ሆነም። ጋላቢው ሰከነ። ረጋ። ስደት በቃኝ አለ። እናት ምድሩን ተዋወቀ። እናት ዘጠኝ ወራት እንደምታምጥ ኢትዮጵያ ዘጠኝ ዓመታት አማጣች። በሕዝቦቿ ብርቱ ትግልም ዓባይን ተገላገለች። በእቅፏ አስገብታው ዓይኗን በዓይኑ ላይ ተከለች። ልጇን ለማሳደግም ሽር ጉዷን ቀጠለች። ምጡን ረስታ ልጇን አንስታለችና ደስታዋ ልዩ ሆነ ! ከዚህ በኋላ ልጇ በሞገስ ያድጋል። በየዓመቱ በአካል ይገዝፋል። መጠኑ ይበዛል፤ ሽፋኑ ይሰፋል። ከዚያም ለአቅመ ኃይል ማመንጨት ይደርሳል። በዚህ ጊዜ ልጅ ወላጅ እናቱን ያስባል። የዘጠኝ ዓመታት ምጧን፣ እርሱን የማሳደግ ልፋቷን ዋጋ ይከፍላል። ጨለማዋን ይገፍላታል። በብርሃን ይሞላታል። ፓውንድ ፣ ዩሮና ዶላር ይሆናታል። ለጎረቤቶቿ ተርፎ በፍቅር ያስተሳስራታል። ኢንቨስትመንትን ጠርቶ፣ ድህነትን ይሸኝላታል። ተሰሚነቷን ጨምሮ ክብርን ይሸልማታል። ዓባይ !
ሐምሌ 15 ቀን ረፋዱ ላይ የተኩላዎችን የተንኮል ወጥመድ የሰበረ ሰበር ዜና ተሰማ። ኢትዮጵያ ፈካች፤ ኢትዮጵያውያን ፈነደቁ። ደስታ ሆነ፣ ትልቅ በዓል። ፌሽታ ሆነ፣ የእንኳን ደስ አለን መልዕክቶች ጎረፉ። ባንክ ቤቶች ቢዚ ሆኑ፤ የቦንድ ግዢው ተጧጧፈ። ወረርሽኙ ባይኖር አደባባዮች በድንገቴ ሰለፎች ይወረሩ ነበር። ደንቅ ታሪክ ተሠራ !
የምሥራቹ ሲሰማ ቤቴ ውስጥ ነበርኩ። ጮሁኩ። ዘለልኩ። ተንበርክኬ ፈጣሪን አመሰገንኩ። ዜናውን ደጋግሜ ለመስማት ቋመጥኩ። ሪሞቱን ሙጢኝ ብዬ ቲቪዬን ቻናል እያፈራረቅኩ አስጨነቅኩት። ለመጀመሪያ ጊዜ የቴሌቪዥን ጣቢያዎቻችን ቁጥር አነሰብኝ። ተቁነጠነጥኩ። ለካስ ደስታ የሚያደርጉትን ነገር ያሳጣል። ኢትዮጵያውያን ይህችን ዕለት ሲናፍቁ ዓመታት ተቆጥረዋል። ይህንን ናፍቆት በልኩ የሚገልጽ ነገር ይኖር ይሆን ስል አሰላሰልኩ። የታምራት ደስታ ዘፈን ትዝ አለኝ። አዎ ! ኢትዮጵያወያን ዓባይን የተቆጣጠርን ዕለት “እኛን ነው ማየት” እያሉ የመናፈቃቸውን ጥግ፣ የአገር ፍቅር ስሜታቸውን ንዳድ ሲገልፁ ኖረዋል። እንዲህ እያሉ ፡-
እኛን ነው ማየት፣ ዓባይ ሲሞላ እሱ ብሎት፤
ለጉድ ተናንቀን፣ በእንባ አንገት ለአንገት፤
ችሎ አያስጥለን፣ ወዳጅ ጠላት ቢኖር፤
አንተን ነውና፣ የተራበው አገር።
አቤት መቼም ይታየኛል፣ ሳታልቅ ካሁኑ ታውቆኛል፣
አንተን በአካል አግኝቼ፣ በናፍቆት ማንባቴን ረስቼ፤
በአሳብ ይታየኝና፣ ቦንዱን እገዛለሁ እገዛለሁ፤
ያቺን ቀን እስከማያት ናፍቃለሁ ናፍቃለሁ።
ደስታ የሚያደርጉትን ነገር ያሳጣ የለ ! የማህፀኗን ፍሬ ለማቀፍ የበቃቸው ኢትዮጵያስ ምን ብላ ትዘፍን ይሆን ብዬ አስብኩ። እርግጠኛ ነኝ የሚኪያ በሃይሉን ዘፈን ነው የምትመርጠው። እናም እንዲ ትቀኛለች ፡-
