“ዕፁብ ነው ድንቅ ነው ከአልማዝ የነጠረ፣
በዚህ ዓለም ውበት ንብረት ያልሰከረ፣
ቃሉ ከግብሩ ጋሩ ጋር በውል የታሰረ፣
ትናንትናም ዛሬም ታማኝ ሰው ከበረ ፡፡” (ያልታተመ)
ታማኝ ሰው ቀድሞ የሚታመነው ለራስ ነው። ለራሱ የታመነ ሰው፣ ሌሎች በክህደትና ውሸት እንዲጎዱ ስለማይፈልግ ሲናገርም ሆነ ሲያደርግ የተቀበለውን ቀናና ሰላማዊ የሆነውን ውድ የታማኝነት ባህሪውን ይተገብራል። ለእርሱ አለመታመን ማለት የሞት ያህል የሚቀፍፍ እና እረፍት የሚነሳ ጎዶሎነት ነውና ፡፡
ሴት አያቴ አንድ ጊዜ ቁም ሳጥኑ ውስጥ ካለ ሌላ ሳጥን ውስጥ (ብዙ ጊዜ ግብር የገበረችባቸውን ካርኒዎች የምታስቀምጥበት ነው፤) እናም የታሰረ ነገር አውጥታ ለሰው ትሰጣለች። ከዚያም ያ፣ ሰው የሰጠችውን የታሰረ ነገር ይፈታና ገንዘቡን አውጥቶ መቁጠር ይጀምራል። አያቴ ሆዬ፣ “ዕሳት ለብሳ ዕሳት ጎርሳ”፤ ያንን ብር ቆጣሪ ሰው ቤቴን ለቅቀህ ውጣልኝ ትለዋለች፤ “ለምን እማማ” ይላታል። “ቆጥረህ ያልሰጠኸኝን የአደራ ገንዘብ ሳትቆጥር ነው ፤ መውሰድ ያለብህ እንጂ፤ የምን መተሳሰብ ነው፤ ለመሆኑ ጎደለብኝ ብትል የምከፍልህ ይመስልሃል? ወይስ ያስቀመጥኩበትን ልትከፍለኝ አስበህ ነው? “ ብላ አፋጠጠችው። ቀጠል አድርጋም የታሰረ ገንዘብ አምጥተህ አስቀመጥክ፤ ወርቅ ይሁን ብር ፈትቼም አላየሁት፤ አሁን በፈለግከው ጊዜ ስትጠይቀኝ አውጥቼ መስጠት ነው፤ ያለብኝ እርሱንም አደረግኩት።ከዚህ ሌላ ምን አስበህ ነው፤ እንደ ብድር ገንዘብ ፊቴ የምትቆጥረው….ንገረኝ እስቲ አለችው፡፡
ሰውየውም ሲያስበው ቆየና ያደረገው ነገር ፀፅቶት ይቅርታ ጠይቋት ወጣ። በኋላም ስጠይቃት አምጥቶ ሲያስቀምጥ የሚያውቀውን የብር መጠን ለምድነው ፊቴ የሚቆጥረው። አየህ ልጄ፣ ሚስቱንና ቤተሰቡን ያላመነ ሰው ራሱንም አያምንም፤ ምንም እንደማያመጣ አውቄ ነው፤ ያንን መልስ የሰጠሁት። ሲሰጠኝ አስተሳሰሩን ምልክት አድርገህ እሰረው፤ እንደተቀመጠ ታገኘዋለህ ነበረ፤ ያልኩት። እንደዛውም አድርጌ መልሼ ሰጠሁት። እርሱ ግን ካላመናት ሚስቱና ልጆቹ እኩል ስላየኝ ነው፤ የተቆጣሁት፤ አለችኝ፡፡
የአደራ ገንዘብ አይነካም። አደራ መብላት (አለችኝ) አደራ መብላት የማይናገርንና የማይጋገርን ህፃን ገላ በስለት መቁረጥ ነው። አደራ በልነት፣ በቤትህና በመሬትህ፣ በቤተሰብህና በውዶችህ ላይ ውሎ አድሮ የሚያስከፍል መዘዝ በምድር ሳለህ ያመጣብሃል። በሰማይም የታማኝነት ዋጋው የከበረ ነው፤ በስውር ሰጥቶህ በስውር መልሰሃልና። አደራ ስትበላ እኮ፣ ሰውየውን ባየህ ቁጥር የሚበጨቀው ውስጣዊ ሰላምህ በምድር ዕረፍት ይነሳሃል፤ አለችኝ። አብረህም ባትኖር የሰውየውን ንብረት፣ ቃልና ገንዘብ ባሰብክ ቁጥር ስቃይ የምታተርፈው አንተው ነህ፤ ስትል መለሰችልኝ፡፡
