የጥራት መንደር እና ትሩፋቶቹ

ባለፉት አምስት አመታት ኢትዮጵያ በርካታ እድገቶችን አስመዝግባለች። የግብርና ኋላ ቀርነትን ቀርፎ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማስከበር በተሠራው ሥራ የባሕልም የውጤትም ለውጥ መጥቷል። ከዚህ በፊት የዝናብ ወቅት ብቻ ይጠብቅ የነበረው የግብርና ባህል መስኖን በመጠቀም፣ በኩታ ገጠም እርሻና መሬት ጦም እንዳያድር በተሠራው ሥራ፣ ዓመቱን ሙሉ የሚመረትበት ባህል እያመጣ ነው። ስንዴን፣ ሩዝን፣ ገብስን፣ በቆሎንና የፍራፍሬ ምርቶችን ትኩረት አድርጎ በተሠራው ሥራ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀዳሚዋ የስንዴ አምራች ሀገር ሆናለች።

ግብርና ባለፉት ዓመታት ከፍተኛ ውጤት የታየበት ዘርፍ ነው። ቀደም ሲል ክረምት እና ዝናብ ተጠብቆ ሲሠራበት የነበረው የግብርና እንቅስቃሴ አሁን ወቅት የማይገድበው ሆኗል። በዚህም ምክንያት ሰብል፣ ጥጥ፣ ሆርቲካልቸር ተደምሮ ክረምት ከበጋ ሰላሳ ሚሊዮን ሄክታር መሬት በማረስ 1.4 ቢሊዮን ኩንታል ምርት እንደሚሰበሰብ ይጠበቃል።

በኢንዱስትሪ እና በማዕድን ዘርፎችም በርካታ ውጤቶች ተመዝግበዋል። ወደ ውጭ የሚላኩ የኢንዱስትሪ ምርቶችን ለማበራከት የሚያስችሉ መሠረቶች ከመጣላቸውም ባሻገር ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ ተኪ ምርቶችን በሀገር ውስ ጥ ማምረት ተችሏል።

ማእድን በሚመለከት በወርቅ፣ ብረታብረት፣ የድንጋይ ከሰል አዳዲስ ፋብሪካዎች ሥራ ይጀምራሉ። በርካታ የወርቅ ፋብሪካዎችም ወደ ሥራ ይገባሉ። ወደ ውጭ ከተላከ ወርቅ ባለፉት ሶስት ወራት ከ500 ሚሊዮን ዶላር በላይ መገኘቱ ብዙዎችን ወደዚህ ዘርፍ እንዲገቡ እንደሚያበረታታቸው ይጠበቃል።

ሲሚቶን ብንወስድ የለሚ ሲሚንቶ ብቻ በዓመት 450 ሺህ ቶን ሲሚንቶ ያመርታል። አሁን ያለውን የሲሚንቶ ምርት 16 በመቶ እድገት ሀገር ውስጥ ያመጣል። እነዚህ ፋብሪካዎች በተሟላ አቅም እየሠሩ ሲሄዱ የኢንዱስትሪው እና የማእድን ዘርፉ ተደምሮ ከፍተኛ እምርታ ያመጣል ተብሎ ይጠበቃል።

ይህም ሆኖ አሁን ከጥራት ጋር የተያያዙ ጉዳች ዛሬም ያልተሻገርናቸው ችግሮቻችን ናቸው ከሀገር የሚወጡ ምርቶች በጥራት ረገድ ጥያቄ የሚነሳባቸው ናቸው። የጥራት መጓደል እንደ አፍሪካ ባሉ ታዳጊ ሀገሮች የንግድ እድሎችን የመፈተሽ፣ በዓለም ገበያ የመወዳደር እና በዓለም አቀፍ የእሴት ሰንሰለት የመሳተፍ አቅም ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ማሳደሩ የማይቀር ነው። በርካታ ኩባንያዎች በንግድ አጋሮች የሚፈለጉትን የጥራት መስፈርቶችን እና የንግድ ደንቦችን ገቢራዊ በማድረግ ረገድ ችግሮች ይገጥማቸዋል።

የጥራት መጓደል በማኑፋክቸሪንግ እና በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ተወዳዳሪነትን በማሳደግ በዓለም አቀፍ የንግድ ለውውጥ ውስጥ እንቅፋት ይሆናል። ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ ምርቶች ተጠቃሚ ጋር ሲደርሱ በርካታ ችግሮች የሚስተዋልባቸው እና ጥቂት ጥቅም ብቻ ሰጥው የሚወገዱ ይሆናሉ።