ሆነልኝ ሞላልኝ፤
ተሳካ ልቤ ረካ።
መጨረሻውን አይቶ፣ ዕቅዱን አሳክቶ፤
እፎይ አለ ልቤ፣ በሥራው ረክቶ፤
ወፌ ቆመች ብለው፣ ያቆሙኝ በእግሬ፤
ይሁኑልኝ ጎኑ፣ በድሌ ቀን ዛሬ።
ይሄን ሁሉ ዘመን፣ ስደክም ስለፋ፤
ስላልቀናኝ ቶሎ፣ አልቆረጥኩም ተስፋ፤
እንቅፋቱ በዝቶ፣ ስወድቅ ስነሳ፤
ይኸው እዚህ ደረስኩ፣ ፈተናው ተረሳ።
ተስፋ ጉልበቴን፣ ኃይሌ አድርጌ መሰረቴ ብርታቴ
ይኸው ህልሜ፣ ጊዜ ፈቶት ደረሰልኝ ሞላልኝ።
ሆነልኝ ሞላልኝ፤
ተሳካ ልቤ ረካ።
ደስታ የሚያደርጉት ያሳጣ የለ! ዓባይ ወንዛችን ራሱ ምን ብሎ ይዘፍን ይሆን ብዬ አሰብኩላችሁ። እናም ናቲ ማን “የጀመሪያዬ ነው” ሲል የተጫወተው ሙዚቃ መጣልኝ።
አዎ ! የልቡ የደረሰው ዓባይ ስሜትህን በሙዚቃ ግለጽ ከተባል እንዲህ የሚል ይመስለኛል ፡-
የመጀመሪያዬ ነው ሀገሬ ስቀር አምርሬ
የመጀመሪያዬ ነው ሀገሬ ስቀር አምርሬ
ሽር ልበል በኢትዮጵያ ላይ
ይፋ ይውጣልኝ መቅረቴም ይታይ
ደስታ የሚያደርጉትን ያሳጣ ያለ ! አዝማሪዎችስ ምን እያሉ ይሆን ስል አሰብኩ። ያለጥርጥር ሲናፈስ በነበረው የፈጠራ
ወሬ ሲረበሹ የቆዩት አዝማሪዎች አሁን እውነታውን አውቀው ግጥም ቀይረዋል። እንዲህ የሚሉ ይመስለኛል፡-
በላኸው አንጀቴን በላኸው ፣
በላኸው አንጀቴን በላኸው ፤
ሱዳን አፋፉ ላይ ጉባ የተኛኸው።
ተገድቧል ሲባል፣ ዝርፊያውን ነው ብዬ፤
ሻጭ ሆኗል ሲሉኝ ፣ ሜቴክን ነው ብዬ፤
ለካስ አንተን ኖሯል፣ ትልቁን ሰውዬ፤
ግድቤ ዓባይዬ፣ መሪዬ አብይዬ፤
እየው ገሃድ ወጣ፣ ከሃዲው ተለየ።
በላኸው አንጀቴን በላኸው፣
በላኸው አንጀቴን በላኸው፣
ሱዳን አፋፉ ላይ ጉባ የተኛኸው ።
ኤጭ ! አንዳች ድምጽ ካለውበት የደስታ ባህር ጨልፎ አወጣኝ። በር ተንኳኳ። ጎረቤቴ ነች። “ውሃ መጥታለች ቅዳ” አለችኝ። ትዝ ሲለኝ ባልዲው፣ ጀሪካኑና በርሜሉ ባዶ ነው። የዓባይ ግድብ ሞላ ሲባል ጓዳዬም የሞላ መስሎኝ ነበር። ለካስ ቀሪ ሥራ አለ ! እውነት ነው በየጓዳችን የምንከውነው ብዙ ቀሪ ሥራ አለ። በእውቀቱ ስዩም በአንድ የወግ ጽሑፉ “ፈጠን ብለን ወንዞቻችንንና ስሜቶቻችንን መገደብ አለብን ” ብሎ ነበር። አሁን አብይ ወንዛችንን ዓባይን ገድበን ወደ ማገባደዱ ነን። አንድ ነገር ግን ይቀረናል። ስሜቶቻችንን መገደብ መቻል አለብን። ጽንፈኞች እኩይ አላማቸውን ለማሳካት መሰዊያቸው ላይ እንዳይሰቅሉን ቆም ብለን ማሰብ አለብን።