ህይወት ራሷ ለታማኝነት ብቁ ትምህርት ቤት ናት። ታማኝ ሰው እረፍት አለው፤ ታማኝ ሰው ሰላም አለው፤ ታማኝ ሰው ከማይታምን ሰው በፀዳሉ ነው፤ የሚለየው። የማይታመንማ ሰው ምን አለውና በምኑ ይከበራል፤ አመዳም ነው። በካዳቸው ሰዎች ፊት ሲቆም ምድር የምትውጠው ነው የሚመስለው፤ ይብረከረካል፤ ስለዚህ ፍርሃቱን ለመሸፈን ይቆጣል፤ በዘለፋ ታጅቦ ለድብድብ እስከመጋበዝ ሊሄድ ይችላል፡፡
በአንድ ወቅት በሀገራችን የነበረ መስፍን፣ የግምጃ ቤት ሃላፊ የሚሆን ሰው ለመምረጥ አስቦ በሥራ ችሎታቸው፣ በቅልጥፍናቸውና በተግባቢነታቸው ከሚያውቃቸው ቅርቦቹ መካከል አራት ሰው መለመለና፤ ለአራቱም በአገልግል የታሰረ ዕቃ ወደ ተለያዩ አራት አውራጃዎች ለአሉ አራት ሰዎች፤ አስይዞ በፈረስ ተጉዛችሁ በሚቀጥለው ቀን መልዕክቱን አድርሳችሁ ተመለሱ፤ ሲል ላካቸው፡፡
ከአራቱ ሁለቱ ሳይመለሱ ቀሩ።አንዱ፣ ተመልሶ መጣና።መስፍን ሆይ፣ መንገድ ላይ ፈረሴ ተንሸራትቶብኝ ገደል ወድቆ ነበረና መልዕክቱን የማድረስ ዕድል ሳላገኝ ቀረሁ፤ ሲል መለሰለት፡፡
ሁለቱ ግን ወደእርሱ ሳይመለሱ ወደ ቤታቸው ገብተው መሸሸጋቸውን ሰማ። ንጉሡም ምህረት አድርጌላችኋለሁና ተመልሳችሁ ኑ፤ አላቸውና መጡ።ሲመጡም፣ መልዕክቱን የላክኋችሁ ምን ያህል ጥብቅ መሆናችሁን ለማወቅ ስል ያዘጋጀሁት ዘዴ ነው፤ በሠራችሁት ሥራ ካፈራችሁና ከተፀፀታችሁ ወደመደበኛው ሥራችሁ በታማኝነት ለመሥራት ተመለሱ፤ አላቸው፡፡
ሦስተኛው ሰው ግን በሐፍረት ጫማው ላይ ወድቆ መሳሳቱን በተማጽኖ ገለፀለት። ይህንንም በለቅሶ መጥቶ የተማፀነውንና አንዳችም ውሸት ሳይቀላቅል ጥፋቱን የተናዘዘውን ሰው ግን ሾሞና ሸልሞ ለሃላፊነት አጨው። ስህተትም ሠርቶም ሸሽቶም መኖር አያዋጣምና።
አራተኛውን ግን አጥፍተህም ሰበብ ሰጥተህም ስለማይሆን ሕግ ጥሰሐልና ትቀጣለህ፤ ምክንያቱም አራት ጥፋት ሰርተሐል። ካንተ ኋላ ኋላ ይከተልህ የነበረ ሰው ነበርና ያደረግኸውን ሁሉ አይቷል። አገልግሉን ከቤተ መንግሥቱ ብዙም ሳትርቅ መክፈትህንና በውስጡ የነበረችው እርግብ መብረሯን አንተም አይተሃል፤ እርሱም፣ ተመልክቷል።
