መብራት የናፈቀው ሻማ ይዞ ያለቅሳል፤ መብራት ያለው በመብራት ያሸበርቃል። ይህን ያላደለው በኩራዝ ይጨናበሳል። የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ለእኛ ለኢትዮጵያውያን ከመብራትም በላይ ነው። የግብፅ ህዝብ ሙሉ ለሙሉ በመብራት እያሸበረቀ የኢትዮጵያ ህዝብ በኩራዝ እየኖረ በአባይ ወንዝ ላይ የሚካሄደውን ታላቁን የህዳሴ ግድብ ግንባታ ፕሮጀክት መከልከል ኢ-ፍታዊ ከመሆኑም በላይ የህግም ሆነ የሞራል ጥያቄ ያስነሳል ።
አቋማችን ሌሎች ይጠሙ ሳይሆን አብረን እንጠጣ፣ አብረን ከምንራቆት አብረን እንለምልም እያልን ባለንበት በዚህ በ21ኛው ከፍለ ዘመን በጣም ግርም የሚለው የግብፁ ድረ ገፅ አህራም ኦንላይን “ኢትዮጵያ የአፍሪካ አህጉር ራስ ምታት” ሲል አንድ ዘገባ አስነብቧል። አህራም ኦንላይን ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ በ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ለቀጣናው ስጋት ሆኖ ብቅ ያለ ክስተት እንደሆነም ያትታል። ታላቁ የሕዳሴ ግድብ በተፋሰሱ ሀገራት መካከል ሊፈጥር ከሚገባው ትብብር እና ስምምነት ይልቅ የወቅቱ ትልቅ የግጭት ምንጭ ሆኗል ይላል ዘገባው።
ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ ለአፍሪካውያን ነፃነት (ግብፅንም ጭምሮ) የቆመች ሀገር መሆኗን የዘነጋው ይህ ሚዲያ ኢትዮጵያ ለአፍሪካውያን ነጻነትና አንድነት በዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ዘንድ ባትቆም ኢትዮጵያ የአፍሪካ አህጉር ራስ ምታት ሆናለች በሚል አርዕስት ለመዘገብና ተበደልኩ በማለት ለተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት አቤቱታዋን ባላቀረበች ነበር።
የተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት የግብፅን አቤቱታ ከተመለከተና ከተወያዩበት በኋላ ታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ለቀጠናው የግጭት መንስኤ ሳይሆን አብሮ ለመልማት የሚያስችል የልማት አውታር ነው ሲል ተደምጧል። ታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ለአካባቢው የደህንነት ስጋት ሳይሆን የልማት ጉዳይ እንደሆነ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ያስታወቀው። ጉዳዩንም ወደ አፍሪካ ህብረት በመመለስ ሶስቱ ሀገራት በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት ችግራቸውን እንዲፈቱ ሲልም ነውያሳሰበው የፀጥታው ምክር ቤት።
በአባይ ወንዝ ላይ የኢትዮጵያ ፍላጎትና አቋም መልማት እንጂ ሌሎች እንዲጠሙ አለመሆኑን አንዱ ማረጋገጫችን ነው። አብረን እንጠጣ፣ በጋራ እንጠቀምበት፣ አብረን እንለምልም ነው። በታላቁ ህዳሴ ግድብ ኢትዮጵያ ትብራ ነው፤ ከኩራዝ እና ከሻማ ትገላገል፤ ከድህነት ቀንበር ትፈታ መሆኑን ልንረዳው የሚገባንና በአንድነት ልንቆም የሚያስፈልግበት ጊዜ ላይ መድረሳችንን የግብፅ ሚዲያ ዘገባዎች መመልከት በቂ ነው።