ይህ ደግሞ በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ የመጡ ዕቃዎች ተገቢውን አገልግሎት ሳይሰጡ እንዲቀሩ እና ያለውን ጥቂት የውጭ ምንዛሬ አቅም አላግባብ እንዲባክን በር የሚከፍት ነው። በዚህም ላይ በተጠቃሚው ዘንድ ከፍተኛ ምሬትን እና ቅሬታንም ያስከትላል ።

ለጥራት ትኩረት መስጠት ፋይዳው የጎላ ነው። የሸማቾች፣ የአምራቾች እና የተቆጣጣሪዎች ጥቅም ለማስጠበቅ ይረዳል። ሸማቾች ጥራት ያላቸውን ምርቶችን ለመምረጥ ያገለግላቸዋል። እውቅና ባለው ላብራቶሪ ተፈትሸው ያለፉ ምርቶች የተወሰኑ በተጠቃሚው ላይ ርካታን ይፈጥራሉ።

አምራቾች ምርቶቻቸው ለገበያ ከመቅረባቸው በፊት ውስንነቶችን በመቅረፍ ከአላስፈላጊ ወጪ ይጠብቃቸዋል። በዓለም ገበያ ለመሳተፍም ዕድል ይፈጥራል፤ መልካም ተሞክሮዎችን ለመቅስም ይጠቅማል፤ በደንበኞች ላይ እምነት ለመፍጠር ያግዛል።

ይህንኑ ከግንዛቤ በማስገባትም የኢትዮጵያ መንግሥት ለጥራት ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቷል። ለዚህም ሰሞኑን ተመርቆ ወደ አገልግሎት የገባው የጥራት መንደር አንዱ ማሳያ ነው። ሰሞኑን የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ብሔራዊ የጥራት መንደርን  መርቀው በከፈቱበት ወቅት እንደተናገሩት ፣ ብሔራዊ የጥራት መንደር የኢትዮጵያ ማንሠራራት ዘመን ጅማሪ ተደርጎ የሚወሰድ ነው።

ኢትዮጵያ እውን ያደረገችው የጥራት መንደርም በግብርና፣ በጤና፣ በግንባታና በሌሎች ዘርፍ ጥራት ያለው ምርትና አገልግሎት ለማቅረብ ወሳኝ ነው። የጥራት መንደሩ ለሀገር ውስጥና ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ ምርቶችን ጥራት በማረጋገጥ በምርት ጥራት ጉድለት የሚያጋጥሙ ጉዳቶችን ያስወግዳል፣ ለዜጎችም ጥራቱ የተረጋገጠ ምርትና አገልግሎት እንዲያገኙ ያደርጋል።

የጥራት መንደር ግንባታው እያደገ ያለውን ኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በእጅጉ የሚደግፍ ነው። በተለይም ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶች ጥራታቸውን ጠብቀው በዓለም ገበያ ውስጥ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ እና የተሻለ የውጭ ምንዛሬ እንዲያስገኙ በር የሚከፍት ነው።

ለአብነትም የጥራት መንደር ወደ ሥራ ከመግባቱ በፊትም ቢሆን በቡና የተገኘውም ውጤት የኢትዮጵያ መጻኢ ጊዜ ብሩህ መሆኑን የሚያመላክት ነው። ኢትዮጵያ ከብራዚልና ከቬትናም ቀጥሎ ሶስተኛዋ ትልቅ ቡና አምራች ሀገር ለመሆን በቅታለች። ባለፈው ዓመት 1.4 ቢሊዮን ዶላር ከቡና ኤክስፖርት አግኝተናል። በዚህ ዓመት ሁለት ቢሊዮን ዶላር ገደማ ይጠበቃል።

ዘንድሮ ከአራት መቶ ሃምሳ እስከ አምስት መቶ ሺህ ቶን ድረስ ለውጭ ገበያ ለማቅረብ እቅድ ተይዟል። ይህ ዕቅድ ሊሳካ የሚችለው ኢትዮጵያ ጥራቱን የጠበቀ ቡና ወደ ውጭ መላክ ስትችል ነው። ለዚህ ደግሞ በጥራት መንደር የተተከሉ ዘመናዊ መሣሪያዎች አስተዋጽኦ ከፍ ያለ ነው።

በርካታ ኢንዱስትሪዎች በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ወደ ምርት መግባታቸው እና አንዳንዶቹም በአፍሪካ ገበያ የማፈላለግ ሥራ ውስጥ መግባታቸው የኢትዮጵያ ምርቶች በቀጣይ የአፍሪካን ገበያ እንዲገቡ መልካም እድል መፍጠር እንደሚያስችል ይታመናል ። የጥራት መንደር ግንባታውም ኢንዱስትሪዎች ከሀገር ውስጥ አልፈው በውጭው ገበያ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ አቅም የሚፈጠር ሆኗል።

እስማኤል አረቦ

አዲስ ዘመን ዓርብ ኅዳር 20 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You