አንደኛ፣ በድንጋጤም ከስፍራው ሳትነሳ ለረዥም ጊዜ ቆይተሃል።ከዚያም መላ ስታወጠነጥን ቆየህና ፈረስህን ስበህና አስደንብረህ ወደገደል ጨመርከው። ሁለተኛ፣ አንድም አካላዊ ጉዳት ሳይደርስብህ ለማቃሰት መሞከርህ ሳያንስ ወጌሻ እንዲታዘዝልህ ጠየቅክ። ሦስተኛ፣ ይህንን ሁሉ አቀናብረህ ስታበቃ ይህንኑ ጥፋትህን ለመሸፈን ዓይን ዓይኔን እያየህ ዋሸኸኝ።አራተኛ መጥተህ ታማኝ ሳትሆን ለመምሰል ሞክረሃል።ስለዚህ ካንተ ጋር እህል ውሃዬ አልቋልና ወደወህኒ ተወርውረሃል፤ ወስዳችሁ እሰሩት አላቸው። እስከዛሬ የሰጠሁት ግልጋሎቴሳ ላልከኝም እውነተኛ እንዳልነበረ የዛሬ ሥራህ አጋልጦብሃል፤ አለውና ሸኘው።
ከአንድ ሳምንት በፊት የአንድ ክፍለ-አገር አቋራጭ አውቶቡስ ሾፌር ከ50 ሰው በላይ አሳፍሮ የሚጓዝ ( በኮሮና ምክንያት ወደ 20 ገደማ ሰው ዝቅ ብሏል፤ መሰለኝ) ይህንን ሁሉ ሰው ይዞ የሚጓዝ ሰው፣ ሃላፊነት ይሰማዋል ብዬ በማሰብ፣ ወዲህም ቢያንስ እነዚህን ሁሉ ሰዎች በታማኝት የተረከበ ሰው፣ ትንሽ መልዕክት ለሚደርስለት ሰው ሳያደርስ አይቀርም በሚል እምነት፣ ከተቀባይ የስልክ አድራሻ ጋር የመላኪያ ገንዘብ ጨምረን ከፍለነው ልከነው ነበረ። ይሁንናም መድረሻው ቦታ፣ ሲደርስ እና ስልክ ሲደወልለትም፣ መልዕክቱን የሆነ ሰው መጥቶ እንደተረከበው ፈርጠም ብሎ በቁጣ መልስ ሰጠ። ደጋግመን ብንለማመጠውም “ዓይኔን ግንባር ያድርገው” ሲል ማለ፤ ይሁንናም ላኪም ተቀባይም እንዲሁ ደከምን እንጂ፤ እርሱ በክህደትና አለመታመን ቀጥሎ መልዕክቱን ውጦ አስቀረ። የሚገርመው በውስጡ የነበረው መልዕክት ለእርሱ ቢጤ ትንሽ ሰው ምንም አያደርግለትም፤ የሞራልና የሥነ-ምግባር መልዕክት ነበረና።“ካፈርኩ አይመልሰኝ“ እንደሚባልም በውሸቱ ፀናና ቀረ፡፡
እንዲህ ዓይነቱ ሾፌር፣ ተሳፋሪዎች ሾፌርና መኪና አግኝተናል በማለት፣ ወደጉዳያችን እንደርሳለን ብለው፣ ከሚሳፈሩ ሰዎች መካከል አንድ ወይም ሁለት ሰው ድንገት ለሽንት ወርደው ቢቀሩና ቢጠየቅ፤ ቀድሞውንም አላሳፈርኳቸውም ከማለት የማይመለስ አደራ በላ ነው።ላኪውም ተቀባዩም ከዚህ ሰው ባህሪ የተረዳነው ነገር ተመሳሳይ ነው፤ ከመልዕክቱ ይልቅ መልዕክቱ የተላከበት “ ትንሽ የሚያምር ዕቃ” ሳያጓጓው አልቀረም።
ታማኝት ርካሽ ቦታ የሚገኝ ሸቀጥ አይደለም፤ ውድም ስለሆነ የሚገኘው ውድ በሆነ ስፍራ እና ውድ በሆኑ ሰዎች ልብ ነው። አንድ ነገር አምናለሁ፤ የከበሩ ነገሮች ሁሉ መገኛ በሥርዓት በታነፀ ባህሪያዊ ማንነት ውስጥ ነው፤ ስለዚህ በየምናምንቴው ቦታና ተራ ሰዎች ልብ ውስጥ ፍቅርን፣ ታማኝነትን፣ የዋህነትንና ሰላምን በመፈለግ፤ አትባዝኑ፤ አትድከሙ። ታማኝነት በአስቸጋሪና አጓጊ ሁኔታ ውስጥ በአምሮት የማይገዛ፣ በጉጉት የማይጎተት ፅኑነት ነው። ስሜትና ስግብግብነትማ የትም ቦታ በሽ-በሽ ነው።እዚህም እዚያም እንደጦስ ዶሮ ይንደፋደፋል ፡፡