ከኢትዮጵያ ተራራማ ቦታዎች ፈልቆ ማረፊያውን ቀይ ባህርን ያደረገው የአባይ ወንዝ ለዘመናት ሲፈስ፤ ድንበር ሲሻገርና ያለፈበትን ሁሉ ሲያጠጣና ሲያለማ ቆይቷል። አባይ እየተጥመለመለ በረሃውን አቋርጦ በደጀን አልፎ፤ እናት ኢትዮጵያን ሳያጠግብ ሱዳን ይገባል። በተቃራኒው ግብጾችን ለዘመናት አረስርሷል። ከምንጩ ዳር ቁጭ ብሎ ሲቀኝለት፣ የአባይን ልጅ ውኃ ጠማው ሲዘፍንለት ለአመታት ኖረ፤ እንዲሁ እንደ ተመኘው እኛን የምንጩን ባለቤቶችን በከንቱ አፈራችንን ይዞ ሲጓዝ ለዘመናት ቆመን ተመልክተነዋል።
ዛሬ ግን ኢትዮጵያን የምንጩን ባለቤት ሊያረሰርስ፣ አቁረን ኩሬ ሰርተን ጭለማችን ሊበራልን ከወጉ ደርሰናል። ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ውሃ የመያዝ ጅማሬውን አንድ ሊል የቀናት ያህል ብቻ ቀርቶታል። በእርግጥ ዛሬ እዚህ ደረጃ ላይ ይደረስ እንጂ የግድብ ግንባታ የመሰረት ድንጋይ ከተቀመጠበት ከመጋቢት 24 ቀን 2003 ዓ.ም ጀምሮ ለዘጠኝ ዓመታት የተደረገው ጉዞ አልጋ በአልጋ አልነበረም ።
የታችኛው ተፋሰስ የዓባይ ልጆች በጥም እርካታ እና በልምላሜ ሲኖሩ፣ የአባይ እናት የሆነችው ኢትዮጵያ ግን ስትጠማና ስትራብ ኖራለች። ከህዳሴ ግድብ የሚመነጨውን የሃይድሮ ኤሌክትሪክ ሃይል የመጠቀም ሙሉ መብት እንዳላት ሁሉም አካል ሊያውቀውና ሊቀበለው የሚገባ እውነት ነው ሲባል ከእውነትም የበለጠ እውነት ነው።
የቱንም ያህል ጫናው ቢበረታ እነሆ ዛሬ ህልማችን እውን የሆነበት ጫፍ ላይ መደረሱን የሚያበስሩ በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ ነው። በወርሃ ሐምሌ ውኃ መሙላት ይጀምራል። ግንባታው በፍጥነት እየተከናወነ ነው። በትንሹ አሁን ላይ እንኳን 74 በመቶ ማድረሳችን ለግብፅ እራስምታት እየሆነባት ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ባሳለፍነው ሳምንት በተከበረው ምክር ቤት ቀርበው ባደረጉት ገለጻ፤ አይናችንን ከግድቡ ላይ አናነሳም ሲሉ፤ የሰማው ምክር ቤት ላለፉት ዘጠኝ ዓመታት ምን እንደተሰራ እንኳን በቅጡ ሳይነግረን በሁለት ዓመታት የለውጥ ጉዞ ግን የህዳሴ ግድብ ዳግም መወለዱን ለመረዳት ችለናል። በአዲስ የግንባታ የአሰራር ስርዓት ተዘርግቶለት ውኃ ለመያዝ በቅቷል። በወርሃ ሐምሌ ግድባችን ውኃ መያዝ ይጀምራል።
ይልቁንም ኢትዮጵያ “ያለሦስቱ ሀገራት ስምምነት ማለትም ከሱዳንና ግብፅ ጋር በሚደረገው ውይይት በስተቀር በተናጠል ውኃ መሙላት እንዳትጀምር!” በማለት ለተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት ከአንዴም ሁለት ጊዜ አቤት ማለቷን በመዘንጋት ጭምር።
ኢትዮጵያውያን እና የኢትዮጵያ ወዳጆችም ከጊዜ ወደ ጊዜ ግብፅ እያራመደችው ያለችው መጠነ ሰፊ የተዛባ መረጃ በተለይም በአረብኛ ቋንቋዎች የምታሰራጫቸውን መሠረተ ቢስ መረጃዎች ላይ እውነታውን ለዓለም በማጋለጥ በኩል ከተደራዳሪነት ያላነሰው ሚናቸው የሚወጡ በርካታ ኢትዮጵያውያን ያስፈልጉናል። በዚህ በህዳሴ ግድብ ዙሪያ በሚሰራጩ ዘገባዎች ላይ የኢትዮጵያን አቋም በመያዝ እውነታውን ለአረቡ ዓለም ለማስተዋወቅ በስፋት የሚሰራው መሀመድ አልዓሩሲን ማንሳት ይቻላል።
በዓባይ ውሃ አጠቃቀም የኢትዮጵያን ፍትሃዊ አቋም ቀድሞ ማንፀባረቅ የእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ የቤት ሥራ ነው። ከመንግሥት እስከ ምሁራን፣ ከታዋቂ ሰዎች እስከ ተንታኞች ጥሪ እያቀረቡ ይገኛሉ። ኢትዮጵያን በሀብቷ የመጠቀም መብትና እውነት በማስረዳት፣ የግብጽን የውሸት ትርክትና ክስ በማጋለጥ በኩል ሁላችንም ድርሻችንን ልንወጣ ይገባናል።
አዲስ ዘመን ሐምሌ 18/2012
ወንድምአገኝ አሸብር