሉዓላዊ ቅጥሮች እንደሚኖሩት የታወቀ ነው ።
የዘረዘርናቸው የቅጥር ዓይነቶች ቅርጻቸው፣ አገነባባቸውና ዙሪያ ጥምጥማቸው እጅግ የተወሳሰበና የተመሳጠረ ቢሆንም አንዱ ያለ አንዱ ድጋፍና መረዳዳት ሊኖር እንደማይችል በግልጽ የታወቀ ስለሆነ “በራሴ ሼል ውስጥ ብቻ ራሴን ሸሽጌ ለመኖር ብቃትም ብርታትም አለኝ” ተብሎ የሚፎከርበት ጉዳይ አይደለም።
አንድን ማሕበረሰብ የሐረሪ ጠቢባን እናቶች በሚሰፉት ሙዳይና መሠል የስፌት ሥራዎች ልንመስለው እንችላለን። ሙዳዩ ሙዳይ ለመባል የሚበቃው በሰበዙ መብዛትና ማነስ እየተመዘነ አይደለም። ሰበዙን አጠንክረው የሚያያይዙትና ውበት የሚጨምሩለት በተለያዩ ኅብረ ቀለማት የተነከሩት አለላዎች ናቸው። አለላዎቹ የማይኖሩ ከሆነ ስፌቱ ከተራ ሰበዝና ከአክርማ ውህደት ስለማያልፍ ልሙጥነቱ ዓይንን አይማርክም፣ ለውበትም አይፈለግም።
የጋሞ ጠቢባን ስለሚሸምኗቸው ውብ የሀገር አልባሳትም ብዙ ማለት ይቻላል። ያደግሁት ከጋሞ ተወላጅ የእድሜ እኩዮቼ ጋር ስለሆነ አባቶቻቸው ወይንም ታላላቆቻቸው የሚሸምኗቸውን የጥበብ ሸማዎች በቅርብ ለመከታተል እድል ነበረኝ። ድሩን ሲያደሩ፣ ማጉን ሲያዳውሩና በተመስጦ ውስጥ ሆነው የጥበብ ዲዛይኖቹን እየቀመሩ ሲራቀቁና ሲጠበቡ ያኔ እንደዋዛ፤ ዛሬ ግን በአድናቆት አስታውሳቸዋለሁ።
ግለሰቦች፣ ቡድኖችም ሆኑ ማኅበረሰቦች የራሳቸው የግል ቅጥር አላቸው ቢባልም የተሸመኑበት ውብ ማሕበረሰባዊና የረጂም ዘመናት የታሪክ ተጋምዶ፣ ውህደትና መደበላለቅ ግን ልክ እንደ ሐረሪ ጠቢባን ሴቶች ሙዳዮች ወይንም እንደ ጋሞ የረቀቁ የሀገረሰብ ጥበቦች ሊታይ የሚገባው ነው። በቀይ፣ በቢጫ አለያም በሐምራዊ አንድ የቀለም ጥለት ብቻ የሚሸመኑ አልባሳት ልሙጥ እንጂ ጥበብ ሊሰኙ አይችሉም። ጥበብን ጥበብ የሚያሰኘው የቀለማቱ ውህደት፣ ስምረትና ውበት ነ ው።
ዛሬ ዛሬ በግላጭ እያስተዋልናቸው ያሉት የበርካታ ሀገራዊ አሳሮቻችን መንስዔያቸው ቢመረመርና በአግባቡ ቢጠና፤ ልንደርስበት የምንችለው ውጤት የብዙ ጉዳዮቻችን ቅጥሮች በጅል አስተሳሰቦችና ተግባሮች ሊፈራርሱ የቻሉበት ዋነኛ ምክንያት ራስ ወዳድ ፖለቲከኞችና ሆድ አደር ህልመኞች በወለዷቸው መዘዞች ምክንያት ደማቁ ኅብረታችን እንዲናድ በመደረጉ ይመስለኛል።