በአስተሳሰባቸው የደከሙና ስሜት የሚገዛቸው ሰዎችማ ራሳቸው በባህሪያቸው ስሜተ-ልሎች ስለሆኑ ሌላውን ሰው ሁሉ የሚያዩት እንዲሁ ባልታረመ ሰብእናቸው ነው፡፡
ስለዚህ ያለማመንታት የሰው ነገር ሲያዩ የራሳቸው ማድረግን ይመኛሉ። በዕቃ የሚገደቡ እንዳይመስላችሁ በአንደበታቸው አረም የበዛባቸው፣ በአስተሳሰባቸው ድውይ ስለሆኑ፣ የሰው ሚስት ሲያዩ ያምራቸዋል፤ የደረሰች የጓደኛቸውን ልጅ ይ መ ኛ ሉ ። እ ን ዲ ያ ው ም የልጃቸውን ጓደኛ ወድደው አበሳቸውን የሚያዩ ክብራቸውን የጣሉ ስንት ሰዎች አሉ። ይህ የሞጭላፊነት ባህሪ በየትኛውም የኑሮ መስክ ላይ ቢቀመጡ አይለቃቸውም ፡፡
ጊዜው ቆየት ብሏል፤ በአንድ የመንግሥት መሥሪያ ቤት ውስጥ ይሠራ የነበረ ወዳጄን አግኝቼ “ለምን ሥራህን ለቀቅህ” ስለው፤ “ የማይነካ ነገር ነክቼ ነው” አለኝ። ፍቃደኛ ከሆንክ ልትነግረኝ ትችላለህ ብዬ ጠየቅሁት፡፡
በሚገባ አለኝና፤ ላገባት ያጨኋት ልጅ ነበረችና ተስማምተን እያለ አለቃዬ፣ ይጨቀ ጭቃት ጀምሯል። በኋላ ቢሮ ገብቼ አሳሰብኩት። “የአራዳ ልጅ አይደለህ እንዴ ምን ታካብዳለህ?” አለኝ። እውነቱ ይህ ነው፤ ዓይንህንም እጅህንም ከእርሷ ላይ አንሳ፤ ካለበለዚያ ለሚስትህ ሄጄ ነግራታለሁ፤ አልኩት። ከት-ክት ብሎ ስቆ ( ጥርሱ ለሙቅ አይትረፍና) ሂድና ንገራት፤ አታምንህም፤ ቀን ቀን የተነገራትን ወሬ ሁሉ ማታ ማታ በጥሩ ላጲስ አጠፋዋለሁ፤ ለማንኛውም አትድከም አለኝ። እልህ ውስጥ ተጋባን፡፡
በሳምንቱ ማለቂያ ላይ፣ አስቸኳይ የሠራተኞች ግምገማ ተብሎ ተጠራንና ገባን። ሠራተኛው ገብቶ እንደተቀመጠም፣ አንድ ሁለት ሦስት ሠራተኞች በተሸኮርማሚ ጥያቄዎች ተገመገሙና ቀጥሎ የእኔ ስም ተጠራ። ከዚያ በኋላ ምን ልንገርህ፤ ከዚህም ከዚያም ተልዕኮ የተሰጣቸው እጆች መወንጨፍ ጀመሩ።
ወደሥራ በሰዓቱ ገብቶ ምን እንደሚሠራ አይታወቅም፤ መስክ መሄድ አይወድም፤ ሕብረት ያስጠላዋል፤ ከሠራተኛ ጋር አይስማማም፤ ካለእኔ አዋቂ የለም ይላል፤ ትምክህተኛ ነው፤ ለሴቶች ንቀት አለው፤ አለቃ አያከብርም፤ በግድ ካላገባሽኝ ብሎ አንዲት የሥራ ባልደረባውን አስቸግሯል፤ ወደመስክ ሠራተኛ ሲወጣ በተለይ ሴቶችን ብቻ ለመጥቀም ሲል እነርሱን ብቻ ያሰማራል። የሚረባም የማይረባም ግላዊም ማህበራዊም የሆኑ ዝባዝንኬ ወቀሳዎች ተደረደሩና መልስ ስጥ ተባልኩ። በቅድሚያ እንኳን ከብርሃኑ ወደጨለማው መድረክ በፍጥነት ለመድረስ በቃሁኝ ።በብርቱ ሠራተኛነት የተመሰገንኩት እኮ የዛሬ ወር ነበረ፤ ከመቼው ረሳችሁትና ተረባረባችሁብኝ። እርሱም ይሁን። ከአንድ እስከ አስራስድስት ከዘረዘራችሁት ውስጥ አንዱም አይመለከተኝም። ወቀሳውና ሂሱ ታማኝ ካልሆነ ምስጋናና እውቅናችሁም የውሸት ነበረና፤ መልሰዋለሁ፤ ብዬ ቀጠልኩ፡፡
