ሀገራዊ ኃይል የማመንጨት አቅም ከስድስት ሺህ ጊጋ ዋት በላይ ደርሷል

አዲስ አበባ፡- ሀገራዊ ኃይል የማመንጨት አቅም ከስድስት ሺህ ጊጋ ዋት በላይ መድረሱን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

በሚኒስቴሩ የኤሌክትሪፊኬሽንና የኢነርጂ መረጃ መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ዳቢ እንደገለጹት፤ እንደ ሀገር በሁሉም ዘርፍ በቂ የታዳሽ የኃይል አቅርቦት እንዲኖር እየተሠራ ነው፡፡ በዚህም የኢትዮጵያ ከተለያዩ ምንጮት ኃይል የማመንጨት አቅም ከስድስት ሺህ ጊጋ ዋት በላይ ማድረስ ተችሏል፡፡ በሁለትና ሦስት ዓመታት ጊዜ ውስጥም ይህን ቁጥር በእጥፍ ለማሳግ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡

በሁሉም ዘርፍ ነዳጅ ላይ ያለውን ጥገኝት በመቀነስ ታዳሽ ኃይል ላይ መሠረት ያደረገ የኃይል አቅርቦት እንዲኖር ለማድረግ በቂ የማመንጨት አቅም፣ ኃይል የማስተላለፍና መሠረተ ልማት መገንባት ሥራ እየተከናወነ መሆኑን የጠቆሙት አቶ መስፍን፤ ከ20ሺህ ኪሎ ሜትር በላይ የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ግንባታ ተከናውኗል፡ ፡ የማሰራጫ መሠረተ ልማቶችም ከ150 ሺህ ኪሎ ሜትር በላይ ደርሰዋል፡፡

ከዚህ በፊት የትራንስፖርት ዘርፉ ሙሉ በሙሉ የነዳጅ ምርቶች ላይ ጥገኛ ነበር ያሉት መሪ ሥራ አስፈጻሚው፤ ታዳሽ ኃይል ላይ መሠረት ያደረገ የትራንስፖርት አቅርቦት እንዲኖር በቂ የኃይል አቅርቦት ሊኖር ይገባል፡፡ ለዚህም ታዳሽ ኃይልን በሚመለከት ያሉ የተቋማት የፖሊሲ አቅጣጫዎች የሚጣጣሙ እንዲሆኑ ተደርጓል ነው ያሉት፡፡

ኢትዮ- ግሪን ሞቢሊቲ 2024 አውደ ርዕይና ኤግዚቢሽን ከነዳጅ ውጪ የታዳሽ ኃይል ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም የሚያስችል ሰፊ እድል መኖሩን የሚያሳይ መሆኑን ገልጸው፤ በሂደትም ነዳጅ ላይ መሠረት ያደረገውን የትራንስፖርት ዘርፍ ሙሉ በሙሉ ታዳሽ የሆነ የኃይል አቅርቦት ልንተካው እንደምንችል ያየንበት ነው ብለዋል፡፡

ታዳሽ ኃይልን መሠረት ያደረገ የትራንስፖርት አገልግሎት ወደ ሥራ መግባት ከነዳጅ የሚወጣውን የካርቦን ልቅት በማስቀረት የአየርን ንብረት ለውጥን በመከላከል በኩል ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ገልጸው፤ በተጨማሪም ሀገሪቱ ለነዳጅ ግዢ በየዓመቱ የምታወጣውን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ በማስቀረትም ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ እንዳለው ጠቁመዋል፡፡

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በሁሉም ዘርፍ ላይ የታዳሽ ኃይል አጠቃቀም እንዲያድግ እንደሚሠራ ጠቁመው፤ አምራች ኢንዱስትሪው፣ የትራንስፖርት ዘርፉ ብሎም በቤተሰብ ደረጃ ያለው የኃይል ፍጆታ ሙሉ በሙሉ በታዳሽ ኃይል ቴክኖሎጂዎች ላይ የተመሠረተ እንዲሆን እየተሠራ ነው፡፡

ለዚህም የኢነርጂ ልማቱ ታዳሽ ኃይልን መሠረት ያደረገና አካታች እንዲሆን የሚያስችል ፖሊሲ ተቀርጾ እየተተገበረ መሆኑን አመላክተዋል፡፡

የታዳሽ ኃይል ቴክኖሎጂዎች ከታክስ ነጻ ሆነው ወደ ሀገር እንዲገቡ ማድረግን ጨምሮ ዘርፉ ላይ የተለያዩ ማበረታቻዎች እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህም የተፋጠነ የታዳሽ ኃይል ልማት እንዲኖር ያግዛል ብለዋል፡፡

ፋንታነሽ ክንዴ

አዲስ ዘመን ህዳር 21/2017 ዓ.ም

Recommended For You