አዲስ አበባ፡- ለስደተኞች የተለያዩ መብቶችን ያጎናጽፋል የተባለው ረቂቅ አዋጅ በጸደቀ በጥቂት ቀናት ውስጥ ከዓለም አቀፍ ተቋማት ለኢትዮጵያ ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ ድጋፍና ብድር ቃል መገባቱን የስደተኞችና ከስደት ተመላሾች ጉዳይ ኤጀንሲ አስታወቀ።
የስደተኞችና ከስደት ተመላሾች ጉዳይ ኤጀንሲ የህግ አገልግሎት እና የስደተኞች እውቅና መስጠት ኃላፊ አቶ ኃይለስላሴ ገብረማርያም በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፤ ዝርዝር ጉዳዮችን ይዞ የወጣውን እና ሰፊ መብቶችን ለስደተኞች የሚሰጠው ረቂቅ አዋጅ ባለፈው ሳምንት ጸድቋል። የረቂቅ አዋጁን መጽደቅ ተከትሎ ዓለም አቀፍ ተቋማት አንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ ለኢትዮጵያ የ1 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ እና የረጅም ጊዜ ብድር ለመስጠት ቃል ገብተዋል።
እንደ አቶ ኃይለስላሴ ገለጻ፤ በተለይ ከስደተኞች ጋር ተያይዞ ዓለም አቀፍ ተቋማት በበጎ ጎን ፊታቸውን ወደ ኢትዮጵያ አዙረዋል። በዚህም መሰረት የዓለም ባንክ በኢኮኖሚ እድል ፕሮጀክት /EOP/ እና በተፈናቃዮች ችግር ምላሽ ልማት ፕሮግራም /DRDIP/ በኩል እስከ 450 ሚሊዮን ዶላር ለመስጠት ቃል ገብተዋል። የዓለም ባንክ በበኩሉ 550 ሚሊዮን ዩሮ በረጅም ጊዜ ብድር ይሰጣል። የተለያዩ ከስደተኞች ድጋፍ ጋር የሚሰሩ ዓለም ዓቀፍ ተቋማትም የየራሳቸውን የገንዘብ ድጋፍ ለማድረግ ተስማምተዋል።
ኢትዮጵያ ከ950 ሺ በላይ ስደተኞችን አስጠልላ በካምፕ ስታኖር ቆይታለች። በ1996 ዓ.ም ያጸደቀችው የስደተኞች አዋጅ ደግሞ ስደተኞቹን በካምፕ ከማኖር ያለፈ መብት አይሰጥም ነበር። የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጥር 9 ቀን 2011 ዓ. ም. ባደረገው አስራ ዘጠነኛ መደበኛ ስብሰባ ደግሞ ዝርዝር መብቶችን የያዘውን የስደተኞች ጉዳይ ረቂቅ አዋጅን በአብላጫ ድምፅ ማጽደቁ የሚታወስ ነው።
የረቂቅ አዋጁን መጽደቅ ተከትሎ በርካታ ዓለም አቀፍ ተቋማት ድጋፋቸውን ለኢትዮጵያ በመስጠት ላይ ናቸው። መቀመጫውን በስዊዘርላንድ ጄኔቫ ያደረገው የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን የኢትዮጵያን የስደተኞችን አዋጅ አስመልክቶ ድጋፉን ለመግለጽ መግለጫ አውጥቷል።
አዲስ ዘመን ጥር 18/2011
በጌትነት ተስፋማርያም