በማንነታቸው ወይንም በራሳቸው አምሳል በጠፈጠፏቸው ቡድኖች ቅጥር ውስጥ ተሸሽጎ ዘርን፣ ቋንቋንና ብሔርን መመከቻ ጋሻ በማድረግ የሌላውን ቅጥር ለማፍረስና ለመናድ መሞከር ዞሮ ዞሮ በኅብር በተሸመነው የማንነት ቀለበት ውስጥ የራስ ቅጥርም የክበቡ አካል ስለሆነ ጉዳቱ እኩል በእኩል ወይንም የጋራ መሆኑ አይቀሬ ነው። ክፋት ብቻ ሳይሆን የጅል ድፍረትንም ጭምር ያስተማረን የሀገራችን ፖለቲካ ለስንቱ ቅጥሮቻችን መናድ ምክንያት እንደሆነ እኛ የገፈቱን ጉሽ በመጎንጨት እየተሳከርን ያለነው የዛሬ ትውልዶች በሚገባ ተረድተነዋል። የዛሬ ክፋታችንን ለነገው ትውልድ በታሪክ ውርስነት በጥቁር የቱቢት እራፊ ለብጠን ለማስተላለፍ መሞከራችንም ሌላው የአሳራችን “ትሩፋት” ውጤት ነው።
በዘመናት ውስጥ ተከባብሮና ተጋምዶ፣ ተዋልዶና ተዛምዶ በጥበብ የተሸመነው ሀገራዊው የኅብረ ብሔሮቻችን የጋራ ቅጥር እንዲሰነጣጠቅ ሲሰራ የኖረው ዱር ውስጥ በተቀናበረ የረቀቀ የበረኸኞች ሴራ እና ዕድሜያቸውን በሙሉ ሥልጣን ቢያነፈንፉም አልሳካላቸው ባሉ ምርኮኛ ስደተኞች አማካይነት ስለመሆኑ ደጋግሞ ተገልጧል። “ስመ ዴሞክራሲን” እንደ ጭንብል ተከናንበው የኅብረ ብሔር ውበት ቅጥራችንን ማፍረሻ ድማሚት ሲቀምሙ የኖሩት እነዚህን መሰል “የእንግዴ ልጆች” ቀደም ሲል በሴራ ፖለቲካ፤ ዛሬ ዛሬ ደግሞ እንደ ኢያሪኮ ጯኺዎችን በማሰለፍ በግላጭና በአደባባይ እኩይ እቅዳቸውን በማቀጣጠል እያደረሱ ያሉት የውድመት ጥፋት ይህ ቀረሽ የሚባል አይደለም። በቅድሚያ የጥፋት ዒላማቸውን ያነጣጠሩት በሚያማክሉን በርካታ የጋራ ሀገራዊ ታሪኮቻችን ላይ ጥቃት በመሰንዘር ስለነበር እንደተመኙትም ጥቁር ቀለም በመድፋት እያሳከሩ ሀገሪቱ በረጂም ዘመናት ታሪኳ እንድታፍር አንገቷን ለማስደፋት ሙከራ ማድረጉን ተያይዘውታል። አንዱ ብሔር ጨቋኝ ሌላኛው ብሔር ተጨቋኝ በማለትም እየፈረጁ የማፈራረሱን ጦርነት ማጋጋል ከጀመሩ ሰነባብተዋል። የሥልጣን ጥማት እንደሚያንቀዠቅዥና እንደሚያሳብድ
እንኳን ለእኛ ለባለጉዳዮቹ ዜጎች ቀርቶ ለሌሎች ሀገራትና ሕዝቦች ጭምር መሳቂያና ማላገጫ እያደረጉን እንደሆነ ጥዝጣዜው በሚገባ እየተሰማን ነው።
“በብሔርህ ቅጥር ውስጥ ተሸሽገህ የሌሎች ብሔረሰብ ተወላጆችን ቅጥሮችና የጋራ እሴት አውድም። በመዋለድ የተቀላቀለውን ደምህን ከቁብ ሳትቆጥር በወንድምነት አብረኸው በኖርከው ዘር ላይ በመዝመት ብርታትህን አሳይ። የንብረቱን ቅጥር ዘለህ በመግባትና ሆ! እያልክ በማቅራራት አውድምና አቃጥል። አንተም ራስህ የምትገለገልባቸውን መንግሥታዊ መ/ቤቶች፣ የሃይማኖት “ደጀ ሰላሞች”፣ የትምህርት፣ የጤና፣ የንግድና መሰል ተቋማት በመንጋ ዘምተህ አውድምና አቃጥል። ግፉን በማጠናከር ንፁሃን ዜጎችን የማፈናቀሉን ሥራ ተግተህ ተግብር።” የሚሉ ዓይነት እኩይ ትዕዛዛትንና የእልቂት