ምክንያቱም የምሠራው ሥራ የታወቀ ነው፤ አልፌ ተርፌ የሌሎች ባልደረቦቼን ሥራ ሸፍኜ የምሠራ ሰው ነኝ። መስክ የማልሄደው የመስክ ሥራ የሚያስፈልገው የሥራ መደብ ላይ አይደለሁም፤ ከመስክ የተመለሱ ሰዎችን ሥራ ገምጋሚ ስለሆንኩ ነው፤ በሠርግም ሆነ በህመም በደስታ በዓልም ሆነ በሃዘን ጠፍቼ ስለማላውቅ፤ የማህበራዊነት ችግር የለብኝም። ሴቶችን ይንቃል ለተባለው ጠንካራ ሴት እናት ስላሳደገችኝ የሴቶችን ብቃት አውቃለሁ፤ አስቸገርካት የተባለችው የሥራ ባልደረባዬ ማን መሆኗን አላውቅም፤ እርሷ ከሆነች ግን (ብዬ ወደእጮኛዬ ጠቁሜ) ወድጃታለሁ ገናም አስቸግራታለሁ (በሳቅ አውካካ ጉባኤው) ይልቅ በሚስቱ ላይ የሚማግጠውን አለቃችንን አትገመግሙም፤ እንዴ? ስል ተሰብሳቢው ሁሉ ፀጥ አለ።አለቃ ከነጥፋቱ ይወደሳል እንጂ አይነካም እኮ። ጆርጅ ኦርዌል ነበረ መሰለኝ።“ሁሉም ሰዎች እኩል ናቸው አንዳንድ ሰዎች ደግሞ የበለጠ እኩል ናቸው” ያለው። ለሌሎቹም ጥያቄዎች መልስ ከመስጠቴ በፊት የሻይ እረፍት ብሎ ግምገማውን አለቃችን በድንፋታ በተነው።
የገረመኝ ግን፣ ስንወጣ የወነጀሉኝ ሁሉ “ወንድ ነህ፣ ጀግና፣ እንዳንተ ያለ ቆራጥ …ወዘተ” እያሉ ሲያሞጋግሱኝ ልቤ ክፉኛ በትዝብት ሃዘን ደማ። አብረው ሊንዱኝ ተዘጋጅተው የነበሩ ብልጣ ብልጥ አድርባዮች ሁሉ፤ የተሰጣቸውን ገፀ ባህሪ ከተጫወቱ በኋላ ሰውየው በሌለበት ሥፍራ ከመቼው ተገልብጠው አድናቂዎቼ እንደሆኑ ሳስብ ግራ ተጋባሁኝ። እርሱ ፊት እርሱን ደጋፊ፤ በእኔ ፊት ደግሞ እርሱን ነቃፊና እኔን አስተዛዛኝ፣ “ለመሆን” ደቂቃዎች ያልፈጀባቸው ሰዎች መከረባበት አስገራሚ ነው፤ ሲል አጫወተኝና በማግስቱ ነው፤ መሥሪያ ቤቱን ለቅቄ የወጣሁት፤ በአስመሳዮች ጉባኤ ውስጥ ዳግም ላለመገኘት ለራሴ ቃል ገባሁ።ቢያንስ ቢያንስ ለራሴ ታማኝ መሆን ይገባኝ የለ? ሲል ነገረኝ። ይሄኔ ነው፤ ታዲያ፡-
“የማታውቁበትን አጠባ ወርዳችሁ፤ አገርን ደነቀው አጠማዘዛችሁ፡፡” (መርስዔ ሐዘን ወልደ ቂርቆስ) ብለው የገጠሙት። ምድረ ጠምዛዥና ተጠምዛዥ ሁሉ፤ አሁን ካንተ ጋር ሆኖ አጀብ አጀብ ያደርግህና ፀሐይ ወደማደሪያዋ ልትገባ ስታሽቆለቁል ደግሞ ከጠሉህ ሰዎች ጋር ሆኖ የድራፍት ብርጭቆውን ደገፍ ብሎ፣ “ድፍረቱ ያላዋቂነቱ ምንጭ ነው፤ ተስማምቶ መኖር ጠልቶ ደርሶ በጀብደኛነት አለቃውን ይዘረጥጣል?! ድሮውንም ሴት ማሽኮርመም የአለቃ ወጉ ነው፤” ይልሃል።ታማኝነት አዲዮስ!!