ባለቅኔው ሎሬት ፀጋዬ ገብረ መድህን የዚህችን አገር የማይፈታ ቋጠሮ ገና በጊዜ ተረድተው ነበር። በ1984 ዓ.ም ለቤዛ መፅሔት በሰጡት ቃለ ምልልስ ግጥሞቻቸው ትራጄዲያዊ የሆኑበትን ምክንያት ሲገልፁ እንዲህ አሉ፡- “የኢትዮጵያ ህዝብ መከራ ተሸካሚ ነው። በተደጋጋሚ የጦርነት ድግስ ይደገስለታል። የድግሱ አዳራሽ ውስጥ ሆ ብሎ ይቃጠላል። ለዚህ በእኔ አስተያየት የተለያዩ ምክንያቶች አሉት። ልቡ ውስጥ የምታበራዋን ነፃነት የሚላትን ዕሳት ለራሱ ለማስቀረት ጦርነት ውስጥ ገብቶ ይቃጠላል። አንገቱን ቀና አድርጋ የምታንቀሳቅሰው ይህች ነፃነት ወዳድነቱ ነች። ይህችን በውስጡ የምትነድ ባህሪውን ገዢዎቹ ለራሳቸው ጥቅም ያውሏታል። ሁለት
ባላባቶች ማዶ ለማዶ ያዋጉታል። ከውጭም ጠላት ሲመጣበት ያው ነው። ነፃነቱን እጅግ ይወዳል። በዚህም ከሌላው ይለያል። መከራውን ችሎ አንጀቱን ቋጥሮ ባዶ እግሩን ያለስንቅ ያለ ደሞዝ ለነፃነቱ ይሞታል። በወንድሞቹ በአፍሪካውያን ዘንድ ያስከበረው ይሄው ባህርይው ነው። ዛሬም ቢሆን ያው ባህርይው እየገፋፋው ይታለላል። እፎይ ብሎ አያውቅም። የሚያጫርሰው አመራር ሁልጊዜም ይከሰትበታል። በውስጥ ለራሳቸው ጥቅም እርስ በእርሱ ያፋጩታል። በውጭም ለነፃነቱ ቀናኢ ስለሆነ እሱን ለሞት አጋፍጠው እንደገና አናቱ ላይ ፊጥ ይላሉ። በዚህም አጥንቱን ይሰብሩታል። እኔ ደግሞ አንድ ገበሬ አጠገብ ቁጭ ብዬ እህ ማለትን እወዳለሁ። ካንድ ዓርበኛ ወታደር ካንዲት የወታደር ሚስት ከአንድ ቄስ ከአንድ ሼህ … ከሁሉም እህ ብዬ እማራለሁ። ሁሉም አንደበታቸው እምባ አዘል ነው። እሮሮ ያፈልቃል ልሳናቸው። ህይወታቸው ሁሉ ብሶት ነው። ይሄ ነው ባጠቃላይ የአገሪቱ ገጽታ። ብእሬን ወደ ትራጀዲ የሚስበውም ይሄው ነው።”
ባለቅኔው ከ28 ዓመታት በፊት የገለፀው የኢትዮጵያ ችግር ዛሬም ህልው ነው። መታለል የለብንም። እርስ በእርስ ለሚያናክሱንና ለሚያጫርሱን ፅንፈኛ ፖለቲከኞች መጫወቻ ካርታ አንሁን። ወደ ሚደገስልን ጦርነት ዘው ብለን አንግባ። ወንድም ወንድሙን ለሚገድልበት ሰጣናዊ ተልዕኮ የሚሰጡትን “ትግል” የሚል የዳቦ ስም አንቀበል። የሥልጣን መወጣጫ እርካብ ለመሆን አንሰዋ። የህዳሴው ግድብ ግንባታ ቆሟል፤ ግድቡ ተሸጧልና ውሃ ለመያዝ ዝግጁ አይደልም ሲባል የነበረው ሁሉ ሀሰት መሆኑ ተረጋግጧል። ዛሬ ሙሌቱ ሀቅ፣ ዓባይም ሃይቅ ሆኗል። ከዚህ በኋላም ለሚነዙ አፍራሽ የፈጠራ ወሬዎች ጆሮ አንስጥ።
ለታላቁ ህዳሴ ግድባችን የምናደርገውን ድጋፍ የምናጠናክርበት ትክክለኛው ጊዜ አሁን ነው። “ብረትን መቀጥቀጥ እንደጋለ ነው” እንዲሉ ደስታችንን ሳንለምደው በፊት የምንችለውን ሁሉ እናድርግ። የታችኞቹን ተፋሰስ አገራት በተመለከተ የምንሰጠው አስተያየትም የጋራ ተጠቃሚነትን መሰረት ያደረገና ኢትዮጵያዊ ጨዋነትን የተላበሰ ይሁን። ጥንቃቄ እናድርግ ለማለት ያህል ነው፤ ደስታ የሚያደርጉትን ነገር ያሳጣ የለ!
አዲስ ዘመን ሐምሌ 18/2012
የትናየት ፈሩ