አዋጆችን ከሚያስተላልፉ ሊቀ ሰይጣናት አለቆቻቸው ይልቅ ፈጻሚዎቹ ጂኒዎች በእጅጉ ሊያፍሩና ሊጸጸቱ በተገባ ነበር። ጤነኛ አእምሮ ያለው ሰው እሳት ውስጥ ተማግደህ ሌሎችንም ማግድ ተብሎ ትዕዛዝ ሲሰጠው እንደምን ቆም ብሎ ለማመዛዘን ህሊና እንደሚያጣ ለመገመት ይከብዳል። የግፍ ተልዕኮውን ከፈጸመስ በኋላ በገደለውና ባወደመው፣ በዘረፈውና ባቃጠለው በድንና ንብረት ላይ ቆሞ ወራሪን እንደማረከ “ጀግና” በግፍ ጀብዱው ሲኩራራ ማየት አይሰቀጥጥም? እያስተዋልን ያለነው ለሰሚው ግራ፣ ለተመልካችም እንቆቅልሽ የሆነውን ይህንን ሰሞንኛ ክስተት ነው። ሴራውና የአመፁ ቅንብር ቢጻፍም ሆነ ቢነገር ተተርኮ የሚያበቃ ስለማይሆን ሁሉንም ጊዜ እስኪገልጠው ድረስ በስክነትና በማስተዋል መሰንበቱ የተሻለ ይሆናል።
በባዕድ ምድር የሚኖሩ ብዙኃን ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ከላይ በምሳሌነት እንደጠቀስነው እንደ ነህምያ የሀገራቸውን ፈርስራሽ ቅጥሮች ተባብሮ ለመጠገን በዘርፈ ብዙ እንቅስቃሴ ሲረባረቡ እያስተዋልን ብንደሰትም በአንጻሩ ደግሞ “ያዳቆናቸው ሰይጣን ያቀሰሳቸው” አንዳንድ የሀገር ሰላምና የትውልድ ፀሮች በምርኮኝነት በተጋዙበት ሀገር ተደላድለው እየኖሩ የማፍረሱን ዘመቻ ግን በጀሌዎቻቸው አማካይነት በሀገር ውስጥ ሲያጧጡፉ መመልከት የልባቸው ክፋት ምን ያህል እንዳሳበዳቸው ጥሩ ማሳያ ይሆናል። የመሸነፋቸውና የሥልጣን ቀረብን ብሶትና ቁጭት ያንገበገባቸው አንዳንድ ግለሰቦችና ቡድኖችም በታቀፉበት የእናታቸው መልካም ጉያና በብሔር ምሽጋቸው ውስጥ በማድፈጥ ከውጭ ጠላት ጋር በአንድ ዋንጫ እየተጎነጩ የሀገርን ሉአላዊነት ለማፍረስ ሲሞክሩ ማስተዋል ምን ያህል ህሊናቸው ጨርቁን ጥሎ እንዳበደ በጥሩ ማሳያነት ይጠቀሳል።
ወቅታዊው የሀገራችን ፈተና ከታሪክ እስከ ፖለቲካ፣ ከሰብዓዊ ጉዳት እስከ ቁስና ሀብት ውድመት ፍርስራሹ በርካታ ቢመስልም ልዩነታችንን ለጊዜው አስወግደንና ተደማምጠን የሚጠገነውን ለመጠገን፣ የሚገነባውን ለመገንባት፣ የወደመውን ለመተካት፣ ያዘኑ ወገኖችን እንባ ለማበስና የሀዘንተኞችን ሀዘን ለመጋራት ካሁን በፊት ስናደርግ እንደኖርነው ሆ! ብለን በጋራ ብንዘምት ብርታታችንና አቅማችን ከችግራችን በላይ በእጅጉ የበረታ ስለሆነ በአጭር ጊዜ ውስጥ ውጤት ማስመዝገብ እንደምንችል ማሳያችን የነህምያ ምሳሌነትና የህዳሴ ግድባችን የደመቀ ጅምር ድል ነው። ሰላም ይሁን!!
አዲስ ዘመን ሐምሌ 18/2012
ጌታቸው በለጠ – ዳግላስ ጴጥሮስ)