የት አገር እንደሆነ አላውቅም፤ ላቲን አሜሪካ ውስጥ ይመስለኛል፤ “ማድ ዴይ” የሚሉት ቀን አላቸው። በዚያን ቀን ማንኛውም ሰው የፊት ጭንብል ይለብሳል፤ ማን መሆኑን ከቤት ጀምሮ አያውቅም።ባሎች ይጠጣሉ፤ ሚስቶችም እንዲሁ ያደርጋሉ፤ ይሳከራሉ። ወንዶቹ የታማኝነትን ድንበር ለመዝለል ወስነው፣ የሴሰኛነት አምሮታቸውን ለመወጣት አምስትና ስድስት ሆነው ሰብሰብ ይሉና፤ በዚህ የእብደት ቀን የሚስቶቻቸውን ስም በቁራጭ ወረቀት ላይ በመጻፍ በአንዱ ሰው ባርኔጣ ውስጥ ከትተው በማዘበራረቅ የወጣችለትን ሴት ይዞ እንዲወጣ ያለማቅማማት ዕጣ ይጣጣላሉ። ከዚያም የሆነው ሲሆን ዕድሌ ነው፤ ዕድልህ ነው፤ ይባባላሉ፤ ክህደቱም በወንዶቹ ፈቃድ፣ በሰከሩት ሴቶች ላይ ይፈፀማል። ይህ ግን ከኤች አይ ቪ/ኤድስ መስፋፋት ጋር ወዲያው እንዲቆም ተደርጓል እንጂ፤ የነባር ወጋቸው አካል ነበረ። አለመታመን የ”ታማኝነት” ካርድ ወጥቶለት የሚፈፀም ክፉ ወግ ነበረ። ይህ ሰብዓዊ ኪሳራ የሚያስከትለው ክፉ ዕጣ በቤት ብቻ አያቆምም፤ ለማህበራዊ ምስቅልቅል የሚዳርግ ክፉ ዕዳም ነው!!
አንዳንድ ፈላስፎች ታማኝነትን ከእውነተኛነት ጋር በማነፃፀር አንዱን ከሌላው ማሳነስ ይፈልጋሉ። እንደ ባህሪ ንጥር መቀበል ያስቸግራል፤ ታማኝት ያንድ ወገን ዕዳ እንጂ እውነትን የሚያክል ነገር የለም ይሉናል። ይህንንም በምሳሌ ሲያጠናክሩት “እናትነት እውነት ሲሆን (አምጣ ወልዳለችና )፤ አባትነት ግን እምነት (ታማኝነት ነው) ይሉናል፤ ይሁንናም ታማኝነት የሌለበት እውነት ከቶውንም እውነት አይደለም። በዚህ ዘመናዊ ዓለም ደግሞ በዲኤንኤ ምርመራ ማረጋገጥም ይቻላል። ይሁንናም የገዛ አካሌን አሳልፌ የሰጠኋትን ፍቅሬን እምነት በሌለበት እውነት ብቻ እንዴት እለካታለሁ። እውነቷም እምነት ነው፤ እምነቴም እውነት ነው፡፡
በነገራችን ላይ የማይታመኑ ሰዎች በከበሩ ድንጋዮችና ለቁጥር በሚያታክቱ ብሮች ላይ ብቻ ሳይሆን፣ የማይታመኑት በየትናንሹም ነገር ነው። “ሌባ ለዓመሉ ዳቦ ይልሳል” ይባል የለ፤ መቼም እነርሱ ይስረቁ፤ እኛም ጨማምረን ጥቃቅኑን ነገር ሁሉ እንሰጣቸዋለን፤ ታማኝነት ግን ወርቅ ነው፤ የታማኝነት ወርቅ ደግሞ ተቀርፆ ላይጠፋ የሚሳለው በልብና በአዕምሮ ገጽ ላይ ነው፤ አበቃሁ!!
አዲስ ዘመን ሐምሌ 18/2012
አገልጋይ ዮናታን አክሊሉ